ጥበብ በታሪክ ገፅ

የታምራት ሥልጣን በ«መክተፏ፣ የሕይወት ታሪክ»

ሠዓሊ ታምራት ሥልጣን የረቀቁ የግራፊክ፣ የሕትመትና ቀለም ቅብ የሥዕል ሥራዎቹን ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በቡደን እና በግል በተዘጋጁ ዐውደ ርዕዮች ላይ ለሕዝብ በማሳየት ይታወቃል። በ2006ዓ.ም. “ከጥላው ሥር” ፣ እንዲሁም በ2008 ዓ.ም. “አፈርሳታ” በሚሉ ርዕሶች በግሉ ያቀረባቸውን ሁለት ዐውደ ርዕዮች የማየት እድል አጋጥሞኛል። ዘንድሮ በ2010 ዓ.ም. ደግሞ “መክተፏ፣ የሕይወት ታሪክ” በሚል ርዕስ ሌላ በሥዕላዊ ፍልስፍናውና በይዘቱ ለየት ያለ የግል ዐውደ ርዕይ በመክፈት ካለፈው በጠለቀና በረቀቀ የፈጠራ ክህሎት የኮረኮረውን ሃሳብ አካፍሎናል። ታምራት እነዚህን በሁሉት ዓመታት ተራርቀው የቀረቡትን የሥዕል ዓውደ ርዕዮች ከማቅረቡ በፊት የመጀመሪያ የግል ዐውደ ርዕዩን ያቀረበው በ1993 ዓ.ም. ሲሆን፣ ከ1989 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት ዓመታት ውስጥ ከ20 በሚበልጡ የቡድን ዐውደ-ርዕዮች ላይ ተሳትፏል።

የዘመናዊት ኢትዮጵያ ሥዕል በዝመና ግፊት የተቀሰቀሰና፣በሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ በአዲስ አበባ ከተማና አካባቢው ተፀንሶ የተወለደ የዘመናዊ ሥልጣኔ ምልክት ነው። በፍላጎቱ ከመንፈሳዊና ሀይማኖታዊ ሥዕል የተለየ ሥዕል የሚሠራው ዘመናዊ ሠዓሊ ከሞላ ጎደል ለሥዕል ታሪክና ንቅናቄ ተጠያቂና ተገዥ ነው። ከአገር በቀል የፈጠራ መንፈስ እና ፍልስፍና የፈለቀ፣ በአገር በቀል እውቀትና ክህሎት የታገዘ አዲስ ስልተ ሥዕልና አዲስ የኪነ ጥበብ ባህል የዘመናዊነት መገለጫ ምልክት ተደርጎ ይታያል። የሥዕል ዘመናዊነት፣ በተለይ በዘልማድ የቀለም ቅብ ሥዕል በመባል በሚታወቀው፣ በግርድፉ ሲታይ በሰሌዳ ላይ ጥልቀት ከሌለው አቀራረብ ወደ ርቀት ክብደትና ሙላት ወደ አለው ምትሃታዊ መሰል እይታ መሸጋገሩ ነው። በዚህ አይነት ያቀራረብ ግፊት የተነሳ ርዕሰ ጉዳዩም ከተፈጥሮ በሚቀሰም የየዕለት ተግባራት ኩነትና ክንውን ላይ ያተኩራል። በአገር በቀል የፈጠራ እውቀት፣ ፍልስፍናና ክህሎት እየታገዘ እውኑን ዓለም ለመቅረጽ በመመኘት፣ በፎቶግራፍ ተፅዕኖና አስተዋፅኦ በሠዓሊው ዓለማዊ ፍላጎት የጀመረው ይህ አይነት ሥዕላዊ አቀራራብ የተሞከረው በቀለም ቅብ ሥዕል ያሠራር ዘዴ ሲሆን፣ታምራት አዘውትሮ የሚጠቀምበት የግራፊክ ሥዕል ስልትና ዘዬ ደግሞ ከግማሽ ምዕተ ዓመት ጀምሮ የታየ ነው።

 በአገር በቀል የፈጠራ ክህሎትና ትውፊታዊ እውቀት፣ ታንጾ በመደበኛ ትምህርት ጎልምሶ ማንነቱን የጠበቀው ያገራችን ዘመናዊ ሥዕል በዚህና በተያያዥ አያሌ ጉዳዮች የተነሣ ከሌላው ዓለም ሥዕል ንቅናቄ በእኩል ደረጃ መታየትና መጠናት ጀምሯል።

 ይህ እንዳለ ሆኖ፣ ብዙ ሠዓሊያን የሚመኙትንና በአንድ አጋጣሚ ዝነኛው ገብረ ክርስቶስ ደስታ “…በዘመናዊ መንገድ በሥነ ጥበብ ምን ያህል ለመራመድ እንደምንችል ለማሳወቅ በመሥራት ላይ እገኛለሁ” እንዳለው በዓውደ ርዕይ ላይ የሚቀርብ ግምገማና ሂሳዊ ዳሰሳም ኪነጥበባትን ለማራመድና ለማበልጽግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል። በተደጋጋሚ በታሪክ እንዳየነውና አሁንም ድረስ ጥቂት ሠዓሊያን እንደሚያደርጉት ፣ ለምሳሌ በታምራትና በሌላው ግራፊክ ሠዓሊ ኃይሉ ክፍሌ መካከል ያለው የሙያ ትብብር ከሀገረሰባዊና ቁሳዊ ጥበብ ባለፈ በምርምር የሚከሰት ዘመነኛ ኪነጥበብ መፍጠር መቻሉን አይተናል።

የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ተለዋዋጭ ዓለም ዓቀፋዊ ኪነ ጥበባ ሰደድ ያቀራረባቸው፣ የደረሱበትንና ያፈቀሩትን ለማሳወቅ ባንድ ሥዕላዊ ንቅናቄ ውስጥ ተሰልፈው የሚንቀሳቀሱ ናቸው። ከቀድሞዎቹ የሚለዩት በተለይ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ፣ ባጠቃላይ በዓለም ዙሪያ ያለውን ሥርዓተ ማኅበር ውጥንቅጥ በምሥለ ነገር በተምሳሌት ማሳየትና ማጋለጥና በዘይቤያዊ መንገድ መከሰትና ተጠያቂ ሆኖ መቅረብን መምረጣቸው ነው።

 በ1967 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ልደታ ሰፈር የተወለደውና በ1991 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አለ ፈለገ ሰላም የሥነ ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት በግራፊክ ሥዕል ዘርፍ የተመረቀው ሠዓሊ ታምራት አቋሙና ሰብእናው እንደሚጠበቀው እንደየዘመኑ ቄንጠኛ ሽቅርቅር ሠዓሊያን አይደለም።ከላይ እንደገልጽኩት ታምራትንና ሥራዎቹን ማወቅ የቻልኩት ከዓመታት በፊት ሲሆን፣ የዘንድሮ ሥራውን ለማየት መሃል ካዛንችስ ከሚገኘው ስቱዲዮው በሄድኩበት ቀን ልጆቹን ትምህርት ቤት አድርሶ ከBMW መኪናው ወጥቶ ነበር የተቀበለኝ። በስቱዲዮው ውስጥ የሥዕል መሥሪያውንና ክፍሉን ከዳር ዳር ያጣበቡትን በርካታ የሥዕል ሥራዎቹን እየተዘዋወርኩ ስቃኝ፤ከሕይወት ያካበተውን ብልህነት፣የሥዕል ፍልስፍናውን፣ የፈጠራ ምስጢሩን፣የአሣሣል ስልትና ዘዬውን እንዲሁም ባህርዩን ይበልጥ ለማወቅና ለመረዳት ቻልኩ። አርዓያ አድርጎ የሚመለከታቸው ሠዓሊያንና መምህሮቹ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ንቅናቄ ከፍተኛ ቦታ ያላቸው ታደሰ ግዛው፣ ዘሪሁን የትምጌታና ዝነኛው ረዳት ፕሮፌሰር ጌታቸው ዮሴፍ መሆናቸውን ገለጸልኝ። ያሠራርና ያቀራረብ ዘይቤውን ፣ የገበታ ቆረጣ/ነቀሳ ኅትመትና ለጠፋ ሥራዎቹን፣ ርዕሰ ነገር ምርጫውንና ተለዋዋጭነታቸውን፣ በመካኒካልና ግላዊ ፈጠራ መንፈስ መካከል ያለውን ልዩነትና የሚከሰተውን ጥበብ በመመርመር መሥራቱን፣… ከእደ ጥበበ፣ ከቁሳዊ ወይም ትውን ጥበብ ለመለየት የትምህርት ቤትና ከዚያም ውጭ ያካበተውን እውቀቱን በሥራው መተርጎሙን ተገነዘብኩ። ታምራት በረጅም ጊዜ ጥበባዊ ጥሞና፣ጥናትና ምርምር የደረሰበትን ውጤት በተደጋጋሚ በሚያቀርባቸው የግልና የቡድን የሥዕል ዐውደ ርዕዮች ላይ ለሕዝብ ዕይታ በተለይም ለሥዕል ጥበብ አፍቃሪው ማቅረቡ በዐቢይነት ሊጠቀስ የሚገባው መልክም ባህርይው ነው። የሱን ዐውደ ርዕይ ከሌሎቹ የተለየ የሚያደርገው ከአንገብጋቢ ወቅታዊ ማኅበረ-ፖለቲካዊ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ኩኑቶች መነሣቱና ለሥነ ጥበብ ታሪክ እውቀት ትኩረት መስጠቱ ነው። እኔም

ከጥላው ሥር

ታምራት በ2006 ዓ.ም. በዉድከት የገበታ ነቀሳ የተሠሩ የሥዕል ሥራዎቹን ያቀረበበትና “ከጥላው ሥር” በሚል ርዕስ የሰየመው ዐውደ ርዕይ ለቤተሰቡ መታሰቢያ ሆኖ የቀረበ ቢሆንም በውስጡ ሌላ ሚስጥር የተሸከመ ነበር። “ሃሳብ ጥላው ሲ..ጎ..ት..ተ..ኝ፣ መዓዛው አወደኝ፣ አፍንጫዬን መታው የቀለሙ ሽታ፣ ውስጠቴን ሊያጸዳ ሃሳቤን ሊፈታ፣” በማለት “ጥበብ … ግን ይከተለኛል ስሮጥ ይይዘኛል ከጥላ የባሰ ውስጤን የነከሰ” በማለት በምሥል ከሳች ዘዬው የተቀኘበት፤ ጥላና ሃሳብ ምንኛ እንዳሰሩት በሥዕሉ ብቻ ሳይሆን በቅኔአዊ ቋንቋ እየተጠቀመ መግለጹን በጊዜው ዐውደ ርእዩን አስመልክቶ  ካሳተመው ካታሎግ ላይ አንብቤያለሁ።

የዐውደ ርዕዩ ቁም ነገር ከጥላው ሥር የምናያቸው በከፊል የተሸፈኑና ያልተሸፈኑ የተለያዩ ኩነቶችን፣በጥቁርና ነጭ ህትመት ሥራ በማቅረብ ግልጹንም ድብቁንም ማሳየት ይመስላል። ይሁንና ታምራትን እየተፈታተነው ያለው ጉዳይ ለረጅም ዘመናት ሠዓሊያንን እያታለለና እየማረከ የቆየው የጥላና ብርሃን አገባብ፣ እንዲሁም ሥዕላዊ ሚስጥር ዋነኛው ነገር ነው ማለት ይቻላል። በሰሌዳ ላይ ምትሃታዊ ዓለም ለመፍጠር የሚያስችለው የብርሃንና ጥላ መሰበጣጠር የገሃዱን አለም ትክክለኛ አቀማመጥ በመለወጥ ይሸውደናል።

አፈርሳቻ

ታምራት በ2008 ዓ.ም. “አፈርሳታ” ብሎ የሰየመውንና በቀለም ቅብና ድብልቅ/ ቅይጥ ዘዴ የተሠሩ ዳር ድንበር ዘላቂ ዛፎችን፣ ዋርካዎችን፣ እንዲሁም በዉድከት የተሠሩና መልከ ብዙ ሚስጥር የተሸከሙ የተዘጉ መስኮቶችን በሥዕል ሥራዎቹ ውስጥ በትእምርትነት የተጠቀመበትን የግል ዐውደ ርእይ አቅርቦ ነበር። «ዛፎችንና የኢትዮጵያን ታሪክ እወዳለሁ» የሚለው ታምራት “ዛፎች የጉባዔ ቦታ፣ የኢትዮጵያ የፍትሕና ርትዕ ሥርዓት ዐቢይ ትእምርት እንዲሁም የማኅበረሰብ ትስስርና አንድነት ምሳሌ ናቸው“ ብሎ ያምናል። “የዛፍ ሥዕል ስሠራ፣ስሩ፣ ገጹና ሁሉ ነገሩ እውቀት ይከስትልኛል፤ ይህን ክስተት፣ ይህን ገጠመኝ ማኅበረሰቡን ለማነቃቃትና ኃይለኛ ሃሳቦችን ለማስተላለፍ እጠቀምበታለሁ።” ይላል። በዐውደ ርእዩ ላይ በቀረቡት ሥዕሎቹ ላይ ዛፎችን በዛፍነታቸው፣ በዋርካነታቸው ብቻ ተማርኮ ያቀረባቸው አይደሉም። ከውበታዊ አቀራረባቸው ባሻገር፣ ታምራት “ በሀገራችን የዘመናት ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊና ማኅበረሰባዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ሀገር በቀል ዛፎች ዋነኛ መሰባሰቢያ እና የኩነቶች መፈጸሚያ ሆነው ሲያገለግሉ ኖረዋል» በማለት እንደገለጸው የነዚህ ዛፎች ተምሳሌትነትና መልዕክት በጥላቸው ስር የሚካሄደው የማኅበረሰባችን ሥርዓተ ፍትሕ፣ምክክርና ጉባዔ – “አፈርሳታ” ወይም አውጫጭኝ ዋነኛው ፍሬነገር ነው።

 በዚያ ዐውደ ርእይ ላይ ታምራት መስኮቶቹንም በመስኮትነታቸው እንድናያቸው በማሰብ የሠራቸው አይደሉም፣ “መስኮቶች ባሉበት ይዞታ የግለሰቡን ማንነትና የኑሮ ሁኔታ የሚገልፁ» በማለት እንዳስረዳን በቀለማት ተውበው ሲቀርቡ የሚያፈላስፉ፣ የግለሰብን ባህሪ የማንነቱንና የኑሮውን ሁኔታ እንዲጠቁሙ ታስበው የቀረቡ ተምሳሌቶች ናቸው። በሰሌዳው ላይ የፈጠረው የደን፥ የጫካ ባጠቃላይ የዛፎች ትእይንት ባንድ በኩል ደስታንና እርካታን ሲፈጥሩ በሌላ በኩል እየጠፉና እየተራቆቱ መሄዳቸውን በማሳየት ለተፈጥሮ ተቆርቋሪ ሠዓሊ መሆኑን አሳይቶናል። “አፈርሳታ” ታምራት ለተፈጥሮ ያለውን ፍቅር፣ ተቆርቋሪነትና ጥልቅ ርኀራሄ ያሳየበት ዐውደ ርዕይ ነበር።

መክተፏ

ታምራት፣ “መክተፏ፣የሕይወት ታሪክ” በማለት ዘንድሮ በ2010 ባቀረበው ዓውደ ርዕይ ላይ ፈጽሞ ያልተለመደ ርዕሰ ጉዳይ አንስቷል።አሁን ባለንበት ዘመን ለሥዕል ጥሩ የሚባል ርዕሰ ጉዳይ ምርጫ ያለ አይመስልም፤ ለጥሩም ይሁን መጥፎ ርዕሰ ጉዳይ ምርጫ ወሳኙ ወይም መራጩ ሠዓሊው ነው። ታምራት በቀደሙት ዓወደ ርዕዮቹ በመረጣቸው ቀለማትና ሥዕላዊ መስመሮቹ የጥላና ብርሃንን ምስጢር፣ የዛፎችን ውበትና ትእምርታዊ ባህርያት ካሳየን በኋላ፤በዘንድሮውና ከላይ ርእሱን በገለጽኩት የግል የሥዕል ዐውደ ርእዩ ላይ ደግሞ ከዛፍ ቁራጭ ተወስዶ ለማድ ቤት አገልግሎት የሚውለውን መክተፊያን ርዕሰ ጉዳዩ አድርጎ አቅርቦታል።

 ሕይወት አልባ የሆነውን ግዑዝ አካል መክተፊያን እንደ ርዕሰ ጉዳይ መርጦ፣ እንደ አራዳ ሠዓሊያን አቀራረብ ሰሌዳው ላይ በተከታታይ ደጋግሞ ደርድሮ፣ በቀለም አሸብርቆ የቁሳቁስ ቦታውን ቀይሮ ሥነ ሥዕል አድርጎ አቅርቦታል። መክተፊያ ዛሬ ጊዜ ብዙ አይነት ቅርጽ ይዞ ከእንጨት ገበታ ባሻገር በተለያዩ ቁሳቁስ፤ በብረት ፣ በመስተዋት፣ በፕላስቲክና በመሳሰሉ እየተሠራ አገልግሎት ይሰጣል። ቅርፁም ከሞላ ጎደል በአራት ማዕዘን የተወሰነ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ግዜ ካገር አገር ከዘመን ዘመን እየተለዋወጠ ሲመጣ ታይቷል። ይሁንና ታምራት በስልተ ሥዕሉ እና ቴክኒኩ የተላመድነውን የመክተፊያን ቅርጽ ፈጥሮ ተቀኝቶበትል፣ ተፈላስፎበታል፣ የመክተፊያን የሕይወት ታሪክን አስነብቦናል። በመክተፊያ ተምሳሌትነት ብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያን እናቶች፣እህቶች፣ የቤት እመቤቶች እና የቤት ሠራተኛች ለዘመናት ያሳለፉትን የከፋ ሕይወት ለመንገር የሣለው የሕይወት ታሪክ ነው።

በዚህ ዐውደ ርእይ ላይ መክተፊያ በሥዕል መልክ ተነድፎና ተቀብቶ ትክክለኛ ቅርጹን ይዞ የተደረሰ ሥዕል ነው። በግንባር እና በስተጀርባ በኅብረ ቀለማት አሸብርቆ በመቅረቡ የተመልካችን ዓይን መሳቡ አይቀርም። በቀለማት ኅብር ምትሀታዊ ውበትን ተጎናፅፈው የተሣሉት የመክተፊያ ምሥሎች እንደሰንሰለት ተያይዘው አንድ ጊዜ ከላይ ወደታች ሌላ ጊዜ ደግሞ የየራሳቸው መደብ ተሰጥቷቸው አለዚያም አውራ የሚመስለውንና ጎልቶ የቀረበውን መክተፊያ አጅበውና ተከትለው ልዩ ጥበባዊ ውህደትን ሲፈጥሩ ያሳየናል። ለዘመናት በሰጡት አገልግሎት የደረሰባቸው የሰውነታቸው ጠባሳና ቁስል እስኪዘገንን ድረስ በሰለጠነና በረቀቀ መንገድ ተገልፅዋል ። ሥዕሉን በማየት በቶሎ ትዝታ ባይቀሰቀሰብን እንኳን አንዳች ተዛማጅ ነገር በምናባችን ፈጥረን ለማገናዘብ እንገደዳለን።

 በማያቋርጥ ንድፍ መስመርና በቀለማት የተነደፈው መክተፊያ በተምሳሌት የወከለው ያንስታይ ጾታን ሰውነት ነው። የመክተፊያው ቅርጽ ሆን ተብሎ ሳይሆን በአንዳንድ አካባቢዎች በዘልማድ አሠራሩ የአንስታይ ገጸ ባሕርያትን አቋቋምና ገጽ ያስታውሳል። በሥዕል አማካኝነት የቤት እመቤትም ሆነ የቤት ሠራተኛ የደረሰባትን ብዝበዛ፣ጭቆና፣ድብደባ፣ በማድ ቤት ውስጥ መገለል፣ መደበቅና መወሰንን በመቃወም፤ የወንዶች የበላይነት እና የሴቶች የበታችነትን በመክተፊያዎቹ ተምሳሌትነት በዚህ ዐውደ ርእይ ላይ በቀረቡት ሥዕሎቹ ማሳየቱ የጾታ እኩልነት ተቆርቋሪነቱንና ፍትሕ ፈላጊነቱንና ያንፀባርቃል። ታምራት በማድ ቤት ውስጥ ብቻ የምናየውን መክተፊያ ከፍ አድርጎ በማቅረብ፣ ከዚህ ቀደም በማንኛውም ጥበባዊ የፈጠራ ሥራ ያልተለመደ ርዕሰ ነገር ማድረግ ብቻ ሳይሆን ፣ብዙዎቻችን ልብ የማንለውን በተለይ ሴትን የማጎሳቆል አሳዛኝ ተግባራትን በመክተፊያ ሥዕሎቹ ተምሳሌትነት በምጸትና ባስደንጋጭ መንገድ በማቅረብ የተመልካቹን ስሜት ይሞግታል።

 በጥናትና ምርምር የደረሰበትን የፈጠራ መንገድ በመቀያየር፤ በግራፊክ ሥዕል ፣ ገበታ/እንጨት ቆረጣ ዉድከት ነቀሳ ሥዕል፣ የሲልክ ስክሪን ኅትመት ሥዕል፣ ቀለም ቅብ ሥዕል፣ ንድፍ ሥዕል ባጠቃላይ በሁሉም ዓይነት የሥዕል ኪነ ጥበብ አንድነትና ልዩነት አስመልክቶ ተመልካች ያለውን ግንዛቤ ማስፋት እንዲችል የበኩሉን አስተዋጽዖ ያደረገ ሠዓሊ ነው። ልሂቅ ስራው በንብረትነት የብዙ ግለሰቦችና ማዕከላት ክምችት በመሆናቸው፣ በፍሬአማ ጥበባዊ ሥራውና በየጊዜው በሚአከናውናቸው ማህበራዊና ሰብዓዊ ድርጊቶች የተነሳ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ ካየናቸው ጠንካራና ስመ-ጥር ሠዓሊያን አንዱ ሆኗል።

ብዙ ሊቃውንትና የሥነ ጥበብ አዋቂዎች የሥዕል እሴት ከራሱ ውጭ ለሆነ ነገር ጥገኛ ፣ ከገሃዱ ዓለምና ከሠዓሊው ንቃተ ኅሊና ብቃት የሚፈጠር መሣሪያ ፣ መሣሪያነቱ ደግሞ እንደ ጥበቡ ጥንካሬ ማኅበራዊ፣ መንፈሳዊ እና ሞራላዊ ግንዛቤያችንን ከፍ ማድረግ ነው ይላሉ። ታምራት በ2006 እና በ2008 ዓ.ም. ባቀረባቸው የግል ዐውደ ርዕዮቹ፤ ሥዕል ከመሥራት ባሻገር ሥዕሉ ሃሳቡን እንዲያስተላልፍለት አገልጋይና ወካይ መሣሪያ ሆኖ መቅረቡን አይተናል። ዘንድሮ “መክተፏ፣የሕይወት ታሪክ” በማለት የሰየመው ዐውደ ርዕይም ይህንኑ ፍላጎቱን አጉልቶ ያሳየበት ርዕዮተ ዓለማዊ መሣሪያ ነው ።በዚህ ዐውደ ርእይ ላይ የቀረቡትን የታምራትን የሥዕል ሥራዎች ተመልካቹ፣የሥነ ጥበብ ታሪክ አጥኚውም ሆነ ሃያሲው ካልተናገረላቸው በራሳቸው የመጮህም ይሁን የመናገር ኃይላቸው ውስን ሆኖ ይቀራል። 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top