አድባራተ ጥበብ

ምጥን ትውስታ

ፍቃዱ በሬድዮ ከተረካቸው መጽሐፎች “እናት መሬት”ን ያስታውሳል። ደራሲው ቸንጊስ አይትማቶቭ ሲሆን ተርጓሚው ደግሞ ካሳ ገብረሕይወት ነበሩ።

 ሶቭየት ሕብረት ኪሚዝ ወረዳ ውስጥ ስላሉ ፍቅረኛሞች እየተረከ መጽሓፉን እንዳጋመሰ፤ ድንገት ይታመማል። ዓይኖቹ በትክክል ማየት ይሳናቸዋል። ከንፈሮቹ ይደርቃሉ። መቀጠል እንዳለበት ያውቃል። ከህክምና በኋላ በብርጭቆ ውሃ ቀርቦለት እንደምንም እያቃሰተ ይጨርሳል።

ታዋቂው ተዋናይ ፍቃዱ ተክለማርያም የተወለደው በ1948 ዓም. አዲስ አበባ አራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት ተብሎ በሚጠራ አከባቢ ተወለደ።

 በልጅነቱ ቄስ ትምህርት ቤት ገብቶ የእነ “ላሜ ቦራ” ተረቶችን ማንበብ ይወድ ነበር። አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲገባ የአምባሳደር ሲኒማ ቤት ባለቤት ልጅ ጓደኛው ነበር። ስለተመለከተው ፊልም ያወራለታል። አንዳንዴ ረጅም ሰዓት ተቀምጠው ወደ የሚማሩበት ክፍል አይገቡም።

ፍቃዱ ፊልም የማየት ጉጉቱ ይጨምራል። ከጓደኞቹ ጋር ወደ ሲኒማ ቤቶች እየሔደ መመልከት ይጀምራል። ቅዳሜ ቀን መዋያው ወወክማ ነበር። በተጨማሪም የሥላሴ መንፈሳዊ ማኅበር አባል እንደመሆኑ ድራማ ይሠራል።  

“በልጅነቱ ቄስ ትምህርት ቤት ገብቶ የእነላሜ ቦራ; ተረቶችን ማንበብ ይወድ ነበር። አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲገባ የአምባሳደር ሲኒማ ቤት ባለቤት ልጅ ጓደኛው ነበር። ስለተመለከተው ፊልም ያወራለታል። አንዳንዴ ረጅም ሰዓት ተቀምጠው ወደ የሚማሩበት ክፍል አይገቡም።”

በልጅነቱ ቀልደኛ ከመሆኑ በተጨማሪ የእነ ባህታን የእነ ምኒልክንና የሌሎችንም ድምፃዊያን ዘፈኖች እያጠና ማንጎራጎር ይወዳል።

በ1967 ዓም. በአሁኑ አዲስ አበባ ቲያትር እና ባህል አዳራሽ ተቀጠረ። በ1968 ዓም. አያልነህ ሙላት የፃፈውን ቲያትር ላይ መሪ ተዋናይ በመሆን ተወነ። የሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን የ “ከርሞ ሰው” እንዲሁም የመንግሥቱ ለማን “ባለካባና ባለዳባ” ቲያአትሮችን ተውኗል።

 በቴሌቪዥን ድራማዎች በይልማ ገብረየሱስ ከተፃፉት የወንጀል ክትትል ታሪኮች “በአብቄለሽ ኑዛዜ” እና በ “ያልተከፈለ ዕዳ” ኋላ ላይም በአብዛኛው ተመልካች አድናቆትን ባገኘበት፤ በነብይ መኮነን በተፃፈው “ባለ ጉዳይ” የተሰኘውን ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ተጫውቷል።

እንዲሁም በሬድዮ በርካታ ድራማዎችን የሠራ ሲሆን በተለይ ከሚታወቅበት በኃይሉ ፀጋዬ ተፅፈው በቅዳሜ መዝናኛ ፕሮግራም ከተላለፉት እንደ “ቅርጫው” ዓይነቶቹ ላይ ስሙ የገነነ ነበር።

 ከመድረክ ቲያትሮች “ንጉሦቹ” ን ሆኖ የተጫወታቸው “ቴዎድሮስ” በሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ተፅፎ በአባተ መኩሪያ የተዘጋጀው፣ “ኤዲፐስ” በሶፎክለስ ተፅፎ በዶክተር ኃይሉ አርአያ የተተረጎመው፣ “ኀምሌት” በሸክስፒር ተፅፎ በማንያዘዋል እንዳሻው የተዘጋጀው ላይ ተሰጥኦውን በማሳየት ተወዳጅነትን አትርፏል።

 ፍቃዱ በአንድ ወቅት “ቴዎድሮስ” የተሰኘውን ቲያትር ሰርቶ ከመድረክ ሲወርድ የገፀ-ባህርይው ተፅዕኖ እንዳለቀቀው ተናግሮ ነበር። ልክ የመጀመሪያውን የግርማቸው ተክለሃወሪያትን “ቴዎድሮስ” ቲያትርን እንደተጫወቱት አቶ መኮነን አበበ፤ እሳቸው የፂማቸውን ጫፍ እና ጫፍ አሹለው፣ አረማመዳቸውን ለውጠው በመራመዳቸው፣ ገፀ-ባህርይው ገና አለቀቃቸውም እየተባለ ይወራ ነበር።

 እሱም ሲናገር፣ ሲራመድ፣ ሰው ላይ ሲያፈጥ የታዘቡት ምን ልትሆን ነው መባሉን ያስታውሳል።

 ተዋናይ ፍቃዱ ተክለማርያም ሁለገብ ከሚባሉት ከያኒያን የሚመደብ ነበር። በርካታ ፊልሞች ላይ የተወነ ሲሆን፤ በተለይ በልደቱ ቀን የሰራውን #ጉዲፈቻ; የተሰኘ ፊልም ያስታውሳል። በመድረክ ግጥሞችን በማንበብ፤ በሬድዮ እና በቴሌቪዥን ማስታወቂያዎችን በመሥራት ይታወቃል።

 ተዋናይ ፍቃዱ በኪነ-ጥበብ ውስጥ ከሚያሳያቸው ተወዳጅ ብቃቱ ሌላ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የቲቢ በሽታ በጎ ፍቃድ አምባሳደር በመሆን ለ5 ዓመታት አገልግሏል።

 ከወራት በፊት በሁለቱም ኩላሊቶቹ ላይ በደረሰበት ህመም ምክንያት በሰሜን ወሎ ሀብሩ ወረዳ ስሪንቃ ቅድስት አርሴማ ገዳም መንፈሳዊ ህክምና ሲያደርግ ቆይቶ በተወለደ በ62 ዓመቱ ከእዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

አንጋፋው ተዋናይ ፍቃዱ ተክለማርያም ከወራት በፊት ታክሞ እንዲሻለው በማሰብ የሙያ አጋሮቹ እና ጥበብ ቤተ-ሰቦች ኮሚቴ አቋቁመው ህክምናውን የሚሸፍን ገንዘብ ሊያገኙ ቢችሉም ፍቃዱ በተመሳሳይ ህመም ህክምና ለምትፈልገው ወጣት ሁለት መቶ ሺህ ብር መስጠቱ ይታወቃል። በወቅቱ የተናገረውም እንዲህ የሚል ነበር።

 “ዕድሜዬ ስድሳዎቹ መጀመርያ ላይ ደርሷል። የቀሩኝ ዓመታት ከጣቶቼ ቁጥር አይበልጡም። ይህች ገና ነገዎቿ ተደርድረው የሚጠብቋት የ18 ዓመት ቀንበጥ ሁለቱም ኩላሊቶቿ ደክመው በገንዘብ እጦት ስትሞት እያየሁ ቀድሜ ልታከም አልችልም። በእዚህች አንድ ሳምንት ውስጥ የኢትዮጵያ ህዝብ ያስተማረኝ ፍቅር ይህንን አያሳይም። በእዚህ ምክንያት መሞት ካለብኝ ልሙት እንጂ ይህቺ ልጅ ሳትድን እኔን ቢላዋ አይነካኝም።; የሚል ነበር።

 ተወዳጁ ተዋናይ ፍቃዱ ተክለማርያም በ1986 ዓም. ትዳር የመሠረተ ሲሆን፤ በ1994 ዓም. በቴአትር ዘርፍ የረጅም ዘመን ተሸላሚ ነበር። የታዛ መጽሔት ዝግጅት ክፍል በታዋቂው ተዋናይ ፍቃዱ ተክለማርያም ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልፃል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top