አድባራተ ጥበብ

ዳንኤል ክብረትና የ‹ወግ› መጽሐፎቹ

1.እንደመነሻ

ዳንኤል ክብረት፣ ከ2002-2010 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ውስጥ ብቻ፣ ስምንት የ‹ወግ› መጻሕፍትን በተከታታይ ያስነበበን፣ ሥራዎቹም በተደጋጋሚ የተነበቡለትና እየተነበቡለት ያለ፣ ከትጉሃን ጎራ የሚመደብ የዘመናችን ደራሲ ነው። መጻሕፍቱም፣‹የሁለት ሐውልቶች ወግ ›፣ ‹ጠጠሮቹ›፣ ‹የኔ ጀግና›፣ ‹ስማችሁ የለም›፣ ‹እኛ የመጨረሻዎቹ›፣ ‹የሚከራዩ አማት›፣ ‹የሰርቆ አደሮች ስብሰባ› እና ‹ኑ! ሀገሬን እናዋልዳት› ተብለው የሚጠሩ ናቸው። ሁሉም ከዐቢይ መጠርያቸው ሌላ ‹እና ሌሎች› የሚል ንዑስ ርዕስ አስከትለዋል። ‹እና ሌሎች› መባላቸው እያንዳንዱ መጽሐፍ፣ ለርዕስነት ከታጨው ወግ ሌላ፣ ሌሎች በአማካይ ከሠላሳ እስከ አርባ የሚሆኑ አጫጭር ድርሰቶች በውስጣቸው ስለያዙ ነው። ከስምንቱ መጻሕፍቱ መካከል፣‹ስማችሁ የለም› የሚለው ግን ይለያል። ‹ስማችሁ የለም› ትኩረቱን ደራሲው በሚከተለው ሃይማኖት ላይ ባሉ የአስተዳደር እንከኖች፣ ሲኖዶሳዊ መዋቅሮች እና የአስተሳሰብ መዛባቶች ላይ ያሉ ድክመቶችን ነቅሶ በማውጣት እና መፍትሔ በመጠቆም ላይ ያተኮረ ነው።

 ዲያቆን ዳንኤል የ‹ወጎች› ብቻ ሳይሆን፣ በሃይማኖት እና በምርምር ላይ ያተኮሩ ከሃያ አምስት በላይ የሆኑ መጻሕፍት ደራሲ መሆኑ ይታወቃል። በየቤተ ክህነት ብቻ ሳይሆን በየቤተ ኪነት ምኩራቦችም ስሙ ጮክ ተብሎ የሚጠራ የድርሰት ሙያተኛ፣ በየመካነ ትምሕርት ጉባዔው ድምጹን እንዲያሰማ የሚጋበዝ ተናጋሪ፣ በየመገናኛ ብዙኃኑ ሃሳቦቹን በትውልዱ ላይ የሚዘራ ንቁ አትክልተኛ ነው። ምንም እንኳን፣ የዚህ መጣጥፍ አቅራቢ ዳንኤል ከሚታወቅባቸው መጻሕፍት መካከል እንደ ‹አራቱ ሃያላን› ላሉ፣ ሳይገለጹ ተከድነው፣ ወይም ተሰውረው፣ ወይም ተድበስብሰው ታልፈው በነበሩ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ለሚያዘጋጃቸው የምርምር መጻሕፍት ክብደትና ክብረት ቢሰጥም፣ ‹ወጎቹንም› በቸልታ እንደማያያቸው መግለጽ ይፈልጋል፤ የ‹ወጎቹን› ተጽዕኖ አሳዳሪነት ብቻ ሳይሆን፣ ደራሲው ሃሳቡን ለመግለጽ በሚጠቀምበት ስልት ሃሳቦቻቸውን በየመገናኛ ብዙኃኑ ለማንሸራሸር የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ጥቂት አለመሆናቸውንም አስተውሏል።

 ይህ መጣጥፍ፣ የዳንኤል ክብረት ስምንት ‹የወግ› መጻሕፍትን ብቻ ለይቶ በማውጣት በወፍ በረር ለመቃኘት የሚሞክር ነው። እንደሚታወቀው፣ ከ‹ሁለት ሐውልት ወግ› እስከ ‹ኑ! ሀገሬን እናዋልዳት› በተከታታይ ማስነበብ የቻለው ዳንኤል፣ መጻሕፍቱ በተደጋጋሚ የመነበብ፣ በሬዲዮና በማኅበራዊ ሚዲያ የመተረክ፣ በተማሪዎች የመተወን ዕድል ገጥሟቸዋል።

 ለሁሉም ጊዜ አለው። ለረጅም ልቦለድም፣ ለግጥምም፣ ለአጭር ልቦለድም ጊዜ አለው። በየዘርፉ የሚታተሙ መጻሕፍት በየጊዜው ቢወጡም፣ አንዳንዶች ዘመን ያዘነብልላቸዋል፤ በለስ ይቀናቸዋል። ዘርፎቹ እየተገለባበጡ የአንባብያኑን ቀልብ ይገዙታል። ደራስያኑ ደጋሾች ናቸው። አንዱ ዘርፍ ይመጣል፤ ሌላው ይከተላል። አሁን ኢ-ልቦለድ ድርሰቶች ተሞሽረው፣ ሌሎች የሥነጽሑፍ ዘርፎች ሚዜ፣ አጃቢና ታዳሚ እየሆኑ ነው። ከኢ- ልቦለድ ዘርፎች ደግሞ ወግ ደምቆና ጎልቶ ፍሬ ሲያፈራ እየታየ ነው።

ከዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ በወግ ደራሲነት ይታወቁ የነበሩ ከያኒያን እጅግ ጥቂቶች ነበሩ። አሁን በዝተውልናል። የስብሀት ገብረእግዚአብሔርን ‹እግረ መንገድ› (በከፊል)፣ የኤፍሬም እንዳለን ‹እንጨዋወት›፣ የበዕውቀቱ ሥዩምን‹ከአሜን ባሻገር› (በከፊል)፣ የመሀመድ ሰልማንን ‹ፒያሳ ማሕሙድ ጋ ጠብቂኝ›፣ የበሃይሉ ገብረእግዚአብሔርን ‹ኑሮና ፖለቲካ›፣ የፍቃዱ ከበደን ‹ግጥም በጠመንጃ›ን እና ሌሎችንንም በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። ይህ ዘመን በኢትዮጵያ የሥነጽሑፍ ሰማይ ላይ የኢ-ልብወለድ – በተለይ የወግ – ጸሃይ የፈነጠቀበት ዘመን ነው ስንልም እውነታው በገሃድ ስለሚታይ ነው። ደራስያኑ በሚያስነብቡን የሕይወት ታሪኮች፣ ሀገረሰባዊ ትርክቶች፣ የጉዞ ማስታወሻዎች፣ ግላዊ አመለካከቶች እና ወጎች ደምቀናል፤ ራሳችንን አንብበናል፤ ስልጣኔያችንን መዝነናል፤ በወጎቻቸው ወጎቻችንን አሳምረናል። ዘመኑ የኢ-ልብወለድ (የሕይወት ታሪኮች፣ የወጎች፣ የመጣጥፎች….) ነው ካስባሉ ፊታውራሪዎች መካከል አንዱ ደግሞ ዳንኤል ክብረት ነው።

 የዳንኤል መጻሕፍት የ‹ወጎች› ስብስቦች ናቸው። በአንድ ወቅት በየጋዜጦች እና መጽሔቶች እንዲሁም በራሱ ጡመራ መድረክ (WWW.danielkibret.com) ላይ የተነበቡ ናቸው። (በነገራችን ላይ እንዲህ ዓይነቱ ልማድ ማለትም በየኅትመት ሰሌዳው ተነበው የነበሩ አጫጫር ድርሰቶችን አሰባስቦ፣ በአንድ መጽሐፍ ማሳተም አሁን አሁን እየተዘወተረ ያለ ቢሆንም፣ ልማዱ በፊትም ነበረ። ከሃምሳ ዓመት በፊት የተነበቡ አንዳንድ ዕውቅ መጻሕፍትም መጀመርያ በ‹አዲስ ዘመን›ና በዘመኑ በነበሩ ሌሎች ጋዜጦች ላይ በተከታታይ ተተርከው ነበረ። የነከበደ ሚካኤል ‹ታላላቅ ሰዎች›፣ የማሞ ውድነህ ‹የሁለተኛው ዓለም ጦርነት›፣ የእጓለ ገብረዮሀንስ(ዶክተር) ‹ከፍተኛ የትምሕርት ዘይቤ› በመጻሕፍት ከመቅረባቸው በፊት በየጋዜጣው የተነበቡ፣ በየመድረኩ የተደሰኮሩ እና በየሬዲዮ ፕሮግራሙ የተደመጡ ናቸው።)

 2. ወግ ምንድነው?

 በአጭሩ ልግለጸው። እንደሚታወቀው ወግ ጥዑም ጨወታ ነው። ወግ መነሻውን ትውስታ፣ ትዝታ እና ገጠመኝ የሚያደርግ የኪን ቤተኛ ነው። ወግ በራስ ላይ የተፈጸመ ወይም በሰው ላይ የተፈጸመ፣ በሆነ ሰሞን የታየ፣ የሆነ ጊዜ የተሰማ እና አዝናኝነቱ የጎላ የድርሰት ዘርፍ ነው። ወግ ኢ- መደበኛ ነው። ‹ክቡራንንና ክቡራት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች…› ዓይነት ‹ጥንቅቅ› ያለ አቀራረብ የሚከተል የዕለቱ የክብር እንግዳ ከመምሰል ይልቅ፣ ‹ምን ሆነ መሰላችሁ!› ብሎ፣ ቀለል አድርጎ፣ መጨነቅና መረበሽ ሳይሰማው ጉዳዩን ይጀምራል። ወይም ‹በነገራችን ላይ…› ብሎ ፈገግታ አጫሪ ወይም አሳዛኝ ሁነት ይጠቅሳል።

ወግ የቸከና የሰለቸ ትረካ አይደለም። ከተለመደው አቀራረብ ወጣ ስለሚል በፍጥነት ከመንፈስ ጋር ይዋሃዳል፤ ይዛመዳል፤ ይዋደዳል። አጫዋች ቢሆንም ተግሳጽ ቁርሱ፣ ምክር ልብሱ ነው። የሚቆረቆርለት፣ የሚቆምለት፣ የሚሞትለት ግብ አለው። ወርውሮ አይስትም። ሁሌም የሚያጸናው ወይም የሚንደው ግንብ አለ። ደበበ ሰይፉ ወግን፣ ‹ቢቆነጥጥ የሚያሳምም፣ ቢጎንጥ የሚያቆስል› ይለዋል። ይህን ያለው መስፍን ሃብተማርያም ባስነበበንና የበኩር መጽሐፉ በሆነው ‹የቡና ቤትሥዕሎች› መግቢያ ላይ ነው።

 3. ወግ እና አጥኚዎቹ

 እኛ ሀገር ወግ በቅጡ አልተጠናም። የጋሽ መስፍንን ሥራዎች ‹ወግ› የሚል ስያሜ ሰጥቶ፣ ከፈረንሳዊው የወግ አባት ከሞንታኝ ሥራዎች ጋር አነጻጽሮ፣ ወግ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ፣ ቅርጹና ይዘቱ ምን እንደሚመስል በማስተዋወቅ እና መንደርደርያ በማስጨበጥ ጋሽ ደበበ ሰይፉ ቀዳሚ እንደሆነ ይነገርለታል።

 ሌላው፣ በተደራጀ መልኩ ሥራዬ ብሎ ‹ወጎች› ተብለው የተፈረጁትን የአማርኛ መጻሕፍት ሲመረምር የማውቀው እንግዳ ወርቅ እንድርያስን ነው። የዲላ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆነውና አሁን የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ የሆነው እንግዳ ወርቅ፣ በ2003 ዓ.ም፣ ከ1976-2001 ዓ.ም ድረስ በታተሙ ወጎች ላይ ለሁለተኛ ዲግሪ ሟሟያ እንዲሆን የሠራው ጥናት አለ- አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሚገኝ። ወደፊት ወግ የብዙ ተመራማሪዎችን አዕምሮ ማንኳኳቱ አይቀርም የሚል እምነት አለኝ።

 የዳንኤል የ‹ወግ› መጻሕፍት ደግሞ ብቻቸውን መጠናት የሚችሉ ናቸው ብዬ አስባለሁ። ደራሲው ‹በዘርፉ ምን አመላለሰው?› ብሎ አለመጠየቅ አስቸጋሪ ነው። ለዚህም ነው፣ ስምንት የ‹ወግ› መጻሕፍት ሲያስነብበን የቆየው ይህ ደራሲ፣ በሥራዎቹ ጎልተው የሚታዩ ጥንካሬዎችና ድክመቶች መስተዋላቸው አይቀሬ ነውና፣ ጥቂት ነጥቦችን በማንሳት፣ስለአከያየን ስልቱ ፍንጭ በመስጠት ሌላውን ለመጎትጎት ምርጫዬ የሆነው። (ይህ መጣጥፍ፣ ዳንኤል ከወራት በፊት ሰባተኛ መጽሐፉን ማለትም፣ ‹የሰርቆ አደሮች ስብሰባ› በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ሲመረቅ፣ መድረክ ላይ ያቀረብኩትን ሃሳብ ለመጽሔት እንዲስማማ አድርጌ ያሰናዳሁት ነው።)

 4.የዳንኤል ክብረት ወጎች የአተራረክ ስልት

 የወግ አተራረክ ስልት፣ የጉዳዩ ባለቤት አጠገባችን ሆኖ፣ የወዳጅነትን ስሜት ፈጥሮ የሚያጫውት ነው። በትረካ ስልቱ ሰበብ ገና ከጅምሩ፣ ስሜትን ቆንጥጦ የመያዝ ወይም አዕምሮን ፈታ የማድረግ አቅም አለው። አይወሰሳብም። ስለሆነም ጉዳዩን በጨወታ፣

“የዳንኤል ሌላው የጽሑፎቹ መቀጃ ምንጭ ጉዞ ነው።በስምንቱም መጻሕፍቱ የጉዞውን በረከት ሳይሰስትአቋድሶናል። ጉዞው ወደ ውጭና ወደውስጥ ነው”

ወይም በጥቅስ፣ ወይም ደግሞ በግጥም፣ ወይም ይህን በመሰለ መነሻ ይጀምረዋል። ‹ወግ አውጊው ምን ሊለኝ ፈልጎ ነው? የሚል ጉጉት እና የጀመረውን ተረክ እንዴት አድርጎ ሊጨርሰው ይሆን? እንዲሁም ለመንደርደርያነት የተመረጠው ጨዋታ (ታሪክ/ገጠመኝ/ተረት/ቀልድ)፣ጥቅስ እና ግጥም መቋጫው ምን ይሆን?› የሚል ጥያቄ በአንባቢው ዘንድ እንዲጫር ያደርጋል።

የዳንኤል የወግ አተራረክ ስልትም የወዳጅነት የሚመስሉና የወግ ባህርይን የተከተሉ ናቸው። ጨወታዎች እና አጫዋቾች አሉት። በአብዛኛው ‹እንዲህ ሆነላችሁ›፣ ‹በአንድ ወቅት እንዲህ አጋጠመኝ›፣ ‹ያነብኩትን ላካፍላችሁ› ብለው የሃሳባቸውን ክብሪት የሚጭሩ ናቸው። መቅድመ ነገር እንዲሉ። መጀመርያ ላይ ብቻ ሳይሆን አልፎ አልፎ በየጽሑፎቹ መካከልም ብቅ ብለው ነገሩን የሚያዋዙት እነዚህ ተረኮች፣ ፍሬ ነገሩን ይበልጥ ተጨባጭ በማድረግ ጽሑፉን ያጎሉታል። የአንዳንዶቹ ጽሑፎች መግቢያ ከግላዊ ገጠመኞች የተቀዱ፣ የአንዳንዶቹ ከመጻሕፍት የተገኙ፣ የአንዳንዶቹ ደግሞ ደራሲው ከሰዎች አንደበት በጨዋታ መሃል ሲነገሩ የሰማቸው ናቸው። ወግን ወግ የሚያሰኘው አንዱ ገጽታውም ይህን የአተራረክ ስልት ተከትሎ መሄዱ ነው።

‹የሁለት ሐውልቶች ወግ› ውስጥ፣ ‹ንጉሥ ከመኾኔ በፊት ሰው ነበርኹ› የሚለው ጽሑፍ፣ ‹የተባበሩት ዐረብ ኤምሬትን መስርተው ለወግ ለማዕረግ ያበቋት ሼህ ዛይድ አልፎ አልፎ ተራ ሰው መስለው መኪናቸውን ራሳቸው እየነዱ ወደ አንድ መስርያ ቤት ይሄዱና የሰውን ችግር ይመለከቱ ነበር ይባላል›(ገጽ 8) ብሎ ከታሪክ የሚታወቅ ሁነት በመጥቀስ ንባቡን ሲቀድስልን፣ ‹እኛ የመጨረሻዎቹ› ላይ ደግሞ ‹ገናዧ› የሚለውን ጽሑፍ፣ ‹ከላስ ቬጋስ ወደ ፊኒክስ አሪዞና በዩ.ኤስ አየር መንገድ በመጓዝ ላይ ነበርኩ።› ብሎ የጉዞ ገጠመኙን በመንገር የነገሩን ድር መፍተል ይጀምራል። ‹የኔ ጀግና›ም፣ ‹አይጧ› በሚል ርዕስ የቀረበውን ጽሑፍ ሲጀምር፣ ‹ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኝ አንድ ማኅበር ጽሕፈት ቤት የተፈጸመ ታሪክ ነው። እንዲህ ልንገራችሁ› (ገጽ 25) እያለ የሰማውን በማስቀደም ሲቀጥል፣ ‹ጠጠሮቹ› ላይ ደግሞ፣ ‹የጃፓን እንቁራሪቶች› የሚለው ጽሑፉን ‹እነሆ ጃፓኖች እንዲህ ይተርታሉ› በማለት ወደ ጉዳዩ ተንደርድሮ ይገባል። ከገጠመኛዊ ተረኩ፣ ከታሪክ ማኅደሩና ከተረት ጎተራው ሌላ ጥቅሶችንና ሥነቃሎችን በማስገባትም ወጎች ይተረካሉ። ‹የሰርቆ አደሮች ስብሰባ› ላይ ‹ሀገር ማለት ሰው ነው፤እስኪ ሙት በለኝ› የሚለው ጽሑፉን፣ ‹ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገርሙኝ ዘፈኖች አንዱ ሀገር ማለት ሰው ነው የሚለው ነው።›(ገጽ 15) ብሎ ሲንደረደር፤ ‹የሁለት ሐውልቶች ወግ› ውስጥ ደግሞ ‹ጉንዳኗ› የሚለውን ጽሑፍ፣ ‹ስልጣኔ ማለት ለዝርዝር ጉዳዮች ትኩረት መስጠት ማለት ነው› ይላል፣ በሩስያ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የሰላ ሂስ በመስጠት የሚታወቀው እና ዶስቶቭስኪ በሚል የብዕር ስም የሚጽፈው ብሎገር› (ገጽ 111) በማለት ወደ ጉዳዩ ዘው ይላል። ‹እኛ የመጨረሻዎቹ› ላይ ደግሞ

“ዳንኤል ወጎቹን አሳምሮ ከሚቀዳባቸው ምንጮች አንዱ ተረት ነው። ተረት ያውቃል፤ ይወዳልም። ተረቶቹን የሚያስገባው በሀገር ውስጥ ብቻ የሚነገሩትን ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ ዓለማት የሚነገሩትንም ጭምር ነው። ተረቶቹ ከኢትዮጵያ፣ ከሶማሌ፣ ከህንድ፣ ከሜክሲኮ፣ ከሩቅ ምስራቅና ከሌሎች ቦታዎች የተገኙ ናቸው”

‹ባዶ አቁማዳ› በሚለው ጽሑፉ፣ ‹ነፍሱን ይማረውና ሀገራችን ካፈራቻቸው የቅርብ ዘመን ገጣምያን አንዱ ደበበ ሰይፉ ከአክሱም ጫፍ አቁማዳ የሚል ግጥም ነበረው (ገጽ 14)› ብሎ ከግጥሙ ጥቂት ስንኞችን ጠቅሶ ሲጀምር፣‹ኑ! ሀገሬን እናዋልዳት› በሚለው መጽሐፉ ውስጥ ያለው ይኸው ‹ኑ! ሀገሬን እናዋልዳት› ጽሑፍ ደግሞ፣ ‹አዋላጇ ጠፍታ ልጁም በእግሩ መጥቶ፤ እናቲቱ ሞተች ልጅዬውም ሞቶ (102)› በሚል ሀገርኛ ስንኝ የጽሑፉን በር ይከፍተዋል።

 እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት አርፍተ ነገሮች- የአንዳንዶች ርዕሳቸውም ጭምር – ገና ከጅምሩ ወግ አውጊው የሚያሳዝን፣ ወይም የሚያዝናና፣ ወይም የሚያስተምር፣ ወይም የሚያስደምም ጉዳይ ይዞልን እንደመጣ እንድንረዳ የሚያደርጉን ናቸው። የወጎቹ ድምቀትና ፍዘትም፣ነገሩን ለማጉላት በሚመርጣቸው ተረኮች የሚወሰንበት አጋጣሚም አለ። ደራሲው እነዚህን ተረኮች የሚጠቀመው የአተራረክ ስልቱን ለማሳመር ብሎ ብቻ ሳይሆን፣ ኋላ ለሚያነሳው ጭብጥ እገዛ እንዲያደርጉለትም ጭምር ነው። ዕገዛ ካላደረጉለት ወግ አውጊው ጉንጩን በከንቱ እንደሚያለፋ ደስኳሪ ይሆናል።

 5. የወጎቹ መገኛ ምንጮች

ወጎች ከተረት እና ከታሪክ፣ ከመጻሕፍት እና ከጉዞ፣ ከራስ እና ከሌላ የሕይወት ልምድ ይቀዳሉ። መፍለቂያቸውም መብቀያቸውም ይሄ ነው። ደራሲው መሰረቱን እነዚህ ላይ አድርጎ ይስፈነጠርባቸዋል። ሲስፈነጠር ደግሞ አንባቢውን ሩቅ አድርሶ ይመልሰዋል። ያልታየ፣ ያልተዳሰሰ፣ እንደዘበት ታይቶ የታለፈውን ዓለም አስጎብኝቶ ይመልሰዋል። የምናውቃቸውን ተረቶች፣ ጥቅሶች፣ በዕለት ተዕለት ቋንቋችን ውስጥ እንኳን ነገር ለማሳመር የምንጠቀምባቸውን አገላለጾች እንደ ምንጭነት ተጠቅሞ ነገሩን በተለየ መንገድ ያብራራልናል – በተብራራው ነገር መስማማት ወይም መቃወም የአንባቢው ፈንታ ቢሆንም።

 ዳንኤል ወጎቹን አሳምሮ ከሚቀዳባቸው ምንጮች አንዱ ተረት ነው። ተረት ያውቃል፤ ይወዳልም። ተረቶቹን የሚያስገባው በሀገር ውስጥ ብቻ የሚነገሩትን ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ ዓለማት የሚነገሩትንም ጭምር ነው። ተረቶቹ ከኢትዮጵያ፣ ከሶማሌ፣ ከህንድ፣ ከሜክሲኮ፣ ከሩቅ ምስራቅና ከሌሎች ቦታዎች የተገኙ ናቸው። እነዚህ ተረቶች ለወጉ መስፈንጠርያዎቹ ናቸው። አንዳንዶቹ ተረቶቹ ብቻቸውን ማንንም ሳይደገፉ ይቀማሉ። ጽሑፉ ተጀምሮ እስኪያበቃ ድረስ ከዐውዳቸው አይነጠሉም፤ ደባል ታሪክ አያስገቡም። እዚህ ላይ ‹የኔ ጀግና› ውስጥ ያለው ‹ንጉሡ ራቁታቸውን ናቸው› የሚለውን፣ ‹የሰርቆ አደሮች ስብሰባ› ውስጥ ‹ከተራራው ጀርባ ያለው ሰው› የሚለውን፣ ‹ኑ! ሀገሬን እናዋልዳት› ውስጥ ‹ተቀምጠው የሰቀሉት› የሚለውን የኢራቅ ኩርዶችን ተረት መነሻ ያደረጋቸውን በምሳሌነት ማንሳት ተገቢ ነው።

ዳንኤል ወጎቹን ለማጣፈጥ፣ እንዲህ ዓይነቱንም ቅመማት አብዝቶ በመጠቀም፣ ወጎቹን ያስኬዳቸዋል። ደግሞም በአንድ ጽሑፉ ብቻ ሁለት ሦስት ተረትና ምሳሌዎች፣ ገጠመኛዊ ተረኮች፣ ሥነቃሎች፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ታሪኮች፣ ከመጻሕፍት የተገኙ ሃሳቦችን መነሻ አድርጎ እያፈራረቀ ይጠቀማል። ታሪኮችንም ይከታተለላል፤ ይመረምራልም። ታሪኮቹ ደግሞ በሃይማኖት ድርሳናት እና በታሪክ መጻሕፍት የሚታወቁ ናቸው።

የዳንኤል ሌላው የጽሑፎቹ መቀጃ ምንጭ ጉዞ ነው። በስምንቱም መጻሕፍቱ የጉዞውን በረከት ሳይሰስት አቋድሶናል። ጉዞው ወደ ውጭና ወደውስጥ ነው። ወደ ሀገር ውስጥ የሚያደርጋቸው ጉዞዎች ገዳማትንና ቅርሶችን ለማስተዋወቅ የሚሞክሩና ሃይማኖታዊ ጽላሎት ያጠላባቸው ሲሆኑ፣ የውጭ ሀገር ጉዞዎቹ ደግሞ አንድን ነጠላ ጉዳይ በማየት መመሰጥ የሚወልዳቸው ‹ቁም ነገሮች› ናቸው። ዓለምን ዞሮአታል። በዙረቱ ውስጥ ሃሳቦች ቶሎ ቶሎ ይጸነሱለታል፤ ወይም ይጸነሱበታል። ቦታዎቹ ድረስ በመገኘት ስለከተማው ወይም ሀገሩ መተረክ ብቻ ሳይሆን፣ እቦታው በሄደ ጊዜ ስላጋጠመው ሰው፣ ሁነትና ኑረት በስፋት ጽፎልናል። ትኩረታቸውን ውጭ ሀገር ካደረጉት መካከል ‹የሁለት ሐውልቶች ወግ› ውስጥ ‹ግመል ጠባቂዎቹ በአቡዳቢ› የሚለውን (ገጽ 19)፣ ‹ጠጠሮቹ› ውስጥ ‹የአማልክት ምድር› (ገጽ 44) የተሰኘውንና ስለግሪክ አቴና የሚተርከውን እና ‹የኔ ጀግና› ውስጥ ‹መመረሽ፣ መፈረሽ፣ መደንበሽ› (ገጽ 115) የሚለውን መጥቀስ ይቻላል። ትኩረታቸውን ሀገር ውስጥ ካደረጉት የጉዞ ማስታወሻዎች መካከል፣ ‹ጠጠሮቹ› ውስጥ ያለውን ‹ይምርሃነ – ያልተጠናው ስልጣኔያችን›(ገጽ 100) የሚለውን ጽሑፍ መጥቀስ ይቻላል።

 6. የዳንኤል ስኬታማ የወግ መንገዶች

 ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታትመው ገበያ ላይ የሚውሉ መጽሔቶች እና ጋዜጦች የዳንኤል ድርሰቶች ከአንባብያን መወዳጃ እና አዲስ ግንኙነት መፍጠርያ ድልድዮች ያደርጓቸዋል። አለ ደራሲው መልካም ፍቃድ ጋዜጣዎቻቸውን እና መጽሔቶቻቸውን ያሟሹባቸዋል። አለምክንያት ይህ አልሆነም። ደራሲው በለዛና ቁምነገር አዘል ጽሑፎቹ ተከታይ ማፍራት እንደሚችል በማመናቸው ነው። ደራሲው ከእኛ ጋር ነው፤ እኛም ከእሱ ጋር – ቤተሰብ ነን፤ አትመጡልንም? ለማለት። ድርሰቶቹ ሰብሳቢ እንደሆኑ – የራቀውን እንደሚያቀርቡ፤ የተወጠረውን እንደሚያለዝቡ -ወይም ከዚህ ተቃራኒ የሆነ ስሜት መፍጠር እንደሚችሉ ስለሚያምኑ። 

ዳንኤል ወግን አክብሮ ይዞታል። ‹ወግ›ን አክብሮታል፤ ተከብሮበታልም። እነዚህ ተከብረው ያስከበሩትን ‹ወጎች› በማንበቡ የሚከስርም፣ የሚከስምም፣ የሚያፍርም ይኖራል የሚል እምነት የለኝም። ይልቁንስ የደራሲው ትጋትና ንቃት ‹ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ› ከአዕምሮ መቀርጨጭ ለማዳን፣ ማኅበረሰባዊ ሃላፊነት ለመወጣት ቆርጦ የተነሳ ይመስላል። በመገረም እና በመቆጨት፤ በሀፍረት እና በድፍረት ስሜት ተውጦ።

 ብዕሩን የሚያነሳው ደግሞ ሰውን ከፍ ለማድረግ ነው። ሰውነትን ለመቀደስ፤ ሰውነትን ንዑድና ክቡር ለማድረግ። ‹ወጎቹ› በአብዛኛው ስለማይሰለቹና ስለማይቸኩ፣ ‹ሰው ማለት ሰው የሆነ ነው ሰው የጠፋ ዕለት!› የተሰኘውን ብሂል ስለሚያስታውሱን፣ የተነገረን ወይም የተነገረልን ይመስለናል። ትልቁንም ትንሹንም በአንድ የማሰባሰብ፣ ለአንድ ግብ የማሰለፍ ዓላማ ያላቸው ይመስላሉ። ደራሲው ስለቤተሰብ መዋቅር መፍረስ፣ስለ ብሔራዊ ኩራታችን መውረድ፣ ስለአማርኛ ቋንቋ ተገቢ ትኩረት መነፈግ፣ ባህላችን ከባህር ማዶ ባህል ጋር ተደበላልቆ ስለፈጠረው ኪሳራ፣ ስለሙያዊ ውስልትና፣ ስለሙስና….በሚጽፍበት ጊዜ አንባቢውም ዙርያውን እንዲመለከት ይገፋፉታል፤ ትዝታውን ቁጭቱን ይቀሰቅሱበታል፤ ለሌላ ጽሑፍና ሃሳብ አሳልፈው ይሰጡታል።

ርግጥ፣ ‹ከፍ ያለ ንባብ አለኝ!› ብሎ ለሚያምን እና ሥነምግባራዊ ድርሰቶችን ማንበብ ለሚታክተው እነዚህን ወጎች መቀበል ይቸግረው ይሆናል። ሆኖም፣ ባልተወሳሰበ አቀራረብ፣ አክሮባት በማይሰሩ ቃላት፣ ባልተድበሰበሰ አገላለጽ ማለት የሚፈልገውን (እቅጩን) ስለሚል፣ ነገሮችን ገልብጦ ማሰብ ስለሚችል፣ አብዛኞቹ ጽሑፎቹ በየጊዜው የሚወሰዱ ክኒኖች መስለው ይታዩኛል። ፓራሲታሞል። እነዚህ ፓራሲታሞሎች ደግሞ ብቻቸውን መድኅን አይሆኑም። በሽታው እንዳይሰማን ድንዛዜውን ይደብቁልናል ያስታግሱልናል እንጂ የሁልጊዜ መድሃኒቶች አይሆኑም። መፍትሄ የሚሆኑት በተነሳው ርዕሰ ጉዳይ ተባባሪ አካላት እጃቸውን ሲያስገቡበት ነው። (ለምሳሌ ፈረንጅኛ ተጭኖናል፤ ቋንቋችን ተጨቁኗል የሚል ይዘት ካላቸው ጽሑፎቹ መካከል፣ ‹ኑ! ሀገሩን እናዋልዳት› ውስጥ ‹የተለመዱ የአማርኛ ስህተቶች እና መፍትሔያቸው› ዓይነት ጽሑፎቹ ለእያንዳንዱ ጋዜጠኛ የሚጋበዙ፣ ለአጭር ሥልጠናም ቢሆን የሚያነሳሱ (ምን ሆነን ነው፣ የኢትዮጵያ ብሮድ ካስት ሰርቪስ ምናምን የምንለው የሚያስብሉ) ናቸው ብየ አምናለሁ። በነገራችን ላይ ዳንኤል ክብረት በቅርቡ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባል በመሆን በቅርቡ ስለተሾመ፣ በቋንቋችን ላይ ያለውን እና ዕድሜ ልኩን ሲቆረቆርለት ያለውን የአማርኛን መሳከር ለመቀነስ ይህ ጥሩ አጋጣሚ ነው ብዬ አምናለሁ፤ ለውጥ ያመጣል ብዬም ተስፋም አደርጋለሁ!)

የዳንኤል ሌላኛው ጥንካሬ በወጎቹ ልማድን ለመፈተን የሚሄድበት መንገድና የሚከተለው ስልት ነው። ልማድን ለመፈተን ሲነሳ ማኅበረሰቡን ለማስበርገግና የቁጣ ቃል ከአንደበታቸው ለመስማት እሽቅድምድም ውስጥ አይገባም። ብዙውን ጊዜ ያዋዛል፤ ያባብላል። ስር የሰደደውን ልማድ እየተዘባበተበት ሊፈትነው፣ ፈትኖም ሊጥለው ሲፈልግ ዙርያችን ካለው ተራ ከሚመስል ነገር ይነሳል። ዛፉንም፣ አዕዋፉንም፣ ወንዙንም፣ ተራራውንም የሰው ልጅ የሚማርባቸው ሰሌዳዎች ያደርጋቸዋል። ሕመሞቻችን እንዴት ተጸንሰው እንዳደጉብን፣ አድገውም እንዴት ሰውነታችንን በሚፈልጉት መንገድ አዋቅረው እንዳነጹት ለመመርመር ሲያስብ ከስር ይነሳል። ከታች። ከአስተዳደጋችን። መሪውንም ተመሪውንም፣ አለቃውንም ምንዝሩንም የፈጠረው ማኅበረሰቡ – ፎክሎሩ፣ ሃይማኖቱ – ነው ለማለት። ‹የኔ ጀግና› ውስጥ ‹አይጧ› በሚለው ጽሑፍ ውስጥ፣ ለአይጥ ልዩ ፍራቻ ያላት አንዲት የጽዳት ሠራተኛ፣ አንድ ክፍል ውስጥ ሞቶ የተገኘውን አይጥ ለማስውጣት ስለገጠማት መረበሽ ሲተርክልን ይቆይና የሚከተለውን እናገኛለን።

 ‹እንዲህ እንደ ራሔል ያለ አይጥ የመፍራትና የመጥላት ዓይነት ልማድ ከልጅነት የሚቀረጽ እንጂ እንደ ሐዋርያው ታዴዎስ እርሻ ዕለቱን በቅሎ፣ ዕለቱን የሚታጨድ አይደለም። ስንሰማቸው በኖርናቸው ተረቶች፣ ታሪኮች፣ አባባሎች አማካኝነት ተጸንሶ፤ በባህላችን ውስጥ ነገሮች በያዙት አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ቦታ ረዳትነት አድጎ፤ ሌሎች ቀደምቶቻችን ሲያደርጉት ባየነው፣ በቀሰምነውና በወረስነው የአኗኗር ዘይቤ በኩልም ጎልብቶ ለወግ ማዕረግ የሚበቃ ነው።›(ገጽ 27)

 የዳንኤል ጽሑፎች አነጻጻሪ ናቸው። ትናንትን ከዛሬ። ሀብታሙን ከድሃ። ጨለማውን ከብርሃን። ውስጡን ከውጭ። ደለሉን ከገደል። እነዚህን ነገሮች አነጻጽሮ የሚያቀርባቸው ‹እንዴት ነው፣ አንድ ኢትዮጵያዊ መኖር ያለበት? እንዴትስ ነው ከገባበት የሃሳብ ድህነት መውጣት ያለበት?› ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ነው። በየሄደበት ሀገሩን ተሸክሞ እየዞረ ያለ የሚመስለው ይህ ደራሲ፣ እግሩ ከኢትዮጵያ በወጣ ቁጥር፣ መጻሕፍትን በመረመረ ቁጥር፣ አንድ ተረትና ምሳሌ ባገኘ ቁጥር፣ አንድ ቃል ብቻውን የተሸከመው ምስጢር በተረዳ ቁጥር (ኡቡንቱን፣ ሪዳ ሐጉካይ-ሻ፣ አል ሙሰማህንና ሌሎችም የአፍሪካውያንና የሩቅ ምስራቅ ቃላት የያዙትን ፍቺ ልብ ይሏል?) ብዕሩን አንስቶ ክፍቱን ለመሙላት፣ ጉድለቱን ሸፍኖ ደለሉን ለመሙላት ‹ሀገራዊ ግዴታውን› ሲወጣ ይታየኛል። ‹ገና ነን፤ ገናና ነን የምንለውን ያህል አይደለንም፤ አስተዳደጋችን የተንሻፈፈ ነው፤ የአስተዳደር ብቃታችንና ኅብረተሰቡን የማረቅ ዘዴያችን፤ ሀገርን የመምራት ችሎታችን ወደኋላ የቀረ ነው፤ ራሳችን የምንገልጽበት መንገድ የተጋነነ ነው፤ ታመናል፤ ተኝተናል፤ ተዘናግተናል፤ ተዘግተናል፤ በመሃላችን አጥር ለማጠር፣ ግንብ ለመገንባት እንጂ ድልድይ ለመዘርጋት አልታደልንም፤ ራሳችንን እልለውጥንም የሚሉ ድምጾች በየጽሑፎቹ ውስጥ ጎልተው ይሰማሉ። እንደየርዕሰ ጉዳዩ ራሳችንን አካሚ፣ ወይም ታካሚ፣ ወይም አስታማሚ ወይም አሳማሚ ሆነን እናገኘዋለን። እንዲህ ያለውን ጭብጥ አንስቶ ለውይይት፣ ለተሃድሶ እና ለለውጥ በማነሳሳቱ ደግሞ የብዙዎቹን በር አንኳኩቶ እንዲገባ አስችሎታል ብዬ አምናለሁ።

 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ(ዶክተር)፣ በአንድ መድረክ ላይ፣ በ‹የሁለት ሐውልቶች ወግ› መጽሐፍ ውስጥ- ‹የላጭ ልጆች› በሚለው ጽሑፍ ውስጥ የሚገኝን ሃሳብ ጠቅሰው – ለደራሲው ያላቸውንም አክብሮት መግለጻቸው ይታወሳል። ላስታውሳችሁ።

‹ርግጥ የአገራችንን እድገት የማይወዱ የውጭ ጠላቶች ድሮም ነበሩ፤ ዛሬም አሉ፣ ወደፊትም ይኖራሉ። ዕድገታችን የሚያማቸው፣ ስልጣኔያችን የሚያቅራቸው፣ ሰላማችን የሚቆረቁራቸው፣ ኅብረታችን የሚያዞራቸው ይኖራሉ፣ አሉም። ነገር ግን እኛ ካልተባበርናቸው ብቻቸውን አንዳች ነገር አያደርጉም። ዛፎች መጥረቢያ ጨረሰን ምን እናድርግ ብለው በጠሩት ስብሰባ ላይ ሽማግሌው ዛፍ፣ ‹ራሳችንን የመጥረቢያ እጄታ ኾነን ያስጨረሰነው ራሳችን ነን። መጥረቢያ እኛ እጄታ ካልኾንነው ብቻውን ምን ያድርግ ነበር› ብለው የተናገሩትን እዚህ ላይ ማንሳት ያሻኛል።› (ገጽ 63)

7.የዳንኤል ክብረት ወጎችና ውስኑነታቸው

 እንዲህ እንደዳንኤል አከታትሎ የሚጽፍ ደራሲ ውስኑነት ይጠፉታል ማለት ዘበት ነው።ያም ሆኖ እንደኔ መረዳት በየጊዜው ዕድገት የሚያሳይባቸው ስልቶችና የሃሳብ አገላለጽ መንገዶች አሉት።ለምሳሌ በፊት ሲጽፍ ‹አንድ ወዳጄ እንደነገረኝ›፣ ‹አንድ ትልቅ ባለስልጣን እንዲህ አድርጎ፣ እንዲህ ተሳስቶ በማለት፣ ትችቱን ለሚመለከተው ሁሉ ተብሎ እንደሚጻፍ ዓይነት፣ ሾላ በድፍን ያደርገው ነበረ። ተከሳሹና ተወቃሹ ማን እንደሆነ ግልጽ አድርጎ ስለማይጠቁመን፣ ተወቃሹ ለመሻሻል ዕድል አይሠጡትም። እንዲህ ያለውን አካሄድ አሁን አሁን የተወው ይመስላል። ‹ስማችሁ የለም› የሚለው መጽሐፉ በቂ ምሳሌ ነው።

አጥፊዎቹ፣ ቤተክርስቲያኒቱን የሚያምሱት እነማን እንደሆኑ በግልጽ ተቀምጠዋል። በሥራዎቹ ውስጥ አልፎ አልፎ ሳይተረጎሙ የተቀመጡ የግዕዝ ቅኔዎች መኖራቸው ስህተት ቢሆንም፣ በተለያዩ ሀገራት እንደተጻፉ ለመጠቆም ከእያንዳንዱ ጽሑፎቹ መጨረሻ ላይ እንደጠቀሰው ሁሉ በየመጽሐፎቹ መግቢያ ደግሞ በምን ምክንያት ወደ ባሕር ማዶ ተሻግሮ ሊጽፋቸው እንደበቃ መነሻ ሃሳብ ባይሰጠንም እነዚህን ድክመቶች የጎሉ ናቸው ለማለት አልደፍርም። ሁለት የጎሉ ክፍተቶች ግን ታይተውኛል። አንዱ የድግግሞሽ ችግር ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ አንደኛው ዘርፍ ከሌላው ጋር ያለውን የልዩነት ድንበር እንዲታወቅ ያለማድረግ ውስንነት ነው። ዳንኤል አንዴ ያስነበበንንና በሌላ ጽሑፉ ውስጥ ያገኘነው ሃሳብ፣ ወይም ትችት፣ ወይም ተረክ መልሶ በሌላ ጊዜ ደግሞ ይተርክልናል። ይህ የሚሆነው ተረኩን በመውደድ ቀደም ሲል በሌላ አጋጣሚ መጻፉን በመርሳት ሊሆን ይችላል። መልሶ በሌላ ጽሑፍ ውስጥ አንድ ሃሳብ የምናገኘው ቀደም ሲል ተርኮት የነበረውን ለመናድ ወይም፣ በተሻለ መንገድ ለማብራራት ቢሆን ምንም አልነበረ። ግን ራሱ ነው። አንድ ሁለት ምሳሌ ልጥቀስ። በቋንቋ አጠቃቀም ዙርያ ሲያነሳም ምሳሌዎቹ ከዚህ ቀደም ራሱ አብራርቶ የነገረን ይሆናሉ።

 በተለይ በተክለጻዲቅ መኩርያ የተጻፈው፣ ‹ዐጼ ቴዎድሮስና የኢትዮጵያ አንድነት› በተደጋጋሚ ይነሳል። ቴዎድሮስ ገልጾ ያልጨረሳቸው፣ እያደር አዲስ የሆኑበት ንጉሥ ይመስላሉ። እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ዘመናቸውም እንደሰሌዳ ይነበቡታል። ጥቂቶችን መዘርዘር ይቻላል። ‹የሁለት ሐውልቶች› ወግ ውስጥ ብቻ ሦስት ጽሑፎች አሉላችሁ። ‹ሰማኸኝ› (ገጽ 41)፣ ‹50 ሠሪ…ደንጓሪ…አነዋሪ› (ገጽ 101) እና ‹የመቅደላው ጌታ› የሚሉ ጽሑፎች

“በአንድ ብሔራዊ ጀግና ሕይወት ማሳያነት፣ ወጎቹን እየደጋገመ እንደሚቀምርልን ሁሉ፣ የወጎቹ አተራረክ ስልትም እየለመድናቸው ስለመጣን፣ የመጀመርያውን አንቀጽ በማንበብ ብቻ፣ ሙሉ የጽሑፉን መንፈስ እንረዳና መታከት ውስጥ ይከተናል። ስለሆነም ከላይ ከተጠቀሱት ስልቶች በተጨማሪ ሌሎች መንገዶች መቀየስ ይኖርበታል።”

(ገጽ 163)። ‹ጠጠሮቹ› ውስጥ ‹ካልሞትክ አይገሉህም›(ገጽ 269)፣ ‹የኔ ጀግና› ውስጥ ‹ቀን ሲደርስ ዓምባ ሲፈርስ› የሚለውን (ገጽ 11) ብንመለከት፣ እንደገና እዚሁ መጽሐፍ ውስጥ ‹እርሻውን ማን ያርመው› (ገጽ 73) እና ‹ለጠላት አንድ ሺህ፣ ለወዳጅ አንድም› በሚል ርዕስ (ገጽ 98) የቀረበውን ጽሑፍ፣ ‹የሰርቆ አደሮች ስብሰባ› ውስጥ ደግሞ ‹የደጃች ውቤ ልቅሶ(ገጽ 22)›ን ለአብነት ያህል ማንሳት ይቻላል። ዘርዝረን አንጨርሳቸውም። ሲጠቃለል አጼ ቴዎድሮስ የዳንኤል ጽሑፎች አዝማች ናቸው። ይመላለሱብናል። ይህ ድግግሞሽ ደግሞ፣ ይህን ነገር ቀደም ሲል አላነበብኩትም እንዴ የሚል ስሜት ያመጣል፤ መሰላቸትን ይወልዳል። ከእዚህ በአንድ ብሔራዊ ጀግና ሕይወት ማሳያነት፣ ወጎቹን እየደጋገመ እንደሚቀምርልን ሁሉ፣ የወጎቹ አተራረክ ስልትም እየለመድናቸው ስለመጣን፣ የመጀመርያውን አንቀጽ በማንበብ ብቻ፣ ሙሉ የጽሑፉን መንፈስ እንረዳና መታከት ውስጥ ይከተናል። ስለሆነም ከላይ ከተጠቀሱት ስልቶች በተጨማሪ ሌሎች መንገዶች መቀየስ ይኖርበታል።

 ሌላው የዳንኤል ውስንነት፣ አንዱን ዘርፍ ከሌላው ዘርፍ ጋር አደባልቆ የማየት ችግር ነው። እንደሚታወቀው ወግ ከመጣጥፍ ይለያል። ከአጭር ልቦለድም ይለያል። አንዱ አንዱን አይመስለውም፤ አይወክለውምም። የዳንኤል ክብረት መጻሕፍት ‹ወጎች› በሚል ርእስ ተቀንብቦ ብናነብም፣ ‹ወጎቹን› ለመቋደስ እዘረጋልን ማዕድ ስር ስንሰበሰብ ግን፣ የወግ  ደራሲ ብቻ እንዳልሆነ እንረዳለን። ደራሲው መጣጥፉንም፣ ወጉንም፣ አጭር ልብወለዱንም በአንድ ስያሜ ይጠራቸዋል። ይህ መሆኑ ደግሞ ለአንባቢውም ለሙያተኛውም ድንግርግርታን ይፈጥራል። ምነው ቢባል፣ አንዱ ዘርፍ በተሰፈረበት ሚዛን ሌላው አይሰፈርም። ወግ ተራኪ ነው። ግላዊ አተያይ ነው። መጣጥፍ ደግሞ የደራሲውን ምልከታ፣ ትዝብት እና የመገንዘብ አቅም የምንመረምርበት ሚዛን ነው። (ለምሳሌ ይህ ጽሑፍ – ዳንኤል ክብረትና የ‹ወግ› መጽሐፎቹ

 (ወግና ወግ አውጊነት) በሚል ርዕስ የቀረበው – መጣጥፍ ነው እንጂ ወግም አጭር ልቦለድም አይደለም። አጭር ልቦለድ የደራሲው ፈጠራ ነው። በድርሰቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት ገጸባሕርያትም በአብዛኛው ደራሲው የሚፈጥራቸው እንጂ ከገሃዱ ዓለም እንደፎቶግራፍ ተለቅመው የተገለበጡ አይሆኑም። ዳንኤል ከጻፋቸው ድርሰቶች መካከል በመጣጥፍ ዘርፍ ሊመደቡ ይገባቸዋል ከምላቸው መካከል ጥቂቶችን ልጥቀስ። ‹የሁለት ሐውልቶች ወግ› ውስጥ ‹በሲኦል በኩል ወደ ገነት› የሚለው እና ‹No Future With Out Forgiveness› የሚለውን መጽሐፍ መነሻ በማድረግ የጻፈውን፣ ‹የሰርቆ አደሮች ስብሰባ› ውስጥ ‹ሕዝብን የሚያዳምጥ መንግስት፤ መንግስትን የሚያዳምጥ ሕዝብ› የሚለው እና በሕዝብና መንግስት መካከል የሚመመሰረተው ትዳር ምን መምሰል እንዳለበት የሚጠቁመውን፣ ‹ኑ! ሀገሬን እናዋልዳት› ውስጥ ደግሞ ‹ቃኘው ሻለቃ፡- የሚፍግ እሳት፣ የማይጠፋ ፋና› የሚለው እና ለደቡብ ኮርያውያን በጦርነት ጊዜ ስለዋልንላቸው ውለታ የሚተርከው ጽሑፍ፣ ‹የኔ ጀግና› ውስጥ ደግሞ፣ ‹የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ስንት ሰዓት ላይ ነው›የሚለው ጽሑፍ፣ ‹ጠጠሮቹ› ውስጥ ‹ይምርሃነ – ያልተጠናው ስልጣኔያችን› የሚለው መጣጥፍ ነው እንጂ ወግ አይደለም። ጽሑፉ ጀምሮ እስከሚያበቃ አካባቢውን ማስጎብኘት ነው። ‹ከአዲስ አበባ በባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ላሊበላ በኩል ወደ አክሱም የሚወስደውን የተለመደውን የቱሪስቶች የጉዞ መስመር ተከትለን ነበር የተጓጓዝነው (ገጽ 100) ወግ ከሚባሉት መካከል ደግሞ፣ ደራሲው ራሱ በመጽሐፍ ርዕስነት ያስቀመጣቸው ‹የሚከራዩ አማት›ን፣ ‹ጠጠሮቹ›ን፣ ‹እኛ መጨረሻዎቹ›ን፣ ‹የኔ ጀግና›ን፣ ‹ኑ! ሀገሬን እናዋልዳት›ን ለምሳሌነት ማንሳት ይቻላል። ሁሉም ተራኪ አላቸው። እንዲህ ሆኜ፣ እንዲህ ደርሶብኝ፣ እንዲህ ሲባል ሰምቼ የሚሉ ናቸው። ሁነቶቹ ደራሲው የፈጠራቸው አይደሉም። የሆኑ ናቸው። ብንፈልግ አናጣቸውም። ደግሞ በትረካ ስልታቸው ወዝ አላቸው። አይቆረቁሩንም፤ አይቆረፍዱንም።

“እርግጥ አንዳንድ ጽሑፎቹ ራስን መምህር ሌላውን ደቀመዝሙር የማድረግ ስሜት ያላቸው ይመስላሉ። የቤተክህነት ሰው በመሆኑ ይሆናል – የሰባኪነት፣ ማኅበረሰብን አገልጋይነት በሥራዎቹ ጎልተው የሚሰሙ ድምጾች የሚሆኑት። አብዛኞቹ ግን ተማሪ ሲሆን፣ እንዴት ሆነ ብሎ ሲጠይቅ፣ ቀደምት ደራስያን፣ ሊቃውንት እግር ስር ውሎ ሲማር እናየዋለን”

አጫጭር ልቦለዶች ናቸው የምላቸው አሉ። ዳንኤል በስምንቱም መጻሕፍቱ አጫጭር ልቦለዶቹን አዳብሎ አውጥቷል። እሱ ይህን ስያሜ ቢነፍጋቸውም። ቢያንስ በአንዱ መጽሐፍ ውስጥ ሦስት አራት አጫጭር ልቦለዶችን አናጣም። አብዛኛዎቹ አጫጭር ልቦለዶቹ ደግሞ አሊጎሪያዊ ናቸው። አሊጎርያዊ ልቦለዶች እኛ ሀገር ውስጥ በቀደምት ደራስያን ሥራዎች ውስጥ እንጂ በቅርብ በምናነባቸው ድርሰቶች ውስጥ እንደልብ የምናገኛቸው አይደሉም። አሊጎሪ አጫጭር ልቦለዶች እንስሳትን፣ ግኡዝ አካላትን፣ ዕጽዋት አራዊትን በአጠቃላይ የማይናገሩ ቁሶችን እና ፍጥረታትን በማናገር ሞራላዊ መልዕክት መስጠት ሥራቸው ነው። ገጸባሕርያት ሰውን የሚወክሉ፣ ለሰው ልዕልና ጥብቅናም የቆሙ  ይሆናሉ። ዳንኤል አሊጎሪያዊ ልቦለድ የመጻፍ ጉልበት አለው። በዚህ ዘርፍ ከደረሳቸው አጫጫር ልቦለዶች መካከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፣ ለመጽሐፎቹ መጠርያነት የተጠቀመባቸው ‹የሁለት ሐውልቶች ወግ› ተብሎ የሚጠራው ጽሑፍ፣ ፋሽስት ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ ተወስዶ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ የተተከለው ሐውልት እና ከጣልያን የመጣው ሐውልት አጠገብ ወድቆ የሚገኘው ረዥም ሐውልት ናቸው ሲነጋገሩ የምንሰማቸው። ‹የሰርቆ አደሮች ስብሰባ› ስንመለከትም በአንድ ትልቅ ስብሰባ አዳራሽ ውስጥ በሌብነት የሚታወቁ ገጸባሕርያት፣ ስለሌብነት በሚሰጡት ትንታኔ ላይ የሚሳለቅ አጭር ልቦለድ ነው። ‹ስማችሁ የለም› የሚለው ጽሑፍ ደግሞ ሰማያዊ ዙፋን ላይ ኢትዮጵያውያን የሃይማኖት ሰዎች ለፍርድ ቀርበው ሲፈረድባቸው ስላሰሙት ጉምጉምታ የሚተርክ ነው።

 ሦስቱም- ወግ፣ መጣጥፍ፣ አጫጭር ልቦለድ – በአቀራረብ ይለያሉ። አንድ የሚያደርጋቸው በዝርው ቋንቋ መደረሳቸው ነው። ዳንኤል በሦስቱ መካከል ድንበር ማበጀት አለበት ብየ አምናለሁ። ሦስቱንም በአንድ መጽሐፍ አካትቶ ማስነበብ የተለመደ ቢሆንም፣ የትኛው እውነት የትኛው ፈጠራ መሆኑን አንባቢ መረዳት ይቸግረዋል። ምንም እንኳን፣ ሁሉም ለአንድ ተልዕኮ የተሰለፉ፣ ምግባራዊ የሆኑ እና ሰውን ማረቅ ላይ የሚያተኩሩ ቢሆኑም፣ድንበር ማበጀቱ ግን አስፈላጊ ነው።

 8.ማጠቃለያ

 በአጠቃላይ የዳንኤል ክብረት ስምንቱ — የወግ፣ የመጣጥፍ እና የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ –መጻሕፍት ለማኅበረሰቡ ግድ ካለው ደራሲ አብራክ የተከፈሉ ለመሆናቸው የሚያጠያይቅ አይደለም። በእርግጥ አንዳንድ ጽሑፎቹ ራስን መምህር ሌላውን ደቀመዝሙር የማድረግ ስሜት ያላቸው ይመስላሉ። የቤተክህነት ሰው በመሆኑ ይሆናል – የሰባኪነት፣ ማኅበረሰብን አገልጋይነት በሥራዎቹ ጎልተው የሚሰሙ ድምጾች የሚሆኑት። አብዛኞቹ ግን ተማሪ ሲሆን፣ እንዴት ሆነ ብሎ ሲጠይቅ፣ ቀደምት ደራስያን፣ ሊቃውንት እግር ስር ውሎ ሲማር እናየዋለን። ከምንም በላይ ስምንቱንም መጽሐፎቹን ስናነብ ቶሎ በአዕምሮአችን የሚመጣው እና የማይካደው ነገር ዳንኤል ሃላፊነት የሚሰማው ደራሲ መሆኑ ነው።

 የዳንኤል ክብረት ወጎች ሀገርን፣ ኢትዮጵያን መውደድ ብቻ ሳይሆን፣ ሰውን መውደድ ለሰው መኖርን የሚሰብኩ ናቸው። ይለውጣሉ። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው፣ የዘመመውን እንዴት ማቅናት፣ የደበዘዘውን እንዴት ማፍካት፣ የተፍረከረከውን እንዴት ማጽናት፣ የታመመ አመላችንን ደግሞ እንዴት ማከም እንዳለብን የሚያሳስቡ ደወሎች ናቸው በማለት ምዘናዬን ልቋጨው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top