ከቀንዱም ከሸሆናውም

ዘፍጥረት፣ አፈታሪኩ እና ውዳሴው

በዚህ ጽሁፍ ስለ ዓለም አፈጣጠር እና ስለ አፈ-ታሪኩ ብዙ ለመግለጽ አልሞክርም፡፡ ለመግቢያ የሚሆኑትን ጥቂት አንቀጾች የተጠቀምኩባቸው በጥንታዊው የህንድ ፍልስፍና ስለ ዓለም መፈጠር የሚገልጽ አንድን ጥልቅ ሥነ-ግጥም ለማስተዋወቅ ነው፡፡

በማናቸውም ማህበረ-ሰብ ውስጥ ስለ ዓለም አፈጣጠር የሆነ አፈ-ታሪክ አለ፡፡ ማህበረ-ሰቡ ስለ ራሱ ያለው አረዳድ እና ስለ ራሱ የሚሰጠው ትርጉም፣ እንዲሁም በዚህ ዓለም ስላለው የህይወት ድርሻ ከአፈ-ታሪኩ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው፡፡ ይህን አመለካከት ማህበረሰቡ ለዘፍጥረት በሚዘምራቸው መዝሙሮች እና በሚያቀርባቸው ውዳሴዎች ውስጥ በቀላሉ መመልከት ወይንም ማድመጥ ይቻላል፡፡

በጥንቱ ዘመን ለህብረተ-ሰብ መሪዎች የመሪነታቸው መብት ምንጭ ወይንም ማረጋገጫ አፈ-ታሪክ ነው፡፡ የህብረተ-ሰቡ የእምነት መሪዎች የአፈ-ታሪኩ ተርጓሚዎች፣ ደንብ አውጪዎች፣ የክብረ-በዓላት ደንጋጊዎችና አስፈፃሚዎች ናቸው፡፡ በአፈ-ታሪኩ መሠረት የህብረ-ተሰብ አባላት ማህበራዊ ድርሻዎቻቸውን፣ ጥቅምና ፍላጎቶቻቸውን ይወስናሉ፡፡ ያስጠብቃሉ፡፡ ያሟላሉ፡፡

ምንም እንኳ አፈ-ታሪክ ብዙዉን ጊዜ የህግን ያህል አስገዳጅነት ባይኖረውም የማህበረ-ሰብ አባላት በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው አክብረው የሚቀበሉት እና የሚተዳደሩበትም ነው፡፡ ዓለም ተፈጥሯል ተብሎ የሚታመንበት ሃሳብ ሌሎች ሃሳቦችንና አስተሳሰቦች የሚከተሉትን መንገድ ይወስናል፡፡ በተጨማሪም ዓለምን የምንረዳበትንና የምንመረምርበትን ስልት እንዲሁም ዓለም ምን እንደሆነች እና እንዳልሆነች የምንመለከትበትን ድንበር ያሰምራል፡፡ የሚቶሎጂ ወይንም የጥንት እምነቶችን የሚያጠኑ ተመራማሪዎች እንደሚሉት ስለዓለም አፈጣጠር የሚተርኩ አፈ-ታሪኮችን ለመረዳት አፈ-ታሪኮቹን የቀመሩትን ሰዎች አእምሮ ወይም ምናብ ለመረዳት መሞከር ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን የአፈ-ታሪኮች ዕድሜ እጅግ የራቀ በመሆኑ ይህን በትክክል መፈፀም አይቻልም፡፡ ሆኖም ስለ ማህበረ-ሰቡ አስተሳሰብ የሆነ ፍንጭ ሊሰጡ የሚችሉት አፈ-ታሪኮቹ ናቸው፡፡ ስለዚህ የማህበረ-ሰቡን አስተሳሰብ ለመገንዘብ አፈ-ታሪኮቹን መመርመር እና የአፈ-ታሪኮቹን ትርጉም ለመረዳት ደግሞ የማህበረ-ሰቡን አስተሳሰብ ማጥናት አስፈላጊ ነው፡፡

የጽሑፌ ርዕሰ-ጉዳይ የሆነው እና ስለ ዘ-ፍጥረት የተጻፈው ጥንታዊ ግጥም የሚገኘው “ሪግቬዳ” ተብሎ በሚታወቀው የጥንታዊት ህንድ ሃይማኖታዊ የውዳሴ ግጥሞች ስብስብ ውስጥ ነው፡፡ ሪግቬዳ የተጻፈው በጥንታዊ የሳንክሪት ቋንቋ ሲሆን “ሪግ” ማለት ውዳሴ ወይንም “ብርሃን” “ቬዳ” ማለት ደግሞ “ዕውቀት” ማለት ነው፡፡ ሪግቬዳ በጥቅሉ ቬዳ በሚል ስም ከሚታወቁት አራት የሂንዱ ይማኖት ቅዱስ መጽሐፍት መካከል አንዱ ነው፡፡ ሪግቬዳ በ10‚600 የግጥም መስመሮች የተቀመሩ 1028 መንፈሳዊ መዝሙሮችን ይዟል፡፡ ሪግቬዳ መቼ እንደተጻፈ በትክክል ማመልከት እንደማይቻል የመስኩ ምሁራን ቢገልፁም ከክርስቶስ ልደት 1700 ዓመት በፊት እንደሆነ ይገምታሉ፡፡ በግርድፍ ንጽጽር ሪግቬዳ ከመዝሙረ-ዳዊት ጋር ሊነጻጸር ይችላል፡፡ ሪግቬዳን ወደ እንግሊዘኛ የተረጎመው ጀርመናዊው የቋንቋ ታሪክና አድገት (ፊሎሎጂ) ተመራማሪ ማክስ ሙለር (እ.አ.አ 1823 -1900) ነው፡፡ ሙለር ጀርመናዊ ይሁን እንጂ አብዛኛውን የህይወት ዘመኑን የኖረው በእንግሊዝ ሀገር ነበር፡፡ ሙለር ሪግቬዳን የተረጎመው ከ1849 እስከ 1874 ድረስ በነበሩት 25 ዓመታት ውስጥ ሲሆን በ1859 “የጥንታዊው ሳንክሪት ሥነ-ጽሑፍ ታሪክ; አሳትሟል፡፡ ከሪግቬዳ ምዕራፍ 10፣ ቁጥር 129 የወሰደውና “ለማይታወቀው አምላክ ” የሚል ርዕስ የሰጠው ግጥም የቀድሞ ርዕሱ “መዝሙር ዘ-ፍጥረት” ወይንም the song of creation የሚል ነበር፡፡

መዝሙር ዘ-ፍጥረት

ያኔ መኖር ራሱም አልነበር፤

አለመኖርም ጭምር፡፡

አየሩም ድንበር አልባ፤ ያልነበረው አንዳች ዲካ፤

በሰማያዊ አድማስ እንኳ የሚለካ፤

ሁሉንም የሸፈነው፣

መጠለያም የሆነው፣

ውሃ ነበር!

የጥልቀቱ ጥልቀት፣

የሚያስቸግር ለመረዳት፤

ሞት የሚባል ነገር አልነበረም፣ አለሞሞት ራሱም፤

ሌትና ቀንን የሚከፍል የሆነ አንዳች ምልክትም፡፡

ትንፋሽ አልባ አንዳች ነገር፣

በራሱ እስትንፋስ ከሚተነፍስ በቀር፣

ሌላ ከቶ ምንም አልነበር፡፡

ጭለማ ግን በእርግጥ ነበር ተጀብኖ በደይን፣

ውሉ በጠፋ ምስቅልቅል

ማንም ሊለየው በማይችል፡፡

ያንጊዜ የነበረ፣

ቅርፅ አልባ ህዋ ብቻ ነበረ፤

በታላቅ የሙቀት ሃይል አስቀድሞ የተፈጠረ፡፡

ከዚያ በኋላማ ፍላጎት ቀድሞ ብቅ አለ፣

የመንፈስ ዋናው ዘር፣

ደቂቅ ህይወት አዘል፣

ሊቃውንት በልብ ሃሳብ፣ ማስነው ማስነው ፈልገውት፣

ካለመኖር ቤተ-ዘመድ ውስጥ መኖርን ሽተ0ው አገኙት፡፡

አግድም የተሰመረ፣ ድንበር- መሰል ትልቅ መስመር፣

ከበላዩ ያለው አይታወቅ፣ ወይ የተቀመጠው ከእርሱ ስር፡፡

የግዙፍ ሃይል ወላጆች፣

ከወዲ-እንዲህ ነጻ ተግባር፣

ጉልበት ከወዲያ ማዶ ባሻገር፣

ማነው በእርግጥ የሚያውቅ፣ ማንስ ነው የሚመሰክር?

ውልደቱ ከየት እንደሆን ፍጥረት የተባለው ነገር፡፡

የመላዕክቱም መወለድ ከዓለም መፈጠር ወዲህ ነው፣

ታዲያ የዘፍጥረት መነሻ የሚያውቅ ፣ ማን የተባለው ፍጡር ነው?

የዘፍጥረት መነሻ የሆነው፣

በሰማየ ሰማያት ሆኖ ይህን ዓለም የሚቃኘው፣

ፈጥሮትም እንደሁ አልፈጠረው፣

እርሱው ነው በውል የሚያውቀው፣

አሊያም ደግሞ የማያውቀው፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top