ፍልስፍና

ፍልስፍና ለምን ዳቦ አይጋግርም ፍልስፍና ለኢትዮጵያ (ክፍል ፪)

ባለፈው ጽሑፌ የፍልስፍናን ምንነትና ታሪካዊ ሚናውን እንዲሁም ሁለንተናዊ ፋይዳውን ለማሳየት ሞክሬያለሁ። የተስተካከለ ሰብዕናን በመገንባት፣ የአስተሳሰብ ልኅቀትን፣ መስተጋብራዊ ሰናይነትንና ባህርያዊ ቀናነትን በማምጣት ፍልስፍና ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አይተናል። ማኅበራዊ ተቃርኖዎችን በማበጠር በየዕለት እንቅስቃሴዎቻችን የምንጋፈጣቸውን ፍዳዎች በመለየት የሰዎችን ነጻነት ለማጎናጸፍ ፍልስፍናዊ መንገድን መከተል የሞት ሽረት ጉዳይ ነው። ያለ አስተሳሰብ ልኅቀትና ምክንያታዊነት ቁሳዊ እድገት የእንቧይ ካብ ነውና ቀጣይነት ያለው ብልጽግናን ሊያረጋግጥ አይችልም። በዚህ ክፍል ደግሞ ፍልስፍና በኢትዮጵያ የሚኖረውን ሚና ለማየት ተሞክሯል።

አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ማንበብና መጻፍ በማይችልባት፣ የተማረውም አካል ለፍልስፍና ቅርብ ባልሆነባት፣ ፍልስፍና እንደ እሾህ በሚፈራባት ኢትዮጵያ ፍልስፍና ምን ሚና ሊጫወት ይችላል? ይልቁንም በአሁኒቷ ኢትዮጵያ የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ምህዳር ፍልስፍና ምን ሚና ይኖረዋል? ጥያቄዎቹን በዚህ አጭር ጽሑፍ ለመመለስ ከባድ ነው። መጀመር የነበረብን ፍልስፍና በኢትዮጵያ ወይም የኢትዮጵያ ፍልስፍና ምን ይመስላል? ከሚለው ጥያቄ ነበር። ከመጀመሪያው ክፍል ጋር እንዲስማማ አጠቃላዩን የፍልስፍና ትርጓሜና ፋይዳ በመያዝ ላለንበት ነባራዊ ሁኔታ ፍልስፍና ምን ሚና እንደሚጫወት ማሳየቱ የተሻለ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ጊዜና ቦታ ሲገኝ የኢትዮጵያን ፍልስፍና ነገር በሰፊው እንነጋገርበታለን።

 ለዚህ ጽሑፍ ያመች ዘንድ ፍልስፍና በትውልዶች መካከል ጤናማ የመንፈስ ትስስርና በባህሎች መካከል በጎ ተግባቦትን በመፍጠር ረገድ የሚጫወተውን ሚና ለማሳየት እሞክራለሁ። እኔ ኢትዮጵያ የምላት በታሪክና በፖለቲካዊ መልክአ ምድር፣ በዘመን ሂደት ውስጥና በገዥ መንፈስ መፈራረቅ ስትጠብና ስትሰፋ፣ የተለያዩ ሃይማኖታዊና ሀገረሰባዊ አስተሳሰቦች እንዲሁም ፍልስፍናዎች አውድማ በመሆን አሁን ላለንበት ማህበራዊ እኔነት የትርጓሜ መሠረት የሆነች በዓለማቀፍ ማኅበረሰብ እውቅና ያላትን ሉዓላዊት አገር ነው። ኢትዮጵያውያን የምላቸው ደግሞ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኙ፣ በህጋዊ መስተዳድር፣ ዜግነታዊ መብትና ግዴታ እንዲሁም በሥነ ልቦናዊ ፈቃድ ራሳቸውን ኢትዮጵያውያን ብለው የሚጠሩትን ሁሉ ነው። በነዚህ አካላት አእምሮ ውስጥ ትናንትን የሚዘክሩበት፣ የዛሬ የርስ በርስ ግንኙነታቸውን የሚበይኑበት፣ እንዲሁም የነገን የጋራ እጣ ፈንታ የሚተነብዩበት የፖለቲካ ኢኮኖሚ መስተጋብር እንዳላቸው እሙን ነው። የዚህን መስተጋብር ቀና

“እውነትን፣ ምክንያታዊነትን፣ ቀናነትንና ሰብዓዊነትን አጉልቶ በማሳየት በቀል የሚተፉ ብሔር ተኮር ብእሮችን ዝም ማስባል ካልተቻለ ተያይዞ መጥፋት የጋራ እጣ ፈንታችን መሆኑ ነው። በዚህ ውስጥ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴትን ጠቅሰው ጨቋኝና ከፋፋይ የሆኑ “በሬ ወለደ” ዓይነት ዲስኩሮችን በሥነ አመክንዮአዊ መንገድ በማጋለጥ ያራማጆቻቸውን አፍ በማዘጋት የገዳዮችን ሰይፍ ማዶልዶም የሚቻለው ፍልስፍናዊ በሆነ ውይይትና ክርክር ነው”

መንገዱን በማሳየትና መልካም ግቡን በማሳካት ጉዞ ውስጥ ፍልስፍና በታሪክ ንባብ ዘይቤያችንና በባህሎች ተግባቦት ውላችን ውስጥ እንደ አስታራቂ ሽማግሌ፣ ታዛቢ ምስክርና ፈራጅ ዳኛ በመቁጠር የማኅበራዊ ስነ ልቦናዊ በሽታችን ሐኪም መሆን እንደሚችል ማሳየት ነው የዚህ ጽሑፍ ዓላማ። በዚህ ዘመን ትልቁ የኢትዮጵያ  ችግር ለታሪክ ያለን አረዳድና ታሪክን የምንጽፍበት፣ የምናነብበትና የምንተረጉምበት መንገድ ነው። ሰው አስታዋሽ ፍጡር ነው። ትናንትናውን ደስታና ሐዘኑን አዝሎ የሚኖር። የነባራዊ ገጠመኙን ብቻ ሳይሆን የወላጆቹን ተግዳሮቶችና ጸጋዎች በተለያየ መንገድ የሚዘክር ፍጡር ነው ሰው። ኢትዮጵያውያን በሁለቱም ሃይማኖቶች (ክርስትናና እስልምና)፣ በሁሉም አገር በቀል እምነቶች ውስጥ ለሙታን ዝክር ማድረግና የሙታን መንፈስ ከኅያዋን ጋር አብሮ እንደሚኖር ይታመናል። ያባቶች መንፈስ ግዘፍ ነስቶ ከኛ ጋር ይኖራል። በዚህም ታሪክ በነባራዊ ሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል ማለት ነው።

 ታሪክ ደግሞ የራሱ የሆኑ ችግሮች አሉት። ከነዚህ ውስጥ የተራኪው ወገንተኝነት፣ የገጸ ባህርያቱ ውሱንነት (ሁሉን አለማካተቱ) እንዲሁም የታሪካዊ ሁነቱ ሙሉ በሙሉ አለመቀረጹ ዋነኛ የታሪካዊ ድርሰት እንከኖች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት፣ እና እኔ ብቻ አዋቂነት ታሪክን ከመማሪያነት ወደ ግጭት መንስኤነት ይቀይረዋል። ይህም ብቻ አይደለም። ታሪክን በዘመኑ መንፈስ ከመረዳት ይልቅ ያለፈን በዛሬ ሚዛን በመለካት የዘመኑ መንፈስ በማይጠይቀው መነጽር በመመልከት፣ ፍርድ ሰጭ በመሆን፣ የፍርዱ ሰለባዎችን ውክልና በመፈለግ፣ የ“አንተ-እኔ” ልዩነትን በመፍጠር አሁናዊ ተግባቦትን በትናንትናዊ ክዋኔ እንወስነዋለን። የታሪክ ንባባችን የጋራ ዳራና ትናንትናዊ አንድነት የሌለን እንደ ቅርጫት ፍራፍሬ በአስገዳጅ ኃይል ታፍነን የኖርን ህዝቦች አስመስሎ ይስለዋል።

 እዚህ ላይ ነው የፍልስፍና ጣልቃ ገብነት የሚያስፈልገው። ታሪክን እንደገና መጻፍ አይቻልም። አላፊን ክዋኔም ማረቅ እንዲሁ አይቻልም። ግን ደግሞ ታሪክን መመርመር ያስፈልጋል። ምክንያታዊ የታሪክ አረዳድ ያስፈልጋል። የተነገረው ሁሉ አልተደረገም፣ የተደረገው ሁሉ ደግሞ አልተነገረም። ዛሬን ላለማስታወስ ትናንትን ብቻ መዘከር የለብንም፣ ትናንትን ለመዘከር ደግሞ ዛሬ መዘንጋት የለበትም። በታሪክ ውስጥ ሁለት መሠረታዊ ነገሮች ያስፈልጋሉ። የሚዘነጋውን መዘንጋት የሚታወሰውን ማስታወስና የሚያዘውን መያዝ ይቅር የሚባለውን ደግሞ ይቅር ማለት። ፍልስፍና በታሪክ ንባብ ውስጥ ትልቁን ሚና የሚጫወተውም የተራኪውን ብዕር ከስሜታዊነት ይልቅ በምክንያታዊነት ማለዘብና የአንባቢውን ስነ ልቡና ታሪኩን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተገንዝቦ በታሪኩ ተዋናይ ቦታ ራሱን እንዲያስቀምጥ በመጋበዝ የዘመኑን መንፈስ ተካፋይ ማድረግ ማስቻል ነው። ከሁሉም በላይ ሄግል እንዳለው የታሪክ ጉዞ የሰዎችን መንፈስ ወደ አንድነት የማስተሳሰር የተቃርኖ ጉዞ ነውና ያለፈን ስንዘክር ከአንብሮው (Thesis) ጨልፈን ተቃርኖውን (Antithesis) ገድፈን መልካም አስተጻምሮ (Synthesis) ላይ ሊያደርሰን ይገባል። በኢትዮጵያውያን የታሪክ አረዳድ ውስጥ ፍልስፍና ይህንን ፋይዳ ያበረክት ዘንድ እድሉ ሊሰጠው ይገባል። በተራኪዎችና በአንባቢዎች እያረረ ያለውን ዳቦ ለመጋገር እና በዚህ የታሪክ አረዳድ ልዩነት እየጠወለገ ያለውን የተግባቦት ሰንሰለት ለማከም ፍልስፍናዊ መንገድ የተሻለ አማራጭ ነው።

 ሁለተኛው የዘመኑ ተግዳሮታችን ባህል ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ነው። ለመሆኑ ባህሎች የራሳቸው የሆነ ድንበር አላቸውን? ሳሙኤል ሃንቲንግተን The Clash of Civilizations በሚለው መጽሐፉ ቀጣዩ የዓለም ጦርነት በባህሎች መካከል በሚፈጠር ሽኩቻ ወይም ውድድር የሚመጣ እንደሆነ ይተነብያል። ስጋቱ ምክንያታዊ ነው። አሁን በምናያት ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ዓይነት ሥጋት ከስጋት አልፎ የግጭት መንስኤ ሲሆን እያየን ነው። ማንነትን መሠረት ያደረገ የሚመስለው ፌደራሊዝም የወለዳቸው መከላለሎችና የማንነት ፍረጃዎች “የአንተ-የእኔ” ማንነት ቀጠናዎችን ፈጥረዋል። ይህ የማንነት ቀጠና ባንድ በኩል ከላይ እንዳየነው ታሪክን መሠረት ያደረገ ሲሆን በዋናነት ግን ባህልንና “ዘርን” ተገን አድርጎ የተፈጠረ የሞት ቀዳዳ ነው። ይህንን ቀዳዳ የሚደፍን የተግባቦት ድልድይ ከመገንባት ይልቅ ሸለቆውን በሚያሰፋ የባህልና የማንነት ጎርፍ የሚሸረሽሩ ኢምክንያታዊ ዲስኩሮች በማንኛውም መንገድ እየተለቀቁ የጉስቁልና ሕይወትን እንድንመራ ምክንያት ሆነውናል። በዚህ በኩል ፈላስፎች የሰዎችን ዲበአካላዊ አንድነትና የባህሎችን መንፈሳዊ ትስስር በማሳየት ረገድ የማይነጥፍ ብዕራቸው በታዳጊነት ይሰለፍ ዘንድ ከምንም ጊዜ በላይ ያስፈልገናል ። ፈላስፋ ወገን የለውም ፣ የፖለቲካና የባህል፣ የብሔር የሚባል ዶግማና ቀኖና የለውም። እውነትን፣ ምክንያታዊነትን፣ ቀናነትንና ሰብዓዊነትን አጉልቶ በማሳየት በቀል የሚተፉ ብሔር ተኮር ብእሮችን ዝም ማስባል ካልተቻለ ተያይዞ መጥፋት የጋራ እጣ ፈንታችን መሆኑ ነው። በዚህ ውስጥ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴትን ጠቅሰው ጨቋኝና ከፋፋይ የሆኑ “በሬ ወለደ” ዓይነት ዲስኩሮችን በሥነ አመክንዮአዊ መንገድ በማጋለጥ ያራማጆቻቸውን አፍ በማዘጋት የገዳዮችን ሰይፍ ማዶልዶም የሚቻለው ፍልስፍናዊ በሆነ ውይይትና ክርክር ነው።

 ሦስተኛ ፖለቲካ ኢኮኖሚያዊ ተቃርኖዎች የወለዱት ጤናማ የሆነ ኢኮኖሚያዊ መስተጋብርና ፖለቲካዊ እሴት ለመገንባት እየገጠመን ያለው ተግዳሮት ነው። ይኸ ከሁለት አካላት የሚመነጭ በስውር ስፍ የተተበተበ አብሮነት ያለው የሃብታሞችና የፖለቲከኞች ሴራ ነው። በሃብታምና በድሃው መካከል ያለው ሰፊ ልዩነት፣ በመሪዎችና በዜጎች ፍላጎት ያለ ሆድና ጀርባነት የወለደው የተበላሸ ፖለቲካ-ኢኮኖሚያዊ ምህዳር መታከም አለበት። አገሪቱ ጸጋዋም ፍዳዋም ለሁሉም እኩል እንዳይዳረስ ይህ ካፒታሊዝም የወለደው ውድድር ትልቁ ደንቃራ ነው። ሰዎች በሰውነታቸው እንዳይታዩ ቁስ ከሰው በላይ ከብሮ በሁሉም ኢትዮጵያውያን መካከል መግባባት ሳይሆን ቅራኔን ፈጥሮ የጋራ ነገ እንዳይኖረን እያደረገን ይገኛል። ቢያንስ ምልክቱ በግልጽ ይታያል። ይህ ፖለቲካ- ኢኮኖሚያዊ ስብራት መጠገን የሚችለው የቢዝነስ ሥነ ምግባር የገባቸው ሃብታሞችና የሰዎች ነጻነት ግድ የሚላቸው ፖለቲከኞች ሲኖሩ ነው። በፖለቲካው ረገድ ገዥውም ሆነ ተቀናቃኞች የፈላስፎች ምክርና ተግሳጽ ያስፈልጋቸዋል። እዚህ ላይ ነው ፍልስፍና የሞት ሽረት ጉዳይ መሆኑ የሚታየን።

 የሁሉም አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ችግር ቢሆንም እንደ ወካይና አራተኛ ችግር አድርጌ የምወስደው የትምህርት ዘይቤያችንን ነው። የትምህርት ዘይቤያችን ከታመመ ውሎ አድሯል። በገፍ ማምረት ላይ መሠረት ያደረገው ፖሊሲያችን ጥራቱን ዘንግቶ የሚያስተምራቸው ተማሪዎች ምን ዓይነት ሰብዕና እና እውቀት እንዳዳበሩ እንኳን ማወቅ የሚፈልግ አይመስልም። የትምህርት ፍልስፍና ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ትምህርት ማለት የአንድ ማኅበረሰብ ኅሊና ነውና ኅሊናው የታመመ ማኅበረሰብ እንዳንገነባ ትምህርት ላይ ሁሉም ሊረባረብ ይገባል። ፓውሎ ፍሬሬ እንደሚለው ትምህርት ባንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ ተቃርኖዎችንና ጨቋኝ አስተሳሰቦችን በማጥራት ሰብአዊነትን ነጻ ማውጣት አለበት። እርግጥ ነው። የኢትዮጵያ ትምህርት ይህንን ከማድረግ ይልቅ በውጭ ሳይንስና ፍልስፍና እየተመራ ካባህልና ከማንነት የተፋቱ ትውልዶችን እያፈራ ያለ ይመስላል። ከላይ እስከታች ያለው የኢትዮጵያ ትምህርት ለአገር በቀል እውቀትና አስተሳሰብን ለሚያጎለብቱ ትምህርቶች ጀርባውን ሰጥቷል። ከዚህም በተጨማሪ የተማረው አካል የመርዶ ታሪክን በመንገር እና የልዩነት ስስ ብልቶችን በመፈልፈል ተቃርኖዎችን በመፍጠር ላይ አተኩሯል። አድለር የተባለ ጸሐፊና ፈላስፋ ትምህርት ማምረትና ማከም እንዲሁም መገንባት የሚችሉ የሙያተኞች መንጋን ከመፈልፈል ባሻገር እነዚህ አካላት እንዴት በጎ ህሊናቸውን እንደሚጠቀሙበት የሚያስችል የንቃተ ኅሊና ደረጃ ላይ ማድረስ አለበት ይላል። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ትምህርት ፍልስፍናን ማበረታታት ሲጠበቅበት ፍልስፍና በኢትዮጵያም ትምህርትን መተቸትና የትምህርት ፍልስፍናን ማስተካከል ይኖርበታል። ፍልስፍና በልጆች ተቦክቶ በአላዋቂዎች እያረረ ያለውን የኢትዮጵያ ትምህርት ሊያክመው ይገባል።

በመጨረሻም በአለማወቅ ወይም ተሳታፊነትን በማጣት የተገለለውን የገጠር ማኅበረሰብና በስሜት ወለድ የማኅበራዊ ሚድያ ሁካታ የሚታመሰውን ወጣት በሰከነ መንፈስ ወደ ጋራ መግባባት ይመጣ ዘንድ ፍልስፍና ቁልፍ ሚና ሊጫወት ይገባል። ፍልስፍና አስታራቂ ሽማግሌ ነው (ከወገንተኝነት የነጻ)፤ ታማኝ ምስክር ነው (በእውነት ላይ የተመሰረተ)፤ እንዲሁም ፈራጅ ዳኛ ነው (በምክንያታዊነት የፈረጠመ)። ከግለሰብ እስከ ሃገር ጉዳይ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ማኅበራዊ መስተጋብሮችን በበጎነት እንዲመሩ የሚጠቁምና ተቃርኖዎችን በሰለጠነ የውይይት መንገድ የሚፈታ ጠንካራ ግንኙነት ያለው ማኅበረሰብ ለመገንባት ፍልስፍና ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። ከያንዳንዱ ሙያ ጀርባ ፈላስፎች ወይም አስተሳሰባቸው መሪውን ሚና ከተጫወተ በመልካም ተግባቦት ላይ የተመሠረተ ነገን ማለም ይቻላል።

 የኢትዮጵያ ታሪክ፣ የባህሎች ልዩነትና ያለው ፖለቲካ ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ለተለያዩ ኢዲሞክራሲያዊ የሆኑ ነገሮች ተጋላጭ ነው። ይህንን ተጋላጭነት በሰለጠነ መንገድ ማከም ካልተቻለ ችግሩ እየሰፋ ይሄዳል። በማንኛውም መንገድ ለፖለቲካዊ ሴራ ወይም ግላዊ ጥቅም ወለድ ፈጠራዎች ተጋላጭ የሆኑ ስስ ብልቶችን ለማከም የፍልስፍና ትንፋሽ፣ የፈላስፎች ጦርና ጋሻ አስፈላጊ ነው። በዚህም ምክንያታዊ ማኅበረሰብ፣ በሰለጠነ መንገድ ችግሮችን መፍታት የሚችል ዜጋ መገንባት ይቻላል። ከምንጊዜውም በላይ፣ ሁሉም ነገሮች ምክንያታዊ መስለው በሚቀርቡበት በዚህ ዘመን የፍልስፍና የመጠራጠሪያና የማጉያ መነጽር ያስፈልገናል። የአቋም ጥንካሬን፣ ምክንያታዊነትን፣ ቀናነትንና የአስተሳሰብ ጽርየትን ማምጣት የሚቻለው አንዱ መንገድ በፍልስፍና ነውና።

 ሰላም!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top