ማዕደ ስንኝ

ስደት

ያንን ተራራማ ወጣሁት፤ ቋጥኙን ቧጥጬ፤

ክምር ስቤን አቅልጬ።

ያንን ዳገትማ ተሻገርኩ፤ መቶ ምናምን ግዜ ወድቄ፤

የተስፋ ስንቄን አንቄ።

ያንን ንዳድ በረሃማ ዘለቅኩት፤ ጉልበቴን በፅኑ ፍቅር መንዝሬ፤

አንድ ሺህ ሌትር ላቤን፤ በአንድ ሺህ ሊትር ሃሞት ቀይሬ።

ያንን ድቅድቅ ጨለማማ አለፍኩት፤ መደነቃቀፍን ችዬ፤

የንጋቱን ጮራ ሳላይ፤ ፍፁም ልዝልም፤ ፍፁም አላርፍም ብዬ።

አይነጠሉኝ እንጂ ፤ በጀርባዬ ያዘልኳቸው፣

‐ በክንዴ የታቀፍኳቸው፣

ያንን ባህርማ አልፈዋለሁ፤ ራሴን ቁልቁል ደፍቄ፤

‐ ሁላችንንም ደብቄ።

ያ ውቂያኖስም አያቅተኝ፤ ከአድማስ የተጣቀሰው፣

የሰማይ ክፋይ መስሎ በሰፊው የብስ የተንጣለለው ።

ማዕበሉ እጅግ ከፍቶ ቢያናውጠኝ ሞገዱ፣

አይጠፋኝም ያ መድረሻ፤ አይርቀኝም ያ መንገዱ፤

ውስጥ ለውስጥ አሰርጋለሁ ትንፋሼን አምቄ

‐የተስፋ ስንቄን አንቄ።

ሆዴ ከጀርባዬ የተጣበቀ ቢመስልም፤ ወደ ውስጥ የጎደጎደ፣

የማይችል የሚመስለው ጫንቃዬ በላብ ጅረት የተናደ፣

ስለ እነሱ የጠጠረ ባት አለኝ፤ የደደረ ትከሻ፣

እምቅ ጉልበት አለኝ፤ ካሰብኩት ፅንፍ ማድረሻ ።

ደረጀ ትዕዛዙ

ሰኔ 27/2010 ዓ.ም

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top