ቀዳሚ ቃል

ሂስ እና ሃያሲ

ሃያሲ የሥነ-ጥበብን ገፅታ ተፅፎ ከቀረበው፣ ተቀርፆ ከቆመው፣ ተስሎ ከሚታየው፣ በላይ ያየበትን ጎን ፍዘቱን፣ ድምቀቱን፣ ለይቶ በማውጣት ያሳያል። የከያኒውን ሥራ፣ እንደ አቀራረቡ መርምሮ እንደመረጠው መንገድ አደራጅቶ ያቀርባል።

በሀገራችን በየዘመኑ የነበሩ፣ ለጥበቡ ያዳሉ፣ የሥነ-ጥበብ ውጤቶችን መዝነው፣ ለተደራሲያን ያቀረቡ ጥቂቶች እንደነበሩ ይታወቃል።

 ይሁን እንጂ ዛሬም ድረስ የሙያው እንግዳነት ተቀርፏል፣ ከሃያሲ ጋር ያለው ርቀት ጠብቧል ማለት አይቻልም። ቀድሞም ቢሆን ከተለመደው የዕለት ተዕለት አባባል ጋር ተደባልቆ ሙያው “አቃቂር”፣ “ግምገማ” ከሚሉት ጋር ተዛምዶ ሃያሲው “አቃቂር አውጪ” የሚል ስያሜ አግኝቶ እንደነበር ይታወቃል። እንደሌላው ዓለም አጀማመር፤ ሃያሲ የከያኒውን የፈጠራ ውጤት ሊያበላሽ፣ ተጨንቆ የተጠበበውን ሥራ ሊያበላሽ እንደተፈጠረ ማሰቡ በእኛም ዘንድ መኖሩ አያጠያይቅም። ሙያውን ተረድቶ ለፈጠራ ሥራዎች ያለውን እገዛ አክብሮ የሃያሲውን ምልከታ፣ የምርምሩን አቅም ከፍታ ተገንዝቦ መከታተሉ፣ ሥራዎቹን በጉጉት መጠበቁ፣ ሰምቶ ወይም አንብቦ ማብላላቱ ላይ ገና ነን ቢባል ማጋነን አይሆንም። ሌላው ቀርቶ ስያሜው ለሥነጽሑፍ ብቻ ተሰጥቶ ሙዚቃን፣ ሥዕልን፣ ተውኔትን ሌሎችንም ዘንግቶ መለኪያው ምን እንደሆነ ሳይታወቅ ሿሚው ማን እንደሆነ ሳይለይ፣ ተሿሚው በተገኘበት መድረክ በመጠራቱ ሳይሸማቀቅ መናገሩ ተለምዷል።

እስከአሁን በሚዲያው የሚጋበዙት ለፈጠራዎቹ ትንታኔ የሚሰጡት ቅርብ ናቸው ተብለው የሚታሰቡት፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ናቸው። መምህራን ውስጥ ሃያሲያን ይገኛሉ። ባይበዙም እንዳሉ ይታወቃል። እነዚህን ሃያሲ ከማለት ይልቅ ተመራማሪ ብሎ ማለፉ ይመረጣል። ሂሳዊ ንባብ እየተባለ እንኳን ሃያሲ ማለት ይፈራል።

ጥልቅ ንባብ በሃሳብ መራቅ፣ በቋንቋ መራራቅ፣ ያመረቷቸውን ሥራዎች ከሌሎች ጋ አዛምዶ፤ ባልታየው መንገድ አዲስ ነገር አሳይተው ሥነጥበቡን የሚደግፉ፣ የተደራሲውን ቀልብ የሚስቡ፣ የከያኒውን መንፈስ የሚያነሳሱ፣ ሃያሲያንን አክብሮ በመያዝ፣ መድረክ አዘጋጅቶ በመጋበዝ፣ ሥነጥበብ እንዳይዳከም ማገዝ ያስፈልጋል። ከሥነጽሑፍ በተጨማሪ በሥዕል፣ በቅርፃቅርፅ፣ በሙዚቃ፣ በተውኔት እና በፊልም ጭምር።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top