ጥበብ በታሪክ ገፅ

የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ሳንካዎችና ጸጋዎች (ክፍል ፩)

፩. ነገረ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን

መገናኛ ብዙኃን (Media) የቃሉ ትርጉም እንደሚገልጸው በተለያየ ቦታ የሚገኙን አካላት በአንድ ርእሰ ጉዳይ ዙርያ እንዲወያዩ፣ እንዲግባቡ ወይም እንዲከራከሩ የሚያስችል መረጃ፣ እውቀት፣ አስተሳሰብና አዲስ ግኝት ለሁሉም የሚደርስበት መንገድ ነው። በአካል መገናኘት ሳያስፈልግ የሐሳብ ተደራሽነትን የሚያረጋግጥ ነው። በድሮ ጊዜ ነጋሪት በመጎሰም ወይም ጥሩምባ፣ መለከት በመንፋት ወይም ተራራ ላይ በመውጣት ወይም በእግር በፈረስ በመንቀሳቀስ በድምጽ በመጮህ አዋጅ ይነገራል፣ በተለያየ ቦታ የሚገኙ ሰዎች መረጃ ይደርሳቸዋል። በኋላም በደብዳቤ፣ በሬድዮና በቴሌቭዥን ከአንድ አካል ወደ ሌላው መረጃ ይደርሳል። ብዙኃኑ ተገናኙ ማለት ነው።

 አሁን ባለንበት ዘመን ደግሞ በስልክ ወይም በሌላ “ዘመን አመጠሽ” የመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት መረጃ መለዋወጥ ከምን ጊዜውም በላይ ቀላል ነው። እንደ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ኢሞ፣ ዋትስ አፕ፣ ቫይበር፣ ኢመይል፣ ትዊተር፣ ዩ ትዩብ፣ ድረ ገጽ ወዘተ በየጊዜው የሚፈጠሩ “Applications” በመጠቀም መረጃዎች ከግለሰብ ወደ ግለሰብ፣ ከተቋም ወደ ተቋም፣ ከተቋም ወደ ግለሰብ፣ ወይም ከግለሰብ ወደ ተቋም በጠቅላላ የግል እና የጋራ፣ አገራዊና ተቋማዊ ጉዳዮች ይተላለፋሉ። ከላይ የተዘረዘሩት መገናኛ ብዙኃን መንገዶች በግለሰብ ደረጃ መጠቀም የሚያስችል ክፍት በር ስላላቸው ማንኛውም ለቴክኖሎጅው ቅርብ የሆነ አካል በቀላሉ መጠቀም ይችላል። ለዚህም “ባለቤት አልባ” ከመሆናቸው የተነሳ ይመስላል “ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን (Social Media)” የሚል መጠሪያ የተሰጣቸው። የመገናኛ ብዙኃንን ታሪክ እድገትና ባህርይ መተንተን አይደለም የዚህ ጽሑፍ ዓላማ። ይልቁንም የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማና ይዘት በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ዙሪያ የሚስተዋሉ ሳንካዎችና ጸጋዎች ላይ ለመነጋገር የሚያስችል ፍልስፍናዊ ሐተታ ማቅረብ ነው።

“ሳንካ (ሳንክ)” የሚለው ቃል መዝገበ ቃላዊ ትርጉሙ “ጥፋት፣ እንከን” የሚል ነው (ኣማርኛ መዝገበ ቃላት፣ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ 1993፣ ገጽ 133)። ደስታ ተክለ ወልድ ደግሞ “ሳንክ” የሚለውን ቃል “ጒትቻ፤ ሰበብ፡ ሁከት፡ ክፉ ሐሳብ” በማለት ይተረጉሙታል (ዐዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ፲፱፻፷፪፣ ገጽ ፲፩፻፺፫)። ይህንን ቃል የምጠቀምበት ማኅበራዊ መገናኛ ብዚኃን ይዟቸው የመጣውን እንከኖች፣ በሰዎች ተግባቦት ላይ ያስከተላቸውን ተግዳሮቶችና እውቀትን፣ ሥነ-አመክንዮን፣ ግብረገብን፣ የመንፈስ ትስስርን በመገደብ ያደረሰውን ስንካሌ (እንቅፋት) ለመግለጽ ነው። ጸጋ ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ ከአንድ ነገር ጋር የተያያዘ መልካም እሴት ወይም በረከት ነው። ለአንድ ነገር ያለን ዋጋ የሚወሰነው ነገርየው ከሚያስገኘው ጸጋ አንጻር ወይም ከነገሩ ጋር የተያያዘውን እንከን ወይም ሳንካ በመገምገም ነው።

 ይህ ጽሑፍ መሠረታዊ ይዘቱ እውቀትን ከማበልጸግ፣ የጋራ ተግባቦትን ከማረጋገጥ፣ የመንፈስ ትስስርንና አገራዊ አንድነት ከማሳካት፣ ሥነምግባራዊ በጎነትንና በባህል፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወዘተ ያሉ አገር በቀል እውቀትን ከማጎልመስ አንጻር ባጭሩ ሰውን ወደ ሰውነት ክብሩ ከፍ ከማድረግ አኳያ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን እያደረገው ያለውን መልካም አስተዋጽኦ ወይም እያስከተለብን ያለውን ተግዳሮቶች መገምገም ነው። በዋናነት ፌስቡክ ላይ የተደረገ ትችት ነው። ጉዳዩ ትልቅ ጥናትና ምርምር የሚያስፈልገው ነው። በተለይ የተግባቦት (Comunications)፣ የሶሲዮሎጂ፣ የሥነ-ልቡና፣ የፖለቲካ፣ የባህል ጥናት ሰዎች ትኩረት ሰጥተው በጋራ ቢያጠኑት የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንን ተቃርኖ ማግኘት ይቻላል። ቴክኖሎጅው ብዙ ነገራችንን እየወሰነ፣ ማኅበራዊ ሚድያው በየጓዳችን እየገባ የየቀን ተግባቦታችንንና ውሏችንን እየመራ ስለሆነ የብዙዎቻችንን ድምጽ ይፈልጋል። ለዚህ ነው ጉዳዩን ከፍልስፍና አንጻር ለመመልከት የተነሳሁት።

 ኸርበርት ማርኩሰ የተባለ የማኅበራዊ ሃሀሲ ምሁር (Social Critic) ቴክኖሎጅው ሁለነገራችንን ከመወሰኑ የተነሳ የግለሰቦችን መብት፣ ነጻነት፣ የሕይወት ዘይቤን ለመምረጥ እንቅፋት በመሆን ንቡርን (Tradition) በእጅጉ ተጭኖታል። ቴክኖሎጂ በፖለቲካ ታሽቶ፣ በጨቋኝ ተቃርኖዎች ተቃኝቶ ስለሚቀርብ ኢ-ወገንተኛ ነው ለማለት ይከብዳል። በዚህም ቴክኖሎጂ [ከላይ ሲታይ ባለ ብዙ አማራጭና የሰዎችን ነጻነት የሚያበረታታ ቢመስልም በውስጡ] ሰዎች ሁሉ በአንድ አቅጣጫ ብቻ እንዲጓዙ እንደ ጋሪ ፈረስ እይታቸውን ሸብቦ በመያዝ አማራጭ የእውነት መንገዶችን እንዳናይ ጋርዶናል ይላል። ይህ ግርዶሽ መገፈፍ አለበት። ምክንያታዊ ማኅበረሰብ ለመገንባት የሚደረግን ማንኛውንም ጥረት የሚያኮላሽ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ጋጋታ በሥሜት የሚመራን መንጋ ስለሚያበረታታ ለእውነትና ለበጎነት፣ ለጋራ መግባባትና ለአንድነት እንዲሁም ለሰው ልጆች ብልጽግና፣ የኑባሬ ከፍታና የመንፈስ ልዕልና ከፍተኛ ጋሬጣ እየሆነ ይገኛል። ለዚህ ነው የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ጉዳይ እንዲሁ ችላ መባል የለበትም የምለው።

 በዋናነት ፌስቡክን እንደወካይ በማየት፣ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንን ሳንካዎችና ጸጋዎችን እንመለከታለን። ፌስቡክ አንዱ የቴክኖሎጅ ውጤት ነውና ማርኩሰ እንዳለው በእያንዳንዳችን ጓዳ እየገባ፣ የኑሯችንን ዘይቤ እስከ መወሰን እየደረሰ ነው። በኔ ትዝብት (ፌስቡክ መጠቀም ከጀመርሁ ከ6 ዓመታት በላይ ሆኖኛል) በኢትዮጵያ ፌስቡክ ሦስት የእድገት ደረጃዎችን አልፏል። በመጀመሪያ ሰዎች ፎቶ የሚለጥፉበት፣ ደስታና ሐዘናቸውን በጋራ የሚያከብሩበት፣ ጓደኝነት የሚያፈሩበት፣ በጠቅላላ የመዝናኛና የትውውቅ መድረክ ነበረ። ሁለተኛ የተለያዩ የፈጠራ ጽሑፎችና ትምህርታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ የፍልስፍና፥ የሃይማኖት እና የሥነ-ጥበብ ሥራዎች የሚቀርቡበት ነበር። ትንሽ ጠጠር እያለ ቁም ነገር አዘል ጽሑፎች የሚቀርቡበት፣ ወይይትና ክርክር የሚያስተናግድበት፣ የእውቀት ሜዳ ወደ መሆን ተሸጋግሮ ነበር። ሦስተኛውና አሁን ያለበት ደረጃ ደግሞ የፖለቲካ ጽሑፎች የበረከቱበትና በተለይ ብሔር ተኮር መተነኳኮሶች፣ መካሰሶች፣ ከፍተኛ የፖለቲካ ተቃውሞ ጽሑፎች የሚቀርቡበት ሆኗል። በፌስቡክ መንደር በቲዎሪ ደረጃ ያየናቸው ሐሳቦች ግዝፍ ነስተው ፖለቲካ ሕይወታችን ላይ ከፍተኛ ጫና ሲያደርሱ ማስተዋል ከባድ አይሆንም። በርግጥ በእያንዳንዱ ደረጃ ላይ ያየናቸው ነገሮች መጠናቸውና ክብደታቸው ይለያይ እንጅ ሁሉም ደረጃ ላይ አሉ።

ለውይይት እንዲያመች ከፍተኛ የፌስቡክ ተሳታፊዎች የትኩረት አቅጣጫ በኔ ትዝብት ከየት ወደየት ተጓዘ የሚለውን ካስማ (Framework) ለማበጀት ነው እንጅ የፌስቡክ ለውጥ በዚህ ብቻ የሚታይ ነው ማለት አይደለም። ፌስቡክን እንደ መነሻ የወሰድሁበት ምክንያት የሌሎቹ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን አንደበት በመሆን በተሳታፊዎቹም ብዛት እና በገደብ አልባነቱ የውክልናውን ድርሻ ይይዛል በሚል እምነት ነው። በግለሰቦች “የውስጥ መስመር” ውይይት የተነገሩትን “ምሥጢሮች” ሳይቀር በፌስቡክ ስለምናገኛቸው ነው። እኔ መረዳት በምችልባቸው ሦስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ትግርኛና እንግሊዝኛ) እንዲሁም በተወሰነ መልኩ በምረዳው የግእዝ ቋንቋዎች የሚቀርቡትን ጽሑፎች መሠረት በማድረግ ነው ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንን በፍልስፍናዊ ሐታታ የምገመግመው። ከተግባቦት፣ ከሰው ባህርያት፣ ከእውቀትና ምርምር እንዲሁም ከጥበብ እድገት፣ ከሰብዓዊነትና ከጋራ ብልጽግና፣ ባጠቃላይ ከአገራዊ አንድነትና ከምክንያታዊ ማኅበረሰብ ግንባታ አንጻር ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን እንዴት ይገመገማል? እያመጣብን ያለው ጦስና እያስገኘ ካለው ጸጋ አንጻር እንዴት እንመለከተዋለን? ማን ምን ማድረግ ይኖርበታል? የሚሉ አበይት ጥያቄዎችን ማዕከል ያደረገ ሰፋ ያለ ሐተታ ነው።

 ፪. ተግባቦት (Communication)

የመገናኛ ብዙኃን ዋና ዓላማ ተግባቦትን ወይም የመንፈስ ትስሥርን ማረጋገጥ ነው ብለናል። ብዙ መራቀቅ ሳያስፈልገን ተግባቦትን በተፈጥሮ ነገሮች የርስ በርስ ቅንጅትና የሕይወት ምህዋር ውስጥ እናገኘዋለን። “ሳይነጋገሩ ከሚግባቡ” እጽዋትና እንስሳት ጀምሮ በቃላት አማካኝነትና በመንፈስ ስበት ከሚግባቡት ሰዎችና መላዕክት እንዲሁም ፈጣሪና ፍጡሮች መካከል ተግባቦት እንዳለ ማመን ባይቻል እንኳ አለማመን በራሱ አጠያያቂ ነው። ስለ ተፈጥሮ መናበብ ወይም ተግባቦት ጉዳይ ካተቱ ፈላስፎች አንዱ ሌብኒዝ የተባለ የዘመናዊው ወቅት ፈላስፋ ይገኛል። ይህ ሰው ዓለም የምትገዛው ሠራዔ መጋቢዋ ቀድሞ ባስቀመጠላት የውሕደት ካስማ ነው ይለናል። “Pre- Established Harmony” የቁስ አካልና የመንፈሳዊ ነገሮች ውሕደት ሰንሰለት እንደሆነ ይነግረናል። ተግባቦት እንግዲህ በሁለት ነገሮች መካከል የሚደረግ ቅርርብ ነው፣ መናበብና መዋሐድ።

ሰው ከሰው፣ ሰው ከተፈጥሮና ፈጣሪ፣ መንፈስ ከመንፈስ ጋር፣ በሚያደርጉት መናበብ የሚፈጠር መስማማት ነው። የመገናኛ ብዙኃን ዓላማ ይህንን የመናበብ ሂደት መደጎም ነው፣ ማገዝ፤ መንፈሶችን፣ ልቡናዎችን ማቀራረብ፣ ያለ መግባባትን ጭጋግ ነድሎ በማለፍ ላንዱ ድምጽ ለሌላው ጀሮ፣ ለአንዱ ቋንቋ (ቅኔ) ለሌላው ተርጓሚ በመሆን መንፈሶችን ማቀራረብ፣ ማነጋገር፣ ማስታረቅ መቻል ነው። በርግጥ መገናኛ ብዙኃን የቱቦነትን ሚና ብቻ የሚጫወት ይመስለናል። ግን ሁለቱ አካላት (ተናጋሪውና ሰሚው) በመልካም ፈቃዳቸው ሲመርጡትና በታማኝነት ሲጠቀሙት ከሚተላለፈው ኃሳብ የዓላማ ጠማሪነት አንጻር ሲታይ ግን መገናኛ ብዙኃን ከመልዕክት ማስተላለፊያነትም አልፎ የመጨባበጫ ድልድይ ይሆናል። ለዚህም ነው መገናኛ ብዙኃን ከመረጃ ልውውጥ ይልቅ የመንፈስ ትስስርን፣ የሁለት ሕሊናዎችን መናበብ ማገዝ አለበት የምንለው።

  ለመሆኑ የመንፈስ መግባባት ምንድን ነው?

ሄግል የተባለ ጀርመናዊ ፈላስፋ የሰው ልጅ የታሪክ ጉዞ መዳረሻው አማናዊውን መንፈስ (Objective Spirit, Geist) እውናዊ ወደ ማድረግ ነው። ይህም እኔነትን (Subject) ወደ አንድነት ማቅረብ ነው። ወደ ውሕደት ማቅረብ። ሊቁ እጓለ ገብረ ዮሐንስ ይህንን ፈላስፋ ጠቅሶ የመንፈስ መዳበር የሚረጋገጠው በተለያዩ የእኔነት መንፈሶች መካከል በሚደረግ ተግባቦት ነው። ይህ ዓይነቱ ተግባቦት ደግሞ ልዩነቶችን በማበጠር አንድነቶችን በማንጠር በሚደረግ የበጎ መንፈሶች መፋፋት ነው። ነገሩ እንዲህ ነው። መጀመሪያ አንብሮ (thesis) አለ። ይህንን ንቡር እንበለው። ለዘመናት ተቀብለነው የኖርነው የእኛ የምንለው እሴት። ቅቡል የሆነ ሐሳብ ነው። ሁለተኛ ተቃርኖ (antithesis) አለ። ይህንን ደግሞ አፈንጋጭ ሐሳብ እንበለው። የዘመን መንፈስ የወለደው ተቃውሞ ነው። ወይም ንቡሩን መፈተን፣ መጠየቅ፣ ሙሉ በሙሉ መቃወም ወይም የስናፍጭ ቅንጣት ታክልም ብትሆን መጠራጠር እንበለው። ታቃርኖ ካልታፈነ፣ አንብሮም በከንቱ ጭፍንነት ካልገነነ ምክንያታዊ የሆነ ሰው ሁለቱን ለማከራከር፣ ለማወያየት ወይም ለማነጋገር ወደ ፍርድ አደባባይ ያቀርባቸዋል። በዚህ ጊዜ ምክንያት ይሉት ማበጠሪያ ከሁለቱም በኩል ያለውን ግድፈት ያስወግድና ዘመን ሊሻገር የሚችለውን በሁለቱ ጽንፎች መካከል ያለውን በጎነት ያብብ ዘንድ ያዋሕደዋል። ይህንን ሊቁ አስተጻምሮ ብሎ የተረጎመው (synthesis) ነው።

እንግዲህ ለሄግል የታሪክ ጉዞ እንደዚህ ዓይነት አስተጻምሮዎችን የመፍጠር ጉዞ ነው። ይህ የበጎ ሐሳቦች ነጥሮ መውጣትና የእኩይ ሓሳቦች ወድቆ መቅረት ጉዞ “ዲያሌክክ” ሲል ይሰይመዋል። የተግባቦት ጫፉም ወደ አማናዊው መንፈስ መቅረብ፣ የመንፈሶች መዋሃድ ነው ይለናል።

በዚህ የመናበብና የመግባባት ሂደት ውስጥ እንግዲህ እውነት እየበለጸገች፣ እውቀት እየጎለመሰች፣ ድንቁርና እየኮሰመነች፣ ከንቱ ስሜት እየተሻረ ምክንያታዊነት እየነገሠች ትሄዳለች። እዚህ ላይ “ከንቱ ስሜት እየተሻረ” ማለታችን ኢ-ምክንያታዊ ታባይነትን እንጅ ፍቅር፣ ወይም እምነትን የሚመለከተውን ስሜት አይደለም። “ሰውኮ ምክንያታዊ ፍጡር ብቻ አይደለም። መንፈሳዊም ጭምር እንጅ” እንዳለው ሊቁ እጓለ ሰውኮ ስሜታዊም ጭምር ነው ብለን እናክልበትና ለማብራራት ትንሽ ቃላት ካስፈለገ እነሆ። ሰው ያስባል፣ ይመራመራል፣ ነገሮችን በሥነ አመክንዮ ለማረጋገጥ ይጥራል። እንዲሁ በፍልስፍና ይራቀቃል፣ በሳይንስ ቤተ ሙከራ ይታትራል። ይህ እንግዲህ ሰው ምክንያታዊ እንስሳ መሆኑን ከሚያሳዩት ባሕርያቱ የሚቀዳ ነው። ግን ደግሞ ስሜት የሚባል የባሕርይ ወይም የ”ተሐዝቦት” (Experience) መገለጫም አለ። ክትክት ብለን እንድንስቅ፣ ስቅስቅ ብለን እንድናለቅስ፣ በጎ ነገርን ስናይ ወይም የክፋትን ጥግ ስንገነዘብ በጥልቅ ተመስጦ ዝም እንድንል የሚያደርገንም ስሜት ነው። በስሜት የምንገልጸውን በምክንያት አናረጋግጠውም፣ በቃላት ላንገልጸው በቋንቋ ላንራቀቅበት እንችላለን። አንድ ጓደኛየ በአንድ መድረክ ላይ ሲናገር ስለዚህ ጉዳይ ሲያስረዳ ከቀደምት አበው አባባል ጠቅሶ “ኢይትነገር አላ ይትነከር በማለት ነበር ይህንን የጥልቅ ስሜት ተመስጦ የገለጸው። የማይነገር የሚደነቅ ብቻ ነገር አለ እንደማለት ነው።

 በዚሁ ወደ እምነት እንራመድ። ሰውና ፈጣሪን ስለሚያገናኘው ነገር ብዙ ፈላስፎችና የሃይማኖት ሰዎች ሲያወሩለት፣ ሲጽፉለት ስለኖሩት እምነት ይህ አጭር ጽሑፍ ምንም ማለት እንደማይችል ብገነዘብም ንቡርን ለመዘከር ብቻ ነው። እምነት የሰው ልጆች በምክንያት የማያረጋግጡትን በስሜት የተረዱትን ውስጣዊ እውነት የሚያኖሩበት የአቋም መካዘን ነው። ከሐተታና ምርምር፣ ከተመስጦና አንክሮ የሚወለድ እውነት ነው። ይህም ከቃላት በላይ ነው። Kierkegaard (ኬጋርድ) የተባለ የ20ኛው ክፍለ ዘመን የሃይማኖት ፈላስፋ የሰው ልጅ እውነተኛው የኅልውና ጥግ የሚረጋገጠው እውነትን በጨበጠበት ልክ ነው ይለናል። ሰው ሦስት የኑባሬ (Existential) ደረጃዎች አሉት። እነሱም ስሜትን በማርካት የሽር ብትን ኑሮ (Aesthetic)፣ ለሕግና ለማኅበረሰባዊ እሴቶች ተገዥ በመሆን የግብረ ገብ ኑሮ (Ethical) እና ለፈጣሪ ትእዛዝ ብቻ በመገዛት የሚደረግ ሃይማኖታዊ ኑሮ (Religious) ናቸው። ለኬጋርድ የሰው ልጅ ሁሌም በሥነ ልቡናዊ በመባተት (psychological despaire) ውስጥ የሚገኝ ብኩን ፍጡር ነው፡፡

“በመነጋገር የሚደረግ መቀራረብ የመጀመሪያው ደረጃ ነው። እንግዲህ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ይህንን መነጋገር በመደጎም ረገድ ይኽ ቀረሽ የሚባል አይደለም። እንዲያውም እጅጉን ተራምዷል ማለት እንችላለን። መነጋገር በራሱ ግን የመጨረሻ ግብ አይደለም”

 የሕይወት ስንክሳር በአያዎ የተሞላችና በየትኛው ይሻለኛል? ምርጫ ንውዘት ውስጥ የታጨቀች ናት። እናም አሳቢው ሰው ይህንን ስነ ልቦናዊ ንውዘት ለመቋቋም ከአንዱ የሕይወት ዘይቤ ወደ ሌላኛው ሲሸጋገር ይኖራል። እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ወደ ሦስተኛው የሕይወት ደርዝ (ደረጃ) ይደርሳሉ-ወደ የሃይማኖት ሕይወት። ይህ ሕይወት የእምነት ሕይወት ነው። ይህንን ሕይወት ሲገልጸው ታዲያ ሌላ የግል ወይም የማኅበር ኃላፊነት ሳይሆን ሰውን የሚያሳስበው እውነት እኔ እና የኔ ምግባር በፍጹሙ ፈጣሪ ፊት ለመቅረብ ብቁዎች ነንን? የሚል ይሆናል ይለናል። ጀርመናዊ ፈላስፋ ይህንን ጉዳይ ሲያስረዳ ይህ ሕይወት ከፈጣሪ ጋር አንድ መሆን፣ ከፍጹሙ ጋር መግባባት ሲሆን ከቃላት በላይ፣ ከቋንቋ ገደብ ውጭ በማኅበራዊው የሕግ ወይም የባህል በጎነትና ነውር መመዘኛ የማይለካ ነው ይለንና ወደዚህ ደረጃ የደረሰ ሰው የእምነት ንጉሥ (The Knight of Faith) ይለዋል። አብርሃምን እንደ ምሳሌ ጠቅሶ ሲያስረዳም፣ የአብርሃም ይስሐቅን ለመሰዋዕትነት ማቅረብ ቅዱስ ተግባር የተባለው በሰው ሕግ መመዘኛ፣ አባት ለልጁ ከሚጠበቅበት የሞራል ኃላፊነት አንጻር ታይቶ ሳይሆን ከቋንቋ ገደብና ከሰው ሚዛን በላይ በሆነው በእምነት መነጽር ነው። ይህም የእምነት አያዎ (the paradox of faith) ነው – ወንጀሉን ወደ ጽድቅ መቀየር፤ አማኒውም ልዕለ ሰብ (Superman) ይባላል።

 ኢማኑኤል ካንትም እውነት እኮ በምክንያት ብቻ የሚደረስባት አይደለችም ወይም ንጹሕ ምክንያት ብቻዋን ፍጹም እውነትን ማግኘት አይቻላትምና ለእምነት ትንሽ ቦታ ማስቀመጡ አይከፋም ይለናል። እምነትን ከተግባራዊነትና ከሞራላዊ በጎነት ጋር በማያያዝ faith is practical reason (እምነት ምክንያትን በተግባር መኖር ነው) ወደሚል ትርጓሜ ይወስደዋል። ሐተታችንን ገደብ እናድርገውና ነገረ ሰውን በሚቀጥሉት ዓረፍተ ነገሮች ቋጭተነው ወደ ተግባቦት እንመለስ።

ሰው እንግዲህ የሥጋና የነፍስ ውሁድ ነው። ሥጋ ያው ሥጋ ነው ከአፈር፣ ከውሃ፣ ከእሳት፣ ከነፋስ የተሰራ በስባሽ ፈራሽ። ነፍስ ግን የጥንት የግሪክ ፈላስፎች አፍላጦንና (Plato) አሪስጣጣሊስ (Aristotle) እንዳሉት ከስሜት፣ ከምክንያት፣ ከመንፈስ የተሰራች ነች። ለግሪኮቹ ስሜት የልብላ ልጠጣ፣ ልዝናና፣ ልዘሙት አባዜ ነው፤ መንፈስ ደግሞ ልክበር ልኩራራ፣ ልንገሥ የሚያሰኘው ውቃቤ ነው፤ ምክንያት ደግሞ ልወቅ፣ ልጠበብ፣ ልራቀቅ የሚለው የሁለቱ አስታራቂ ሽማግሌ ነው። በርግጥ ስሜት የነፍስ ባህርይ ወይስ ከሥጋ ፍላጎት የሚመነጭ የሚለው ጉዳይ አከራካሪ ነው። ባጭሩ ግን ሰው የሦስቱ ስሜቶች መገለጫ ወይም የጦር ሜዳ ነው ማለት ይቻላል። የኛ አባቶችም ስለ ነፍስ በግእዝ ቃላት ከዚህ ጋር ተቀራራቢ (የተለየም ማለት ይቻላል) የሆነ ሐተታ አላቸው። ነፍስ ነባቢት፣ ልባዊትና ሕያዊት ናት (ተናጋሪ፣ አሳቢ ወይም ተገንዛቢ፣ ተመራማሪና ዘለዓለማዊት ናት) ማለታቸው ነው። ሰው እንግዲህ የስጋና የነፍስ ውሁድ ነው። የሕይወቱ ውስብስብ ውጥንቅጥም ከዚህ የምድራዊና የሰማያዊው (የቁሳዊና የመንፈሳዊ ዓለማት) አማካኝ ሕላዌው ይመነጫል። ግሪኮቹን ለጊዜው እንተዋቸውና ከተነሳንበት ርዕሰ ጉዳይ ጋር የኛዎቹ ልኂቃን ሐሳብ ስለሚቀራረብ ነፍስን ነባቢነቷ ለተግባቦት መንስኤ፣ ልባዊነቷ እውነትን ለመመርመር በር፣ ሕያዊነቷ ደግሞ ለሥነ-ምግባራዊ በጎነት መሠረትና ሰውን ወደ ሰውነት ክብሩ ከፍ ማድረጊያ መነሻ እንደሆነ በመሞገት እንቀጥል።

ከላይ “ምክንያታዊነትን ማንገሥ” የሚለውን ሐረግ ስሜትን መጫን እምነትን መደፍጠጥ ነውንዴ? የሚል ጠያቂ አንባቢ አይጠፋም። ያ ማለት አይደለም። ይልቁን ሰው የማሰብና የአስተውሎት ተፈጥሮአዊ ጸጋውን እስከ ጥግ ድረስ መጠቀም ወደ ሚችልበት ልዕልና ማድረስ ለማለት ነው። ሰው ስሜቱንም እምነቱንም ምክንያቱንም አስታርቆ መኖር አለበት። ሁሉም የየራሳቸው ፋይዳ ላቸውና። ይልቁን ስሜት ምክንያትን ተጭኖት ተጭኖት ወደ ሰብዓዊነት የሚደረገውን የግሉንም ሆነ የሌሎችን መንገድ እንዳይዘጋ ተግባቦትን እንዳያኮላሽ ሰከን ረጋ ብሎ ማሰብን፣ መመርመርን የሚያበረታታ ሐሳብ ነው።

 እንግዲህ ተግባቦት ከላይ ያየናቸውን የሰው ባሕርያት ወደ አንድነት ማምጣት ነው። ለጊዜው በሰዎች መካከል የሚደረግን ተግባቦት ብቻ ነው እየተመለከትን ያለነው። ግን እዚችጋ አንድ በር ገርበብ አድርገን እንለፍ። ጥርቅም አድርገን ሳንዘገው፣ ብርግድ አድርገንም ሳንከፍተው እንዲሁ ለመመለስ ወይም ለማፈትለክ እንዲያመቸን። ተግባቦች በሰዎች መካከል ብቻ ያልተገደበ እንደሆነ ከላይ ጠቃቅሰነዋል። ያገሬ ባላገር መልእክት ከተፈጥሮ ጋር የሚልዋወጥባቸው መንገዶች ሌላ የጥናትና ምርምር፣ የፍልስፍናዊ ዳሰሳና ሐተታ በር ከፋች ናቸው። አዳኝ ታዳኝን ፍለጋ በጫካ ውስጥ ሲንገዋለል፣ ሲሹለከለክ፣ ሲንከራተት አንዳች ደቃቃ ወፍ ድምጿን እያሰማች እሪ ትላለች፣ ወይም ባማረ ዜማ ትዘምራለች። ይሄኔ አዳኙ ወይም ሰይፉን ወደ ሰገባው መልሶ ይፈረጥጣል፣ አልያም እያደባ ይከተላታል። ወፍን ከሰው ጋር ምን አግባባቸው? የሆነ የነፍሳት ዘር ይውለከለካል ወይም የእጽዋት ዓይነት ያብባል፣ ይለመልማል ወይም ቅጠሉን ያረግፋል፣ ማጭዶሽ (የወፍ ዘር) ትልቅ ዛፍ ላይ ወይም ቁጥቋጦ ላይ አልያም ድንጋይ ላይ ሆኖ ይለፈልፋል፤ እነዚህ ሁሉ ለገበሬው ወይም ለከብት አርቢው ባላገር የመጭውን ክረምት መዘግየት ወይም መፍጠን፣ ጭራሹኑ መቅረት ወይም የዝናቡን ሙላት መጠን ይነግሩታል። ይቆዝማል ወይም በትፍስህትና በሙሉ ተስፋ ገበሬው ሰኔን በዘር ያሳልፋል። ለመሆኑ ባላገሩ ተፈጥሮን እንዲያነብ ያደረገው ከልምምድ የመጣ ነው ወይስ ተፈጥሮ ሹክ የምትልበትን ዘዴና ቋንቋዋን ተርድቶ? ፈረንጆቹ የሥነ ልቡና ባለሙያዎች Telepathy ይሉታል፣ ያገሬ ባለ አውሊያ ደግሞ ቀልብያዬ ሹክ አለኝ ይሉና በቦታና በጊዜ የተራራቁ አካላት ይናበባሉ። በውሻ ማላዘን፣ በጅብ እንጉርጉሮ ወይም በጉጉት ማጉተምተም፣ በእንቅፋት (ደቦ በተሰኘ ሥብስብ ሥራ ውስጥ፣ ተሾመ ገብረሥላሴ “በሕይወት መንገድ ላይ” በተሰኘ ማጣጥፍ፣ 2010፣ ገጽ 115)ወይም “በገደቢስ ጥቁር” እንስሳ አማካኝነት አንዳች ጥሩ ያልሆነ ዜና እንደሚነገር ያምናሉ። ብዙም ሳይዘገይ መርዶ ከተፍ ይላል ወይም ከቅርብ አንድ መዓት ይወርዳል። የውሻውና የጅቡ፣ የጉጉቷን ልቡና ማን መ ርምሮት ይሆን? የተጎለትን “ግዑዝና ዱዳ” ድንጋይ በእንቅፋት አማካኝነት መልዕክተኛ መሆኑን በምን ቋንቋ መተርጎም ቢቻል ነው? ይህንን ታሪኩን በምናነብለት ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ሕይወት ውስጥ ተስተዉሏል። የትልን መልዕክት ሲገነዘብ ወይም የአእዋፋትን ዜማ ሲያዳምጥ፣ ወይም በንጉሡ ሰይፍ አማካይነት የደረሰውን ሹክታ እንዴት ቢገነዘበው ነው የሕይወቱ ምኅዋር እንዲያ የተውሰበሰበው? ባለዛሩ ከ”እርኩስ መንፈስ” (እርኩስ መንፈስ ከሃይማኖት አንጻር እንጅ ጉዳዩ ከባህል፣ ከሥነ ልቡና ወይም በፍልስፍና እይታ አከራካሪ ነው) ጋር፣ ጻድቁን ከመላእክት ወይም ከፈጣሪ ዘንድ የሚያግባባቸው የለሆሳስ ልሳን መዝገበ ቃላቱ የት ይገኝ ይሆን? እነዚህን ጥያቄዎች በይደር በማቆየት በሌላ ርእሰ ጉዳይ ለመገናኘት ካበቃን ወይም ብልህ ተመራማሪ መነሻ አድርጓቸው የተሻለ ምርምር ይዞልን ከመጣ ለመጋበዝ ነው በሩ ገርበብ ያለው ቤት ውስጥ እንደዋዛ ሻጥ አድርገናቸው ማለፋችን።

ተግባቦት እንዲህ ሰፊ ነገር ነው። የሰዎች ለሰዎች ተግባቦትን ርእሰ ጉዳያችን እናድርግና እንቀጥል። የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ዓላማም ተበታትነው የሚገኙ የሚመስሉትን ሰዎች የቦታና የዘመንን ገደብ ሽሮ፣ የባህልና የታሪካዊ ዳራን ልዩነት ጭጋግ ገፍፎ፣ የፍላጎትና የጠባይ ታቃርኖዎችን አስታርቆ ወደ አንድነት ማምጣት ነው። ተቃርኖዎችን በማስወገድ የሰውን ልጅ ዲበአካላዊ (ተፈጥሮአዊ) ባሕርይ ሳይጋፋ ሰውን ከሰው ጋር ማግባባት ነው። ይህም ተግባቦት የሚጀምረው ከነባቢት ነፍስ ነው። በመነጋገር የሚደረግ መቀራረብ የመጀመሪያው ደረጃ ነው። እንግዲህ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ይህንን መነጋገር በመደጎም ረገድ ይኽ ቀረሽ የሚባል አይደለም። እንዲያውም እጅጉን ተራምዷል ማለት እንችላለን። መነጋገር በራሱ ግን የመጨረሻ ግብ አይደለም። የመገናኛ ብዙኃኑ ተጠቃሚ ግን እንዴት ነው የምንነጋገረው? የሚለውን ያሰበበት አይመስልም። የዘመናችን ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ተግባቦት ከነባቢት ነፍስ እውነተኛ ተፈጥሮ የመነጨ ነውን? ነፍስ ነባቢት ብቻ አይደለችምና ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ምን ዓይነት ነፍሶችን ነው እያነጋገረ ያለው? በምን ዓይነት መንገድና በምን ዓይነት ጉዳዮች ላይ ነው እያነጋገረስ ያለው? እነዚህን ጥያቄዎች እዚህ ላይ ለመመለስ መቸኮል የሐተታችንን ሙሉ መንፈስ እንዳይረብሸው በመስጋት አንባቢን ከራሱ ጋር እንዲወያይ፣ ቆም ብሎ ራሱ ብይን እንዲሰጥ እና ከጎኑ ካሉት ጋር እንዲነጋገርበት በመጋበዝ ለቀጣይ ቀጠሮ እንያዝ።

 ይቀጥላል!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top