ፍልስፍና

በፍልስፍና መንገድ የሚጠቅመኝን ሳላውቅ ኖርኩኝ!

ድህነትና እድል በመንገዴ እየቆሙ ጉዞዬ ሁሉ ሸካራ እንዲሆን አድርገውታል። ብዙውን የህይወቴ ዘመን ያሳለፍኩት ግሳንግስ ነገር ስሰበስብ ነው። ተገቢና ጠቃሚ የሆነ ትምህርት የቱ እንደሆነ ያወቅኩት ሁሉም ነገር ካለፈ፤ ከመሸ በኋላ ነበር። እንደ ገጠሯ ልጃገረድ እድሜዬን መልስልኝ ብል የማይሆንልኝ ሆነ። ጊዜ ወደፊት እንጂ ወደኋላ ማጠንጠኛ የለውምና። የገጠሯ ልጃገረድ ያደረገችው እንደዚህ ነው። ከአንዱ እረኛ ጋር ስትዳራ

“በመጨረሻ ዘመነ ካፒታሊዝም መጣ! የሰውን ክብር በሚያወጣው ዋጋ የሚመዝን፣ የባርነት ዘመን መልኩን ቀይሮ መጣ። በባርነት ዘመን የሰው ልጅ ተገዶ በኃይል እየተያዘ ነበር የሚሸጠው። አሁን ግን በራስ ፈቃደኝነት፣ ከአስፈሪው የኑሮ መከራ ለማምለጥ በወዶ ገባነት፣ ሰው ሁሉ ራሱን ለገበያ ያወጣል።”

ድንግልናዋን ታስወስዳለች። ይሄ ነገር የኋላ ኋላ በቤተሰቦቿ ዘንድ መሰማቱ አልቀረም። እናም ወላጆቿ ሲቆጧት ጊዜ የተወሰደው ድንግልና የሚመለስ መስሏት እረኛውን ጠርታ “ያን ባለፈው የወሰድከውን ነገር አባትና እናቴ ስለተቆጡ መልስልኝ” ትለዋለች። እረኛው ግን ፍቅር ብቻ ሳይሆን ቁም ነገርም አዋቂ ኖሮ፦

 “እናትሽ ወንድምሽ

ቢፈርጡ እንደ እምቧይ

አባትሽ ቢዘሉ ቢደርሱ ሰማይ፣

 የፈሰሰ ውሃ ይታፈሳል ወይ?”

ብሎ ቁርጧን ነገራት ይባላል። የእኔም ነገር እንደዚያ ነው። የእውቀት ብዛት ትካዜ ያመጣልና እንዲል መጽሐፉ ከንባብ ያገኘሁት ነገር ሀዘንና ትካዜ፣ መሸበትና መገርጀፍ ሆነ። የኮረዶችን ነገር ልተወውና ጡታቸው ሁለት ልጅ እንዳሳደገ የሚያሳብቅባቸው ሴቶች ሳይቀሩ “አባባ ሰዓት ስንት ሆነ” እያሉ ይጠይቁኝ ጀመር። እውነታቸውን ነው። አለባበሴ ራሱ ጡረታ የወጣ አስተማሪ ነው የሚያስመስለኝ። በጠዋቱ የእድሜ ክፍል ብዙ ሲያዩዋቸው የሚያማምሩ ሰፋፊ ጎዳናዎች ከፊት ለፊቴ ነበሩ። የስህተት ጎዳናዎች መሆናቸውን አላወቅኩምና ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከባርነት ወደ ነፃነት የሚያደርሱኝ መስሎኝ በእነዚያ መንገዶች ተንከራተትኩ። ነገር ግን፣ ከጨለማ ወደ ጨለማ፤ ከባርነት ሠንሠለት ወደ ሌላ የባርነት ሠንሠለት አሸጋገሩኝ እንጂ ወደተመኘሁት የነፃነት አለም አላደረሱኝም።

ከአንዱ ሰፊ ጎዳና ወደ ሌላው ሰፊ ጎዳና፣ ከአንዱ አንዱ እንደሚሻል ወይም እንደማይሻል በደንብ ረጋ ብዬ ሳላረጋግጥ እየቀያየርኩ ተጓዝኩባቸው። መከራዬን አበዙት፣ ስቃዬን አረዘሙት እንጂ የቀደመው ስህተቴን የሚያርሙ አልነበሩም።

 በዚህ ምክንያት በከንቱ ስንከላወስ ከእድሜዬ ቀትር ላይ ደረስኩኝ። ከዚህ በኋላ ቢያንስ ማምሻዬን እንኳ ማሳመር አለብኝ ብዬ አሰብኩ። ራሴንና አኗኗሬንም ለመቀየር ተነሳሁ። ለምን ቀለል ያለና ብዙ ደመወዝ የሚያስገኝ ትምህርት አልማርም ብዬ ብዙ ጊዜ ሴቶችና ሞልቃቃ የከተማ ልጆች የሚማሩትን የትምህርት ዓይነት መርጬ ለመመዝገብ ወደ አንዱ ዩኒቨርሲቲ ሄድኩ። ለማንኛውም ብዬ ግን አንድ ሦስት የሚሆኑ የትምህርት ዓይነቶችን በአማራጭነት ይዤ ነበር ወደ ሬጅስትራሩ የሄድኩት።

በሬጅስትራሩ መስኮት በኩል ያገኘኋት መዝጋቢ ሴትዮ በእድሜ ብዛት ይሁን በስጋ ብዛት የተሰላቸች ትመስል ነበር! በመሰላቸቷ ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት መመዝገብ የምፈልጋቸውን የትምህርት ዓይነቶች ተመለከተቻቸውና በተቆጣ ፊት “ከአንድ በላይ መመዝገብ አይቻልም” አለችኝ። እኔም “እሺ የእኔ እመቤት” ብዬ የመጀመሪያ ምርጫዬ የሆነውን ብቻ ሞላሁ።

 እንደዚህች ዓይነት ሴት የእኔ እመቤት ከምትሆን ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል። የፊቷ አስጠሊታነት፣ የሰውነቷ ውፍረት፣ የቆዳዋ መለዘዝና የሰውነቷ መፍዘዝ ሬሳ ነው ያስመሰላት። ብዙውን ጊዜ የሰው ልጅ ሲያረጅ አያምርበትም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ይህቺን ሴት መሰሎች ሲያረጁና ከመጠን በላይ ሲወፍሩ ያስጠሉኛል። አሳማ ነው የሚመስሉኝ!

የተመዘገብኩት ትምህርት የመግቢያ ፈተና ነበረውና የምፈተንበትን ቀን ብጠብቅ ብጠብቅ ወሬው ጠፋ። እየተመላለስኩ በየቀኑ ማስታወቂያ እከታተላለሁ። በሌሎች ዲፓርትመንቶች የተመዘገቡት ስም ዝርዝራቸው ወጥቶ ሲለጠፍ፣ እኔ የተመዘገብኩበት ዲፓርትመንት ግን ሊወጣ አልቻለም። ከዚያ መጨረሻ ላይ ይሄ ነገር ቀርቶ ነው ወይስ ምንድን ነው የሆነው ብዬ ለመጠየቅ በቀጥታ ወደ ዲፓርትመንቱ ሄድኩና ኃላፊውን አገኘሁት።

 ኃላፊው ከአለባበሱ ጀምሮ ዘበኛ ነው የሚመስለው። መልኩ አያምር፣ አነጋገሩ አይገባ! እናም ይሄን አስጠሊታነቱን እየታዘብኩ “እንዴት ነው የመግቢያ ፈተና አይወጣም እንዴ?” ብዬ ጠየቅኩት። ኃላፊው በተቀመጠበት ሶፋ ላይ በተዝናና መልኩ ወደፊትና ወደኋላ እየተለጠጠ “ማስታወቂያ ለጥፈናል፣ በተባለውም ቀን ተማሪዎች መጥተው ተፈትነዋል” አለኝ።

 ይህን ሲለኝ ማመን አልቻልኩም። በእርግጠኝነት ማስታወቂያ እንዳልተለጠፈ አውቅ ነበርና፣ በየቀኑ ማስታወቂያ በሚለጠፍበት ሥፍራ ስከታተል እንደነበር አስረዳሁት። በቀላሉ እንደማልፋታው ሲረዳ “ና ከፈለግህ ላሳይህ” ብሎ መስኮቱን ከፈተና አውራ ጣቱን እየጠቆመ የተለጠፈበትን ቦታ አሳየኝ። ማስታወቂያውን ለምን እንዳላየሁት ወዲያው ገባኝ። በሴት ተማሪዎች መፀዳጃ ቤት በር ላይ ነበር የተለጠፈው! እፁብ ድንቅ ብዬ ተገረምኩ።

 እንደእውነቱ ከሆነ ይህን ማስታወቂያ ማየት እችል ዘንድ የሚከተሉት ሦስት ነገሮች መሟላት ነበረባቸው። አንድም የዩኒቨርሲቲው ተማሪ መሆን ነበረብኝ። ይህ ብቻ ግን በራሱ በቂ አይደለም። ሴት ተማሪም መሆን ግድ ይለኛል። የዚህ ዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪ ከሆንኩ ብቻ ነው ወደዚህ መፀዳጃ ቤት ልመጣ የምችለው። እኔ ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ተማሪ አልነበርኩም። በፆታዬ ወንድ ሆኜም ወደዚህ ዓለም መጥቻለሁ።

 በነገራችን ላይ ኃላፊውን “ለመሆኑ አግብተሃል?” ብዬ ልጠይቀው ፈልጌ ነበር። ወዲያው ግን በግራ እጁ ጣት ላይ የጋብቻ የሚመስል ነገር ስላየሁበት ተውኩት። ዲፓርትመንቱ ግን እንዲህ የሴቶች መፈንጫ ሆኖ የቀረው ወንዶችን እንዲህ እያባረረ ነው እንዴ? ብዬ ማሰቤ አልቀረም። ግን ለምን ነበር መማር የፈለኩት!?

 መማር በራሱ ቁም ነገር ነው ወይ? ብዬ ራሴን ጠየቅኩኝ። እርግጥ ነው መማር ነገረ ዓለማትን ለማየት ጥሩ መነፅር ይሰጥሃል። መማር ለሁሉም ነገር ጥሩ ነው፣ ለመኖርም ቢሆን። ነገር ግን ሳትማርም በደንብ መኖር ትችላለህ። እነ ወፍ፣ እነ ከብት፣ እነ አንበሳ፣ እነ ነብር ተምረው አይደለም የሚኖሩት። ተፈጥሮ በሰጠቻቸው ብልሀት እንጂ። ትምህርት ፋይዳ የማይሰጥበት ሁኔታ እንዳለ ለመገንዘብም በራሱ መማር ሳያስፈልግ አይቀርም።

ከዚህ በፊት የተማርኩት ሁሉ እንዳልጠቀመኝ ተረድቻለሁ። ቢያንስ ከበፊቱ አሁን ለመማር ግልጽ የሆነ ምክንያት ነበረኝ። ብዙ ሰው ትምህርት የሚማረው ለማወቅና አውቆም በእውቀቱ ሰርቶ ለመኖር ነው። ለመኖር ግን ትምህርት የግድ እንዳልሆነ ለመረዳት ብዙ መመራመር የሚያስፈልግ አይደለም። ያልተማሩ ሰዎች ደህና ሲኖሩ ታያለህ።

ስለዚህ፣ ትምህርት ለእውቀት ሳይሆን ትምህርት ለሥራ የሚል ነገር የፈጠሩት ጥቅመኛ ሰዎች ይመስሉኛል።

የሰውን ልጅ እንደመሳሪያ የሚያዩና የተሻለ መሳሪያ እንዲሆን የሚፈልጉ ናቸው ትምህርትን ለስራ ያዋሉት። ትምህርት ለእውቀትና ለነጻነት ሲሆን ነው ጥሩ የሚሆነው። ትምህርት አንዱ የጭቆና መሳሪያ ነው። ሰዎች በትምህርት ሽፋን የበሰበሰ አስተሳሰባቸውን፣ ምክንያት የለሽ እምነታቸውንና ጠባያቸውንም ጭምር ይጭኑብሃል።

 በጥንት ዘመን ትምህርት የተጀመረው፣ ለማወቅ፣ ለመመራመር፣ ለመደነቅ ተብሎ ብቻ ነበር። አንድ ሰው በራሱ መንገድ ተመራምሮ የደረሰበትን የእውቀት ደረጃ ለሌሎች በነፃነት ያካፍላል፤ ያስተምራል። ሆኖም በመጀመሪያ ሶፊስቶች የሚባሉ መጡና ጥበብን፣ እውቀትንና ትምህርትን ገበያ ላይ ለማዋል ሙከራ አደረጉ።

 በመጨረሻ ዘመነ ካፒታሊዝም መጣ! የሰውን ክብር በሚያወጣው ዋጋ የሚመዝን፣ የባርነት ዘመን መልኩን ቀይሮ መጣ። በባርነት ዘመን የሰው ልጅ ተገዶ በኃይል እየተያዘ ነበር የሚሸጠው። አሁን ግን በራስ ፈቃደኝነት፣ ከአስፈሪው የኑሮ መከራ ለማምለጥ በወዶ ገባነት፣ ሰው ሁሉ ራሱን ለገበያ ያወጣል። ደመወዝ በሚል ስም ይሸጣል። ድርጅቶች ይገዙታል። እድሜውን፣ ችሎታውን፣ ጉልበቱን መዝነው አውርደው አውጥተው ይገዙታል። ስሙን ግን ቅጥር ነው የሚሉት፤ ግዢ አይሉም።

አልፎ አልፎ በእግር ኳስ፣ በስፖርቱ አካባቢ ነው በእውነተኛ ስሙ ሲጠራ የምንመለከተው። በዘመነ ካፒታሊዝም ሁሉም ነገር ወደ ገበያ ነው። ሽንትና አይነምድርም ወደ ኃይል ማመንጫነት፣ ወደ ማዳበሪያነት ተቀይረው በገበያ ውለዋል። ሁሉም ነገር ወደ ገበያ በሚለው ሕጉ ጥበብም- ትምህርትም- እንደዚሁ የገበያ ሸቀጦች ሆኑ። “ዘ ይገርም” ይል ነበር ደራሲ አቦይ ስብሃት!!!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top