ጣዕሞት

የተመራቂዎቹ ፊልሞች

አነስተኛዋ አዳራሽ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና መምህራን ተሞልታለች። መሐል ላይ ገምጋሚዎች ተቀምጠዋል። ከእነሱ ጀርባ ዙሪያውን ተማሪዎች አሉ። የዘንድሮ ድህረ ምረቃ ተማሪዎች ሥራቸውን ያቀርባሉ። መምህራን ካስተማሯቸው አንፃር የሰሩትን መዝነው የሚገባቸውን ነጥብ ይሰጣሉ።

 አቅራቢዎቹ በየተራ ስማቸው ይጠራል። ከተመልካቾቹ ፊት ለፊት ይቆማሉ። ከአጭር ገለፃ በኋላ ፊልሞቻቸውን ይጋብዛሉ። ብዙዎቹ ራሳቸው ገፀ-ባህርይ መርጠው፣ ዳይሬክተርም፣ ኤዲተርም ሆነው የሰሩ ናቸው። የብዙዎቹ ፊልሞች ጭብጦች ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኩራሉ።

ፊልሞቹ እንደተመራቂዎቹ ምርጫ እና ዓይነት ቀርበዋል። የጊዜ መጠናቸው ከ15 እስከ 20 ደቂቃ ነው፡፡ መምህራኑ ከአዲስ አበባ አለ ሥነ-ጥበብና ዲዛይን፣ ከያሬድ ሙዚቃና ከቴያትር ጥበባት ትምህርት ቤቶች የመጡ ናቸው።

 ፊልሙ እንዳበቃ አቅራቢው ይጠየቃል፣ ይመልሳል። የተማረውን ምን ያህል ወደ ተግባር እንደለወጠው ይተነተንለታል። ምልዓት ጉድለቱ ይነግረዋል። ይህም በየዓመቱ የሚካሄድ የተለመደ ተግባር ነው። የተመራቂዎቹ ፊልሞች ብዙዎቹን ተመልካቾች ማርከዋል። ጥያቄው ከተመረቁ በኋላ ስንቶቹ ወጪያቸው ተሸፍኖላቸው ወይም በከፊል ታግዘው ይሠራሉ ነው።

ተመራቂዎቹ በተሰጣቸው ጊዜ ማሟላት የሚገባቸውን ባለሙያዎች እና ቁሳቁሶች አሰባስበው፣ አስጠንተው፣ ለቀረፃ አዘጋጅተውና ቀረፃውን በሚገባ አከናውነ አቅርበዋል። ከቀረቡት መካከል አንዱ የአጭር ልብወለድ ተብሎ የሚታወቀው የአሜሪካዊው ኤዳጋር አለን ፖ “The Tell- Tale Heart” የተሰኘ አጭር ልብወለድ “ልብ ሲያውቅ” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ ተመልሶ ታይቷል። አቅራቢው እንዳለው ይህ አጭር ልብወለድ በታዋቂው ደራሲ እና ተርጓሚ ሣህለስላሴ ብርሃነማርያም “ጠቋሚው የልብ ትርታ” በሚል ርዕስ ተተርጉሞ “እምቢ ባዮች” በተሰኘው የአጭር ልብወለድ (ትርጉም) መጽሐፍ ውስጥ ተካትቷል። የ”ልብ ሲያውቅ” ትርጉም ግን የራሱ እንደሆነ ተናግሯል።

 አብዛኞቹ ተመልካቾች ተመሳሳይ ሃሳብ አላቸው። ተመራቂዎቹ ተመርቀው ከወጡ በኋላ ለሙያው ትልቅ እገዛ እንደሚያደርጉ ይጠቁማሉ። የመምህራኑ አስተያየት ከሙያ ጋር የተያያዘ እንደመሆኑ ግቢውን መሻገር እንዳለበት ይናገራሉ። ተጋብዘው አስተያየት መስጠት ቢችሉ ሙያው እያደገ ይሄዳል የሚል ተስፋ አላቸው።

ሰው፣ ቀለማት እና ክረምትክረምት

የሰዓሊ በቀለ መኮንን (ተ/ፕሮፌሰር) ሐሳቦች

የሰው ልጅ አካባቢውን ነው የሚመስለው። ከአካባቢው ጋር ራሱን አስማምቶ፣ በአካልም ሆነ በመንፈስ ባህርዩን ገርቶ ለመኖር፣ የምድር ላይ ቆይታውን ያሳምራል፤ ያራዝማል። የራሱን ባህርይ ለተፈጥሮ እንደሚያስገዛ ሁሉ ተፈጥሮንም ለራሱ ፍላጎት ገርቶ እና አርቆ ለኑሮው ተስማሚ ለማድረግ በብዙ ሲደክም ኖሯል።

 በነዚህ ራስንና ተፈጥሮን በማስማማት ሒደት ውስጥ ብዙ ምርምር የማይሹ፣ ከጥንት ጀምሮ በቀላሉ ማድረግ የለመድናቸው ነገሮች አሉ። ለምሳሌ እሳት ማንደድ። እሳትን በመሰረቱ ሙቀት ለማግኝት ራሳችንን ከብርድ እና ቅዝቃዜ ለመጠበቅ ስንል እናነዳለን።

 ሙቀትን የሚያመነጩ የእሳት ላንቃዎች ሁሉ ደግሞ ቀይ ወይም ጥልቅ ብርቱካናማ ናቸው። በዚህ ምክንያት በተፈጥሮ ልምምድ የተነሳ ከእሳት ውጪ ማናቸውም ቀይ ወይም ቢጫና ብርቱካናማ ቀለም ያላቸው ቁሶች እና መልኮች፤ ሞቃታማ ስሜትን በመፍጠር የሚመረጡ ሆነው ይገኛሉ።

ከጭጋጋማ ይልቅ ብርሃናማ ቀኖች እና ሥፍራዎች ከላይ ከጠቀስናቸው ቀለማት ጋር የሙቀትነት ስሜትን በተፈጥሮ ያመጣሉ ተብለው ይመረጣሉ።

 አዲስ የሃሳብ ድንበር

 የተለመደ ድንበርን መግፋት እና አዲስ የሃሳብ ድንበር መፍጠር፣ የአስተሳሰብ መስመር ገፍቶ ሌላ ተጨማሪ አስተሳሰብ ማምጣት ነው አንዱ እና ትልቁ የጥበብ ሥራ ስሌቱ። ሆን ብለው ይህን ሙከራ የሚያደርጉ አሉ። ይህ ደግሞ በሁሉም ዘንድ የሚፈፀም ይመስለኛል። ልክ ከሳጥን ውጪ ማሰብ (Thinking outside the box) እንደሚባለው የሥነ-ጥበብ ሂደት የራስን አተያይ ለመፍጠር ብቻ ሳይሆን ቀድሞ ያለውን በሚገባ ተረድቶ፤ አብላልቶ በመጠየቅ እና ነባሩን በመናጥ ወይም በነባሩ ላይ በመጨመር ወይም ነባሩን በመሻር አዲስ አተያይ ማምጣት አዲስ ድንበር መፍጠር ማለት ነው።

 ይህ በሁሉም የህይወት መንገድ ውስጥ ይኖራል። በክረምት ውስጥ በጋን ማሰብ ማለት በድህነት ውስጥ ምናልባት ሀብትን ማለም ሊሆን ይችላል። በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ስለተስፋ ማሰብ ሊሆን ይችላል። ሌሎችም በርካታ ያልተለመዱ መንገዶችን ለማየት ይጠቅማል።

 የተለመዱ ስሜቶችን አንዳንዶች ወጣ ብለው “የለም እኛን የሚሰማን ሌላ ነው” የሚሉ ተቃራኒ አስተሳሰቦችን ይዘው ይነሳሉ። በነዚያም ተቃራኒ ሥራዎች ሊታዩ ይችላሉ። እዚያ ላይ ሃሳብ መዳበር ይጀምራል። ንድፈ- ሃሳብ መገንባት ይጀምራል።

አዲስ ነገር የሚገኘው እምቢ በሚሉ አሳቢዎች ነው። አንዳንዴ ብልሆች ከሞኝ ጋር ይመሳሰላሉ የሚባለው በዚህ አፈንጋጭ መንገድ የተነሳ ነው።

ጨለማ፣ ልብስ እና ቀለማት ጭጋግ፣ ጉም፣ ደመና እና ውርጭ ክረምት የሚገለጥባቸው ምልክቶች ናቸው። በዚህ ጊዜ ሰው ሁሉ ወደ አንዳች ጥግ መሸሸግ፣ መንቀጥቀጥ፣ መኮማተር፣ መጠቅለል ሲበዛ የሚታወቅባቸው አካላዊ ምላሾች ናቸው። ይህም መልስ ሙቀትን ለመቆጠብ፣ ሙቀትን ለማምጣት ከማሰብ የመጣ ተፈጥሯዊ ግብረ መልስ ነው።

 የሥነ-ጥበብ ሰዎች ክረምትና ቅዝቃዜው

“ሙቀትን ከመፈለግ ጋር የቤትን ቀዳዳ መጠቅጠቅ፣ ቤትን ማጨለም የተለመደ ነው። ብርሃን ከምን ጋር እንደሆነ አይታወቅም በዛ ሲል እኛ ዘንድ ይፈራል። ይሄ መጠናት ያለበት ነገር ይመስላል።”

 እንዳለ ስሜቱን ከመፍጠር ተሻግረው ደግሞ ይሁነን ብለው ከደለበ ዳመና ውስጥ የፀሐይን ጨረሮች በመሰግሰግ ሙቀትን የሚያሳስቡ ሙቀታማ ቀለማትን በመምረጥ፤ የብርድ እና የሙቀትን ሚዛን እንዲስተካከል ማድረግ ይችላሉ።

አለባበስን ስንመለከት አብዛኛውን ጊዜ በክረምት ከፀጉር እስከ እግር ድረስ የሚሸፈንበት በእጅ የሚንጠለጠሉ ነገሮች ሙቀትን ለመፈለግ (አብዛኛው ምርጫ ከኢኮኖሚ ከባህል እና ከአካባቢ ጋር ቢያያዝም) በቀለም ደረጃ አለባበሱ ጠቆር ያለ እና ዓይነቱ ወደ ግራጫ ሊያደላ ይችላል። ሆኖም ስለፋሽን እና ስለቀለም ንቁ እና ብልህ የሆኑ ሰዎች በተለይም ሴቶች ባለ ሞቃታማ ቀለማት ልብሶችንና ቁሶችን ሲያዘወትሩ ይታያል።

 ቤት፣ ክረምት እና ብርሃን

ሙቀትን ከመፈለግ ጋር የቤትን ቀዳዳ መጠቅጠቅ፣ ቤትን ማጨለም የተለመደ ነው። ብርሃን ከምን ጋር እንደሆነ አይታወቅም በዛ ሲል እኛ ዘንድ ይፈራል። ይሄ መጠናት ያለበት ነገር ይመስላል።

 የቤት ውስጥ ወለሎች፣ ግድግዳዎች፣ መደርደሪያዎች ሁሉ በክረምት ወራት ጥቅጥቅ ይላሉ። ውጭ ደጃፍ እና ጣራ ላይ የነበሩ ሁሉ በክረምት ወደ ቤት ይሰበሰባሉ። ቤት ውስጡ ይጨልማል። በዚያም ሙቀት መፈጠሩ ሳይታመንበት አልቀረም።

 ክረምት እና ዘመናዊ ሥነጥበባት

 መቼም በሁሉም ዘመን የሰው ልጅ ስሜቱን በየወቅቱ ጥበባት አማካይነት እየገለፀና እየተናገረ ዛሬ ላይ ደርሷል። የዛሬውን ፍላጎቱንና ስሜቱን ደግሞ በዛሬው የጥበብ ዓይነት ቢገልፅ ይመረጣል። ሁሉም ጥበብ የጊዜውን ሀሳብ እና ፍላጎት ተሸክሞ ከጊዜው ምቾት እና ግብ ላይ አድርሷል። ዛሬም ከዚያ የተለየ አይደለም። ያም ሆኖ የሰው ልጅ በአስተሳሰቡ ከሚያስገኛቸው የሥልጣኔ ትሩፋቶች ውጪ መሠረታዊ የሰው ልጅነቱ ስለማይለወጥ ወይም የማይለወጡ ባህሪያት በመኖራቸው የተነሳ አንዳንድ ሁሌም ሊፈፅም የሚወዳቸው የጋራ ድርጊቶች አሉ። ለምሳሌ ሙቀትና ንቃት ፍለጋ ብሎ በክረምት ወይም በቅዝቃዜ ወቅት አረቄን ከውስጥ ይለብስ ነበር። ዛሬም አረቄ ከውስጥ የሚለበስባቸው አገሮች እና ማኅበረሰቦች ብዙ ናቸው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top