ስርሆተ ገፅ

ህይወት በአጎዛ ላይ

ሠዓሊ እያዩ ገነት

ከአ.አ.ዩ አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ ቤት በተጨማሪም ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያው ዲግሬ አግኝቷል። ከአ.አ.ዩ የሥነ-ጥበብ ት/ቤት በሁለተኛ ዲግሪ ተመርቋል።

በጎተ የባህል ማዕከል፣ በአሊያንስ ኢትዮ- ፍራንሲስ፣ በአሜሪካ ኤምባሲ፣ በአለ የሥነ- ጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት እና ሌሎችም በተጨማሪም በባህርዳር በግሉ እና በቡድን አውደ-ርዕይ አቅርቧል።

በውጭ ሀገር በአሜሪካ ላስ ቬጋስ በኔቫዳ ዩኒቨርሲቲ፣ በኤኳደር፣ በስዊዝላንድ እና በስዊድን ሥዕሎቹን አሳይቷል።

 በሀገር ውስጥ በሞያው በማስተማር በውጭ ሀገርም ከስራው ጋር በተያያዘ ትምህርታዊ ገለፃ አድርጓል።

 በተለያዩ ጊዚያት በአዲስ አበባ እና በአማራ ክልል በተካሄዱ ውድድሮች አሸንፏል።

ከየት ጀመርክ?

ጥናት ከማድረግ፤ የሥነ-ጥበብ ተማሪ እንደመሆኔ በገጠር ውስጥ ከሚከወኑ፣ አሁን ካለው እውቀት ጋር ተገናዝበው በሆነ ቲዎሪ ውስጥ ተካትተው ስም ያልወጣላቸው ግን ከሥነ-ጥበብ የማይተናነሱ ምናልባትም ግሩም የሆኑ ተግባሮች በማሰብ ዘጋቢ ባህርይ ያለው ጥናት ለመጠቀም ፈለግሁ።

 በቆዳላይ?

 አጎዛን! አጎዛን ለምንድነው የገጠር ሰዎች አድርቀው የሚሰቅሏቸው፣ የሚለብሷቸው፣ አንጥፈው የሚተኙባቸው? ለበሬዎች ያላቸው ቅርበት ምንያህል ነው?

 አየህ በምዕራቡ ዓለም በአብዛኞቹ የሥነጥበብ አረዳድ ቁሳዊ ባህል ወይም ሰው ለዕለት ተዕለት መገልገያው የሚሠራቸው ዕቃዎች ተደርገው ይወሰዳሉ።

 እኔም በተወለድኩበት አከባቢ አንድ ቤት ግድግዳ ላይ የተሰቀለ አጎዛ በተለያዩ ቀለማት የተሰሩ ሰፌዶች ይኖራሉ። ማንም ወደ ቤቱ የገባ ሰው በእነዚህ ዕቃዎች አማካኝነት ከባለቤቱ ጋር ይግባባል።

 መነሻህን ታስታውሳለህ?

 የዘመናዊ የሥነ-ጥበብ አረዳድ ትኩረቱ አንድ የሥነ-ጥበብ ውጤት ዓይን ላይ ከሚያልቅ ጨዋታ አልፎ ማኅበረ-ሰቡ ውስጥ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማበራዊ ጉዳዮችን የተሸከመ ይሆንና ሰው ያንን ተመልክቶ ከተለያዩ የህይወት ገፅታዎች ጋር አገናኝቶ ትርጉም እየሰጠ በጥያቄ ላይ ጥያቄ እየፈጠረ፤ ዕውቀትን እንዲያገኝ በሆነ መንገድ መደገፍ ስለሚመስለኝ ይሄ እንደነገሩ ዕደ-ጥበብ ብቻ ተብሎ ከሥነ-ጥበብ አንሶ የታየን ነገር ለማጉላት ነው።

 ደረጃውን ከፍ ለማድረግ የትኛውን ዓይነት መረጥክ?

  የ”Appropriation Art” መንገድን ነው የመረጥኩት። ይህ አንድ ነገር ከእዚህ በፊት ያገለግል ከነበረው አውድ አውጥተህ በሌላ መንገድ ስታቀርበው እንደማለት ነው።

አየህ የአሁን ጊዜን የሥነ-ጥበብ አስተሳሰብ ተከትዬ አጎዛውን አምጥቼ አራት ማዕዘን ፍሬም ውስጥ ባካትተው ምን ዓይነት ትርጉም እንደሚሰጥ አሰብኩ።

ምናለ ከተቻለ ባስታርቃቸው? አይ አንታረቅም ግን ደሞ አንጣላም ካሉም ጎን ለጎን ቢቀመጡ ምን ዓይነት ስሜት ይፈጥራሉ የሚለውን ለማሳየት ነው የሞከርኩት።

 ጥናት ስታካሔድ ከጠየቅካቸው የምታስታውሰው አለ?

 የጠየቅኳቸው አርሶ አደሮች ስለነገሩኝ ላጫውትህ

 ጥሩ!

 ለበሬዎቻችን ክብር አለን። በእነሡ እናርሳለን። እንወቃለን። እናበራያለን። እንጠቀጥቃለን። ተጠቅመነባቸው ስናበቃ ደሞ አረጁ ብለን ወደ ወይፈኖቹ እንዞራለን። ካላቸው ባህርይ በመነሳት ስም እናወጣላቸዋለን።

 የሰው ሰብል የማይበሉትን፣ ማረሱ ላይ ጠንካራ የሆኑ፣ የሚያስደሱትንን ከሞቱ በኋላ ደግሞ በጀንዴያቸው እንተኛለን።

 ጀንዴያቸው?

 ቆዳቸው ላይ ሲሉ ነው።

 መልካም!

 እንዳይረሱ ስም ይኖራቸዋል። “ወሰን” የሚባል በሬ ነበረን። ይህ በቃ እንደ ሰው ይሰማል። የታዘዘውን ይፈፅማል። ተው ሲሉት ይተዋል። ዙር ሲሉት ይዞራል። ታማኝ በመሆኑ ስሙን እንደ ዘር በቅብብሎሽ ይዘን እንዘልቃለን።

 በሬዎቻችንን ቸግሮን ብንሸጣቸውም፣ ስጋቸውን አንበላም። ቆዳቸውን ገዝተን እንሰቅለዋለን።

የአንዲቷን ላም ስም “ትርባልን” ብለናታል። ብዙ ልጆች ድራልናለች። ዘጠኝ ላሞች ወልዳለች። ወተታም ናት፡ ሽል ቶሎ ጠላፈ….

ሽል ቶሎ ጠላፈ ማለት?

ቶሎ ትፀንሳለች ማለት ነው።

 ብዙን ጊዜ የሚያወድሷቸው በግጥም እና ዜማ አይደል?

 የማስታውሰውን ልንገርህ።

 መልካም!

 አያ በሬ ሆሆ!

 አያ በሬ ሆሆ!

ባንተ ይባስ ያልኸኝ ይኸው ባንተ ባሰ

 እርሻው ባይታረስ ገለባው አነሰ

 አትዋል ይዋሉብህ አትምከር ይምከሩ

“ነቅሼ ያወጣሁት ይበልጥ ያተኮርኩበት በገጠር ግድግዳ ላይ የሚሰቀሉ፣ ቤት ውስጥ የሚቀመጡ፣ የተለያዩ ዕቃዎች ላይ ነው። እነዚህ ከዕቃነት አልፈው ራስን እንደመግለጫነት ለማሳየት፣ ከዕቃነት ዘለው በውስጣቸው ጠንካራ የሆነ ፍልስፍና እንዲኖራቸው ለማድረግ ሞክሬያለሁ።”

ከመከሩት ገደል ሳይገቡ አይቀሩ

 ቆዳቸውን እዴት አሰብካቸው?

እዛው ገጠር ውስጥ የገዛኋቸው አሉ። በውሰትም ወስጃለሁ። ሲያውሱኝ አስምለውኝ ነበር። እኔም እንዳሰብኩት በሚገባ ተጠቅሜባቸዋለሁ። አየህ ቆዳዎቹ ማንነቴ ውስጥ ገብተዋል። እኔም ውስጣቸው እንዳለሁ ይሰማኛል።

 ቆዳውን ሳስብ ከባለቤቱ ጋር ያለውን ቁርኝት ደስታ፣ መከራና መስዋዕትነት የተሞላ ህይወቱን ሳስታውስ፣ ከበሬ የተሻለ የሚገልፅልኝ አላገኘሁም። እየተገረፈ የሚያርስ፣ ስጋውን ለምግብ፣ ቀንዱን ለጥዋ፣ ለአረቄ መለኪያ፣ ቆዳውን ለልብስ፣ ለነጋሪት፣ የዙፋን ጠፈር፣ አልጋ፣ ከበሮ ሆኖ ለዝማሬ፣ በሠርግ ጊዜ ለደስታ፣ ምን አለፋህ ከቆዳነት በላይ ብዙ ነገሮችን አቅፏል።

 ምን ያህል የምትፈልገውን ገልፆልሃል?

 ቆዳዎቹን ዝምብየ አይደለም ሰብስቤ ያመጣኋቸው። በተማርኩት መሠረት በመመዘንና በመለየት ነው። የተጠቀምኩባቸው የተመልካቹን ስሜት ይነካል ብዬ ነው። ይህንኑም ባሰብኩት ደረጃ መንካቱን ተገንዝቤያለሁ። የተለያዩ አስተያየቶች አሉ። አንዳንዶቹ ይኼማ የትም የምናየው የበሬ ቆዳ ነው ሲሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በጣም መደሰታቸውን ስሰማ በእርግጥ በእዚህ ደረጃ ስሜታቸውን ነክቶት ነው? ብዬ እጠይቃለሁ።

“ቆዳዎቹን ዝምብየ አይደለም ሰብስቤ ያመጣኋቸው። በተማርኩት መሠረት በመመዘንና በመለየት ነው። የተጠቀምኩባቸው የተመልካቹን ስሜት ይነካል ብዬ ነው። ይህንኑም ባሰብኩት ደረጃ መንካቱን ተገንዝቤያለሁ። የተለያዩ አስተያየቶች አሉ።”

ትርጉም ሰጥተዋል ብለህ ታስባለህ?

በገጠር በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ ራሳቸውን ለመግለፅ፣ ትዝታን ለማቆየት፣ ለመኖር፣ ተፈጥሮን ለማድነቅ፣ ፈጣሪያቸውን ለማመስገን-ለማወደስ፣ ቁሳቁሶችን በመጠቀም የሚከወኑ ብዙ ነገሮች አሏቸው።

 ነቅሼ ያወጣሁት ይበልጥ ያተኮርኩበት በገጠር ግድግዳ ላይ የሚሰቀሉ፣ ቤት ውስጥ የሚቀመጡ፣ የተለያዩ ዕቃዎች ላይ ነው። እነዚህ ከዕቃነት አልፈው ራስን እንደመግለጫነት ለማሳየት፣ ከዕቃነት ዘለው በውስጣቸው ጠንካራ የሆነ ፍልስፍና እንዲኖራቸው ለማድረግ ሞክሬያለሁ።

 አጎዛ እያዩ መደሰቱ ላይ ወይስ መጠቀሙ ላይ? በሥራህ የቱ ጎልቷል?

 አጎዛ ተሰቅሎ ይታያል። ታይቶ አይጠገብም። ደግሞ ተሰቅሎ አይቀርም። ማታ ላይ ትተኛበታለህ። በሁለቱም ደረጃ ክብር አግኝቷል። አየህ ስለተኛህበት አላቀለልከውም። እንዲያውም ከሰውነትህ ጋር ቀርቦ፣ ተነካክቶ በአንዳች ነገር ይቆራኛል። ይህን እንደውም ብዙን ጊዜ የአፍሪካ ሥነ-ጥበብ ተግባር ላይ ያተኩራል የተባለለትን ማለትም ተግባርን ከኪነ-ውበት ጋር የማያያዝ ሥራ በተወሰነ መንገድ ለማምጣት ጥሪያለሁ። 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top