አድባራተ ጥበብ

የቴአትር ጉልበቱ

ተመልካች የጎረፈላቸው ብዙ ተውኔቶች አሉ ። ሀገር ፍቅር ቴአትር የቀለጠው መንደር የተሰኘ ተውኔት ምንያህል ተወዳጅ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ቆየት ካሉት የጠለቀች ጀምበርን እናስታውሳለን።

ይሁንና ስለተመልካች ጎርፍ ላወራችሁ የተነሳሁት ለእነዚህ ዝነኛ እና ተወዳጅ ተውኔቶችን አይደለም። ከፍተኛ ተወዳጅነት እንዲኖራቸው ያደረጋቸው የተውኔቶቹ ጥንካሬ፣ ታሪካቸው፣ ወይንም ሴራቸው፣ ዝግጅታቸው ወይንም የትወናው የአገላለጽ ብቃት የመሳሰሉት ናቸው። ይሄ ከተውኔት የሚገኝ አንዱ ጥበባዊ ትሩፋት መሆኑ ይታወቃል። የኔ ትኩረት መነሳሳትን በከፍተኛ ሁኔታ ተመልካች ላይ ጭረው ስለነበሩት ተውኔቶች ይሆናል።

 በ1966 ዓም የኢትዮጵያ አብዮት እንደፈነዳ ጉድ ያሰኘው የመጀመሪው ተውኔት የጸጋዬ ገ/መድህን ሀሁ በስድስት ወር ነው። ይህ ተውኔት በጊዜው ባልተለመደ ሁኔታ ከፍተኛ ተመልካች ከማግኘቱም በላይ በተመልካቹ ዘንድ ከፍተኛ ስሜት የፈጠረ ነበር። የመንግስት ባለስልጣኖችን፣ ፖለቲከኞቸን፣ የደርግን ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች እኩል የሳበ ተውኔት ነበር። ይኸው ከፍተኛ ስሜት በእናት አለም ጠኑም ከአመት በሁዋላ ተደግሟል። ይህ ከምን የመጣ ነበር?

 ፀጋዬ እንዲህ ከፍተኛ ስሜት የሚያጭር ተውኔት በ1985 ዓ.ም ሰልሷል። ሀሁ ፐፑ። ይህ ተውኔት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር ይቀርብ በነበረበት ወቅት ቲኬት ቆርጦ የመግባት እድል ከገጠመው ታዳሚ ይልቅ ቲኬት አጥቶ በቁጭት ይመለስ የነበረው ተመልካች በትንሹ ሶስት እጥፍ ይሆን ነበር። ይበልጥ ደግሞ አስገራሚ የሆነው ቴአትር ቤቱ ሀሁ ፐፑን በሳምንት ሶስት ቀን እያሳየው እንኳ በሶስቱም ትርኢት ቀናት ወንበር አጥቶ ይመለስ የነበረው ተመልካች ቁጥሩ እጅግ የበዛ ነበር።

 በቅርቡ ደግሞ የአንድ ሰው ትርኢት ( one man show) የነበረው እያዩ ፈንገስ ይገኛል። ይሄ በረከት በላይነህ ፅፎት ግሩም ዘነበ ይጫወትበት የነበረ ተውኔት በተለያዩ የግል ቴአትር ቤቶች በሳምንት ውስጥ በአብዛኞቹ ቀናት ይቀርብ ነበር። ተውኔቱ በሳምንት ውስጥ ብቻ ብዙ ትርኢቶች የነበሩት ሲሆን መግቢያ ቲኬት መግዛት ተቸግሮ የሚመለሰው ተመልካች የትየለሌ ነበር።

 እነዚህን የጠቃቀስኳቸውን ተውኔቶች የሚያመሳስላቸው ትልቁ ጉዳይ ተመልካች ላይ ከፍተኛ ስሜት የሚያጭሩ መሆናቸው ነው። በሌሎች ተውኔቶች ላይ አዘውትረን የምናገናቸው እንደ መሳቅ፤ ማዘን ፣መደሰት፣ መሳቀቅ፣ የመሳሰሉ ስሜቶችን ጨምሮ የድጋፍ ወይም የተቃውሞ ጭብጨባዎች ፤ፉጨቶች ፤ ጩኸት ከፍተኛ የአሸናፊነት ስሜት ሞራል የመሳሰሉ ጥልቅ ስሜቶችን ያስተናግዳሉ። እኔን እንደገባኝ እንዲህ አይነት ተውኔቶች ዝናቸው ከሰደድ እሳትም ይፈጥናል። ቴአትሩ ለህዝብ መቅረብ ከጀመረ በሳምንት ወይንም በአስራ አምስት ቀን ውስጥ የተመልካች ጎርፍ ያጥለቀልቀዋል። በመዲናችን የወሬ ርእስ ይሆናል። ከዚህም አልፎ በክልል ከተሞችም መቼ መጥቶልን የሚል ጉጉት ያሳድራል። የፖለቲከኞችን እና የባለ ስልጣኖች ትኩረት ይስባል።

 ይህን ትዝታ ወደ ቀሰቀሰብኝ ተውኔት ልመለስ በቶፊቅ ኑሪት ተፅፎ በዳግማዊ ፈይሳስለተዘጋጀው ከመጋረጃው ጀርባ

“የቴአትር ጉልበቱ እና ትልቁ ፋይዳውም ወቅታዊነት ይመስለኛል። ቴአትር ያስተምራል፤ ያዝናናል ቢባልም የህዝብን ስሜት በመግለጽ ራስን የመግለጽ ባህል እንዲዳብር ትልቅ ሚና አለው። እኛ በተለይ በዚህ ዘመን የሚያስፈልገን ተውኔት የሀሳብ ብዝሀነትን እና ነጻነትን የሚያበረታታ መሆን አለበት፤ ለቴአትር እድገት አሰተዋጽኦ ይኖረዋል።”

 እኔ ከአንድ አመት ከመንፈቅ በፊት አንድ ተውኔት በዚህ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት አሳይቼ ነበር። በወቅቱ ቴአትር ቤቱ ከሚያቀርባቸው ተውኔቶች በሙሉ ከፍተኛ ተመልካች የነበረው ይህ ተውኔት ከፍተኛ የተመልካች ቁጥር አምስት መቶ ግድም ነበር። የቴአትር ቤቱ የእሁድ ስምንት ሰዓት ተውኔት እጅግ በጣም ዝቅተኛ ተመልካች ነበረው። በተመልካች እጥረት ምክንያትም ዝግ ያደረጋቸው ቀናትም አሉት። ከእነዚህ ቴአትር ቤት በቅርብ እርቀት የሚገኘው አዲስ አበባ ቴአትር እና ባህል አዳራሽም በተመልካች ረሀብ ምክንያት ብዙዎቹን ቀናት ዘግቷል።

ታዲያ ይህ ተውኔት መጣና በተመልካች ረሀብ ይሰቃይ የነበረው ቴአትር ቤት ድንገት በተመልካች መጨናነቅ ጀመረ። ከዚህ ተውኔት ጋር በሆነ ነገር ግንኙነት ያለው አንድ ሰው ይህ ውጤት የተገኘው ቴአትራቸውን ማስተዋወቅ በመቻላቸው እንደሆነ ፌስቡክ ላይ ጽፎ ተመልክቻለሁ። እኔ ይሄ ስህተት የሆነ ድምዳሜ ነው ባይ ነኝ። ከዚህ በላይ በፖስተር፣ በጋዜጣ፣ በቴሌቪዝን እና በሬዲዮ የተዋወቁ ተውኔቶች ከወትሮው ተመልካቻቸው ትንሽ በዛ ያለ ተመልካች አግኝተው ይሆናል እንጂ ተመልካቹ ሲጎርፍላቸው አልተመለከትንም።

ታዲያ የተመልካቹ መጉረፍ ምክንያቱ ምንድን ነው?

ከተዋንያኑ አንዱን ይገረም ደጀኔንን ጠይቄው ነበር። የሕዝቡን ህመም ችግር ፍላጎት ስለሚያንጸባርቅ ነው። ወቅታዊ ስለሆነ ነው አለኝ። አዘጋጅ ዳግማዊ ተመሳሳይ መልስ ሰጠኝ። ይሁን እንጂ አቀራረቡም አስተዋፅኦ እንዳለው ነገረኝ። እዚህ ላይ ጸብ የለኝም።

 የእኔም ሀሳብ ወደዚሁ የሚያደላ ነው።

 ቴአትር አንድ ማህበረሰብ በመስታወት ራሱን እየተመለከተ ራሱን የሚመረምርበትን ጥበባዊ ወይንም ባህላዊ መድረክ ይፈጥርለታል። ከላይ እንደምሳሌ የጠቀስኳቸው የጸጋዬ ተውኔቶች በሀገሪቱ ህዝቦች አንዳች የፖለቲካ ጥያቄ ባገረሸበት ወቅት ያን ያገረሸ የፖለቲካና ማህበራዊ ጥያቄ ጉዳያቸው አድርገው የሚያነሱ እና ተመልካቹ ራሱን ቴአትሩ ውስጥ ተወክሎ መገኘቱን የሚያሳዩ ናቸው። እናም ይህ የሀገር ፍቅር ቴአትር ተውኔትን ትክክለኛ ጥያቄን በትክክለኛው ሰአት በማንሳቱ የተወደደ ይመስለኛል። ህብረተሰቡ ውስጥ ያለን ህመም ወይንም ጥያቄ ዙሪያ ገባውን ተመልካቹ እንዲመለከት እና እንዲመረምር እድል ይሰጠዋል። ተመልካቹ ራሱን ቴአትሩ ውስጥ ስለሚያገኘው ተውኔቶቹ ውስጥ በአሉት ክስተቶች ምክንያት አንዳች የስሜት ጥሪ ላይ ይደርሳል።

 አንድ ሰው ቴአትር ቤት ደጃፍ ላይ የገጠመውን በርካታ ተመልካች ፎቶገራፍ በፌስቡክ ገፁ ላይ ለጥፎ ሲያበቃ ይህ ሁሉ ታማሚ ነው። ግን በአግባቡ መድሀኒቱን እያገኘን አይደለም ብሎ የጻፈው እና ሌላው ደግሞ ጋዜጣ ላይ ስለተውኔቱ ሲጽፍ ርእስ ያደረገው ዘመኑን ነቃሽ ቴአትር ብሎ የገለጸው ቴአትሩ ተወዳጅ የሆነበትን ምክንያት የሚያመለክቱ ይመስለኛል። ፖስተር ላይ ከመጋረጃው ጀርባ ከሚለው ርእስ ስር የተቀመጠው አንድነትን የሰበከ ቴአትር የሚለው መሪ አረፍተ ነገር ቴአትሩ ከተመልካች ጋር ለመተሳሰር ያሰበውን ገመድ የሚያመለክት ነው። ፍቅር እና አንድነት የኢትዮጵያ ህዝቦች ጥማት በሆነበት በዚህ ዘመን፣ ይህ ተውኔት ይህን ይዘት ይዞ መቅረቡ የተወዳጅነቱ ምንጭ ነው ብዬ አምናለሁ።

 ሀገራችን ላይ ብዙም የማንደፍረው ወይንም የማናስታውሰው አንዱ ትልቁ የቴአትር ጉልበት ይህ ይመስለኛል። ወቅታዊነት።

 ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ቴአትሮች መስራት ጠንክሮ የታየው በደርግ ዘመን ነበር። እነዚህ የቅስቀሳ ተውኔቶች መንግስት የሚከተለውን ርእዮተ-አለም ሀያልነት፣ አሸናፊነት፣ ህዝባዊነት ህዝቡ ላይ ለማስረጽ የሚወጠኑ ቢሆንም ይህንኑ የመንግስትን ተራማጅነት ለመግለጽ የተቃራኒውንም ጎራ አመለካከት (ፀረ ህዝብነት ) ለመወከል ፀረ አቀንቃኝ ገጸባህርያት የሞሉባቸው ነበሩ። የተውኔቶቹ አላማ ታጋዮች የሚገጥማቸውን እልህ አስጨራሽ ትግል በመጨረሻው ግን በአሸናፊነት እንደሚወጡ ያሳዩ ነበር።

ይሁን እንጂ ሁሉም ተመልካች ላይ ተመሳሳይ ምላሽ የነበራቸው አልነበሩም። በስጋት ታፍነው ስሜታቸውን በይፋ ለመግለጽ የሚቸገሩ ግን ደግሞ ልባቸው ፀረ ህዝብ ተብለው ከተፈረጁ ገጸ ባህርያት ጋር የሚሸፍትባቸው ተመልካቾችም ነበሩ።

የቴአትር ጉልበቱ እና ትልቁ ፋይዳውም ወቅታዊነት ይመስለኛል። ቴአትር ያስተምራል፤ ያዝናናል ቢባልም የህዝብን ስሜት በመግለጽ ራስን የመግለጽ ባህል እንዲዳብር ትልቅ ሚና አለው። እኛ በተለይ በዚህ ዘመን የሚያስፈልገን ተውኔት የሀሳብ ብዝሀነትን እና ነጻነትን የሚያበረታታ መሆን አለበት፤ ለቴአትር እድገት አሰተዋጽኦ ይኖረዋል።

የቤርቶልት ብሬሽትን አባባል እዚህ ላይ ልዋስ መሰለኝ።

We need a type of theatre which not only release the feelings, insights and impulses possible within the particular historical field of human relations in which the action takes place , but employs and encourages those thoughts and feelings which help transform the field itself .

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top