በላ ልበልሃ

ሁለት አገሮች፣ አንድ ማህበረ-ሰብ፤ የኮንፌደረሽን ጎዳና ለኢትዮጵያና ለኤርትራ

ተስፋጽዮን መድኃንየ (ፕሮፌሰር)

ብርመን ዩኒቨርሲቲ፤ ጀርመን

ኮንፌደረሽን

ኮንፈደረሽን ሃሳብን የሚቃወሙ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ነበሩ፤ ባሁኑ ወቅት ስለ ኮንፈደረሽን ያለው አመለካከት እየተሻለ መጥቷል። የሁለቱ አገሮች ተነጣጥሎ መኖር ካለው እውነታ ጋር የማይጣጣም መሆኑ ባሁኑ ጊዜ በተግባር እየታየ ነው። ኢትዮጵያና ኤርትራ በይፋ ቢፋቱም በመሬት ላይ ያለው እውነታ የሚመሰክረው በተግባር ያልተለያዩ መሆናቸውን ነው። ኤርትራውያን ከኢትዮጵያውያን ጋር ተሳስረዋል፡ ተዛምደዋል። በስደት አብረው ይኖራሉ። አንዳንዶቹ ተጋብተው ትዳር መሥርተው በፍቺ ምክንያት ኤርትራም ኢትዮጵያም ብዙ ችግር እያሳለፉ ናቸው። በተግባር አልተለያዩም ብቻ ሳይሆን፤ እንድያውም ሊለያዩ አይችሉም ማለት እደፍራለሁ።

 ስለ ኮንፌደረሽን ያለው ትርጉም አሁን የተሸለ ቢሆንም በቂ አይደለም። ኮንፈደረሽን ማለት የሁለት ወይም በቁጥር ከዚያ የበለጡ ሉዓላዊ አገሮች ህብረት (ዩኒዮን) ማለት ነው። አባል አገሮቹ ለህብረቱ የተወሰነ ሃይል ወይም ስልጣን ይሰጡታል። ህብረቱ እነርሱ ካስተላለፉለት በላይ ሃይል ወይም ስልጣን የለውም።

 አንዳንድ የኮንፌደረሽን አገሮች ከወራሪዎች ለመከላከል የሚያቆሙት ጊዜያዊ ህብረት ነበር። የጋራው ችግር – ወራር ይሁን ሌላ – ካቆመ በኋላ ኮንፈደረሽኑ ያበቃል። እንዲህ ዓይነት ኮንፈደረሽን ወደ ፈደረሽን ይሁን ወይም ወደ ሌላ ዓይነት ውህደት ሊያመራ አይችልም።

 ሌላው ዓይነት ኮንፈደረሽን ለተወሰነ ጉዳይ ተብሎ የሚቋቋም ትብብር ሳይሆን በይዘቱ ሰፊ ወይም አጠቃላይ ጊዜያዊ ሳይሆን ቀጣይ የሆነ ነው። ይዘቱ እየጨመረ ሄዶ የአገሮቹ ዝምድና እያደገ እና እየጠነከረ ይመጣል። እንዲህ ዓይነቱ ኮንፈደረሽን እስከ ፈደረሽን፡ እስከ ውህደትም ሊደርስ ይችላል። የዚህ ዓይነት በአሜሪካና በጀርመን ታሪክ ውስጥ ይታያል።

ፌደረሽን እና ኮንፌደረሽን

ፈደረሽን ከኮንፈደረሽን ይለያል። በፈደረሽን የሚተሳሰሩት አገሮች ሉዓላዊ አይደሉም፤ ለማእከላዊው መንግስት ይታዘዛሉ። ተደምረው የሚያቆሙት አንድ ሉአላዊ አገር ነው፡፡

የኮንፌደረሽን ዝምድና በተለያዩ ስሞች ይጠራል። ለምሳሌ ማህበረ-ሰብ (አውሮጳ)፡ ህብረት (አውሮጳ)፡ የነፃ ሀገሮች ኮሞንወልዝ (ሩሲያና ሌሎች)፡ ሊግ (በተለይ በድሮ ዘመን) ወዘተ።. የዝምድናው ይዘትም ይለያያል፤ አባል አገሮቹ የተስማሙበት ነው የሚሆነው። በዘመናችን አብዛኛውን ጊዜ ኮንፈደረሽን ሲባል መከላከያን፣ ውጭ ጉዳይንና አለማቀፋዊ ንግድን በተመለከተ የጋራ ተቋማትና የጋራ ፖሊሲ ይኖሩታል። እንዲሁም በአውሮጳ ህብረት ታሪክ እንደታየው የአገሮቹ ድንበሮች በበለጠ ክፍት እየሆኑ መጥተው ዜጎቹ በተዛመዱት አገሮች ሁሉ ሊኖሩ፣ ሊሰሩ፣ ሊነግዱ እና ንብረት ሊያፈሩ ይችላሉ ማለት ነው።

የአንድ ኮንፌደረሽን ግብ ዝምድናው እያደገ መጥቶ በሂደት እስከ ሙሉ ውህደት መድረስ ይችላል። ይህ ግን ግቡ ምን እንደሆነ በስምምነቱ ይጠቀሳል ማለት አይደለም፤ ከይዘቱ መገንዘብ ይቻላልና።

ከፌደራላዊ ዝምድና አስተማማኝ ጠንካራና ታዳጊ የሚሆነው የአወቃቀሩ ሂደት ህዝባዊ መሠረት ሲኖረውና በህዝብ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት።

 ስትራቴጂ መጨረሻውን ግብ ለመሟላት የሚያገለግል ብልሃት ነው ከሚለው ሀቅ ተነስተን ስለ ኮንፌደረሽን ልንገነዘበው የሚገባ መሠረታዊ ነጥብ አለ። ኮንፌደረሽን በይዘት ባለበት የሚረጋ ወይም የማይለወጥ አይደለም። ይሻሻላል፣ ይቀየራል። አንዳንዱ በየጊዜው የሚታደስ ኮንፌደረሽን [Renewable confederation] ይባላል።

ለምሳሌ የኮንፌደረሽኑ ዕድሜ አምስት ዓመት እንደሆነ ይደነገጋል። ከአምስት ዓመት በኋላ ግንኝነቱ ያከትማል ማለት አይደለም። ከአምስት ዓመት በኋላ የኮንፌደረሽኑ ዝምድና ዋናውን ግብ ወይም ራዕይ ለማሟላት ምን ያህል እንደረዳ ይገመገማል። በዚሁ መሠረት ይሻሻላል ያድጋል። ህዝቡ እንደገና በነፃ ሪፈረንደም የታደሰውን ኮንፌደረሽን ያጸድቃል ወይም ይቃወማል። ሪፈረንደም በየጊዜው እየተደጋገመ ኮንፌደረሽኑ ፌደረሽን እስከመሆን ድረስ ሊያድግ ይችላል። የአውሮጳ ህብረት ይህንን ሂደት ተከትሎ እያደገ መጥቶ አሁን ፌደረሽን ለመሆን ተቃርቧል።

 በሌላው በኩል አንድ አባል ሀገር ከኮንፌደረሽኑ በቂ በሆነ መጠን አልተጠቀምኩም ብሎ ከህብረቱ ሊወጣ ይችላል። ለምሳሌ እንግሊዝ በ1973 የአውሮጳ ህብረት አባል ሆና ነበር፤ ባለፈው ዓመት ደግሞ ሪፈረንደም ተካሂዶ ጥቅሟን ለመጠበቅ ከህብረቱ ወጣች። ይህ ሊሆን የቻለው ኮንፌደረሽን የሉአላዊ ሀገሮች ህብረት በመሆኑ ነው።

 የኢትዮ-ኤርትራ ኮንፌደረሽን ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የአፍሪቃ ቀንድ አገሮች በሙሉ በኮንፌደረሽን ሊተሳሰሩ ይይችላሉ የሚል አስተያየት ያላቸው ምሁራን አሉ። በአፍሪካ ደረጃም ኮንፌደረሽን ቢያንስ እንደ ራዕይ ይታሰባል። በተጨባጭ ኮንፌደረሽንን አስመልክቶ ውይይት የተካሔደበት የደቡብ ሱዳን ጥያቄ ነበር። ሞዋቹ ጆን ጋራንግ (ዶክተር) የኮንፌደረሽን ስርዓት ለሱዳን በጠቅላላ መፍትሔ ይሆናል የሚል አቋም ነበረው። ይሁን እንጂ በቂ ድጋፍ አላገኘም። በሪፈረንደም ደቡብ ሱዳን ተገነጠለች።

በአፍሪካ ቀንድ አገሮች ምን ያህል ስኬታማ ይሆናል በሚለው ላይ የሀሳብ ልዩነት ሊኖር ይችላል። በኮንፌደረሽን ለመተሳሰር ታሪካቸው እና ሁኔታቸው በእጅጉ የሚፈቅድላቸው ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ናቸው። በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ እና በተፈጥሮ ፀጋ እርስ በርሳቸው የሚፈላለጉ ወይም ተደጋጋፊ (ኮምፕሊመንታሪ) ናቸው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ መሬት እና ውሃ ሲኖራት፤ ኤርትራ ደግሞ አስፈላጊ የሆኑ የባህር በሮች አሏት። ህዝቦቹ አንድ ዘር ወይም አንድ ነገድ ናቸው። ባህሎቻቸው በአብዛኛው አንድ ካለበለዚያ እጅግ ተመሳሳይ ናቸው። ዋናዎቹ ሃይማኖቶች ክርስትና እና እስልምና በሁለቱም ናቸው። ድንበሮቻቸው አውሮጳዊ ቅኝ ግዛት የፈጠረው ነው። የነገድ ወይም የባህል ክልሎች አይደሉም። በአብዛኛው አንድ ናቸው እርስበርሳቸው ይተዋወቃሉ። ይግባባሉ። ለዘመናት አብረው ኖሮዋል። ተዛምደዋል። ተዋልደዋል።

ንካራ እና ደካማ ጎኖች

 የኮንፈደረሽንን ራእይ በኢትዮጵያና ኤርትራ መሃከል ይሁን በአፍሪካ ቀንድ ደረጃ የሚያራምድ ሃያል ወይም በህዝቦቹ ተቀባይነት ያለው መሪ ይሁን ንቅናቄ የለም። ጥያቄውን በተመለከተ በኢትዮጵያና በኤርትራ ልሂቃን መሃከል በቂ መግባባት የለም። እያንዳንዱ  ሀገር ከኮንፈደረሽኑ እንዴትና ምን ያህል ይጠቀማል በሚለው ጥያቄ ላይ አለመግባባት ያለ ይመስላል።

 ሀገሮቹ ወይም መንግስታቱ ሉዓላዊነታቸው እያነሰ ቢመጣም እጅግ ቀናተኞች በመሆናቸው ለኮንፌደራላዊ ውህደት የተወሰነ ስልጣን ማስረከብ በሚለው ሃሳብ ይሰጋሉ።

 ኮንፈደረሽን የመገነጣጠልን አደጋ በማስቆም ላይ ትልቅ ሚና ይኖረዋል። በኢትዮጵያና በኤርትራ መሃከል የሚቋቋመው ኮንፈደረሽን አቅጣጫው አንድነታዊ ነው። ጨርሰው በህግ የተለያዩ ሁለት ሀገሮች በኮንፈደረሽን መተሳሰር ሲጀምሩ ወደ አንድነት እየመጡ ናቸው። በሁለቱ ሀገሮች መሃከል የሚሰፍነው የፖለቲካ አየር የአንድነት ሆኖ በውስጣቸው ባለው የህዝቦች ወይም ብሄሮች ግንኙነት ላይም አንድምታ ይኖረዋል። በሌላ አነጋገር ኮንፈደረሽኑ የብሄሮች ዝምድናን በተመለከተ አርአያነት ይኖረዋል። የመለያየትንና የመገንጠልን ስነ-አእምሮና አዝማሚያዎች እያዳከመ መቀራረብንና ወንድማማችነታዊ ዝምድናን ያበረታታል። ስለዚህ ኮንፈደረሽን ለሁለቱ ሀገሮች ቀጣይ ህልውና አስፈላጊ ነው ማለት ይቻላል። ሰላማዊ ግንኙነትን ያጠናክራል፤ ጥላቻን በመቆጣጠር ጦርነትን ሊያስወግድ ይችላል፤ ለመረጋጋት ለዕድገት ተስማሚ ነው፤ በሁለቱም ሀገሮች የመንቀሳቀስና የመኖር ነፃነት ስለሚኖር፤ በድንበር ሰበብ የሚኖረው ግጭት አነስተኛ ይሆናል። ኮንፈደረሽን ለሁለቱም ሀገሮች ሰፊ ገበያ ያቀርብላቸዋል። የሚያመርቱትን ለመሸጥ ዕድል ያገኛሉ። ይህም ለዕድገት ጠቃሚ ይሆናል።

 ኮንፌደረሽኑ በደምብ ሥራ ላይ ከዋለ ሁለቱን ሀገሮች ያበለፅጋል። ያሳድጋል። ይህም ሲሆን ሉአላዊነታቸው ይጠነክራል። ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በኮንፌደረሽን ተሳስረው በመጠንከር ሉአላዊነታቸውን በማጠናከር ለአፍሪካ ኩራት፣ ተስፋ እና አብነት ሊሆኑ ይችላሉ።

አስተዋይና ሀገር ወዳድ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ጨምሮ ከዚህ ጋር በተያያዘ የወደብ ጉዳይ በተለይ ዓሰብን በተናጠል ያነሳሉ። እንደሚመስለኝ፡ ኮንፈደረሽኑ ይጀመር እንጂ ይህ ጉዳይ አከራካሪ አይሆንም። አለመግባባቶች ኮንፈደረሽኑ ከተቋቋመ በኋላ የሚፈቱበት ዘዴዎች ይፈጠራሉ።

 አንዳንድ ኤሪትራዊያን ኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላታችን ናት ብለው የሚከራከሩ አሉ። ይህ የተሳሳተ አመለካከት ነው። ይህ አመለካከታቸው በጣም የተሳሰተ ነው። እንኳንስ ኢትዮጵያና ኤርትራ በታሪክና በባህል በተራራቁ ሀገሮች መካከል ቋሚ ጥላቻ የሚባል የለም። እንዲያውም ጠላቶች የነበሩ አገሮች ወዳጆችና ተባባሪዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ በታሪክ ታይቷል። የፈረንሳይና የጀርመን ታሪክና ያሁኑ ዝምድና አንድ አብነት ነው።

ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በተለይ የደጋው ኤርትራውያን ረጅም የጋራ ታሪክና የተሳሰረ ባህል እንዳላቸው አያውቁም። ኤርትራውያን ለኢትዮጵያ ነፃነትና ዕድገት ያደረጉት አሰተዋፅኦ ምን ያህል ታላቅ መሆኑን አይረዱም። ይህ የኤርትራ ልሂቃን ይህንን ክስተት ለማረም ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።

 ኮንፈደረሽን እንዲሁ በችኰላ በማንኛውም ሁኔታና ጊዜ የሚቋቋም ነገር አይደለም። አስቀድመው መሟላት ያለባቸው ነገሮች አሉ። የኢትዮጵያና የኤርትራ ዜጎች ኮንፈደረሽን ምን ማለት እንደሆነና እንዴትስ እንደሚጠቅማቸው መጀመሪያውኑ መረዳት ያስፈልጋቸዋል። ለእዚህም በሁለቱ ሀገሮች ነጻ ውይይትን የሃሳብ መለዋወጥን እና ለፖለቲካዊ ዓላማ መደራጀትን የሚፈቅድ ዲሞክራስያዊ የሆነ ስርዓት መኖር አለበት።

 በኢትዮጵያና በኤርትራ እንዲህ ዓይነት ስርዓት ሲሰፍን ህዝቦቹ የኮንፈደረሽንን ጥያቄ በተመለከተ ሃሳባቸውንና ፍላጐታቸውን በሙሉ ነጻነት ሊገልጹ ይችላሉ። ኮንፈደረሽን እንዲህ በመሰለ ሁኔታ ሲከሰት አጥጋቢ አስተማማኝ እና በውህደት አቅጣጫ የሚያድግ ይሆናል።

 ማጠቃለያ

 የኮንፈደረሽንን ሂደት ለማስተጋባት መሟላት ስላለባቸው ሁኔታዎችና ቅደም-ተከተላቸው ምን እንደሚመስል መጠነኛ ሃሳብ በማቅረብ መልእክቴን ማጠቃለል እወዳለሁ።

 በኢትዮጵያም በኤርትራም ባሁኑ ወቅት ሁኔታዎቹን ሊያረጋጋ የሚችል ተቋም አንጋፋዎቹን የፖለቲካና የሲቪል ህብረተ- ሰብ ቡድኖች ያካተተ የሽግግር መንግስት ያስፈልጋል ነው። በኢትዮጵያ አሁን የለውጥ ሂደት የተጀመረ ይመስላል። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አቢይ አሕመድ በሀገር ውስጥም በውጭም ከፍ ያለ ተቀባይነት አግኝተዋል። የዶክተር አቢይ አስተዳደር የለውጡ ሂደት እንዲቀላጠፍና የሚፈለገው የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ብልህና ቆራጥ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል።

በመቀጠልም በይዘቱ ከብሄራዊ አንድነት መንግስት ከዲሞክራሲ እና ከአድማሳዊ የሰብአዊ መብቶች አዋጅ ጋር የሚጣጣም ህገ- መንግስት ተነድፎ በህዝብ ይፀድቃል። በህገ- መንግስቱ መሰረት ምርጫ ተካሂዶ መለያው የብሄራዊ አንድነት መንግስት የሆነ ስርዓት ሀገሮቹን ያስተዳድራል።

 የሁለቱ ሀገሮች ህገ-መንግስታትና ሌሎች ህጎች እንዲሁም መሰረታዊ ፖሊሲዎች

 የሚጣጣሙ ወይም ተመሳሳይ እንዲሆኑ ይደረጋል። መንግስታቱ የኮንፈደረሽን መቋቋምን በተመለከተ ድርድርና ተዛማጅ ሂደቶች ይጀምራሉ። ከዚህ ጋር በተያያዘ ስለኮንፈደረሽን ትርጉምና ሊገኙ ስለሚችሉት ጥቅሞች የሁለቱ ሀገሮች ህዝብ አስፈላጊው ግንዛቤ እንዲኖረው ህዝባዊ ውይይት (ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን አብረው የሚሳተፉበትን ጨምሮ) እንዲደራጅና እንዲካሄድ ይደረጋል። ኮንፈደረሽንን በማቋቋም ላይ በሁለቱ ሀገሮች ሪፈረንደም ይካሄዳል። ውጤቱ ሃሳቡን የሚደግፍ ሲሆን የኮንፈደረሽኑ ጉዞ ይጀመራል።

 ኮንፈደረሽኑ እውነታው በሚፈቅደው ከፍተኛ የጋራ ተቋማትና የጠበቀ ግኑኝነት እንዲነሳ ተደርጎ ይነደፍና የመጀመርያው ኮንፈደረሽን ዕድሜ 5 ዓመት ይሆናል። አምስት ዓመት ሲያልቅ እንደገና ረፈረንደም ይካሄዳል። በ5ቱ ዓመታት ዝምድናው ምን ያህል የህዝቦቹን ህይወት ለማሳደግ እንዳገለገለ ይገመገማል። ኮንፈደረሽኑ አጥጋቢ ፍሬ ሰጥቷል ከተባለ ይዘቱ ከፍ እንዲል ተደርጎ በሁለቱ ሀገሮች ህዝቦች ነፃ ፍላጎት ይሻሻላል። ይህ ማለት ኮንፈደረሽኑ ሀገሮቹን በበለጠ በሚያቀራርብ መልክ ይታደሳል ማለት ነው። እንዲህ እያለ ኮንፈደረሽኑ በውህደት አቅጣጫ ያድጋል። ይህ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል። ችኰላን ማስወገድ አለብን። በቅርብ ታሪካችን በችኰላ የተወሰዱ አላስፈላጊ እርምጃዎች እያጉላሉን ያሉ ችግር ፈጥረውብናል።

የኮንፈደረሽን ሃሳብ ብዙ ለኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ለኤርትራ ህዝብ በጎ የማይመኙ ጠላቶች አሉት። በደቡብ ሱዳን ጉዳይ እንደታየው ጠባብ አመለካከት ያላቸው አንዳንድ ተንቀሳቃሾች መገንጠልን ነፃነት ብለው ወደሱ፤ ኮንፈደረሽንን ደግሞ ባርነት ብለው ኰነኑ። እንዲህ የመሰለ አሉታዊ አመለካከት ደቡብ ሱዳን ተገንጥላ አሁን ጨለማ የነገሰባት ሀገር ሆናለች።

 ኮንፌደረሽኑ በጥንቃቄ ከተተገበረና አካሄዱ ከአማረ ህዝቦቹን በበለጠ ከአረካ፣ ከአቀራረበ፣ ከአፋቀረና ካስተማመነ ኮንፈደረሽኑ በውህደት አቅጣጫ ያለማቋረጥ ያድጋል። በህዝቦቹ ሙሉ ፈቃድ መጨረሻው ፌደረሽን ሊሆን ይችላል።

ይህ ፅሑፍ ለመድረክ የቀረበ ሲሆን፤ ለመጽሔት በሚሆን መልኩ የተስተካከለ ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top