ጥበብ እና ባህል

የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ሳንካዎችና ጸጋዎች በኢትዮጵያ (ክፍል ፪)

፫. እውነት፣ እውቀትና ሐተታ

(ለባዊት ነፍስ)

በክፍል አንድ ጽሑፍ ስለ ነገረ መገናኛ ብዙኃንና ተግባቦት እንደ መግቢያ የሚሆኑን ነጥቦችን ተነጋግረናል። ከነባቢት ነፍስ የሚመነጭ መነጋገር የተግባቦት መነሻ ነው። በዚህ ክፍል ደግሞ ከመናገር ባሻገር ሰሚዋ ነፍስ መርማሪ እንደሆነች እናያለን። ለመግባባት መጀመሪያ መረዳዳት (በተናጋሪውና በሰሚው መካከል) የትርጉም አንድነት፣ የስሜት መጋራትና በእውነተኝነቱ ላይ መስማማት ያስፈልጋል። ይህንንም ለማድረግ መርማሪ ነፍስ (ለባዊት ነፍስ) ያስፈልጋል።

 ስለ እውነት፣ ስለ እውቀትና ሐተታ ሳናወራ ወደ ዘመናችን የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ተግባቦት ዘው ብለን ብንገባ ውይይታችንን ቁንጽል ያደርገዋል። በርግጥ የነፍስ ነባቢነት ባህርይ ቃል አውጥቶ ለሌሎች በሚሰማ ልሳን መናገር ነው። መናገር ሲባል ትርጉም ያለው ነገር፣ በሰሚው እዝነ ልቡናና ስሜት ቆንጥጦ በመያዝ አድማጩ ቦታ ሰጥቶት ምላሽ ሊያደርግበት የሚገባ ሐሳብ ማስተላለፍ ነው። ጩኸት ሁሉ ሙዚቃ እንዳልሆነ ሁሉ ንግግር ሁሉ እውነት አይሆንም። አንድ ንግግር / የምልክት ገለጻ ወይም ጽሑፍ/ ከስሜት ቀስቃሽነት ባሻገር ትርጉም ሰጭነትና እውቀት ጨማሪነት ወይም አዲስ ነገር አስተዋዋቂነትን ሲላበስ ነው የተግባቦት መሠረት የሚሆነው። ለዚህ ነው ከንግግር ሁሉ እውነትን መርጦ ማውጣት፣ መመርመርና ለጋራ ተግባቦት የሚሆነውን መለየት አስፈላጊ የሚሆነው። ይህንን ማድረግ ደግሞ የአድማጭ ነፍስ ለባዊነት ባህርይ መገለጫ ነው።

“ለባዌ” የሚለው የግእዝ ቃል ተመራመረ፣ ወደመረዳት ተጠጋ፣ አጠየቀ፣ ተነተነ የሚል ትርጉም ይሰጣል፤ “Rational Examination, Critical Reflection” የሚሉ የእንግሊዝኛ ሐረጋት አቻ መሆኑ ነው። ከጥንት ዘመን ጀምሮ የነበሩ ፈላስፎች የሰውን ልጅ ምክንያታዊነት በተለያየ መንገድ ሲገልጹ ኖረዋል። ምክንያታዊነት እንዲያውም ሰውን ከሌሎች እንስሳት የሚለየው ባህርይ እንደሆነ ያስረግጣሉ። ይህ ምክንያታዊነት ሰውን ወደ ጥበብ የሚያመራው ተፈጥሮአዊ ጸጋው ነው። ለነገሮች ማስረገጫና ማብራሪያን መፈለግ፣ ከዘፈቀዳዊ እምነት ይልቅ ለእውነት ድጋፍን መሻት፣ በጭፍን ከማመን ይልቅ መጠራጠርን ማስቀደም የነፍስ ለባዊነት መገለጫ ነው። ነፍስ ራሷን ካልዋሸች አንድን ነገር ከመቀበሏ ወይም ከማመኗ በፊት ቀድማ መመርመር፣ መፈተሽ፣ ትችላለች እንጅ እንዲሁ የተነገረን፣ የተጻፈን ነገር ብቻ እንደወረደ አትቀበልም። ይህንን ካደረገችም ከክብሯ፣ ከመንበሯ ዝቅ ብላለች ማለት ነው።

 ለምሳሌ ሶቅራጥስ ያልተመረመረ ሕይወት እንዳልተኖረ ይቆጠራል (“Unexamined life is not worth living”) ሲል የነፍስ ትክክለኛ ባህርይ የሕይወትን ምስጢር ምንነት መፈተሽ፣ መመርመር እንደሆነ ሲያስረግጥ ነው። እንዲያውም ሶቅራጥስን እስከ ሞት ያደረሰው በዘመኑ የነበሩ ባለስልጣናትና “አዋቂዎች ነን” ባዮች ሳይመረምሩ የማያውቁትን እንደሚያውቁት በማስመሰል መኖራቸው ከሰውነት ተራ በታች እንዳደረጋቸው ስላጋለጠባቸው ነበር። ከታች በሰፊው እንደምንመለከተው በምድራዊ ሕይወት የነፍስ ተመራማሪነት እውነትን ወደ ማግኘት ሲያስጠጋት ከሞት በኋላ ለሚቀጥለው ዘለዓለማዊ ሕይወትም እንደ ግብአት ይሆናል። አጠር ባለ ቋንቋ ተመራማሪ ሕይወት ኢ-መዋቲና ዘለዓላማዊት ናት እንደማለት ነው።

 የሶቅራጥስ ተማሪ የነበረው አፍላጦንም መመራመር ወደ እውነት የሚያደርሰን መንገድ እንደሆነ የነፍስ ምክንያታዊነት ደግሞ አማናዊነትን (Forms) እንድንገነዘብና ከፍተኛ መረዳት ደረጃ (Understanding) ላይ እንድንደርስ ይረዳናል። ከፍ ወዳለ የመረዳት ማማ መውጣት፣ የሕሊና ልዕልና የአስተሳሰብ ጽርየት (አንጽሮተ ኅሊና) ከዚሁ የነፍስ ምክንያታዊነትና ተመራማሪነት የሚመነጭ ነው። እናም እስከ አሁን ድረስ የሚጠቀስለት “እውቀት ምንድን ነው?” ለሚለው ጥያቄ የሰጠው መልስ ከነፍስ ተመራማሪነት ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ አለው። ይኸውም “እውቀት ማለት የተረጋገጠ እውነተኛ እምነት ነው” (“Knowledge is justified true belief”) በማለት የደመደመው ነው። ማረጋገጥ የነፍስ ኃላፊነት ሲሆን ማመን ደግሞ የኅልውና መሠረት መሆኑ ነው። ትክክለኛው የሰው ከመጠራጠር ወደ ማረጋገጥ፣ ከማረጋገጥ ወደ እምነት ከእምነት ወደ እውቀትና መረዳት መጨረሻም እውነት ላይ መድረስ ነው። የአፍላጦን ተማሪ አሪስጣጣሊስ በበኩሉ ሰው ምክንያታዊ እንስሳ ነው ያለው ንግግሩ ለዘመናት ሲወሳ ይኖራል።

የነፍስ ምክንያታዊነት በመጽሐፍ ቅዱስም አጽንኦት ተሰጥቶታል። እንኳን በአንደበት የተነገረን ሰዎች የሚያደርጉትን ግብርና ቃላዊ ዲስኩር ይቅርና ለሰው ልጅ “መንፈስን ሁሉ የመመርመር” ኃላፊነትና ግዴታ ጠሰጥቶታል። ስለዚህም ነፍስ “መንፈስን ሁሉ” መመርመር፣ መጠየቅ አለባት። (1ኛ ዮሐንስ 4፥1) ይህ የለባዊት ነፍስ ባህርይ ነው።

ከዚህ በመነሳት አያሌ የሃይማኖት ፈላስፎች ሰው በተሐዝቦት (Observation) እንዲሁም በExperience የሚያገኘውን እውቀት ነፍስ መመርመር እንዳለባትና ከዚያ ውጭ ያለው ደግሞ የሚገለጥ እውነት እንደሆነ ያትታሉ።

 ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ለExistentialists (ኒች፣ ሳትረና ሃይዲገር) የሚገለጥ እውቀት ወይም የተፈጥሮ ኑባሬ (ተፈጥሯዊ ባህርይ) የሚባል ነገር የለም። ሰው ነጻ ፍጡር እንደመሆኑ ስሜቱ (ሕይወት) የምትጠይቀውን ሁሉ እያስተናገደ ይኖራል። እናም የጋራ እውነት ወይም ቅቡል የሚባል ባህል ወይም የሃይማኖት ህግን መከተል እንደማይገባንና፣ ምክንያታዊነት የሚባል የተፈጥሮ ባህርይ አለመኖሩን ይሞግታሉ (በተለይ ኒቼ)። ሰው ከተፈጠረ (ወደዚህ ምድር ከተወረወረ) በኋላ ማንነቱን ራሱ ይፈጥራል በማለት ይሞግታሉ። ይህ የፍልስፍና ዘርፍ የሰውን ልጅ ነጻነት የተጎናጸፈ ፍጡር እንደሆነ በማስረገጥ ዲበአካላዊ ቅድምናን (ከፈጣሪ የተሰጠ የተፈጥሮ ባህርይ) በመተቸት ሰው ራሱን ይሰራል ወደሚል ድምዳሜ የሚደርስ ነው። ይህ የቅርብ ዘመን የፍልስፍና ክንፍ ሰፊ ሐተታ የሚያስፈልገው ስለሆነ እዚህ ላይ ማብራራት አይቻልም።

ይልቁንም ለውይይታችን ማዕከላዊ ስፍራን የሚይዝ አንድ ጥቅስ እንውሰድና እንቀጥል። ቃሉን ከታላቁና “አወዛጋቢው” የ17ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ዘርዓ ያዕቆብ ነው የተዋስነው። እንዲህም ይላል:-

 እስመ እምተረፈ ልቡናሁ ፈጠረኒ [እግዚአብሔር] ለባዌ አኮ በከንቱ ዘከመዝ ፈጠረኒ ዳዕሙ ከመ እኅሥሦ ወእለቡ ኪያሁ ወጥበቢሁ በፍና እንተ ፈጠረኒ ወእሰብሖ እስከ አመ ሀሎኩ። ወሐለይኩ ወእቤ በይነ ምንት ኲሉ ሰብእ ኢይሌብዉ ጽድቀ እንበለ ሐሰት ወመሰለኒ እስመ ፍጥረተ ሰብእ ድክምት ወሀካይት ይእቲ። ወሰብእሰ ይሠምር በጽድቅ ወጥቀ ያፈቅራ ወይፈቅድ ያእምር ኅቡአተ ፍጥረት ወባሕቱ ዕፁብ ውእቱ ዝንቱ ነገር ወኢይትረከብ እንበለ በዓቢይ ፃማ ወትእግሥት።

 ትርጉም (ዓለቃ ያሬድ ፈንታ: ሐተታ ዘርዓ ያዕቆብ ወሐተታ ወልደ ሕይወት፣2007 ዓ.ም፣ ገጽ 9)

 እግዚአብሔር [ከተትረፈረፈው ጥበቡ] ለባዊ (ተመራማሪ፣ ሐታቲ) አድርጎ ከፈጠረኝ እንዲሁ በከንቱ የፈጠረኝ አይደለም። በፈጠረኝ መንገድ እፈልገው ዘንድ እርሱንና ጥበቡን አውቅ ዘንድ እስካለሁ ድረስም አመሰግነው ዘንድ ነው እንጂ ብዬ አስባለሁ። ሰዎች ሁሉ ከሐሰት በቀር ስለምን እውነትን አያውቁም? ብዬ አሰብሁ። ለእኔ የሰው ተፈጥሮ ደካማና ሐኬተኛ ስለሆነች መሰለኝ። ሰው ግን ጽድቅን ይወዳል፤ እጅግም ያፈቅራታል። የፍጥረት ምሥጢርንም ያውቅ ዘንድ ይወዳል። ነገር ግን ይህ ነገር እጹብ ድንቅ ነው። ያለ ታላቅ ድካምና ትዕግሥት አይገኝም።

በዚህ ጥቅስ ውስጥ የሰው ልጅ አሳቢ፣ ጠያቂና ተመራማሪ ሆኖ መፈጠሩን ይነግረናል። ይህም ብቻ አይደለም፤ የሰው ልጅ እውቀትን ለማግኘት፣ እውነት ላይ ለመድረስ የሚኳትን፣ አዲስ ነገርን ለማወቅ የሚባዝን ፍጡር እንደሆነም ይሞግታል። ነገር ግን ሰዎች እውነትን ለማግኘት ሰነፎች እንደሆኑም ይነግረናል። አሪስጣጣሊስ የሰው ልጅ እውቀትን ለማግኘት ይጓጓል ያለውን ቅዱስ መጽሐፍም ስለ አቴናውያን የተናገረው ምስክር ነው። “ወሰብአ አቴንሰ ወእለ ይነግዱ ኲሎሙ ህየ ባዕድ ትካዝ አልቦሙ ዘእንበለ ዳዕሙ ለአጽምኦ ወነቢብ ዘሐዲስ” (የአቴና ሰዎችና በዚያም የነበሩ እንግዶች ሁሉ አዲስ ነገርን ከመናገርና ከመስማት በቀር ሌላ አሳብ አልነበራቸውም) (የሐዋርያት ሥራ 17፥21)። አንዳንድ የአውሮፓ ልሂቃን ይህ ምክንያታዊነት ለአፍሪካውያን ወይም ለጥቁሮች እንደማይሰራ ምክንያታዊ ያልሆነ ድምዳሜ ቢኖራቸውም እንደ ራሞሴ ያሉ የአፍሪካ ልሂቃን ያስተባብላሉ። በአጠቃላይ እውቀትን መሻት፣ መመርመር የሰው ልጆች ሁሉ ተፈጥሮአዊ ባህርይ ነው ማለት ይቻላል። የዘርዓ ያዕቆብ ደቀ መዝሙር የነበረው ወልደ ሕይወትም እንዲህ ይላል:- “ሐተታ አንቀጸ ጥበብ፣ ወልቡናሰ መርኆ ለአንቀጸ ጥበብ” (ሐተታ ወይም ምርምር የጥበብ በር ናት፣ ልቡና ደግሞ የጥበብ በር መክፈቻ ቁልፍ)።

 ይህንን ጥቅስ እዚህ ላይ ያመጣሁት የዘመናችን “የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ትውልድ” እውነትን ለመመርመር የነፍሱን እውቀትን መሻት እንዴት እያስተናገዳት እንደሆነ ለማጠየቅ ነው። ለዘመናችን በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ጋጋታ ለሚናውዙ ነፍሳት የታመነ ቃል፣ ሁነኛ መፍትሔ ነው። ከነባቢት ነፍስ የሚወጣ ቃል በለባዊት ነፍስ ተመርምሮ ከሌሎች ነፍሶች ጋር ስምምነት ላይ ሲደረስ እውነት ሆነ ይባላል፣ በዚያው ተግባቦት አለ ማለት ይቻላል። ይህንን የነፍስ መርማሪነት ወይም ለባዊነት ሁሉም ሰዎች ሲጎናጸፉት ምክንያታዊ ማኅበረሰብ ተፈጠረ ይባላል። ይህም የስልጡን ማኅበረሰብ እውናዊ መሆን እንኳን የመገናኛ ብዙኃን ጋጋታና የመትረየስ፣ የመድፍ ኳኳታ የማያስበረግገው ምክንያታዊ በራስ መተማመን ላይ የደረሰ ይሆናል። ለባዊት ነፍስ የምትመራው “መረጃ አይናቅም፣ አይደነቅም” በሚል መርህ ነው።እንዳይናቅ እውነት ሊሆን ይችላል፤ እንዳይደነቅ ደግሞ ሐሰት ሊሆን ይችላልና። ታዲያ የሰው ልጅ ጥንተ ተፈጥሮ መመርመር ከሆነ፣ ፍላጎቱም እውቀትን ማግኘት፣ ሕይወቱም ጥበብን የመሻት መኳተን ከሆነ ስህተትና በአሉባልታ መነዳት ከየት መጣ? እንዴት እንደበቀቀን የተነገረውን እያስተጋባ (በፌስቡክ Share and Like)፣ እንደጋሪ ፈረስ በተቀደደለት ቦይ እየነጎደ የሚሄድ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን መንጋን ልናይ ቻልን? እዚህ ላይ ባንድ ዘመን የነበሩ፣ በቦታ እና በባህል እጅግ የተራራቁ ሁለት ፈላስፎች አንድ ዓይነት ድምዳሜ ላይ ይደርሳሉ። ፈረንሳዊ ሬኔ ዴካርት (Rene Descartes) ና ኢትዮጵያዊው ዘርዓ ያዕቆብ፣ የስህተት ምንጩ ነጻ ፈቃድና ሳይመረምሩ ማመን ነው ይላሉ። የሰው ልጅ የመመርመር ተፈጥሮና ምክንያታዊነት በምልዓት ተሰጥቶት ሳለ ነጻ ፈቃድን ያላግባብ በመጠቀምና ለመመርመር በመስነፉ ለስሕተትና ሐሰትን ለማመን ተጋልጧል። በሌላ አገላለጽ ነፍስ ሕያዊነቷን መዘንጋቷ ነው የስሕተት ሁሉ ምንጭ። እውነትን ባለመቀበሏና ሐሰትን በማመኗ ለቅጣት እንደምትዳረግ የሞራል ኃላፊነት እንዳላት በመዘንጋቷ። የዘመናችን መገናኛ ብዙኃንም በሰነፍ ነፍሶች ላይ የመፍሰስ እድል የተሰጠው ይመስላል። መረጃን በላይ በላዩ እየላከ ለመመርመር ፋታ ሳይሰጣቸው እንዲሁ እንዲቀበሉት እያስገደደ ይገኛል። የመረጃው መደራረብና ብዙኃኑ እየተቀባበሉ ሲያራግቡት ውሸቱ እውነት እውነቱ ደግሞ ውሸት የሚሆንበት እድሉ ይሰፋል። ምክንያቱም “ብዙኃን ይመውኡ” (ብዙዎች ያሸንፋሉ) ነውና ከመረጃው ጎርፍ ውስጥ የቱ ብስል የቱ ጥሬ፣ የቱ እንክርዳድ የቱ ስንዴ እንደሆነ እንኳ የመመርመር እድላችንን ይዘጋዋል። ይህም ከተግባቦት ይልቅ ግራ መጋባትና መጋጨትን ያስከትላል። ይህንን በቦታው በሰፊው አብራራዋለሁ።

፬. ሕያዊት ነፍስ (የሥነ ምግባራዊ በጎነት መሠረት)

የሰውን ተፈጥሯዊ ምንነት ከሚመለከቱ ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ “ከሞት በኋላ ሕይወት አለ ወይ?” የሚለው ነው። በርግጥም የዚህ ጥያቄ መልስ በምድራዊ ሕይወት ለምንከተለው ግብራዊ እንቅስቃሴ ሁሉ መሠረት ነው። የየቀን መስተጋብራችን፣ ከሌሎች ጋር የሚኖረን ግንኙነትና ተግባቦት ከሞላ ጎደል ለነገ ባለን የሕይወት ትርጉም ላይ የተመሠረት ነው። ይህ ጥያቄም ነው ለአብዛኛዎቹ ሃይማኖቶች መሠረት፣ ለአያሌ ፈላስፎችም የክርክር መንስኤ የሆነው። እስኪ ክርክሩን እንለፈውና የአብዝሃኛዎቹ ምክንያታዊ ድምዳሜ ላይ እንነሳ:- “ነፍስ የማትሞት፣ የማትበሰብስ ዘለዓለማዊት ናት” ከሚለው።

ነፍስ ለባዊት ናትና እውነትን ከሐሰት፣ በጎን ከክፉ፣ ቅቡልን ከነውር፣ ለይታ ታውቃለች። እንዲያውም እንደ አበው አስተምህሮ ከማንኛውም የመጽሐፍ ሕግ ወይም የቃል ትምህርት በፊት ነፍስ ክፉን ከበጎ የምትለይበት ሕገ ልቡና ነበረ። የነፍስ ክፉን ከበጎ መለየቷ ብቻውን ግብ አይደለም። ከነፍስ ተፈጥሮ ጋር የሚስማማውን ከኅያዊነቷ ጋር የማይቃረነውን ትመርጥ ዘንድ፣ ምርጫዋንም በተግባር ትገልጥ ዘንድ ታውቃለች። ይህ የነፍስ ምርጫ ነው እንግዲህ በሥነ ምግባር ሚዛን በጎ ወይም መጥፎ ተብሎ የሚፈረጀው። ጠያቂው ማን፣ መቼ እና እንዴት እንደሚጠይቅ ስምምነት ላይ ባይደረስም የነፍስ ዘለዓለማዊነት ወይም ከሞት በኋላ ሕይወት አለ የሚለው ሙግት ግን ወደ ሥነ ምግባራዊ በጎነት መግቢያ በር እንደሆነ አያከራክርም። ካንት ሞራሊቲ ከምክንያታዊ ፍጡር ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ አለው ሲል፤ ፈላስፋው ወልደ ሕይወት ደግሞ የበጎ ምግባር መሠረቱ የምክንያታዊት ነፍስ ኢ-መዋቲነቷን ማወቋ ነው ይለናል።

ይደልወነ እንከ ንእመን እንበለ ኑፋቄ ከመ ነፍስነ ኢመዋቲት ይእቲ። ወበከመ ወጽአት ብርህተ እምሕጽነ ፈጣሪሐ ከማሁ ትገብእ ኀቤሁ እምድሕረ ዝንቱ ንብረት። እስመ ልቡናነ ያጤይቄነ ይኩን ከማሁ ወዝንቱ ትምህርት ያስተፌስህ ኅሊናነ ወያጽንአነ በተስፋ ዘኢይማስን ወያሤኒ ኲሎ ንብረተነ ወይከውን መሠረተ ለኩሉ ምግባረ ሰናይ ወለኩሉ ጽድቅ።

ትርጉም :- አለቃ ያሬድ ፈንታ፣ (ከላይ የተጠቀሰው፣ ገጽ 46)

 እንኪያስ ነፍሳችን ሟች እንዳልሆነች ያለጥርጥር እናምን ዘንድ ይገባናል። ከፈጣሪዋ ሕጽን (እቅፍ) ብርህት ሆና እንደወጣች እንዲሁም ከዚህ ኑሮ በኋላ ወደእርሱ ትመለሳለች። እንዲህ ይሆን ዘንድ ልቡናችን ያስረዳናልና። ይህ ትምህርትም ኅሊናችንን ደስ ያሰኛል። በማይጠፋ ተስፋም ያጸናናል። ኑሯችንን ሁሉም ያሳምረዋል። ለበጎ ነገር ሁሉ፣ ለእውነትም ሁሉ መሠረት ይሆናል።

 ይህንን በጎና ክፉ የሚለየውን የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ጸጋ እጓለ ገብረ ዮሐንስ “ብጹዓን ንጹሐነ ልብ:- ስለ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር መሠረት” በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ “ብርሃነ ልቡና” ሲሉት ክፉ ስንሰራ ሳይዋሽ የሚወቅሰንን የህሊና ውስጠ ሙግት ደግሞ “የሕሊና ወቀሳ” ብለውታል። (1983፣ ገጽ 64)። የነፍን ኢ-መዋቲነት በእምነት ካልሆነ በቀር በምክንያት ማስረገጥ አይቻልም። በርግጥ ፈላስፎች ሞክረዋል። ለምሳሌ ሶቅራጥስ ፌዶ (Pheado) በተሰኘ የአፍላጦን ድርሰት ውስጥ የነፍስን ዘለዓለማዊነትና የሞትን ምንነትና ምንምነት (ሞት የሚፈራ ነገር አለመሆኑን) ለመረዳት ሕይወትን በሙሉ በጥበብና በምርምር መኖር እንደሚገባን ሲመክር የፍልስፍናን ሕይወት ወደ ዘለዓለማዊነት የሚደረግ ዝግጅት ነው ይለዋል። ይህም ሞትን መለማመድ፣ በሞት ላይ መድፈርና ሞትን ድል መንሳት ነው።

 በምድራዊ ሕይወት ደግሞ “ልጅ መውለድ የሞት መድኃኒት ነው” የሚል የአገሬው አባባል አለ። ይህንን አባባል በቀላሉ ችላ ልንለው አይገባም። ምክንያቱም ሰው (ሃይዲገር እንደሚለው) የትናንት ውጤት ብቻ ሳይሆን የነገም እቅድ ነውና። በርግጥ ይህ የነገ እቅድነት በአንድ ግለሰብ ሕይወት ወይም እድሜ ብቻ የሚያከትም መሆን የለበትም። የቀጣይ ትውልዶችን መጻኢ እጣፈንታ፣ የዛሬ ትውልድ በበጎ ወይም በመጥፎ ሊወስንባቸው የሚችላቸው መንገዶች አያሌ ናቸው። ከያዝነው ርእሰ ጉዳይ አንጻር እንዲያውም በተለያዩ የተግባቦት መንገዶች የምንገነባው ማኅበረሰብ የነገን ትውልድ ታሳቢ ያደረገ ስለሚሆን። ከያንዳንዳችን ውስጥ ያልተወለደ ልጅ አለና ተግባቦታችንም ቀጣዩን ትውልድ መሠረት ያደረገ እንደሚሆን እናስባለን። በተግባቦት ላይ የምናጎለብተው ሥነ ምግባራዊ በጎነትም ለመጭው ትውልድ ምቹ የጋራ እሴትን መገንባት ላይ ያለመ መሆን ይኖርበታል። ከዚህ አኳያ ሲታይ አገራዊ አንድነት ማዕከላዊውን ስፍራ ይይዛል። ለመነሻ የሚሆን ግንዛቤ ጨብጠናል በሚል እምነት የነፍስን ሐተታ እዚህ ላይ እንግታውና የጋራ ዘለዓላማዊነትን ለማረጋገጥ የዘመናችን መገናኛ ብዙኃን ተግባቦት ምን ይመስላል? ወደሚለው እንቀጥል።

 ፭. የውይይትና ክርክር ባህል

ማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ታዲያ የጋራ አንድነትን ለማረጋገጥ ምን አተረፈልን? ከመገናኛ ብዙኃን የሚጠበቀው አንዱና ዋናው ቁም ነገር የውይይት፣ የክርክርና የሙግት ባህልን ማፋፋት መቻሉ ላይ ነው። የውይይት ሂደት ውስጥ ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ይኖራሉ። አንደኛው በርካታ አካላት ተሰብስበው በአንድ የጋራ ጉዳይ ላይ በመወያየት የጋራ አቋም ለመያዝ የሚደረግ የሐሳብ መዋጮ ነው። እዚህ ላይ ከተወያዮቹ የሚጠበቀው የግል ጉዳያቸውን ከማስቀደም ይልቅ ለጋራ ዘላቂ ደህንነት ሲባል ትልቁ አንድነት ላይ ማተኮር ይኖርባቸዋል። ይህም ሲባል የራስን ፍላጎት መስዋዕት ማድረግ ሳይሆን በጋራ የምንገነባው ማኅበራዊ እሴት ለሁሉም ጠቃሚ ይሆናል ከሚል አንጻር ነው። ተቃርኖዎችን እየፈቱ አንብሮዎችን እያጸኑ የሚደረግ የማስተጻመር ሂደት ነው ውይይት። እንደ ሃበርማስ (J. Habermas) ያሉ ፈላስፎች ለተሳካ የውይይት ሂደት ሁነኛ መፍትሄ ሁሉም ተወያዮች ሃይማኖት፣ ባህል፣ የፖለቲካ ርእዮተ ዓለምና ተፈጥሯዊ ማንነታቸውን ጭምር በመሻገር (ባጭር ቋንቋ የማንነት ዘባተሏቸውን አውልቀው ጥለው) የሚያደርጉት “postmetaphysical discourse” ነው ይለናል። ይህም ወደ Cosmopolitanism የሚደረግ ሽግግር ነው። ይህ ለኛ ማኅበረሰብ የሚመከር አይመስልም። ሐሳቡ ግን እንዲሁ በዋዛ ችላ የሚባል አይደለም።

በሌላ በኩል ደግሞ ራውል (John Rawls) “A Theory of Justice” በተሰኘ ድንቅ መጽሐፉ አንድ ፍትሃዊ ተቋማት ያሉት የፖለቲካ ማኅበረሰብ ግንባታ ሂደት በምክንያታዊ ሰዎች መካከል ስለግል ጥቅማቸው ሳይጨነቁ የራሳቸውን ጥቅም ከመጋረጃ ጀርባ ትተው ስለ ሰው ልጆች አጠቃላይ ስነልቡናዊ፣ ተፈጥሯዊ ፍላጎትና ስለኢኮኖሚያዊ መርሆዎች እውቀት ባላቸው አካላት መካከል የሚደረግ ምክንያታዊ ውይይትና የውል ስምምነት አማካኝ ነው ይለናል። ስለዚህ የእያንዳንዳቸው ሐሳብ የሰውን ልጆች አጠቃላይ ፍላጎት መሠረት ያደረገ እንጅ “በመጻኢው ማኅበረሰብ ቦታ ምን ድርሻ ይኖረኛል?” በሚል የግል ፍላጎት አኮፈዳቸውን ያነገቡበት አይደለም ማለት ነው። በዚህ ውይይት ሂደት ውስጥ የሚፈጠረው የጋራ ፖለቲካ ኢኮኖሚያዊ ማኅበረሰብ የሚመራባቸው ሁለት የፍትህ መርሆዎችን ይፈጥራል። አንደኛው ሁሉም የሰው ልጆች “በአርአያ ሥላሴ” አምሳል የተፈጠሩ የማይጣሱ ተፈጥሮአዊ መብቶችን የተጎናጸፉ ክቡራን እንደሆኑ የሚያስረግጥ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የአባላቱን የሃብትና የንብረት፣ የኢኮኖሚ እኩል ተጠቃሚነት ፍላጎት በእኩልነት የሚያስተናግድ ሲሆን ልዩነት እንኳን ቢፈጠር ቀድመው የተበደሉትን ለመካስ ስለሁሉም ረብ (ጥቅም) የሚደረግ ምክንያታዊ አድልዎ ነው ይለናል። ይኸው የ20ኛው ክፍለዘመን እውቅ ፈላስፋ “Political Liberalism” በተሰኘው ሌላኛው መጽሐፉ መግቢያ ላይ የማይታረቁ የሃይማኖት፣ የባህል፣ የፖለቲካና የሞራሊቲ ልዩነቶችና ተቃርኖዎች ሲያጋሙ ደግሞ ለጀምዓው (ለህብረቱ) ዘላቂነትና ደህንነት ሲባል ሁሉም የሰው ልጆች ምክንያታዊ መስተጋብርና የአስተሳሰብ አውዳዊ የባህል ልዩነቶች እንሆኑ በማመን “እውነት ከኛ ዘንድ ብቻ ነች” የሚለውን እብሪት መሻገር እንዳለብን ያሳስባል።

ክርክር ደግሞ ከዚህ ይለያል። ይኸኛው ሙግት ነው። በሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ አቋሞች መካከል የሚደረግ “እውነት ከየት ዘንድ ነች” የሚለውን ለማስረገጥ የሚደረግ ፉክክር ነው። በፍርድ ቤቶች በሕግ ፊት የሚደረገውን ክርክር ለአሁኑ እናቆየውና በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ስለሚደረገው ዳኛ አልባ እሰጥ አገባ እንለፍ። ከዚያ በፊት ግን ስለ ክርክር መርሆዎች ትንሽ እንበል። የስነ አመክንዮ (Logic) ምሁራን በሁለት ተከራካሪ ወገኖች መካከል ስለሚደረግ ፍልስፍናዊ ሙግት ብዙ መላምት ያስቀምጣሉ። አብዛኞቻችን የሚወክል አንድ ባለሙያ እንጥቀስ። Edward T. Damer የተሰኘ የሥነ አመክንዮ መምህር በዚህ መጽሐፉ (“Attacking Faulty Reasoning: A Practical Guide to Fallacy Free Arguments”, Wadsworth Publishing Company, Belmont 1995, PP. 5-11) በመጀመሪያው ምዕራፍ አንድ አከራካሪ ሐሳብ በሚደረግ ሙግት ውስጥ የተከራካሪዎቹ ሙግት (Argument) ይዘት ምን መምሰል እንዳለበት፣ ተከራካሪዎቹ ምን ዓይነት ምሁራዊ ሥነ ምግባር መላበስ እንዳለባቸው፣ የክርክር ዓላማ ምን እንደሆነ ያስረዳል። ከተጠቀሱት 12 ያክል መርሆዎች አንድ ሙግት በበቂ ማስረጃ ላይ የተመሰረተ፣ ትክክለኛ ሥነ-አመክንዮታዊ ሂደትን የተከተለ፣ በትክክለኛና ርእሰ ጉዳዩን በቀጥታ የሚመለከቱ ማስረጃዎችን ያካተተ፣ ማንኛውንም የተቃውሞ ሐሳብ ሊቋቋም የሚችል መሆን አለበት።

 ተከራካሪዎቹ ደግሞ ምሁራዊ ቀናነትና ቀጥተኝነት (Intellectual Honesty)፣ እውነትን ለመሻት ሁሉም ከፊል እውነት (በክርክር ሂደት ውስጥ ነጥሮ የወጣው ሃሳብ እንደሚያሸንፍ የሚያምኑ፣ እነርሱም ጋ ስህተት ሊኖር እንደሚችል ያልዘነጉ) እንደያዙ የሚያምኑ፣ የተከራካሪን ሃሳብ ሳ ይ ሸ ራ ር ፉ ና ሳ ያ ጣ ም ሙ የ ሚ ተ ረ ጉ ሙ ፣ ለያዙት አቋም ማስረጃ ማቅረብና የ ማ ብ ራ ራ ት ኃላፊነት የሚሰማቸው መሆን እንዳለባቸው ያትታል። በዚህ የሙግትና የተሟጋቾች ስብዕና አማካኝነት ያለፈ ሙግት ግልጽ ሆኖ የሚታይ ሚዛን የሚደፋ ሙግት የያዘው ሐሳብ ተቀባይነት ሲኖረው ምናልባትም ሁለት ወይም ከዚያ በላይ አቋሞች ተመሳሳይ ክብደት ካላቸው ውሳኔን በይደር ማቆየት (Suspension of Judgement) እንደሚኖርበት ያብራራል። እንግዲህ ክርክርና ውይይት በዚህ መንገድ አልፎ ነው የአንድን ሐሳብ እውነትነት ወይም ተግባራዊ ተቀባይነት የምናጸድቀው።

 ከፍ ብሎ የተቀመጠው ሐተታ የመገናኛ ብዙኃንን ለመገምገም የምንጠቀምበት ንድፈ ሐሳብ ነው። እነዚህ የክርክርና የውይይት መርሆዎች ለዘመናችን የመገናኘ ብዙኃን የመረጃ ጎርፍ ዓይነተኛ መሣሪያዎች እንደሚሆኑና የመገናኛ ብዙኃን ዓላማም መልካም ተግባቦትን ለመፍጠር ጤናማ የክርክርና ውይይት ባህልን ማምጣት እንዳለበት ለማሳየት ነው።

 ከዚህ በመነሳት የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ጸጋዎችና ሳንካዎች ምን ይመስላሉ?

 ከጸጋዎቹ እንጀምር። ፌስቡክ በኢትዮጵያ አያሌ ጸጋዎችን ይዞ ብቅ ብሎ ነበር። በኔው ትዝብት በግርድፉ ሲዳሰስ ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው:-

 አንደኛ:- የማይተዋወቁትን በማስተዋወቅ ከመልካም ልደት ምኞት እስከ ፌስቡክ አማጭ ሆኖ ያጋባቸውን የትዳር ጓደኛሞች ማግኘት ይቻላል። በማኅበራዊ ፋይዳው ብዙ ሊግባቡ የሚችሉ ሳይተዋወቁ ሊቀሩ የነበሩ ልቡናዎችንና መንፈሶችን ማቀራረብ ችሏል ማለት ይቻላል። “ጎርፍ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው” እንዲሉ፣ ዋዛን ከቁም ነገር እያስተባበረ ብዙሃንን በማዝናናትና በማጽናናት “ወደማይቀርበት የፌስቡክ ቤተሰብነት” ዘው ብለው እንዲገቡ አድርጓል። ብዙዎቻችንን በሳቅ ፍርስ የሚያደርጉ ቁም ነገር አዘል ቀልዶች እና ትችት አዘል አሽሙሮች የዚህ ማኅበራዊ ጥቅሙ መገለጫዎች ናቸው።

ሁለተኛ:- በርካታ ጀማሪ ጸሐፍያን ያላቸውን ተውህቦ (Talent) የሚገልጹበት የተጠረገ ሜዳ ሆኖ አገልግሏል። በዚህ በኩል ውዳሴ ከንቱ ያጠቃቸው ቢኖሩም በመልካም ገንቢ ትችቶች አማካኝነት ራሳቸውን እያረሙ ወደ ትልቅ ጸሐፊነት መሸጋገር የቻሉ በርካታ እንደሆኑ መታዘብ ቀላል ነው። ለዚህም ከፌስቡክ መንደር ያየናቸው “ቁርጥራጭ” ሃሳቦች በመጽሐፍ መልክ ግዝፍ ነስተው ገበያው ላይ መከሰት ችለዋል።

ሦስተኛ:– በመረጃ ፍሰት ረገድ በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ብቻ ተቀንብቦ የሚቀርብልንን የመረጃ መቁንን በማስናቅ ሁሉም በያለበት ያየውንና የሰማውን ዓይንና ጆሮ በመሆን “ለሁሉም” በማጋራት የበኩሉን ሲወጣ ነበር ማለት ይቻላል። የአገራችንን ጓዳ ጎድጓዳ ገመናዎች ከነ ግድፈቱም ቢሆን እንደወረደ ማየት ያስቻለን ይኸው ፌስቡክ ነው። ገና ከምጣዳቸው ያልወረዱ ትኩስ የመረጃ (የማስረጃ አላልሁም) ጋጋታን በላይ በላዩ እየለቀቁ አስኮምኩሞናል።

 አራተኛ:- አስተምህሮዎች (የሳይንስ፣ የፍልስፍና፣ የሃይማኖት)፣ የመጻሕፍት ትችቶች፣ ዳሰሳዎችና ጥቆማዎች፣ ለጥንቃቄ የሚረዱ መጠቁሞች (የእሳት አደጋ፣ በሽታ መከላከልና ህክምና፣ አመጋገብና ጤንነት)፣ ሙያዊ ማብራሪያዎች ወዘተ በማንሸራሸር እውነትን ለመግለጥ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል። በዚህ በኩል በሳል ባ ለ ሙ ያ ዎ ች በግል ገጻቸው ወይም በቡድን ገጾች አማካኝነት ትኩስ የቴክኖሎጂ ውጤት ወይም የሳይንስ ግኝቶችን፣ የተለያዩ ባህላዊ መልካም ተሞክሮዎችን፣ የጠፉ ወይም የተዘነጉ የታሪክ ሰነዶችን ወዘተ ለፌስቡክ ማኅበረሰቡ ያለ ስስት እንካችሁ እያሉን ይገኛሉ።

 አምስተኛ:- የመናገር ነጻነት ከምን ጊዜውም በላይ በታፈነበት በኛ ዘመንና ሀገር ሁሉም በስውር ስም ወይም በቀጥታ ማንነቱ፣ በስም ለበስ ቅኔ ወይም በግልጽ እንዲተች፣ ስሜቱን እንዲገልጽ እድል ሰጥቶታል። ይህም ነጻ ሚድያ በሌለበት አህጉር ታላላቅ ገዥ መንፈሶችን የሚተቹ፣ ጨቋኝ አስተሳሰቦችን የሚሞግቱ በሳል ጸሐፍያን የማኅበረ ፖለቲካዊ ተቃርኗችንን እርቃኑን ማስቀረት ችለው ነበር። በፌስ ቡክ ያነበብናቸው መላምቶች መሬት ወርደው ሲተገበሩ አይተናል። የዓረብን አብዮት ያስከተለው የማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ንቅናቄ የኛዋን ሀገርም ዳብሷታል፣ እየዳበሳትም ነው። በተለይ በትችት ረገድ ፌስቡክ ያደረገው አስተዋጽኦ ምንም ነው የሚባል አይደለም። የሰውነትን ክብር የሚጋፉትን አምባገነናዊ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች በመተቸት ረገድ ያሰማው የነበረው ጩኸት ብዙ ግንቦችን ማፈራረስ ችሏል፤ ጨቋኝ ጠንካራ ክንዶችንም ተፈታትኗል (አሽመድምዷል ለማለት ካልደፈርን)።

 ስድስተኛ:- የመወያያ ሐሳቦችን ለሙግት በማቅረብ ረገድ ታላላቅ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ሳይቀሩ የሕዝቡን አስተያየት በመሰብሰብ አማራጭ ሐሳቦችን ማግኘት አስችሏል። ለዚህም የተቋሞቹንና የመርሃግብሮችን አማራጭ የፌስቡክ ገጾች እንደ አማራጭ መንገዶች ይታያሉ። አንዳንድ ተቋሞች ደግሞ ምርታቸውን ለማስተዋወቅ፣ የሥራ ወይም ሌላ ማስታወቂያ ለተጠቃሚው በአጭር ጊዜ ለማድረስ ፌስቡክን እንደሁነኛ አጋራቸው እየተጠቀሙበት ነው።

 ሰባተኛ:- የመንግሥት ፖሊሲዎችና ስትራተጂዎች ለህዝቡ ተደራሽ በመሆን የህዝቡን የልብ ትርታ ማድመጥ የሚያስችል የመረጃ መረብ በመሆን አገልግሏል። ከታላላቅ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ስሞች (እውነተኛ ወይም የተውሶ ሊሆን ይችላል) እስከ ታላላቅ ተቋማት የተለያዩ ትኩስና ነባር መረጃዎችን ማግኛ መንገድ በመሆን ስለ ሀገር ጉዳይና የጋራ አጀንዳ መወያየት አስችሏል። አንዳንድ “ምሥጢሮች አፈትልከው በመውጣት” ወይም ሆን ተብሎ በመረጃ ሰዎች በመለቀቅ የህዝቡን የልብ ትርታ “ለመሰለል” እና ቀጣይ ፖሊሲዎችን ለማውጣት ወይም ስለ ህዝብ ደህንነት ሲባል (ሌላ መንግሥታዊ ምክንያትም ሊኖር ይችላል) የጥንቃቄ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችል ግብዓትን ማግኘት አስችሏል።

 ከላይ የተዘረዘሩት ጸጋዎች (ያልተዘረዘሩትም) “ሁሉም” ለማለት በሚቻል መልኩ በውስጠ ወይራ እኩይ የፌስቡክ ሳንካዎች የታጀቡ የማር ልውስ እሬቶችም አሉባቸው። ከነዚህ ጸጋዎች ጀርባ ያየናቸው ፍዳዎች ቢቆጠሩ ምናልባትም ምነው በቀረብን? ሊያስብል ይችላል። ለመሆኑ የዘመናችን ፌስቡክ ዋና ዋና ሳንካዎች ምን ምን ናቸው? በሚቀጥለው ክፍል ሰውን ወደሰውነት ክብሩ ከፍ እንዳይል አፍኖ በመያዝ “አቀንጨራ” የሆኑበትን የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ሳንካዎችና ዘባተሎዎች ለማየት የዚያው ሰው ይበለን።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top