ከቀንዱም ከሸሆናውም

አንዳንድ ጥቅሶች ከደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ሥራዎች

ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አስተዳደር ያስፈልጋታል?

መቼም ለውጥ የፍጥረት ህግ ስለሆነ ዛሬ ባይሆን ነገ ለውጥ ማምጣቱ አይቀርም። ጥያቄው #ለውጥ በሰላም? ወይስ ለውጥ በደም?; ስለሆነና ለውጥ በሰላም ሊሆን ሲችል ለውጥ በደም እስኪሆን መጠበቅ ሁሉን ከመጉዳት በቀር ማንንም ስለማይጠቅም ለውጥ በሰላም የሚሆንበትን መንገድ አሁን ጊዜው ሳያልፍ ማበጀት አስፈላጊ ነው። (ገጽ 1-11)

 በየትም ቢሆን ሁልጊዜ ባለም ታሪክ ሞልቶ የሚታየው አንድ ሕዝብ የሚኖርበት የፖለቲካ የኢኮኖሚክ እና የማኅበራዊ ኑሮ ሁኔታ ደስ የሚያሰኘው ሲሆንና እንዲያ ያለውን ሁኔታ የሚያሻሽልበት ሰላማዊ መንገድ የማይከፈትለት ሲሆን ከዚያ ከማይወደው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚክ እና የማኅበራዊ ኑሮ ሁኔታ በኃይል ሰብሮ ለመውጣት ሲነሳ በዚያ ምክንያት አገርን የሚያደኸይና የሚሳዝን የህይወትና የሀብት ጥፋት ሲደርስ፣ ከዚያ በኋላ የመጨረሻ ለውጥ ሲመጣ ነው። ነገር ግን ለዚያ ህዝብ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚክ እና የማኅበራዊ ኑሮው ስሜቱን እየተከተለ ወይም ከስሜቱ እየቀደመ የሚሻሻልበት ሰላማዊ መንገድ የተከፈተለት እንደሆነ ለውጡ ሽብር ሳይነሳ ህይወት እና ሀብት ሳይጠፋ የታሪክ እና የመልካም ባህልን መሠረት ሳይለቅ፣ በፀጥታ ሲፈፀም ይታያል። (ገፅ 2)

በኔ አስተያየት ዛሬ ለኢትዮጵያ በጣም የሚያስፈልገው ኢኮኖሚዋን አፋጥኖ አልምቶ በጠቅላላ የህዝቧን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል እና ያስተዳደርዋን ሆነ የፍር ሥራትዋን ለዘመናዊ ኑሮ እንዲስማማና ልማቱን እንዲረዳ ማድረግ ነው። እንጂ የምዕራብን ወይም የምሥራቅን የስተዳደር ሥራት እንዲሁ እንዳለ ተውሶ መልበስ ምሥራቅን ወይም ምዕራብን ሊያደርጋት አይችልም። ስለዚህ ያቀረብነው አሳብ ከምዕራብ እና ከምሥራቅ የመንግሥት ሥራቶች ለኢትዮጵያ ዘመናዊ አሥተዳደር እና ልማትዋን ለማፋጠን ይረዳሉ ተብሎ የሚታመንባቸው አሳቦች ተዋጥተው ያሉበት በእዚያ ላይ ከኢትዮጵያ ባህል እና ታሪክ ጋ የሚስማሙ አዳዲስ አሳቦች የተጨመሩበት ዓይነተኛ ዓላማው ባሥር ዓመት ውስጥ ኢትዮጵያ በፖለቲካ በኢኮኖሚክ እና በማኅበራዊ ኑሮ አሁን ካለችበት ዝቅተኛ ቦታ በኃይል ገፍቶ ወደፊት ሊያራምዳት ይችላል ብለን የምናምንበት ነው። (ገፅ 3-4 ) የመንግሥት ሥልጣን የሚመሠረተው በኮሎኔ ወይም በቀኝ አገር ነው። በቀኝ አገር ህዝቡ ድል ሲሆን ሕጋዊ መብቱንም ፈቃዱንም ከነፃነቱ ጋር አብሮ ስለሚቀማ ሕግም ፈቃድም ሁሉ ያው በኃይል የሚመሰረተው በወራሪው ፈቃድ ብቻ ነው። በነፃ አገር ግን ለመንግሥት ሥልጣን ህጋዊ መሠረቱ የጠቅላላው ህዝብ ፈቃድ ነው። (ገፅ 8-9)

 መንግሥት የህዝብ እንጂ ህዝብ የመንግሥት አለመሆኑ ጥርት ብሎ በማያጠራጥር ሁኔታ መታመን አለበት። ይህ በህዝብ እና በመንግሥት መሐከል ላለው ግንኙነት ሥር መሠረት ወይም ግንድ የሆነው ነገር ከታመነ ሌላው ሁሉ የሱ ዘርፍ እና ቅርንጫፍ ነው። (ገፅ 10-11)

አሰናጅ ፈቃደ አዘዘ

ለክቡር ዶክተር ሀዲስ አለማየሁ 90ኛ ዓመት የልደት በዓል ክብር በ1992 ዓም. ከተዘጋጀው የኢትዮጵያ የቋንቋዎች እና ሥነ-ፅሑፍ መጽሔት የተወሰደ።

 የአባይን ውሃ ስለመለካት

ይድረሥ ከክቡር ጸሐፌ ትዕዛዝ ወልደመስቀል የጽህፈት ሚኒስትር ጤና ይስጥልኝ እያልሁ ከማክበር ጋር ሰላምታ አቀርባለሁ።

 ሙሴ ቫርኖስኪ የአባይን ውሃ እየለካ በአሥራ አምሥት አሥራ አምሥት ቀን ቁጥሩን ወደዚህ እንዲልክ እዚያው ጣና ባህርዳር ተቀምጧል። ስንቄን ላኩልኝ ብሎ በዶክተር ጋብሪኤሎፍ በኩል ጽፎ ኖሮ ይህንኑ አልጋ ወራሽ ለጸሐፌ ትዕዛዝ ነግሬአለሁ ብሎ ነገሩኝ። አሁን መልዕክተኞቹ ደብዳቤውን ተቀብለው ተነስተዋል። ስንቁን ሳይዙበት የሄዱ እንደሆነ ሰውየው ተበሳጭቶ ሥራውን እንዳያበላሽ እና ስሙ በኛ ላይ እንዳይሆን የታዘዘለት ነገር እንዳለ አስበው እንዲያደርጉለት እና መልዕክተኞች በተሎ ይዘውለት እንዲሄዱ አስታውቅዎታለሁ።

 ለመልዕክተኞቹም የይለፍ ወረቀት በአገር ግዛት ሚኒስቴር እንዲያሰጧቸው አስታውቅዎታለሁ።

 ግንቦት 13 ቀን 1918 ዓም.

 አ.አ

 ከ ከቤተ-መንግሥት ዶሴ

የብላታ ወልደማሪያም መዘክር መጽሐፍ

 አሰናኝ፡- መኩሪያ መካሻ

 ለኢትዮጵያ ሥልጣኔ መሠረቱ እንደ ደሴት በሁለት ትልልቅ ወንዞች ተከባና ታጥራ የነበረችው ሜረዌ የምትባለው አገር ናት ይላሉ።

 የሜረዌ አገር ከጥንት ጀምሮ የተደላደለ መንግሥት እና የህዝብ አስተዳደር ህግ ነበረው። ስልጣኔን ግብፅ ለኢትዮጵያ ሰጠች ወይስ ኢትዮጵያ ናት ለግብፅ ያወረሰች? ብሎ ለመናገር የታሪክ ሊቃውንት ብዙ ክርክር አድርገው ሊስማሙበት አልቻሉም። ይሁን እንጂ ምንም እንኳን የማያከራክር ማስረጃ ገና ባይገኝለት ሥልጣኔን እና አምልኮን ለግብፅ የሰጠች ኢትዮጵያ መሆኗ ታምኗል።

 በጣም ሩቅ በሆነው በጥንታዊ ዘመን የቤተ- ክህነት ሰዎች ከሜረዌ ወደ ግብፅ ሄደው አገር እንዳቀኑ ሲወርድ ሲዋረድ በኖረ በአፋዊ ታሪክ ይነገራል።

ሴቶች ከወንዶች (ወታደሮች) ጋራ እየተሰለፉ በጦርነት ላይ ብዙ ጊዜ ሲዋጉ የታዩ በመሆናቸውና ለመንገሥም ይፈቀድላቸው ስለነበረ ይኸው ነገር በሜረዌ አገር ከተለመዱት የግል ሥራቶች እንደ አንዱ የተረጋገጠ ልዩ ባህርይ ሆኖ ተቆጥሯል። ስትራቦን የሚባለው ታሪክ ፀሐፊ ህንዳኬ የምትባል ጦረኛ የሆነች የኢትዮጵያ ንግሥት እንደነበረች ይናገራል።

ቀድሞ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ናፖታ ነበረች። በኋላ ግን መንግሥቱ ወደ ሜረዌ ተዛወረ። ከናፖታ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ዋና ከተማ ሜረዌ ሆነ።

 ከዓለም ታሪክ መጽሐፍ በከበደ ሚካኤል

 የብርሃንና ሰላም ጋዜጣ አጀማመር

 ልዑል አልጋ ወራሽ በግቢያቸው ውስጥ ላቆሙት የመጻህፍት ማተሚያ ቤት ዲሬክተር ያደረጉት አቶ ገብረክርስቶስ ተክለሃይማኖት ሥራውን ለማሥፋፋት እጅግ ይተጋ ነበር። በዚህም ዘመን ማተሚያ ቤቱ አንድ የሣምንት ጋዜጣ እያተመ ቢያወጣ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ መሆኑ በመግለፅ ለልዑል አልጋ ወራሽ ሐሳብ አቅርቦ እያስታወሰ ቆይቶ ነበረ እና ስለፈቀዱለት ሥራውን ለመጀመር ይሰናዳ ጀመር። በዚሁም ጊዜ ለጋዜጣው ጽሕፈት የአማርኛ ችሎታ ያለው አንድ ሰው ይታዘዝልኝ ብሎ ልዑል አልጋ ወራሽን ስለ ለመነ እኔን የእልፍኝ አሽከሩ ልጅ በልሁ ደገፉ አስጠርቶ የጋዜጣ ሥራ ጸሐፊ እንድትሆን ከልዑልነታቸው ታዘሃል ብሎ አስታወቀኝ። ቀጥሎም ወደ አቶ ገብረክርስቶስ ወስዶ አገጣጠመኝ እና ሥራውን ተረክቤ እሠራ ጀመር። የጋዜጣው ዋጋ በኢትዮጵያ ውስጥ በዓመት አምስት ብር ሲሆን ለውጭ አገር ግን በዓመት ሰባት ብር ሆኖ ተወሰነ። ከዚህ ጊዜ በኋላ የጋዜጣው ስም ምን ተብሎ እንደሚሰየም እና በምን ቀን መውጣት እንደሚገባው የሥራውንም አጀማመር በማጥናትና ሐሳብ በማቅረብ ሦስት ሳምን ያህል አለፈ። በመጨረሻም ልዑል አልጋ ወራሽ ጋዜጣውን “ብርሃንና ሰላም” ብለው ሰየሙትና የመጀመሪያው ጋዜጣ ታኅሣሥ 23 ቀን 1917 ዓም. ኃሙስ በአራት ገጽ ታትሞ ወጣ።

 “በመጀመሪያው ቁጥር ጋዜጣ ዲሬክተሩ አቶ ገብረክርስቶስ ስለ ብርሃንና ስለ ሰላም ሐተታ በመሥጠት ጽፏል።” ይላሉ። መርስኤ ኃዘን ወልደቂርቆስ አምኃ መርስኤ ኃዘን በአዘጋጁት “ትዝታዬ ስለራሴ በማስታውሰው” በሚለው መጽሐፍ ሐተታ ካሉት ጥቂቱን እነሆ፤

 ብርሃን የጨለማ ተቃራኒ ነው።

ሰላምም ደግሞ የጠብን ተቃራኒ ነው።

ብርሃን በሌለበት ጨለማ ይሰለጥናል።

ሰላም በሌለበትም ጠብ እና ሁከትጦርነት ይሰለጥናል።

 የፀሐይ ብርሃን ለሰው እና ለእንስሳ፣ ለተክል ህይወት ሊሆን የሚያስፈልግ ነገር ነው።

 የሌሊቱ ጨለማ ማለዳ ፀሐይ ስትወጣ ይርቃል።

 ፀብ እና ሁከትም ሰላም ሲመጣ ይጠፋል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top