ስርሆተ ገፅ

“ፍለጋ አያልቅም”

ገጣሚ በክሪ አሕመድ በቅርቡ “የኔ ዓለም” በሚል ርዕስ የግጥም መጽሓፍ አሳትሟል። ገጣሚው ከግጥሞቹ መካከል ስለሐሳቡ አጫውቶኛል። አራቱን እዚህ ዓምድ ለማስተናገድ መርጫቸዋለሁ።

ፍለጋ

በመልስ አልባ ኑሮ

 እውነትን ፍለጋ

 ውበትን ፍለጋ

ምንድነው ፍለጋ

 ቀድሞ በታተመ የትንቢት ቀጠሮ

ገጽ -3-

በክሪ አሕመድ፡- ፍለጋ አያልቅም። ፍለጋ አይታወቅም። ለምሳሌ ይርብሐል፣ ለሆድ ከሆነ ምግብ ትፈልጋለህ። ርሃብህ ሌላ ከሆነ ታስባለህ። ትመርጣለህ። ትወስናለህ። ርሃብህን ለማስታገስ ትወጣለህ። አገኛለሁ ብለህ የምትሄድበት ቦታ ልታጣ ትችላለህ። ወይም ያገኘኸው ነገር ርሃብህን ሊያስታግስልህ አይችልም። እናም ዳግም ያንን የምትፈልገውን ነገር ለማግኝት መንገድ ትጀምራለህ። ምናልባትም ጉዞ ላይ ወደ ሌላ ፍለጋ የሚያመራህ ጉዳይ ልታስብ ትችላለህ።

ስለምትፈልገው ነገር ወይም ስም ልትናገር ትችላለህ እንጂ ስለምታገኘው ነገር እርግጠኛ አትሆንም። ፊት ለፊት የተቀመጠ ፈጥነህ የምትደርስበት አይደለም ፍለጋ። ድካም አለው። ትደክማለህ። መንገድ አለው ትጓዛለህ። የምትፈልገው ነገር ቀረብ ስትል ይርቃል። ወደ እሱ እየደረስኩ ነው ስትል ሌላው ፍላጎት ይተካና ፍለጋ እንደገና ትነሳለህ። ይኸው ይመስለኛል።

የኔ ዓለም

 እውነት ነው!

 ህይወት ነው

 ብዬ እንዳልሞግትሽ

ቅዥት ነው ዓለሜ

 እውነቱን ልንገርሽ

ገጽ -27-

በክሪ አሕመድ፡- ከስም አወጣጥ ልነሳ፤ አባ ራሱን በልጁ ውስጥ ሲገልፅ ወይም እናት በልጇ ውስጥ ራሷን ስታገኝ “የኔ ዓለም” ይመጣል። ይህ ከመጠሪያም በላይ ነው። ልዩ ስሜት አለው።

 ደሞ የኔ ዓለም በሌላ መንገድ ይመጣል። ዓለምን ሳስብ እኔን አገኛለሁ። ውቂያኖስ ውስጥ ከጠብታም ባነሠ መልኩ፤ ወይም መሬት ላይ የደቃቃ አሸዋ አካል መስዬ መኖሬ የሚታወሰኝ ሌላው ዓለም በሚሰጠኝ ነገር ነው።

ወይም በተቃራኒው ዓለሜ ልክ ሆኖ ይታየኛል። ግለ-ሰብ ሁኜ ሀገር የማክልበት የራሴን ክልል ፈጥሬ፣ ራሴን ጠይቄ ለራሴ መልሼ። ተሟግቼ ገንብቼ የማፈርስ፤ ከእዚህ ውስጥ ይመስለኛል የወሰድኩት።

 ሕይወት

 ትላንት እንደ ነገ

ነገ እንደ አሁን

 አሁን እየጦዘ

ያዙሪቱ መድረሻ

 የመነሻው መጨረሻ

ሕይወት።

 ገጽ -44-

 በክሪ አሕመድ፡- ትስስር አለው። ስትፈጠር የነበረው ሒደት፤ ይህችን ዓለም ስትሰናበትም ተመሳሳይነት አለው። እናም የመጨረሻህ መጀመሪያ ወይም መጀመሪያው እንደ መጨረሻህ የሚመስለው ለእዚያ ይመስለኛል።

ስትኖር መሃከል ሆነህ ዳር የደረስክ ይመስልሃል። ተንሳፈህ ጠልቄያለሁ ብለህ ታስባለህ። ቢነጋም በጨለማ ውስጥ እንደተቀመጥክ ትቆጥራለህ። ሳትራመድ ትርቃለህ። እየቃዠህ ህልምህን ትኖራለህ። ወይም ሁሌም ትጠይቃለህ። ጥያቄዎችህ ይበዛሉ። ፍላጎቶችህ አይመጠኑም። ለመድረስ የምታስብበት ሥፍራ አይወሰንም።

በእርግጥ አንዳንዴ እንደታሰበው ይሆናል። ይህን ማሳየት ምናልባት በግጥም መልክ ላይሆን ይችላል።

 ወፍ ዘራሽ

 ከብርሃን ሽሽት

 ምናቡን ጋረደ

 በጭፍን ተራግሞ

 በጭፍን ወደደ

ዘሩ የጠፋበት

 ደረቅ አፈር ሆነ።

 ገጽ -60-

በክሪ አሕመድ፡- ከተዘጋጀበት ወይም ተከልሎ ከተወሰነበት ውጪ የበቀለው ወፍ ዘራሽ ይባል ይሆናል። አንዳንዴ ሰው ዘርቶትም በወፍ ሊሳበብ ይችላል። በተለምዶ የመጣውን በተለይ የሚነወረውን ለሌላ ነገር ግዑዝ ነገር ወይም በእንስሳት ማላከክ ይቀላል። ችግሩ ዘሩ ላይ ሳይሆን ዘሪው ላይ ይመሥለኛል። ከበቀለ በኋላ ነቅሎ የሚጥል የለም። እንዳያድግ የሚከላከል አይኖርም። ብቻ የተፈጠረበት ይታሰብ እና የዘር ወጉ ባልጠበቀ መንገድ መብቀሉ ይታወቅ እና ቢቀጭጭም፣ ቢወፍርም፣ በያጥርም፣ ቢረዝምም ከወቀሳ አያመልጥም። ከእርግማን አይድንም።

ወፍ የመጣበት መሥመር ላይታወቅ ይችላል። ከተሸነቆረ ከረጢት የሾለከች ትሁን በንፋስ የተገፋች፣ መንገደኛ የጣላት ወይም ከእንስሳት ሆድ የወጣች አትታወቅም። በቀለም ብትለይም፤ የአከባቢው አይደለችም፤ ብትባልም ዘር ናት ወፍ ዘራሽ 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top