በላ ልበልሃ

የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የባህር በር መብት

“የኢትዮጵያ ብሔራዊ ራስ ምታት” ተብሎ የሚጠራው የባህር በር አልቦነት አባዜ (syndrome) በየጊዜው በውስጥ ፖለቲካዊ ትኩሳት አንዴ ሲደፈጠጥ ሌላ ጊዜ መቃወሚያ ሲሆን ኖሯል። አሁን የአልጀርሱ ስምምነት ተግባራዊ ከሆነ መብታችንን እስከወዲያኛው የምናጣበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። የውስጥ ፖለቲካዊ ስልጣን ከዘላቂ የኢትዮጵያ ጥቅም ጋር የሚፃረር በሚያስመስል መልኩ ሁሉም መንግስታት በአንድ ወይም በሌላ መልኩ መብታችንን የራሳቸውን ስልጣን ለማደላደል ሲገፈትሩት ኖረዋል። ኤርትራ ነፃ አገር ስትሆን የባህር በር በማጣታችን ኢትዮጵያ አንገቷ ተቆርጧል ብለው ሲጮሁ የነበሩ አንዳንድ ምሁራን በወቅቱ ፖለቲካዊ ትኩሳት ታውረው እርግፍ አድርገው ትተውታል። ትግራይን እስካዳከመ ድረስ (በአልጀርስ ስምምነት ወደ ኤርትራ የተካለሉት የኢትዮጵያ መሬቶች በአብዛኛው በትግራይ ክልል ነው የሚገኙት) የባህር በርን ጉዳይ ትተውታል። የትግራይ መዳከም የኢትዮጵያ መዳከም መሆኑን በሚያሳፍር ሁኔታ የዘነጉት ይመስላል። መደመር ይሉሃል ይሄ ነው። የባህር በር የማጣት ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ እንዳልሆነ ሁሉ እርግፍ አድርገው ትተውታል። በፖለቲከኞችና ምሁራን ጊዚያዊ የፖለቲካ ትኩሳት የምትነዳ አገር ዘላቂ መብቷንና ጥቅሟን ልታጣ ትችላለች። ከታሪክ ተጠያቂነት እጃችን እናውጣ።

ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ የአገራችንን ህልውና አደጋ ውስጥ ሊከት የሚችለውን የባህር በር እጦት በቸልተኝነት የምናልፍ ከሆነ አገራችን የጀመረችው አቃፊ ፖለቲካ፤ ፍቅር፤ ይቅርታና መደመርን መሰረት ያደረገ የህዳሴ ጉዞ ዘላቂ ማድረግ አይቻልም። ከኤርትራ መንግስት ጋር ያለው “ሁለተኛው የጫጉላ ሽርሽር” (honeymoon፣ የመጀመሪያው ከ1983-1990 ዓ.ም. የነበረውና ወደ ጦርነት ያመራው ነው) ሳያዘናጋን ኳታር (Qatar) የባህር በር ባይኖራት ምን ትሆን ነበር? ብለን ዴሞክራሲን እንደ ጠላት የሚፈርጀው፤ ቀይ ባህርን ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር ፍላጎት ያለው፤ የኢትዮጵያን ትልቅነት እንደ ስጋት የሚመለከት፣ ፔትሮ ዶላር (petro dollar) ያሰከረውና በወታደራዊ አቅሙ ተማምኖ የመንን የወረረ የቅንጅት ኃይል ባለበት የመካከለኛ ምስራቅ ተዝረክርከን መቆየታችን ይቅርታ የማይሰጠው ነው።

 በዚህ ጽሑፍ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ህግ ኣኳያ ስላላት ሉዓላዊ የባህር በር መብት፣ የአልጀርሱ ስምምነት የሃገራችንን መብትና ጥቅም የሚያሳጣ ስለመሆኑና ስምምነቱን ለመሻር ስላለን ሕጋዊ መብት ለሁለተኛ ዲግሪ መመረቂያ በ1999 ያዘጋጀሁትን ጥናት ተመርኩዤ ለማቅረብ እሞክራለሁ። የተያያዝነውን የለውጥ ሂደት ለማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ለማድረግ ሉዓላዊ የባህር በር መብት ወሳኝ ነውና።

 ኢትዮጵያና ፈረንሳይ እንደ አ.አ. በ1897 ባደረጉት ስምምነት በጂቡቲ በኩል ሊኖረን የሚችለውን የባህር በር ጥያቄ በይፋ (officially) አሳልፈን ሰጥተናል። በተለያዩ የውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ ምክንያት በኤርትራ በኩል ያሉትን ወደቦች እንደፈለግነው ባንጠቀምባቸውም ኢትዮጵያ ሉዓላዊ የባሕር በር መብት እንዳላት ማሳወቋ አልቀረም። በቅኝ ኃይሏ ጣሊያንና ኢትዮጵያ መካከል እንደ አ.አ አቆጣጠር በ1900፣ በ1902 እና በ1908 በተደረጉ ስምምነቶችም አትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ያውም በጦርነት አሸንፋ ሉዓላዊ የባሕር በር መብቷን አሳልፋ ሰጥታለች። ኤርትራ በፌደሬሽን ወደ ኢትዮጵያ ከተቀላቀለች በኋላ እንደገና ሉዓላዊ የባሕር በር መብቷን ማረጋገጥ ችላ ነበር። ከአርባ ዓመታት ባለመብትነት በኋላ ኤርትራ ነፃነቷን ስትጎናፀፍ አገራችን እንደገና ያለ አግባብ ወደብ የለሽ ሆነች። በጦርነት አሸንፈን መብታችንን አሳልፈን መስጠት ባህላችን እስኪመስል ድረስ የኤርትራን ወረራ ከቀለበስን በኋላ የሃገራችንን መብትና ጥቅም የሚያሳጣውን የአልጀርስ ስምምነት ተዋዋልን። አገራችን እስከ ወዲያኛው የባህር በር በምታጣበት ጫፍ ላይ ትገኛለች። በኢትዮጵያ ህልውና ውስጥ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ መፍትሔ የሚሻ ወሳኝ ነገር ነው። ጉዳዩም በስልጣን ላይ ካለው መንግስት ባሻገር ሊታይ ይገባዋል። የኤርትራን ህዝቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትና ነፃነትም እውቅና እሰጣለሁ። ነገር ግን የኤርትራ ነፃነት እና የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ሉዓላዊ መብት አንዱ ሌላውን የሚተካ (exclusive) እንዳልሆነ አምናለሁ።

የ1900፣ 1902 እና 1908 ስምምነቶች ጣሊያን የጣሰቻቸው፣ ኢትዮጵያም በሕግ የሻረቻቸው ናቸው።

የአልጀርስ ስምምነት የተሻሩትንና በ1900፣ በ1902 እና በ1908 የተደረጉ ስምምነቶችን መስረት ያደረገ ነው። በነዚህ ስምምነቶች መሰረት በኢትዮጵያ በኩል ይቀርብ የነበረው ተደጋጋሚ የድንበር ማዋሰን ጥሪ በጣሊያን በኩል ሰሚ አላገኘም። ይልቁንም በተለያዩ አካባቢዎች ጦሯን ታደራጅ ነበር። ጣሊያን ስምምነቶችን በቀና መንፈስ ለመፈፀም ዝግጁ አልነበረችም። በዚህም በ1928 ዓ.ም. ኢትዮጵያን ስትወር የነበራት ድብቅ ዓላማ ተጋለጠ። ኢትዮጵያን መውረር ብቻ ሳይሆን የጣሊያንን የምስራቅ አፍሪካን ቅኝ ግዛት ለመመስረት በነበራት እቅድ የሶማሊያ፣ ኤርትራና ኢትዮጵያን ድንበሮች ደባልቃ አምስት ግዛቶች ያሉት የጣሊያን የምስራቅ አፍሪካ ቅኝ ግዛት ተመሰረተ። በዚህ አረመኔያዊ ውሳኔ ጣሊያን ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የማጥፋት እና ስሟንም ከታሪክ ማህደር የመፋቅ ፍላጎት ነበራት። በአምስቱ ዓመታት የጣሊያን ወረራ ዘመን እነዚያን የ1900 ውሎች የሚያስፈፅመው አንዱ ወገን (ኢትዮጵያ) ህልውና እንዳይኖረው ተደርጓል። የቪዬና ድንጋጌ የስምምነቶች ህግ በአንቀጽ 60 በሁለትዮሽ ስምምነት ውስጥ በአንዱ አካል የሚፈፀም የህግ ማፍረስን የተመለከቱ ጉዳዮች በሌላኛው አካል ስምምነቱን ለማቋረጥ ወይም ተፈፃሚነቱን በከፊልም ሆነ በሙሉ ለማቆም መብት ይሰጣል ይላል። በሌላ አነጋገር አንዱ ወገን ስምምነት በመጣሱ ምክንያት ተግባራዊነቱ እንዲቆም ወይም እንዲቋረጥ ሲደረግ የስምምነቱን ዋነኛ ጥሰት ስለሚያሳይ ሌላው ወገን ሊሽረው (Null and void ሊያደርገው) ይችላል ማለት ነው። የሁሉም ስምምነቶች መሰረት የሆነው የ1900 ውል አንቀፅ 2፤ “የጣሊያን መንግስት ቀጥሎ በተዘረዘሩት አካባቢዎች ለየትኛውም ሌላ ኃይል ላለመሸጥ፣ ላለመስጠት ራሱን ያስገዛል” ይላል። በዚህ መስረትም ጣሊያን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ስትሸነፍ ግዛቶቿን ለኢትዮጵያ ማስረከብ ነበረባት። በአፄ ኃይለሥላሴ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት ኤርትራ በፌደሬሽን ኢትዮጵያን ስትቀላቀል (የኤርትራና ኢትዮጵያ ፌደሬሽን አይደለም) ጊዜ ጣሊያን ያፈረሰቻቸው ስምምነቶች እንደማይሰሩ አውጀው ውድቅ አድርገዋቸዋል። በወቅቱ ተረቆ በታወጀው የኤርትራ ህገመንግስት መሰረት የ1900፣1902 እና 1908 የኢትዮጵያና ጣሊያን ስምምነቶች ውድቅና የማይሰሩ እንዲሆኑ አድርገዋል። እነዚህ የ1900ዎቹ ውሎች በ1947ቱ የፓሪሱ የሰላም ጉባኤ እና የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ ሀሳብ መሰረት የማይሰሩ ሆነዋል።

ውልን አንደኛው ወገን ሲጥሰው ሌላኛው ተዋዋይ ያለውን ውድቅ የማድረግ መብት በሚመለከት የሙኒክ ስምምነት እና የሪጋ ውል በሚል የሚታወቁት ዓለማቀፍ ውሎች ህያው ምስክሮች ናቸው። የሙኒክ ስምምነት የታላቋ ብሪታንያ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይና ጣሊያን ከቀድሞዋ ቺኮዝላቫኪያ የሱድተን ላንድ ግዛቷን ወደ ጀርመን መቀላቀል በተመለከተ መስከረም 29/1938 በጀርመኗ ሙኒክ ከተማ ያደረጉት ስምምነት ነው። ስምምነቱ ቺኮዝላቫኪያን ከጀርመን ወረራ ለመታደግ ለተፈጠሩት አዲስ ወሰኖች አለማቀፍ እውቅና (ማረጋገጫ) በመስጠት ሁለተኛው የዓለም ጦርነትን ለማስቀረት የተደረገ ነበር። ይሁን እንጂ ጀርመን ቺኮዝላቫኪያን በመውረር ሀገሪቱን በሙሉ ያዘች። ጀርመን ሆን ብላ ስምምነቶችን በመጣሷ የፈረንሳይና የታላቋ ብሪታንያ መንግስታት የሙኒክ ስምምነት የማይሰራ እና ውድቅ መሆኑን አውጀዋል። ከዚያ ስምምነት ጋር የተያያዘ የትኛውንም ተግባርና የሚያስከትለውን ውጤት (ለውጥ) በሙሉ ውድቅ ማድረጋቸውን ገልፀዋል። በመሆኑም የሀገሪቱ ድንበር ከመስከረም 1938 በፊት የነበረው የቺኮዝላቫኪያ ሪፐብሊክ ወሰን እንደሚሆን አረጋግጠዋል።

የሶቪዬት ህብረት ከጥቅምቱ አብዮትና ከፖላንድ ጦርነት በኋላ ተዳክማ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነበረች። ወታደራዊ ኃይሏንም ከድንበር አካባቢ የመለሰች በመሆኑ በአወዛጋቢ የድንበር አካባቢዎች የግዛት ማካካሻ ለመስጠት ከፖላንድ ጋር በ1921 የሪጋ ስምምነትን ተፈራረመች። በመስከረም 28/1939 ሶቪዬት ህብረት የሪጋ ስምምነትን በተናጠል በመጣስ ከጀርመን ጋር ፖላንድን ለመቀራመት ተስማሙ። በሰኔ 22/1941 የጀርመን ወታደራዊ ኃይል ሶቪዬት ህብረትን ወረረ። በሰኔ 30/1941 ደግሞ ሶቪዬት እና ፖላንድ ጀርመንን ለመውጋት ሲስማሙ የ1921 ሪጋ ስምምነትም ታደሰ። ሆኖም ከጥር 11/1944 በኋላ ሶቪዬት ህብረት ከአሜሪካ እና ከእንግሊዝ ጋር የገባችው ውል እንደገና ታድሶ የነበረው የሪጋ ስምምነት በፖላንድ ጭምር ውድቅ እንዲሆን ተደርጎ ተጠናቋል። ሶቪዬቶች ይጠይቁት የነበረው የኩርዘን መስመር የፖላንድና የሶቪዬት ድንበር እንዲሆን እንግሊዞች ባቀረቡት ምክረ ሀሳብ የሪጋን ስምምነት ሻሩት። ኢትዮጵያ በ1928 በጣሊያን ወረራ ሲፈፀምባትና ስትያዝ የ1900ዎቹን ስምምነቶች ውድቅ የማድረግ መብት በሚገባ የሚገልፁ ሲሆን የሁለተኛው የዓለም ጦርነትን ለማስቀረት፣ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን፣ የወሰን መብቶችን ለድርድር ስለማቅረብ እንዲሁም ከጦርነቱ በኋላ በወሰን አከላለል ስራዎች ውስጥ ወታደራዊ ኃይል ስለሚኖረው ሚናና ለፖሊሲ ዓላማዎች እንደ ሁኔታዎች የታየው መለሳለስ ከላይ ካነሳናቸው ተግባራት አኳያ ትምህርት የሚወሰድባቸው ናቸው።

 የ1900ዎቹ ውሎች ውድቅ ከሆኑ ኤርትራ ነፃ ስትወጣ ድንበሩ በየትኛው ዓለማዊ ህግ ይገዛል?

በየካቲት 10/1947 ከጣሊያን ጋር የተደረሰው የሰላም ውል ስምምነት ጣሊያን በአፍሪካ ያሏትን ግዛቶች ማለትም ሊቢያ፣ ኤርትራ እና የጣሊያን ሱማሌላንድ ሙሉ መብትና ባለቤትነት እንድትለቅ የሚያደርገው ይገኝበታል። ኢትዮጵያ በአምስት ዓመት ትግል ነፃነቷን በማረጋገጧ ጣሊያን በግዛቶቿ ላይ የነበሯትን መብቶች እና ኃላፊነቶች በሰላም ስምምነቱ አንቀፅ 23 መሰረት ስትተው በኢትዮጵያና ጣሊያን መካከል የነበረው ውል ማብቂያ ሆኗል።

በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚመለከተው ሌላ አዲስ ሕጋዊ ማዕቀፍ (Legal Regime) ተመስረተ። አቃፊው ሕግ “በተባበሩት መንግስታትና በኢትዮጵያ መካከል የተደረገ ስምምነት” ሆነ። በግልፅ ለማስቀመጠም በ1952 ኤርትራን በፌደሬሽን ከኢትዮጵያ ያዋሃደው “የሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሸናፊ ኃያላን መንግሰታት እና የኢትዮጵያ ስምምነት” ነው። የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ምክረ ሃሳቦች ከራሱ ከመንግስታቱ ድርጅት ውጭ አስገዳጅ ህጋዊ ውጤት ያላቸው አይደሉም። ይሁን እንጂ ጣሊያን በቅኝ ግዛቶቿ ላይ ያላትን መብት የወረሱት አሸናፊዎቹ ኃያላን መንግስታት በጠቅላላ ጉባኤ ስለወከሉትና ሃሳቡን በመቀበል ስለተገበሩት ነው። በመሆኑም በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ – ኤርትራ 390A መሰረት ኤርትራ ራስ ገዝ ሆና በኢትዮጵያ ዘውድ ስር በፌደሬሽን እንድትቀላቀል የተደረገበት የፌደሬሽኑ መሰረታዊ መርሆዎችና እምነቶች ናቸው አቃፊ ሕግ የሚሆኑት።

የውሳኔውን የፍላጎት መንፈስ (intent) ለመረዳት የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ በመስከረም 24/1948 ባካሄደው 143ኛ ስብሰባ፣ የቀረቡ አስተያየቶች በዋናነት ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር በማቀላቀል ላይ ያተኮሩትን ማየት ተገቢ ነው። ነገር ግን በትክክል የትኞቹ ግዛቶች እንደሚካተቱ ሠፊ አለመግባባት ነበር።”

/ የኤርትራ ምስራቃዊ ክፍል ከኢትዮጵያ ጋር መቀላቀል አለበት፣ ቀሪው የምዕራቡ ክፍል ሌላ መፍትሄ ይፈለግለታል። (ታላቋ ብሪታንያና አሜሪካ)

 ለ/ ሁሉም የኤርትራ ክፍል በፍጥነት ወደ ኢትዮጵያ መተላለፍ አለበት (ላይቤሪያና ኢትዮጵያ)

/ በባለ አደራ ምክር ቤት በሚሾም አስተዳደር በተባበሩት መንግስታት ባለአደራነት ስር ሆኖ በአማካሪ ኮሚቴ ድጋፍ ይደረግ። ኢትዮጵያ በአሰብ በኩል የባህር በር እንድታገኝ የግዛት ማካካሻ ይደረግላት። (ሶቪዬት ህብረት፣ ዩጎዝላቪያ፣ ቺኮዝላቫኪያ፣ ፖላንድ፣ ቤሎሩስያና ዩክሬን)

 / የሰሜን ኤርትራ ክፍል በጋራ (በህብረት) ባለ አደራ አስተዳደር ስር ሆኖ ጣሊያን የባለአደራ አስተዳደር ትሁን። ደቡባዊው የሀገሪቱ ክፍል ወደ ኢትዮጵያ ይጠቃለል። (አርጀንቲናና ቱርክ)

/ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ እንዳለ ሆኖ ዘርንና ኃይማኖትን መሰረት በማድረግ የተወሰነው የኤርትራ ክፍል ወደ ኢትዮጵያ መጠቃለል አለበት። ቀሪው የሀገሪቱ ክፍል ጣሊያን አስተዳዳሪ ሆና በተባበሩት መንግስታት ባለ አደራነት ስር መሆን አለበት። (ቤልጂየም፣ ቺሊ፣ ኮሎምቢያ፣ ኮስታሪካ፣ ዶሚኒካን ሪፐብሊክ፣ ኢኳዶር፣ ኤልሳልቫዶር፣ ጓቲማላ፣ ሆንዱራስ፣ ፓናማ፣ ፓራጓይ፣ ፔሩ፣ የደቡብ አፍሪካ ህብረትና ቬንዙዌላ)።

 የጣሊያን ግዛቶችን በተመለከተ ኃላፊነት የወሰዱት ኃያላን መንግስታት በተጠቀሱት ግዛቶች መለቀቅ ዙሪያ ድርድር የማድረግና መፍትሄ የማምጣት ኃላፊነት ነበር የወሰዱት። ነገር ግን በማስለቀቁ ጉዳይ ላይ ለመስማማት አልቻሉም።

ታላቋ ብሪታንያ-

 (1) ኢትዮጵያ ለአስር አመታት ያህል ኤርትራን ለማስተዳደር መመደብ አለባት።

 (2) ከአስር አመት በኋላ የኢትዮጵያ አስተዳደር በምን ሁኔታ ለዘለቄታው መቀጠል እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ ይወስናል።

 (3) የኢትዮጵያን አስተዳደር የሚደግፍ የአማካሪዎች ምክር ቤት ይመደባል። ምክር ቤቱ ኤርትራውያንን፤ የአራቱ ኃያላን መንግስታት ወኪሎችን እንደዚሁም የጣሊያን፣ የስዊዘርላንድ፣ የአንድ ስካንድኔቪያን አገርና የአንድ ሙስሊም አገር ወኪሎችን ያካተተ ይሆናል።

 ፈረንሳይ-

(1) ከዙላ ባህረሰላጤ እስከ ፈረንሳይ ሱማሌላንድ ካለው ግዛት ውጭ ያለው የኤርትራ ክልል በጣሊያን ሞግዚትነት መያዝ አለበት።

(2) ከዙላ ባህረ ሰላጤ እስከ ፈረንሳይ ሱማሌላንድ ያሉት ግዛቶች ከሙሉ ሉአላዊነት ጋር ለኢትዮጵያ መሰጠት አለባቸው።

(3) ለኢትዮጵያ በተሰጡት ግዛቶች እና በጣሊያን ሞግዚትነት ስር ባሉት ግዛቶች መካከል ያለው ድንበር የአካለ ጉዛይ ምስራቃዊ አስተዳደራዊ ወሰንን ተከትሎ ከዙላ ባህረ ሰላጤ እስከ አሁኑ የኢትዮጵያ ድንበር ያለውን የያዘ መሆን አለበት። ከኢትዮጵያና ጣሊያን ወገን በእኩል በሚወከሉ ሰዎች አማካኝነት ወሰን የማካለል ስራው ከመስከረም 15/1949 በፊት መጠናቅቀ አለበት።

አሜሪካ-

የደቡባዊ ኤርትራ ክፍል ወደ ኢትዮጵያ እንዲጠቃለል ሀሳብ አቅርባለች። ይህ አካባቢ የደናኪል ዳርቻ የአካለ ጉዛይና ሰራየ ግዛቶችን በማካተት አዲሱ ድንበር ከዙላ ባህረ ሰላጤ የአካለ ጉዛይና ሰራየ ሰሜናዊ ድንበርን ተከትሎ እስከ ኢትዮጵያ ድንበር ያለውን ይይዛል።

ጣሊያንም ብትሆን ይሄንን መብት እውቅና መስጠት ነበረባት። የመጀመሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባዔ በለንደን ከመደረጉ አስቀድሞ የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለአሜሪካ አቻቸው ተከታዩን መልዕክት ፅፈው ነበር። “በሶማሊላንድ ሞግዚትነት (የባለአደራ ስርዓት) ላይ የሚመከር እንኳ ቢሆን የረጅም ጊዜ ቅኝ ግዛታችን በሆነችው ኤርትራ የጣሊያን ሉአላዊነትን መጠበቅ ተገቢ ነው። ይህ የኢትዮጵያን የባህር በር የማግኘት ጥያቄ የሚያካክስ ነው። ለዚያ ብለንም ከደሴ ወደ አሰብ የሚወስድ መንገድ ገንብተናል። ይህ መብት ሊረጋገጥ የሚችለው በጣሊያን ግዛት ውስጥ አሊያም ጥያቄው ከቀረበ ደግሞ በድንበር ማካለል (rectifications) ነው።

 በኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ የተባበሩት መንግስታት ውሳኔ 390 v መግቢያ የሚከተለውን ይላል። ከዚህ የሚከተለውን ከግምት በማስገባት፤

/ በኤርትራ የተለያዩ ብሄረሰቦች፣ የሀይማኖትና ፖለቲካ ቡድኖች አስተያየትና የህዝቡ ራስን የማስተዳደር አቅምን ጨምሮ የኤርትራ ነዋሪዎች ፍላጎትና ደህንነት፣

ለ/ የምስራቅ አፍሪካ ሠላምና ፀጥታ ሁኔታዎች፣

/ ከመልክአምድር፣ ከታሪክ፣ ከብሄረሰቦችና ከኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች በመነሳት በተለይም የኢትዮጵያን ህጋዊ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ እና መብቶች፣

 መ/ የውጭ ኃይሎች ለኤርትራ ኢኮኖሚ ልማት የሚኖራቸውን ቀጣይነት ያለው ትብብር የማረጋገጥ ጠቀሜታን ከግምት በማስገባት፣

/ የኤርትራ መለቀቅ ከኢትዮጵያ ጋር ቅርበት ያለው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚ ውህደትን መሰረት ማድረግ እንዳለበት እውቅና በመስጠት፣

ረ/ የዚህ የውህደት ስምምነት ፍላጎት ለኤርትራ ነዋሪዎች፣ ተቋማት፣ ሀይማኖቶች፣ ቋንቋዎችና ልማዶች ሙሉ ክብርና ጥበቃን ለማረጋገጥ ብሎም ስፋት ያለው ራስን የማስተዳደርና በተመሳሳይ የኢትዮጵያን ህገመንግስት፣ ተቋማት፣ ልማድ እና ዓለማቀፍ እውቅናና ተቀባይነት በማክበር ነው ይላል። የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ በኤርትራ ኮሚሽን ሪፖርት ላይ በጠቅላላ ጉባዔው ጊዜያዊ ኮሚቴ ሪፖርት መሰረት 390-A(V) የውሳኔ ሀሳቡን አሳለፈ።

በዚህ ውሳኔም ኤርትራ ራስ ገዝ ሆና ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እንድትቀላቀልና በኢትዮጵያ ዘውድ ሉአላዊነት ስር እንድትሆን ውሳኔ አሳለፈ። የውሳኔ ሀሳቡ (390v) በአጠቃላይ ዓለማቀፍ ህግን ተከትሎና በተለይ ደግሞ የቪዬና ውሎችን ህግ ድንጋጌ መሰረት ተደርጎ ሊተረጎም ይገባዋል። የቪዬና ድንጋጌ የውሎች ህግ አንቀፅ 31(1) እንደሚያትተው “አንድ ውል በመልካም ጎኑ መተርጎም ይኖርበታል። የውሉ ቃላቶች በመደበኛ የአውድ ይዘታቸው እንዲሁም ጭብጥ እና ፍሬ ነገር መሰረት በማድረግ ሊታይ ይገባል። በአንቀፅ 31(1) የሰፈሩት መሰረታዊ መርሆዎች የቀናነት መርህ፣ መደበኛ ትርጉም፣ አውድ፣ ጭብጥ እና ፍሬ ነገር ናቸው።

 እላይ የተጠቀሱት ምሳሌዎች በቪዬና ድንጋጌ የውሎች ህግ አንቀፅ 31 መሰረት የኤርትራን ሁኔታ በተመለከተ በአራቱ ኃያላንና በኢትዮጵያ መካከል የተደረሰው ስምምነት ዋና ዓላማና ተግባር የኢትዮጵያን ሰላም ለማስጠበቅና የባህር በር ባለቤትነት መብቷን ለማረጋገጥ ነው። ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌደሬሽን እስከተቀላቀለችበት ጊዜ ድረስም በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኋላም ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩት አክሊሉ ሀብተወልድ የሚመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ኤርትራን ለማስመለስ ካልተቻለም የሀገሪቱን የባህር በር መብት ለማረጋገጥ ታግሏል። የአዲሱ ስምምነት ተዋዋዮች ማለትም ኢትዮጵያና አሸናፊዎቹ ኃያላን መንግስታት ኤርትራን ወደ ኢትዮጵያ በፌደሬሽን ሲቀላቅሉ አንዱ ታሳቢ የተደረገው የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የባህር በር የማግኘት መብት ነው።

 ከእንግዲህ ወዲህ ከኤርትራ ጋር የሚደረግ ማናቸውም ድንበርን ማእከል የሚያደርግ ድርድር የኢትዮጵያን ሉዓላዊ የባህር በር የማግኝት መብት ማእከል ያደረገና በድንበር አካባቢ የሚኖሩ የሁለቱ አገር ህዝቦች ፍትሐዊ ውሳኔ በሚያገኙበትና ሊያሠራ በሚችል ዓለማቀፋዊ ሕግ (applicable international law) መሰረት መሆን ይገባዋል።

 የአልጀርስን ስምምነት ለመሰረዝ ሕጋዊ መበት አለን

 ይህ ስምምነት ወራሪና ተወራሪን፣ አሸናፊና ተሸናፊን እኩል የሚያደርግ መሆኑ አሳፋሪ ቢሆንም የአገራችንን መብት አሳልፎ የሰጠ በመሆኑ ዘላቂ ሰላም ሊያረጋግጥ አይችልም:: የኢትዮጵያን አጠቃላይ ደህንነት በተለይም የኢኮኖሚ ደህንነትን አደጋ ውስጥ የሚያስገባ ነው። የኢትዮጵያን ታሪክና ክብር የማይመጥን ስምምነት ነው። የኤርትራ መንግስት ጦርነት ጫረ፤ ተሸነፈም። ላደረሰው ጥፋትና ጦርነቱን በመጀመሩ ተጠያቂ መሆን ነበረበት፣ ወራሪ በመሆኑም ሰራዊቱ ለመውረር በማያስችለው ሁኔታ መገደብ ነበረበት። ከዚያ በላይ ለስምምነቱ መነሻ ሃሳብ ሲቀርብ ማእከሉ የሉዓላዊ ባህር በር ጉዳይ

“የአልጀርሱ ስምምነት ኢትዮጵያን ከድል መንጋጋ ሽንፈት እንድትወስድ አድርጓል። ያረጁ የወደቁ እና የተተኩ የ1900ዎቹ ውሎች በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የድንበር ጉዳይ መደራደሪያ ሊሆኑ አይችሉም። አቃፊው ሕግ “በተባበሩት መንግስታት እና በኢትዮጵያ መካከል የተደረገ ስምምነት” ሆነ። በግልፅ ለማስቀመጥም በ1952 ኤርትራን በፌደሬሽን ከኢትዮጵያ ያዋሃደው “የሁለተኛው ዓለም ጦርነት አሸናፊ ኃያላን መንግስታትና የኢትዮጵያ ስምምነት” ነው”

መሆን ነበረበት። ካልተቀበለ ቅጣቱ ከፍተኛ ይሆን ስለነበር የኤርትራ መንግሥት ከመቀበል ውጭ ሌላ አማራጭ አልነበረውም። የአልጀርስ ስምምነት ሕጋዊ ውል ነወይ? በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ አዋጅ ቁጥር 225/1993 “በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክና በኤርትራ መንግስት መካከል የተደረገውን የሰላም ስምምነት ለማጽደቅ የወጣ አዋጅ” የሚል ሲሆን የታወጀበት ወቅት ሕዳር 29 1993 (8/Dec/2000) ነው። የአልጀርስ ስምምነት የተፈረመው ግን ታህሳስ 3 1993 (12/Dec/2000) ከአራት ቀን በኋላ ነው። እንደሚታወቀው የአልጀርሱ ስምምነት እስኪቋጭ ድረስ ድርድር ነበረበት። በሕገ መንግስታችን አንቀጽ 55 (12) “የሕግ አስፈጻሚው አካል የሚዋዋላቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ያጸድቃል ይላል” ሕገ መንግስታችንን ይፃረራል። ከሕገ-ፍልስፍና (Jurisprudence) አኳያም የሕግ- አውጭው ስልጣኑን አሳልፎ መስጠት የተከፋፈለ መንግስትን መርህ ይፃረራል። ተዋዋዮች ሁሉ ስምምነቶቹን በየሃገሩ ባሉት ስርዓቶች መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው። በዚህም ምክንያት ሕጋዊነቱ ላይ ጥያቄ ያስነሳል።

 ውሉ ሕጋዊ ቢሆን እንኳን ገና ከመጀመሪያው የኤርትራ መንግስት ማፍረስ በመጀመሩ ኢትዮጵያ ለመሰረዝ (Null and Void ለማድረግ) ሕጋዊ መሰረት አላት። የአልጀርስ ስምምነት አንኳር በአንቀጽ I (1 እና 2) ናቸው። ዋና ዓለማው በሁለቱ አገሮች ሰላም ማስፈን ነው። 

የድንበር፣ የካሣ፣ ወዘተ. ጉዳዮች የመጨረሻ ግባቸው ሰላምን ማረጋገጥ ነው።

(1) Article I 1. The parties shall permanently terminate military hostilities between themselves. Each party shall refrain from the threat or use of force against the other.

 2. The parties shall respect and fully implement the provisions of the Agreement on Cessation of hostilities. በንኡስ አንቀጽ ሁለት የተጠቀሰውን ተፃብኦ ለማቋረጥ (Cessation of hostilities)

 የ25 ኪሎሜትር ጊዜያዊ የደህንነት ቀጣና (Temporary Security Zone)፣ የጦርነትን አደጋ ለመቀነስ (buffer zone) ተመስርቶ ይህንም የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ይጠብቀዋል ይላል። የኤርትራ መንግሥት ከተወሰኑ ወራት በኋላ የሰላም አስከባሪ ኃይሉን በማባረር ጊዜያዊ የደህንነት ቀጣናውን አፍርሶ ወታደሮቹን አሰፈረ።

 ንኡስ አንቀጽ አንድን በመፃረር የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያን ለማተራመስ በማሰብና በመንቀሳቀስ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ስጋት ሆኗል። በኤርትራ ውስጥ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎችን በማሰበሰብ፤ በማሰልጠን፤ በማስታጠቅና በማሰማራት ቀጣይነት ያለው ትንኮሳ ሲፈፅም ቆይቷል። በሶማሊያ በኩል የውክልና ውጊያ (proxy war) በተደጋጋሚ በመክፈት ኢትዮጵያን የማተራመስ እቅዱን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ያካሂድ ነበር። የቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በየጊዜው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያሰሙት የነበሩት ስሞታዎች፣ የተባበሩት መንግስታት ሪፖርቶችና እነሱን መሰረት አድርጎ የጣላቸው ማዕቀቦች በቂ ማስረጃዎች ናቸው። እላይ በዝርዝር እንደተገለፀው አንዱ ተዋዋይ ወገን ውሉን ካፈረስ ሌላኛው ወገን የመሰረዝ መብት ያለው በመሆኑ ኢትዮጵያ ስምምነቱን የማፍረስ ሕጋዊ መብት አላት። ሰርዣለሁ ብላ ማወጅም አለባት።

ማጠቃለያ

 የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ የምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካና ኢኮኖሚክ ሕብረት አስተሳሰብ የሚደነቅ ነው። ይህ ግን በረዥም ጊዜ የሚፈጸም ስራ ነው። ከአሁኑ መጀመር ቢኖርበትም ብዙ ውጣ ውረድ አለበት። የአካባቢያችንን ሀብትና ወታደራዊ አቅማቸውን እያፈረጠሙ ያሉት ሀገራት ብዙ መሰናክል ይፈጥራሉ። አብዛኛዎቹ በአካባቢያችን ያሉ አገሮች በነሱ ተጽዕኖ ስር የወደቁ ናቸው። በራሳቸው የሚወስኑ አይደሉም። የኢትዮጵያ የባህር በር ጉዳይ ከኤርትራ ጋር ብቻ ሳይሆን ከጂኦ ፖለቲክስ ማዕዘንም መታየት አለበት።

 የአልጀርሱ ስምምነት ኢትዮጵያን ከድል መንጋጋ ሽንፈት እንድትወስድ አድርጓል። ያረጁ የወደቁ እና የተተኩ የ1900ዎቹ ውሎች በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የድንበር ጉዳይ መደራደሪያ ሊሆኑ አይችሉም። አቃፊው ሕግ “በተባበሩት መንግስታት እና በኢትዮጵያ መካከል የተደረገ ስምምነት” ሆነ። በግልፅ ለማስቀመጥም በ1952 ኤርትራን በፌደሬሽን ከኢትዮጵያ ያዋሃደው “የሁለተኛው ዓለም ጦርነት አሸናፊ ኃያላን መንግስታትና የኢትዮጵያ ስምምነት” ነው። የአልጀርስ ስምምነት ሕጋዊ ውል አይደለም። ኤርትራም በተደጋጋሚ የጣሰችው በመሆኑ ኢትዮጵያ የመሰረዝ መብት አላት። በርካታ ምሁራን የኢትዮጵያን ሉዓላዊ የባህር በር መብት በሚመለከት በጥናታቸው አረጋግጠዋል። ለጊዜውም ቢሆን ሉዓላዊ የባህር በር የማግኘት መብቷንና ሌሎች የውስጥ ግዛቶቿን አጥታለች። ከእንግዲህ ወዲህ ከኤርትራ ጋር የሚደረግ ማናቸውም ድርድር የኢትዮጵያን ሉዓላዊ የባህር በር የማግኘት መብት ማእከል ያደረገና በድንበር አካባቢ የሚኖሩ የሁለቱ አገር ህዝቦች ፍትሐዊ ውሳኔ በሚያገኙበትና ሊያሠራ በሚችል ዓለማቀፋዊ ሕግ (applicable international law) መስረት መሆን ይገባዋል። ለጊዚያዊ ፖለቲካ የአገራችንን ዘላቂ መብትና ጥቅም አናጥፋው። የአልጀርስን ስምምነት አሽቀንጥሮ መጣያው ጊዜ አሁን ነውና!!! 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top