አጭር ልብወለድ

«የቋንቋ፣ የጽሑፍ የሂሳብ እና የገንዘብ መንስዔ በፍንጃል»

(ክፍል አንድ)

መግቢያ

ለመንደርደሪያ ያህል

 በማራኪ ድርሰት፣

 በሰለተ ቅኝት፣

 በሊቃውንት ዓለም፣

 ቋንቋ ድምፆች ናቸው፣ ፊደላት አይደሉም፤ ወኪል ተጠሪ እንጂ፣ ባለቤት አይሆንም ።(ከስንኝ መሰሮ)

ምን ነበር? የት ነበር?

ማስታወስ ቸገረ፤

የችግር መቅረፊያ ጽሑፍ ተፈጠረ።

ምን ያህል? ስንት ነው?

ስሌት አስቸገረ፤

የችግር መፍተሄ ሂሳብ ተቀመረ።

1 በቋንቋ መግባበት በጽሑፍ እና በሂሳብ ስሌትመጠቀም እንዲሁም መግዛት እና መሸጥ የዕለት ከዕለት ተግባሮች ስለሆኑ፣ የእነሱን አመጣጥ በመጠኑም ቢሆን መገንዘብ ጠቀሜታ አለው ብዬ ስለማምን ይህችን ዓይነት ጽሑፍ ለአንባቢያን ለመቅርብ ከተመኘሁ ዘመናት አልፈዋል። ከዘመናት በኋላ ሁኔታው ስለተመቻቸልኝ (ለዚህ ተግባር እኔ በምፈለገው መንገድ ትኩረት የሰጡ መጻሕፍት ባለፉት ዓመታት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ስለታተሙ) አሳቤ ተሳክቶልኝ የተመኘሁትን በጨረፍታም ቢሆን ለመዳሰስ በቅቻለሁ፡፡

 ይህን ዓይነት ጽሑፍ ለማቅረብ በሚሞከርበት ጊዜ አንባብያኑ ስብጥር እንደመሆናቸው መጠን ፍላጎታቸውም ስብጥር ስለሚሆን፣ በምን ደረጃ እና ጥልቀት ጽሑፉ መቅረብ አለበት የሚለው አንድ አቢይ ችግርነው። ለአንባብያን ሁሉ ተመጣጣኝ የሆነ ጽሑፍ ማዘጋጀት ያዳግታል፣ በተጨማሪም በእኔ ላይ የሙያ አባዜ አለብኝ፣የሥነ-ሕያው ተማሪ እንጂ የቋንቋም ወይም የሂሳብ ባለሙያ አይደለሁም። ያም ቢሆን ያለኝን መጠነኛ ግንዛቤ ከማካፈል የሚገታኝ የለም።

 የቋንቋ መሠረት ምንድን ነው? የቋንቋ መሠረት (አመጣጥ) ብዙ ሊቃውንትን የሚያወዛግብ ጉዳይ ነው፣ ስለ ቋንቋ አመጣጥ ብዙ የተሰነዘሩ አስተያየቶች አሉ፣ ሆኖም በዚህ ጽሑፍ የቋንቋንአመጣጥ በግርድፉ በሁለት ፈለጎች ብቻ እወስነዋለሁ።

 ሀ/ አንዱ፣ ቋንቋ ከሰበ-ቀደምት ቅድመ አያቶቻችን (እንስሳት) ቀስ በቀስ እየተቀየረ የተወረሰ ችሎታ ነው፣ ያለማቋረጥ ቀስ በቀስ የተደረገ ሂደት ውጤት ነው የሚለው ሲሆን፣ይህም «ኮንቲኒዊቲ ቲዎሪ» ተብሎ ተሰይሟል።2በዚህ አስተያየት የሚያምኑ፣ የቋንቋ ምንጭ ነባር የሆነ የሕያው አካል መሠረታዊ ችሎታ እንደሆነ መወሰድ አለበት ይላሉ።

 / ሁለተኛው፣ ቋንቋ በሌሎች እንስሳት ዘንድ መሰል የሌለው፣ በሰው ልጅ ዝግመተ ለውጥ በድንገተኛ የሃብለ-በራሂ መቀየር መንስዔ ከ100,000 ዓመት በፊት የተከሰተ ልዩ የሰው ልጅ ችሎታ ነው የሚለው ሲሆን፣ይህም አመለካከት«የዲስኮንቲኒዊቲ ቲዎሪ» የሚበላው ነው። በዓለማችን አሁን አሉ ከሚባሉት ጥቂት ሁለገብ ሊቃውንት አንዱ «ኖኣም ቾምስኪ» እንደ ብዙ ሌሎች የዘመናችን የታወቁ የቋንቋ ሊቃውንት ሁሉ ቋንቋ በድንገት የተከሰተ ችሎታ ነው ብሎ ነው የሚያምን።

 ለቋንቋ አመጣጥ መሠረት አንድ ዓይነት አስተያየት ብቻ ባይሰጥም ብሎም ስምምነት ባይኖርም በቋንቋ ተግባር ላይ ግን ስምምነት ያለ ይመስላል። ቀደም ብሎ በመተሻሸት በመደባበስ አማካኝነት ይገለጥ የነበረውን ቅርበት እና መግባባትን፣ ቋንቋ በድምጽ ወኪልነት ነው የተካው ይላሉ። የእንስሳት ቡድን ስብስብ ቁጥሩ እየጨመረ በሄደ መጠን፣ ከእያንዳንዱ ነጠላ አካል (ግል- አካል) ጋር መተሻሸት መደባበስ አይቻልም። የማይቻልበትም ዋና ምክንያት ሁሉንም ለመዳበስ በቂ ጊዜ ስለማይኖር ከጊዜ ማባከን አኳያ ታይቶ ነው። በቋንቋ ግን ለብዙ መሰል አካላት በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ መልእክቶች ማሰራጨት ይቻላል። በቋንቋ «እከኪልኝን»፣ «ዝለይልኝን» ዓይነት ድርጊት ወደ «ዝፈኝልኝ» ተቀየረ፣ ድርጊቱን ድምጽ ተካው እንደማለት ነው።

 ሌሎች ሊቃውንት ደግሞ ቋንቋ የተካው ከአካል ክፍል የሚተገበረውን ንቅናቄ ነው ይላሉ፣ የአካል ምልክት መስጠትን (ለምሳሌ በእጅ ውዝዋዜ መልዕክትን ማስተላለፍ)። ለዚህም አስተያት ዋናው መሠረት ጭንቅላት ውስጥ ቋንቋን የሚያስተናግደው (የሚመራው) የአንጎል ክፍል እና በእጅ ምልክት መስጠትን የሚመራው የአንጎል ክፍል ተጠጋግተው (ቅርብ ለቅርብ) ስለሚገኙ ነው። ከላይ የተተነተነው በቋንቋ አመሠራረት ያለውን አስተያየት በጨረፍታ ለማመልከት ብቻ ያህል ነው ፣ ቋንቋ ራሱን የቻለ ሰፋ ያለ ገለጣ ያሸዋል፣ ያም ከዚህ ጽሑፍ ዓላማ ውጭ ነው።

 ቋንቋ ለሰው ልጅ ያበረከተውን አዲስ አቅም እና የዚያን አቅም ውጤት ልዳስስ

 ) ቋንቋ፣ የሰውን ልጅ ስለሚኖርበት አካባቢ በአንድ ጊዜ ብዙ መረጃን እንዲያስተላልፍ አስችሎታል፣ የዚያም የጎላ ውጤት ቀደም ብሎ እቅድ ለማውጣት፣ በአንድ ጊዜ ውስብስብ ድርጊቶችን ማከናወን ማስቻል ነው። ለምሳሌ ድኩላ ማደንን እና በአንበሳ እንዳይጠቁ መጠንቀቅን፣ ሁለት ተፃራሪ ተግባራት በጥሞና አስልቶ መፍትሄ ማግኘት የሚያስችል፣ መልእክት በአንድ ጊዜ ለማስተላለፍ ያበቃል። ለምሳሌ ብዙ ዱኩላዎች ከወንዙ ማዶ አሉ፣ ወንዙን ስትሻገር ግን በግራ በኩል ዛፍ ስር አነበሶች ስለአሉ ተጠንቀቅ ብሎ የተለያዩ መልእክቶችን በአንድ ጊዜ ለማስተላልፍ ቋንቋ ያስችላል።

 ለ) ስለ ሰው ልጅ የእርስ በእርስ ግንኙነት ብዙ መረጃ ያበረክታል። የዚያም የጎላ ውጤት ከሌሎች እንስሳት በላቀ መልክ የብዙ የስብስብ አባሎች የጋራ ትስስር መፍጠር ማስቻሉ ነው። የሌሎች እንስሳት ማህበራዊ ስብስብ ቢበዛ እስከ አርባ ወይ አምሳ ቢሆን ነው ይባላል፣ የሰው ልጅ ግን በቋንቋ ታግዞ ቁጥራቸው እስከ 150 የሚሆኑ ግለሰቦችን ያሰባሰበ ሕብረት መፍጠር፣ ብሎም መምራት፣ ማስተባበር፣ ይችላል። ሐ) የሰው ልጅ፣ በቋንቋ ታግዞ፣ አንጎል የፈጠረው የሌለን «አካል- አልባ» የሆነ ጉዳይ፣ እንዳለ አድርጎ ማሳመን ይችላል።

ስለዚህ ጭንቅላቱ ውስጥ ስለፈጠረው «አካል-አልባ» የማይታይ፣ የማይዳሰስ፣ የማይሸተት አካል፣ በተጨባጭ አከል ሁኔታ መረጃ ማስተላለፍ ችሎ ሌሎችም በጉዳዩ እንዲያመኑ ያደርጋል ማለት ነው። ለምሳሌ እንደ «ኩባንያ»፣ «የሰው ልጆች መብት» ወዘተ….ያሉትን ጉዳዮች፣ «አካል-አልባ» ቢሆንም እውን እንደሆነ (አካል አነዳለው) አድርጎያወሳል። የዚያም የጎላ ውጤት በጣም ብዙ ሰዎችን በአንድ አስተሳሰብ ጥላ ስር እንዲጠለሉ ማድረግ ማስቻል፣ ፈጣን የሶሽያል ለውጦችን ማካሄድ፣ ወዘተ መቻሉ ናቸው።

የቋንቋ ዋና ተግባር

የቋንቋ ዋና ተግባር የአንድ ስብስብ ማሰተሳሰሪያ ገመድ ሆኖ ማገልገሉ ነው። ቋንቋ በቀላሉ መልእክትለማስተላለፍ፣ መረጃ ለመስጠት፣ ወዘተ የሚያስችል ችሎታ ነው። ለዚህ ተግባር ይረዳን ዘንድዘመዶቻችንን ችምፓንዚዎችን እንደ ምሳሌነት እንውሰዳቸው። ከዘመዶቻችን ጋር የዘር ሀረጋችን የተለያየ ከስድስት እስከ ሰባት ሚሊዮን ዓመታት ከሚገመት ጊዜ በፊት ነው (ይህ ጊዜ ከሕያው የ3.4 ቢሊዮን ዓመት ጉዞ ጋር ሲነፃፀር በጣም አጭር ዘመን ነው) ።  ችምፓንዚዎች በቡድን (ሕብረት) ነው ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ የሚያድኑ ከጠላቶቻቸው ጋር የሚጋፈጡ። የቡድን መሪ አውራ (አለቃ) አላቸው፣ አለቃው ሁልጊዜም ወንድ ነው፣ አውራ አልፋ ተባእት በመባል ይታወቃል። ጭፍሮችም ለአለቃቸው ይሰግዳሉበአጠቃላይ ሽር ጉድ ይላሉ። አውራውም የሚመራው የቡድኑ አባላት በሥነ-ሥርዓት እንዲተዳደሩ ይቆጣጠራል፣ በጭፍሮች መኻል ግጭት ሲፈጠር ጠብ ሲጫር ያስታርቃል ይገላግላል። የቡድን አባላት ዝምድና ቅርበት በመተቃቀፍ በመሳሳም በመተሻሸት በስጦታ ይተገበራል ይረጋገጣል።

 አውራው የበላይነቱን የሚያረጋግጥ በጡንቻው ተመክቶ በጡንቻው በመጠቀም (ጉልበተኛነት) ብቻ አይደለም። የበላይነቱን የሚያረጋግጥ የማህበሩ (ቡድኑ) ትስስር እንዳይላላ በመቆጣጠሩ ጭምርም ነው። ቡድኑ ምግብ ተጋርቶ እንዲበላ ጠላት ሲመጣ በመተጋገዝ እንዲመክት፣ ወዘተ፣ ማድረግ በመቻሉ ነው፣ ስለሆነም በዱር እንስሳት ዓለም ስንኳ ግዛት በዘዴ እንጅ በጉልበት አይተዳደርም።

የአንድ ችምፓንዚ ቡድን አባላት ቁጥር ቢበዛ እስከ አምሳ ይደርሳል። የአባላቱ ቁጥር ከዚህ ከፍ ካለ ቡድኑን ለመቆጣጠር ያዳግታል። የቁጥር መጨመር ችግር የሚፈታው ሌላ ቡድን በመመሥረት ነው። የተለያዩ ቡድኖች ብዙ ጊዜ እርስ በእርስ አይስማሙም፣ የመሰማሪያ ቦታ ይዞታም ሆነ፣ በምግብ ፍለጋ፣ በቡድኖች መኻከል ግጭት ይከሰታል።ችምፓንዚዎችን ከዚህ አንፃር ስንመለከት ከሰው ልጅ ጋር ተመሳሳይ ባህሪዎች አሏቸው፣ ለምሳሌ አለቃ እና ጭፍራ አላቸው፣ በህብረት (በቡድንም) ይኖራሉ።

 የጥንት የሰው ልጆች ቡድን አባላት ብዛት ከ150 አይበልጥም ነበር ይባላል። ቁጥሩ ከዚህ ከላቀ እርስ በእርስ የጠበቀ ግንኙነት ለመፍጠር አዳጋች (አስቸጋሪ) ይሆናል። በአሁን ዘመን ስንኳ የጠበቀ ግንኙነት ለመፍጠር እና ለመተዋወቅ የሚችሉ ግለሰቦች ቁጥር ወደ 150 ገደማ ነው ብለው በሙያው የተሰማሩ ግለሰቦች ያወሳሉ፣ቁጥሩ መጠነኛ በሆነ መጠን መቀራረቡ (መተሳሰቡ) የጠነከረ ይሆናል። በዚህ ይዘት የቤተሰብ ንግድ ካለሂሳብ ሹሞች፣ ፍትህ ካለ ፍርድቤት ማካሄድ፣ እንዲሁም ጥቂት ወታደሮችን ካለ የበላይ መኮንን (ካለ አዛዥ) ማሰማራት ይቻላል።

 ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሰው ልጆች ይህንን የቡድን አባላት የመጠን ገደብ ለመጣስ ችለዋል። ይህን ለማድረግ የሚቻለው በሚሊዮኖች/ ቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ግለሰቦችን የሚያስተሳስር/የሚያስማማ፣ ሁሉም በጋራ የሚያምኑበት አካል ሲኖር ነው። በሂደት በህብረት በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ግለሰቦችን የሚያስተባብሩ መንግሥታትን ለመመሥረት፣ እንዲሁም በተለያዩ መንግሥታት ስር የሚተዳደሩ ቢሊዮኖች የሚቆጠሩ፣ በዘር በቋንቋ ግንኙነት የሌላቸውን ሕዝቦች በአንድ የእምነት ጠለላ ለማሰባሰብ ተችሏል። ይህንን ለማድረግ እንዴት ተቻለ? ለሚለው ጥያቄ መልስ ያሻል። ችግሩን ለመፍታት ያስቻለው፣ ሚስጢሩ፣ «ልብ ወለድ እምነት» ሳይሆን አይቀርም ይባላል።

ለምሳሌ በመንግሥታት ጠለላ ስር ከሩቅ ገጠሮች የተሰባሰቡ የማይተዋወቁ ግለ ሰቦች በጋራ አገር ወራሪ ጠላትን ይከላከላሉ። ሁለት የማይተዋወቁ ኢትዮጵያውያን ውጭ አገር ሲገናኙ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለብዙ ዘመናት የሚተዋወቁ በመሰለ ደረጃ በጋራ ከተሞችን ሲጎበኙ ምግብ ሲመገቡ ሲጫወቱ ይታያሉ። ይህን ለማድረግ ያስቻላቸው የአንድ አገር ሰዎች መሆናቸው ነው። እንዲሁም ሁለት የማይተዋወቁ የሕግ ባለሙያዎች (ጠበቃዎች) ለአንድ ጉዳይ ቡድን መስርተው (ቦድነው)፣ በሕግ ፊት ቀርበው ከተቃራኒ ወገን ጋር ሲከራከሩ ይታያሉ። ጥያቄው እነኝህን የማይተዋወቁ ግለሰቦች ምን አስተሳሰራቸው? የሚለው ይሆናል።

 እንግዲህ በጦርነት አገር ለመጠበቅ ጠላት ለመከላከል የተሰማሩትን ግለሰቦችንም ሆኑ፣ ውጭ አገር የተገናኙ ኢትዮጵያውያን ያስተሳሰራቸው፣ ኢትዮጵያ የምትባል የጋራ አገር ስላለቻቸው፣ እንዲሁም የሕግ ባለሙያዎችም መሠረታዊ የሰው ልጅ መብት (የሰው አንጎል የፈጠረው) አለ፣ የመተዳደሪያ ሕግ አለ ብለው ስለአመኑ ነው። ከላይ እንደተጠቀሰው ግለሰቦችን ሕዝቦችን ያስተሳሰሩ ያቀራረቡ፣ ከጋራ ግንዛቤ የፈለቁ የማይታዩ የማይዳሰሱ ክስተቶች ናቸው።

ከሰው ልጅ አስተሳሰብ (እምነት) ውጭ አገርም ሆነ የሕግ ሥርዓት የለም። የሁሉም ዋልታ (ምሰሶ) የጋራ እምነት፣ አስተሳሰብ ነው ይባላል።

 ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰው ጭንቅላት የፈለቀ ልብ- ወለድ ቅርፅ (በምድር ላይ የሌለ ዓይነት እንስሳ ቅርፅ ነው) ፣ ያም የሰው አካል እና የአንበሳ ጭንቅላት ያለው ምስል የተገኘ ጀርመን አገር አንድ ዋሻ ውስጥ ነው። የተቀረፀም ከ32,000 ዓመት በፊት እንደነበረ ይገመታል። የሌለን እውን ያልሆነ ነገር አለ ብሎ ማሰብ መቻል፣ ብሎም አካልን መቅረፅ ልብ ወለድ (አእምሮ ፈለቅ) ነው።

ለዚህ ዓይነት አስተሳሰብ በዝርዝር ትችት ያቀረቡ ብዙ ምሁራን አሉ። በዚህ ጽሑፍ «ኖህ ሃራሪ» የሚባል የታሪክ ምሁር ያቀረባቸውን አስተያየቶች እና ምሳሌዎች በገፍ አካትታለሁ። «ኖህ ሃራሪ» የሌለን አካል እንደ አለ አድርጎ መውሰድን ለማስረዳት የተጠቀመው «የፔጆ» ኩባንያን እንደ ምሳሌነት በመውሰድ ነበር።

 «ፔጆ» የተቋቋመው በ13ኛው ምዕት ዓመት፣ ድርጅቱን የመሠረተው የመጀመሪያው ግለሰብም በዘመኑ የተሰማራ በፈረስ የሚጎተት ጋሪ በመሥራት ላይ ነበር። ሆኖም የሠራው ጋሪ ከአሠራር ጉድለት በድንገት ቢሰበር፣ ተከሳሹ ግለሰቡ ነበር፣ ለሥራ ማካሄጃ ገንዘብ ቢበደር ከፋዩ ግለሰቡ ነበር፣ ተከሳሽም ታክስ ከፋይም፣ ወዘተ፣ ግለሰቡ ነበር። ብድር ባይከፍል ቤቱ ፈረሱ፣ ወዘተ. ተሸጠው፣ እዳውን (የተበደረውን) የመክፈል ግዴታ ነበረበት።

 ስለሆነም በዚያን ዘመን በንግድ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ግለሰቦች፣ ገንዘብ ከመበደራቸው በፊት መጠበብ መጨነቅ ነበረባቸው፣ ምክንያቱም ብድሩን መመለስ ቢሳናቸው ሕይወታቸው በጠቅላላ ይመሰቃቀል ስለነበረ ነበር። ይህን ችግር ለመፍታት ሰዎች ተሰብስበው የልብ ወለድ (የአእምሮ ፈጠራ/ አእምሮ ፈለቅ) አካል ፈጠሩ፣ «አካል-አልባ» የማይታይ የማይዳሰስ የማይሸተት ልብ ወለድ «አካል» («አካል- አልባ») ተፈጥሮ «ኩባንያ» የሚባል ስም ተጎናጸፈ። ከዚያም ኩባንያዎችም ልክ እንደ ግለሰቦች ሁሉ እንደ «አካል» ተቆጠሩ፣ አካላት ሆኑ፤ ሲያተርፉ ትርፍ ተካፋይ የጋራ ባለቤቶች ሲሆኑ፣ ሲከስሩ ግን በግል ተጠያቂዎች ኩባንያዎች ብቻ ሆኑ። ከዚህ የላቀ የፈጠራ ስሌት ከወዴት ይገኛል?

 ከላይ የጠቀስነው «ፔጆ»፣ በ1896 ድርጅቱን በወረሰው በአርማን ፔጆ ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ በስሙ ተቋቋመ። ምንም ኩባንያው በስሙ ቢጠራም ኩባንያው ራሱን የቻለ አካል ነበር። ለምሳሌ በጥራት ጉድለት አንድ የፔጆ መኪና ከሥራ ውጭ ቢሆን የሚከሰስ ኩባንያው እንጂ አርማን ፔጆ አልነበረም። የሰው ልጁ አርማን ፔጆ በ1915 አርፏል፣ ኩባንያው ግን አሁንም አለ። በመሰረቱ ተረትን ፈጥሮ ሌሎች በተረቱ እንዲያምኑ ማድረግ ማሳመን ቀላል አይደለም። ለማሳመን ከተቻለ ግን ከዚያ የተሻለ የማይተዋወቁ ግለሰቦችን የሚያስተሳስር ኃይል የለም (ለምሳሌ በኩባንያ ደንቦች፣ ሕጎች፣ ሥርዓት ለመገዛት፣ አንድ አካባቢን አገሬ ብሎ ለማመን፣ ወዘተ)። በመጀመሪያ የ«ፔጆ»ን አርማ እንውሰድ፣ አርማው ከሰው ጭንቅላት የፈለቀ አንበሳ መሰል አካል ነው። «ፔጆ» በፈረንሳይ አገር ለዘመናት መኪና በመፈብረክ ላይ የተሰማራ የመኪና ፋብሪካ ነው። በዘመናችን ፔጆ ከ200,000 በላይ ሰዎች ቀጥሮ በሥራ ላይ አሰማርቷል፣ በየዓመቱ በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ መኪናዎች ያመርታል፣ እንዲሁም በየዓመቱ በቢሊዮኖች የሚተመን፣ ዩሮ ያተርፋል።

 እንግዲህ ስለ «ፔጆ» ስናወሳ፣ ብዙ መኪናዎች እንደሚፈበርክ አውስተናል፣ መኪናዎች ኩባንያው አይደሉም፣ ኩባንያውም ፔጆ መኪናዎች አይደለም፣ መኪናዎች እና የፈበረካቸው ኩባንያ የተለያዩ አካላት ናቸው። ለምሳሌ ነገ ጠዋት በዓለም ላይ ያሉ የ«ፔጆ»መኪናዎች ሁሉ ተጨፍልቀው ቢቀልጡ፣ ኩባንያው ሕያው እንደሆነ ይቀጥላል፣ ወይም በተቃራኒው ኩባንያው ቢከስር እና በሕግ ቢዘጋ፣ ከስሟል ሞቷል ቢባል፣ መኪናዎች ሥራቸውን አያስተጓጉሉም፣ የመኪናዎችም ባለቤቶች የኩባንያው መፍረስ ጉዳዩ አይነካቸውም (ወቅታዊ ችግር አይፈጥርባቸውም)። እንዲሁም ነገ የ«ፔጆ» ሠራተኞች ሁሉ ከሥራ ቢባረሩ፣ ኩባንያው ከምድር ገፅ አይወገድም፣ የተፈበረኩ መኪናዎችም እንዲሁ።

 ስለሆነም የ«ፔጆ» ኩባንያ ከእምነታችን ውጭ፣ የሚታይ እና የሚዳሰስ አካል የለውም፣ ባለቤቶችም ሆኑ ሌሎች የንብረቱ ተጋሪዎች ባይኖሩ፣ «ፔጆ» የፈበረከው መኪና አንድም ስንኳ መንገድ ላይ ባይታይም፣ «ፔጆ» ኩባንያ አለ። ያለው ግን የሚዳሰስ ወይም የሚታይ አካል ሆኖ ሳይሆን በጋራ እምነት ላይ ተመሥርቶ ነው። ከእምነታችን ውጭ «ፔጆ» ሊኖር አይችልም፣ አካለ-ቢስ ነው። በአካባቢያችን ያሉ አካላትን መኖር የምናረጋግጥባቸው ሕዋሳት፣ የ«ፔጆ»ን መኖር አያረጋግጡልንም፣ የሚታይ ወይም የሚዳሰስ አካል አይደለም፣ የሚጣፍጥ ወይም የሚመር ጣእም የለውም፣ አይሸትም መዓዛ አልባ ነው።

 በተጨባጭ ዓለማችን ውስጥ «ፔጆ» አለን? ብሎ መጠየቅ ይቻላል። በሕያው መረጃ አሰባሰብ ላይ መሥርተን (ማለት ማየት፣ መዳሰስ፣ ማሽተት፣ ወዘተ) መልሱ

“ለምሳሌ በመንግሥታትጠለላ ስር ከሩቅገጠሮች የተሰባሰቡየማይተዋወቁ ግለሰቦች በጋራ አገር ወራሪጠላትን ይከላከላሉ።ሁለት የማይተዋወቁኢትዮጵያውያን ውጭአገር ሲገናኙ በአጭርጊዜ ውስጥ ለብዙዘመናት የሚተዋወቁበመሰለ ደረጃ በጋራከተሞችን ሲጎበኙ ምግብሲመገቡ ሲጫወቱይታያሉ። ይህንለማድረግ ያስቻላቸውየአንድ አገር ሰዎችመሆናቸው ነው”

የለም ነው። የሕግ ባለሙያዎች የ«ፔጆ» መኖርን ዓይነት ሁኔታ ሕጋዊ ልብ ወለድ ብለው ሰይመውታል። የ«ፔጆ» መኖሩን የሚያረጋግጥልን ሕግ ብቻ ነው። አካል-አልባ ሕጋዊ አካል ሕግ የፈጠረው ልብ ወለድ አካል ነው። እንደ አንድ ግለሰብ ሁሉ በሕግ ሊጠየቅ ይችላል፣ የመንግሥት ታክስ ይከፍላል፣ እንደ ግለሰብም የባንክ ሂሳብ ይከፍታል፣ ከግለሰቦች ጋር ሆነ ከሌላ የሱ አምሳያ ልብወለድ አካላት ጋር ስምምነት (ውል) ሊገባ ይችላል፣ በሕግ ፊት ሌሎች ሕያው አካል በሚታዩበት ዓይን ይታያል፣ ይፈረጃል።

ይህ አስተሳሰብ «ልብ ወለድ አስተሳሰብ”፣ የሰው ልጅ ከፈጠራቸው፣ ከዋናዋናዎቹ፣ ተግባራት ሁሉ በላቀ ደረጃ ይመደባል። የጥንት ሰዎች ለብዙ ሺ ዓመታት፣ ለዚህ የሰው አእምሮ ለፈጠረው አስተሳሰብ ሳይገዙ ይኖሩ ነበር። በዚያን ዘመን ሃብት በግለሰቦች እጅ ነበር። ባለሃብቶች የሚታዩ፣ የሚዳሰሱ፣ የሚሸተቱ፣ ሥጋ ለበስ አካላት ብቻ ነበሩ።

 በሚታይ፣ በሚዳሰስ ላይ መስርተን፣ ለምሳሌ በአካባቢያችን በሚገኝ ተራራ፣ በመንደራችን ጥግ በሚፈስ ወንዝ፣ በእንስሳት፣ወዘተ. ታሪክ ላይ መስርተን የሚያስተሳስረን ኃይል ለማግኘት በጣም ያዳግታል። ሆኖም በአንፃሩ የማይታይ የማይዳሰስ፣ «አካል» አንጎል ፈብርኮ አካባቢውን ለማሳመን ከቻለ የፀና ትስስር ለመገንባት ይቻላል። የሰው ልጅ ያን ለማድረግ ስለቻለ ነው ዓለምን የተቆጣጠረው ይባላል።

 ይህ ነው እንግዲህ የአስተሳሰብ አብዮት መሠረት ነው የሚባለው። ከዚህ አብዮት በኋላ የሰው ልጅ በሁለት ዓለም ውስጥ መኖር ጀመረ፣ በሚታየው እና በማይታየው ዓለም (በማይዳሰሰው ዓለም)።በዚህ መንገድ በሥነ ሥርዓት በማህበራዊ ሕግ የሚተዳደር፣ ከጫካ (አራዊት) ሕግ የተለየ ዓለም ተፈጥሯል። ይህን አስተሳሰብ አንግበው ሥርዓቱን በጥሞና ለሚጠቀሙበትም፣ በተመጣጣኝ ደረጃ ባይሆንም፣ ለብዙ ለተለያዩ ህዝቦች አለኝታ ለመሆን በቅቷል። በሰላም የመኖር አለኝታ የህብረተሰብ አስተባባሪ፣ ሥርዓት መሠረት ሆኗል።

 አንድለየት ያለ የቋንቋ ተግባር ስለማይታዩ ስለማይዳሰሱ ከአእምሮ የመነጩ ጉዳዮችን አስልቶ፣ ስለ እነሱ መረጃ ማስተላለፍ መቻሉ ነው። ከላይ እንደተጠቀሰው ቋንቋ ያለን፣ የሚታይን አካል፣ ጉዳይ፣ መግለጫ ብቻ ሳይሆን፣ ከአእምሮ የፈለቀንም ጉዳይ ማስረጃ ማስፋፊያ፣ ማሰራጫ ሆነ። ይህ የፈጠራ ችሎታ የሰው ልጆች የትም ይኑሩ የት ማስተሳሰሪያ ብሎም በአንድ መንገድ እንዲያስቡ የሚያደርግ ዋና መሣሪያ ሆነ።

 ለምሳሌ ንቦችም ሆኑ ጉንዳኖች በህብረት የሚተገብሯቸው ጉዳዮች አሉ፣ ግን ያተገባበሩ ስልትም ሆነ ተግባሮች ውስን ናቸው። ህብረቱ ትስስሩአንድ ላይ በመኖር እና በዝምድና ይገረገራል፣ ይታጠራል፣ የእነሱ ተግባሮች ሙሉ በሙሉ ለበራሂ ተገዢዎች ናቸው፣ መሠረቶቻቸው ሙሉ በሙሉ በራሂዎች ናቸው።

 አዲስ የተገኘው ችሎታ («ቋንቋ») የመግባቢያ ስልት ቀደም ከነበረው የመግባቢያ ስልት በምን ይለያል? ጦጣዎች የተለያዩ ድምጾችን በማፍለቅ ለወገኖቻቸው መልእክትን ማስተላለፍ ይችላሉ። ለምሳሌ «ተጠንቀቁ ከላይ ንስር እያንዣበበ ነው»፣ ወይም በመሬት «አንበሳ እያደባ ነው» እያሉ። እነኝህን የተለያዩ ድምጾች በድምጽ መቅጃ ቀርፆ (ቀድቶ) በማሰማት፣ ጦጣዎች ንስር ከላይ እያንዣበበ ነው ሲባል ሲደበቁ፣ አንበሳ በመሬት እያደባ ነው ሲባል ወደ ዛፍ ላይ ዘለው ሲወጡ ለማየት ተችሏል።

የሰውን ልጅ ቋንቋ ከዚህ ዓይነት መልዕክት ማስተላለፍ የሚለየው በቋንቋ ሊተገበር የሚችለው መልዕክት ተዝቆ የማያልቅ በመሆኑ ነው፣ ቋንቋ ባህር ነው። አንድ ግለሰብ ለሌላ ግለሰብ በዱር አውሬ እንዳይጠቃ፣ ለምሳሌ በአነበሳ፣ መልዕክት ሲያስተላልፍ፣ አንበሳ በአካባቢው መታየቱን ብቻ ሳይሆን፣ ዘርዘር ባለ ሁኔታ (በምን ርቀት፣ የት አካባቢ፣ በየት አቅጣጫ፣ ለምሳሌ ዛፍ ጥላ ስር፣ በውሃ መጠጫችን መንገድ በግራ ዳር፣ ከወንዙ ጥግ ብሎ) ማስረዳት ይችላል።

ቀደም ሲል በመቶ ሺዎች የሚገመቱ የተለያዩ ቋንቋዎች አንደነበሩ ቢታወቅም ፣ በዘመናችን ያ አሃዝ በጣም ቀንሷል፣ የሰው ልጆች ግንኙነት እየጨመረ በሄደ መጠን ቋንቋዎች ይከስማሉ። በእኛ ዘመን ስንኳ በኢትዮጵያ ይነገሩ የነበሩ ጥቂት ቋንቋዎች (ምሳሌ ጋፋት) ከስመዋል። አሁንም ለምሳሌ በናይጀሪያ ከሁለት መቶ በላይ፣ በኢትዮጵያ ከሰባ በላይ የሆኑ የተለያዩ ቋንቋዎች አሉ።

 ከቅርብ ጊዜ በፊት (ከመቶ ሺ ዓመት ያነሰ) ዓለምን የሚጋሩን ሌሎች የሰው ዘሮች ነበሩ፣ እኛ፣ በሳይንሳዊ ስያሚያችን «ሆሞ ሳፕያነስ» ነው የምንባል፣ ከኛ ጋር መሬትን ይጋሩ የነበሩ፣ ሁለቱን ላውሳ፣ «ሆሞ ኒያንደርታሌንሲስ»ንእና «ሆሞ ኤሬክተስ»ን። አነኘህ የቅርብ ዘመዶቻችን ልብ ወለድ አሳብ ለማመንጨት፣ ብሎም ወገንን በአሳብ ለማስተሳሰር ስላልቻሉ፣ የወንድም ጠላት የሆንነውን እኛን «ሆሞ ሳፕያንስን» መቋቋም ተሳናቸው። ዝምድናን ትንሽ ግልጥ ለማድረግ እንዲረዳን ያህል አንበሳ እና ነበርን እንደምሳሌነት ወስጄ የዘመዳመነት መግለጫውን ላውሳ። አንበሳ የሳይንስ ስሙ፣ «ፓንቴራ ሊዎ» ሲሆን የነብር ደግሞ «ፓንቴራ ፓረዱስ» ነው፣ የጋራ ስያሚያቸው «ፓንቴራ» የዝምድና ማስረጃ መግለጫ ነው።

 «ሆሞ ኒያንደርታሌንሲስ» እና «ሆሞ ኤሬክተስ» ሽንፈታቸውን እስከማረም የሚያበቃ የአእምሮ ችሎታ አልነበራቸውም። ዋናው ምክንያት እነሱበተፈጥሮ ሕግ ብቻ ነበር የሚተዳደሩ፣ አነሱን የሚያስተባብር የማይታይ የማይዳሰስ፣ የማይሸተት «አካል» አልፈጠሩም ነበር።

 እምነት እና ንግድ ብሎም ገንዘብ

እንደ እኛ አካባቢ የቅርብ ትዝታ እያንዳንዱ ግለሰብ ለኑሮው የሚያገለግለውን ተግባር ሁሉ በግሉ ነበር የሚያከናውን። ለምሳሌ በኛ አካባቢ በአርሶ አደሩ ህብረተሰብ ባል ያርሳል ልጆች እና ባለቤት እንደ ሥራው ሁኔታ ለአባት፣

“ጽሑፍ ከሰው ልጅ ጭንቅላት ውጭ ሆኖ የጭንቅላት አጋዥ ሆነ፣ የመረጃ የሕግ የዕውቀት ማጠራቀሚያ ማሰራጫ ሆነ። ጽሑፍም ከትውልድ ትውልድ በሰነድ መልክ ይተላለፋል፣ እንደ አእምሮ የመረጃ እቃቤትነት ግለሰቦች ሲሞቱ አብሮ አይወድምም”

ለባል እገዛ ያደርጋሉ (በጉልጓሎ በአረም በአጨዳእንዲሁም ምርትን እና የከብት መኖን ወደ ሰፈር በማጋዝ)።የምግብ መሰናዶ የእናት እና የሴት ልጆች ተግባር ሲሆን፣ ሴት ልጆች እናትን በቤት ሥራ ሁሉ በመሳተፍ ያግዛሉ።

 ሆኖም ቤተሰቡ ሊያበጃቸው የማይችል ተፈላጊ ቁሳቁስ አሉ፣ ለምሳሌ ልብስ ሽመና፣ ምጣድእንስራ ወዘተ መሥራት፤ እንዲሁም ከብረት የሚሠሩ የእርሻ መሣሪያዎች (ወገል፣ ማረሻ ማጭድ ወዘተ) ማዘጋጀት። የጋማ ከብት የጭነት ዕቃዎች (ኮርቻ፣ ወዘተ) በባለሙያዎች ያበጃሉ። ስለሆነም አገልግሎት መለዋወጥ (መመንዘር) ይቻል ነበር፣ ለምሳሌ ሸማኔ የሸመነበትን አገለግሎት፣ ገበሬው የሸማኔውን ማሳ ሊያርስ ይችላል። በብዛትም ባይሆን አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች ይህን ዓይነት የአገልግሎት ልውውጥ ይደረጋል።

 በብዛት ይካሄድ የነበረው ልውውጥ አንደን አካል/ ቁስ (ምግብ ልብስ የቤት እንስሳ ወዘተ) በሌላ አካል/ ቁስ መቀየር ነበር። ይህም የአከፋፈል ስልት አስቸጋሪ እየሆነ መጣ። ለምሳሌ አምስት ለኑሮ የሚያስፈልጉ ግብይቶችን ለማከናወን በሌሎች አምስት መለወጫዎች (እቃ፣ ከብት፣ ምርት፣ ወዘተ) 25 የመለዋወጫ ሚዘኖች ማጥናት፣ ተመጣጣኝነት መለኪያዎችን፣ የመለዋወጫ  ሚዛኖችን ማስታወስ፣ የግድ ያስፈልግ ነበር።  ለምሳሌ በሬ ለመግዛት ቢፈለግ፣ ማረሻ ያለው  በስንት ማረሻ፣ አንካሲ ያለው በስንት አንካሲ፣  በርበሬ ያለው በስንት ፈረሱላ በርበሬ፣ ጨው  ያለው በስንት አሞሌ ጨው እያሉ ማስላት  ያሻል። የመለዋወጫው እቃ በጨመረ መጠን  ውስብስብነቱ እየጎላ ይሄዳል። እንዲሁም  የመገበያያ እቃዎች ዋጋ በተቀያየረ ቁጥር ፣  በግዥ (በሽያጭ) እቃዎች የሚለዋወጡበት  ስሌት አብሮ ይቀያየራል።

 በተጨማሪየምንገበያይባቸው (እቃዎች/  የምግብ ዓይነት/ከብት) ብዛት ሲጨምር፣ የምናስታውሳቸው የመለዋወጫ የሂሳብ  ስሌቶች ቁጥር አብረው ይንራሉ፤ መገበያያዎቹ  ስድስት ቢሆን፣ ማስታወስ የሚሻን ስሌት 36  ፣ ሰባት ቢሆን 49፣ ስምንት ቢሆን 64፣  ዘጠኝ ቢሆን 91፣ አሥር ቢሆን 100፣ መቶ  ቢሆን 10,000 ይሆናል። በዚሁ መንገድ  ሌሎች ብዙ ሰንጠረዦችን የሚሞሉ የሂሳብ  ስሌቶች ይኖራሉ።

 እንዲሁም የሕዝብ ቁጥር በጨመረ መጠን  የሥራ ክፍፍል ሂደቱም እየበረከተ መጣ።  ለሹማምንት ልብሶች (ካባ፣ በርኑስ ወዘተ.)፣  ለወይዛዝርት ጌጣጌጦች፣ ለእምነት ሥርዓት  አስፈላጊ የሆኑ ቁሳ ቁስ ለእምነት አባቶች  አልባሳትልዩ ልዩ የሽመና የአንጥረኝነት  ሙያተኞች ያስፈልጋሉ።ለቤትም ብዙ ከሸክላ  የሚሠሩ እቃዎች እያስፈለጉ መጡ። በዚህም  ምክንያት ልዩ ልዩ በአንጥረኛነትየሸክላ ሥራ  (ደበንአንሳ) እንዲሁም በሽመና ክህሎቶች  ያዳበሩ ግለሰቦች አስፈለጉ። የሥራ ክፍፍሉም  እየጨመረ ሄደ። በዚህ መንገድ የተፈጠረው  የሰዎች ውስብስብ ግንኙነት በሕግ፣ በደምብ  መተዳደር ነበረበት። ሕግ አዋቂዎችዳኞች  ጸሐፊዎች እቃ (ሸቀጣ ሸቀጥ) አቅራቢዎች  አሻሻጮች ንብረት ጠባቂዎች፣ ወዘተ፣  በአጠቃላይ በተለያዩ ተግባራት የሚሰማሩ  የማህበረሰብ አባላት መታየት ጀመሩ  (ተፈጠሩ)።

  ጽሑፍ- የአስተዳደር  ሥርዓት ውጤት

  ቋንቋ ለሰው ልጅ የማህበራዊ ግንባታ አቅም  ቢያዳብርም በንግግር ብቻ ሊፈቱ የማይችሉ  ሌሎች ችግሮች ተከሰቱ። የሰው ልጅ ማህበራዊ  ሕግጋት ግን በበራሂ የተገረገሩ አይደሉምና  ከወላጅ ወደ ልጅ ብሎም ወደ ልጅ ልጅ  ሊተላለፉ አይችሉም። ሥርዓቱን ከወላጅ ወደ  ልጅ (ከአንድ ትውልድ ወደ ተከታይ ትውልድ)  ማስተላለፊያ ዘዴ ያሻል። ትውልድ ተከታታይ  እና የሚያቋርጥ ሂደት ስለሆነ ደምቦችሕጎች  መቋረጥ የለባቸውም፣ አለበለዚያ ሥርዓት  አልባ ስብስብ ነው የሚፈጠረው።

 ለምሳሌ መንግሥት ሕዝብን በሥርዓት  ያስተዳድራል፤ የሥርዓቱ አካላትም  ቀረጥ (ታክስ) መሰብሰብን ወታደር  መመልመልንፍትሕ ማስፈንን ወዘተ ያሻል።  ይህ ሁሉ የሥርዓት ዝርዝር በየግለሰቡ  አእምሮ ሊታመቅ አይችልም። ስለሆነም  በጋራ የሚጠቀምበት ተመሳሳይ አስተሳሰብ  ለሕዝብ ለማስጨበጥ ለመንግሥትም አዳጋች  ይሆናል (ያዳግታል)። የሰው ልጅ አእምሮ  ሊያስተናግድ የሚችል የተወሰነ መረጃዎችን  ብቻ ነው። መረጃዎችም በብዛት ለግለሰቡ  በተለይ ለአካሉ ሕያውነት መቆጣጠሪያ፣  መጠበቂያ የሚያገለግሉ ናቸው። ለማህበራዊ  ኑሮ የሚያገለግሉ ውስን መረጃዎች  እንኳ በግለሰብ አእምሮ ውስጥ ቢቀረጹ፣  የተጠራቀሙት መረጃዎች ከግለሰቡ ሕልፈተ-  ሕይወት ጋር አብረው ይወድማሉ።

 በሜሶፖታሚያ ይኖሩ የነበሩ ማህበረሰቦች፣  ሳምራውያን ፣ ከክርስቶስ ልደት በፊት  ከ3,500-3,000 ዓመት ገደማ የግብርና  ምርታቸው እየተትረፈረፈ፣ የማህበራዊ  ግንኙነቶቻቸው ውስብስብ እየሆኑ መጡ።  ከዚያም በዛ ያለ መረጃ ማቋት የሚያስችል  ዘዴ ፈጠሩ። ከግለሰቦች አንጎል (ጭንቅላት)  ውጭ የሆነ፣ ለማህበራዊ ተግባራት ማስተናገጃ  የሚሆን ዘዴ ሥርዓት ተፈጠረ፣ ያም በጽሑፍ  መልክ መረጃን ማስፈር፤ መረጃን በሥርዓት  ማስቀመጥ፣ ማጠራቀም ነበር።

 ጽሑፍ ከሰው ልጅ ጭንቅላት ውጭ ሆኖ  የጭንቅላት አጋዥ ሆነ፣ የመረጃ የሕግ  የዕውቀት ማጠራቀሚያ ማሰራጫ ሆነ።  ጽሑፍም ከትውልድ ትውልድ በሰነድ  መልክ ይተላለፋል፣ እንደ አእምሮ  የመረጃ እቃቤትነት ግለሰቦች ሲሞቱ አብሮ  አይወድምም። ለመደበኛው አካል ከአካሉ  ውጭ የሆነ ቋት፣ መደበኛውን አካል አጋዥ  በዘመናችን «ኤክስተርናል ዲስክ» ወይም  ኮምፒውተር የምንለው ዓይነት የመረጃ  ማመቂያ ማስተናገጃ ለሰው ሰራሹ አካል  ተሰናዳለት (ተበጀለት)።

 ሂደቱ እንደሚከተለው ነበር። በሜዲትራኒያን  ምሥራቃዊ አካባቢ በሚገኙ አገሮች፣ በተለይ በሜሶፖታምያ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ3,000-2,500 ዓመት ገደማ ቀስ በቀስ የቃላት ወኪሎች የሆኑ ቅርጾች መሳል ጀመሩ፣ ፊደላት ተቀረፁ። ከክርስቶስ ልደት በፊት በ2,500 ዓመት ገደማ ወዲህ መመሪያዎችን ሕግጋትን ነገሥታቱም ሆኑ የእምነት (ሃይማኖት) መሪዎች (አባቶች) በጽሑፍ ማስፈር ጀመሩ። ጽሑፍ ዋና የሃሳብ ማጠራቀሚያ ብሎም ማሰራጫ ዘዴ ሆነ።

 የመጽሐፍ መሠረቶች ብዙ ናቸው፣ ምንም የጊዜ ቅደም ተከተል ቢኖራቸውም አንድ ቦታ ብቻ አልፈለቀም። አጀማመሩ አንድን አካል በምስል መልክ በመቅረጽ ነበር፣ ቀስ በቀስ ከአንድ ጉዳይ ምስል በተለያዩ ፊደላት ቅንብር መጻፍ ተጀመረ። ለምሳሌ ቀደምት ጽሑፎች በሜሶፖታምያም ሆነ በግብፅ (ምሥር) በቅርጽ መልክ ብቻ ነበር የሚገለጡ።

 ከዚያም በሂደት በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ፊደላት ተቀረጹ፣ ሲቀረጹም ብዙዎች ተነባቢዎች ጥቂቶች አናባቢዎች ሆነው ነበር። አንዳንድ ቋንቋዎች አናባቢዎችን በያንዳንዱ ፊደል ላይ ሲያስገቡ ሌሎች ደግሞ አናባቢዎችን ለይተው እንዳስፈላጊነታቸው በየቃላቱ ውስጥ እየሰገሰጉ ጽሑፍ ማዘጋጀት ጀመሩ።

 በዘመናችን የሚሰራባቸው ፊደላት አመዳደብ ቢያዳግትም በግርድፉ ለሦስት ይከፈላሉ። የአመዳደቡ ሁኔታ ግን ቁልጭ ያለ አይደለም፣ አንዱ ከሌላው ተደራራቢ እንዲሁም ተወራራሽ ሊሆን ይችላል።

አንደኛው እውነተኛ አልፋቤት የሚለው የላቲንን እና የኮርያን ሃንጉል ያካትታል። ሁለተኛው አብጀድ ይባላል፣ ይህም አረብኛ እና እብራይስጥን ያጠቃልላል። ሦስተኛው አቡጊዳ ይባላል፣ ይህ ደግሞ ኢትዮጲክ (ኢትዮጵያን ጽሑፍ) ሂንዱን እና ታይ ይይዛል። በነዚህ ደረጃ ባልረቀቁ ፊደላት የቻይና እና የጃፓን ሕዝቦች ይጠቀማሉ።የተለያዩ ቋንቋዎች መግለጫ የሆኑትም ፊደላት በቁጥር ብዛት ይለያያሉ። አመዳደቡ ከዚህ ውስብስብ በሆነ መልክም ይተገበራል።ያም ሆኖ እኛ በቀላሉ ለመረዳት እንድንችል ብቻ ነው፣ ግልጥ ድምበር ያበጀንላቸው። ከላይ እንደተገለጸው፣ የፊደላቱ ባህሪያት ስለሚወራረሱ አመዳደቡ በጣም ግልጥ አይደለም።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቋንቋ ታግዘን የረቀቀ ዕውቀትን ከቀደምት ትውልድ ወደ ተከታይ ትውልድ ለማስተላለፍ ችለናል። ለዚህ ተግባር እንዲያመች ትምህርት ቤቶች (በተለያዩ ደረጃዎች) የምርምር ማዕከላት፣ ተዋቅረዋል። እውቀቱም በጽሑፍ መልክ ይሰነዳል። ስለሆነም በቋንቋ አጋዥነት ተዝቆ የማያልቅ የዕውቀት ባህርም ተዘጋጅቷል። በተጨማሪ ጽሑፍ የድረሰት የቅኔ ማበርከቻ፣ ከድምጽ ጋር በስልት ተደምሮ የሙዚቃ መቀመሪያ የዜማ ማንቆርቆሪያ ለመሆን በቅቷል። (ይቀጥላል…..) 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top