ዘባሪቆም

የፍቅር ነገር

በማዣንግ ብሔረሰብ አንድ ለአቅመ-አዳም የደረሰ ወጣት ለትዳር አጋር ትሆነው ዘንድ የፈቀዳትን ለማግባት በመጀመሪያ ሽማግሌ መላክ አያስፈልገውም። ወደ ወጣቷ ቤተሰቦች ቤት በመሄድ በቤታቸው አጠገብ መኝታውን አንጥፎ ይቀመጣል። እህል ውሃ ሳይቀምስ እዚያው ለሦስት እና ለአራት ቀን ይቆያል።

ይህን የሚያደርገው ለወጣቷ ያለውን ጥልቅ ፍቅር ለመግለፅ እንደሆነ ይታመናል። ወጣቷ ሁኔታውን አይታ እሷን ብሎ፣ እሷን አፍቅሮ፣ እሷን ፍለጋ እንደመጣ ስለምትረዳ እሱ እያያት ምንም ነገር ወደ አፏ አትወስድም። እህል አትበላም ውሃ አትጠጣም።

 ምንም እንኳን እሱ ውጭ ተቀምጦ አልበላም አልጠጣም ትበል እንጂ ወደ ጓዳ ገባ ብላ መጉረሷ አይቀርም። በዚህ መሐል የወጣቷ አባት የወጣቱ አመጣጥ ምን ፍለጋ እንደሆነ ስለሚገባቸው ለእሷ ያለውን የፍቅር ጽናት የመንፈስ ጥንካሬውን ብርታቱን መፈተን ይጀምራሉ።

 የእሷ አባት አፈቀርኳት ያለውን ወጣት ገጀራ ያቀርቡለት እና ለምንጣሮ ወደ ጓሮ እንዲሄድ ያዙታል። ወጣቱ ሳያንገራግር ገጀራውን ይዞ አባቷን ይከተላል። ምንም እንኳ ምግብ ሳይበላ ቢቆይም ርቦኛል ማለት አይችልም። ባለው አቅሙ የታዘዘውን ይጀምራል። የገጀራ አያያዙም የሥራ ፍላጎቱና ችሎታው በወጣቷ ወገኖች ይመዘናል። የሥራው ውጤት አስደሳች ከሆነ፣ ጉብዝናው ከተረጋገጠ እህል ውሃ በፍቅረኛው አማካኝነት በድብቅ ይላክለታል። እሱ ግን በአቋሙ ይጸናል። አይበላም አይጠጣም። የጀመረውን ምንጣሮ እስኪያጠናቅቅ ድረስ የተላከለትን አይቀምስም።

ሥራውን ሲጨርስ ቀደም ብሎ ካነጠፈው መኝታ ላይ ይቀመጣል። በመጨረሻም ከጥቂት ቀናት በኋላ ይፈቅድለት እና በጓደኞቹ አማካኝነት ያፈቀራትን ወጣት ይዞ ይሄዳል። በፍቅረኛው አናት ላይም ተለቅ ያለ ቅቤ ይኖራል። ይህም መተጫጨታቸውን ወይም በቃልኪዳን መተሳሰራቸውን የሚያሳይ ነው።

በብሔረ-ሰቡ ቅቤ የተቀባች ልጃገረድ ትከበራለች። ሌሎች ወንዶች ቀና ብለው አያዩዋትም። … የእሱ እንደሆነች ከተረጋገጠ በኋላ ወደ ወላጆቿ ቤት በመመለስ ሽማግሌ ይላካል። ቤተሰቦቿ ይፈቅዱ እና ጋብቻቸው ይፈፀማል።

 ለጥሎሽ ጦር፣ ጨሌ እና ጠገራ ወይም መፍለጫ መስጠት የተለመደ ነው። አግቢው አቅም ከሌለው የቅርብ ጓደኞቹን ይጠይቃል። እነሱ ከሌላቸው ፈልገው በማምጣት ይሰጡታል። የለንም ብለው አይመልሱትም። አያሳፍሩትም።

ከደቡብ ፕሮፋይል

ጅራፍ እና ጭብጨባ

አንድ ጥፋት ያጠፋ ወይም የሰረቀ፣ የደበደበ ሰው በድንገት ባለበት ቦታ ክስ ይመሰረትበታል። እዚሁ አዲስ አበባ ወደ ኋለኛው ዘመን አንድ ከሳሽ ያመለክታል። ያዙልኝ ይላል። በአከባቢው የተገኘው ሰው ይከባል። በአካባቢው ከተገኘው ሰው አንዱ የዳኝነቱን ሥራ ይሰራል። ክሱን አዳምጦ ይፈርዳል። የፍርድ ሂደቱ በጣም ቀላል ነው።

ብዙ ጥያቄዎች ይደረግላቸዋል። ከሳሽም ተከሳሽም ከተደመጡ በኋላ ዳኛው ፍርድ ይሰጣል። የተሰበሰበው ህዝብ በማመዛዘን ድጋፉን በጭብጨባ ይገልፃል። በደመቀ ሁኔታ የተጨበጨበለት የፍርድ ውሳኔ ይፀናል። ፍርዱ እንደ ጥፋቱ ዓይነት ይሆናል። እስከ ስቅላት ቅጣት ድረስ ሊሆን ይችላል። የመጨረሻው የሞት ፍርድ በንጉሡ መጽደቅ አለበት።

የመጨረሻውን ፍርድ ሰጪ እሳቸው ይሆናሉ። በጅራፍ መገረፍ ግን ከመቅፅበት እንደተፈረደ እዚያው ህዝቡ እንደከበበው ተፈፃሚ ይሆናል።

 አንድ ቀን ከቀትር በኋላ አንዱን ወጣት እንዴት እንደገረፉት አስታውሳለሁ። አንድ ተሰሚነት ያላቸውን አለቃ ተተናኩሎ የነበራቸውን ደረጃ አላወቀም ነበረና ክብር በመንካቱ የፈፀመው ወንጀል ተብሎ ተበዳዩ በንዴት እና በብስጭት በከፍተኛ ድምጽ በመጮኽ ብዙ ህዝብ ይሰበሰባል። ፍርዱን እንዲሰጥም የመረጠው ዳኛ አንድ ለማኝ ነበር። አርባ ጅራፍ ፈረደበት። ለግማሽ ሰዓት ያህል ተቀጠቀጠ። ለማመን የሚከብድ ነው። በዚያች አጭር ጊዜ ውስጥ እዚያው ተከሶ እዚያው ተፈረደበት። እንዳልነበረ ሆነ።

 ትርጉም ተስፋዬ መኮንን ባይለየኝ

ከ“ቀይ አንበሳ” መጽሐፍ

ርኛ ወሬዎች

ከሞተው በሬ፣

ያጨድነው ፍሬ!

በዛሬው የወርኛ ወሬዎቼ የወርሃ ሃምሌ (ጁላይ) ወግና ክስተቶችን ላስታውስ። በሃገረ አሜሪካ ጁላይ 4 ታላቅ የነፃነት ቀን በዓል ነው። ይሁንና ይሄው ታሪካዊ ቀን ጁላይ 4 አሜሪካ ሁለተኛውን ፕሬዝዳንቷን ጆን አዳምስን፣ ሶስተኛውን ፕሬዝዳንት ቶማስ ጀፈርሰንና አምስተኛውን ጀምስ ሞንሮን በሞት ያጣችበት ክፉ ቀን ጭምር ነው። በተለይ ጆን አዳምስና ቶማስ ጀፈርሰን በተመሳሳይ አመት (እ.አ.አ. በ1926) በሰዓታት ልዩነት መሞታቸው አጋጣሚውን ይበልጥ አስገራሚ ያደርገዋል። ከዚህ ባለፈ ጁላይ አሜሪካ እስካሁን በሞት ካጣቻችው 38 ፕሬዝዳንቶቿ ውስጥ 7ቱን በመውሰድ ከወራት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። ያም ሆኖ አሜሪካና አሜሪካውያን ያጧቸውን ጀግኖችና አርበኞች ሳይሆን ያገኙትን ነፃነትና አንድነት፣ ካለፉ መሪዎቻቸው ይልቅ ለትውልድ ጥለውት ያለፉትን ህግና ስርዓት በመውረስ ጁላይን ከመግቢያው እንደንጉስ ተንከባክበው ይቀበሉታል፣ ያከብሩታል። ሰሞኑን ባገራችን እየታየ ላለው ለውጥ ይህ አንድ ጥሩ ተሞክሮ አይሆንም ይላሉ?

 የጁላይ ወር በኛ በኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ዘንድም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ወቅት ነው። ታላቁ ዓመታዊ የስፖርት ፌስቲቫል። ይህንን ጽሑፍ ስከትብ ወደዘንድሮዋ አዘጋጅ ዳላስ ቴክሳስ ጉዞዬን ጀምሬያለሁ። እዚያ ስደርስ የሚገጥመኝን ከዝግጅቱ መልስ ለማጋራት እሞክራለሁ። ለዛሬ ከባለፈው የሲያትል ትዝታዬ እነሆ:-

 “ባንዲራ ከኛ ወኔ ከነሱ”

 ሲያትል በተካሄደው ዓመታዊ የኢትዮጵያውያን የስፖርት ሳምንት ወዳጄ በውቀቱ ስዩም የግጥም መጽሐፉን ሲሸጥ አገኘሁት። መጽሐፉን ለማሻሻጥ በያዝኩት ጥሩምባ ለፍፌ ህዝብ ከሰበሰብኩ በኋላ አንድ ወጣት በጄ ከያዝኩት መፅሃፍ ይልቅ “ጥሩምባውን ትሸጠዋለህ?” ብሎ ሲጠይቀኝ በውቄ ባለመስማቱ ብፅናናም ነገሩ ስላስፈገገኝ ቀስ ብዬ በጆሮው ስነግረው “ንባብ አይበሉን እንጂ ለመንፋትማ ማን ብሎን!” ሲል ያፈንኩትን ሳቅ ራሱ አስወጣልኝ። በዚሁ የስፖርት ዝግጅት የመክፈቻ ስነስርዓት ላይ ታዳሚውን ያዝናና ለየት ያለ አንድ ትርኢት ታየ። የኢትዮጵያ ባንዲራ ከስታዲየሙ በላይ ሰማይ በፓራሹት አንዣቦ ቁልቁል ሲወርድ የፈጠረው ስሜት ልዩ ነበር። ከበውቄ ጋር እንደተገናኘን ከሰላምታ አስቀድሞ “ባንዲራ ይዘው ካየር ላይ የወረዱት ኢትዮጵያውያኖች ናቸው?” ሲል ጠየቀኝ።

“አይደሉም በኪራይ ነው” አልኩት የሰማሁትን።

“ባንዲራ ከኛ ወኔ ከነሱ ነዋ!” ብሎኝ እርፍ! 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top