ጥበብ በታሪክ ገፅ

“ኵርዓተ ርእሱ” የጠፋው የሃገር ሥነ ሥዕልና የተረሳው ሃገራዊ ሥነ ጥበብ

“ኵርዓተ ርእሱ” በሌላ ስሙ “አክሊለ ሦክ” በኢትዮጵያ እጅግ ጥንታዊና የከበረ መንፈሳዊ የሥነ ጥበብ ቅርስ ነው። የጠፋው ከአንድ መቶ ሃምሳ ዓመት በፊት ነው። ስለ ጉዳዩ ከሐበሻ ሀገር የተላኩ ሁለት የንጉሠ ነገሥቱ ደብዳቤዎች በእንግሊዝ ቤተ መንግሥት ውዝግብ ፈጥረዋል። የደብዳቤዎቹ ዋና ይዘት “ከመቅደላ የተዘረፉ ቅርሶቻችን ይመለሱ” የሚል ሲሆን ከሁሉም በላይ ደግሞ “ኩርዓተ ርእሱ” የተባለው ሥዕልና “ክብረ ነገሥት” የተባለው መጽሐፍ እጅግ በጣም እንደሚያስፈልጉ በአጽንዖት ያስታውቃል። ዐፄ ቴዎድሮስ ካረፉ አራት ዓመት በኋላ ደጃዝማች ካሳ ጥር 13 ቀን 1864 ዓ.ም. አክሱም ላይ ሥርዓተ ንግሣቸው ተፈጽሞ ዐፄ ዮሐንስ አራተኛ ንጉሠ ጽዮን ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብለው ነገሡ። ንጉሡ በዚያው ዓመት በነሐሴ ወር መጀመሪያ ሁለት ደብዳቤዎችን ወደ እንግሊዝ ላኩ። አንደኛው ደብዳቤ በቀጥታ ለንግሥት ቪክቶሪያ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በውጭ ጉዳይ ኃላፊው በኧርን ግሪንቪል አድራሻ የተላኩ ናቸው። ንግሥቲቱም የደብዳቤውን ይዘት በማጤን ከሹማምንቶቻቸው ጋር ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኋላ “ለመልካምነትና አጋርነትን ለመግለጽ ያህል /gracious and friendly act” ሁኖ የተጠየቁት ሁለት ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ለንጉሠ ነገሥቱ እንዲሰጡ የጽሑፍ መመሪያ ለሙዚየሙ ጻፉ። የሙዚየሙ ዋና ኃላፊም ከመቅደላ የዘረፏቸውን በርካታ ንብረቶች በማገላበጥ “ሁለት የክብረ ነገሥት መጻሕፍትን” እንዳገኘና የአጻጻፍ ጥበቡ የማይማርክ ታሪካዊ አስፈላጊነት (ቅርስነት) የሌለውን ለመመለስ እንደሚችሉ ሲገልጽ፤ “ኵርዓተ ርእሱ የተባለው ሥዕል” በዝርፊያ ስብስቦቻቸው ውስጥ እንደሌለ ለንግሥቲቱ ያሳውቃል። በሙዚየሙ ኃላፊና የቅርስ ስብስባ ባለሙያዎችም አስተያየት ይህንን “ክብረ ነገሥት” የሚመልሱት መጽሐፉ ካለው አላስፈለጊነት እንጅ ሁኔታው ለሌሎች ቅርሶች መመለስ በር መክፈት እንደሌለበት የሚያመለክት ነበር። የሆነው ሁኖ “ክብረ ነገሥት” በተጠየቀ በጥቂት ወራት ውስጥ ከባለሥልጣናቱ ብዙ ውይይት በኋላ በ1865 ዓ.ም. ከእንግሊዝ ሙዚየም ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ።

 የ“ኵርዓተ ርእሱ” ጉዳይስ? ዐፄ ዮሐንስ ክብረ ነገሥቱን ማስመለሳቸው እንደተጠበቀ ሁኖ “ኩርዓተ ርእሱን” በተመለከተ ከእንግሊዝ የውጭ ግንኙነት ኃላፊና ከንግሥት ቪክቶሪያ ሁለት ደብዳቤዎችን ተቀብለዋል። ግሪንቪል ለንጉሠ ነገሥቱ በሰጠው መልስ “ግርማዊ ሆይ ሥነ ሥዕሉን በመፈለግ እጅግ በብዙ ችግር ደከምኩ ግን ሊሳካልኝ አልቻለም፣ ስለመኖሩ ማንም ሊነግረኝ አልቻለም” ብሏል። ንግሥት ቢክቶሪያ በበኩላቸው “ሥነ ሥዕሉን በተመለከተ ምንም ፍንጭ ማግኝት አልቻልንም በምንም ሁኔታ፣ ወደ እንግሊዝ የመጣም አይመስለኝም” በማለት ለዐፄ ዮሐንስ ደብዳቤ ላኩ። (ፓንክረስት 2001)፤ ይሁን እንጅ የታላቋ ንግሥት ቪክቶሪያም ሆነ የውጭ ጉዳይ ኃላፊያቸው ግሪንቪል መልስ ትክክል አልነበረም፣ ራሳቸውንም ንጉሠ ነገሥቱንም ዋሽተዋል። ለምን?

መቅደላ ድረስ የመጣውና በኋላ የንግሥቲቱ የቤተ መጻሕፍት ወመዘክርና የመዛግብት ኃላፊነትን የተሾመው ሪቻርድ ሆልምስ ዐፄ ዮሐንስ ከሞቱ በኋላ በዓመቱ ሥዕሉን ለንደን ለሚገኘው የደች እንደራሴ ማሳየቱ ተነገረ። ጥቂት ቆይቶም በ1897 ዓ.ም. የሥዕሉ ፎቶ “የክርስቶስ ከአንገት በላይ ሥዕል ቀደም ሲል የዐፄ ቴዎድሮስ የነበረ አሁን በሪቻርድ ሆልምስ እጅ የሚገኝ” በማለት በርሊንግቶን መጽሔት ላይ ታተመ። የሥዕሉንም ስም “ኵርዓተ ርእሱ” በማለት ፈንታ “የተከዘው የፍሌሚሽ ሰው ምስል” በማለት ገልጾታል (ስታንሰላው፡1983)። አሁን ጥያቄው “ኵርዓተ ርእሱን” አስመልክቶ ከንግሥት ቪክቶሪያ ጀምሮ መላው የእንግሊዝ ባለሥልጣናት ለምን ዋሹ? የሥዕሉ ማንነት እየታወቀ ለምን በሌላ መጠሪያ ተጠራ? ንጉሡ ከሞቱ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ተጠብቆ ለምን ታተመ? ንግሥቲቱን የዋሸው ሁነኛ ታማኝ የቪክቶሪያ መዛግብት ኃላፊ ምን ተደረገ? (ተሾመ!!)። ሥነ ሥዕሉ ምን ያህል አስፈላጊ ቢሆን ነው? የወርቅ ዘውድና አክሊሎች፣ የወርቅ መስቀሎች፣ ጽዋ፣ ጫማ፣ ጋሻ፣ ጽንሐሕ፣ የሐርና ወርቀዘቦ አልባሳት፣ ከአንድ ሺህ በላይ መጻሕፍት፣ ከወርቅና ከብር የተሠሩ እጅግ በርካታ ንዋያት፣ ከዐሥር በላይ ጥንታውያን ታቦታት፣ በ1868 ዓ.ም. ተሰርቀው ከ16 በላይ በሆኑ ዝሆኖችና ከ200 በላይ አህዮች ተጭነው እንደሄዱ ለሁሉም በይፋና በዝርዝር ሲታወቁ “ኩርዓተ ርዕሱ” ሥዕል በእንግሊዝ ለምን ድብቅ ምሥጢር ሆነ?

 ፈጣሪ በመንግሥቱ ያክብራቸውና እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ፤ የሪቻርድ ሖልምስን ሕትመት መሠረት አድርገውና የሥዕሉን ጥንታዊ የታሪክ መሠረት በሚገልጽ መንገድ “ለጠፋው የኢትዮጵያ ሥነ ሥዕል ኩርዓተ ርዕሱ ክብር /Kureate Re’esu: Homage to the Lost Art of Ethiopia” በሚል ርዕስ ስታይሉን በመቅዳት በራሳቸው ትርጉም በኢትዮጵያዊ ገጸ ንባብና ቅለማ ሥለውታል። ሥዕሉ ሊቪንግ ባይብል ኢንተርናሽናል በ1980 ዓ.ም. ባሳተመው ሕያው ቃል-ሐዲስ ኪዳን ውስጥም በቀለም ታትሟል።

የኢትዮጵያዊው የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ “ኵርዓተ ርእሱ” ትርጉም ሪቻርድ ሖልምስ ካሳተመው የ“ኵርዓተ ርእሱ” ዋና ቅጅ ፎቶ ጋር በብዙ መልኩ ይለያል። ሆልምስ ከመቅደላ የሰረቀውና፣ የለም ብሎ ዋሽቶ በኋላ አለኝ ብሎ ያሳተመውን ሥዕል የኢትዮጵያ አላለውም። “ከኢትዮጵያ የተወሰደ የፍሌሚሽ ሰው ሥዕል” ብሎ ጠርቶታል። ማለትም በታሪካዊ መሠረቱም ሆነ በሀገሩ በሚታወቅበት ስም ለይቶ አላስቀመጠውም። ይህ ሁሉ ለምን አስፈለገ? የሚለውን ከመጠየቅ ጀምሮ አውሮፓውያንን ጨምሮ አንዳንድ ተመራማሪዎች መጠርጠራቸውም አልቀረም! ለመሆኑስ የሥዕሉ ታሪካዊና ሥነ ጥበባዊ ትንታኔ ምንድን ነው? እነሆ በአጭሩ!

 በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የቆስጥንጥያን መንግሥትና እምነት ታሪክ፣ የጥንት ክርስቲያኖችን አኗኗርና ታሪክ በመጻፍ የሚታወቀው አውሳብዮስ ዘቂሳርያ እሱ ከነበረበት ቀደም ብሎ ጀምሮ “የክርስቶስና የሐዋርያት ባለቀለም ሥዕሎች በክርስቲያኖች ዘንድ ተጠብቀው ይገኛሉ። ከእነዚህም ውስጥ በሰው እጅ ያልተሣለ /Mandylion/ የሚባል የኤዴሣ ሥዕል ይገኝበታል” በማለት ሂስቶሪያ ኤክሊሲያ ላይ ዘግቧል። ከተጠቀሱት ታሪኮችም አንዱ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተምር በነበረበት ወቅት ኤዴሳ በምትባል የሶርያ ክፍል አብጋር የነበረ አምስተኛ ራስ ገዝ ንጉሥ (ጥቁሩ አብጋር) ታሪክ ይገኝበታል። ንጉሡ ፊቱ ላይ አብዝቶ በወጣ “ለምጽ”ና በሌላ ሕመም በጠና ታሞ ስለነበር ኢየሱስ ወደ ሀገሩ መጥቶ እንዲፈውሰው ደብዳቤ ይጽፍ ነበር። ወንጌላዊው ማቴዎስ (4፡24) ላይ የክርስቶስ የፈውስ ዝና ከኢየሩሳሌም አልፎ በሶርያም እንደተሰማ ገልጧል። የኤዴሳ ንጉሥም ሰው የሆነ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም ሲያስተምር፣ ሕሙማንን ሲፈውስ፣ ሙታንን ሲያስነሣ ሰው ይሠራቸዋል ተብለው የማይታመኑ ብዙ ተአምራትን ሲያደርግ ዜናውን ሰምቶ ስለነበር ለመዳን በመጓጓት ደብዳቤ እንደጻፈ ይነገራል። ይሁን እንጅ ክርስቶስ ወደ እርሱ አልሄደም። በመጨረሻ ቢያንስ ኢየሱስ ወደ እርሱ ሄዶ በእጁ ዳሶ፣ በቃሉ ተናግሮ፣ ወይም በትምህርቱ ባይፈውሰው የመልኩን ገጽ አይቶ እንደሚድን አመነ። ለዚህም አናንያ (ሐናንያ) የሚባል ገበዝና ከፍተኛ የሥዕል ችሎታ ያለው ባለሟል ስለነበረው ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ የኢየሱስን የፊት መልክ በቀለም ሥሎ እንዲያመጣለት አዘዘው። (ካሊስቶስ 1998)

የአይኮኖሎጅ ጸሐፊው ሊዎኒድ ዑስፔንስኪ “ዘቲዎሎጅ ኦፍ ዘአይከን” በሚለው መጽሐፉ የመጀመሪያ ቅጽ በግርጌ ማስታወሻው ካሠፈረው ታሪክ አንፃር በምሥራቅ ኦርቶዶክስና በሶርያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት አናንያ ለሥራ የሚያስፈልገውን የሥዕል መሣሪያና የንጉሡን መልእክት ይዞ በ33 ዓ.ም. ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዟል። ሠዓሊው በመንገዱ ኢየሱስ ክርስቶስን ሲያስተምር፣ ወይም ሲፈውስ ወይም ሙት ሲያስነሣ እንዴት እንደሚሥለው በማሰብ ኢየሩሳሌም ደርሷል። ሆኖም የአብጋርን መልእክት ለክርስቶስ በማድረስ ፊቱን ለመሣል ብዙ ሙከራ ቢያደርግም ከገጹ ግርማና በዙሪያው ካለው ጸጋ የተነሣ መሣል አልቻለም፤ ስለዚህም ክርስቶስ ራሱ አናንያ ለመሣል ባዘጋጀው ንፁሕ ጨርቅ ፊቱን በመጥረግ የፊቱን ምስል ሰጥቶታል። ያንንም ይዞ ወደኤዴሳ ተመለሰ። በዚህም መሠረት የሥዕሉ ስያሜ በምሥራቅ ኦርቶዶክሳውያን ዘንድ አኺሮፖይታ (ἀχειροποίητα / made with no hand) ወይም በሰው እጅ ያልተሣለ ሥዕል ይባላል። (ዑስፔንስኪ፡ 1992፣ ገጽ 51) እንደ አውሳብዮስ ገለጻ በኋላ ዘመን ከሰባሁለቱ የክርስቶስ አርድዕት አንዱ ታዴዎስ ክርስትናን ለኤዴሳ ሰዎች ሰብኮላቸዋል። ከጥንት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ይኽ ሥዕል ሲሣል ሁለት ትውፊታዊ አሣሣሎችን የተከተለ ነው። አንዱ ገጹን በቀጥታ ለሥዕል በተዘጋጀው ሰሌዳ ላይ መሣል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሥዕሉን ከመሣል በፊት ወይም ከሥዕሉ መልክዓ-ገጽ ጋር በተስማማ መንገድ ሥዕሉ ከተሰጠበት ነጭ ጨርቅ ላይ እንደተሣለ አድርጎ መሣል ነው። በሂደት የሥዕሉ ትውፊት እያደገና በርካታ የአሣሣል ትርጉሞችን በመከተል ተጨማሪ ድርሰቶች እየተካተቱበት መጥቷል። ለምሳሌ በጉልህ ከታዩት ጭማሪዎች ውስጥ ከመካከለኛው ክፍለ ዘመን በኋላ በምሥራቁም ይሁን በምዕራቡ ዓለም ከላቲኑ ትውፊት በመውሰድ አኺሮፖይታ አክሊለ ሦክን አካቷል። የግሪክ ቋንቋ ቅርጸ ፊደሎችን የተከተሉ ምሕፃረ ሐረጋትና የስም ወካይ ፊደሎችን እያካተተና በራስ ዙሪያ ያለው ክበበ ብርሃን የሚጠቀሱ ዕድገቶች ናቸው።

 የሩሲያው አይኮኖግራፈር ዩሻኮቭ ትርጉም በ17ኛው ክፍለ ዘመን

 የዚህን ሥዕል ታሪክ በአካል ተገኝተውና በዓይን አይተው ከጻፉ የታሪክ ምሁራን ውስጥ በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው አቫግሪዎስ ስኮላስቲከስ ይገኝበታል። አቫግሪዎስ ሥዕሉን በፈጣሪ የተሣለው ሥዕል (θεότευκτος) (ቴዎቲንክቶስ) በማለት ሲተርክ፣ አብጋር ባገኝው ፈውስና ድኅነት ያመልከው የነበረውን ጣዖት ትቶ በከተማዋ መግቢያ ላይ የነበረውን ቤተ ጣዖት አፍርሶ፣ የዚሁ ሥዕል ማክበሪያ ቤተ መቅደስ ሠራ። በሂደት ሦስተኛው የአብጋር ትውልድ መልሶ የዚህን ሥዕል ቤት አፈረሰው፣ የመብራቱንም ሥርዓት እንዲረሳ አደረገ። በ544 ዓ.ም. ፋርሶች ኤዴሳን በመውረር የከተማውን መግቢያ ቤት ለማፍረስ ሲጠጉ ይህ ቦታ ቀድሞ በቦታው በነበረው የክርስቶስ ሥዕል ተአምራዊ ሥራ ከተማዋንና ነዋሪዎቿን ታደጋት። በዚህም ምክንያት ሥዕሉም ዳግም በኤዴሳ ተከበረ፣ የከተማዋ ጠባቂና መከታ እንደሆነም ታመነ።

 የሥዕሉ የድል አድራጊነትና የጠባቂነት ተምሳሌት በሮምና በቆስጠንጥንያ ተሰማ። የ836 ዓ.ም. ጉባኤ በሥዕላት ላይ ለተነሣው ተቃውሞ መከራከሪያነትና ሥዕልን ፈጣሪ ራሱ እንደተቀበለው ለማስረጃነት ቀርቦ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር። በአሥረኛው ክፍለ ዘመን ወደ ታላቋ የቆስጠንጥንያ ከተማ ተወሰደ፣ የዘመኑ ነገሥታትም ሥዕሉን በክብር በመቀበል በታላቋ የአጊያ ሲፍያ “የእግዚእብሔር ሰማያዊ ጥበብ ቤተ መቅደስ” በአሁኑ ኢስታንቡል ለሕዝብ ታዬ። ንጉሡ ቆስጠንጥንዮስ ፖርፊሮጀኒቱስም በእግዚአብሔር እጅ የተሣለውን ሥዕል የሀገራችን ጠባቂ (Palladium) ብሎ በአደባባይ ሰየመው። በቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን እንዲቀመጥና በየዓመቱ በነሐሴ 16 ቀን ክብረ በዓሉ እንዲሆን ወሰነ። ትውፊቱ በመቀጠሉ በተከታዮቹ ክፍለዘመናት በስሙ አብያተ ክርስቲያናት እንደታነፁና ልዩ ልዩ ቅዱሳት መካናት እንደተሰየሙ በታሪክ ተመዝግቧል። በመጨረሻ በ4ኛው የመስቀል ጦርነት ቆስጠንጥንያ በከፍተኛ ደረጃ ስትጎዳና በመስቀል ጦረኞች ስትዘረፍ ሥዕሉም ጠፋ። ከዚህ በኋላ በተለያዩ ቦታዎች ታዬ ይባላል እንጅ ጥንታዊው ስለመገኘቱ ፍንጭ የለም፣ አምሳያው ግን ልዩ ልዩ ሥያሜዎች እየተሰጡት በየሀገሩ ይገኛል። በአገልግሎትም በምሥራቅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በብዙ የጸሎትና የምሕላ ንባቦች ላይ ከነታሪኩ ሲጠቀስ፣ በውጊያ ጊዜ ሥዕሉን ይዞ መሔድ የተለመደ ነበር፣ ለምሳሌ በጥንት ኦርቶዶክስ  ሩሲያውያን ሠራዊት እንደ ጠባቂ ዓርማ አድርገው በጦር ጋሻዎቻቸው ላይ ይሥሉት ነበር። በአርመን ኦርቶዶክስ አብጋር በጣም የሚከበር ንጉሥና እውነተኛ ሰው ሲሆን ታሪኩ በአርመን ብሔራዊ የብር ኖት ላይ አብጋር ከአኺሮፖይታ ጋር ተሥሎ ይገኛል።

ሁለተኛው ትውፊት በምሥራቁና በኦሬንታል ክርስቲያኖች በሰፊው የማይታወቀው በሂደት ግን በመላው ዓለም እየሰፋ የመጣው “ቅዱሱ ፊት/ Volto Santo ” የቬሮኒካ ሻሽ/ Veronica’s Veil” ተብሎ የሚጠራው ሥነ ሥዕል ትውፊት ነው። የቬሮኒካ መሐረብ ማለትም እውነተኛው ሥዕል የተሣለበት ጨርቅ እንደማለት ነው)። የዚህኛው ትውፊት መነሻ ደግሞ ቬሮኒካ የተባለች ሴት ጌታ መስቀሉን ተሸክሞ ወደቀራንዮ ሲወጣ ደክሞትና አልቦት ስለነበር የአንገት ልብሷን አንሥታ ፊቱን እንደጠረገች ከዚያም የፊቱ ምስል በልብሷ ላይ እንደቀረ የሚተርከውና በምዕራቡ ዓለም በሰፊው የሚነገረው ትውፊት ነው። በኢየሩሳሌም ዶሎሮዛ ጎዳና የቬሮኒካ ቤት በሚባለው ቦታ በሥዕሉ ስም “የቅዱሱ ገጽ/ምስል” ቤተ ጸሎት ተሰይሞ ይገኛል።

 ከላይ በአጭሩ ከተተረከው አንፃር ለእኛ “ኵርዓተ ርእሱ/አክሊለ ሦክ” ትውፊት መሠረት የሆነው በምሥራቁ ዓለም የነበረውና በተለይም የአርመንና የሶርያ ኦርቶዶክስ ትውፊት ነው። ኤዴሳ ከዘመነ አክሱም ጀምሮ በሀገራችን የምትታወቅ ሀገር ናት፤ በተለይም ከቅዱስ ላሊበላ ታሪክና ከሮሃ ምሥረታ ጋር በተያያዘ ሰፊ ቦታ ተሰጥቷል። ምንም እንኳ የሥዕለ ሉቃስ “ምስለ ፍቁር ወልዳ” እና የሥዕለ ዮሐንስ ወንጌላዊ “ሥዕለ ሥነ ስቅለት” በሰፊው የታወቁ ቢሆንም “ኵርዓተ ርእሱ” የራሱ የሆነ ታሪክና መንፈሳዊ አገልግሎት ነበረው። እዚህ ላይ አስፈላጊው ጉዳይ ኢትዮጵያውያን ሥዕሉን በምሥራቅ ኦርቶዶክስም ይሁን በምዕራባውያን ይጠራበት በነበረው ስም አልጠሩትም። የሥዕሉን ድርሰት በመጠኑ ለውጠውታል፤ ማለትም ለስሙ በሚመች መንገድ አክሊለ ሦኩንና ራሱን የተመታበትን በትር፣ የታሠረበትን ገመድ ጨምረውበታል። በታሪካዊ ሂደቱ ደግሞ ሥዕሉ የበለጠ ጎልቶ የታወቀው ከአሥራ አራተኛው ክፍለ ዘመን በኋላ ነው።

 ከኵርዓተ ርእሱ ሥዕል መጥፋት ጋር በተያያዘ “the History of Kuer’ata Re’esu: an Ethiopian Icon” በሚል ርዕስ አጭር ጽሑፍ የጻፉት ፓንክረስት የዐፄ ዳዊትን ዜና መዋዕል (14ኛው መቶ ክ/ዘ) በመጥቀስ የግብፁ ማምሉክ ለዐፄ ዳዊት ከላካቸው ንዋየ ቅድሳት መካከል አንዱ እንደሆነ ጽፈዋል። የግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም መጽሐፍ የሆነው መጽሐፈ ጤፉት እንደሚዘግበው የጌታችን መስቀል ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ “ኵርዓተ ርእሱ” አብሮ እንደመጣና በ15ኛው መቶ ክ/ዘ በዐፄ ዘርዓያዕቆብ

“ለማጠቃለል ያህል የሚቆጨው ጉዳይ የጠፋውና ያልተመለሰው ቅርስ ብቻ ሳይሆን የምርቱ ምንጭ የሆነው ሀገራዊ ሥነ ጥበብም እንዲሁ አብሮ መጥፋቱ ነው። እንደ “ኵርዓተ ርእሱ” ዓይነት የገበታ ሥዕሎች የሚሣሉበት ዘመን ሙሉ በሙሉ ቀርቶ፣ እጅ ሥራ ተትቶ ገበያው በሕትመት ሥራዎች ተጥለቅልቋል”

ዘመነ መንግሥት ወደ መስቀለኛው የአምባሰል ተራራ ተወስዶ በግሸን ማርያም በክብር እንደተቀመጠ ይናገራል። “ወእምዝ ኀቢሮሙ ፈነው ሎቱ … መስቀሎ ለክርስቶስ ወሥዕላተ እግዝእትነ ማርያም ስብዑ ዘሠዓሎን ሉቃስ ወንጌላዊ ወሥዕለ ኵርዓተ ርእሱ” ከዚህ በኋላ … ተማክረው የክርስቶስን መስቀል፣ ሉቃስ የሣላቸውን ሰባቱን የእመቤታችን ሥዕሎችና የጌታችንን ኵርዓተ ርእሱ ላኩለት” (መጽሐፈ ጤፉት፡ 2006)። የመምጣቱን ምክንያት ኢግናቲዎስ ጉይዲ (እ.ኤ.አ. 1978) ከግብጽ መዛግብት ጋር በማያያዝ እንደጻፈው ንጉሡ ከዓባይ ወንዝ ጋር በተያያዘ በነበራቸው ጉዳይ ሥዕሎቹን እንደላኩ ይገልፃል። (ጉይዲ፡1926)

 ሥዕሉ ወደ ሀገራችን ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ በርካታ የሥዕል ትምህርት ቤቶች በተለያየ ድርሰት መሠረቱን ጠብቀው ብዙ “ኵርዓተ ርእሱ” ሥዕሎችን ሥለዋል። በተለይ ነገሥታቱ ከሥዕሉ ጥንታዊ የምሥራቅና ኦሬንታል ኦርቶዶክስ ትውፊት ጋር በማያያዝ ይመስላል በዘመቻም ይሁን በታላላቅ ጉዞዎች “ኵርዓተ ርእሱን” ይዘውት ይጓዙ ነበር። የሥዕሉ ቅጅ ጎንደር የኢትዮጵያ ዋና ከተማ በነበረችበት ወቅት በጎንደር ቤተ መንግሥት በንጉሡ ቤተ ጸሎት ውስጥ እንደነበርና በ17ኛው መቶ ክ/ዘ በቀዳማዊ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት “የጌታችንን ሥዕል” በመያዝ እንደዘመቱ ዜና መዋዕሉ ይናገራል። (ፓንክረስት፡ 2001)፤ ጀምስ ብሩስ ጎንደር በነበረበት ጊዜም ከሥዕሉ ጋር በተያያዘ ያየውን አስደናቂ ትእይንት ዘግቧል። (ብሩስ)

ኤነሪኮ ቸሩሊ ስለ “ኵርዓተ ርእሱ” ባጠናው መሠረት ሥዕሉ በታተመበት ወቅት አውሮፓ ውስጥ ልዩ መወያያ እንደነበር ሲናገር፤ ስያሜው ኢትዮጵያውያን ከማቴዎስ ወንጌል 27፡30፣ ወይም ማርቆስ ወንጌል 15፡19 ላይ ያለውን ገጸ ንባብ በመውሰድ በሌላው ዓለም በማይታወቅበት ስም መሰየማቸውን በመጠኑ አትቷል። ስታንስላው ዮናስኪ (Stanislaw Chojnacki፡ Major Themes in Ethiopian Paintngs፡ 1983) ለሥዕሉ አውሮፓዊ መነሻ በመስጠት የተከዘው ሰው “Ecce Home” ከሚባለው አውሮፓዊ የሥዕል ድርሰት ጋር በማያያዝ የሥዕሉን ምንጭ አውሮፓዊ ሲያደርጉ በኢትዮጰያ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ከሚሰጣቸው የሥነ ጥበብ ርእሶች ውስጥ ዋናው እንደነበርና ከልዑላኑ ጋር የነበረውን ትስስር በሰፊው ጽፈዋል። ዮናስኪ ስለ ሥዕሉ ምንጭና ሥያሜ የሰጡት መነሻ የራሱ የሆነ ሌላ ችግር ስለሆነ ለጊዜው እንተወውና የሥዕሉን አስፈላጊነትና በሀገራችን ሥነ ጥበብ ውስጥ የነበረውን ጉልህ አስተዋጽኦ በጥልቀት እንመርምር። ሥዕሉ ከመንፈሳዊ ሕልውናው በተጨማሪ በነገሥታቱና በሕዝቡ ዘንድ ልዩ ቦታ ነበረው። ቢያንስ ከጎንደር በኋላ ባሉን ሰነዶች ውስጥ ሠራዊቱ ወደ ውጊያ ከመግባቱ በፊት በታማኝነት ለመዋጋት መነሣቱን ለማረጋገጥ “ቃለ መሐላ” የሚፈጽመው በዚሁ ሥዕል ነበር፤ በውጊያ ጊዜም ሠራዊቱ የድል ወኔ እንዲያድርበት ልዩ አስተዋጽኦ ነበረው። ይህን ትውፊት ቀደም ሲል በሶርያ ኤዴሳና በሩሲያ ካየናቸው ታሪኮች ጋር ተመሳሳይነት ነበረው። ስለዚህ በሀገራችን እምነትና የሰዎች ሃይማኖታዊ ማንነት እንደተጠበቁ ሆነው ሥነ ጥበብ የነበረውን ትልቅ ድርሻ ከታሪኩ እንረዳለን። ማንኛውም ሥነ ጥበብ የኅብረተሰብን ሁለንተናዊ ዕሳቤ፣ ዕሴትና መሠረታዊ ድብቅና ጉልሕ ኩነታት በመግለጽ፣ በመዘገብ፣ በማስተዋወቅና በመተርጎም የማይተካ ሚና አለው። በእምነትም የሃይማኖት ምሥጢራትንና ታሪክን ከማሳየት፣ ትምህርተ መለኮትን፣ ነገረ አምላክን ከማስተማር ባሻገር መንፈሳዊ ጸጋንና ሰማያዊ ሀብትን በማስተላለፍ፣ በሥርዓተ አምልኮት ውስጥ ከፍተኛ አገልግሎት ይሰጣል። የኵርዓተ ርእሱም አስፈላጊነት ከዚህ ጋር የተያያዘ ነበር። ሲቸገሩ ይለምኑበታል፣ ሲደሰቱ ያመሰግኑበታል፣ ሲታረቁና ሲደራጁ በሥዕሉ ይማማላሉ፣ ጠላት ሲመጣ ይዘውት ይዘምታሉ፣ በረሐብና በቸነፈር ጊዜ ምሕላ ያደርሱበታል።

 “ኵርዓተ ርእሱ” በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ልዩ ቦታ እንደነበረው እንግሊዞች በእርግጠኝነት አስቀድመው ያውቃሉ። አንድ የጦር መሪ ውጊያ ከማድረጉ በፊት ስለባላጋራው ከሚያጠናቸው ጉዳዮች ውስጥ፣ የባላጋራውን የጦር መሣሪያ ብዛትና ዓይነት፣ የሠራዊቱን ብዛት ብቻ አይደለም። የሠራዊቱን የወኔና የኅብረት ጽናት ምንጭ፣ የጥንካሬ መገኛ፣ የሚያከብረውንና የሚወደውን ነገር፣ አምልኮውን እና የሚያዜመውን ዜማ ሳይቀር በጥልቀት ያጠናል። ይህም ውጌያውን በመሣሪያ ብቻ ሳይሆን በሥነ ልቦናም ለማሸነፍ ከፍተኛ ዕድል ይፈጥርለታል። ሀገራችንን የወረሩ የአውሮፓ መኰንኖች ይህንን በደንብ ተጠቅመዋል፣ የመቅደላ ጦርነት በሰሞነ ሕማማት መደረጉ ድንገተኛ አልነበረም፣ የአድዋ ጦርነትም በአቢይ ጾም አጋማሽ መደረጉ ሳይታሰብ የተደረገ አልነበረም። ጣሊያን የክርስቲያኑን ሥነ ልቦና ለመጣል አስቦ እንጂ መቀሌ የእንዳ ኢየሱስን ቤተ ክርስቲያን አፍርሶ ምሽግ ማድረጉ ሌላ ቦታ አጥቶ እንዳ ኢየሱስ የግድ አስፈላጊ ቦታ ስለሆነ አልነበረም። ከዚሁ አንፃር ከመቅደላ ጦርነት ፍጻሜ በኋላ አርኬዎሎጅስትና የቅርስና የቤተ መጻሕፍት ባለሙያ ሳይቀር ይዘው የዘመቱት የነበራቸውን ቅድመ ዝግጅትና የመረጃ ጥንቅር በሚገባ ያሳያል። የባሰው ደግሞ ከሠራዊቱ ጋር የዘመተው የቅርስና መዛግብት ባለሙያ ሪቻርድ ሆልምስ ለዝርፊያው በጣም ከመጎምጀት ይመስላል ከመቅደላ ሌላ እንደአክሱም፣ ላሊበላና ግሸን የመሳሰሉ ቦታዎችን የመጎብኝት ፍላጎት እንደነበረው በኋላ ታውቋል። እንኳንም የቀረ! (ዮናስኪ፡ 1983)

ንጉሠ ነገሥቱ ዐፄ ቴዎድሮስ በጎንደር፣ በደብረ ታቦር፣ በላስታና በየጁ፣ በሳይንትና በበሸሎ አካባቢ ከነበሩ ታላላቅ አድባራት በግድም በውድም የሰበሰቡትን በቁጥር ከሦስት ሺህ በላይ የወርቅ፣ የብር፣ የብረት፣ የነሐስ፣ የሐር፣ የብራናና የዕጽዋት ቅርሶች እንግሊዞች አንድም ሳያስቀሩ ዘረፉ። ሀገራችን የጥንታዊ ሥነ ጥበብ ሀገር መሆኗ በመዛግብት ማስረጃ ከመደገፍ በላይ በታሪክም በተረትም ሲነገር የኖረ ሐቅ ነው። ይሁን እንጂ ቀደም ባሉት ጊዜያት በየዘመኑ ከውስጥም ከውጭም የሚነሱ ብጥብጦችና ወረራዎች የጠቢብ ልጆቿን ሥራ በጥቂት ወራት ውስጥ ድራሻቸውን ሲያጠፉት ኑረዋል። ከሺህ ዓመታት በላይ የዘለቀው የአክሱም ሥነ ጥበብ ሃያ ዓመት ባልሞላው የዮዲት ጉዲት ጦርነት ጠፋ፤ ከዚያ ከ9ኛው እስከ 16ኛው መቶ ክ/ዘ ድረስ ለስድስት መቶ ዓመታት ያህል ሲደከምበት የነበረው የጥበብ ውጤት ቱርክንና አረብን አስተባብሮ በተነሣው የግራኝ ወረራ እንዲሁ ተዘረፈ፣ ተቃጠለ፣ ቀለጠ፣ ጠፋ። ተክለፃድቅ መኩሪያ “የግራኝ አህመድ ወረራ” በሚለው መጽሐፋቸው እንደገለጹት ግራኝ ባይነሣ ኖሮ የኢትዮጵያውያን የሥነ ጥበብ ውጤት የት በደረሰ ነበር። (ተክለፃድቅ፡ 1970) ከዚያ በኋላ መቅደላ ሌላው የጅምላ ውድመት ነበር።

 የመቅደላን ዝርፊያ ልዩ የሚያደርገው ከሀገር ተዘርፎ የወጣው ንብረት በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ በየሰፈሩ የጨረታ ገበያ ሲቸበቸብ መኖሩና ሻጮቹና ጠባቂ ነን ባዮቹ አሁንም ራሳቸውን እንደባለቤት ቆጥረው መቀመጣቸው ነው። ለዚህም ኵርዓተ ርእሱና ባለቤት ነኝ ባዩ ሆልምስ አንድ ማሳያ ናቸው። የሀገሩም ንግሥት ቪክቶሪያና ጠያቂው ዐፄ ዮሐንስ ከሞቱ በኋላ ሌላ ጠያቂ ይኑርም አይኑር ትንሽ ጊዜ አይቶ ለሕትመት አበቃው፤ እሱ በ1913 እ.ኤ.አ. ከሞተ በኋላ አሮጊት ሚስቱ ለጨረታ አውጥታ ሸጠችው አሉ!! ሁለተኛው ገዥ ደግሞ አሁንም እንደገና በ1950ዎቹ ለጨረታ አቀረበውና “ማንነቱ እንዲታወቅ ለማይፈልግ ለሦስተኛ ሰው ሸጠው” ብለው በአውሮፓ የሚታተሙ የዜና ምንጮች ዘግበውት አንብበናል። አሁንም እያነበብን እንገኛለን!!

 እንግዲህ ነገሥታቱ ይይዙት ከነበሩት አንዱና ትልቁ የሀገራችን የሥነ ጥበብ ሥራ ውጤት “ኵርዓተ ርእሱ” ከሀገር እንደወጣ አልተመለሰም፣ ሌሎቹም የዐፄ ቴዎድሮስ የጸጉር ቁራጭን ጨምሮ የመቅደላን ሣር ቅጠል ሳይቀር የተወሰዱትን ቅርሶች ለማስመለስ ይህ ነው የሚባል የተባበረ፣ ከፍተኛ ቁርጠኝነት ያለበት፣ ተከታታይነት ያለውና ያላሰለ ጥረት እስከ አሁን አልተደረገም። ከመቅደላ የተዘረፉት ቅርሶችና የተቃጠለው ቤተ ክርስቲያን መቶ በመቶ ለመባል ትንሽ እስኪቀረው ድረስ አሥር ታቦቶችን (ጽላቶችን) ጨምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ንብረቶች ናቸው፣ ሥዕሎቹ፣ ባለመስቀሉ የእቴጌ ጥሩወርቅ የክብር ቀሚስና የሐር-ወርቀዘቦ አልባሳቱ፣ የክብር ዕቃዎቹ በየግለሰቡና በየሙዚየሙ የአውሮፓውያን ስብስብ ማድመቂያ ሁነዋል። በአውሮፓ በተለያዩ ወቅቶች በሚደረጉ የጨረታ ገበያዎች እነዚህ ንብረቶች ከአንድ ሰው ወደሌላ ሰው ሲዘዋወሩ ሁልጊዜ “ከመቅደላ የተወሰዱ” መባላቸው አይቀርም። ለእነሱ እንደ ጀግንነት!! ማለት ነው። በእኛ በኩል የፈረሰውንም ለመሥራት፣ የጠፋውንም ለመፈለግ ያለው ተነሣሽነት ወደሩ እስከ አሁን አልታሰበም። በአፍሮሜት የተወሰኑ ጥረቶች ተደርገው የተወሰነ ውጤት ታይቶ ነበር። ከዚያ በኋላስ? የወጣውን ከማስመለስ ጎን ለጎን የፈረሰውን ለመሥራት፣ የተቃጠለውን የመድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን መልሶ ለመገንባት ምን ተደርጓል?

 ይህንን ነገር ልብ ብሎ ለሚያየው የተለያዩ አንድምታዎችን ያሳያል። አንደኛ ለራሳችን የማንነት መገለጫ ቅርሶች የሰጠነው ግምት፤ ሁለተኛ ለሀገራዊው ሥነ ጥበብ ያሳየነው አነስተኛ ፍላጎት ውጤትና ሌሎቹንም። በመቅደላ የጠፋው ቅርስና ንብረት አንገብጋቢነት ወርቅ ወይም ብር መሆኑ ሳይሆን ትልቁ ጉዳይ በወርቅና በብር የተሠራው ጥበብ ነው። ለምሳሌ የዐፄ ቴዎድሮስ ዘውድ እየተባለ በብዙ ሜዲያዎች የሚታየው ዘውድ በቤተ ክርስቲያን እቴጌ ምንትዋብ የተጠቀሙበት የዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ምስልና የነቢያት የካህናተ ሰማይ ምስል የተሠራበት ከወርቅ ብቻ በጎንደር የተሠራ አስደናቂ የጥበብ ውጤት ነው። የጠፋው የአቡኑ አክሊልና የዕጣን ማጠኛ ጽንሐሕ፣ በውሕድ ማዕድን የተሠሩና ጥበቡ የመጠቀ ምሳሌያዊ ትርጉማቸው የረቀቁ ንዋያት ናቸው። የእቴጌ ጥሩ ወርቅ የሐር ቀሚስ ከሐርነቱ በላይ በአንገት በኩል ዙሮ የትከሻ ሙሉ ጥልፍ ከደረት እስከ አብራክ በሚደርስና በኪሩብ ክንፍ ምስል በረቂቅ ድርብ የጌጥ ስንስል ሐረግ የሚወርድ ሆኖ በመጨረሻው በጣም ረቂቅ በሆነ መስቀል የተቋጨ፣ እጅጌዎቹ ርስ በርሱ በሚናበብ ሥነ ጥበብ ያጌጡ የክብር ልብሶች ጥበብ ያለተተኪ ቀርተዋል። በርካታ የገበታ ሥዕሎች፣ የእጅ፣ የአንገት፣ የመጾር መስቀሎች፣ የዕጣን ሙዳይ፣ መንበርና አትሮኖስ ሳይቀር፣ በትሮቹ ጽዋዎቹ፣ ጋሻና ጦሩ፣ እነሱ ከነገሩን ውጭ እኛ በቁጥር የማናውቃቸው ብርቅየ የብራና መጻሕፍት ሁሉ ሀገራዊ ጥበብና ዕውቀት የያዙ ናቸው።

ለማጠቃለል ያህል የሚቆጨው ጉዳይ የጠፋውና ያልተመለሰው ቅርስ ብቻ ሳይሆን የምርቱ ምንጭ የሆነው ሀገራዊ ሥነ ጥበብም እንዲሁ አብሮ መጥፋቱ ነው። እንደ “ኵርዓተ ርእሱ” ዓይነት የገበታ ሥዕሎች የሚሣሉበት ዘመን ሙሉ በሙሉ ቀርቶ፣ እጅ ሥራ ተትቶ ገበያው በሕትመት ሥራዎች ተጥለቅልቋል። ጥበቡ ሀገራዊ ምንጩ ሲደርቅ የሌላ ሀገር ጥበባዊ ውጤት ተገዥ ስንሆን ምርቱን ብቻ ሳይሆን የምርቱ አስተሳሰብና ትርጉም ተገዥ እንሆናለን፣ የራሳችን የምንለው የጥበብ ነገር አይኖረንም። ስለዚህ የጠቢባን ሥራ መፍታትና ለወደፊትም አዳዲስ ጠቢባንን የማግኘት ወኔን ያከስማል። ከዚህ ጀምሮ ስለ ራስ ገዝ ኢኮኖሚ፣ ስለ ጥበባዊ ሥራ ፈጠራ ለማውራት መንገዱ በመጠኑም ቢሆን ትንሽ አቀበት ይሆናል። ስለዚህ ለጠፋው የሀገር ጥበብ ከመቆጨትና ከመጣር ጎን ለጎን አሁንም ያለአስተዋሽ ለቀረው ሀገራዊ ሥነ ጥበብም ትኩረት እንስጥ።

 እጅግ የተከበሩ ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የ“ኩርዓተ ርእሱ” ትርጉም

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top