ጥበብ እና ባህል

ጾምና የጾም ፍች ማህበረ ባህላዊ ፋይዳ በእስልምና ረመዳን፣

ጾምና ፍች (ኢደል ፍጡር) ረመዳን

‹‹ረመዳን›› የአረብኛ ቃል ሲሆን በሂጅራ አቆጣጠር የዘጠነኛው ወር ስም መጠሪያ ነው። የእስልምና የዘመን አቆጣጠር በጨረቃ ዑደት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ በእኛ የዘመን አቆጣጠር አንጻር በየአመቱ አስር ወይም አስራ አንድ ቀን ይንሳል። በዚህ ቀመር የተነሳ የሂጅራ አቆጣጠር ወሮች ሁሉንም ወቅቶች በዙር ይደርሳሉ። የረመዳን ወር ቅዱስ ቁርኣን ለሰው ልጆች ሁሉ ይደርስ ዘንድ የነብዩ ሙሀመድ መወረድ የተጀመረበት፣ ምንዳዋ ከሺሕ ወር በላይ የሆነች የመወሰኛይቱ ሌሊት የምትገኝበት፣ ታላቁ የበድር ጦርነት ድል የተገኘበት ወር ነው።

 ጾም፡

 ‹‹ጾም›› የሚለው ቃል በእስልምና ‹‹ማቆም›› ወይም ‹‹መከልከል›› የሚል ፍች አለው። በሸሪኣዊ አገባቡ ደግሞ ለአላህ ትእዛዝ ለመገዛት በሚል ውስጣዊ ውሳኔ ከፈጅር እስከ ጸሐይ ግባት ከምግብ፣ ከመጠጥና ከትዳር ጓደኛ ጋር የሩካቤ ስጋ አለመፈጸም፣ እኩይ ቃል ከመናገርና እኩይ ድርጊት ከመፈጸም መታቀብ፣ ወዘተ የሚል ጥቅል ትርጉም ይዟል።

 በእስልምና ጾም በመደበኛ ጾምና በሱና ጾም ይከፈላል። የሱና ጾም በልዩ ልዩ ምክንያቶችና ሁኔታዎች አብዛኛውን ጊዜ በግል የሚፈጸም ግዴታ የሌለበት የጾም አይነት ሲሆን፤ የሱና ጾም በማንኛውም ጊዜ ሊጾም ይቻላል። መደበኛው ጾም ደግሞ በዚጌ ገደብ ውስጥ በቡድን የሚጾም ግዴታ የሆነ የጾም አይነት ነው። ይህ የግዴታ ወይም መደበኛ ጾም በሂጅራ አቆጣጠር ዘጠነኛ በሆነው የረመዳን ወር ይጾማል።

የሂጅራ የጊዜ አቆጣጠር በጨረቃ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የረመዳን ወር ሀያ ዘጠኝ ወይም ሰላሳ ቀን ስለሚሆን የጾሙም ጊዜ ሀያ ዘጠኝ ወይም ሰላሳ ቀን ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ የጨረቃ የጊዜ አቆጣጠር ቀመር በየአመቱ አስር ወይም አስራ አንድ ቀን ስለሚቀንስ ጾሙ ሁሉንም ወሮችና ወቅቶች ይሸፍናል። በዚህ ቀመር አንድ ሰው የአመቱን ወሮችና ወቅቶች በጾም ለማሳለፍና ከጀመረበት ለመድረስ 36/37 አመታት ሊፈጅበት ይችላል።

የረመዳን ወር ጾም ከእስልምና አምስቱ ማዕዘናት አንደኛው ነው። ይህም ድንጋጌ በቅዱስ ቁርኣን ተገልጾ ይገኛል። ‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ጾም በእነዚያ ከእናንተ በፊት በነበሩት (ሕዝቦች) ላይ እንደተጻፈ በእናንተም ላይ ተጻፈ (ተደነባ)፣ ልትጠነቀቁ ይከጀላልና።›› (2፡183) ‹‹(እንድትጾሙ የተጻፈባችሁ) ያ በርሱ ውስጥ ለሰዎች መሪ፣ ከቅን መንገድና (እውነትን ከውሸት) ከሚለዩም ገላጮች (አንቀጾች) ሲኾን ቁርኣን የተወረደበት የረመዳን ወር ነው። ከእናንተም ወሩን ያገኘ ሰው ይጹመው።›› (2፡125)

የረመዳን ወር ጾም እድሜው ለደረሰና ጤነኛ ለሆነ ሙስሊም ሁሉ ግዴታ በመሆኑ በልዩ ልዩ አሳማኝ ምክንያቶች ለምሳሌ በበሽታና በጉዞ፣ በእርግዝናና ልጅ በማጥባት ምክንያት በወሩ ለመጾም ያልቻለ ሰው የታመመው ከበሽታው ሲድን፣ ተጓዡም ከጉዞው ሲመለስ፣ ወላድም በሰላም ተገላግላ ጡት ካጠባች በኋላ ባልተጾመው ቀን ልክ በመጾም ሊያካክሱት ይችላሉ። ፍጹም መጾም የማይችል ደግሞ በጾሙ ቀኖች ልክ የተቸገረውን በማጾም (ጾመኛን በማብላት) ማካካስ ይችላል። በቁርኣን የሚከተለውን አንቀጽ እናገኛለን።

 ‹‹የተቆጠሩን ቀኖች (ጹሙ)። ከእናንተም ውስጥ በሽተኛ ወይም በጉዞ ላይ የሆነ ሰው ከሌሎች ቀኖች ቁጥሮችን መጾም አለበት። በእነዚያም ጾምን በማይችሉት ላይ ቤዛ ድኻን መብላት አለባቸው። (ቤዛን በመጨመር) መልካምንም ስራ የፈቀደ ሰው እርሱ (ፈቅዶ መጨመሩ) ለርሱ በላጭ ነው። መጾማችሁም ለናንተ የበለጠ ነው፤ የምታውቁ ብትኾኑ (ትመርጡታላችሁ)። … አላህ በእናንተ ገሩን (ነገር) ይሻል። በእናንተም ችግሩን አይሻም። ቁጥሮችንም ልትሞሉ አላህንም ቅኑን መንገድ ስለመራችሁ ታከብሩትና ታመሰግኑት ዘንድ (ይህን ደነገግንላችሁ)። (2፡184-185)

ፍች (ኢደል ፍጡር)። ‹‹ፍጡር›› የሚለው ቃል በመዝገበ ቃላዊ ትርጉሙ ጾም መፍታት ይሆናል። ‹‹ኢደል ፍጡር›› የሚለው ቃል ትርጓሜ ደግሞ የረመዳን ጾም እንዳለቀ ባሉት የሸዋል ወር ሶስት ተከታታይ ቀናት የሚካሄድ የጾም ፍች አከባበር ነው። የረመዳን ፍች በሶስት ተግባራት ይታጀባል። የመጀመሪያው ከጾም ፍቹ ቢያንስ አንድ ቀን አስቀድሞ ለተቸገሩ የጾም ፍቺ የሚሆን ስጦታ ይበረከታል። ስጦታው ዘካተል ፍጡር ይባላል።

 ዘካተል ፍጥሩ የግዴታ ሲሆን መጠኑ በጊዜው የቤተሰብ አባል ብዛት ይወሰናል። ለምሳሌ የአንድ ሰው የቤተሰብ አባላት አምስት ቢሆኑ ለሁሉም የዘካተል ፍጡር ይከፈላል። ክፍያው በአብዛኛው በአይነት ማለትም ለምግብ አገልግሎት የሚውል የእህል አይነት የሚሰጥ ሲሆን ካልተቻለ በየወቅቱ ዑለሞች በሚያወጡት የወቅቱ የገበያ ተመን መሰረት ክፍያው ወይም ስጦታው በገንዘብ የሚሆንበት አጋጣሚ አለ።

 ሁለተኛው የጾም ፍች ከአራቱም ማእዘናት ሙስሊሞች አደባባይ በመገኘት የጾም ፍች ስግደት በጋራ ይፈጽማሉ። ሶስተኛው፣ በሶስቱ ተከታታይ ቀናት አላህን ከማመስገን ጋር እርስ በርስ በመጠያየቅና በመዘያየር ሚዛናዊ በሆነ አግባብ ከወትሮው በተለየ መንገድ በደስታና በፍስሃ ማሳለፍ ነው።

የረመዳን ወርና ልዩ ልዩ ተግባሮች የቁርአን ንባብ፡-

 ቅዱስ ቁርኣን መውረድ ከጀመረበትን ቀን ጋር በመያያዙ የቅዱስ ቁርኣን ወር ነው ተብሎ ይጠራል። ቅዱስ ቁርኣንን መቅራትና በትእዛዛቱና በአስተምሮው መመራት የዘወትር ተግባር ቢሆንም በረመዳን ወር ከሌሎች ወሮች በተለየ በግልና በቡድን ይቀራል። የቡድን ቂርኣት ባህርይ የወሎ ሙስሊሞችን እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል። ብዙውን ጊዜ የዝሁር ወይም የአስር ሶላት እስከሚደርስ ድረስ መስጅድ ውስጥ ክብ ሰርተው ይቀመጣሉ። ክቡ አብዛኛውን ጊዜ ሁለት ዙር ይኖረዋል። የመጀመሪያው ቅዱስ ቁርኣን መቅራት በሚችሉ፣ ሁለተኛው ክብ በማይችሉ ይያዛሉ። በሌላ አገላለጽ በመጀመሪያው ዙር ያሉት ቁርኣን ሲቀሩ፣ በሁለተኛው ዙር ያሉት አዳማጭ ይሆናሉ። የህም ሂደት ተራ በተራ በዙር ይፈፀማል። የጀምኣው ወይም የስብስቡ አበጋር የተወሰኑ የቁርኣን አንቀጾችን ድምጹን ከፍ በማድረግ ይቀራል። በዚህን ጊዜ ሌሎቹ የአበጋሩን አቀራር ይከታተላሉ። እሱ የተወሰኑ አንቀጾችን እንደጨረሰ በስተቀኙ ላለው ያስተላልፋል። ተቀባዩ ከቆመበት በመጀመር የተወሰኑ የቁርኣን አንቀጾችን ድምጹን ከፍ አድርጎ በመቅራት ሲጨርስ በቀኙ ላለው ያስተላልፋል። አድማጭና ተከታታይ የሆኑ ቁርኣን መቅራት የሚችሉ ሰዎች ተረኛው ስህተት ከፈፀመ አስተካክሎ እንዲቀራ ያርሙታል። በመከታተልና በማድመጥ ብቻ የሚወሰን አይደለም። አንዱ ከሌላው እንዲማር ያደርጋል። የማረሚያና የመማሪያ አጋጣሚ ያመቻቻል።

በእዚህ የቁርኣን ንባብ በርካታ መለኮታዊ፣ መንፈሳዊ፣ ታሪካዊ፣ ሞራላዊ፣ ህጋዊ ወዘተ… የጸሎት ትምህርቶች እንዲታወሱና እንዲሰርጹ እድል ይፈጥራል። ለምሳሌ ከምእራፍ አንድ አላህ እጅግ በጣም ሩኅ ሩኅ እጅግ በጣም አዛኝ፣ የአለማት ጌታ፣ የፍርዱ ቀን ባለቤት፣ እሱን ብቻ የሚገዙት፣ እሱ ብቻ እርዳታ የሚጠየቅ ወዘተ እንደሆነ ይማሩበታል።

በምእራፍ 112 አላህ አንድና የሁሉ መጠጊያ እንደሆነ፣ አላህ አልፋና ኦሜጋ፣ ያልወለደና ያልተወለደ እንደሆነ፣ ለእርሱ አምሳያ አንድም ብጤ እንደሌለው ያውቁበታል።

 የተራዊህ ሶላት፡-

 ‹‹ተራዊህ›› የሚለው የአረብኛ ቃል ‹‹ማረፍ›› የሚል ትርጉም አለው። የተራዊህ ሶላት ሲባል አስር ረከዓ ሶላት እያረፉ መስገድ ማለት ነው። ባብዛኛው በረመዳን ወር ምሽት በመስጅድ ካልሆነም በኸለዋ በቡድን ይፈጸማል። በአገራችን በየሁለቱ ረከዓ መካከል በሚኖር የእረፍት ጊዜ በለስላሳ ዜማ ወይም መንዙማ ፈጣሪን ያውቁበታል፣ ነብዩን ይዘክሩበታል፣ ዱዓ ያደርጉበታል።

ፍጡር፡-

 በእስልምና ጾመኛን ማስፈጠር ልዩ ቦታና ደረጃ አለው። ያስፈጠረ ሰው በተግባሩ ከፈጣሪው ምንዳ እንደሚቸረው ያምናል። በዚህ መንፈሳዊ ምንዳ የተነሳ ሙስሊሞች ከጎረቤት፣ ከመንገደኛ፣ በተለይም ከችግረኛ ጋር ለማፍጠር ወይም ለማስፈጠር ይጣደፋሉ። በአንድ ማእድ ዙሪያ ተሰባስበው ቤት ያፈራውን ይቃመሳሉ።

 ሶደቃ፡-

 ሶደቃ ለራስ፣ በህይወት ለሌለ የቤተሰብ አባል ወይም ለአንድ ለሚያውቁት ሰው ተብሎ ለተቸገሩ የሚሰጥ የምጽዋት አይነት ነው። ኃጢያቶችን ያነጻል፣ ወደፊት ሊመጡ የሚችሉ አደጋዎችን ይታደጋል ተብሎ ይታመናል። በመሆኑም የፈጣሪ ጸጋ ለማግኘት ብዙ ሙስሊሞች የረመዳን ጾምን ይመርጣሉ። የረመዳን ወር ጸጋ በደረጃ የላቀ መሆኑን በማሰብ ሶደቃው በስፋት ይካሄዳል።

 ፊዳያ፡-

‹‹ፊዳያ›› ሙስሊሞች በህመም፣ በጉዞ፣ በእርጅና፣ በተለይ ሴቶች በእርግዝና፣ በወሊድና ልጅ በማጥባት ወዘተ ምክንያቶች የረመዳንን ወር በሙሉ ወይም በከፊል መጾም ሳይችሉ ሲቀሩ ላልጾሟቸው ቀኖች የተቸገሩንን የማስፈጠር የማካካሺያ (compensation) ተግባር ነው። ይህም ሁለት መልክ አለው። አንደኛው ጊዜያዊ ማካካሻ ልንለው እንችላለን። ለምሳሌ አንድ ሰው በበሽታው ምክንያት ከረመዳን ወር ውስጥ አስር ቀን ሳይጾም ከቀረ፣ ሲድን በወሩ ውስጥ ያልጾማቸውን አስር ቀኖች በመጾም ሊያካክስ ይችላል።

 ሁለተኛውን ቋሚ ማካካሻ ልንለው እንችላለን። የተቸገረን በማብላት ይፈፀማል። ለምሳሌ አንድ ሰው በህመሙ ምክንያት በረመዳን ወርም ይሁን ከዚያ ውጪ ለመጾም የማይችል ከሆነ በእያንዳንዱ ቀን አንዳንድ ሰው በማስፈጠር ፊዳያውን ቋሚ ማድረግ ይችላል።

ከፋራህ፡-

በእስልምና አንድ ሰው በጾም ወቅት የተከለከሉ ሀላልም ሆኑ ሀራም የሆኑ ድርጊቶችን ሲፈጽም ኃጢኣት ይሆኑበታል። ከድርጊቶቹ የሚነፃበት ክፍያ ‹‹ከፋራህ (expiation)›› ይባላል። የከፋራህ አይነቱና መጠኑ እንደ ድርጊቱ አይነት ይለያያል። ለምሳሌ አንድ ሰው በረመዳን ወር በጾም ላይ እያለ ከባለቤቱ ጋር የግብረ-ሥጋ ግንኙነት

“በረመዳን ሰዎች ከሌሎች ወሮች በተለየ በመስጅድ ወይም በኸለዋ ተሰባስበው ልዩ ልዩ እንደሚፈጽሙ አይተናል። በተጨማሪም በጾም ፍቺ አደባባይ ወጥተው እንደሚያከብሩ አውስተናል። እነዚህ ክንውኖች በሰዎች መካከል ትውውቅ እንዲፈጠር፣ የእርስ በርስ ግንኙነት እንዲዳብርና እንዲጠናከር አቅም የመፍጠር ፋይዳ ያበረክታሉ”

ቢያደርግ እንደ ኃጢኣት ይወሰድበታል። ከዚህ ኃጢኣቱ ለመንጻት በተከታታይ ስድስት ወር መጾም ይጠበቅበታል። ካልቻለ ስድሳ ችግረኞችን በማብላት ከፈጸመው ኃጢኣት መንጻት ይኖርበታል።

 ዘካተል ፍጡር፡-

‹‹ዘካተል ፍጡር›› የረመዳን ወር የፍቺ ክብረ በአልን ለማክበር አቅም የሌላቸው ሰዎች እንደሌሎቹ ተደስተው እንዲውሉ የሚሰጥ ግዴታ የሆነ ክፍያ ነው። ያልከፈለ ሰው የተሟላ ጾም እንደ ጾመ አይቆጠርለትም። ይህ ለተቸገሩት የሚሰጥ ክፍያ ብዙውን ጊዜ በአይነት የሚፈጸም ሲኾን እንደ ሁኔታው በገንዘብ ሊተካም ይችላል። በአይነት ሁለት እፍኝ ስንዴ ይኾናል። በገንዘብ ሲኾን የእህሉ ተመን በረመዳን ወር ገበያ የሽያጭ ዋጋ ይወሰናል።

 ዘካተል ፍጡር በቤተሰብ አባላት ብዛት ላይ ያተኩራል። ለምሳሌ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ አምስት አባላት ቢኖሩ አምስቱም የቤተሰቡ አባላት እያንዳንዳቸው አስር ኪሎ ስንዴ ወይም የአስር ኪሎ ስንዴ የገበያ ዋጋ ለተቸገሩ ይሰጣሉ።

 ኢደል ፍጡር፡-

‹‹ኢደል ፍጡር›› ቃሉ አረብኛ ኾኖ የጾም ፍች ህዝባዊ ክብረ በአል እንደማለት ነው። ጾሙም ሆነ የጾም ፍች በጨረቃ ዑደት ላይ በመመስረቱ ፍችው በሰላሳኛው ወይም በሀያ ዘጠነኛው ማግስት ሊኾን ይችላል። ከሁለቱ ባንዱ ቀን አንስቶ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ኢደል አልፍጡሩ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ይከበራል። የመጀመሪያ ቀን የዋዜማ ምሽት ሴቱ የሴቱን፣ ወንዱ የወንዱን ዝግጅት ያደርጋሉ። የሚበላው የሚጠጣው ይሰናዳል። ሌሊቱ በጸሎት ይታለፋል። ንጋት ላይ ሁሉም ገላውን ተጣጥቦ፣ ጸአዳ ልብስ ለብሶ፣ ህጻን አዛውንት ሳይለይ ለስግደት አቅራቢያው ወደሚገኝ አደባባይ ተክቢራ እያለ ይወጣል። በአደባባዩ ቢያንስ ሶስት ተግባሮች ይከናወናሉ።

 ዋናው የስግደቱ ስነ ስርአት ሲሆን ሁለተኛው ድስኩር ነው። በድስኩሩ ፈጣሪን ከማመስገን በተጨማሪ ስለ ሙስሊሙና አገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮችና የትኩረት አቅጣጫዎች መልእክት ይተላለፍበታል። በሶስተኛ ደረጃ የመንግስት አካሎች ከሙስሊሙ ህብረተሰብ ጋር ያለን ግንኙነት የሚያጠናክሩ መልእክቶች እንዲተላለፉ እድል ይሰጣል።

 ከአደባባዩ ስነ ስርአት በኋላ ሁሉም ወደየቤቱ ይጓዛል። ሲመለስ ጉዞው በመንዙማ ይደምቃል። ሁሉም እንደየብሔረሰቡ የመንዙማ አይነት እያወረደ፣ እራሱን እያስደሰተ ጊዜውን የደስታ፣ ድባቡን የፍስሃ ያደርገዋል። ቀሪ ጊዜውን ከቤተሰቡ፣ ከጎረቤቱ ጋር ቡና በመጠጣት፣ አብሮ በመብላት፣ ዘመድና ወዳጅ በመጠየቅ ያሳልፋል።

የረመዳን ወር ጾም ፋይዳ

የረመዳን ጾም በልዩ ልዩ መንገድ ሰፊ ትንተና ሊደረግባቸው የሚችሉ መንፈሳዊ፣ ስነምግባራዊ፣ አካላዊ፣ ባህላዊና ማህበራዊ ፋይዳዎች አሉት። በእዚህ ጽሁፍ እነዚህን ሰፊ ፍቺና ጥልቅ ትርጓሜ ያላቸውን የረመዳን ወር ፋይዳዎች ባጭሩ ለማስተዋወቅ ይሞከራል። የረመዳን ወር ጾም ፋይዳ መሰረት መንፈሳዊነቱ ነው። የረመዳን ወር ጾም ከእስልምና ማእዘናት አንዱ የኾነ መለኮታዊ ትእዛዝ እንደሆነ ይታወቃል። በትዕዛዙ ውስጥ ጿሚዎች የሚያገኙትን ምንዳ አላህ በቁርኣኑ እንዲህ ሲል ገልጾታል፤- ‹‹ጿሚዎች ወንዶችና ጿሚዎች ሴቶችም … አላህ ለእነርሱ ምህረትንና ታላቅን ምንዳ አዘጋጅቶላቸዋል(33፡35)›› ለነብዩ ሙሐመድ አላህ ለጾመኛ ሰው የሚሰጠውን ምንዳ ‹‹(አላህ አንድን ጾመኛ አስመልክቶ እንዲህ ብሏል) ‹‹ምግቡን፣ መጠጡንና ስጋዊ ስሜቱን ለኔ ሲል ትቷል። ጾም ለኔ ነው፣ እኔም ነኝ ምንዳውን የምሰጠው›› የመልካም ስራ ምንዳ (በዚህ ወር) አስር እጥፍ ነው። የሰው ልጅ ተግባር ሁሉ ለራሱ ነው – ጾም ሲቀር፤ እርሱ ግን ለኔ ነው። ምንዳውን እኔው ራሴ እሰጠዋለሁ›› እንዳላቸው ተዘግቧል።

 ጾመኛ ሰው ለጌታው ብሎ ሲጾም ውሎ ሲያፈጥር የምስርር መንፈሳዊ እርካታም ያገኛል። ነብዩ ሙሐመድ ይህን መንፈሳዊ እርካታ ‹‹ጾመኛ ሁለት ደስታዎች አሉት። ሲያፈጥር ይደሰታል። ከጌታው ጋር ሲገናኝም በመጾሙ ደስ ይለዋል›› በማለት ተናግረዋል።

ስለምግባራዊ ፋይዳ፡-

 የጾም ስነምግባራዊ ፋይዳ በልዩ ልዩ መንገድ ይገለፃል። የመጀመሪያው ጾመኛው ለፈጣሪው ባለው ታማኝነት ሲሆን በግል ስለሚፈፀም መፆሙ የሚታወቀው በጿሚውና በፈጣሪው ብቻ ይሆናል። ፈጣሪ መኖሩን አምኖ፣ ያውቅብኛል ብሎ ጾም ከሚያፈርሱ ድርጊቶች ታቅቦ መጾሙ ታላቁ የስነ ምግባር ልእልና ነው። ሌላኛው የጾም ስነ ምግባራዊ ፋይዳ ለጋስነትና እዝነት ያለበት ይሆናል። በልዩ ልዩ ሁኔታዎች ችግረኞች ይታሰባሉ። ደስ ብሏቸው ይጾሙ ዘንድ በሶደቃ፣ በፍጡር፣ በዘካተል ፍጡር ወዘተ አመካኝነት ያላቸው ሰዎች ለሌላቸው በማካፈል ለጋስነታቸውን እዝነታቸውን ያዳብራሉ። የረመዳን ወር ጾም ምግብና መጠጥ፣ እንዲሁም ከባለቤት ጋር ከመተኛት በመታቀብ ብቻ የሚወሰን አይደለም። ሀሰት መናገርና እኩይ ተግባር መፈጸም የጾምን ምንዳ ያሳጣል። ይህን የሰናይ ስነምግባር ባለቤትነት በሚመለከት ነብዩ ሙሐመድ እንዲህ አይነቱን ድርጊት አስመልክተው ‹‹ሀሰት መናገርንና በርሱ መስራትን ያልተወ ሰው ከምግብና ከመጠጥ ተገልሎ ከመዋሉ አላህ ምንም ፍላጎት የለውም›› ማለታቸው ተዘግቦ ይገኛል። በአጠቃላይ የረመዳን ወር መልካም ስራ ከሌላው ቀን መልካም ስራ ከአስር በላይ የሆነ ምንዳ ያስገኛል ተብሎ ይታመናል።

 አካላዊ ፋይዳ፡-

የረመዳን ወር ጾም በጥቅሉ የሰውነትን ፍላጎት የመግታት፣ ልማዳዊ ድርጊትን የመቆጣጥር ሃይል የመፍጠር፣ የማሳደግና የማዳበር ፋይዳ አለው። ለምሳሌ በጾም የምግብ ክምችት እንዲቃጠል፣ የሰውነት ክብደት እንዲቀንስ፣ ቁመና የማስተካከልና ጤና የመጠበቅ ፋይዳው ይጎላል። በጾም ወቅት እንደ ቡና፣ ሻይ፣ ጫት ወዘተ የመሳሰሉ የዘወትር ልማዳዊ ድርጊቶች ስለሚከለከሉ፣ ሰዎች የልማድ ተገዥዎች እንዳይኾኑ ስሜትን የመግራትና የመቆጣጠር አቅም እንዲዳብር ይረዳል።

ባህላዊ ፋይዳ፡-

 የቁርኣን ምንባብ ወቅቶች፣ የስጦታ ድርጊቶች፣ የከበራ ድርጊቶች ወዘተ በድምሩ የሙስሊሙ ማንነት መገለጫ የእስላማዊ ባህል ክፍሎች ናቸው። በተጨማሪ በረመዳን ወር ምሽቶች ሰዎች በየቤቱ ተሰባስበው እጅጉን በመንዙማ መልክ ታሪክ በመተረክ፣ ለአላህ ውዳሴ በማቅረብ፣ ነብዩ ሙሀመድንና ደጋግ ሰዎችን በመዘከር ወዘተ ያሳልፋሉ። በጥቅሉ የረመዳን ወር የእስላማዊ ባህላዊ ትምህርትና ንባብ፣ እንዲሁም የጥበብ መግለጫ አጋጣሚዎች የሚፈጠርበት ነው።

ማህበራዊ ፋይዳ፡-

በረመዳን ሰዎች ከሌሎች ወሮች በተለየ በመስጅድ ወይም በኸለዋ ተሰባስበው ልዩ ልዩ እንደሚፈጽሙ አይተናል። በተጨማሪም በጾም ፍቺ አደባባይ ወጥተው እንደሚያከብሩ አውስተናል። እነዚህ ክንውኖች በሰዎች መካከል ትውውቅ እንዲፈጠር፣ የእርስ በርስ ግንኙነት እንዲዳብርና እንዲጠናከር አቅም የመፍጠር ፋይዳ ያበረክታሉ። ጾም ትልቅ ትንሽ፣ ሃምታም ድሃ፣ ጠንካራ ደካማ ሳይለይበት ሁሉም የሚጾሙት በመኾኑ፣ በሁሉም ዘንድ የእኩልነት መንፈስ እንዲሰፍን ያግዛል። ረመዳን ሃብታሙ ድሃውን የሚያስብበት ወር በመኾኑ፣ ይህም የማህበራዊ የመረዳዳት ፋይዳ ያስገኛል።

 ከዚህ በላይ ባጭሩ ስለረመዳን ወርና ጾም፣ በጾም ውስጥ ስለሚከወኑ ልዩ ልዩ ድርጊቶች፣ በጾሙ የሚፈፀሙ መንፈሳዊ፣ ስነልቦናዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ፋይዳዎች ለማሳየት ተሞክሯል። ከእነዚህ ሀሳቦች በመነሳት የረመዳን ወር የሰላም፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ የወንድማማችነት ወዘተ ወርና የእነዚህ እስላማዊ እሴቶች የስልጠና ወር ነው ማለት ይቻላል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top