ከቀንዱም ከሸሆናውም

ጋባዥ እና ተጋባዥ

ፀሓፌ ትዕዛዝ ገ/ስላሴ ስለ ሆቴል ቤቱ ሲያብራሩ #ስሙም ሆቴል ተባለ; ይላሉ። ኃላፊነቱንም ሥራውንም እቴጌ ጣይቱ ተረክበው ይመሩና ያሥተዳድሩ ጀመር። በ1900 ዓ.ም. ጥቅምት 25 ቀን ምኒልክ በአዲስ አበባ ያሉት ዲፕሎማቶችንና የውጭ ሀገር ሠዎችን ጋብዘው ሆቴሉን አስመረቁ። የመጀመሪያው ሥራ አስኪያጅም ሙሴ ፍሬድሪክ ሐል ነበረ። በኋላ ግን አቶ ዘለቀ አጋርደው ተሾሙ።

 እንደ አገር አባባል ጣይቱ እጅ የሚያስቆረጥም ወጥ እየሠሩ ገበያ ቢጠብቁ ጠፋ። እንኳን ምግብ መብላት ለግሪኮች ሻይ ቤት ለሠራተኞች የማታ ራት ይሆን ጀመር። የሚስታቸው ገበያ ማጣት ያሳሰባቸው አጤ ምኒልክ አንድ ቀን ከችሎት ሊነሱ ሲሉ በአካባቢያቸው ላሉ መኳንንቶች “ጣይቱ ምግብ የሚሸጥበት ቤት ከፍታለች እና ኑ እንሂድ እና ልጋብዛችሁ” ብለው ወሰዷቸው። መኳንንቱ በሉ ጠጡና ምኒልክ 30 ብር ከፈሉ። በማግሥቱ እንደተለመደው ገበያ ቢጠበቅ ጠፋ። ቀጥሎም ጠፋ። ቀጥሎም ጠፋ። እንደገና ምኒልክ ሆቴል ገብቶ መብላት ነውር ያለመሆኑን ለመኳንንቱ ገልፀው እንደገና ምሳ ጋበዙ። በሌላው ቀን አሁንም ገበያ አልተገኘም። ቢጠበቅ ቢጠበቅ ድርሽ የሚል ሰው ጠፋ። በሌላ ቀን ደግሞ አጤ ምኒልክ ከችሎት ሊነሱ ሲሉ በዙርያቸው

“የሚስታቸው ገበያ ማጣት ያሳሰባቸው አጤ ምኒልክ አንድ ቀን ከችሎት ሊነሱ ሲሉ በአካባቢያቸው ላሉ መኳንንቶች “ጣይቱ ምግብ የሚሸጥበት ቤት ከፍታለች እና ኑ እንሂድ እና ልጋብዛችሁ” ብለው ወሰዷቸው። መኳንንቱ በሉ ጠጡና ምኒልክ 30 ብር ከፈሉ”

ላሉ መኳንንት “ሰማችሁ ወዳጆቼ አሉ፣ በፈረንጅ አገር አንድ ቀን አንድ ሰው የጋበዘ እንደሆነ ያ የተጋበዘ ሰው በሌላ ቀን ደግሞ ብድሩን ይከፍላል። ብድሩን ካልከፈለ ግን እንደ ነውር ይቆጠርበታል” ብለው ንግግራቸውን ሳይጨርሱ መኳንንቱ “እርሶን ፈርተንና አፍረን ነው እንጂ የሚሆንልን ከሆነ የምኒልክን ብድር ለመክፈል እኔ አለሁ” እያሉ ተራ በተራ ከሆቴል ቤት ምኒልክንና ጣይቱን ይጋብዙ ጀመር። ገበያው እየደራ ሄደ። ምሳችን እቴጌ ሆቴል ሄደን እንብላ የሚለው ስለበዛም ስሙ እቴጌ ሆቴል ተባለ።

ከጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ” መጽሐፍ የተወሰደ

ቀደም ሲል ነግሬሃለሁ!

በ1839 ዓ.ም. ፕላውዴን በኢትዮጵያ የኢንግሊዝ ቆንሲል ሆኖ ተመለሠ። ራስ ዓሊም በከፍተኛ ደረጃ ተቀብለውት ውል ተፈራረሙ።

 ከዚህ በኋላ ፕላውዴን ቆንሲልነቱን ለማስተዋወቅ በመኖሪያ ቤቱ የኢንግሊዝን ሰንደቅ ዓላማ ለመትከል ራስ ዓሊን ጠየቀ። ራስ ዓሊም “በኔ በኩል ፍቃደኛ ብሆንም ህዝቡ የተለመደውን ተግባር ስታደርግ ግጭት ያመጣል። ከህዝቡ ለሚነሳው ተቃውሞ ኃላፊ እንደማልሆን አውቀህ ብትሰቅል መልካም ነው” የሚል መልስ ሰጡት። ፕላውዴን በቆንሲላው ግቢ ሰንደቅ ዓላማ ለመትከል ያቀረበውን ሀሳብ እና ራስ ዓሊ የሰጡትን መልስ ለቤል አማከረው። ቤልም “የሠላም ዘበኛው ከኔ ጋር በመሆኑ በዚህ በኩል ችግር የለም፤ እኔ ኃላፊነቱን እወስዳለሁ” በማለቱ ፕላውዴን ሰንደቅ ዓላማውን በግቢ ውስጥ ተከለ። ነገር ግን አገሬው ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የኢንግሊዝን ሰንደቅ ዓላማ ጠባቂ አይደለንም በማለት አውርዶ ቀደደው። አዲሶቹ በቤል የሚሰለጥኑት የሰላም ዘበኞች የአገሬውን ድርጊት እንዲያስቆሙ ቢጠየቁ የኢንግሊዝ ሰንደቅ ዓላማ ጠባቂ አይደለንም በማለት አሻፈረን አሉ። ፕላውዴን የደረሰበትን ችግር ለራስ ዓሊ ሄዶ ሲያመለክት ቀደም ሲል ነግሬሃለሁ የሚል መልስ ከማግኘት ሌላ ያተረፈው አልነበረም።

 አእምሮ ንጉሴ ከ”ጥንታዊ የኢትዮጵያ የሠላም ጥበቃ ታሪክ” መጽሐፍ

ሙዚቀኞቹ የአርመን ልጆች

በትልቁ የዓለም ጦርነት ጊዜ ቱርኮች በአርመኖች ላይ ብዙ መከራ ስላደረሱባቸው እና ስለ ፈጇቸው የሙት ልጆች የሆኑት የአርመን ወጣቶች ወደ ኢየሩሳሌም እና ወደ ሌላም ሥፍራ እየተሰደዱ እንደየችሎታቸው በየሥራው ተሰማርተው ነበር። ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን 1916 ዓ.ም. አውሮጳን ለመጎብኘት በጉዞ ላይ ሳሉ መጀመሪያ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው ነበር። እና ሙዚቃኞቹ የአርመን ወጣቶች ሙዚቃ እየነፉ ደስ አሰኝተው በአክብሮት ተቀበሏቸው። ከዚህም በኋላ በኢየሩሳሌም ያሉ የአርመን ሊቃነ ጳጳሳት አርኪቢሾፕ ቴሪዚያን ከልዑል ዘንድ ቀርበው የወጣቶቹን ሁኔታ እና ችግር ስለአስረዷቸው ከእነርሱ ውስጥ አርባውን ልጆች እና አስተማሪያቸውን ወደ ኢትዮጵያ ለመውሰድ እንደሚፈቅዱ ገለጡላቸው። ሊቀ- ጳጳሳቱ ስምምነቱ ለአራት ዓመት የሚፀና ሆኖ እንዲሔዱ ከልዑል አልጋ ወራሽ ጋር ተነጋግረው ጨረሱላቸው እና በ1917 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ በመርከብ ተሣፍረው በጅቡቲ በኩል ወደ ኢትዮጵያ መጡ።

መስከረም 16 1917 ዓ.ም. አዲስ አበባ የመኖሪያ ሥፍራ የልጅ ኢያሱ ግቢ በሚባለው ውስጥ ትልቁ አዳራሽ ተፈቅዶላቸው እና በነፍስ ወከፍ የወር ቀለብ 35 ብር እየተቀበሉ በአስተማሪያቸው በሙሴ ኪቦርክ ናልባንዲያን መሪነት የሙዚቃውን ሥራ ያካሔዱ ጀመር። የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤትም ለሙዚቃ ትምህርት የመረጣቸው ልጆች ከእነርሱ ዘንድ እየተማሩ በሙዚቃ ሰለጠኑ።

 ምንጭ፣ ካየሁት ከማስታወሰው መፅኃፍ /ለዑል እምሩ ኃ/ስላሴ

ትያጥሮን

በሀገራችን ቲያትር የሚባለው ቋንቋ ግዕዝ ላልተማሩ ሰዎች ባሁኑ ጊዜ የመጣ አዲስ ቋንቋ ሳይመስላቸው አይቀርም ይሆናል። #ቲያትር ማለት ግን ምንም መሠረቱ የጽርዕ ልሳን ቢሆን ከቀዳማዊ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የሀገራችን የቅኔ መምህራን ቲያትር በማለት ፋንታ ትያጥሮን እያሉ በግዕዝ ትምህርት ሲናገሩ ቆይተዋል። መጽሔት በሚባለውም በሰዋስው መጽሓፍ ትያጥሮን ማለት የጫዋታ ቦታ ማለት ነው; ብለው ተርጉመው ጽፈውታል።

 በመሠረቱ በፅርዓውያን አነጋገር እስከ ዛሬ ድረስ ትያትሮን ይባላል ይሉናል። ትርጓሜው አሁን እንደተባለው የጫዋታ ቦታ ማለት ነው። ስለዚህ ቲያትር ከማለት በቀድሞ ጊዜ እንደተለመደው እንደ ግዕዙ ቃል በአማርኛም ቋንቋ ትያጥሮን ብለን ብንሰይመው ጥንተ- ነገሩ ከመሠረቱ ቋንቋ የማይፋለስ ይሆናል።

 ከዮሐንስ አድማሱ “ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ፣

 አጭር የህይወቱ እና የጽሑፉ ታሪክ

-ከ1887-1939” መጽሐፍ የተወሰደ

ሻምበል ግርማ ሓድጉ

ሻምበል ግርማ ረጅም ነው። ቀላ ያለ ዝምተኛ ይመስላል። ግን የዜማ ምንጭ ነው። ከእርሱም እየፈለቁ በጥላሁንና በሌሎችም የተሰሙት ዜማዎች የህዝብን ልብ አርክተው በፍቅር ስጥመት አጥለቅልቀውታል።

 ሻምበል ግርማ ሓድጉ በአሥመራ ተወልዶ የ13 ዓመት ልጅ እንደሆነ የሙዚቃ ፍቅር ያደረበት ሰው ነው። ከአሥመራ ወደ አዲስ አበባ በ1941 ዓ.ም. በክብር ዘበኛ ዕጩ መኮንንነት ተቀጥሮ በአሁን ወቅት ከሻምበልነት ማዕርግ ለመድረስ የቻለ ከፍተኛ የሙዚቃ መፈልሰፍ ተሰጥኦ ያለው የ34 ዓመት ጎበዝ ነው።

 ሻምበል ግርማ ከ450 በላይ የሆኑ ዜማዎችን ደርሷል። ዜማዎቹም ለቁጥር መሙያ የቀረቡ ሳይሆኑ ሁሎቹም ልብ የሚነኩ ናቸው። ከብዙ በጥቂቱም፡- “የመስከረም አበባ፣ አልቻልኩም፣ ኡኡታ፣ ኧረ ምን ይሻለኛል፣ መቼ ነው ሰዓቱ፣ ጭር ባለ ሌሊት” ብቻ ቢጠቀሱ ለታላቅ የዜማ ደራሲነቱ በቂ ማስረጃ ሊሆኑ ይችላሉ። ከዚህም በላይ በክቡር ዘበኛ ቲያትር ክፍል ዘመናዊ ጨዋታን የጀመረ እርሱ ሲሆን የመጀመሪያ ዜማዎቹም የሰው ነገር ራስ ያዞራል እና ገና በልጅነት የተባሉት መሆናቸውን ገልጽዋል።

ከሰለሞን ተሰማ

“አስደሳቾቻችንን እንወቃቸው” መጽሔት የተወሰደ

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top