በላ ልበልሃ

የቅጂን መብትና የጋራ አስተዳደር ብዥታ

የኪነ-ጥበብ፣ የስነ-ፅሁፍ እና ሳይንሳዊ ስራዎች በአንድ አገር ውስጥ ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም። በዚህም ምክንያት አገሮች በተናጥል በቂ የሚሉትን ጥበቃ በሚያወጧቸው የውስጥ ሕጎች እንዲሁም በጋራ የሁለትዮሽ እና አለም አቀፍ ስምምነቶችን በመፈጸም ጥበቃ ያደርጋሉ። በአገራችንም ከዚህ አስተሳሰብ ጋር በሚጣጣም መልኩ የሥራ አመንጪዎችን ሕገ- መንግስታዊ መብቶች ለማስፈጸም የሚያስችሉ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ወጥተው በአገራችን በስራ ላይ ይገኛሉ።

 እነዚህ ሕጎች ከሞላ ጎደል የተሟሉ፣ ግልጽ እና ከአለም አቀፍ የቴክኖሎጂ እድገትና ሉላዊነት ጋር የተመሳከሩ ናቸው። በአገራችን የአእምሯዊ ንብረት ሕጎች ድንጋጌዎች ላይ አስተያየት የሚሰጡ ምሁራን ሕጎቹን ጠንካራና ለታዳጊ አገር ከበቂ በላይ በማለት ይገልጾቸዋል። በአብዛኛው ችግሮች የሚታዩት ጥበቃ በሚሰጡት ሕጎች ድንጋጌዎች ላይ ሳይሆን በመብት ማስፈጸምና በተለያዩ ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ እጥረት ላይ ነው። ይህ ችግር በመብት ባለቤቶች፣ በመንግስት አስፈጻሚ አካላት፣ በተጠቃሚዎች እንዲሁም በአጠቃላይ በሕዝቡ ዘንድ የሚታይ ነው። ከግንዛቤ እጥረት ጋር በተያያዘ በመጀመሪያ የሚነሳው ጉዳዩ አጠቃላይ የአእምሯዊ ንብረት ምንነት እና ባህሪ ላይ የሚታይ ነው።

 ግዙፍነት ወይም ተጨባጭ ጠባይ የሌላቸው በመሆኑ ኢኮኖሚያዊ ዋጋቸው በእጅጉ አንሶ የሚታያቸው ሰዎች ጥቂት አይደሉም። ለዚህም ነው በከፍተኛ ደረጃ የመብት ጥሰቶች የሚከሰቱት። ነገር ግን እነዚህ ንብረቶች በተለይ በዚህ በእውቀት ላይ በተመሠረተና ሉላዊ አለም ላይ ያላቸው ዋጋ ከፍተኛ ነው። ሁለተኛው ጉዳይ ሥራዎቹ በቀላሉ ሊተላለፉ ወይም ሊዘዋወሩ የሚችሉ በመሆኑ በንብረቶቹ የግልነት ባህሪ ላይ የሚታዩ ክፍተቶች ናቸው። ይህ በተለይ በቅጂና ተዛማጅ መብቶች ሕጎች ጥበቃ በሚደረግላቸው የኪነጥበብና ስነጽሁፍ ስራዎች ላይ ጎልቶ የሚታይ ጉዳይ ነው።

ይሁንና በበርካታ (በተለይ) በአደጉት አገራት በእነዚህ የእእምሮ ውጤቶች የንብረት ባህሪ ላይ ጥያቄ የማይነሳ በመሆኑ ጠንካራ ጥበቃ ይደረግላቸዋል። እንዲያውም ከኢንተርኔት መምጣትን ተከትሎ የሕዝብ ጥቅም በአግባቡ እየተጠበቀ አይደለም፤ ለመሰል የአእምሯዊ ንብረቶ የሚሰጠው ጥበቃ ከፍተኛ በመሆኑ መረጃን እና እውቀትን እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ የግብርና፣ የጤና እና የትምህርት ማቴሪያሎች በአግባቡ ለሕዝብ እየደረሱ አይደለም በማለት የሚከራከሩ ወገኖች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ይህ በአንዳንድ የአደጉ አገሮች ባለሙያዎች እና በታዳጊ አገር ተመራማሪዎች ዘንድ እየተራመደ ያለ ሃሳብ ነው።

የጋራ ማኅበራት አስፈላጊነት

 በአገራችን በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 55(1) መሠረት የወጣው የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 410/1996 (ከዚህ በኃላ አዋጅ ቁጥር 410/1996 እየተባለ የሚጠቀሰው) ላይ የሚታዩ እንዳንድ ክፍተቶች ያሉ ቢሆንም ከላይ እንደተጠቀሰው ሕጉ ጠንካራና እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት በቂ ነው።

 በአዋጁ ቁጥር 410/1996 የተሰጡ መብቶችን ባለመብቶቹ ስራዎቻቸውን ሕጋዊ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተጠቃሚዎች ወይም ሕዝቡን በማስገደድ ረገድ የሚያግዶቸው ብዙ ችግሮች አሉ። ከእነዚህም ውስጥ የባለመብቶቹ የኢኮኖሚያዊ አቅም ማነስ እና የአስፈጻሚ አካላት ግንዛቤ እጥረት እንደምክንያትነት ሊነሱ የሚችሉ ጉዳዮች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ለረጅም አመታት ሲነሳ የነበረው ጉዳይ የሮያሊቲ አሰባሰብ ስርዓቱ በሕግ ያልተደነገገ መሆኑ ሲሆን ይህም በቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ (ማሻሻያ) አዋጅ ቁጥር 872/2007 ተፈትቷል። ይህም በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው በሚገኙ ባለሙያዎች ዘንድ ደስታን የፈጠረና ለአገራችን የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ሥርዓት ከፍተኛ አስተዋጽዖ የሚያደርግ ነው።

 የጋራ አስተዳደር ማህበራት በተለያዩ ምክንያቶች አስፈላጊ ናቸው። የዚህን ስርዓት አስፈላጊነት ከሁለት አቅጣጫ ማየት ይቻላል። በመጀመሪያ የመብት ባለቤቶች ስራዎቻቸው በአንድ አገር ውስጥ ወይም በአለም ደረጃ በተለያየ መልኩ ጥቅም ላይ ሲውሉ መቆጣጠር የማይችሉ በመሆኑ እንዲሁም እንቆጣጠር ቢሉ ስራዎቹ ጥቅም ላይ እንዴት ዋሉ የሚለውን በመለየት፣ ተጠቃሚዎቹን በማሳደድና ከሁሉም ተጠቃሚዎች ጋር በመደራደር ፍቃድ ለመስጠት የማይችሉና እናርግ ቢሉ እንኳን ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጣቸው በመሆኑ በጋራ ማስተዳደሩ የተሻለ ይሆናል። በሁለተኛ ደርጃ እነዚህ ማህበራት ተጠቃሚዎች ስራዎችን በአንድ ቦታ፣ በግልፅ በተቀመጡ ዝርዝር ሁኔታዎች እና የክፍያ መጠን እንዲያገኙ ስለሚያግዝ የመብት ጥሰት እንዲቀንስ በማድረግ ስራዎች በሕጋዊ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ያደርጋል።

የሙዚቃ ባለሙያዎች መብት

ከቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጋር በተገናኘ በአገራችን በከፍተኛ ደረጃ የሚታየው የግንዛቤ እጥረት በሚያሳዝን ሁኔታ በኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤትም ላይ የሚታይ ክስተት ነው። ጽ/ቤቱ ከዚህ ቀደም በማቋቋሚያ አዋጁ የተጣሉበትን ኃላፊነት በበቂ ሁኔታ ባለመወጣቱ ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ክፍተቶች እንዲባባሱ ያደረገ ሲሆን ይህ ችግር በሮያሊት አሰባሰብ ሂደቱ ላይም እንዲደገም እድል እየከፈተ ይገኛል።

ጽ/ቤቱ በዚህ ረገድ የባለመብቶች እና/ወይም ባለሙያዎችን ጥቅም ለማስጠበቅ ያልቻለበት ሁኔታ ግልጽ አይደለም። በቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 410/1996 እና በማሻሻያ አዋጁ ቁጥር 872/2007 ላይ ለባለመብቶች ከተሰጡት መብቶች የሚገኘውን የሮያሊቲ ክፍያ በሙዚቃው የተለያዩ ዘርፎች ውስጥ ተሰማርተው ለሚገኙ ባለሙያዎች በአግባቡ ለማዳረስና ከዚህ በፊትም በሙዚቃ ኢንዱስትሪው የሚታዩ ኃላቀር አሠራሮች በሮያሊቲ አሰባሰብ ሥርዓቱ ላይ እንዳይደገሙ ረጅም ትግል ባለሙያዎች ሲያደርጉ ቆይተዋል፣ አሁንም እያደረጉ ይገኛሉ። ከእነዚህም ውስጥ ባለሙያዎች በ2009 ዓ.ም በተለያዩ ጊዜያት በተለይ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መ/ቤት ባደረጉት ክርክር መነሻነት ሚኒስትሩ እንዲሁም በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቋሚ ኮሚቴ ኃላፊ በተገኙበት መጋቢት 28 ቀን 2009 ዓ.ም በተደረገው ስብሰባ ላይ ሙዚቀኞች የራሳቸውን ንብረት እራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር።

አንድ ሚኒስቴርም ሆነ የሚያስተዳድረው መ/ቤት ከሕገ መንግስቱ ጀምሮ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቁ አዋጆችን መሻር፣ መጣስ ወይም በዚህ ምክንያት መብቶቹን መገደብ የማይችል በመሆኑ ይህ ከሕግ ፊት ሲታይ ምንም አይነት ፍይዳ የማይኖረው ቢሆንም በባለሙያው ሞራል እና በማሕበረሰቡ ግንዛቤ ላይ ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል። ከዚህ በላይ ስለ መንግስት እና የመንግስት መ//ቤቶች ግንዛቤ እጥረት የተጠቀሰው አንዱ መገለጫ ይሄ ነው።

በቅጂ መብት ወይም በተዛማጅ መብቶች ሕጎች ጥበቃ የሚደረግላቸው ስራዎች የግል ንብረት እንደመሆናቸው የማስተዳደር ሃላፊነትም ሆነ መብት የባለመብቱ ሆኖ እያለ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴሩም ሆነ የአእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት በዚህ ደረጃ ጣልቃ መግባታቸው አላስፈላጊ ስህተት ነው። ከዚህ በኃላም ሚያዝያ 28 ቀን 2009 ዓም አእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት ከተለያዩ የሙዚቃ ባለሙያዎች ጋር በተደረገ ውይይት ይህ ስምምነት ታሳቢ ተደርጎ ባለበትና በሙዚቃ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ የሙዚቀኞች ማኅበር አስተባባሪነት ይህንን እውን ለማድረግ በርካታ ስራዎችን እየሰሩ ባለበት ሁኔታ ጽ/ቤቱ የግል ንብረትን የማስተዳደር ነጻነት በሚገድብ መልኩ አይወክለንም በማለት በተለያዩ መደረኮች ለገለጹት አካል ሰኔ 11 ቀን 2009 ዓ.ም እውቅና ሰጥቷል።

ይህ እውቅና የተሰጠው እና የኢትዮጲያ የቅጂና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማኅበር የሚል ስያሜ ያለው አካል በጥበብ ዘርፍ የተለያዩ ሙያዎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ባለሙያዎችን ያቀፈና ከሙዚቃ የተለያዩ ዘርፎች የሚገኙ መብቶችንም ለማስተዳደር የተቋቋመ ሲሆን የሁሉም ማለት ይቻላል ሙዚቀኛ ይሁንታ የሌለው ማኅበር ነው። የዚህን “የጋራ አስተዳደር” ማኅበር እውቅና ማግኘት ቀጥሎ በወቅቱ የአእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት ዋና ደይሬክተር የነበሩት ግለሰብ ሙዚቃ ለብቻው ማስተዳደር አይችልም በማለት በሬዲዮ ላይ በመውጣት እስከመናገር ደርሰው ነበር። ለዚህም መሰረት ያደረጉት በዋናነት “ዘርፍ” የሚለውን ቃል ትርጓሜ ይመስላል።

በወቅቱ የሙዚቃ ባለሙያዎች በተለያዩ ሚዲያዎች እና መድረኮች መብታችንን እና ንብረታችንን እራሳችን እናስተዳደር በሚል ሃሳባቸውን ሲገልጹ የነበረ ቢሆንም ከአንድ የሕዝብ ሃላፊነት እንዲሁም ተጠያቂነት አለበት ተብሎ ከሚጠበቅ የመንግስት ተቋም በማይጠበቅ መልኩ በሬዲዮ በመቅረብ ሃሳባቸውን ገልጸዋል። ይህ ከአንድ የአእምሯዊ ንብረት ባለሙያ የማይጠበቅ ተግባር ነው። በማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 872/2007 ላይ የተቀመጠውና የጋራ አስተዳደር ለማቋቋም አስፈላጊ ናቸው ተብለው ከተቀመጠቱ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል ቢያንስ ሦስት የዘርፍ ማኅበራት መኖር የሚለውን ለማሟላት ሙዚቀኞች ተፈጻሚነት ያላቸውን የሕግ ድንጋጌዎች በማሟላት የኢትዮጵያ የሙዚቃ ስራ አመንጪዎች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ከዋኞች ማኅበር እና የኢትዮጵያ የድምጽ ሪከርዲንግ ፕሮዲዩሰሮች ማኅበር የተባሉ ማኅበራትን አቋቁመዋል። በወቅቱ የነበሩት የጽ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ሃሳብም ከላይ እንደተጠቀሰው ኪነጥበብ የተወሰኑ ዘርፎች አሉት የሚለውን ሃሳባቸውን መሰረት በማድረግ ነው። ይህ ሕግ የመተርጎም ስልጣን የሌለው አካል ወይም ግለሰብ የሰጠው እንደመሆኑ ተቀባይነት የሌለው እና ሌሎች በስራ ላይ የሚገኙ ሕጎች ወቅት የሚሄዱበትን አካሄድ ነው።

 የጋራ አስተዳደር ገጽታ

 በቅርቡ የፌደራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ግንቦት 2010 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፓርት ላይ ሙዚቀኞች ከ2008ዓ.ም ጀምሮ ሲያነሱ የነበሩ ችግሮችን የአእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት ላይ ባደረገው ምርመራ እንደችግር አንስቷል። የኢትዮጵያ የቅጂና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳድር በሚል ስያሜ በአሁኑ ወቅት የሙዚቃ ስራን ጨምሮ ሌሎችን በቅጂና ተዛማጅ መብቶች አዋጅ ጥበቃ የሚደረግላቸውን ስራዎች ለማስተዳደር በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኘው ማኅበር እውቅናውን ያገኘበትን መንገድ ጨምሮ ሌሎች የታዩ ችግሮችን ይፋ አድርጓል። ይህ ሙዚቀኞች ለሁለት አመታት ሲገልጹኣቸው የነበሩ ነገር ግን በሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ችላ የተባሉ ችግሮች ናቸው።

 ይህ አስተያየት የተዘጋጀው ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች መንስኤያቸው ናቸው ተብለው የሚገመቱትን ነጥቦች ከግምት ውስጥ በማስገባ ሙዚቀኞች ከሕግ አንጻር ያላቸውን መብት ለማብራራት ሲሆን የሚከተሉት ነጥቦች በአገራችን የሚቋቋመው የጋራ አስተዳደር ማኅበር ምን ምን ነገሮችን ከግምት ውስጥ ሊያስገባ ይችላል የሚለውን እንደሚከተለው ለማስቀመጥ እሞክራለሁ።

 የአእምሯዊ ንብረት የግል ንብረት መሆናቸው

 የአእምሯዊ ንብረት የግል ንብረት ነው። የግል ንብረት ደግሞ በሕገመንግስቱ ጥበቃ የሚደረግለትና ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያለው መሆኑ በሁሉም ዘንድ የሚታመንበት ጉዳይ ነው። በኢትዮጵያም የግል ንብረት በኢፌዴሪ ሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 40 ላይ የተቀመጠና ለሁሉም ዜጋ የተሰጠ መብት ነው።

የግል ንብረት የማፍራት፣ የመያዝ፣ የመጠቀም እንዲሁም የሌሎችን ዜጎች መብቶች እስካልተቃረነ ድረስ ንብረትን የመሸጥ፣ የማውረስ ወይም በሌላ መንገድ የማስተላለፍ መብቶችን በሕግ አግባብ የማስተዳደርና የመቆጣጠር መብት የባለንብረቱ ሕገመንግስታዊ መብት ነው። ከላይ እንደተገለጸው በአገራችን የቅጂና ተዛማጅ መብቶች እንዲሁም ሌሎች የእእምሯዊ ንብረቶች አጠቃቀም ላይ የሚታዩ ክፍተቶች እና የመብት ጥሰቶች የሚመነጩት ከእነዚህ ንብረቶች ባህርይ ነው።

የቅጂና ተዛማጅ መብቶች የሚያስገኙ የኪነ-ጥበብ፣ የስነጽሁፍ እና ተመሳሳይ የፈጠራ ስራዎች እንዲሁም በሌሎች የእእምሯዊ ንብረት ሕጎች ጥበቃ የሚደረግላቸው የአእምሮ ውጤቶች ግዙፍነት እንዳላቸው ንብረቶች በተቃራኒው ሊዳሰሱ የማይችሉ ግዙፍነት የሌላቸው በመሆኑ ያላቸው ኢኮኖሚያዊ ዋጋ ለብዙዎች ግልጽ አይደለም። ይሁንና የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ልክ እንደማናቸውም ግዙፍነት እንዳላቸውና ሊዳሰሱ እንደሚችሉ ንብረቶች የግል ንብረት የሆኑና ያለባለንብረቱ ፈቃድ ወይም ይሁናታ ጥቅም ላይ ሲውሉ ለሌሎች ግዙፍነት ላላቸው ንብረቶች በሕግ የተሰጡ ጥበቃዎች ያሏቸው መሆኑ ግንዛቤ ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ ነው።

ለምሳሌ በአንድ የሙዚቃ አልበም ላይ የሚሳተፉት ሰዎች መብቶቻቸውን አዋጅ ቁጥር 410/1996 በሚደነግገው መሠረት በጥቅም ላይ እንዲውሉ የመፈቀድ ወይም የመከልከል ማለትም በአጠቃላይ ከንብረቶቹ በሚመነጩ መብቶች ላይ የማዘዝ መብት በመጀመሪያ በስራ አመንጪዎቹ፣ ከዋኞች እና የድምጽ ሪከርዲንግ ፕሮዱዩሰሮች ላይ ይገኛል። በአንድ ሙዚቃ ላይ ደግሞ በርካታ ባለመብቶች ይገኛሉ። እነዚህም ዜማ ደራሲ፣ ግጥም ደራሲ፣ አቀናባሪ፣ ድምጻዊ፣ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዎቾች እና የድምጽ ሪከርዲንግ ፕሮዲዩሰሮች ናቸው። እነዚህ ሁሉ የተለያዩ መብቶች በአዋጅ ቁጥር 410/1996 ላይ በግልጽ ተሰጥቷቸዋል። መብታቸውን በአዋጅ ቁጥር 410/1996 አንቀጽ 7፣ 8፣ 26 እና 27 ላይ ተደንግገው ይገኛሉ።

 በመሆኑም መብቶች ሕጋዊ በሆነ መንገድ ባልተላለፉበት ሁኔታ ማንኛውም ሰው ያለባለመብቱ/ስራ አመንጪው በንብረቶቹን ሕጋዊ በሆነ መልኩ ሊጠቀም አይችልም። ለዚህም መሠረት የሚሆነው የሕገ- መንግስቱ አንቀጽ 40 እንዲሁም አዋጅ 410/1996 አንቀጽ አንቀጽ 7፣ 8፣ 26 እና 27 ናቸው።

በብቸኝነት የመፈጸም እና/ወይም ሌላ ሰው እንዲፈጽም የመፍቀድ መብት ያላቸው ስለመሆኑ

 ከዚህ በላይ ለስራ አመንጪዎች፣ ከዋኞች እና የድምጽ ሪከርዲንግ ፕሮዲዮሰሮች በአዋጅ ቁጥር 410/1996 የተሰጡት ተነጣጥለው ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ መብቶች የመጀመሪያ ባለቤቶች የሥራ አመንጪዎቹ፣ ከዋኞቹ እና/ወይም የድምጽ ሪከርዲንግ ፕሮዲዩሰሮቹ ናቸው። ለምሳሌ በአዋጁ ቁጥር 410/1996 አንቀጽ 7 ላይ የተዘረዘሩት ኢኮኖሚያዊ መብቶች ለስራ አመንጪው በመጀመሪያ ደረጃ የተሰጡ ሲሆን እነዚህም የማባዛት፣ የመተርጎም፣ የማመሳሰል፣ የማቀናበር ወይም ወደ ሌላ አይነት የመቀየር፣ በሽያጭ ወይም በኪራይ ኦሪጅናል ሥራን ወይም ቅጂውን የማከፋፈል፣ ኦሪጅናል ሥራውን ወይም ቅጂውን ከውጭ ሀገር የማስገባት፣ ኦሪጂናል ሥራን ወይም ቅጂውን ለህዝብ የማሳየት፣ በይፋ የመከወን፣ ብሮድካስት የማድረግ፣ እና ሥራን በሌላ መንገድ የማሰራጨት መብቶች ናቸው።

 በአዋጁ ድንጋጌ መሠረት ማንኛውም የሥራ አመንጪ መብቶቹን በሌላ አኳኃን በሕግ የተቀመጡትን ቅድመ-ሁኔታዎች ባሟላ መልኩ ለሌላ ሰው የማስተላለፍ መብት ያለው ሲሆን መብቱን በሕግ አግባብ ያላስተላለፈ ሲሆን ተጠቃሚዎች ለሚፈጽሙት የመብት ጥሰቶች ለመከላከል በሕግ የተቀመጡ መፍትሄዎች አሉት።

በመሆኑም እነዚህን ሥራዎች ጥቅም ላይ ከማዋሉ በፊት አንድ ሰው ፈቃድ ሊያገኝ ይገባዋል። ፈቃድ ሳያገኝ መጠቀም በማንኛው ደረጃ መብት ጥሰት እንደመፈጸም የሚቆጠር ነው። ነገር ግን በእነዚህ የግል ንብረቶች ላይ ለብቻ የማዘዝ መብት ያለገደብ የተሰጡ አይደሉም። እነዚህም አዋጅ ቁጥር 410/1996 ከአንቀጽ 9 እስከ አንቀጽ 19 የተዘረዘሩት እንዲሁም የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት አግባብ ሆኖ ሲያገኘው የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ አላማ ሥራዎቹ ያለመብት ባለቤቶቹ ፈቃድ ለተወሰኑ አላማዎች ጥቅም ላይ ሊውሉ እንዲችሉ የግዳጅ ፈቃድ ሊሰጥ ይችላል። እነዚህ ገድቦች ግን ከሕዝብ ጥቅም አንጻር ማለትም ለትምህር፣ ለጤና እና መሰል ማህበራዊ አላማዎችን ለማሳካት ብቻ የተቀመጡ ገደቦች ናቸው። ከዚህ ውጪ ያሉ ያለፈቃድ ስራዎችን በጥቅም ላይ የማዋል ተግባራት የመብት ጥሰት የሚያስከትሉ በመሆኑ ለማንኛውም የግል ንብረት የተሰጡ የሕግ ከለላዎች በሚመለከታቸው ሕጎች (የፍ/ ብሄር ሕግ፣ የወንጀል ሕግ፣ በቅጂና ተዛማጅ ሕጎች እና ሌሎች ተፈጻሚነት ያላቸው ሕጎች) አማካኝነት ጥበቃ ይደረግላቸው።

 1) ስለፈቃድ አሰጣጥና መብት ማስተላለፍ ሂደቶች

 1.1. የመብት ማስተላለፍ ወይም ፈቃድ መስጠት ተግባር በጽሁፍ መደረግ ያለበር ስለመሆኑ፡ የአዋጅ ቁጥር 410/1996 አንቀጽ 23(2) የመብት ማስተላለፍ ወይም የፈቃድ መስጠት ተግባራት በጽሁፍ መደረግ እንዳለባቸው ይደነግጋል። በፍ/ብሔር ሕግ ቁጥር 1719 ላይ ውሎች በሕግ በሌላ አኳኃን ካልተቀመጠ በስተቀር ተዋዋይ ወገኖች በሚፈልጉት መልኩ ሊደረጉ ይችላሉ በማለት የተዋዋይ ወገኖችን የመዋዋል ነጻነት ያስቀምጣል። ይሁንና የአንቀጽ 1719(2) በሕጉ በግልጽ የሚያስገድድ አጻጻፍ (ፎርም) ካለ ውሉ በዚህ አጻጻፍ (ፎርም) መሠረት መደረግ እንዳለበት ያስቀምጣል። የዚህ አንቀጽ አለመሟላት ውሉን በረቂቅ ደረጃ ያለ ሆኖ እንዲቆጠር ያደርገዋል (የፍ/ብ/ሕግ ቁጥር 1720(1)ን ይመልከቷል)። ይህን ድንጋጌ ከአዋጅ ቁጥር 410/1996 (እንደተሻሸለው) አንቀጽ 23(2) ጋር ሲታይ በጽሁፍ ያልተደረገ የመብት ማስተላለፍ ወይም የፈቃድ መስጫ ውል ረቂቅ እንጂ በሕግ አግባብ ተፈጻሚነት ያለው አለመሆኑን ያሳያል። በመሆኑም ይህ ቅደመ-ሁኔታ መሟላቱ አስፈላጊ ነው።

 1.2. የሚተላለፉትን መብቶች ወይም ፈቃድ የተሰጠባቸውን መብቶች በግልጽ ማስቀመጥ አስፈላጊ ስለመሆኑ፡

በአዋጅ ቁጥር 410/1996 አንቀጽ 23(3) መሠረት የሚተላለፉ ወይም በፈቃድ የሚሰጡ መብቶች ዝርዝር በግልጽ መቀመጥ አለበት። ይህም ማለት ሁሉንም በአንቀጽ 7 ላይ የተዘረዘሩትን ወይም ከእነሱ ውስጥ የተመረጡትን የሚመለከት መሆኑን ማስቀመጥ አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ አንድ የቅጂ መብት ባለመብት በአንቀጽ 7 ላይ የተቀመጡትን መብቶች በሙሉ ማለትም የማባዛት፣ የመተርጎም፣ የማመሳሰል፣ የማቀናበር ወይም ወደ ሌላ አይነት የመቀየር፣ በሽያጭ ወይም በኪራይ ኦሪጅናል ሥራን ወይም ቅጂውን የማከፋፈል፣ ኦሪጅናል ሥራውን ወይም ቅጂውን ከውጭ ሀገር የማስገባት፣ ኦሪጂናል ሥራን ወይም ቅጂውን ለህዝብ የማሳየት፣ በይፋ የመከወን፣ ብሮድካስት የማድረግ፣ ሥራን በሌላ መንገድ የማሰራጨት መብቶች ለሌላ ሰው ባለቤትነቱን ሊያስተላልፍ ወይም ይህ ሰው እንዲጠቀምበት ፈቃድ ሊሰጥ ይችላል።

ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ የመብት ባለቤቱ የማባዛት መብቱን ወይም ለሕዝብ በሌላ መልኩ የማሰራጨት መብቶቹን አስተላልፎ ወይም በፈቃድ ሰጥቶ ሌሎቹን ቀሪዎቹን መብቶች ባለቤትነት ለራሱ ሊያስቀር ይችላል። ይህንን ከአንቀጽ 23 ንዑስ አንቀጽ 3 መንፈስ መረዳት ይቻላል። ከዚህ ውጪ ያለ የመብት ማስተላለፍ ሂደት ወይም ፈቃድ አሰጣጥ ተቀባይነት ሊኖረው የሚችልባቸው ሁኔታዎች ጠባብ ናቸው።

 1.3. የመብት ማስተላለፍ ወይም ፈቃድ የጊዜ ወሰን፡

በአዋጁ አንቀጽ 24(3) ላይ እንደተደነገገው ተዋዋይ ወገኖች (መብት አስተላላፊው እና መብት ተቀባዩ) መብቶቹ ለምን ያህል ጊዜ ይተላለፋሉ የሚለውን ሊወስኑ ይችላሉ። ይህም ማለት ተዋዋይ ወገኖች አንድን የኢኮኖሚያዊ መብት ወይም ሁሉንም የኢኮኖሚያዊ መብቶችን በተመለከተ ጥበቃ ለሚደረግላቸው ጊዜ ወይም ከዚያ ላነሰ ለማኛውም ጊዜ ሊዋዋሉ ይችላሉ። መብቱ የተላለፈው በሕግ ጥበቃ ለሚደረግለት ለሙሉ የጥበቃ ጊዜ ከሆነ በዚህ ላይ ከጊዜ ጋር የሚነሳ ጉዳይ አይኖርም። በተመሳሳይም በውሉ ላይ በግልጽ የተቀመጠ የጊዜ ገደብ ካለ ይህ ተፈጻሚ ይሆናል። ማለትም የጊዜ ገደቡ ከተጠናቀቀ በኃላ የመብት ባለቤትነቱ ተመልሶ ወደ ሥራ አመንጪው ወይም አስተላላፊው የመብት ባለቤት ይመለሳል።

ይሁና በአገራችን በተለይ በሙዚቃው ኢንዱስትሪ የሚታየው ጉዳይ ከዚህ የሕጉ ድንጋጌ ውጪ በሆነ መልኩ መብት ማስተላለፍ እና የፈቃድ አሰጣጥ ተግባራት መከናወናቸው ነው። ይህም በሁለት መልኩ ሊይታይ ይችላል። የመጀመሪያው ቀደም ባሉት ጊዜያት የጊዜ ገደብ እና/ወይም የቅጂ መጠን ተቀመጦባቸው የሚደረግ ውሎች ሲሆኒ በኢንደስትሪው የሚታያው ግን አሳታሚዎች የውሉ ጊዜ ወይም የቅጂ መጠኑ ካለቀ በኃላ ሙዚቃውን ማባዛት ወይም መሸጥ መቀጠላቸው ነው። ይህ ከሕጉ መንፈስ ጋር የሚቃረን በመሆኑ የመብት ጥሰት ተግባር ነው። ሁለተኛው አብዛኞቹ ውሎች የጊዜ ገደብ የማያስቀምጡ መሆኑ ነው። ይህ ሲሆን የአዋጁ አንቀጽ 24(3) ተፈጻሚ ይሆናል።

 ውሉ የመብት ማስተላለፍ ሆኖ የጊዜ ገደብ ያልተቀመጠበት ከሆነ የአዋጁ አንቀጽ 24(3) የውሉን የጊዜ ገደብ አስር አመት ያደርገዋል። ውሉ ፈቃድ መስጫ በሚሆንበት ጊዜና ውሉ ላይ የጊዜ ገደብ ያልተቀመጠ ሲሆን የአዋጁ አንቀጽ 24(3) የውሉ ጊዜ በአምስት አመት ይገድበዋል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ በሕጉ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ እንደተጠናቀቀ ባለቤትነቱ ወይም የመጠቀም መብቱ ተቋርጦ ውሳኔ የመስጠት መብት በድጋሚ ወደ ዋና ሥራ አመንጪው ወይም ወደ ባለቤቱ ይመለሳል።

1.4. የመብት ማስተላለፍ ወይም የፈቃድ ወሰን፡

 በአዋጅ ቁጥር 410/1996 መሠረት ተዋዋይ ወገኖች የመብት ማስተላለፉን ወይም የፈቃድ ወሰንን በተመለከተ የመስማማት ነጻነት አላቸው። ማለትም ተዋዋይ ወገኖች በአዋጁ የሚሰጡትን ሙሉ ኢኮኖሚያዊ መብቶች ወይም ከተሰጡት መብቶች መካከል ጥቂቶቹን በተመለከተ ሊስማሙ ይችላሉ። ይሁናን በአዋጁ መሠረት ስምምነቱ የካተታቸውን መብቶች በመገልገል ወይም በመጠቀም ላይ የተገደበ መሆኑ ነው። ለምሳሌ ውሉ የሚመለከተው አንድን የሙዚቃ አልበም ማከፋፈል ላይ ከሆን ከዛ ውጪ ያሉትን መብቶች አይመለከትም። ይሁንና የአንቀጽ 24(4) የተላለፉት መብቶች አጠቃቀምን በተመለከተ ክፍተቶች ሲኖሩ እንዴት ይሞላሉ የሚለውን በተመለከተ የሚያስቀምጠው መፍትሄ አለ። ይህም “መብቱ ሥራ ላይ የሚውልበት መንገድ ወይም ዘዴ በግልጽ ሳይመለከት ከቀረ መብቱ የተላለፈለት ወይም ፈቃድ ተቀባዩ ተዋዋይ ወገኖች በጋራ ያላቸውን ዓላማ ለማሳካት አስፈላጊ የሆኑ ዘዴዎችና መንገዶች በመጠቀም መብቱን በሥራ ላይ ሊያውሉ ይችላሉ” የሚል ነው።

 ለምሳሌ ከላይ የተመለከተውን አንድን የሙዚቃ ስራ የማከፋፈል መብት የተላለፈለት ሰው በመብት ማስተላለፊያ ውሉ ላይ በግልጽ በምን መንገዶች ወይም ዘዴዎች አልበሙን ማከፋፍል አለበት የሚለው ካልተቀመጠ መብት የተላለፈለት ሰው ስራዎቹን በሲዲ ወይም በፍላሽ ዲስክ አልያም በኢንተርኔት ሊያከፋፍል ይችላል። በኢንተርኔት የሚደረጉ ስራን ማከፋፈል ተግባራት ግን ሌሎች መብቶችን (በይፋ የመከወን እና/ወይም ለሕዝብ በሌላ መልኩ ማሰራጨትን) ሊነኩ የሚችሉ በመሆኑ በዚህ ረገድ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ከዚህ በላይ በተቀመጠው ትንታኔ ላይ መረዳት የሚቻለው መብት ማስተላለፍ ወይም ፈቃድ መስጠት አካሄዶች እራሳቸውን የቻሉና በፍ/ብሔር ሕጉ እንዲሁም በቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ በተቀመጠው መልኩ መሆን እንዳለባቸው ነው።

ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት ቅድመ-ሁኔታዎችና የሕጎች ድንጋጌዎች የሙዚቃ ሥራ ጥቅም ላይ ሲውል በስራው ላይ ያሉ በርካታ ባለመብቶችን ፍላጎት እና/ወይም ጥቅም በማይጎዳ መልኩ መከናወን ያለባቸው መሆኑን ያስረዳሉ። ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ ድንጋጌዎች የአንድን በሙዚቃ ስራ ላይ መብት ያለውን ሰው ፈቃድ ሳይገኝ የሚደረጉ ተግባራት ሕገወጥ መሆናቸውን የሚያሳዩ ነው።

ማንኛውም ሕገ-ወጥ ተግባር በአዋጅ ቁጥር 410/1996 ከቀመጡት ገደቦች (ማለትም ከአንቀጽ 9-19) ውጪ የተፈጸመ ተግባር ሲሆን የመብት ጥሰት የሚያስከትል ይሆናል። የመብት ጥሰትን ለመከላከል እንዲሁም በባለመብቱ ላይ የደረሱትን ጉዳቶች ለማካካስ አዋጅ 410/1996 በርካታ የአስተዳደራዊና የዳኝነት መፍትሄዎችን ያስቀምጣል። ይህ በማንኛውም መብት በሚጥስ ተግባር ላይ የተሰማራ ሰው ላይ ተፈጻሚ የሚሆን ነው።

 ከዚህ አንጻር በሙዚቃው የተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው የሚገኙ ባለሙያዎችን ፈቃድ ሳያገኝ መብቶቹን አስተዳድራለሁ በሚል ተቋም ላይም ተፈጻሚ የሚሆኑ yhon በማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 872/2007 መሠረት ሊቋቋም የታሰበው የጋራ አስተዳደር ማኅበር መሠረት የባለሙያዎች ፈቃድ ነው። የጋራ አስተዳደር ማኅበር ከተጠቃሚዎች ጋር ሊደራደር እና/ወይም የሮያሊት ክፍያ ሊጠይቅ የሚችለው ከባለመብቶች በአዋጅ ቁጥር 410/1996 (እንደተሻሻለው) በተቀመጠው መሰረት መብት ሲተላለፍለት ብቻ ነው።

 የጋራ አስተዳደር መመስረቱ ብቻ ስራዎቹንና ተያይዘው የሚመነጩትን መብቶች የማስተዳደር ስልጣን ወዲያውኑ የሚገኝ የሚመስላቸው ወገኖች ጥቂት አይደሉም። ይሁንና መብቶቹን ማስተዳደር ስልጣን የሚገኘው በሕግ አግባብ የመብት ማስተላለፍ ተግባር በባለመብቶች እና በማኅበሩ መካከል ከተፈጸመ በኃላ ብቻ ነው። ያለመብት ማስተላለፊያ ውል ስራዎችን ማስተዳደር የሚቻለው በማሻሻያ አዋጁ መሠረት በፍ/ቤት ባለቤት የላቸውም ተብለው ለተወሰኑ ስራዎች ብቻ ነው። በመሆኑም ከላይ የተነሱትን ነጥቦች ከግምት ውስጥ በማስገባት የተቀላጠፈና የህግ ድንጋጌዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ የጋራ አስተዳደር ስርዓት መገንባት ይቻላል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top