ጣዕሞት

ህፃናት፣ ስዕል እና ስሜት

ከአምስት ዓመት በፊት ነበር። ታምራት “Artist for charity” በተሰኘ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ አባል ይሆናል። ኤች.አይ.ቪ ኤድስ በደማቸው ያለ ወላጅ አልባ ህፃናትን መንከባከብ እና የድርጅቱ ተግባር ነበር።

ታምራት ወደ አሜሪካ በመጓዝ ተከታታይ የስዕል አውደ-ርዕይ ያዘጋጃል። ሲመለስ በየትምህርት ቤቱ እና በየሆስፒታሉ ያሉ ህፃናትን ማገዝ ይፈልጋል። ከጓደኞቹ ጋር ይመካከራል። ኃይሉ ክፍሌ፣ ዮሴፍ ሶበቅሳ፣ ሔኖክ ፀጋዬ፣ አብርሃም ፀጋዬ እና ሌሎችም በሐሳቡ ይስማማሉ።

መጀመሪያ ወደየትምህርት ቤቱ ለመሔድ ይነጋገራሉ። የተወሰኑትን ለማየት ይሞክራሉ። አመቺ አልነበሩም። ትተው ወደ ሆስፒታሎች ይጓዛሉ። ደርሰው ታመው የተኙትን ህፃናት ይመለከቱና ያዝናሉ። ብዙዎቹ ከሩቅ ሀገር የመጡ ናቸው። ጠያቂ የላቸውም። ህመማቸውን የሚረሡበት ነገር እንደሌለ ይታዘባሉ።

 ይነጋገራሉ። እየሄዱ ስዕል ይስሉላቸዋል። ከተቻለ የመጫወቻ ሥፍራ በመፍጠር አንዳንድ ነገሮችን እንዲሰሩ ለማገዝ ያስባሉ። በእርግጥ ሁሉም ነገር እንዳሉት አልሆነም። የተወሰኑ ሆስፒታሎች ውስጥ ካሉ ኃላፊዎች ጋር አልተግባቡም። ህፃናቱን ለማገዝ ያለ ክፍያ እንደሚሠሩ ቢነግሯቸውም አላመኗቸውም። ተስፋ ሳይቆርጡ ወደ ሌሎቹ በመሔድ ይጠይቋቸዋል። ይፈቀድላቸዋል። የጀመሩት በየካቲት 12 ሆስፒታል ነበር። በዘውዲቱ እና በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታሎች በመገኘት ሥራቸውን ይቀጥላሉ።

ሥዕል ይስላሉ። በሥዕሉ የልጆቹን ስሜት ይመለከታሉ። ንድፍ በመሥራት ያሳይዋቸዋል። ህፃናቱ እያዩ መሳተፍ ይጀምራሉ። ለውጣቸውን በመመልከት የተኙት ልጆች እየታቀፉም እየታዘሉም መጥተው ቀለም እንዲቀቡ ያደርጓቸዋል።

ቀስበቀስ ሥዕል መሳሉ፣ ቀለም መቅባቱ በልጆቹ ውስጥ ልዩ ስሜት በመፍጠሩ ታምራት እና ጓደኞቹ ቅዳሜ እና እሁድን በሆስፒታሎች ማሳለፍ ይጀምራሉ።

 ህፃናቱን ያዝናናቸዋል፤ ብለው ባሰሉት መንገድ የተለያዩ ስዕሎችን በመሳል የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎችን በመጋበዝ ከእነሡ ጋር በነፃነት እንዲሠሩ በመረዳት ብቻ ተወስነው መቅረት እንደሌለባቸው ያምናሉ። እናም ወደ ሌላ ተግባር ይሸጋገራሉ።

ጥረታቸው ቢሳካም ችግር እንዳላጣቸው ታምራት ያስታውሳል።

 “ከአንዳንድ ወዳጆቼ ጋር እንግሊዝ ኤምባሲ በሞያችን ሠራን፤ ክፍያ አልነበረውም። ለህፃናቱ አሻንጉሊቶች እንዲያመጡ፣ ቃል አስገባናቸው። የማይችሉት ገንዘብ አዋጥተው መቀመጫ እንዲገዙላቸው ተናገርን። ያልነውን አደረጉ። ሰብስበን በመውሰድ ለአንዱ ሆስፒታል አስረከብን። ይሁን እንጂ ከቀናት በኋላ ስንሔድ አሻንጉሊቶችቹ ግምጃ ቤት ተቆልፎባቸዋል። ምክንያታቸውን ስንጠይቅ ሊጠፉ ስለሚችሉ ኃላፊነት የሚወስድ ሰው የለም ነው ያሉን። ለልጆቹ በምን መልኩ መድረስ እንዳለበት ለማሳመን ሞክረን ተመልሰናል” ይላል።

ብዙዎቹ ሐኪሞች ያግዟቸዋል። ልጆቹን ያዘጋጁላቸዋል። የመጫወቻ ሥፍራዎችን ያስተካክላሉ።

 ሠዓሊዎቹ ለሚሠሯቸው ሥዕሎች የሚሠጣቸው የምስክር ወረቀት ብቻ ነው። ታምራት “ዓላማችን ኃላፊነት መወጣት ነው። ሀገራችን ብዙ ሰጥታናለች። እኛ ምን ማድረግ አለብን ብለን መጠየቅ ይገባናል። መልካሙን ነገር ማየት ወደ ጥሩ ተግባር ይገፋፋናል። ወደፊት ከአዲስ አበባ ውጭም ለመሥራት አስበናል“ ይላል። 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top