ፍልስፍና

ለመሆኑ “የአፍሪካ ፍልስፍና” ከወዴት ነው

(ክፍል አንድ)

ምን ዓይነት ጥያቄ ነው? የአፍሪካ ፍልስፍና ከማለት በፊት ለመሆኑ አፍሪካ ማን ናት? አፍካውያንን አንድ የሚያደርጋቸው ማንነትስ አለ ወይ (ከጥቁረታቸው ውጭአሃ! ሁሉም ጥቁሮችስ አፍሪካውያን ናቸው እንዴ? ወይም ሁሉም አፍሪካውያን ጥቁሮች ናቸው ወይ?) ለመሆኑስ ፍልስፍና ዘር ወይም ነገድ አለው እንዴየአፍሪካ ፍልስፍናወይም የእከሌ ፍልስፍና ተብሎ የሚፈረጀው? ለፍልስፍናስ ድንበር ማበጀት ይቻላል ወይ?የአፍሪካ ፍልስፍና የሚባል ነገር ካለስ ከወዴት ነው? ለአፍሪካውያን ብሎም ለዓለም ህዝብ የሚኖረው ተግባራዊ ፋይዳስ ምንድን ነው?” የሚሉ የጥያቄ መዓት ማጉረፍ ይቻላል። በእዚህ ጽሑፍ አንዱ ዓላማም የጥያቄ መዓት በማጉረፍ ወደ እውቀት የሚደረገውን የሰው ልጆች ጉዞ ማገዝ፣ መደጎም፣ የብርሃኑን ችቦ መለኮስ ነው። ለዛሬ መተንኮሻ ይሆን ዘንድ ይኸው የአፍሪካ ፍልስፍናን ጉዳይ አነሳሁ። ይህ ጽሁፍ በአፍሪካ ፍልስፍና ዘርፍ ጥናት ያደረገ የባለሙያ ሐተታ አይደለም። ይልቁን ከግል ንባብ የተገኘ የግል ትዝብትና እስኪ ለዛሬ በዚህ ጉዳይ እንነጋገር? የሚል የጥሪ ግብዣ ነው፤ በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ትንታኔ የሚሰጡንን ለመጋበዝየሐሳብ መዋጮ እቁብ ማኅበርተኞችን ለመጥራት።

አውሮፓውያን ፈላስፎች ስለአፍሪካውያን እንዲህ ብለው ያስቡ ነበር አሉ። ኧረ ጽፈውትም አንብበናዋል፣ ሐሳባቸውም ሥጋን ተዋሕዶ መሬት ወርዶ አይተነዋል። “የሰው ልጅ ምክንያታዊ እንስሳ ነው። ይህ ምክንያታዊ እንስሳም የማሰብ ተሰጥኦውን በመጠቀም ኑሮውን ለማሻሻል ባደረጋቸው የሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ አሁን ያለበት የእድገት ደረጃ ላይ ሊደርስ ችሏል። በእርግጥ በዚያ በባህር ማዶው ጫካ ውስጥ የሚሽሎኮሎኩ ሰው መሰል ፍጡሮች አሉ። እነዚያ ምክንያታውያን ሳይሆኑ በስሜት ብቻ የሚመሩ ወደሰውነት ክብር ከፍ ያላሉ ለዓለም የሥልጣኔ ጉዞ ምንም አስተዋጽኦ ያላደረጉ ፍጡሮች ናቸው።” ታላላቆቹ አሳቢዎች ሳይቀሩ ይህንን ሃሳብ ተናግረውት አልፈዋል። (ሄግል፣ ካንት፣ ሂዩም እናም ሌሎች)። የግሪኩ ፈላስፋ አሪስቶትል ሰዎች ሁሉ ምክንያታዊ እንስሳት ናቸው፤ ፖለቲካዊም ጭምር ናቸው ሲል ከዘመነ ዘመናት በፊት ተናግሯል። ይህ አገላለጽ ጥቁሮቹን የሚመለከት አይደለም (ህንዳውያንንም ጭምር) የሚሉ ፈላስፎችና የታሪክ ጸሐፊዎች ቁጥራቸው የሚናቅ አይደለም። ሰዎች ሁሉ ምክንያታውያን ናቸው ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲካዊ እንስሳት ናቸው ማለትስ? ይህንን በቦታው በሰፊው እናየዋለን።

 ይህ ቃላዊ ዲስኩር በተለያዩ መንገዶች ወደ አፍሪካ ምድር መጣ። ቀደምቶቹ አሜሪካ የተባለች የዘመናችንን “ታላቅ” መንግሥት ሲመሰርቱ ከወባና የተለያዩ የጫካ በሽታዎችና  ፈተናዎች ጋር ታግለው ጥጥና ሌሎች የግብርና ምርቶችን ያመርቱላቸው ዘንድ ባርያዎችን ከምዕራብ አፍሪካ ያግዙ ነበር። ይህም በታሪክ መዝገብ ውስጥ “የባርያ ንግድ” በመባል የሚታወቀው ነው። ቀጣዮቹ የሰውን ልጅ ለሰማያዊ ጸጋ የሚያበቁ “ሃይማኖተኞች” ናቸው። “እናንተ አፍሪካውያን ሆይ፣ ይህ ያረጀ ያፈጀ አገር በቀል እምነታችሁ እኮ ሰማያዊውን መንግሥት አያወርስም። ይልቅ እኛ ይዘንላችሁ የመጣነውን አዲሱን ወንጌል ተቀበሉና ከክርስቶስ ጋር አንድ ሁኑ” አሏቸው። እምነት ነውና ይዘው የመጡት ምስኪኖቹ አፍሪካውያን አመኗቸው። ደሃርተኞቹ የፖለቲካ መሪዎች አውሮፓውያንም እኒህ አሳሾችና የሃይማኖት ሰዎቻቸው በቀደዱላቸው ቦይ ከች አሉ። አዛኝ ቅቤ አንጓቾቹም “አፍሪካውያን ሆይ እንዴት ይህንን ለምለም መሬትና ሃብታም የተፈጥሮ መዓድን ይዛችሁ እስከዛሬ በድህነት፣ በችጋር፣ በበሽታ ትማቅቃላችሁ? አልሰማችሁም እንዴ? በዚያ በሌላው ዓለም የሰው ልጅ የትና የት እንደደረሰ? ይኸውና ችግራችሁ ቢያሳስበን እኛ ልናለማችሁ መጥተናልና የመልካም ዓላማችን ተቋዳሽ ሁኑ። የምን በችግር መጨማደድ ነው?” አሏቸው። ይህም ፍጹም የማስመሰል ቃል እንጅ ከሐዘኔታ የመጣ አልነበረም።

የሃይማኖት ስብከት ሽፋን የመንፈስ ልጅ የሆነውን አፍሪካንን የመቀራመት እቅድ በበርሊን ተመከረበት። “የልማት አብሳሪዎቹም” ጦርና መጽሐፍ ቅዱስን ተሸክመው ዘመቱ፤ “ያመነውን በመጽሐፍ ያመጸውን በሰይፍ” ነውና ነገሩ አፍሪካ በአዳዲስ ዜጎች ተጥለቀለቀች። የደቡብ አፍሪካው መነኩሴ (ዴዝሞንድ ቱቱ?) እንዲህ ብለዋል ይባላል። “አውሮፓውያን መጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው እናምን ዘንድ ሰበኩን። እንዴት መጸለይና መስገድ እንዳለብንም አስተማሩን። እኛም አመንናቸውና ለመጸለይ አይናችንን ጨፍነን ራሳችንን ዝቅ አድርገን ለጌታ ተንበረከክን። ከአጎነበስንበት ቀና ስንል ግን መጽሐፍ ቅዱስን በእጃችን ያባቶቻችንን ርስት ደግሞ በእጃቸው አገኘነው።” (ቃል በቃል አይደለም) ይዘቱ ግን ይኸው ነው። ሰማያዊውን ትፍስኅት አስጎምጅተውን ምድራዊውን ንብረታችንን ቀሙን ማለታቸው ነው ሽማግሌው።

 እናም የቅኝ ግዛት ፍዳ የአፍሪካን ምድር አጥለቀለቃት። “ምክንያታዊ ነን” ባዮቹ አውሮፓውያን አፍሪካን ያለ ምክንያት ከፋፈሏት። እነሆም በምድራቸው ላይ መስመር አበጁበት። ብዙዎቹ አፍሪካውያንም የራሳቸውን ባህል፣ እውቀት፣ ሃይማኖት፣ ማንነትና ትውፊት እንዲጠየፉ ተሰበኩ። ስለዚህ ጉዳይ ችንዋ አቸቤ በዚያ “Things Fall Appart” በተሰኘ ድንቅ ልቦለድ መፃፉ የአውሮፓውያንን የመጀመሪያ ስብከትና ተከታይ የግብር ተቃርኖዎችን አበጥሮ ያስነብበናል። እንዲያውም በአንድ ቦታ ላይ በመሬት ምክንያት የተነሳን ክርክር አንድ አውሮፓዊ ዳኛ ጉቦ ተቀብሎ ኢ-ፍትሐዊ ፍርድ በመስጠቱ የተደመመው ኦኮንክዎ የተባለው ገጸ ባህርይ “ለመሆኑ ይህ ነጭ እኛ ስለመሬታችን ያለንን ዋጋ ያውቀዋልን?” ሲል ይጠይቃል።

አያይዞም “እንዴት ቋንቋችንን እንኳ ሳያውቅ በኛ ላይ ዳኛ ሆነ? የኛን ባህል አይረባም ብሎ ያጣጥላል?” “ይህ ነጭ ብልጥ ነው። መጀመሪያ በዝምታና በሰላም ሃይማኖቱን ይዞ መጣ። እኛም በሞኝነቱ ተደንቀን እንዲቆይ ፈቀድንለት። አሁን [በስብከቱ] የኛን ሰዎችም ሳይቀር ልብ አሸፈተ። ከእኛ ውስጥ እንደሱ ብልጥ የሚሆን ጠፋ። በመጨረሻም He has put a knife on the things that held us together and we have fallen apart.”

መዝሙረኛው ዳዊት “ኢየሩሳሌም ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ” እንዳለ፣ ያገሬ ሰው “እትብቴ የተቀበረበት መሬት፣ ያገሬ አፈር ይብላኝ” እያለ የሚያንጎራጉረው፣ መሬቱ አፈሩ ከነፍስ ከስጋው የተዋሐደ መሆኑን ሲያስረግጥ ነው። አንድ The Oakland Institue የተሰኘ ድርጅት በ2011 እ.አ.አ በሰራው ጥናት ላይ በጋምቤላ አካባቢ ስለሚደረገው “ኢንቨስትመንት ለበስ” የመሬት ቅርምት (Land Grabbing in the Name of Investment) ያገሬውን ሰዎች ስለ ሁኔታው ሲጠይቃቸው [ቅዝዝ ብለው፣ ከከሲታ ፊታቸው ላይ የንስር ዓይኖቻቸውን ወደ ጫካው አተኩረው እየተመለከቱ] “ይኸ ጫካ እኮ ዝም ብሎ ጫካ አይደለም። የአባቶቻችን መንፈስ የረበበበት የህልውናችን ምስጢር የተቋጠረበት ቅዱስና ክቡር ቦታ ነው። እንዴት ልብ ያለው ሰው በቡልዶዘር ደብዛውን ያጠፋዋል?” ሲሉ በምሬት እንደመለሱለት አንብብቤያለሁ።

 “Any villager, even though they are doing shifting cultivation, cannot come to the territory without proper consultation with the village. It is not just a forest, it is demarcated, they know historically who it belongs to. So land is not only economical, it is historical, political, spiritual and very emotional.”

የናይጄሪያውና የጋምቤላው አኝዋክ (የስም አጠራሬ ላይ ስህተት ካለ ካለማወቅ ነው) አባት ስለመሬት አንድ ዓይነት የሃሳብ ድር ላይ ይገኛሉ። እዚህ ላይ ይህንን ጉዳይ ማንሳቴ አፍሪካውያን ስለ ተፈጥሮ ያላቸውን ፍልስፍና፣ ለተፈጥሮ ያላቸውን ቀረቤታ በፍልስፍናቸው ላይ እንዴት እንደሚንጸባረቅ ለመጠቆም ነው። ታች (በቀጣዩ ክፍል) በሰፊው እናየዋለን። እንዲሁ በአልፎሂያጅ አነሳሁት እንጅ ይህ የመሬት ቅርምት ጉዳይ ትልቅ ጥናትና ፍልስፍናዊ ትችት የሚያስፈልገው ርእሰ ጉዳይ ነው። እድሉ ሲገኝ እንመለስበት ይሆናል።

ይህንን የአፍሪካውያንን ለመሬት ያላቸውን ባህል ችላ ያለው አውሮፓዊ ቀኝ ገዥ ነው ያባቶቻቸውን ርስት “ተጨፈኑ ላሞኛችሁ” በሚል ፈሊጥ ከእጃቸው ፈልቅቆ የወሰደው። የቀኝ ግዛቱን የባህል ወረራና የማንነት ድፍጠጣ የኔዋ አጭር ጽሑፍ በምልዓት ልትዘግበው የምትችል አይመስለኝም። ይልቁን ንጉጊ ዋ ቲዮንግ የተባለ ኬንያዊ ጸሐፊ ያስቀመጣትን ትዝብት መጥቀሱ ነገሩን ባይሰበስበው እንኳን በነጭ ጋቢ ላይ ያለች ጥቁር ጠብታን ያክል ያገዝፈው ይሆናል። ተቀራራቢ ትርጉሙ ይኸውና:- “እንግሊዛዊው ያደረገብን ነገር ምንድን ነው? ትንንሽ ልጆች እያለን ትምህርት ቤት ስንማር በኬንያ ቋንቋ እንድንናገር አይፈቀድልንም ነበር። እንዲያውም በስህተት አንድ ልጅ እንግሊዝኛን ረስቶ በኬንያኛ ቋንቋ ቢናገር በቆርቆሮ ላይ የተጻፈ “እኔ ደደብ ነኝ ወይም እኔ አህያ ነኝ” የሚል ጽሑፍ ከጀርባው [በሱቅ በደረቴ አምሳል] አንግቶ/ አዝሎ እንዲውል ይደረግ ነበር። ያች እዝል የምትወርድለት ሌላ “አህያ” ሲገኝ ነው። ይችን እዝል ለመገላገል ታዲያ መምህራኑ ተረኛውን “ስህተተኛ” ፈልገው ማግኘት አይጠበቅባቸውም። ራሳችን እንጠቋቆም ነበርና [እኛ በትምህርት ቤታችን መሃረቤን ያያችሁ? እንደምንጫወተው “አህያዬን ያያችሁ?” መሆኑ ነው]።” በማለት ከገለጸው በኋላ ቀጣዮቹ ዓረፍተ ነገሮች ህሊናን ሰርስረው ልቡናን ሰብረው በመግባት የቅኝ ግዛትን አስከፊነት በዘለዓላማዊ ምስክርነት መክተብ ይችላሉ። እንዲህ ይላል “ባጭሩ የኬንያ ህጻናት ትምህርት ቤት ሲሆኑ በአውሮፓ ቋንቋ እንዲናገሩ፣ እንዲያስቡ ይገደዱ ነበር። ወደቤታቸው ሲሄዱ ደግሞ በኬንያ የሕይወት ዘይቤ ኑሯቸውን ይመራሉ። እናም የቀኝ ገዥ ትምህርት በኬንያ አካል የሌላቸው ኅሊናዎችን ሲፈጥር የኬንያ መንደር ኑሮ ደግሞ ኅሊናቢስ አካላትን ያፋፋ ነበር። On a larger social scale it is like producing a society of bodiless heads and headless bodies. ትምህርት ከራሳችን ማንነት እያሸሸ ወደ ሌላ ማንነት ይገፋን ነበር።”

 ከዚህ ላይ ምን ይታከልበታል? እንኳን ለአስርት ዓመታት የቆዩትንና ለ5 ዓመታት የነበሩት ጣልያኖች ኢትዮጵያን እንዴት እንዳደረጓት የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። ምንም ዓይነት ዘመናዊ ትምህርት በኢትዮጵያ እንዳይኖር ከመከልከላቸውም በላይ የተማረ ኢትዮጵያዊ እያሳደዱ ይገድሉ እንደነበ የነሰጣርጋቸው ቀናውና ራንዲ ባክሲቪክ ጥናት ያሳያል። የማንነት ጥፋቱ አሁንም ድረስ በቦታዎቻችን ስሞች ላይ ቅሪቱ ይታያል። እነ መርካቶ፣ ፒያሳ፣ ካዛንችስ ጣልያንኛ ናቸው የሚሉ አሉ። አካላዊ ግርፋቱ፣ ማንቋሸሹ፣ ውርደቱ ሁሉ ተቆጥሮ አያልቅም ነበር። የደብረ ሊባኖሱና የስድስት ኪሎው እልቂቶች የቅኝ ግዛት ሰቆቃዎች አሻራዎች ናቸው። አጼ ምኒልክ እንዳሉት ቀኝ ገዥ “ሃይማኖትንና ማንነትን የሚያጠፋ አገርን የሚወር መሬት የሚቆፍር ፍልፈል” ነበር። ይህ አካላዊና ስነልቡናዊ (መንፈሳዊ) የቀኝ ግዛትጭቆና ምሁራኑ ብዕራቸውን፣ ዓርበኞቹ ደግሞ ጦራቸውን እንዲያነሱ አስገደዳቸው። የነጻነት ፍላጎት ሰብዓዊ ነውና ጭቆና ያንገፈገፋቸው ብዕሮችና ክንዶች ከአፍሪካ ከብደ ምድር (ከአፍሪካው ማህጸን) ይወለዱ ጀመር። ከኢትዮጵያውያን አርበኞች ጎን ተሰልፈው በተባ ብዕራቸው የነጻነት ቅኔን ሲቀኙ ከነበሩት ልኂቃን መካከል እነ ዮፍታኄ ንጉሤን ማስታወስ ይቻላል። የወታደሮቹን ጉዳይ የታሪክ ሰዎች በደንብ ስለሚነግሩን ወደዚያ አንገባም። ይልቅ ስለ ፈላስፎቹ ትንሽ እንበልና የዘመናችንን የአፍሪካ ፍልስፍና ጥንተ ነገር (ምንጭ)፣ ከየት መጣነት እንፈልግ።

የቅርብ ዘመን ትውስታችን እንደሚነግረን ዘመናዊዎቹ ፈላስፎች ሳይቀሩ (ለምሳሌ:- እነ ብሩሁል ሃለን) የአፍሪካውያንን ተፈላሳፊ ኅሊና ሊቀበሉ አልቻሉም። በዚህ ላይ አብዛኞቹ አንድ ነገር ፍልስፍና ለመባል በግለሰቦች የማሰብ ተመስጦ የመጣ፣ ስነ አመክንዮአዊ ፍሰቱን የጠበቀ፣ እንዲሁም የተጻፈ መሆን አለበት።

በዚህ ስሌት ደግሞ አፍሪካውያን ከዚህ ግባ የሚባል (እንዲያውም ምንም) የፍልስፍና ንብረት የላቸውም። ስለዚህ አፍሪካውያን ፍልስፍና የላቸውም ወደሚል ድምዳሜ ደረሱ። ሌሎቹ ተከራካሪዎች ደግሞ “ምነውና የናንተ ታላላቅ ፈላስፎች እነ ሶቅራጥስ መቼ ብዕርና ወረቀት አገናኝተው አንዲት ሐረግ ጻፉና ነው ፈላስፎች የተባሉት? ደግሞስ ወደ ቀያችን ጎራ ብላችሁ ሽማግሌዎችን ብትጠይቁ ስንትና ስንት የነገረ ህልውና፣ የእውቀት፣ የሥነ-ምግባር፣ የሥነ-መለኮት፣ የፖለቲካ ወዘተ ፍልስፍና ባለቤት የሆኑ ጠቢባን ነፍ አይደለም ወይ?” ክርክሩ እየጠነከረ ሄደ። አንዳንዶቹ “ዘወር ብዬ ባየው ትካሻዬ ቀለለኝ” እንደሚባለው እውነትም የተጻፈ ነገር በአፍሪካውያን ጓዳ እንደሌለ ለማመን ተገደዱ። ለምሳሌ:- ኋላ ላይ በአፍሪካ ፍልስፍና ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገውና “የአፍሪካ ፍልስፍና አጋር” አርታኢ (Editor of A Blackwell Companion to African Philsophy) የሆነው ክዋሲ ዊረዱ የግል ተሞክሮውን እንዲህ ያስነብበናል። “በ1958 (እ.አ.አ) በፍልስፍና ስመረቅ እነዚያ በእውቀታቸውና በስነ ምግባራቸው የተመሰገኑ መምህራኖቼ ስለ አፍሪካ ፍልስፍና ምንም ነገር አያስተማሩኝም ነበር። በርግጥ አልወቅሳቸውም፤ እንዲያውም የአውሮፓን ፍልስፍና በደንብ ስላስተማሩኝ አመሰግናቸዋለሁ።” በማለት በግል ንባቡ መሠረት ከፈላስፎቹ ይልቅ አንትሮፖሎጂስቶቹ በተሻለ የአፍሪካን ፍልስፍናና አስተሳሰብ እንደከተቡልን ይነግረናል። ይህ የአፍሪካ ፍልስፍና ተጽፎ አለመገኘት ግን በአፍሪካ ምድር ፍልስፍና የለም ማለት እንዳልሆነ ብዙዎቹ ሞገቱ። በበኩሌ የሙግቱን አሳማኝነት ከሚቀበሉት ነኝ። ምክንያቱም ሐሳብ በጽሑፍ ብቻ መቅረብ አለበት፣ አስተሳሰብ በስነ አመክንዮብቻ ተሰድሮ መቅረቡ ሕይወትን በምልዓት ይገልጻላታል ማለት ስላልሆነ። እንዲያውም ስሜትም የሕይወት አካል ነች። በዚህ በኩል “የቅኔ ቋንጣ የለውም” በሚል ብሂል ታላላቆቻችን ጽፈው ስላላስቀሩልን በቃላቸው ነገረ መለኮትን ሳይቀር የሚተቹ በሳል ፍልስፍናዊ ቅኔዎችን አላጎረፉም ማለት አይደለም። (ለምሳሌ:- የአምባሳደር ብርሃኑ ድንቄን “አልቦ ዘመድ” የሚመለከት ሰው ይህ አስተሳሰብ ይገባዋል)።

 እንዲያውም የዓለም ፍልስፍና ባለቤቶችና የአውሮፓ ፍልስፍና ምንጭ ባለርስቶች እኛው ራሳችን ነን የሚሉ የታሪክ ተመራማሪዎች ብቅ አሉ። ለዚህም ዋስትናቸው ግብጽ ነበረች።

በዚህም አፍሪካውያን የራሳቸው ፍልስፍና ያላቸውና ለዓለም ፍልስፍናም አስተዋጽኦ ያደረጉ ናቸው የሚል ድምዳሜ ላይ ደረሱ (እንደ ፍራንሲስ ፋኖን፣ ማሳሎ፣ ሼክ አንታ ድዮፕ፣ መሳይ ከበደና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር በቀለ ጉተማ ያሉትን ልብ ይሏል)። ለምሳሌ:- ማሳሎ የጥንቱ አሌክሳንድርያ ትምህርት ቤት ለሰውልጆች እውቀት ማደግ ያደረገውን አስተዋጽኦ ጠቅሶ ታላላቅ የአፍሪካ ጠቢባን በሮማ ዘመን እንደነበሩ ይሞግታል። ይህ በርግጥም የሚደገፍ ሐሳብ ይመስላል። የኢትዮጵያ ባህላዊ የቤተክርስትያን ትምህርት፣ የመስጊድ ትምህርት እንዲሁም አገር በቀል የትምህርት ሥርዓት (ገዳ ሥርዓት) ያሌቃቸው ጠቢባን በዓለም መድረክ ምን አስተዋጽኦ እንነበራቸው ጥናት ማድረግ ይኖርብናል። ከቅድመ ዘመነ አክሱም ጀምሮ የነበረው ዓለማቀፍ ግንኙነት በባህሎች መወራረስ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደነበረው የአቴናን ታሪክ ማንበቡ በቂ ነው። የወደብ ከተማቸው ትልቁ የገበያ ስፍራቸው ላይ ከአራቱም አቅጣጫ የሚመጣውን ነጋዴ ስለ መጣበት ዓለም ነጽሮተ ዓለም ይጠይቁ፣ እውቀትን ይቀስሙ ነበት፤ ታላላቆቹ ፈላስፎቻቸውም ዓለምን ይዞሩ ነበር። ለምሳሌ አፍላጦን “The Republic” የተሰኘ ትልቅ ድርሳኑን ሲጽፍ የግብጽ ፎርኦኖች ዲሞክራሲያዊ አስተዳደርና የግብርና ልማት ቁሳዊ ሥልጣኔያቸውን በመጎብኘቱ የቅርብ ትውስታ ሕሊናውን ዳብሶች ነው የሚሉ አሉ። በግብጾቹ የትፍስኅትና ሥርዓት ያለው ሕይወት በመደመሙና የራሱን ህዝቦች የጉስቁልና ሕይወት ሲያይ በመበርገጉ ያንን የቢሆን ዓለም ጻፈ።

 He [Plato] seems to have gone first to Egypt; and was somewhat shocked to hear form the priestly class which ruled that land, that Greek was an infantstate, without stabilizing traditions or profound culture, not yet therefore to be taken seriously by these syphinxly pundits of the Nile. But nothing so educates us as a shock; the memory of these learned caste, theocratically ruling a static agricultural people, remined alive in Plato’s thought, and played its part in writing his Utopia. (Will Durant, 1961, p. 14)

ይህንን የዊል ዱራንትን ምስክርነት ችላ ልንለው አንችልም። ኢትዮጵያውያን መነኮሳት በ15ኛው ክፍለ ዘመን አውሮፓ ምድር ምን ያደርጉ እንደነበር ዶናልድ ሌቪን አስነብቦናል። ስለሀገራቸው ባህል፣ ሃይማኖትና ቋንቋ አውሮፓውያንን ያስተምሩ ነበር። እንግዲህ በአክሱም ስልጣኔ ለንግድ ወይም “ለስለላ” የመጡ አውሮፓውያን ምን ጥበብ እንደወሰዱ፣ የገዳን ዲሞክራሲ የጎበኙ የዘመኑ “መጤዎች” ምን ዓይነት ሐሳብ “መንትፈው” እንደሄዱ ባይታወቅ እንኳን አለመጠርጠር አይቻልም። ዘርፈው ወስደው በየሙዚየሞቻቸው ያጨቋቸው የብራና መጻሕፍቶቻችንና የሥነ- ጥበብ ውጤቶቻችን ለዚህ ሕያው ምስክሮች ናቸው።

 እነዚህ አፍሪካውያን ተከራካሪዎች “ካስፈለገም!፣ ካስፈለገም የተጻፈ ፍልስፍና መቼ አጣንና!” የሚሉ መጡ። እነዚህ የኢትዮጵያን የብራና ድርሳናት ያገላበጡቱ “በትውልድ ካናዳዊ በምርጫ ኢትዮጵያዊ ነኝ” ያለው የክላውድ ሳምነር ዓይነቶቹ ናቸው። በዚህ መንፈስ በመነሳሳት ሦስት የትርጉምና ሁለት ወጥ (ከ5ኛው ክፍለ ዘመን እስከ 17ኛው ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ የነበሩ) የፍልስፍና ድርሳናትን ይዞልን መጣ። የነዚህንና ሌሎች ጽሑፎችን ፍልስፍናዊ ይዘት ትንተና በሌላ ጊዜ እናየው ይሆናል። ሌሎቹ ደግሞ “ምነውና የሰው ልጅ በሕይወት ዘመኑ እንዴት? ከየት መጣሁ? ወዴት እሄዳለሁ? ፈጣሪዬ ማን ነው? ግዴታዬ ምንድን ነው? ተፈጥሮ ምንድን ነች? ሕይወቴ ትርጉም ምንድነው? ሳይል ሊኖር ይችላል?” ከሚል መጠይቅ በመነሳት በባህላዊው የአፍሪካውያን ኑሮ ውስጥ ፍልስፍናን መፈለግ ጀመሩ። ምን አግኝተው ይሆን?

እስኪ የክርክሩን ሂደት በሁለት ወይም በሦስት የተሰናሰሉ ነቁጠ አስተሳሰቦች (Critical Points) እንሰረው። ምግቶቹን መፈተሽና መቀበል አለመቀበል የአንባቢው ነው። አንደኛው ከላይ የጠቀስኩት የዊረዱ ሙግት ሲሆን እሱም “የአፍሪካ ባህላዊ አስተሳሰብ ከአውሮፓ ዘመናዊ አስተሳሰብ ጋር ማወዳደር ስለሌለብን ካለብንም ባህላዊውን ከባህላዊው ጋር፣ ዘመናዊውን ደግሞ ከዘመናዊው ጋር ነው። በዚህ ከተስማማን አውሮፓውያንም የራሳቸው ባህላዊ የሆነ “uncritical” አስተሳሰቦች አሏቸው። አፍሪካውያንም ጠቢባኖቻቸው (ኦዴራ ኦሩካ Sages የሚላቸው) የዘመናዊ አስተሳሰቦች ባለቤቶች ናቸው።” የሚለው ነው። በዚህም ዊረዱና የዚህ ሃሳብ ደጋፊዎች የውሮፓውያን ስለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ስለራሳቸውም የተሳሳት እውቀት አላቸው የሚል ነው። ሁለተኛው ከታች በስፋት እናየው ይሆናል እንደነ ሳንድራ ሃርዲንግ ያሉ ልሂቃን ደግሞ “እውቀት ነገድ የላትም። ሁሉም ባህሎች በሰው ልጅ የአስተሳሰብ እድገት ውስጥ የራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል። ስለዚህ ባንድም በሌላም መልኩ አሁን ለደረስንበት የሳይንስና የፍልስፍና ልህቀት ባለቤቶቹ ሁሉም የሰው ልጆች ናቸው።” የሚለው ክርክር ነው። ሦስተኛው ደግሞ ከሁለቱ ጋር የሚስማማ ይመስላል። የነ ጸናይ ሰረቀ ብርሃን ሐሳብ ነው። “ያለ ምንም ክርክር አፍሪካውያን የራሳቸው የሆነ አገር በቀል እውቀት ባለቤቶች ናቸው። አሁን ያለውን ዘመናዊውን ሳይንስና ፍልስፍና ከባህላዊው እውቀት ጋር በማዋሃድ ዘመናዊውን የአፍሪካ ፍልስፍና መስራት ይቻላል።” የሚል ነው።

“እስኪ የክርክሩን ሂደት በሁለት ወይም በሦስት የተሰናሰሉ ነቁጠ አስተሳሰቦች (Critical Points) እንሰረው። ምግቶቹን መፈተሽና መቀበል አለመቀበል የአንባቢው ነው። አንደኛው ከላይ የጠቀስኩት የዊረዱ ሙግት ሲሆን እሱም “የአፍሪካ ባህላዊ አስተሳሰብ ከአውሮፓ ዘመናዊ አስተሳሰብ ጋር ማወዳደር ስለሌለብን ካለብንም ባህላዊውን ከባህላዊው ጋር፣ ዘመናዊውን ደግሞ ከዘመናዊው ጋር ነው።”

በዚህ ጎራ እንደ እጓለ ገብረ ዮሐንስ ዓይነቶቹ “በተዋሕዶ ከበረ” የሚል የትምህርት ፍልስፍና ይሁንታ አቅራቢዎችን ማግኘት ይቻላል። (“የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” የተሰኘች በገጽ ብዛቷ ትንሽ ነገር ግን የሐሳብ ቱጃር የሆነችን መጽሐፉን ልብ ይሏል)። ይኸውና እዚህ ደረስን። “የአፍሪካ ፍልስፍና የለም!” የሚለውን “አለ እንጂ!” ብሎ የሚመልስ አካል እንደ ኤድዋርድ ቲ. ዳመር አገላለጽ የማረጋገጥ ኃላፊነት (The Burden of Proof) ስላለበት “በል እንግዲህ አሳይ!” የሚል ሌላ ጠያቂ ወይም ዳኛ ከፊት ለፊቱ ሲጋፈጥ ለማሳየት ያለውን መበርበር፣ ኪሱን፣ ጓዳ ጎድጓዳውን መፈተሽ ጀመረ። ይህ የማሳየት ሂደት ውስጥ የአፍሪካ ፍልስፍና ምንድን ነው? ነገዱስ ከወዴት ነው? መገለጫውስ ምን ይመስላል? ተግባራዊ ፋይዳውስ? የሚሉ ተንታኝ ጥያቄዎችን አዝሎ ከች ይላል። እነዚህን ከማብራራታችን በፊት ጥቂት ቃላት ላንድ ርእሰ ጉዳይ ማብራሪያ ያስፈልጋል። ይኸውም “የአእምሮ ቅኝ ግዛት” (Mental Colonialism) ስለሚባለው ነው። ከላይ ያለው የክርክሩ ሂደት ቁጥሩ ከየአፍሪካ ፍልስፍና ጋር አይደለም። ይልቁን የአፍሪካ የነጻነት ትግል ጉዞ አካል ነው። አውሮፓውያኑ በአካል ከአፍሪካ ምድር ከወጡ በኋላ በመንፈስ አፍሪካን ማስተዳደር ፈለጉ። በእጅ አዙር እውቀት ሁሉ ከኛ ዘንድ ናትና የናንተው አሮጌ አስተሳሰብ መረሳት አለበት በሚል በዘመናችን የሳይንስና የቴክኖሎጅ እንዲሁም የፖለቲካ ኢኮኖሚ በይነ-ገዝ (Monopoly የሚለውን ይተካልኝ ይሆን?) ሆነው ብቅ አሉ። እናም የትምህርት ሥርዓታቸው ስውር ተቃርኖ አንዱ አጀንዳ “እውቀትን መግደል” “Epistemicide) (ሳንቶስ) ሆነ። ስለዚህ ባህላዊው እውቀት ለዘመኑ የሳይንስ እድገት ምንም አስተዋጽኦ የለውም፣ እንዲያውም ወደ ኋላ ጎታችና ሁለቱም ተቃራኒ ናቸው የሚል ሙግት ተነሳ።

እንግዲህ ይህ ሙግት አውሮፓውያን ብቻ ሳይሆኑ አፍሪካውያንም ጭምር ለራሳቸው ባህላዊ እውቀት ንቀት እንዲያድርባቸውና ስለ ባህላዊው እውቀት ድኩምነት እንዲመሰክሩ በእጅ አዙር ተሰራበት። በዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን ፖሊሲያቸውን፣ ሥርዓተ ትምህርታቸውንና የትምህርቱን ይዘት ሳይቀር በገንዘብ ምጮቻቸውና በፖለቲካ ኃላፊዎቻቸው በጎ ፈቃድ እንዲያደርጉት እየተሰራበት እንደሆነ ብዙ ጥናቶች አመላካች ናቸው። ጥናቶቹ እንደሚያሳዩት፣ ትምህርት በአፍሪካ በአገር በቀልና በውጭ ፍልስፍና የታሸ ሰውን ወደሰውነት ክብሩ የሚመራ ከመሆን ይልቅ እንደ በቀቀን ሸምዳጅና እንደ ጋሪ ፈረስ በአንድ መስመር ብቻ የሚመራ እያደረገው ይገኛል። ከውጭ ጫናዎች በተጨማሪ (በበለጠም ሊሆን ይችላል) የውስጥ ጨቋኝ ገዥዎችና የርስበርስ ግንኙነት ተግዳሮቶች የበጎ አሳቢ አፍሪካውያን ምሁራንን ቀልብ መሳብ ችለዋል።

ይኸ ሁሉ ራስን የማዳን ትግል ብሶት የወለደው የአልሞት ባይ ተጋዳይ መፍጨርጨር እንግዲህ “የአፍሪካ ፍልስፍና ምንድን ነው?” “የአፍሪካን ፍልስፍና አሳይ?” የሚሉ ጠያቂዎችና “ይኸውና የአፍሪካ ፍልስፍና ይኸን ይመስላል … የአፍሪካ ፍልስፍና አስተዋጽኦዎችም እነዚህ መሆን አለባቸው” የሚሉ ዲስኩሮችን ይዞ ብቅ አለ። ነገር ግን የአፍሪካ ፍልስፍና ዋናው ምንጩ ይኸ አይደለም። ይኽ ለዘመናዊው የአፍሪካ ፍልስፍና መጸነስና ለውልደቱም አፋጣኝ ምክንያት እንጂ የአፍሪካን ፍልስፍና ሙሉ ማንነት የሚያሳይ አይደለም። ታዲያ የአፍሪካ ፍልስፍና ከወዴት ነው? አብረን እንፈልገው? ይቀጥላል! 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top