ማስታወሻ

ዝክረ ደራሲ አሰፋ ገብረማርያም ተሰማ

ይህች በአብዛኛው የግል ትዝታዎቼን መሰረት አድርጌ የፃፍኳት ማስታወሻ ዋና ዓላማዋ በቅርቡ በሞት የተለየንን ጋሼ አሰፋ ገብረማርያም ተሰማ መዘከር ነው። ዜና እረፍቱን ከወዳጁ ከፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ከሰማሁበት ዕለት ጀምሮ ማስታወሻዎቼን፣ አንዳንድ ሥራዎቹን፣ በተለይም ግጥሞቹንና ኢሜሎቹን ለመመልከት ሞክሬያለሁ። ከአንድ አስር ዓመት በፊት ጋሼ አሰፋ ለኢትዮጵያው ሚሊኒየም ክብረ በዓል ከሚኖርበትና ‘እሳቱ ከተማ ወቁማሩ አውድማ’ ከሚለው የላስ ቬጋስ ከተማ ወደዋሺንግተን ዲሲ በመጣበት ጊዜም ቃለመጠይቅ አድርጌለት ነበር። ስለዚህ ያን መረጃም እንደአስፈላጊነቱ ተጠቅሜበታለሁ።

 ጋሼ አሰፋ የተወለደው በአዲሰ አበባ ከተማ መስፍነ ሐረር መንገድ ተብሎ ይጠራ በነበረው አካባቢ በቅዱስ ጊዮርጊስና በቅዱስ ዮሐንስ አብያተክርስቲያናት መካከል ሲሆን ዘመኑም መስከረም 16 ቀን 1928 ነው። ባላምባራስ እማኙ እውነቱ የተባሉ አገር ወዳድ በግቢያቸው ውስጥ ባቋቋሙት የቄስ ተማሪ ቤትም በየኔታ ፍቅረማርያም አማካይነት ፊደል ቆጥሮ ዳዊት ሊደግም በቅቷል። ከዚያ ራስ ደስታ ሆስፒታል አካባቢ በተከፈተው የስዊድን ሚሽንና በአርበኞች ትምህርት ቤትም ተመዝግቦ ተምሯል። ከ1944 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ገብቶ ለአምስት ዓመታት ትምህርቱን ተከታትሏል። ሲጨርስ እናቱን ለመርዳት በማሰብ በትምህርት ሚኒስቴር ዋናው መ/ቤት ተቀጥሮ መስራት ይጀምራል። ወደ እንግሊዝ አገር ሄዶ የከፍተኛ ትምህርቱን ለመማር በሚያስብበት ወቅት ደግሞ በኢትዮጵያና በሶቪዬት ኅብረት መካከል የባህል ስምምነት ይፈረማል። ይህንኑም ተከትሎ የአማርኛ ቋንቋን ለማስተማር በ1953 -ከታህሳሱ ግርግር ማግስት- ወደ ሌኒንግራድ ያቀናል። ለስድስት ዓመታትም ያህል ቀን ቀን እያስተማረና ማታ ማታ እየተማረ ይቆያል። የደርግ መንግስት ስልጣን ከያዘ በኋላ በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ የነበረው የሥነጥበብ መምሪያ አዲስ ወደተቋቋመው የባህል ሚኒስቴር ሲዛወር የመምሪያው ሃላፊ ሆኖ ይመደባል። በአጠቃላይ ለ36 ዓመታት ያህል አገሩን በተለያየ የስራ ሃላፊነት አገልግሏል። ጋሼ አሰፋ የሶስት ሴቶች፣ የአንድ ወንድና የስድስት የልጅ ልጆች አባት ሲሆን ላለፉት ሃያ ዓመታትም አብዛኞቹ ልጆቹና የልጅ ልጆቹ በሚገኙበት በሃገረ አሜሪካ ኖሯል። አንደኛዋ ልጁ በስዊድን ትኖራለች።

 ከጋሼ አሰፋ ጋር የተዋወቅኩት በ1979 ዓ.ም. ነው። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመርቄ በባህል ሚኒስቴሩ የሥነጥበባትና ቴያትር መምሪያ በተመደብኩበት ዓመት ማለት ነው። እሱ ያኔ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዳሚ ዋና ፀሐፊ ነበር። ታዲያ አንዱን ቀን የአካዳሚውን ቢሮዎች አቋርጬ ወደ ወመዘክር ሳልፍ ከመምህሬ ከአብዬ መንግስቱ ለማ ጋር ሆነው ከፊት ለፊቴ ሲመጡ ተገናኘን። አቶ መንግስቱ የአካዳሚው ጉባኤ ምክትል ሊቀመንበር ነበሩ። በተለይ ያን ወቅት የግዕዝ ቅኔያት የተባለውን ታላቅ ስራ ለማሳተም ከአከካዳሚው ባልደረቦች ጋር ደፋ ቀና የሚሉበት ጊዜ ነበር። ከሁለቱም ጋር የእጅ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ “አቶ አሰፋን ታውቀዋለህ?” አሉኝ አብዬ መንግስቱ። ሆኖም መልስ ከመስጠቴ በፊት ጋሼ አሰፋ “አሰፋ!” አለና እጁን እንደገና ለሰላምታ

“በአንድ ወቅት በአብርሃ ደቦጭና በሞገስ አስገዶም አማካይነት በግራዚያኒ ላይ በተሞከረው የመግደል ሙከራ ላይ የተመሰረተ አንድ ቴያትር በብሔራዊ ቴያትር ተዘጋጅቶ ነበር። ጋሼ አሰፋ ይህ ስራ ከክብርት ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ “የልቤ መጽሐፍ” ላይ የተወሰደ ነው ብሎ በማመኑ መጽሐፉን በፎቶ ኮፒ እያባዛ ከፃፈው ትችት ጋር ለሚመለከታቸው ሁሉ ያሰራጭ እንደነበርም አስታውሳለሁ። እኔም አንድ ቅጂ ደርሶኝ ነበር።”

ዘረጋልኝ። አፀፋውን መለስኩ። “ደቀ መዝሙሬ ነው በደንብ እወቀው” አሉትና ተለያየን።

 በማግስቱ ይሁን በሳልስቱ ጋሼ አሰፋን መንገድ ላይ ሳገኘው አስታወሰኝና “ሰሞኑን ከተመቸህ አንድ አፍታ ቢሮዬ ብቅ በል” አለኝ። እሺ አልኩና ያንኑ ዕለት ሄድኩ። የግጥም መድበሎቹን “የመስከረም ጮራ”ን እና “The Voice” እንዲሁም አንድ ሁለት የአካዳሚውን የህትመት ውጤቶች ፈረመና ሰጠኝ። አያይዞም “ወጋየሁ ንጋቱና ሙያው” የተሰኘ መጽሔት እያዘጋጀ መሆኑን ጠቁሞኝ በረዳት አዘጋጅነት አብሬው እንድሰራ ጠየቀኝ። የመጽሔቱ ዓላማም የከያኒውን ሥራና ሕይወት ለመዘከርና ለመታከሚያ የሚሆነውን ገንዘብ ከሺያጩ ለማሰባሰብ እንደሆነ ገለፀልኝ። ኃላፊነቱን በደስታ ተቀበልኩ። ሌላው ረዳት አዘጋጅ የምወደውና የማከብረው ሠዓሊ እሸቱ ጥሩነህ እንደሆነ ነገረኝ። በእውነቱ መጽሔቱ ግሩም ሆኖ ተዘጋጀ። የብዙ ምሁራንና ታዋቂ ሰዎችን ሥራዎች ይዞም ወጣ። ከዓላማዎቹ ያሳካነው ግን አንዱን ብቻ ነበር። ምክንያቱም የመጽሔቱ ህትመት ከመጠናቀቁ በፊት ታላቁ ከያኒ ወጋየሁ ንጋቱ አረፈ። እርግጥ ነው ጽሑፎቹን በሙሉ አንብቧቸዋል። ወዷቸዋልም። እንግዲህ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ከጋሼ አሰፋ ጋር ይበልጥ ተቀራረብን። ወዳጅነታችን በአሜሪካም አልተቋረጠም። እንደውም እዚያማ ታይፒስቱ – በእግረ መንገድም ምስጢረኛው- አደረገኝ ማለት እችላለሁ።

 ጋሼ አሰፋ የሃገር ባለውለታዎችን ወይንም የወዳጆቹን ለምሳሌ የፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስን፣ የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትን፣ የልጅ ሚካኤል እምሩን፣ የከያኒ ጥላሁን ገሠሠን፣ ዜና እረፍት ሲሰማ በግጥም ይዘክራቸዋል። በእጁ የፃፈውን ግጥም ይልክልኝና በኮምፒውተር ጽፌ እመልስለታለሁ። ወዳጁ ደራሲ አምኃ አስፋውም የኮምፒውተር ባለሙያም ስለሆነ ብዙ ሥራዎቹን አሳምሮ ጽፎለታል፣ አቀናብሮለታል። ሌላ ጊዜ ደግሞ “ውድ የኢንተርኔት ማህበርተኞቼና ወዳጅ ዘመዶቼ” ለሚላቸው ወገኖቹ ሃሳቡንና ምስክርነቱን በኢሜል ያካፍላቸዋል። እነሆ ግንቦት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ያሰራጨውን መልዕክት እንደ አንድ ምሳሌ ላቅርብላችሁ።

ሰላም ውድ የኢንተርኔት ማህበርተኞቼና ወዳጅ ዘመዶቼ፤ በዚህ ሰሞን መቼም ውድ አገራችን ኢትዮጵያ አዛውንትና ጎልማሳ ልጆቿን በተከታታይ ማጣቷን በሃዘን እናስታውሳለን። ከነዚህም አንዱ ባለፈው አንድ አስር ቀን ውስጥ የቀብር ስነስርአቱ በካሊፎርኒያ ኦክላንድ አጠገብ በሚገኝ ከተማ መፈፀሙን ከወዳጄ ከእውቁ ጋዜጠኛ ከአቶ ተክሉ ታቦር የተረዳሁት የክፉ ቀን ወዳጄ አቶ መስፍን ፋንታ ነው። አቶ መስፍን ፋንታ [በአሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ] የብዙ አመት ጎረቤቴ ሲሆን፤ በልዩ ልዩ የመንግስት ስራ በሃላፊነት ያገለገለ የህግ ምሁር፤ በመጨረሻም በጤና ጥበቃ ምክትል ሚኒስትር የነበረ ባለትዳርና የአራት ወንዶችና የሁለት ሴቶች ልጆች አባት ነበር። አባቱ ባልሳሳት ፊታውራሪ ፋንታ የራስ መኮንን ባለሟል … እንደነበሩና አቶ መስፍንም እዚያው መወለዱን እንዳጫወተኝ ትዝ ይለኛል። አቶ   መስፍን ከሰው ጋር ተግባቢ፣ ለሰው ችግር ደራሽ፣ ለሃገሩና ለወገኑ ተቆርቋሪ፣ ታሪክ አዋቂ፣ የእነልኡል ራስ እምሩ ቤተሰብ፣ የእነአቶ መንግስቱ ለማና ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የቅርብ ወዳጅ ነበር። … ወዳጄ አቶ መስፍን ፋንታ ያረፈው በተወለደ በ89 አመቱ ነው አፈር ይቅለለውና! ለባለቤቱ ለወ/ሮ ብርሃኔና ለውድ ልጆቹ፤ ለቤተሰቦቹና ለቅርብ ወዳጆቹ ሁሉ በአበው መልካም ዘይቤ ፈጣሪ ፅናቱንና ብርታቱን ይስጣቸው! ነፍስ ይማር! ደግ ደጉን፤ ቸር ወሬ ያሰማን።

አሰፋ ገብረማርያም ተሰማ

ይህን ባህሪውን የተመለከቱት ወዳጁ ኮማንደር አሰፋ ሰይፉ ታዲያ በአንድ ወቅት “ከምንተዋወቅበት ከልጅነት/ወጣትነት ዘመናችን ጀምሮ ሁሌም ቅን አሳቢነትህን፣ ስለምታውቃቸው ኹሉ የምትሰጠው አስተያየት ለጋስነት የተሞላበት…” ነው በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። የሰዎችን በጎ ተግባር ከመዘከር ጎን ለጎን የሚጎረብጠው ነገር ካለም በእግረ መንገድም ቢሆን ጠቆም ማድረጉ አይቀርም። ጋሼ አሰፋ “ሙት ወቃሽነትን” እምብዛም የሚፈራ ሰው አልነበረም።

 ውድ የልጅነት ጓደኛዬ ፍቅሩ ኪዳኔ፤ በየጊዜው ሳታሰልስ የምትመይልልኝ ቁምነገር አዘል ዜናና መጣጥፍ ሁሉ ይደርሰኛል፤ ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው ውድ ፍቅሩ! እኔም በበኩሌ ለብዙ የኢንተርኔት ማህበርተኞቼ እንደዚሁም ለበርካታ ወዳጅ ዘመዶቼ በግል አካፍላለሁ፤ እመራለሁ! ዛሬ የላክህልኝንም እንደዚሁ አደርጋለሁ! … ነፍሳቸውን ይማረውና ክቡር አቶ …ን የማውቃቸው ገና በልጅነቴ አርበኞች ት/ቤት ስማር ነው፤ በዚያን ጊዜ በነፃ ይኖሩበት የነበረው የመንግስት ቤት ተወልጄ ያደኩበት ሰፈር … አጠገብ ነበር! በወቅቱ የደረሷት በግእዝ ፊደል የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማስተማሪያ ትንሿ የ’ጅ መፅሃቸውም ትዝ ትዝ ትለኛለች … ባንደኛዋ ልጃቸው በኩል ከጃንሆይ ጋራ ጋብቻሞች እንደነበሩም አውቃለሁ፤ ምንም እንኳ ነፍሳቸውን ይማረውና “ጥቃትና በደል” እንደደረሰባቸው በህይወት ታሪካቸው መፅሃፍ ውስጥ በሰፊው ቢያማርሩም! ከመፅሃፋቸው ውስጥ በበኩሌ የወደድኩላቸው የኢትዮጵያ መሬት ለባእድ ተቆርጦ ቢሸጥ ወይም በኮንትራት ቢሰጥ የሚያስከትለውን ጠንቅ ጃንሆይን እያሳመኑ የፃፉትንና የተከላከሉትን ክፍል ነው። (አጽንኦት የኔ፣ የክቡርነታቸውን ስምና አድራሻ ያወጣሁትም እኔው ነኝ።) ጋሼ አሰፋ ስሜቱን የሚነካ በጎ ነገር ሲያጋጥመውም እንዲሁ ነው። ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በተመረጠ ጊዜ “ብሩኩ ኦባማ” የተሰኘ ግጥም መፃፉን አስታውሳለሁ።

በሆነ ነገር ሲከፋ ወይ ቅር ሲሰኝ ደግሞ የዘወትር ልማዱ “የታሪክ ማስታወሻ” በመፃፍ መተንፈስ ነው። ለዚህም አንድ ምሳሌ ልስጥ።

 በ1981 ወይም በ1982 ዓ.ም. የኤች አይ ቪ ኤድስን መስፋፋት ለመቆጣጠርና የህዝቡን ግንዛቤ ለማዳበር ያለመ የተውኔት፣ የስነግጥምና የአጭር ልብወለድ ውድድር በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ ነበር። የገምጋሚ ኮሚቴው አባል ሆኜ ተመድቤያለሁ። እስከማስታውሰው ድረስ፣ የውድድሩ ዐበይት ዓላማዎች፣ 1ኛ/ የበሽታውን መተላለፊያ መንገዶች በመጠቆም ህዝቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግና የባህሪይ ለውጥ እንዲያሳይ ማሳሰብ እና 2ኛ/ በበሽታው የተያዙ ወገኖችን ከማግለል ይልቅ ማቅረብ፣ ፍቅር ማሳየትና መንከባከብ እንደሚገባ መምከር የሚሉት ነበሩ። ሥራዎቹ ሁሉ የምስጢር ቁጥር የተሰጣቸው ስለሆኑ የቱ የማን እንደሆነ እኛ አናውቅም። የተውኔቱን ውድድር “እውነተኛዋ ቅፅበት” የተሰኘው፣ ኋላ እንደተረዳነው የጌትነት እንዬው ድርሰት ሲያሸንፍ፣ በግጥም ዘርፍ ሁለት ሥራዎች ነጥቀው የወጡ ሲሆን በመልዕክት ደረጃ የመጀመሪያው ከሁለቱ አንደኛውን ግሩም አድርጎ ገልጾታል፣ ሌላኛው ደግሞ ሁለተኛውን በጥሩ ሁኔታ አቅርቦታል። ስለዚህ ሁለቱን ግጥሞች እንደ አሸናፊ ወስደን ግን ደግሞ ተዋህደውና አንድ ግጥም ሆነው ቢቀርቡ ውጤታማ ይሆናሉ የሚል ሃሳብ ተነሳና ኮሚቴው አመነበት። እናም በአወዳዳሪው ክፍል አማካይነት ውሳኔው ለገጣሚዎቹ ተገልጾ ስምምነታቸው እንዲጠየቅ አሳሰብን። በአጋጣሚ ከሁለቱ ገጣሚዎች አንዱ ጋሼ አሰፋ ነበር። ስለዚህ “የታሪክ ማስታወሻ”ውን ፃፈና (ቁጥር ስንት እንደነበር ዘነጋሁት) ደህና አድርጎ ቀለደብን። ትዝ እንደሚለኝ “በቀዶ ጥገና ግጥም አይወለድም” የሚል አይነት ይዘት ነበረው። ከዓመታት በኋላ ዋሺንግተን ስንገናኝ ባነሳበት፣ “ያ ሁሉ ነገር ከመሠረታዊ እምነቴ የሚመነጭ ነው” አለኝ።

 በነገራችን ላይ ጋሼ አሰፋ በተለይ ሃገራዊ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚፅፋቸውን “የታሪክ ማስታወሻ”ዎች ለኮ/ል መንግስቱ ኃ/ ማርያምና በዙሪያቸው ለነበሩት ባለስልጣናት ሁሉ ይልክ እንደነበር አስታውሳለሁ። እንደውም አንዳንዶቹን በስም እየጠራ “እሱ እንኳ የሚረባ ሰው አይደለም፣ ብቻ ተነጥሎ ሲቀር ቅር እንዳይለው ይሂድለት” እያለ ብዙ ሰው ባለበት ሁሉ ይቀልድባቸውም ነበር።

 በአንድ ወቅት በአብርሃ ደቦጭና በሞገስ አስገዶም አማካይነት በግራዚያኒ ላይ በተሞከረው የመግደል ሙከራ ላይ የተመሰረተ አንድ ቴያትር በብሔራዊ ቴያትር ተዘጋጅቶ ነበር። ጋሼ አሰፋ ይህ ስራ ከክብርት ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ “የልቤ መጽሐፍ” ላይ የተወሰደ ነው ብሎ በማመኑ መጽሐፉን በፎቶ ኮፒ እያባዛ ከፃፈው ትችት ጋር ለሚመለከታቸው ሁሉ ያሰራጭ እንደነበርም አስታውሳለሁ። እኔም አንድ ቅጂ ደርሶኝ ነበር።

 አሁን ደግሞ ወደ አንድ ትውስታዬ ልውሰዳችሁ። ጋሼ አሰፋ “በመኖሪያ ቤቴ ውስጥ አንድ ዝግጅት ስላለኝ ብትመጣ ደስ ይለኛል” አለና የጥሪ ወረቀቱን ሰጠኝ። ሳነበው የሚቀልድ ነበር የመሰለኝ። ርዕሱ “የቡና ግብዣ – ያውም የግንቦት!” ይላል። ዝርዝሩ ደግሞ የማስታውሰውን ያህል ይህን ይመስላል። “ለእከሌ” ከሚለው በታች “ግንቦት … ቀን … ዓ.ም. በ … ሰዓት፣ ዮሐንስ ቤተክርስቲያን አካባቢ በሚገኘውና The old bachelor በምኖርበት በደጓ፣ በድሃ ኩሩዋ፣ በጅሩዬዋ፣ በውዷ እናቴ መኖሪያ ቤት ውስጥ በማደርገው የቡና ግብዣ እንዲገኙ በአክብሮት ተጋብዘዋል። በዕለቱም ከጨዋታ በተጨማሪ የቁርሳ ቁርስና የመጠጣ መጠጥ መስተንግዶ ይኖራል” ይላል፣ አድራሻውንም ይገልፃል። የግብዣው ዕለት በቦታው ስደርስ ታዋቂው ድምፃዊና የመሰንቆ ተጫዋች ደርባባው አቡኑ ከቮክስ ዋገን መኪናው ሲወርድ አገኘሁት። መሰንቆውን በልኩ የተሰፋለትን ልብስ አልብሶ እንደቦርሳ አንግቶታል። ሺክ ብሎ ለብሷል። እሱን ተከትዬ ወደግቢው ስገባ ግን አይኖቼን ማመን አልቻልኩም። የባህል ሚኒስትራችን ሻለቃ ግርማ ይልማ፣ የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ያየህራድ ቅጣው፣ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌና አርቲስት አያሌው መስፍን ከጋሼ አሰፋ ጋር ውጪ ቆመው፣ የሚጠጣ ነገር እንደየምርጫቸው ይዘው ይጫወታሉ። አንጋፋው ከያኒ ዓለማየሁ ፋንታ በአንድ ጥግ ተቀምጠው በገናቸውን ይቃኛሉ። አሁንም ከያኒ ደርባባውን ተከትዬ ከእንግዶቹ ጋር ተጨባበጥኩ። ወዲያው ጋሼ አሰፋ ወደውስጥ ወሰደንና ከእህል ውኃ ጋር አገናኘን። ከዚያ የምንጠጣውን ነገር ይዘን ውጪ ካሉት እንግዶች ጋር ተቀላቀልን። ከዚያ ከያኒ ዓለማየሁ ፋንታ በበገና ጨዋታ መንፈሳችንን አደሱት። ካልተሳሳትኩ አርቲስት አያሌው መስፍንም አንድ ሁለት ዜማዎቹን በኪቦርድ ተጫውቷል። በደንብ የማስታውሰው ቀጥሎ የምነግራችሁን ነው። ከያኒ ደርባባው መሰንቆውን አወጣና መጫወት ጀመረ። ፊት እንደተለመደው መዲናና ዘለሰኛ፣ ለጥቆ ከተወዳጅ ሥራዎቹ አንዱን አካል ገላን ተጫወተ። ከዚያ ወዲያ ግን ያለምንም ስጋት ግለሰቦችን እያወዳደሰ ሽልማቱን መሰብሰብ ያዘ። ትዝ እንደሚለኝ የጀመረው በሻለቃ ግርማ ነበር። ያው ከስማቸውና ከሚመሩት ተቋም ጋር አያይዞ ግርማ ሞገስህ፣ ባህል ጠባቂነትህ፣ ወግ አዋቂነትህ፣ እንዲህ እያለ በዙሪያቸው ሲሽከረከር ጋሼ አሰፋ ፈጠን አለና የገንዘብ ቦርሳውን ከፍቶ “ጓድ ግርማ፣ ካልሸለምከው አይለቅህም፣ አልያዝክ እንደሆን ላበድርህ”፣ ብሎ የሃምሳ ብር ኖት አወጣና ሰጣቸው። እሳቸውም ተቀብለው ሸለሙት። ምስጋናውን በዚያው በዜማው ካቀረበ በኋላ ደግሞ ወደ ዶ/ር ያየህራድ ዞረ። አንድ ሁለት ዙር ግጥሞቹን በዜማ ከተጫወተ በኋላ የጠበቀውን ምላሽ ባለማግኘቱ ከራሰ በራነት ጋር ወደተያያዘ ቀልድ አምርቶ ነበር። እንደው ከድፍረት አይቆጠርብኝና ሙሉውን ምስል ለመስጠት ስል ብቻ ግጥሟን ላካፍላችሁ።

“እወዳለሁ አለች፣ ‘ወዳለሁ መላጣ

ልጅ እየመሰላት ጠጉር ያላወጣ”

ደግነቱ ጋሼ አሰፋ በተለመደ ፍጥነቱ ደርሶ ያንኑ የሃምሳ ብር ኖት ብድር አቀረበና ገላገለን። ቀጣዩ የደርባባው ጉዞ ወደ ታላቁ ሠዓሊ ነበር። አንደኛው ግጥም፣ ቃል በቃል ባላስታውሰውም እንኳ፣ መንፈሱ፡-

 አፈ ወርቅ ያሉህ፣ አባትህ ተሳስተው ወርቁ እጅህ ላይ እንደሁ፣ እሳቸው መች አይተው የሚል አይነት ነበር።

‘እያዳመጥኩህ ነው’ በሚል አይነት ራሳቸውን እየነቀነቁ ሲመለከቱት ጊዜ ተበረታታ መሰል ሥራቸውን፣ ዓለም አቀፍ ታዋቂነታቸውን፣ ወዘተ. እያነሳሳ ሰፋ አድርጎ ተጫወተ። እሳቸውም አንድ ሁለት ግጥም የሰጡት ይመስለኛል። በመጨረሻ የጋሼ አሰፋን ብድርም ሳይጠብቁ የመቶ ብር ኖት አወጡና ሸለሙት። ከዚያ ቀጥሎ ጋሼ አሰፋ “ባሌት” የተሰኘችውን፣ በ1961 ዓ.ም. ሌኒንግራድ ውስጥ የፃፋትን ግጥም አነበበልንና “እንግዲህ ወፍ እንዳገሯ ትበራለች ይባላልና እስቲ አንዴ ፅዋችንን እናንሳ” ብሎ እሱ ከቮድካው ሌሎቻችንም ከየምርጫችን ተጎነጨን። በነገራችን ላይ ግጥሟ ውስጥ የሚከተሉትን ስንኞች እናገኛለን።

የውብ ውብ ጨዋታ፣ በሙዚቃ ድምፅ

 አፍ ሳይላወስ፣ ስሜት የሚገልፅ

ባሌት የተባለ፣ የውቦች ጨዋታ

 ረቂቅ ጥበብ ነው፣ የመንፈስ ደስታ!

 ውበት ለተጠማ፣ ለቅኔ ዘራፊ

 ጥበብ ላሰከረው፣ ለስዕል ነዳፊ

 ሙዚቃ ላጠነው፣ ለኖታ ጠቢብ

 ባሌት ወለላ ነው፣ የመንፈስ ምግብ!

ለተመልካች ሁሉ፣ ውበት ለሚያደንቅ

ባሌት ነው ገነቱ፣ መንፈስ የሚያፀድቅ!

አንዳንዴ ደግሞ ጋሼ አሰፋ ድፍረቱና የሚሰራው ስራ ያስገርመኛል። ለምሳሌ በ1968 ዓ.ም. የዓለማቀፍ የሠራተኞች ቀን (ሜይ ዴይ) በአዲስ አበባ አብዮት (ዛሬ መስቀል) አደባባይ ሲከበር አስር ያህል መፈክሮችን ደብቆ አስገብቶ በደርጎቹ ፊት እያሳየ አልፏል። በወቅቱ በኮሎኔል (ኋላ ጄኔራል) መርዕድ ንጉሴ ሰብሳቢነት የሚመራ የሰልፍ ዝግጅት አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል መሆኑን ተጠቅሞ ነው ይህን ያደረገው። ከነዚሁ መፈክሮችም መካከል 1. “የጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት የስልጣን ዘመን ይወሰን” 2. “የመፃፍና የመናገር መብት ይከበር”፣ 3. “የብዙሃን ፓርቲዎች ይቋቋሙ”፣ 4. “የታሰሩት የስነጥበብ ባለሙያዎች ይፈቱ” የሚሉት ይገኙባቸዋል። በማግስቱም ከባህል ሚኒስቴር የሥነጥበባትና ቴያትር መምሪያ ሃላፊነቱ በራሱ ፈቃድ ይለቃል። እስከ 1972 ዓ.ም. ድረስም በመምህርነት ሲያገለግል ይቆያል።

 ሌላው ላነሳ የምፈልገው ነገር ጋሼ አሰፋ በራሱም ጭምር ለመቀለድ ወደኋላ የማይል ሰው የነበረ መሆኑን ነው። ለዚህም አንድ ምሳሌ ላቅርብ። በ1974 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የባህል ማዕከል ደራሲ በዓሉ ግርማ ተጋብዞ ሄዶ ነበር። እና በዶ/ር ፈቃደ አዘዘ በተመራው የውይይት መድረክ ጋሼ አሰፋ ስላቀረበው ጥያቄና ስለተሰጠው መልስ ከሰዎች የሰማሁትን ከራሱ አንደበት ለማረጋገጥ ፈልጌ ብጠይቀው ከት ከት ብሎ ሳቀ። በግማሽ ልብ አብሬው ልስቅ እየሞከርኩ “አይ፣ ካልፈለግክ ሊቀር ይችላል” አልኩት ተንኮል ነገር ያሰብኩ እንዳይመስለው ሰግቼ። እሱ ግን በዚያው የሳቅ መንፈስ ውስጥ እንደሆነ ታሪኩን አጫወተኝ። የማስታውሰውን ያህል ነገሩ ይህን ይመስላል። “ደራሲ በዓሉ! ብዙውን ጊዜ በአጠገብህ ያሉ ሰዎችን በድርሰትህ ውስጥ ገፀባህሪይ እያደረግክ ትቀርፃቸዋለህ ይባላል። ከነመልካቸው ከነባህሪያቸው። በዚህም ምክንያት ባንተ ልብወለዶች ውስጥ እከሌ የተባለው ገፀባህሪይ እኮ እከሌ ነው ማለት የተለመደ ነው። እና ለምን ይሆን?” ሲል ጋሼ አሰፋ ይጠይቃል። ደራሲ በዓሉም “መቼም ቢሆን አንድ ደራሲ ስራውን የሚቀዳው ከሕይወት ነው። እኔም ከዚያ የተለየ ነገር የሰራሁ አይመስለኝም። የሆነ ሆኖ እንዲህ አይነት ነገሮችን ከዚህ ቀደምም ሰምቻለሁ። አሁን ለምሳሌ አንድ ወፈር ያለ፣ ጠጉሩ ከአናቱ ገባ ያለ፣ ድምፁ ሰለል ያለ ገፀባህሪይ ብስል አቶ አሰፋ ገብረማርያምን ነው የሳለው ይሉኛል፣ እንግዲህ እኔ ምን ላድርግ?” አለና ታዳሚውን ሁሉ አሳቀው፣ ጋሼ አሰፋን ጨምሮ። ከሃያ ምናምን ዓመታት በፊት የሆነውን ይህንን ታሪክ ነግሮኝ ሲጨርስ እንኳ ጋሼ አሰፋ እንባውን በመሃረቡ እየጠረገ ነበር።

ወደፈጠራ ሥራዎቹ ስንመጣ፣ ከዊልያም ሼክስፒር የተረጎመውና በ1949 ዓ.ም. ያሳተመው “ጁልዬስ ቄሳር” ተውኔት እንዳይሰራጭ ታግዶበታል። እንደሚታወቀው በዚህ ተውኔት ብሩተስ የተባለው የጁልዬስ ቄሳር ታማኝ ወዳጅ ቄሳርን ለማስገደል ከሌሎች ጋር ያሴራል። ይህ ብቻ አይደለም፣ ከበስተጀርባውም ይወጋዋል። ቄሳር ይህን ባዬ ጊዜ፣ በተስፋ መቁረጥ መንፈስ “ብሩተስ! አንተም?” ብሎ መከላከሉን ያቆማል። ሃያ ሶስት ጊዜ ተወግቶም ሕይወቱ ያልፋል። ሌሎቹ በጥላቻና በቅናት እንዲሁም ለጥቅም ሲሉ ሲረባረቡበት፤ ብሩተስ ግን ቄሳርን ከራሱ ባላነሰ ሁኔታ እንደሚወደው ሆኖም ፍቅሩ ከሮም ስላልበለጠበትና አምባገነንነቱን በመጥላት ለሃገሩ ሲል ሊገድለው መነሳቱን ይናገራል። አፄ ኃይለሥላሴ ተውኔቱን አልወደዱትም። “ይኼ ምን ትምህርት ለመስጠት ነው? እንዴትስ አንድ አገልጋይ የሃገር መሪ ይገድላል? ባይሆን ቄሳር ብሩተስን ይግደለው” ብለው ነበር ይባላል። የሆነ ሆኖ ተውኔቱ በየትኛውም መድረክ ለመቅረብ ሳይታደል ቀርቷል። ከኒኮላይ ጎጎል የተረጎመው “ዋናው ተቆጣጣሪ” ተውኔት በስብሃት ተሰማ አዘጋጅነት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴያትር ግሩም ሆኖ ተመድርኳል። በመንደርደሪያዬ የጠቀስኳቸው የግጥም ስራዎቹ “የመስከረም ጮራ” እና “The Voice”ም ለህትመት በቅተዋል። “ለንደን – አዲሳባ” የተሰኘ የቴያትር ድርሰት የጻፈም ቢሆን በመድረክ መቅረብ አለመቅረቡን ለማረጋገጥ አልቻልኩም። ከዚህ ሌላ የሚታወቅበት ከአሁኑ በፊት የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር ግጥም ደራሲ መሆኑ ነው። ሰንደቅ ዓላማ ሲወጣና ሲወርድ ለሚዘመረው መዝሙር ውድድር የፃፋቸው ግጥሞችም አሉት። በስራ ላይ ግን አልዋሉም። የሚከተሉት ስንኞች ለጠዋቱ የሰንደቅ ዓላማ ማውጫ ካዘጋጃቸው የተወሰዱ ናቸው።

ያገራችን ውበት፣ የወንዝ የተራራ

የተስፋችን ብርሃን፣ የማለዳ ጮራ

 የታሪክ ቅርሳችን፣ የደም ያጥንታችን

ትውለብለብ ዘላለም፣ ሰንደቅ አላማችን!

ለ32ኛው የኢትዮጵያውያን ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ (ESFNA) ዓመታዊ ክብረ በዓል “ዘመናዊ መወድስ ዘ’ግር ኳስ” በተሰኘ ርዕስ ከጻፈው ግጥም ደግሞ፣

 አለ በያገሩ ብዙ አይነት ጨዋታ

ዋና፣ የቅርጫት ኳስ፣ ዝላይና ሩጫ!

 ግን ማን እንደ’ግር ኳስ ተወዳጅ ጨዋታ

 ስሜት የሚማርክ፣ የሚሰጥ እርካታ?! …

 ምንድነው ምታትሽ? አፍዝ አደንግዝሽ?

 ምንድነው ምስጢርሽ? ምንድነው አብዶሽ? …

 የ’ነይድነቃቸው ቀለም፣ የ’ነመንግስቱ ፊርማ

 የ’ነለውጤ ጥበብ፣ የ’ነነፀረ አርማ

 የ’ነአየለ ጅቦ፣ የ’ነፀጋዬ አብዶ አሻራ

 የ’ነድሬ ቴርሲኖ፣ የ’ነ አመለወርቅ ቴስታ

የታተመብሽቱ፣ ውዲቷ የ’ግር ኳስ ጨዋታ

 ውብ ድንቅ ነሽ’ኮ፣ ለአካል ለመንፈስ ግንባታ!

የሚሉት ስንኞች ይገኙበታል። ከስሩም “የገጣሚው ትዝታ በድሮው በ”ካምቦሎጆ” የ’ግር ኳስ ቡድን በተለይም በጊዮርጊስ ላይ ያተኮረ መሆኑን ልብ ይሏል። … መልካም የኳስ ጨዋታና ትዝታ” የሚል ማስታወሻ ጽፎበታል።

 ሌላው ጋሼ አሰፋ የሚታወቅበት ጉዳይ ደግሞ የሃገር ባለውለታዎችን የመዘከርና በሕይወት ያሉትን የማመስገንና እውቅና የመስጠት ልማዱ ነው። ሰዎችን እያስተባበረና ከባዱን ሸክም እሱ ራሱ እየወሰደ፣ እኒህን መሰል ፕሮግራሞች ብዙ ጊዜ አዘጋጅቷል። ለምሳሌም ያህል በአሜሪካ ነዋሪ ከሆነ ወዲያ የአቶ ሀዲስ ዓለማየሁን 100ኛ ዓመት የልደት በዓል፣ የፕሮፌሰር አስራት ወልደዬሰን 80ኛ ዓመት የልደት በዓል፣ በሕይወት ላሉት ታላቅ ኢትዮጵያዊ የቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ምሁር ለፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ደግሞ የምስጋናና የእውቅና በዓል እንዲዘጋጅላቸው ጉልህ አስተዋ ጽዎ አድርጓል።

 በመጨረሻ ላነሳ የምወደው ጋሼ አሰፋ የሕይወት ታሪኩንና ትዝታዎቹን እየጻፈ እንደነበር ደጋግሞ አጫውቶኛል። ወደማገባደዱ ገደማ ሳይሆን እንደማይቀርም እገምታለሁ። ስለሆነም ልጆቹ፣ የእኛ የወዳጆቹ ትብብርና ድጋፍም ታክሎበት፣ ለህትመት ያበቁለታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top