አጭር ልብወለድ

አንድ የመኸር ወቅት ሌሊት

በማክስሲም ጎርኪ

ትርጉም – በመኮንን ዘገዬ

አንድ ጊዜ በመኸር ወቅት እንዲህ ሆንኩላችሁ። በወቅቱ በጣም ደስተኛ አልነበርኩም። ምን አለፋችሁ በአጠቃላይ አልተመቸኝም ነበር። ያለሁበት ከተማ ገና አሁን ነበር የደረስኩት። ደሞ የማዉቀዉ ሰዉ አልነበረኝም። ኪሴ ወስጥ አንድም ሳንቲም የለም። ማደሪያም አልነበረኝ።

 ባለፉት ጥቂት ቀናት እንደትርፍ የምቆጥራቸዉን ልብሶቼን ሸጫቸዋለሁ። በከተማዉ በኩል አድርጌ የስቴ ወደምትባል ቀበሌ ሄድኩ። ቦታዉ በጉዞ ወቅት በእንፋሎት የሚሠሩ መርከቦች ጩኸት የማይለየዉ የሥራና የሁካታ ቦታ ነዉ። አሁን ግን ጭር ብሏል። ምክንያቱም የጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ነዉ ያለነዉ።

በቀዝቃዛዉ አሸዋ ላይ እየተራመድኩ ትክ ብዬ መሬት መሬት እመለከታለሁ። የወደቀ ቁራሽ ዳቦ የማገኝ መስሎኝ። ብቻዬን የሰዉ ዘር በማይታይባቸዉ ህንፃዎችና መጋዘኖች መካከል ተጓዝኩ። የተራበዉ ሆዴን የሚያጠግብ የሚበላ ነገር ባገኝ ብዬ እያሰብኩ። መቼም በዚህ ዘመን የአእምሮ ርሀብ ከሥጋዊ ርሀብ በበለጠ ፍጥነት መርካት የሚችልበት እንደሆነ የታወቀ ነዉ። መቼም በከተሞች ስትዘዋወር ደስ በሚሉ ሕንፃዎች መከበብህ የማይቀር ነዉ። ዉስጣቸዉም ቢሆን ተራ በሆኑ ዕቃዎች እንዳልተሞላ በመተማመን መናገር ትችላለህ።

ሕንፃዎቹን ስታያቸዉ ስለ ኪነ-ሕንፃ ፣ ስለአካባቢ ንፅሕና አና ስለሌሎች ትላልቅ ጉዳዮች ስሜትህን የሚቀሰቅስ ነገር ይሰማሃል። የሚሞቅና ንፁሕ ልብስ የለበሱ ሰዎች ልታገኝ ትችላለህ። በጣም ትህትና የተላበሱ ናቸዉ።

ግን ወዲያዉ ትተዉህ በዘዴ ከአንተ ገሸሽ ይላሉ። ምክንያቱም የአንተን አሳዛኝ የሕይወት እዉነታ ማየት አይፈልጉም። ይሁን እንጂ፣ የተራበ ሰዉ አእምሮ በደንብ ከበላና ከጠጣ ሰዉ አእምሮ በጣም የዳበረ፣ የበለፀገና ጤናማ ነዉ።

ምሽቱ እየተቃረበ ነዉ፣ዝናቡ ይዘንባል፣ከሰሜን አቅጣጫ ሃይለኛ ነፋስ ይነፍሳል። በሕንፃዎቹ መካከል፣ በሱቆች መካከል፣ በመጠጥ ቤቶች መካከል ያፏጫል። የወንዞችን ማእበል እየጋለበ አረፋ ያስደፍቃቸዋል። ወንዙ የክረምቱን እየቀረበ መምጣት ያወቀ ይመስላል።

 ሰማዩ በጣም ከብዶታል፤ በዚያ ላይ ጨልሟል። ስስ ዝናብ ያለማቋረጥ ይዘንባል። በነፋሱ ሃይል የተገለበጠችዉ ጀልባና በነፋሱ የሚሰቃዪት ያረጁ ዛፎች በቀዝቃዛዉ ነፋስ መድረሻ አጥተዋል። ብቻ በዙሪያዬ ያለ ማንኛዉም የማየዉ ነገር ወድሟል፣ ተራቁቷል፣ ሞቷል።

ሰማዪ ደግሞ ማለቂያ የሌለዉ እምባዉን ያነባል። በጣም ቀዝቃዛ ሞት ከፊቴ እየጠበቀኝ ነዉ። የዚያን ጊዜ አሥራ ስምንት አመቴ ነበር – ጥሩ ዕድሜ ላይ ነበርኩ! ለማንኛዉም በሚዘቅዘዉ አሽዋ ላይ ጉዞዬን ቀጠልኩ። ጥርሶቼ አየተንገጫገጩ በላዬ ለሚፈሰዉ ቅዝቃዜና አንጀቴን ለሚሞረምረኝ ርሃብ አክብሮታቸዉን እየገለፁ ነበር።

የሚበላ ነገር አገኛለሁ ብዬ አንድ ባዶ ሳጥን ስመለካከት ከሳጥኑ ኋላ ድንገት አንድ በዝናቡ ልብሷ የበሰበሰ ሴት ቁጭ ብላ ቁሻሻ ስታገለብጥ አየሁ። ልብሷ ትከሻዋ ላይ ተጣብቋል። ወደ ሴትየዋ ተጠጋሁና ምን እንደምታደርግ ለማወቅ ሞከርኩ። አሻዋዉን በእጅዋ እየጫረች ጉድባ ነገር አድርጋዋለች። “ለምንድንዉ የምትቆፍሪዉ?” በማለት ወደ አጠገቧ ተጠግቼ ተቀመጥኩና ጠየቅኋት። ደንግጣ እንደ መጮህ አለችና ከተቀመጠችበት ተነስታ ቆመች። ቆማ ግራጫ የመሰሉ ዓይኖችዋን አፍጣ እያየችኝ ነዉ። የፈራች መሆኗ ከዓይኖቿ ያስታወቃል። እድሜዋ ከኔ ዕድሜ አይበልጥም። ፊቷ የደስደስ አለዉ። ብቻ በመጥፎ አጋጣሚ ሳይሆን አይቀርም ሦስት ትላልቅ ጠባሳዎች ተጋድመዉበታል። ጠባሳዎቹ ስፋታቸዉ እኩል ነዉ። ሁለቱ ጠባሶች ከዓይኖቿ ሥር ናቸዉ። አንደኛዉ ጠባሳ ደግሞ ከአፍንጫዋ ከፍ ብሎ ግንባሯ ላይ ነዉ የተጋደመዉ። የሰዉ አካል በማበላሸት የተካነ የጥሩ ሠዓሊ ሥራ ነዉ የሚመስል። ልጅቷ እየተመለከተችኝ ነዉ። ቀስ በቀስ ዓይኗ ላይ ይነበብ የነበረዉ ፍርሃት እየጠፋ ሄደ።

 አሻዋዉን ከእጇ ላይ አራገፈች። ከጥጥ የተሠራዉን ኮፍያዋን አስተካከለች። ጎነበስ አለችና “እንደ ሚመስለኝ ከሆነ አንተም የሚበላ ነገር የምትፈልግ? ከሆነ ና ቆፍር እኔ እጄን ደክሞኛል” አለችኝ።

መቆፈሩን ተያያዝኩት። እሷም ትንሽ ቆየችና አጠገቤ ቁጭ ብላ ታግዘኝ ጀመር። ፀጥ ብለን መቆፈራችንን ቀጠልን። በጠቅላላ አሳባችን ሳጥኑ ዉስጥ ምን ሊኖር እንደሚችል ማሰብ ነበር። ምሽቱ እየተቃረበ መጣ። ግራጫማዉ ቀዝቃዛ ጭጋግ በዙሪያችን ጥቅጥቅ እያለ ሄደ። ማእበሉ ከበፊቱ የበለጠ ጩኸት አሰማ። ዝናቡ የሳጥኑ ክዳን ላይ በሃይልና በፍጥነት ዘነበ።

 አንድ ቦታ አንድ የምሽት ጠባቂ የማስደንገጫ ቆርቆሮዉን ያንኳኳ ጀመር። “ሳጥኑ መጨረሻ አለዉ እንዴ?” በማለት በለስላሳ ድምፅ ረዳቴ ጠየቀች። ምን ማለት እንደፈለገች አልገባኝም ነበር እና ዝም አልኩ።

 “ሳጥኑ መጨረሻ አለዉ እንዴ ነዉ ያልኩ – ካለዉ ለመስበር የምናደረገዉ ሙከራ ከንቱ ነዉ። አሁን ዙሪያዉን እየቆፈርን ነዉ። ምንም ሳናገኝ ወፍራም ካርቶን ብቻ ነዉ ያገኘነዉ። እንዴት አድርገን ቁልፉን እንገንጥለዉ። የማይረባ ቁልፍ ነዉ።”

መችም ጥሩ ሃሳቦች የሴቶችን ጭንቅላት አልፎ አልፎ ነዉ የሚጎበኙት። እኔ ደሞ ለጥሩ ሃሳቦች ሁልጊዜ ከፍተኛ ዋጋ አሰጣለሁ። ደሞ እስከምችለዉ ድረስ አጠቀምባቸዋለሁ። ሳጥኑ የተቆለፈበትን ቁልፍ አገኘሁና ገነጠልኩት። ረዳቴ ወዲያዉ ጎንበስ አለችና የተከከፈተዉ ሳጥን ዉስጥ ገብታ እንደ እባብ ተጠቀለለች።

 “አንተ ብረት ነህ!”

በዛሬ ጊዜ ከሴት ልጅ የማገኘዉ ቅንጣት ታህል ሙገሳ ከጥንታዊያኑና ከዘመናዊያኑ የመናገር ችሎታ ካላቸዉ ወንዶች ከማገኘዉ ሙገሳ የበለጠ ነዉ። የዚያን ጊዜ የፍቅር ስሜት በዉስጤ አልነበረኝም። ጓደኛዬ ለሰጠችኝ ሙገሳ ምንም ትኩረት ሳልሰጥ

 “እንዴት?” በማለት ድርቅ ያለ ጥያቄ ነበር ያቀረብኩላት። አሰልቺ በሆነ ቅላፄ ሳጥኑ ዉስጥ ምን እንዳለ መዘርዘር ጀመረች። ቅርጫት ሙሉ ጠርሙሶች፣ወፍራም ፀጉራም ልብስ፣ የፀሐይ መከላከያና ባልዲ ዉስጡ እንዳለ ነገረችኝ። እሚገርመዉ ነገር እነዚህ ሁሉ የሚበሉ ነገሮች አይደሉም። ተስፋዬ ብን ብሎ ሲጠፋ ተሰማኝ። ግን በድንገት በደስታ ፈነደቀች።

 “የምንፈልገዉ ነገር ተገኘ !”

 “ምን?”

“ዳቦ ነዋ … ግን አርጥብ ነዉ … በልያዝ !”

እግሬ ሥር አንድ ዳቦ ዱብ አለ። ከዚያ አሷም አንድ ወሰደች። ዳቦዉን አንዴ ገመጥኩለትና አፌን ሞልቼ ማኘክ ጀመርኩ።

ጨምሪልኝ!

… እዚህ መቆየት የለብንም … ወዴት እንሂድ?

ዙሪያዉን ተመለከተች … ጨልሞ ነበር፣ አርጥብ ነዉ፣ ዝናቡ ያጉረመርማል።

“ተመልከት! እዚያጋ እንድ ጀልባ ተገልብጣለች … ወደዚያ እንሂድ።”

“እንሂድ!” አለኩና ሄድን። እየሄድን ዳቦአችንን ጉንጫችን እሰኪሞላ ድረስ እንገምጥ ነበር …

ዝናቡ በጣም እየባሰበት ሄደ፤ ወንዙ አጓራ፤ ከሆነ ቦታ ረጅም የቀልድ የሚመስል ፉጨት ያስተጋባል። አንድ ማንንም የማይፈራ ሃያል ቁልቁል በምድር ያሉ ተቋሞችን እየተመለከተ የሚያፏጭ ይመስላል። ከፉጨቱ ጋር አስፈሪዉ የመከር ነፋስ እና አኛ ጀግኖቹ አብረን ነን። ይሄ ፉጨት ፍርሃት ጨመረብኝና ልቤ ይመታ ጀመር። ይሁን እንጂ በስስት ስሜት ዳቦዉን መብላቴን አላቆምኩም። በግራ ጎኔ በኩል ያለችዉ ወጣት እርምጃዋን ከኔ እርምጃ ጋር አስተካክላ እየገሰገሰች ነዉ።

 “ስምሽ ማነዉ?” በማለት ጠየቅኋት።

 “ናታሻ እባላለሁ” በማለት በአጭር መለሰችልኝ፣ ዳቦዋን ድምፅ አስኪሰማ እያኘከች። ትኩር ብዬ አየኋት። ልቤን አመመኝ፤ ከዚያ ፊት ለፊቴ ወደ አለዉ ጭጋግ አፈጠጥኩ። የዕጣ ፈነታዬ ገፅታ በፈገግታ፣ በኩራትና በቀዘቀዘ ስሜት የሚስቅብኝ መስሎ ታየኝ። ዝናቡ ግንዶቹን ያለማቋረጥ በሃይል እየመታቸዉ ነዉ። ስሱ ወጨፎ የሀዘንና የትካዜ ስሜት ይፈጥራል። ንፋሱ ቁለቁል እየነፍስ ሲያፏጭ የጀልባዉን የታችኛዉን ክፍል ሲመታዉ የተሰነጠቁ እንጨቶችን ሲያወዛዉዛቻዉ የሚፈጥሩት ድማፅ የሚረብሽና የሚጫጫን ነዉ። የወንዙ ማእበል በተከታታይ እየተወረወረ የወንዙን ዳርቻ ይገርፈዋል። ድምፁ ደግሞ የሚሰለችና ተስፋቢስ ነዉ። ልክ አንድ መጥፎ ነገር የሚናገር ይመስላል። ደሞ የዝናቡ ድምፅ ከማእበሉ ድማፅ ጋር የተዋሃደ ይመስላል። እኛ ተጠልለን የቆምንበት እንጨት ምቾት የለዉም። ጠባብና እርጥብ ነዉ። ትናንሽ የዝናብ እንክብሎች ይንጠባጠባሉ። እንግዳ ነፋስ ዘልቆት ይገባል። ብርዱ እያንቀጠቀጠን ፀጥ ብለን ተቀመጥን። መተኛት እንዳለብኝ አሰብኩ። ናታሻ ጀልባዉን ተደገፈችና እንደ ትንሽ ኳስ ተጠቀለለች። ጉልበቶቿን በእጆቿ እቅፍ አድርጋ አገጭዋን ጉልበቷ ላይ አስደግፋ ዓይኗን አፍጥጣ ወደ ወንዙ ትመለከታለች። ምንም እንቅስቃሴ አታደርግም። ዝም ብላለች። ይህ ሁኔታዋ ቀስ በቀስ በዉስጤ እንድፈራት አደረገኝ። ላናግራት ፈለኩ ግን አንዴት እንደምጀምር አላወቅኩም።

“ምን የተረገመ ነገር ነዉ ሕይወት!”

 በማለት በግልፅ ተናገረች። ቅር በመሰኘት አልነበረም የተናገረቻዉ። በፍፁም እምነት ነበር የተናገረችዉ። በቃላቷ ዉስጥ በጣም ብዙ ቅሬታ አልባ ስሜት ነበረበት። ይቺ ፍጥረት ያሰበችዉ እንደተረዳችዉ ነዉ። አሰበችና በመቀጠል ማጠቃለያዋን በግልፅ ተናገረች። ማጠቃለያዋን ደግሞ ራሴን መቃረን እንዳይሆንበኝ ልቃወመዉ አልደፈርኩም- ዝም አልኩ። እሷ ደሞ አጠገቧ እንደ ሌለሁ ቆጥራ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ሳታደርግ ቁጭ አለች።

 “ ብናማርር … ምን አለበት … ?”

በማለት ቀጠለች ናታሻ፣ አሁን ቀስ ብላ እያሰበች ነዉ የተናገረች። ግን አሁንም ቢሆን ንግግሯ በወስጡ ቅሬታ የለበትም። ግለፅ ነዉ። ይቺ ሰዉ ከራሷ ሕይወት ተነስታ የደረሰችበት ማጠቃለያ ነዉ። የዚህ ሃሳብ እዉነትነት ለኔ ልገልፀዉ ከምችለዉ በላይ አሳዛኝና የሚያሳምም መሆኑ ተሰማኝ። ስለዚህ ከዚህ በላይ ዝም ካልኩ መችም በእዉነት ማልቀሴ የማይቀር ነዉ። ሴት ልጅ ፊት ደግሞ ይህን ማድረግ አሳፋሪ ነዉ። ምክንያቱም እሷ ራሷ እንኳ አላለቀሰችም። እና አሁን ላናግራት ወሰንኩ።

 “ማነዉ እንደዚህ አድርጎ የፈነካከተሽ?”

 በማለት ጠየቅኳት። ለጊዜዉ ከዚህ የተሻለ የምጠይቃት ነገር አልነበረኝም።

 “ፓሽካ ነዉ እነደዚህ ያደረገኝ”

 በማለት መለሰችልኝ በሰለቸና ለዛ በሌለዉ ድምፅ።

“ምንሽ ነዉ?”

 “ፍቅረኛዬ ነዉ … ዳቦ ጋጋሪ ነዉ።”

 “ ሁልጊዜ ነዉ የሚመታሽ? “

“ በሰከረ ቁጥር ይመታኛል!”

ከዚያ ድንገት ወደኔ ዞር አለችና ስለ ፓሽካና ስለእሷ ግንኙነት ታወራኝ ጀመር።

 “ፓሽካ ሥራዉ ዳቦ መጋገር ነዉ። ፂሙ ቀይ ነዉ። ባንጆ በደንብ መጫወት ይችላል።”

እሷን ለመጠየቅ ነበር የመጣዉ። ቀልድ ስለሚያዉቅ በደንብ አድርጎ አዝናንቷታል። 

አስራ አምስት ሩብል የሚያወጣ ሰደርያ ለብሶ ነበር። ያደረገዉ ቡትስ ጫማ በለጠጉር ነዉ። በዚህ ምክንያት በፍቅር ወደቀችለት። ገንዘብ “ተበዳሪዋ” ሆነ። በዚህ ምክንያት ሌሎች ጓደኞቿ ገንዘብ ሲሰጧት ይወስድባታና ይጠጣበታል:: ከዚያ እሷን ይመታታል። ይህ ሁሉ ምንም አልነበረም ግን ይባስ ብሎ ዓይኗ እያየ ሌሎች ሴቶች ያማግጣል።

 “ታዲያ ይህ ድርጊት ከስድብ አይቆጠርም?”

“እኔ ከሌሎች ሴቶች በምንም አላንስም። ከጀርባዬ እየቀለደብኝ እንደሆነ ገብቶኛል። ከትናንት በስትያ እመቤቴን አስፈቅጄ ፈቃድ በመዉሰድ ወደ እሱ ሄጄ ነበር። ዲምካ አብራዉ ቁጭ ብላ ስትጠጣ አገኘኋት። እሱም በጣም ስክር ብሎ ነበር። “አንተ የማትረባ!” ብዬ ሰደብኩት። እሱ ደግሞ በርግጫ እየመታ ፀጉሬን ይዞ መሬት ለመሬት ጎተተኝ። ቀጥሎ ያደረገኝ የከፋ ነበር። ጠቅላላ የለበስኩትን ልበስ አበላሸቶብኝ አሁን እንደምታየኝ ሁኛለሁ! እመቤቴ ዘንድ ምን ለብሼ እንደምሄድ አላወቅም? አዲስ የገዛሁትን ጃኬት ቀዳደደብኝ። ሻሼን ከራሴ ወሰደዉ። አቤት አምላኬ እንዴት ታደርገኛለህ! አሁን ምን ይዉጠኛል?”

 አለችና በድንገት መነጫነጭ ጀመረች። ነፋሱ ያሰገመግም ጀመር። የበለጠ እየቀዘቀዘና እያጓራ ሄደ። እንደገና ጥርሶቼ ይደንሱ ጀመር። ከብርዱ ለማምለጥ ራሷን አጥፍጥፍ አደረገች። ወደ እኔ በጣም ተጠጋች። እና የዓይኖቿ ብርሃን በጨለማዉ ታየኝ።

 “እናንተ ወንዶች ምን አይነት እርጉሞች ናችሁ! ብችል ሁላችሁንም በአንድ ምጣድ ባንጨረጨርኳችሁ፣ በከታተፍኳችሁ ነበር። አንድ ወንድ ቢሞት አፉን ከፍቼ ምራቄን እተፈበታለሁ እንጂ ፍፁም አላዝንለትም። የማትረቡ ማጥማጦች! ተለማማጮች! ፈሪ ዉሻ ይመስል ጭራችሁን ትቆላላችሁ። እኛ ጅሎቹ ደግሞ ራሳችንን አሳልፈን ለእናንተ እንሰጣለን። ጥፋቱ የኛ ነዉ እናንተ ምን ታደርጉ! ወዲያዉ ጥላችሁ እንደ ቆሻሻ መጥረጊያ ትረጋግጡናላችሁ። ምስኪን ከርታቶች።”

ከፍ ዝቅ አድርጋ ረገመችን። ግን ጭካኔ፣ ክፉ ምኞትና ጥላቻ በምስኪን ከርታቶች ላይ አልነበረበትም። የንግግሯ ቅላፄ ከቁምነገሩ ጋር የሚጣጣም አይደለም። ንግግሯ የተረጋጋ ነዉ። ለማንኛዉም ሁኔታዋ አንድ በደንብ ከተቀናበረና መጥፎ ስሜት ለመፍጥር ከተዘጋጀ አሁን ድረስ ደጋግሜ ከማነበዉ ንግግር የበለጠ ጠንካራ ስሜት ፈጠረብኝ። ለመሞት በመጣጣር ላይ የሚገኝ ሰዉ ስቃይ በቃላት ከሚዘረዘር የሞት ገለፃ የበለጠ እዉንና አሰቃቂ ነዉ። ለማንኛዉም በአሁኑ ሰዓት ከጎረቤቴ ንግግር ይልቅ በብርዱ ነዉ የበለጠ የተሰቃየሁት። ቀስ ብዬ አጉረመረምኩና ጥርሶቼን አፋጨሁ። በድንገት ሁለት እጆች አንዱ አንገቴ ላይ፣ አንዱ ፊቴ ላይ ሲያርፉ ተሰማኝ። አብሮ አንድ ለስላሳ የወዳጅ የመሰለ ድምፅ እንዲህ የሚል ጥያቄ አቀረበልኝ።

 “ምንድ ነዉ ህመምህ?”

 እኔ ግን ጥያቄዉ የቀረበልኝ ከሌላ ሰዉ እንጂ ከጥቂት ጊዜ በፊት ወንዶችን ትኮንን ከነበረችዉ ከናታሻ ነው ብዬ ማመን አልቻለኩም። እሷ ነበረች። በፍጥነት መናገር ጀመረች።

“ምንድነዉ የሚያምህ?”

 “በረደህ እንዴ?”

 “ቀዘቀዘህ እንዴ?”

 “ምን አይነት ሰዉ ነህ ዝም ብለህ እንደ ትንሽ ጉጉት እዚህ ትቀመጣለህ! ለምን ቀደም ብለህ የበረደህ መሆንክን አትነግረኝም ነበር። ና … እዚህ ተኛ … ዘርጋ እኔ ደግሞ ከጎነህ እተኛለሁ! እንዴት ነዉ? በል እቀፈኝ? ጥብቅ አድርገህ እቀፈኝ! እንዴት ነዉ? አሁን ይሞቅሃል። ከተሟሟቅን በኋላ አንደገና ጀርባችንን ተሰጣጥተን እንተኛለን። ከዚያ ሌሊቱ ቶሎ ይነጋልናል። እወነቴን ነዉ የምልህ፣ ቆይ እንዴት እንደሚሞቅህ ታያለህ። አንተም ጠጥተሃል መሰለኝ? እራስህን ስተሃል ማለት ነዉ … ወይኔ?”

 ግን ምንም አይደል። አስደሰተችኝኮ … አበረታታችኝኮ። ምን አለ ሦስት ጊዜ የተረገምኩ ብሆን! ምን አይነት ያልተጠበቀ ክስተት ነዉ የገጠመኝ! እስቲ አስቡት! እዚህ ሁኜ ስለ ሰዉ ልጅ እጣ ፋንታ፣ ማህበረሰቡን እንደገና እንዴት ማደራጀት እደሚገባ፣ የፖለቲካ አብዮት አስፈላጊ ስለመሆኑ፣ጠቃሚነታቸዉ ወደር የማይገኝላቻዉ መፃሕፍት እያነበብኩ ንቁ የለዉጥ ሃይል ለመሆን እየሞከርኩ ነዉ። አሁንም ቢሆን በከፊል ግቤን የመታሁ ይመስለኛል። እስካሁን የገባኝ ነገር ቢኖር ተቀናቃኝ የሌለበት የመኖር መብት ያለኝ መሆኔን ነዉ። አስፈላጊዉ መብት አለኝ፣ የሕይወት ህልዉናዬን መኖር እንድችል። ይሄ ማለት እኔ ሙሉ ችሎታ አለኝ ታሪካዊ ድርሻዬን ለመከወን። አሁን አንዲት ሴት ከብርድ ልትገላግለኝ በሰዉነቷ ሙቀት እየሰጠችኝ ነዉ። ይቺ ሴት ምስኪን፣ የተጎሳቆለች፣ ተሳዳጅ ፍጡር፣ በሕይወት ቦታና ዋጋ የሌላት ናት። እኔ ከእሷ እንዴት እርዳታ መግኘት እንደምችል ፈፅሞ አላሰብኩም ነበር እሷ ሯሷ ተነሳስታ እስክትረዳኝ ድረስ። እኔ ግን አሁንም እንዴት ልረዳት እንደምችል አላዉቅም። አሁን ይህ ሁሉ የደረሰብኝ ነገር በእዉኔ ሳይሆን በመጥፎ አሰቃቂ ህልም ነዉ ብዬ ለማሰብ ዝግጁ ነበርኩ። ግን ምን ያደርጋል! እንደዚህ ማሰብ አልችልም። ቀዝቃዛ የዝናብ ጠብታ እያራሰኝ ነዉ፣ ሴቷ ተጣብቃብኛለች፣ ከዉስጧ የሚወጣዉ ትንፋሽ በመጠኑ የቮድካ ሽታ ቢኖረዉም ፊቴን እያሞቀዉ ነዉ። ነፋሱ ያጓራል፣ ዝናቡ ይወርዳል፣ ማእበሉ ይወረወራል። ሁለታችን የተጣበቅን አስክንመስል ተቃቅፈናል ብርዱ እያንቀጠቀጠን ነዉ። ይህ ሁሉ ሁኔታ እዉን የሆነ ነገር ነዉ። አርግጠኛ ነኝ ማንም ይህን እዉነታ የሚያሰቃይና አስፈሪ ህልም ነዉ ሊል አይችልም። ናታሻ በዚህ ሁሉ ሁኔታ መሃል አንዴም ሳታርፍ ስለተለያዩ ነገሮች ታወራለች። ስታወራ ደግነት በተሞላዉ የሴትነት ርህራሄ ነዉ። ከለስላሳ ድምፅዋና ከደጋግ ቃሎቿ ጀርባ ትንሽ እሳት በዉስጤ መቀጣጠል ጀመረ። እና ልቤ ዉስጥ አንድ ነገር ሲቀልጥ ተሰማኝ። ከዚያ ከዓይኖቼ እንባዬ እንደ በረዶ ዱብ ዱብ እያለ ከዚህ ሌሊት በፊት ልቤ ዉስጥ ተጠራቅሞ የኖረዉን ክፋት፣ጦርነት፣ ሃዘን፣ መቆሸሽ ያጥብልኝ ጀመር። ናታሻ ከስቃይ ገላገለችኝ።

 “ና፣ና፣ በቂ ነዉ፣ትንሽ ይበቃሃል! እግዜር ሌላ እድል ይሰጥሃል … ራስክን አስተካክለህ እንደገና በሚገባህ ቦታ መቆም ትችላለህ። ከዚያ ነገሮች ሁሉ ይስተካከላሉ።”

 አሁንም እየሳመችኝ ነዉ … ደጋግማ ደጋግማ ሳመችኝ … ልቤ አስኪጠፋ ሳመችኝ … ግን ከኔ ምንም ፈልጋ አይደለም … ሴት ልጅ ስትስመኝ የመጀመሪያ ጊዜዬ ነበር። ምርጥ የሆነ አሳሳም ነበር የሳመችኝ። ምንም አላደረኩላትም በነፃ ነዉ የሳመችኝ።

 “ንቃ እንደዚህ አትሁን አስቂኝ ነህ! በነገዉ እለት ማደሪያ ካላገኘህ እኔ እፈልግልሃለሁ።”

እነዚህ ተስፋ ሰጪ ቃሎችዋ በህልሜ የምሰማቻዉ ነበር የሚመስሉኝ። እንደተቃቀፍን እስኪነጋ ተኛን። ሲነጋ ከተኛንበት ተነስተን ወደከተማ ሄድን። ከተማ ስንደርስ ተሰናብተን ተለያየን። ከዚያ ወዲህ ተገናኝተንም አናወቅ። እኔ ግን አንድ ዓመት ሙሉ በየስርቻዉና በየጉራንጉሩ ፈሊግያት ነበር። የተረኩላችሁን የመከሩን ሌሊት አብራኝ ያሳለፈችዉን ደጓን ናታሻን ፈፅሞ ላገኛት አልቻልኩም። 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top