በላ ልበልሃ

የምርቃት ባህልና ከፍተኛ ትምህርት

እንደ ሚያዝያ ወር የሰርግ ሰሞን፣ ተማሪ ኮሌጅን የሚበጥስበት፣ የየአመቱ ሰኔና ሀምሌ የምርቃት ሰሞን፣ ሞቅ ደመቅ ይላል። እንደሰርጉ ሁሉ ፣ የምረቃዉም ባህል ከአመት አመት በፈጠራ ክንዋኔ ጥልቀትና ስፋት እያገኘ፣ ሽርጉዱ ከተማዎችን ስራ ብዙ ሲያደርጋቸዉ ይስተዋላል፤የሚገዛና የሚሸጥ፣ የሚበላና የሚጠጣ፣ፈንጠዝያዉ በደሀ አገር ዉስጥ ያለን መሆናችንን እስኪያጠራጥር ድረስ።

በአሁን ጊዜ በሚታየዉ የምርቃት ባህል ፣ ከሰላሳ አመት በፊት ከነበረዉ በየይዘትና ቅርጽ ልዩነትን ፈጥሯል። በዘዉዱ ዘመን የከፍተኛ ትምርት ተቋማት አምስት ያህል በነበሩበት ወቅት ዲፕሎማ ወይንም ዲግሪ ለመቀበል ፉክክሩ፣ጣጣዉና መከራዉ ብዙ በሆነበት፣ይህን በታታሪነት አቸንፎ በሚመረቅ ተማሪ ዘንድ የጎላ የፍንደቃ ዝግጅትና ስነስርአት የሚታይ አልነበረም። ስርአቱ ብዙ ተማሪን ተቀብሎ ለማስተማር የሚያስችል አቅምና የተደራሽነት ባህርይ ስላልነበረዉ በአጠቃላይ የአገራችን የከፍተኛ ትምርት ተቋማት ተማሪ ቁጥር በጥቂት ሺዎች የተገደበ ነበር። ሁኔታዉ ተመቻችቶለት ወይንም በሽምደዳ አበሳ ፣በመርፌ ቀዳዳ ግመልን የማሾለክ ጭንቀት ያህል ዉስጥ አልፎ ኮሌጅ ለገባ ተማሪ ቀጣዩ አራት አመት፣ የማንበብ፣ የማጥናት፣ የመጻፍ፣በዚህም ጫና የእንቅልፍና የእረፍት እጦት ጊዜ ነበር። ጥብቅ የማጥራት ሂደቱ በሚፈጥረዉ የእባረራለሁ ስጋትና ጭንቀቶች፣ የመሬት ላራሹ መፈክር የሚያስከትለዉ ቆመጥና የነኮልፌ እስር ቤት ወታደራዊ ቅጣት ተደምሮበት፤ ለተማሪዉ ፋታ የማይሰጡ ጊዜያት ነበሩ። እንዲያ ተሁኖ በማለፊያ ዉጤት የሚመረቅ ተማሪ ለደስታዉና ለምረቃ ስርአቱ የሚሰጠዉ ቁብ የጎላ አልነበረም። እንኳን ድግስ ሊደግስ፣ ከንጉሰ ነገስቱ እጅ ዲፕሎማ ወይንም ዲግሪ የመቀበልን ብርቅ አጋጣሚን አቅልሎ ከአዳራሽ የማይገኝ ተመራቂ ቁጥር ጥቂት አልነበረም። በደርግ ጊዜም ቢሆን ለገበሬ ልጅ ልዩ የመግቢያ ነጥብ አስተያት እየተደረገ የኮሌጁም ቁጥር ትንሽ ከመጨመሩና የትምህርት ፕሮግራሙ አመት ከማጠሩ በስተቀር ጭንቀቱና ስጋቱ፣የምረቃ ክብረበአሉም ከአለፈዉ ዘመን እጅግም የተለየ አልነበርም።

 ከደርግ በኋላ ፖሊቲካዊ ትርጉም ተሰጥቶት የከፍተኛ ትምርት ተቋማት ቁጥር በሚያስገርም ሁኔታ እየጨመረ ከአርባ በላይ ወደማደጉ በሚራመድበት ወቅት፣ ቅበላዉ፣ የመማር- ማስተማር ሂደቱና ስርአቱ፣ ካለፉት መንግስታት ዘመን በይዘትም በቅርጽም ልዩ ክሰተቶችን እያበቀለና እያሳደገ ሄዷል። የምረቃዉ በአል ሁኔታም እንዲሁ እየተቀየረ ተጉዟል። የትምህርትን ተደራሽነት ከማስተካከልና ለአገር ልማት በቂ የተማረ የሰዉ ሀይልን ለማፍራት ከሚል በጎ እሳቤ በመነሳት፣ በርካታ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤቶችን፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ለመገንባት፣ መምህራንንና የትምህርት ግብአትን ለሟላት ከመንግሰት ብዙ ሚሊዮኖች ገንዘብ ወጪ ተድርጓል። ከ65 የሚበልጡ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ተከፍተዋል። የመጀመሪያዉ ኮሌጅ በአዲስ አበባ እንደተከፈተ ለአምስት አመታት የኢትዮጵያን መምህራን ቁጠር ዜሮ እንዳልነበረ ሁሉ፣ በ1950ዎቹ አጋማሽ መቶ እንዳልሞላ ሁሉ፣ በአሁኑ ወቅት የመምህርን ቁትር ከ16 ሺህ በላይ ሆኖዋል።በጥቂት መቶና ሺህ ተገድቦ የነበረዉ የተማሪ ቁጥር ዛሬ የአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ሩብ ያህል ሊደርስ እየገሰገሰ ነዉ። በአመት ወደ መቶ ሺህ ተማሪ ወደመመረቁ ነዉ።

 እነዚህ አሀዞች እደግመዋለሁ-እነዚህ አሀዞች ሲታዩ አንድን ዜጋ ምንኛ ያኮራሉ! በጎ እሳቤዉ በተገቢዉ ሁኔታ ሊተገበር አለመቻሉና፣በዚህም ሳቢያ የአገራችን የትምህርት ስርአት ከአመት አመት እያሽቆለቆለ፣ የትምህርት ጥራቱ እጅግ መኮሰሱ በአኩዋያዉ አንድን ተቆርቋሪ ዜጋ ምንኛ ያሳፍረዋል; ብዙ ተማሪ ዩኒቨርሲቲ በመግባቱና በገፍ በመመረቁ ሁለት የተለያዩ ሀሳቦች ይንጸባረቃሉ። አንደኛዉ፣ የትምህርት ጥራቱ የወደቀም ቢሆን ከተለያዩ ስፍራዎች በርካታ ተማሪዎች በየኮሌጆቹ አብረዉ መኖራቸዉ ራሱ በተዘዋዋሪ ስለማህበራዊ ግንኙነት የሚያስተምራቸዉ ፋይዳ አለዉ። በአራት አመት ቆይታቸዉ የመርሀግብሩን ሙሉ እዉቀት ባይጨብጡም ስለዘርፉ ጥቂት ማወቃቸዉ አይቀርም በማለት በበጎ ሁኔታ  የሚመለከቱ አሉ። በሌላ ወገን ደግሞ፣ መንግስት እንደአሸን እየፈላ ላለዉ እልፍ አእላፍ ወጣት የስራ እድል ለመፍጠር ስላልቻለ፣ጥያቄዉን ለማድበዝበዝ በዩኒቨርሲቲ ሰም የተሰየሙ ሰፋፊ ማጎሪያ ካምፖችን በየቦታዉ ገንብቶ ቁጥጥርና ክትትል ሊያደርግባቸዉ ነዉ ሲሉ የሚደመጡ አሉ። የሁለቱ ሀሳቦች መንስኤ ስለትምህርት ጥራቱ ከመቆርቆር ያለፈ አይመስለኝም።

 ከዚህ ጋር በተያያዘ ‹ትምህርት ጨርሻለሁ› በሚሉት የሰርቲፊኬት፣የዲፕሎማና የዲግሪ( ቢ.ኤ፣ አም.ኤ፣ ፒ.ኤች.ዲ) ተመራቂዎች የሚያስገርም የደስታ በአል አከባበር ባህል እየተንሰራፋ ነዉ። ይህንን ባህል እሰቲ በወፍ በረር እይታ እንመልከት፡- /ለመዝናናት ያክል።/

ከየአመቱ ሰኔ አጋማሽ ጀምሮ በየከፍተኛ ትምህርት ቅጥር ግቢ ዉስጥ ከወትሮዉ የተለየ እንቅስቃሴ ይታያል፤ከምረቃ ዝግጅት ጋር በተያያዘ። ሁሉም ተማሪ ስለመመረቁ ቅንጣት ያክል ስለማይሰጋ ለዝግጅቱ ይንቀሳቀሳል። ከሁለት ሶስት አመት በፊት ትምህርት አስጠልቶት ከኮሌጅ በመጥፋቱ የተሰረዘ ተማሪ ጭምር ለምረቃ ይንቀሳቀሳል። ሊመረቅ ከፈለገ እንደሚመረቅ እርግጠኛ ነዉና!

ለእርግጠኛነቱ አንዱ መንስኤዉ የወዳቂ ተማሪን ቁጥር ለመቀነስና የትምህርት ብክነትን ለመቅረፍ በቀና ልቦና የታሰበዉ ‹ተማሪ መዉደቅ የለበትም› የሚል ጥብቅ የመንግስት መመርያ ሆኖ ይገኛል። ይህን መልካም አስተሳሰብ ዉጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ስነትምህርታዊ ብልሀቶች አሉ። ይሁንና፣አብዛኛዎቹ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ስለዚህ መልካም አስተሳሰብ በስፋት የመወያየት እድል ሳይገጥማቸዉና ስነትምህርታዊ ብልሀቶቹን ተገንዝበዉ ከራሳቸዉ ለማዋሀድ እንዲችሉ ባለመታገዛቸዉ፣ ከመንግስት እንደተላለፈ አግላይ ቀጭን ፖሊቲካዊ ትእዛዝ ይወስዱታል። ያላወቁትንና ያላመኑበትን በአግባቡ መፈጸም መቼም የሚሆን አይደለም። ቅሬታ ኖሮት ከልቡ የማያስተምር መምህር ብቁ የተማረ ዜጋ ያፈራል ብሎ መገመት ከቶ የዋህነት ወይንም እንትንነት ነዉ። ስለዚህም መወደቅ ክልክል በመሆኑ ተማሪዉ በአግባቡ ሳይማር አሳልፎ የማስመረቁ ሂደት እንደ ባህል ፈክቶ ወትቷል።

 በዚህ ላይ ተማሪ ከወደቀ ስህተቱ የመምህሩ እንደሆነ፣ስለዚህ መምህሩ ተማሪዉን እንደምንም ‹ማብቃት› እንዳለበት የሚነፍሰዉ መመሪያ የተማሪዉን ትኩረት ከትምህርቱ በላይ እየገዛዉ ያንዳንዱን ልብ ያደነድነዋል። ማጥነቱን ቸል እንዲል ይገፋፋዋል። የቤት ስራ እንዳይሰራ ያደፋፍረዋል። ያላጠናና የቤት ስራ ያልሰራ ተማሪ ሲፈተን ደግሞ ዉጤቱ ስራዉንና ልፋቱን ስለሚያንጸባርቅ ነጥቡ ዝቅ ይልበታል። በዚህ ምክንያት የወደቀ እንደሆነ መመሪያዉ መምህሩን ዋና ተጠያቂ ያደርገዋልና፣ በስራ ዋስትና እጦት ፍርሀት፣ ወይ በልጎማ ‹ጎመን በጤና› ብሎ ለወደቀዉ ማለፊያ ነጥብ ሊያስቀምጥ ይገደዳል። በተለይ በተዘዋዋሪ የተማሪ ማህበር አመራር መሆናቸዉን ያሳወቁትን፣ እሱ እያስተማረ እያለ እያዛጉ-ግን ‹ኢትዮጵያ፣የአሜሪካ ዲሞክራሲ፣የሂትለርን ጨፍጫፊነት ወዘተ..

ብሎ በተናገረ ቁጥር ተጣድፈዉ ማስታወሻ እየያዙ ተለማማጅ ነጋሪ መሆናቸዉን በዘዴ የሚጠቁሙትን ፣ ‹ያንተ ብሄር ስላልሆንኩ ነዉ የጣልከኝ› ሊሉት የሚችሉትን የራሱ ብሄረሰብ ያልሆኑ አባላት ተማሪዎች ጠንቅቆ ለይቶ ህሊናዉ እየቆረቆረዉ ማርክ የሚጨምር መምህር ጥቂት አይደለም። በአኳያዉም፣ ለመልከ ቀና ዳተኛ ተቃራኒ ጾታ ተማሪዎች ያለስራ የተዛነፈ ማርክ እየሰጡ የማስነፉ ባህልም እያቆጠቆጠ ሄዷል። እንግዲህ በእንዲህ አይነት የመማር- ማስተማር ግድፈት ብዙ ተማሪ ሳያጠና ያልፋል። ሳያልፍ – አልፈሀል፣ ሳይማር- ተምረሀል ይባላል። የየአመቱ መማር ማሰተማሩ ባህል እንዲያ እያለ ይቀጥላል፣ ወደምረቃ ያመራል።

‹ትምህርቴን ጨርሼ› ተመረቅሁ እያለ በድፍረትና በፈገግታ ለዘመድ አዝማዱ የሚያበስረዉ ደግሞ እጅግ ብዙ ነዉ። በዚያን ሰሞን ገንዘብ ማፈላለጉ አእምሮዉን ወጥሮ ይይዛል። ሙሉ ልብስ ከነካራባቱ፣ ከነጫማዉ መገዛት አለበት፤ ይህ ያሳስበዋል።ለሀሳቡ ግለት እሳት የሚለኩሰዉ ደግሞ፣በዩኒቨርሲቲዉ ቅጥር ፊትለፊት በትልቅ ሰሌዳ ላይ የሚወጠረዉ የልብስ ስፌት ካምፓኒዎች ማስታወቂያ ነዉ።ሙሉ ልብስ ለብሰዉ ካራባት ባንጠለጠሉ፣ወይንም ባለመነሳንስ ቆብና ጋዋን ለብሰዉ በሚፈነድቁ ታወቂ የፊልም ተዋንያን ምስል የገነነ ማስታወቂያ። በማስታወቂያ የታየዉን ልብስ ለመግዛት መነቃነቅ፣ገዝቶ ለማሟሸት ይሁን ከወጣትነት ወደአዋቂነት ለመሸጋገር ይሁን.. ከምረቃ ቀደም ባሉት ቀናት ለብሶ ደጋግሞ መንቀሳቀስ፣ ፎቶዎች መነሳት፤ደስታን በጩከት ማጀብ ባህል ሆኗል።

 በማስታወቂያዉ ሰሌዳ አናት ላይ በትልቁ ጽሁፍ ይሰፍራል፤ <CONGRADULATION> የሚል::(CONGRADULATIONS ሊባል ሲገባዉ)። የእንግሊዝኛ ትምህርት በዶክተሬት ደረጃ በሚሰጥበት ኮሌጅ ፊትለፊት፣ በአደባባይ አንገት የሚያስደፋ የእንግሊዝኛ ቃል በኩራት ይሰየማል፤ በእንዲህ አይነቱ የልሂቃን ዩኒቨርሲቱ ቅጥር ግቢ ዉስጥ በያመቱ CONGRADULATION ያለበት የማስታወቂያ ወረቀት በማህተም ታጅቦ ሲለጠፍ ማየት የተለመደ ሆኗል( ቦታ ላለማጣበብ መረጃዉን እዚህ ላለመለጥፍ እቆጠባለሁ)።

በምረቃዉ እለት ጋዋን ተደርቦ፤ ወጣት በደስታ ፈገግታ ሲዋብ ማየት ያስደስታል። በምረቃዉ አበሳሰር ወቅት እያንዳንዱ ተማሪ በልቦናዉ ምን እየተሰማዉ አንደሆነ የሚያዉቀዉ እሱና አንድየዉ ነዉ። እፎይ ተመረቅሁ! እያለ በእርካታና በተስፋ ከሚፍክነከነክ ታታሪ ተመራቂ ይልቅ፣ አሁን እኔ የምር ተመራቂ ነኝ ;ምን እዉቀት ገበየሁ; እያለ በለሆሳስ ራሱን የሚታዘብና የሚወቅስ የእዉነተኛ..ግን የዳተኛ ተመራቂ ቁጥር ጥቂት ሊሆን አይችልም። ‹ እንኩዋን ደስ አላችሁ› የሚለዉ የምርቃት ስነስርአት መዝሙር ሲዘመር፣ እንቅልፍ አጥቶ፣ ለፍቶ ግሮ ሰርቶ ከሚመረቀዉ በላይ የእጥፍ እጥፍ መመረቂያ ቆቡን ወደሰማይ የሚያጎነዉ ደግሞ ዳተኛዉ ሊሆን ይችላል፡ ፡ዳተኛዉ ስርአቱ እስኪያልቅ በትእግስት መከታተልም እየሰለቸዉ ከብጤዉ ጋር ያወራል። ጫጫታ ይፈጥራል። እንደተለመደዉ የእለቱ የክብር እንግዳ ስለትምህርት ሂደቱ ዉጤታማነት፣ለኢትዮጵያ ስንት ሺህ የተማረ የሰዉ ሀይል እንደተፈጠረ፣ባህላዊዉን ዲስኩር ሲያደርግና የወደፊቱን ሀላፊነታቸዉን በምክር መልክ ሲያስረዳ ጫጫታዉ ንግግሩን የዋጠዉ ከሆነ የተመራቂዉን ዉጤታማነት ደረጃ ምን ያህል እንደሆነ ለመለካትና ለማመላከት ይቻላል።

 የዚያን ሰሞን በቴሌቪዥን የሚታየዉ የተመራቂ ብዛት ያስገርማል። በእንደዚያ ባለ እጅግ የሚያሳስብ የትምህርት ስርአት የተኮተከተ ተመራቂን ስታይ ልቧ የሚሸበረዉ ግን ኢትዮጵያ ብቻ ናት። እንዲህ እያለች፡– ዛሬ ከሚመረቁት ልጆቼ ዉስጥ የተበላሸ እግር እናክማለን ብለዉ ደህነኛዉን የማይቆርጡት የትኞቹ ይሆኑ? ለህጻን ሽሮፕ እንደማዘዝ የእንትን ማድረቂያ የሚያጠጡትስ? ግንባታዉ እንደተጀመረ የሚፈርስ ህንጻና፣ በጎርፍ የሚጠረግ ትኩስ አስፋልት- መንገድ የሚሰሩ መሀንዲሶቼስ? የተገነባዉንና የተገዛዉን የህዝቤን ንብረት ሲቆጥሩ እንደምትሀት የሚሰወርባቸዉ ተመራቂዎቼስ? ህዝቤን እንደማገልገል የሚዘርፉትና የሚያንገላቱትስ? ፍርደገምድሎቼስ የትኞቹ ይሆኑ? ሌሎቹን ልጆቼን እንደ ወንድም እህት በፍቅር እያዩ ‹ወገኔ› የሚሉትስ ስንቶቹ ይሆኑ? አልሞ ከጣለ በኋላ‹ ቁም!› የማይለዉስ የቱ ይሆን? የመሀረቤን ቋጠሮ ተሸሽጎኝ የሚፈታዉስ? ጊዜያቸዉን፣ ጉልበታቸዉን፣እዉቀታቸዉን፣ ድሎታቸዉንና ህይወታቸዉን ለብልጽግናዬ፣ ለሰላሜ፣ ለልጆቼ እኩልነት የሚያዉሉ ተመራቂዎች እዉነት እነዚህ ዉስጥ አሉልኝ? በሚሉ ጥያቄዎች የምትብሰለሰለዉ ኢትዮጵያ ነች ..በዚያን ሰሞን።

ከምረቃ በኋላ ተማሪዉ ትምህርቴን ‹ጨርሼ› ተመረቅሁ እያለ በድፍረትና በፈገግታ ለዘመድ አዝማዱ እያበሰረ ያስደስታል። አብዛኛዉ ዘመድ አዝማዱ ጥሪቱን እያሟጠጠ ይደግሳል።የማብላት ማጠጣቱ ባህላችን ያለጥርጥር እያጋራ ደስታን የሚያጎናጽፍ ነዉ።

ክፋት የሚሆነዉ ተመራቂዉ በከማን አንሼነት ስሜት እንደጓደኞቼ ሰንጋ ካልተጣለልኝ፣ ዉስኪ ካልተንቆረቆረልኝ፣ድንኳን ካልተዘረጋልኝ፣ሀብል ካልተጠለቀልኝ ብሎ ያላቅም ቤተሰቦቹን ያስጨነቀ እንደሆን ነዉ። ካገኘዉ እዉቀትና የህዝብ አገልጋይነት ዝግጁነት በላይ የሚያወጣ ዋጋ የጠየቀ እንደሆነ ነዉ። በአደባባይ ከተኮለኮሉ ነዳያንና የኔ ብጤዎች በቅርብ ርቀት ባሉ የአዲስ አበባ ቁንጮ ሆቴሎች የሚደገሱ የልጅ ምርቃቶች ዉስኪና ኮኛች እንደሚፈስባቸዉ፤አዉሮፓና አሚሪካ ደርሶ መልስ የአየር ቲኬት እንደሚሸለሙባቸዉ፣ መኪና በስጦታ እንደሚለገስባቸዉ ሰምቶ የኔም ከዚህ በትንሹም ይቀራረብለኝ ብሎ ለፍቶ አዳሪ ቤተሰቡን ያስጨነቀ እንደሆነ ነዉ ክፋቱ። አንጂ እንዳቅሚቲ ደስታዬን ተጋሩ ማለት ( አዉነት ከልብ ደስታ የሚያስገኝ ዉጤት ኖሮ ከሆነ) በጎ ነዉ። ገና በአዳራሹ ስርአቱን ያጠናቀቀዉን ጋዋን እንደለበሱ በተጋባዥ መሀል እየተጎማለሉ መደነቁም ክፋት የለዉም። ልጄ ተመረቀልኝ ብሎ ወጪ አዉጥቶ፣ እየተንጎማለለ የዋለዉን በተስፋ እያየ፣ ከቀናት በኋላ ተመራቂዉ ትምህርቱን ካቋረጠ አመታት እንዳለፈዉ ጭምጭምታ ሰምቶ እቅሉን የሚጥል ቤተሰብ የሚያጋጥምም በዚሁ በምረቃ ሰሞን ነዉ።

 በዚህ ሰሞን በወጣቶቹ ዘንድ ብቻም ሳይሆን ጥቂት በማይባሉ ጎልማሶች ዘንድ የሚታይ፣ ከእዉቀት ምዘና ጋር በሂሳብ ለመወራረድ የማይመጣጠን ባህልም እየጎለበተ ነዉ። በተለይ ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ተመራቂ ‹ምሁራን› አካባቢ። መቼም የድህረምረቃ መርሀግብር መግባት በመስቀል አደባባይ የመዘዋወርን ያክል ነጻና ልቅ ከሆነ ሁለት አሰርት አልፎታል። ማንም ድግሪ ያለዉ ሁሉ ሊገባበት እንደሚችል መመርያ ያዛል። የመግቢያ መነሻ ነጥብ 2 ስለሆነ ያለብቃት የተመረቀዉም ሁሉ የሚገባበት ሆኖዋል። ቀድሞ በኛ አገር፤አሁን ደግሞ በፈረንጅ አገር የድህረ ምረቃ ፕሮግራም ለመግባት በመጀመር ዲግሪ ቢያንስ በ3 ነጥብ መመረቅን ይጠይቃል። በዚህ ምክንያት ለሁለተኛና ለሶስተኛ ዲግሪ ለመማር የሚያልም ሁሉ የመጀመሪያ ዲግሪዉን ዉጤት ከፍ ለማድረግ ሌት ተቀን ይሰራል። በዚያም ሂደት እዉቀትን ይሻማል። በዚህ ዘመን ባገራችን የሚታየዉ ግን የተለየ ነዉ። ለመመረቂያ የመጨረሻ አነስተኛ ነጥብ ያመጣ ዳተኛዉ ሰተት ብሎ ይገባል። ፈርዶበት መምህሩ በእንግሊዝኛ እንደአቅሙ ሲያስተምር አንዳች ቁብነገርን ወደአእምሮዉ ለመላክ የሚቻለዉ አብዛኛዉ አይደለም። ዋና ግዴታዉ ክፍል ዉስጥ መገኘት ነዉ። የቤት ስራ ለማስረከብ የሚጨንቀዉ አይሆንም። ለጎበዝ ጓደኛዉ ትንሽ ብር ሰጥቶ ያሰራል። በፈተና ወቅት አጠሪራ ይዞ ይገለብጣል። ብዙ መምህር እያወቀ እንዳላወቀ ሆኖ ያልፈዋል። በኋላ መዘዙ ብዙ ነዉና ምን አነታረከኝ ብሎ። መጣል ክልክል ነዉና ማለፍያ ነጥብ ሰጥቶት ይገላገላል። የመመረቂያ ጽሁፉም የሚያሳስበዉ አይደለም። በጥቂት ሺህ ብሮች ከሱቅ ዉስጥ ተዋዉሎ አጽፎ ያስረክባል። ይመረቀና ድግሱን ያቀልጠዋል።በተለያየ የብልጠት ስልት እንዲህ ያለዉ ያልተማረ ተመራቂ ሳይማር የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ሆኖ ሊቀጠር ይችላል። ያኔ ወዮለት ክፍል ዉስጥ ላለ ጎበዝ ተማሪ! አወይ! ኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትሽ!

ለሶስተኛ ዲግሪ ምረቃም አዲስ ባህል ተፈጥሯል። ተመራቂዉ ቪቫ! ፒ.ኤች. ዲ የሚል በጉልህ በተጻፈ ስር በከለር ያበደ ፎቶግራፉን በትልቁ ለጥፎ በየኮሌጁ መግቢያና ቅጥር ግቢ ማስታወቂያ ማዉጣት የተለመደ ነዉ። በተቋቁሞዉ እለት ዶክተር ሆነሀል ይባላል። ይመረቃል፣ ይደገሳል። እናት እትዮጵያ የተመራቂዉን ብዛት ስታይ ደስ ይላታል። ግን በዚያን እለት የምትጠይቃቸዉ ጥያቄዎች አሏታ። እዉነት ሊያስመርቅህና ለኔ ጠቀሜታ የሚያበቃ እዉቀትና ክህሎት እንድትገበይ የትምህርቱ ስርአት ፈቅዶልህ ነዉ ዛሬ ተደስተህ ድግስ የደገስከዉ? ዉስጥህ ምን ይሰማሃል? ለብልጽግናዬ፣ ለሰላምና ለዲሞክራሲ በጽናት እንድትቆም እምሮህን የሞረደ እዉቀት ገብይተሀል? ለመሆኑ የተመረቅህበት ጽሁፍ ስለምንድነዉ? ለኔ ችግር መፍቻ አንድ ጋት የሚያስኬድ ምርምር ነዉ? ነዉ ወይስ ዶክተር ለመባል ብቻ የሚያበቃህ ነዉ? .. ኢትዮጵያ እነዚህን ጥያቄዎች በመመረቂያ አዳራሽ ጎዋን ለብሰህ ባለህበት ትጠይቃለች። እና ምን ትመልስላታለህ።

 እኔም ፒ.ኤች ዲ በተመረቅሁበት እለት እንደ አንዳንዶቹ ጥቂት ባለህሊናዎች ለነዚህ ጥያቄዎች አዎንታዊ መልስ ለመስጠት አለመቻሌና መሰቀቄ ትዝ ይለኛል። ‹እንኳን ደስ አላችሁ … እማ መርቂኝ..› የሚሉትን መዝሙሮች ስሰማ በዚያ የምረቃ አዳራሽ መገኘቴ ምቾት ነስቶኝ ነበር። አዉሮፓ ለሁለተኛ ዲግሪ ስመረቅ በምረቃ ስነስርአቱ ላይ አለመገኘቴ ምንም ቅር አላሰኘኝም ነበር፤ አላጎደለብኘምም። አሁን ሽርጉድ ማለቴ ደግሞ አንዳች የጨመረልኝ ደስታ አልነበረም። እንዴት እንደተማርኩ፣ የመመረቂያ ጽሁፌ ምን እንደሆነ ሳስብ ለዚህ ፈንጠዝያ የሚያበቃኝ እንዳልሆነ ልቤ ይቆጠቁጠኛል። በወላጆቼ ግፊት ለደስታቸዉ ስል እኔም ወይፈን ጥዬ፣ ከቁጠባ ባገኘሁት ብድር አንዳንድ ጠርሙስ ዉስኪ በየጠረጴዛዉ ደርድሬ፣ ጎረቤትን ጭምር ሊያስቀይም የሚችል ሙዚቃ በሞንታርቦ ለቅቄ፣ አሸሻ ገደሜ እያሰኘሁ፣ መመረቂያ ልብስ ሳላወልቅ እያዛገሁ ስንገዋለል መዋሌን ሳስታዉስ ህሊናዬ ይኮሰኩሰኛል። ቀደም ሲል በፒ.ኤች ዲ የተመረቁት አንዳንድ የስራ ባልደረባዎቼ ልክ እንደተመረቁ ባህርያቸዉን መለወጣቸዉን እንዳልኮነንኩ ሁሉ፣ሳላዉቀዉ እኔም ለአመታት ያንኑ መከተሌ ዛሬ ዛሬ ቅር ይለኛል። አካሄዴን ‹የዶክተር› አስመስያለሁ። ትህትናዬን በመኮፈስ፣ ፈገግታዬን በመኮሳተር ተክቼዋለሁ፣ሳቅ አቋርጫለሁ። ከሰዉ እንደወትሮዉ ላለመቃለድና ላለመጫወት ቁጥብ ሆኛለሁ…‹ቀልድና እንትን ቤት ያበላሻል› አይነት እንዳሆነብኝ። ማንም በድፍረት እንዳይጠጋኝ ተከላክያለሁ። ከማን እኩል መሆኔን ዘንግቼ የበላይ መሆኔ በይፋ እንዲረጋገጥልኝ የሚቻለኝን ጥረት አድርጌያለሁ። ከኔ ጋር የሚደረግን ክርክር በቁጡነት፣ በግድ በአሸናፊነት መወጣት እንዳለብኝ አምኛለሁ። ማንም ሰዉ ..ባለቤቴና ልጆቼ ጭምር በነጠላ ስሜ ‹እዉነቱ› ብለዉ ሲጠሩኝ የሆነ ክብር እንደተቆረጠብኝ ተሰምቶኛል። እንዳንዶች እንደሚሉት እኔም ‹ለፍቼ ያገኘሁትን መጠርያ አትቀንስ› ወደማለቱ ሲዳዳኝ ነበር፡ ምን ነክቶኝ ነበር? ባህሉ እኔንም በቁጥጥሩ ስር ስላደረገኝ ይሆን?

 ፈረንጅ አገር ሳለሁ ግን ዶክተር የሚል መለያ በህክምና ዘርፍ ለተሰማሩት የመጀመርያ ዲግሪ ተመራቂዎች የሚሰጥ መሆኑን ተረድቻለሁ። የህክምና ተመራቂ ዶክተር ይባላል- ፒ.ኤች ዲ ያልተቀበለ ቢሆንም። ፒ.ኤች ዲ ያገኘን ዶክተር ብሎ መጥራቱ ያልተለመደ ነዉ። እንዲህ ብለህ ካልጠራሀኝ ብሎ የተቀየመ ፈረንጅ አስተማሪ ወይ ወዳጅ አይቼም አላዉቅም። እዚህ እንደሚደረገዉ ከሰዉ ጋር ሲተዋወቁ ‹ዶክተር እገሌ ነኝ› ለማለት የሚደፍርም የለም። ምክንያቱም ዶክተርነትን እንደሹመት የሚቆጥረዉ የለምና። ደብዳቤ ሲልክ እንኳን ከዶክተር እገሌ ብሎ አይጽፍም። ስሙን ጽፎ ከጎኑ የትምህርት ደረጃዉን ለማሳየት ፒ.ኤች ዲ ብሎ ነዉ የሚያስቀምጠዉ። እና ፒ.ኤች ዲ ማግኘት የልዩ ክብር መለኪያ ሳይሆን ፣ጥናትና ምርምር ለማድረግ የመቻል ላይሰንስ ማግኘት ብቻ ነዉ። ለወደፊት በአንዲት ዘርፍ ጥናትና ምርምር ለማድረግ መሰረታዊ ብልሀት እንዳገኘሁ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እንጂ ሹመት ወይንም የአጠቃላይ እዉቀት ጣርያ መንካት ማረጋገጫ እይደለም። ይህን ጥርት አድርጌ እያወቅሁ እኔም የባህሉ አራማጅ ሆኛለሁ። እንዲህ መናዘዜም ከዚህ ባህል ለመዉጣት የማደርገዉ ጥረት አንድ አካል ይሆን ይሆናል። ነገ ደግሞ ከረዳት ፕሮፌሰርነት ወደ ተባባሪ ፕሮፌሰርነት እና ፕሮፌሰርነት ስሸጋገር፣ ሽግግሩ ሶስት አራት ጥናት ማሳተሜን የሚያሳይና እንደ መ.ፕ የደመወዜ እርከን ከፍ ማለቱን ከማመላከት ባሻገር እንደ መሳፍንትና መኳንንት፣ፊታዉራሪነትና ደጃዝማችነት ግብር የሚያስጥል፣ ፌሽታ የሚያስደርግ ሹመት አለመሆኑን አምኜ ከይሉኝታ ተላቅቄ ከአንዳንድ ባልደረባቼ የምርቃት ፌሽታ ባህል ላፈነግጥ መናዘዜ ይሆናል። ያዉም አንዳንዴ ለራስ፣ ወይ ለወዳጅ ወይ ለጠላት በልክ የሚሰፋ የሴኔት ህግ በየጊዜዉ እየተቀያረ ረዳት ፣ተባባሪ እና ሙሉ ፕሮፌሰርነት በሚያሰጥበት ዘመን። ስለክብር ዶክተሬት ምርቃት ዛሬ ይለፈኝና ላጠቃልል፡–  የምርቃት ደስታ መግለጫ ባህላችን በልኩ፣እንደዉጤቱና እንደእዉነታዉ ሲሆን ያረካል። ዋጋዉ በዋጋዉ መጠን ሲሆን ይጥማል። ከእሴት በላይ ዋጋ አርቲፊሻል ይሆንና ዝቅም ያደርጋል። ኢትዮጵያ፣ለወግ ለማእረግ ሊያበቋት የሚችሉትን ልጆችዋን በጥራት አስተምራ ስታስመርቅ ያኔ ዉቅያኖስ የሚያክል ፌሽታ ይደረግ፤ አገር ያክል ዳስ ይቀለስ፤ እልፍ አእላፍ ፍሪዳ ይጣል፤ሺህ በሺህ ጋን ጠጅና ጠላ ይንቆርቆር፤ መለከት ይነፋ፤ ከበሮ ይደለቅ፤ እልልታ፣ ዘፈንናና ጭፈራ ምድሯን ያጥለቅልቅ፤ሰማይዋ ላይ የፍቅርና አንድነት ዝማሬ ይሙላ።በቀረዉ እርሶ ይጨምሩበት። 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top