አጭር ልብወለድ

መኖር ሰው ገደለ

አንድ ግብዳ የሚያህል መዳፍ ማጅራቱን ጨምድዶ እንደያዘው፤ መኖር ልብ አላለም ነበር። መኖር ሰማይ ምድሩ ዞሮበታል። የሟቹን ሰውዬ አስክሬን አንቡላንስ ወደ ፊቼ ጤና ጣብያ ሲወስደው፤ መኖርን ጨምድዶ የያዘው መዳፍ ደም እያዳፋ ከቀበሌ አድርሶታል። ቀበሌም ተቀብሎ ለፖሊስ ጣቢያ አሳልፎታል።

ትንሽቷ የፍቼ ከተማ በድንገቴው አደጋ ወሬ እየታመሰች ነው። ትንሹ ልጅ መኖር ተሊላ ከፖሊስ ጣቢያው ደጃፍ ቆሞ በፍርሃት ተሰቅዞ ይርዳል። ያላፊው አግዳሚ አይንና አፍ ሁላ ያሟሸዋል። መላ ምቱን የሚያሰላበት፣ የማይተቸው፣ የማይረግመውና የማይሰድበው የሰው ዓይነት የለም።

 “አንድ ፍሬ ልጅ እኮ ነው!… ምን ዓይነቱ ጨካኝ ቢሆን ነው አቦ?!…”

 “ጨካኝ ብቻ ትላለህ እንዴ?… አሬስ የሰይጣን ቁራጭ እንጂ!…”

“ይሄ አውሬ ነው እንጂ፤ ከሰው የተፈጠረም አይዶል… አሲዳም!…”

 “እቆራጣ እጁ ላይ በተንዘለዘለው እጅጌው ነው አሉ- አንቆ የገደለው!…” ይላል ደሞ ሌላው።

 “የለም የለም!… በካራ ወግቶት ነዩ፤ አንገት ላንገት ተናንቆስ ትልቁን ሰውዬ ሊገለው አይችልም!”

 “ጥጋበኛ ብጤ ነው ያስታውቃል!… አይኖቹን ደም አስለብሶ ሲያጉረጠርጥ አታየውም?…”

መኖር ተግራና ተቀኝ የሚሰነዘርበትን ትችትና እርግማን በሰማ ቁጥር ይበልጥ ጨነቀው። ወደ ጥቁረት የሚያደላ የገፁ ቀለም ተለውጦ፤ አመድ የተነፋበት ቁርበት መስሏል በድንጋጤ። ተዚያች ኩርማን ሰውነቱ ላይ ሙዳ ሙዳ ሥጋ እየተነሳለት፤ በፍርሃት መቁለጭለጩን ቀጥሏል። ሰውም ያለ ርህራሄ ያንን አንድ ፍሬ ልጅ መገሸለጡን ተያይዞታል።

  “አካለ ስንኩል መሆኑን አይቶ ነው እንጂ፤ መቼ ቀናስ ብሎ ሊያየው ነበረ… ወይ ነዶ!..” አለ ደሞ ሌላው ተቺ።

 “ለዚህ ለዚህ ዓይነቱ ተንኮል አይበቃም ብለህ ነው? ቢያንስ አንድ አስራሶስት ዓመት ይሆነዋል!…”

መለሰ ተጎኑ ያለ ሌላ አድማጭ።

 “እስቲ ምን አለ አነስ አነስ አድርጎ እየቆራረጠ ቢያጎርሰው ነሮ!… ክፉ!… የክፉ ሽንት ቅራሬ!…”

 ደሞ ሌላው የግሉን ፍርድ ሰጠ።

 “ በስጋ ነው እንዴ አንቆ የገደለው? አበስኩ ገበርኩ እናንተዬ!… ቱ!… ቱ!…” የሰማውን ማመን የተሳነው ሌላው አዳናቂ።

 “ እንግዲያስ?!… ጡጫ ጡጫ የሚያካክል ጉማድ አጉርሶት አይደል እንዴ ጠብ ያደረገው!…”

 “አጀብ!… አጀብ!… እጅ የለውም እና እጄን ላውሰው ብሎት…” ባዘን ስሜት የከንፈር ልቅሶ አሰማ ይሄኛው።

 “እንግዲያሳ… እጅ ላውስ ብሎ እጁን አስያዘ… አወይ የቀን ፍርጃ…”

አረጋገጠለት ሌላኛው። እጅግ ጥቂቶች ነበሩ ለትንሹ መኖር የሚያዝኑት። አብዛኞቹ ጥርሶቻቸውን በቁጭት እያንቀራጨጩ ያፈጡበታል፣ ይዝቱበታል፣ ይረግሙታል፣ ይሰድቡታል… መኖር ትንፋሹን ውጦ ከማልቀስ ሌላ አማራጭ አልነበረውም። የፖሊስ ጣቢያውን ደጃፍ ያጨናነቀውን ሕዝብ ገለል አስደርጎ፤ በጽና ሊያነጋግረው ወደ ቢሮው ይዞት የገባው የጣቢያው አዛዥ ብቻ ነበር።

 መኖር ከዚያ ሁሉ አጀብ እይታ ተገላግሎ ወደ ቢሮው ውስጥ በመግባቱ ትልቁ እፎይታ ስለተሰማው በረዢሙ ሲተነፍስ አዛዡ ሰማው።

 “አይዚህ በርታ በል!… ለመሆኑ ስምህ ማነው?…”

 “መኖር… መኖር ተሊላ!…”

 “ ዕድሜህ ስንት ነው?”

 “አሥራ አራት!…”

 “ወላጆች አሉህ?…”

“አባቴ ሞቷል… እናቴ ገጠር ትኖራለች…”

 “የት ገጠር?…”

 “ ደገም… ደገም ገንደ ሸኖ!…”

 “ ታዲያ አንተ እዚህ ምን ትሰራለህ? ከማንስ ጋር ነው የምትኖረው?…” የፖሊሱ አዛዥ አዘኔታ በተላበሰ አባታዊ ትህትና ተላብሶ ነበር የሚያናግረው። እናም መኖር ለተጠየቀው ሁሉ ተረጋግቶ ምላሽ ለመስጠት ተደፋፈረ።

“ እማራለሁ… ስምንተኛ ክፍል ነኝ። ከባለ ሉካንዳ ቤቱ ከጋሼ ቶልቻ ዘንድ ተጠግቼ ነው የምኖረው…”

 “ሰውየውን ማን ገደለው?…”

 “ሥጋው ነዋ!… ሰው ግን “መኖር ሰው ገደለ” እያለ ሲያዋክበኝ የዋለ። እኔ አልገደልኩትም!…” እምባው በአይኖቹ ተሾመ።

“ አይዞህ… አታልቅስ… የሆነውን ሁሉ ትክክለኛውን ግለፅልኝ… ”እያለ አዛዡ የመኖርን ራስ ፀጉር እያሻሸለት እንዲረጋጋ አበረታታው።

“ ሰውየው ሁሌም የሉካንዳ ቤታችን ደምበኛ ነው። ሥጋ ሊበላ ይመጣል። ሁሌ ግማሽ ኪሎ ሥጋ ነው የሚገዛው ታዲያ አንድ እጅ ስለሌለው ሁሌም እኔ ዌም ጋሼ ቶልቻ እንቆራርጥለታለን። ግማሹን ጥሬ ሲበላ ግማሹን ጥበሱልኝ ይላል። እናም ዛሬ ጋሼ ቶልቻ ሥራ ስለበዛበት፤ እኔ ነበርኩ የቆራረጥኩለት…”

 “ እና ተዚያ በኋላስ?…” የፖሊሱ አዛዥ ቀጥሎ የሆነውን ለመስማት ጓጓ።

 “ ከዚያማ… ጥሬ ጥሬውን የሚበላውን ቆራርጬ ሰጠሁት እና የሚጠበሰውን ልጠብስ እኔ ወደ ውስጠኛው ጓዳ ገባሁ…”

 “ ከዚያስ?…” አለው አዛዡ፤ ድቅቅ ያሉት አይኖቹን ከተደበቁበት ዋሻ ወደ መኖር አቅጣጫ እያስፈተለከ። ፈጠን ፈጠን እያለ ማስታወሻ መያዝ ከጀመረ ቆይቷል።

 “ ከዚያማ ትንሽ ቆይቶ ለካስ የጎረሰው ሥጋ አንቆት ኖሮ፤ ነፍሱ ልትወጣ ሲያጣጥር ጠረጴዛውን ክፉኛ አንንገረባበደው…”

 “ ከዚያስ?…” የጣቢያ አዛዡ የሆነውን ለመስማት ይበልጥ ቋምጦ፤ በጠረጴዛው ላይ በደረቱ ተስቦ ወደ መኖር ተጠጋ።

 “ከዚያማ እኔም ጋሼ ቶልቻም የሚንገረባበደውን ድምፅ ወደ ሰማንበት ስንደርስ፤ ሰውየው ከመቀመጫው ተንሸራትቶ እጠረጴዛው ሥር ሲንደፋደፍ ደረስንበት…?”

 እነዚያ ጉርጥ ርጥ የመኖር አይኖች ይበልጥ ተጉረጥርጠው፤ የሆነውን ሁሉ ላዛዡ በስሜት ማስረዳት ቀጠለ።

 “እሺ አይዞህ ቀጥል!…”

 “ጋሼ ቶልቻ ከጠረጴዛው ሥር ሊያነሳው ሲሞክር ከጁ ላይ ተዝለፍልፎ ቀረ… ቶሎ ብሎም ማጅራቱን በጡጫ ሲለው… ከጉሮሮው የተሰነቀረው ሥጋ ቱር ብሎ ወጣ… ሰውየው ግን እንደተዝለፈለፈ ጸጥ ብሎ ቀረ…”

አዩ… ነፍሱ ከወጣች በኋላ ምን ዋጋ አለው… እኔ ላይ እየጮኸ ፖሊስ ሊጠራ ወደ ውጭ ሮጠ። ውሸቱን ነው… እኔ አልገደልኩትም!…; አለና እምባ በተሸሙት አይኖቹ የጣቢያውን አዛዥ ተማፀነው።

 የጣቢያው አዛዥ ህፃኑ መኖር ከወንጀል ነፃመሆኑን ለመወሰንና በነፃ ሊያሰናብተው ሲወስን ጊዜ አልፈጀበትም።

“አይዞህ!… ያንተ ጥፋት አይደለም። የቀን ጎዶሎ ነው የፈረደበት ያንን ምስኪን… አሁን ወደ ቤትህ መሄድ ትችላለህ…” እያለ በማጽናናት መልክ ትክሻውን ቸብ ቸብ እያደረገ እደጅ ድረስ ሸኘው።

 ጣቢያውን ከቦ የቆመው ወሬኛ አሁንም ጢም እንዳለ ነበር። መኖር እንደተጀነነ በመሃላቸው ሰንጥቆ ወደ ሉካንዳ ቤቱ ሲያመራ ያልተኮማሸሸ ወሬኛ አልነበረም።

 “ሂዱ ከዚህ!… ሥራ ፈት ወሬኛ ሁላ!…” ብሎ ያባረራቸው ያው የጣቢያ አዛዡ ነበር።

 መኖር ያሰውየ ከሞተ በኋላ ሰላም አላገኘም። የሉካንዳ ቤቱ አቶ ቶልቻ፤ የከተማው አንዳንድ ነዋሪዎች ፣ በትምህርት ቤት የሚያውቁት ተማሪዎች እና የሰፈር ልጆች አፍና ግልምጫ ከሰውነት ጎዳና እያወጡት ነው።

 “መኖር ሰው ገደለ” የሚለው ሀሜት ከቶም ሊቆም አልቻለም። ስለዚህ መፃኢ አክራሞቱና አኗኗሩ በእጅጉ አሳሰቡት። እንቅልፍ ነስተው ወደ አንዳች የማያውቀው አገር ብረር ብረር አሉት። መወሰን ግን አልቻለም። እናም ገጠር ለሚኖሩት ድሃ እናቱ ደብዳቤ ፅፎ ጭንቀቱን ለማካፈል ወሰነ።

 “ይድረስ ለእናቴ ለወ/ሮ ግምጃ ሳላሌ”

 “ እማዬ ለጤናሽ እንደምን ከርመሻል?… እኔ እንዳለሁ አለሁት። ሰሞኑን በጥሩ ሁናቴ ላይ አይደለሁም ያለሁት። አዲስ ነገር ስለገጠመኝ ነው ይሄንን አሳዛኝ ደብዳቤ ዛሬ የጻፍኩልሽ። ካንቺ ከናቴ በላይ ማን በዚህ ክፉ ሰዓት ከጎኔ ሊቆም ይችላል?… የጭንቀቴ ተካፋይ ትሆኚ እና ከዚህ ጉድ ውስጥ ታወጪኝ ዘንድ እምነቴ ነው እማዬ። የሆንኩትን ስትሰሚም እንዳትበሳጪ፣ እንዳታዝኚም አስቀድሜ እለምንሻለው። ይኸውልሽ እንዲህ ሆነ እማዬ… ባለፈው ሳምንት አንድ የሉካንዳ ቤታችን ደምበኛ የጎረሰው ሥጋ አንቆት ከሞተ በኋላ፤ የፍቼ ሰው ሁላ በክፉ አይኑ ያየኛል። ሰውዬው ከሞተበት ዕለት ጀምሮ ወደ ሉካንዳ ቤታችን የሚገባው ሰው ቁጥር ቀንሷል። ወሬውን ያልሰሙ አንዳንድ ሰዎች ብልት ብልቱን እየጠያየቁ፤ ከስንት አንዳንዶቻቸው ብቻ አስጠቅልለው ይሄዳሉ። የገዛውን ሥጋ እራሱ መሸከም የተጠየፈው ደሞ እንደተለመደው እኔኑ በዘምቢል አሸክሞኝ ከኋላ ኋላው ያስሮጠኛል። ጥቂቶቹ ትንሽ ሳንቲም ቢጥሉልኝም፤ አብዛኞቹ ግን በነፃ ነው የሚያሸክሙኝ። “ልጄ በርታ እና ትምህርትህን ተማር” ያልሽኝን ሁሌም ስለማልረሳ፤ የጋሼን ቶልቻን ቁጣ አዘል ትዕዛዝና የሥራው ጫናውን እንግልት እየቻልኩ፤ በማዝገም ላይ ነኝ። ታዲያ እማይዬ ሰሞኑን የሚሰማኝን ጭንቀት የሚያብስብኝ፤ ይሄ ሥጋ አሸክሞኝ ከኋላ ኋላው የሚያስሮጠኝ ሁላ ድንገት ቆም ብሎ፤ “መኖር ማለት አንተ ነህ? ሰውየውን ለምን ገደልከው?…” ብሎ የሚያፋጥጠኝ እየመሠለኝ፤ ሰውነቴ በሀሳብ እልቅ ይላል። አንዳንዱም የገዛውን ሥጋ እቤት ደርሶ ለመብላት ካለው ጉጉት የተነሳ ተካልቦ ሲያካልበኝ ሮጦ ሲያስሮጠኝ፤ ምናልባት የዚያ የሟቹ ሰውዬ ዘመድ ሁኖ ተቤቱ ስደርስቢበቀለኝስ ብዬ ማሰቤና መጨነቄም አልቀረም።

 የኔ እማዬ ይሄ ዓይነቱ ክፉ አሳብ ከራሴ ላይ የሚራገፈው፤ ሥጋውን ያሸከመኝ ሰውዬ ከቤቱ እንደደረስን፤ የኔን መፈጠር ረስቶ ያንን የገዛው ሥጋ ከጠረጴዛ ላይ አጋድሞ፤ “ተሎ ብዩ!… ቢላ አምጪ…” እያለ በሚስቱ ላይ የትዕዛዝ ናዳ ሲያወርድ እና፤ አስሬ ምራቁን እየዋጠእጆቹን ሲያፋትግ ሳይ ነው። ይሄኔ ቀስ ብሎ ዘንቢሌን አንጠልጥዬ እሾልክ እና ወደ ልኳንዳ ቤቱ እፈረጥጣለሁ። ግን ምን ያደርጋል! ምን ያህል እራሴን ሰውሬ ስርቻ ለስርቻ እየተሸሎከሎኩ ብጓዝም፤ ወሬኛው ሁላ ሲያየኝ “ያውና ያ ሰውዬውን የገደለው ልጅ!…” እያለ መንገድ አላስኬድ ይለኛል። ይሄኔ ያው እንደተለመደው የሆድ ብሶቴን በእምባዬ እበሳ እየተወጣሁ፤ ግራና ቀኝ ሳልገላመጥ ወደ ልኳንዳ ቤቱ እሸመጥጣለሁ።

 እማይዬ እስቲ እንዲያው አንቺው እራስሽ ስታስቢው እኔ ይሁነኝ ብዬ ትልልቅ ሥጋ ከትፌ ሰውዬው ታንቆ እንዲሞት የማደርግ ይመስልሻል?… በጭራሽ!… በእርግጥ ሰውዬው በጣም ርቦት ስለነበረ፤ “ቶሎ ቶሎ ቁረጥልኝ… በጣም ርቦኛል…” ሲለኝ ፈጠን ፈጠን እያልኩ እንደቆራረጥኩለት ትዝ ይለኛል። ግን ስራስር ያለው ጎርሶ፣ እጥርሱ ውስጥ ተሸንቅሮ የሚገለው ዓይነት ሥጋ ቆርጬ ማብላቴ ከቶም ትዝ አይለኝም። በኔም በሱም የቀን ጎዶሎ ፈረደብን እንጂ..

. ”በዚሁ ግርግርና ወከባ ምክንያት የምወደውን ትምህርቴን ካቋርጥኩ ሳምንት ሞላኝ እማዬ። ወደ ትምህርቴ ለመመለስ ሳስብ ትልቅ ጭንቀት ውስጥ እገባለሁ። የክፍሌን ልጆች ዐይን ደፍሬ ለማየት የሚያስችለኝ ወኔ አጣና ተስፋ ቆርጬ ብስጭትጭት እላለሁ። ክፉ አፋቸውን ገና ከሩቁ መሸሽን ነው ውስጤ የሚነግረኝ። መምህራችን መልአከ ገነት ስላማርኛ ምሳሌያዊ አነጋገሮች ሲያስተምሩን፤ “የሰው አፍ እርጥብ ያደርቃል” የሚለውን አባባል እንድንፈታ ሲጠይቁን፤ ተገቢውን መልስ ለመስጠት ብለን ስንፈላሰፍ የዋልነው ትዝ ይለኛል። የምሳሌው ትክክለኛ ምስጢር ይሄው በኔ ላይ ተፈቶ አየሁት ዛሬ- እማምዬ። ለትሳስ የተክልዬ ንግስ ተዜጋመል ስትመለሺ በፍቼ ያለፍሽ ጊዜ ያስተዋወቅሁሽን ጓደኛዬን ደረሰን ታስታውሺዋለሽ መቼም… ’እንደኔው በትምርቱ ላይ የሚተጋ ጎበዝና ጥሩ ልጅ ስለሆነ እንደ ወንድሜ ነው የማየው” ያልኩሽም ትዝ እንደሚልሽ እገምታለሁ። ያ ልጅ ያ በጣም የምወደው ጓደኛዬ ሳይቀር ፊቱን አዙሮብኛል፤ ሸሽቶኛል። እሱም ሰውዬውን እኔ የገደልኩት መስሎት አሉባልታውን አምኖ አፍሮብኛል ማለት ነው – ያሳዝናል።

እማምዬ ትናንት የደረሰብኝ የሳር ተራ ልጆች ስድብና ዱላማ አያድርስ ነው። የሉካንዳ ቤቱ ባለቤት ጋሽ ቶልቻ “ሰምበርና ምላሱን እንዳትሸጡት ብለህ ለብልት አውጪውና ለረዳቱ ንገር…” ብሎ ልኮኝ በማለዳ ቄራ ወርጄ ነበር። ታዲያ ስመለስ ገና የዘረፈትን ዳገት ስያያዘው ነገር እያሳደደ ይገርፈኝ ጀመር። “እዩት ይሄን ጉድ!… ተዌት ነው እሚመጣው?… አልታሰረም እንዴ እስካሁን?… ይሄው ድሃውን የልጆች አባት ገሎ እሱ ይሽከረከራል…” እያሉኝ ሲጠቃቀሱብኝ ችዬ ሳር ተራ ደረስኩኝ። እዚያ ስደርስ ካንድ ቁና ውሪ ፀሐይ ሟቂ ጋር ተገጣጠምን። እማዬ መቼም በዝናም ቢሆን የሳር ተራ ልጆችን አፈኝነት ሳትሰሚ አትቀሪም። ከግሪካዊው ልብስ ነጋዴ ከሉካ ሱቅ እስከ ሸቀጣሸቀጥ ነጋዴው ያገሩ ልጅ እስተ እስጥሊያኖስ ሱቅ ድረስ እየተጠራሩ መጥተው ከበቡኝ። ተዚያማ ምን ልንገርሽ ባፋቸውም፣ በጡጫቸውም፣ በእርግጫቸውም ተቦጫጨቁኝ እማይዬ…

 እነዚህ የሳር ተራ ልጆች እንኳንስ እንዲህ ያለ ሰበብ አግኝተው እንዲያውም እንዲያው ናቸውና አልራሩልኝም። አንዱ የኔ እኩያ ልጅ ገና ሲያየኝ፣ “አንተ ነፍሰ ገዳይ!…” ሲለኝ፤ ንዴቴ ባፍጢሜ ሊደፋኝ ሲታገለኝ፤ በተቀዳደደ ቁምጣው ውስጥ ያየሁትን አይቼ ላልፈው አልፈለኩም። “አንት ወሸላ… አንተም ሰው ሆነህ!?…” ስለው፤ ያ ሁሉ ውሪ እላዬ ላይ ፈሰሰብኝ። አንዱ ጨርቄን ሲጎትተው፣ አንዱ ሲተፋብኝ፣ አንዱ እራሴን በኩርኩም ሲያናጋው፣ አንዱ ሲረግጠኝ፣ አንዱ ሲያጮለኝ… ጉንዳን የወረረው የወደቀ ኩላሊት አስመሰሉኝ። የስድቡን ነገርማ አታንሽው እማምዬ… “ይሄ ቅንጥብጣቢና ሽንፍላ የነፋው!… ጥጋበኛ!… ነፍሰ በላ!… ቁሬማ!…” እያሉ ሲረባረቡብኝ፤ ያንዳንዶቹ ወላጆችም አጃባዎቻቸው ነበሩ። ቂም ባዘሉ የበቀል ዐይኖቻቸው የጎሪጥ እየተመለከቱኝ፤ ስስና ወፍራም ለንጨጫቸውን ስድ ለቀውብኛል። ምን ልበልሽ እማዬ… የምገባበት ጉድጓድ የምሸሸግበት ዋሻ ነው አጥቼ የነበረው። አውድማ ላይ ብቻዋን ተገኝታ በእረኖች የገና ዱላ ልትቀጠቀጥ እንደተከበበች አይጥ

“ደሞም ያ በብር ታላድ የገባሁት እቁብ ገና አላለቀልኝም። የሰው ገንዘብ በልቼ እንዴት አባቴ ጨክኜ እሰወራለሁ?… እንዲያውም ሰውዬው ከሞተበት ቀን ጀምሮ እስከ ነገው እሁድ ድረስ የሁለት ሳምንታት እጣ መደብ ድርሻዬን አልጣልኩም ማለት ነው። ሰውዬው ባለፈው ቅዳሜ እንደሞተ ቀበሌና ፖሊስ ጣቢያ ያንከራተቱኝ ለታ አንዲትም ሳንቲም አልቋጠርኩም”

ሆኜልሽ ነበር እማምዬ… እግዜር ትረፍ ሲለኝ እንደምንም ከበባውን ጥሼ አመለጥኩ።

 እማዬ ይሄ ጋሼ ቶልቻ የልኳንዳ ቤቱ ጌታ ሳይቀርኮ አልራራልኝም። “ገበያዬን ዘጋህብኝ…” በሚል ሰበብ ስገባ ስወጣ ይጎነታትለኛል። አንዳንዴም ድንገት ባየኝ ቁጥር ሁሌም ከጁ የማይለየውን ትልቁን ካራ ባየር ላይ እየሳለብኝ ይዝትብኛል። “አንተ እርጉም ልጅ… በዚህ ነበር አንተን መበለት!… “ እያለ ያስፈራራኛል። ይሄኔ ሽብር ይይዘኝና ከዛሬ ነገ አይቀርልኝ ይሆናል እያልኩ እጨነቃለሁ እማምዬ። ጋሼ ቶልቻ እነዚያን የብርሃን ጨረር ያለገደብ የሚረጩ ትንታግ ዐይኖቹን ደጋግሞ እያፈጠጠብኝ፤ “እንዴት ደምበኛዬን ትገላለህ?…” እያለ ቁምስቅሌን ያሳጣኛል። አንዳንዴ ደሞ ይሁን ብዬ ሰውዬውን የገደልኩት አስመስሎ ሲያቆስለኝ፤ “አሁን ያንን የልጆች አባት ገድለህ ምን ትጠቀማለህ?…” ይለኛል። ምንም መልስ ሳልሰጠው ወደ ጓዳ ሹልክ እልና በእምባዬ ፊቴን አብሳለሁ። መልስ መልሼለት የት እገባለሁ?… ሁሉንም ነገር ጣጥዬው ወዳንቺ እንዳልመጣ ተመልሼ እዚያው እረኝነት መግባት ይሆንብኛል ብዬ እሰጋለሁ። እናም “ሁሉንም ችለህ በትምርትህ ላይ በርታ!…” ያልሽኝን ምክር አጥብቄ ይዤ እየተንገታገትኩ ነኝ እማምዬ… ደሞም ያ በብር ታላድ የገባሁት እቁብ ገና አላለቀልኝም። የሰው ገንዘብ በልቼ እንዴት አባቴ ጨክኜ እሰወራለሁ?… እንዲያውም ሰውዬው ከሞተበት ቀን ጀምሮ እስከ ነገው እሁድ ድረስ የሁለት ሳምንታት እጣ መደብ ድርሻዬን አልጣልኩም ማለት ነው። ሰውዬው ባለፈው ቅዳሜ እንደሞተ ቀበሌና ፖሊስ ጣቢያ ያንከራተቱኝ ለታ አንዲትም ሳንቲም አልቋጠርኩም። በቅንጥብጣቢና በጥብሳጥብስ ልቸረችረው የገዛሁት የበሬ ጭንቅላት ሥጋም፤ ከተሰቀለበት በስብሶ እንደተላ በሚያወጣው መጥፎ ሽታ እያሳበቀብኝ ነው። ጋሼ ቶልቻ አስሬ እየጠራ “ምንድነው ቤቱን እንዲህ የምታገማብኝ?… የሠራኸው ክፉ ሥራ ሳያንስህ፤ ደሞ ቤቴን እያገማህ የተረፉኝን ደምበኞች ልታባርርብኝ ነው?… በል ይህን ግማትህን ባስቸኳይ አውጥተህ ጣልልኝ!…” እያለ በወጣ በገባ ቁጥር ይነተርከኛል። እንዴት ይሆናል፣ እንዴት ይቻላል እማይዬ?… ያንድ በሬ ሙሉ ጭንቅላት አውጥቶ መጣል ማለት የመነገጃ ዋና ገንዘብን የውሻ እራት ማድረግ ማለት ነው። አሥራ ሦስት ብር ቀልድ አይደለም! አልችልም። አልሞክረውም እማይዬ! ባይሆን ይህንን ያልታደለውን ዋና ገንዘቤን የተሸከመውን የበሬ ጭንቅላት በዘዴ እድሜ ልገዛለት እሞክራለሁ። ክፉኛ እየሸተተ የመጣውን የጭንቅላት ሥጋ ትላትሉን ከውስጡ እያራገፍሁ፤ ጨው እየነሰነስኩበት ላንድ ቀን ከመጥበሻ ቆጡ ግርጌ፣ ሌላ ቀን ደሞ ከወተት አንጀቱ መስቀያ ሜንጦ ላይ፣ አልሸጥ ብሎ አሁንም ውሎ ካደረ ደሞ ከቆዳው መደበሪያ ቆጥ ላይ በሞራ ሸፍኜ እሸሽገዋለሁ እያልኩ አስባለሁ። ግን ማን ያውቃል አንዱ ደግ ገበያተኛ ወይ ድንገት መጥቶ ሁሉንም በጅምላ ገዝቶኝ ከሀሳብና ከኪሳራ ይገላግለኝ ይሆናል እማይዬ።

 የሆነው ሆኖ፤ የመጣው ይምጣ እንጂ ይሄን የሕይወቴ እስትንፋስ መገኛ የሆነ ሉካንዳ ቤትና ትምህርት ቤቴን አለቅም እያልኩ ከራሴ ጋር በመሟገት ላይ ነኝ። ግን ይህን በሬ ወለደ ባይ አፈኛ ሁላ የሚይዝልኝ አንዳች ኃይል ይገኝ ይሆን?… እማይዬ ለማንኛውም ይህን ደብዳቤ እንዳስነበበሽና የገባሁበትን አጣብቂኝ ጉዳይ እንደተረዳሽ፤ ውለሽ ሳታድሪ ወደ ፍቼ ብቅ በዪና ከርታታ ልጅሽን እዪኝ… ተዝቆ ከማያልቀው ወርቃማ ምክርሽ አንድ በዪኝ።

ናፋቂ ልጅሽ፣

መኖር ተሊላ  (መጋቢት 14 ቀን 2006 ዓ.ም

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top