አጭር ልብወለድ

ጫማ ሠሪውና ሰይጣን

ድርሰት፡- አንቷን ቼኾቭ

ትርጉም፡- መኮንን ዘገዬ

ዕለቱ የገና ዋዜማ ነበር። ማርያ ምድጃው አጠገብ ተቀምጣ ለረጅም ጊዜ እያንኮራፋች ነው። ኩራዙ ጋዙ አልቆ ከጠፋ ቆይቷል። ፍዮዶር ኒሎቭ አሁንም ሥራ ላይ ነው። እስካሁን ሥራውን አቁሞ ወደ ጎዳና ይወጣ ነበር። ያ የኮሎኮልኒ ነዋሪ ደንበኛው ከአስራ አምስት ቀን በፊት ጫማ እንዲሠራለት አዝዞት ስላልሠራለት ትናንትና መጥቶ እንዳይሸጥ እንዳይለወጥ አድርጎ ሰድቦት ለነገ ጠዋት ከቅዳሴ በፊት እንዲያደርስለት ከባድ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶት ነው የሄደው።

 “የባህታዊ ሥራኮ ነው” በማለት ፍዮዶር አጉረመረመ። “አንዳንድ ሰዎች ገና በጊዜ ተኝተዋል፤ ሌሎቹ ደግሞ ራሳቸውን እያዝናኑ ነው፤ አንተ ምስኪኑ ግን እዚህ ተቀምጠህ በውድቅት ሌሊት ማንም የማያደርገውን ጫማ ትሠራለህ …።”

እንቅልፍ እንዳይጥለው አጠገቡ ካለው ጠርሙስ እየደጋገመ ይጎነጫል። ታዲያ በተጎነጨ ቁጥር እንደ ማንገፍገፍ ያደርገዋል። “ለመሆኑ የገናን ዋዜማ ምክንያት በማድረግ ደንበኞቼ ሲዝናኑ እኔ እዚህ ተኮርምቼ የነሱን ጫማ የምሠራበት ምክንያት ምንድነው? እነሱ ገንዘብ ስላላቸውና እኔ ደግሞ ምስኪን ስለሆንኩ ነው?” ሁሉም ደንበኞቹ አስጠሉት። በተለይ ደግሞ ኮሎኮልኒ የሚኖረው ደንበኛው በጣም አስጠላው። አዎ ሰውየው የተከበረ ቢሆንም ሁኔታው ቀፋፊ ነው። ፀጉሩ ረጅም ነው። ፊቱ ቢጫ ነው። ሰማያዊ መነፅር ያደርጋል። ድምፁ ጎርናና ነው። ስሙ ደግሞ የጀርመን ስለሆነ ለመጥራት ያስቸግራል። ምን እንደሚሠራ አይታወቅም። ከአስራ አምስት ቀን በፊት ፍዮዶር የእግሩን ልክ ለመውሰድ ሲሄድ ሰውየው መሬት ተቀምጦ አንድ የሆነ ነገር በሙቀጫ ይወቅጥ ነበር።

ፍዮዶር “እንደምን አደራችሁ?” ብሎ ሳይጨርስ ሙቀጫው ውስጥ ያለው ነገር ተንጣጣና ደማቅ ቀይ ቀለም እያበራ በየአቅጣጫው ተበተነ። የድኝና የተቃጠለ ላባ ሽታ አየሩን በከለው። ቤቱ በጭስ ታፈነ። ፍዮዶር አምስት ጊዜ አስነጠሰው። ወደቤቱ ከተመለሰ በኋላ “እግዜርን የሚፈራ ሰው መቸም እንዲህ ያለ ነገር አይሠራም” ብሎ አሰበ። የሚጎነጭለት ጠርሙስ ባዶ ሲሆን ፍዮዶር የሚሠራውን ጫማ ወረወረና በሃሳብ ጭልጥ ብሎ ሄደ። ትልቅ ጭንቅላቱን በእጆቹ ደግፎ የተስፋ ጭላንጭል ቅንጣት ታህል እንኳ የማይታይበትን የድህነት ሕይወቱን ማሰብ ጀመረ። ቀጥሎ ትልቅ ቤት ውስጥ የሚኖሩትን፣ በሠረገላ የሚፈሱትን፣ የሩብል ረብጣ የሚቆጥሩትን ሀብታሞች አሰበ። “ምን አለ ሰይጣን የነዚህን ሀብታሞች ቤቶቻቸውን ብድግ አድርጎ ቢወስደው፣ … ቢያፈራርሰው፣ ፈረሶ ቸው ቢሞቱ፣ ምን አለ ፀጉራም ኮቶቻቸውና ኮፍያዎቻቸው አርጅተው ቢነትቡና ቢቦጫጨቁ። ምን አለ ቀስ በቀስ ሁሉም ሀብታሞች ለማኝ ቢሆኑና ምስኪኑ ጫማ ሰፊ ሀብታም ሆኖ ለገና ዋዜማ ሌላ ድሀ ጫማ ሰፊ አዝዞ ጫማውን ቢያሠራ” እያለ ሲያልም ቆይቶ ፍዮዶር በድንገት ዐይኖቹን ከፈተ። “አሁን መሄድ አለብኝ” አለ ሠርቶ የጨረሰውን ጫማ እየተመለከተ። “ጫማውን ሠርቼ ከጨረስኩ ቆየሁ ግን እዚሁ ተቀምጬ ቀረሁ። አሁን ጫማዎቹን ወስጄ ለሰውየው ማድረስ አለብኝ።” ጫማዎቹን በቀይ ጨርቅ ጠቀለለና መንገዱን ቀጠለ። የሚወርደው ኃይለኛ በረዶ ፊቱን እንደ መርፌ ይወጋው ጀመር። በረዶው ያንሸራትት ነበር፤ ጨልሟል፤ በጋዝ የሚሠራው የፋኖስ ብርሃን ደብዝዟል፤ በሆነ ምክንያት መንገዱ ሁሉ ጋዝ ጋዝ ይሸት ነበር። ፍዮዶር ሳለና ጉሮሮውን አፀዳ። ሀብታሞቹ የአሳማ ሥጋ አየበሉ፣ ቮድካ እየጠጡ በመኪና ወዲያ ወዲህ ይላሉ። ሀብታሞቹ ወጣት ሴቶች ደግሞ ፍዮዶርን ሲያዩ ምላሳቸውን እያወጡበት “አንተ ለማኝ! አንተ ለማኝ!” እያሉ ያበሽቁታል። ተማሪዎች፣ ወታደሮች፣ ነጋዴዎች ፍዮዶርን እየተከተሉ ጮክ ብለው “ሠካራሙ! ሠካራሙ! ጫማ ሰፊው! ለማኙ” እያሉ ያናድዱታል። ፍዮዶር ይህ ሁሉ የስድብ መአት ሲወርድበት መልስም ሳይሰጥ ዝም ብሎ ይሄዳል። ብቻ አልፎ አልፎ በንቀት ምራቁን ይተፋል። በመሃል ከዋርሶ የመጣ ኩዝማ የተባለ የታወቀ ጫማ ሰፊ አገኘውና “አንዲት ሀብታም ሴት አግብቻለሁ፤ ሠራተኛም ቀጥሬ ማሠራት ጀምሬያለሁ። አንተ ግን አሁንም የምትበላው የሌለህ ለማኝ ነህ” አለው። ፍዮዶር ደንበኛው ቤት እስኪደርስ ድረስ ተከትሎት ሄደ። ደንበኛው የመጨረሻው ፎቅ ቤቱ ሲደርስ ደንበኛው ልክ ከአስራ አምስት ቀን በፊት ያደርግ እንደነበረው፡ ወለሉ ላይ ተቀምጦ አንድ ነገር በሙቀጫ ሲወቅጥ አገኘው።

 “ጫማውን አምጥቼልዎታለሁ” አለ ፍዮዶር። ደንበኛው ከተቀመጠበት ተነሳና ፀጥ ብሎ ጫማውን መሞከር ጀመረ። ፍዮዶር ጎንበስ ብሎ በአንድ ጉልበቱ ተንበርክኮ ከደንበኛው እግር ያደረገውን አሮጌ ጫማ አወለቀለት። ወዲያው በድንጋጤና በፍርሃት በርግጎ ወደ በሩ ተንደርድሮ ሄደ። ደንበኛው የሰው እግር ሳይሆን የፈረስ ሸኾና አይነት ነበር ያለው።

 “እንዴ! ብሎ አሰበ ፍዮዶር፣ አሁን ማምለጥ አለብኝ!” አለ በሃሳቡ።

መጀመሪያ ማድረግ ያለበት ማማተብ ነበር። ከዚያ ሁሉንም ነገር ትቶ በደረጃው በኩል ቁልቁል ለመሮጥ ዳዳ። ግን ለመጀመሪያና ምናልባትም ለመጨረሻ ጊዜ ሰይጣንን እንዳገኘ አድርጎ አሰበ። በዚህ አጋጣሚ ከሰይጣኑ ማግኘት የሚገባውን ነገር ሳያገኝ ማለፉን እንደጅልነት ቆጠረው። እና ራሱን ተቆጣጥሮ እድሉን ለመሞከር ወሰነ። እንዳያማትብ እጆቹን ወደኋላ አቆላለፈ። ቀስ ብሎ ሳለና “ሰዎች እንደሚሉት ከሆነ በምድር ላይ ከሰይጣን የበለጠ ክፉና ሃጢያተኛ የለም። እኔ ግን ጌታዬ ሰይጣን በላቀ ደረጃ የተማረና ያወቀ ነው የሚል ሃሳብ አለኝ። ሸኾናና ጭራ ቢኖረውም ከብዙ ተማሪዎች የበለጠ የማሰብ ችሎታ አለው” አለ።

“በአስተያየትህ ተደስቻለሁ” አለ ሰይጣን በተሰጠው ጥሩ አስተያየት ተሸንግሎ። “ለመሆኑ ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” ጫማ ሠሪው ጊዜ ሳያጠፋ ስለ ኑሮው አጥብቆ ማማረር ጀመረ። ከልጅነቱ ጀምሮ በሀብታም ሰዎች ይቀና እንደነበር ተናገረ። “ሁሉም ሰዎች በትላልቅ ቤቶች ለምን አይኖሩም? ሁሉም ሰዎች ለምን ጥሩ ጥሩ ፈረሶች አይኖራቸውም?” እያለ ያማርር እንደነበረ ለሰይጣን ነገረው። “እኔ ለምን ድሀ ሆንኩ? ኑሮየ ከኩዝማ ለምን አነሰ? እሱ የራሱ ቤት አለው:: ሚስቱ ኮፍያ አላት። ምክንያቱ ምንድን ነው? እኔ ከማንኛውም ሀብታም ጋር ተመሳሳይ የሆነ አፍንጫ፣ እጅ፣ እግር፣ ራስ፣ ጀርባ አለኝ። ታዲያ እኔ በሥራ ስንገላታ ሌሎቹ የሚዝናኑበት ምክንያት ምንድን ነው? ለምንድን ነው ማርያን ያገባሁት? ለምንድን ነው ሽቶ ሽቶ የምትሸት ሴት ያላገባሁት?”

ሀብታም ደንበኞቹ ቤት በሄደ ቁጥር የሚያማምሩ ወጣት ሴቶች ያያል። ዞር ብለው አያዩትም። እንዲያውም አንዳንዴ ካዩት ይስቁበታል። “ምን አይነት ቀይ አፍንጫ ነው ያለው!” እያሉ ይንሾካሾኩበታል::

“ማርያ መቸም ጥሩ፣ ደግ፣ ብርቱ ሠራተኛ ሴት ነች። ብቻ አልተማረችም፣ እጅዋ ጠንካራና ሸካራ ነው፣ በእሱ ስትማታ ደግሞ ታሳምማለች። ከሷ ጋር ድንገት ስለፖለቲካ ብታነሳ ወዲያው የማይረባ ነገር ማውራት ትጀምራለች።”

 “እና አሁን ምንድን ነው የምትፈልገው?” በማለት ደንበኛው ጣልቃ ገብቶ ጠየቀው።

 “የተከበሩ ሰይጣን ኢቫኒቲች ሃብታም ቢያደርጉኝ በጣም ደስ ይለኛል።”

 “በእርግጠኝነት ሀብታም አደርግሃለሁ። አንተ ደግሞ ነፍስህን ትሰጠኛለህ! በል ፈጠን በልና እዚህ ወረቀት ላይ ነፍሴን ሰጥቸዋለሁ ብለህ ፈርምልኝ።”

 “ክቡር ጌታዬ” አለ ፍዮዶር በትህትና በመቀጠል “እርስዎ ጫማ እንድሠራልዎት ሲጠይቁኝ ገንዘቡን በቅድሚያ እንዲከፍሉኝ መቼ ጠየቅሁዎት። ገንዘብ የሚጠየቀው መጀመሪያ የታዘዙትን ከሠሩ በኋላ ነው” አለ።

 “በጣም ጥሩ እንዳልክ ይሁንልህ!” በማለት ደንበኛው ተስማማ። ደማቅ ነበልባል ከሙቀጫው ውስጥ ወጣ። ሐምራዊ ቀለም ያለው ጭስ ተከተለ። የተቃጠለ ላባና የድኝ ሽታ ይሸት ጀመር። ጭሱ እየጠፋ ሲሄድ ፍዮዶር ዓይኖቹን አሸ። አሁን የበፊቱ ፍዮዶር አይደለም። የበፊቱ ጫማ ሠሪ አይደለም። አሁን ፍፁም የተለየ ሌላ ሰው ሆኗል። የሚያምር ልብስ ለብሷል፤ ሰአት አድርጓል፤ የሰአቱ ማሰሪያ ያምራል፤ ግራ እና ቀኝ መደገፍያ ያለው ወንበር ላይ ተቀምጧል። ትልቅ ጠረጴዛ ከፊቱ አለ። ሁለት አስተናጋጆች የተለያየ የምግብ አይነት እያቀረቡለት “ይበሉ ጌቶች፣ የሚበሉት የተባረከ ይሁንልዎ!” እያሉ የምግቡን አይነት ያከታትሉት ጀመር። ፍዮዶር በምግቡ መሃል ምርጥ ቮድካ ልክ እንደ አንድ ጀኔራል ወይም እንደ አንድ መስፍን በደንብ አድርጎ ይጎነጭ ጀመር። በመጨረሻ በአንድ ትልቅ ማሰሮ ሙሉ ማር አቀረቡለት። እራት ከተበላ በኋላ ሰይጣን ሰማያዊ መነፅር አድርጎ ተመልሶ መጣና “እራቱ ተስማማህ?” በማለት ፍዮዶርን በትህትና ጠየቀው።

ፍዮዶር አንድም ቃል መናገር አልቻለም። ከአቅሙ በላይ ስለበላ ቁንጣን ወጥሮታል። ያለበትን ሁኔታ ለመሸፈን ሲል የግራ እግሩን ጫማ እየተመለከተ “ድሮ እኔ ለዚህ ጫማ ብዙ አላስከፍልም ነበር። ለመሆኑ ማነው የሠራው?” በማለት ጠየቀ።

“ኩዝማ ነው የሠራው” በማለት አሽከሩ መለሰ።

“በል ወደዚያ ውሰድና መልስለት!” በማለት ትዕዛዝ ሰጠ።

ኩዝማ ጊዜ ሳያጠፋ መጥቶ በትህትና በሩ አጠገብ ቆመና “ጌታዬ ምንድነው ቅር ያለዎት?” በማለት በትህትና ጥያቄ አቀረበ።

 “በል ዝም በል” አለና ፍዮዶር በግራ እግሩ መሬቱን በንዴት ይመታ ጀመር። “ለመከራከር አትድፈር። ጫማ ሠራተኛ መሆንክን ደሞ አትርሳ! ድንጋይ ራስ! ጫማ እንዴት እደሚሠራ አታውቅም! ለመሆኑ ለምንድነው የመጣኸው?”

 “የሠራሁበትን ገንዘብ ለመውሰድ ነበር።”

 “የምን ገንዘብ? ሂድ ከዚህ! ቅዳሜ ተመልሰህ ና! አሽከር እባክህ አንድ ጥፊ አቅምሰውና አባረው!”

 ግን ብዙም ሳይቆይ በፊት የእሱ ደንበኞች እንዴት ያደርጉት እንደነበር ትዝ አለው። እና በውስጡ ተሰማው። ነገሩን ለመርሳት ከደረት ኪሱ ቦርሳውን አወጣና ገንዘቡን ይቆጥር ጀመር። ብዙ ገንዘብ ነበረው። ቢሆንም ግን ፍዮዶር የበለጠ ገንዘብ እንዲኖረው መመኘቱ አልቀረም። ሰማያዊ መነፅር ያደረገው ሰይጣን ሌላ ወፍራም በገንዘብ የታጨቀ ቦርሳ አምጥቶ ሰጠው። አሁንም የበለጠ ገንዘብ እንዲኖረው ተመኘ። የበለጠ ገንዘብ በቆጠረ ቁጥር የበለጠ  ገንዘብ የመጨመር ጉጉቱ እየበረታበት ሄደ።

ምሽት ላይ ሰይጣን አንዲት በጣም የደላት የተመቻት ቀይ ቀሚስ የለበሰች ሴት አዲስ ሚስት እንድትሆነው ይዞለት መጣ። እየበሉ እየጠጡ እየተሳሳሙ አምሽተው የሚመች አልጋ ላይ ተኙ። ግን እንግዳ ሆነበትና እንቅልፍ ሊወስደው

 “ገንዘባችን በጣም ብዙ ነው። ሌባ ሰብሮ ገብቶ ሊዘርፈን ይችላል። ስለዚህ መብራት አብሪና ቤቱ ሰላም መሆኑን ቃኝው።”

 ሌቱን ደጋግሞ እየተነሳ ገንዘብ የተቀመጠበት ሳጥን ያለ መሆኑን ያረጋግጣል። ጠዋት ወደ ቤተክርስቲያን መሄድ ነበረበት። ሀብታም ሆነ ድሀ የሚያደርሱት ፀሎት አንድ አይነት ነው። ፍዮዶር ድሀ በነበረ ጊዜ “ሀጢያቴን ይቅር በለኝ!” እያለ ነበር የሚፀልየው። አሁንም ሀብታም ሆኖም ፀሎቱ አልተለወጠም። ምንድነው ልዩነቱ? ከሞተ በኋላም ቢሆን ሃብታሙ ፍዮዶር በወርቅ ወይም በዕንቁ አይቀበርም። ያው እንደማንኛውም የመጨረሻ ድሀ ለማኝ አፈር ውስጥ ነው የሚቀበር። ፍዮዶር ይህን ሁሉ “አሜን” ብሎ መቀበል አልፈለገም። ከሚገባው በላይ ስለበላ ደግሞ መፀለይ እንኳ አልቻለም። ሣጥን ሞልቶ ስለተቀመጠው ገንዘቡ፣ ስለሌቦችና በገንዘብ ስለተሸጠችው ነፍሱ ሲያስብ ቆየ።

 ከቤተክርስቲያን ሲወጣ ተናዶ ነበር። ከዚህ በፊት ያደርግ እንደነበረው ጭንቀቱን ለመርሳት ድምፁን ከፍ አድርጎ መዝፈን ጀመረ። ወዲያው  አንድ ፖሊስ መጥቶ ሰላምታ ሰጠውና “ጌታዬ እንደርስዎ ያለ የተከበረ ሰው መንገድ ላይ አይዘፍንም! እርስዎኮ ጫማ ሠሪ አይደሉም!”

ፍዮዶር አንድ አጥር ላይ በጀርባው ተደግፎ ቆመና “ራሴን እንዴት አድርጌ ላስደሰት?” ብሎ በመጠየቅ ማሰብ ጀመረ። ወዲያው አንድ ተሸካሚ መጣና “ጌቶች አጥሩን አይደገፉት ኮትዎን ያቆሽሽብዎታል!” አለው።

 ከዚያ ፍዮዶር ወደ አንድ የሙዚቃ መሣሪያ ወደሚሸጥበት ሱቅ ገብቶ አኮርድዮን ገዛና ሙዚቃውን እየተጫወተ ወደ ጉዳና ወጣ። ሰዎች ሁሉ እያዩ ይስቁበት ጀመር። “የተከበረ ሰው ነው፤ ጫማ ሠሪ ይመስል በጎዳና ላይ ሙዚቃ ይጫወታል?” እያሉ ቀለዱበት።

 “አንድ የተከበረ ሰው በጎዳና ላይ እንደዚህ ሥርአት ማጣት ይገባዋል?” በማለት አንድ ፖሊስ ገሰጠው። “ጌታዬ ወደ አንድ ቡና ቤት ቢገቡ ይሻልዎታል” አለው። ለማኞች ደግሞ ፍዮዶርን ከብበው “ፍራንክ ስጠን! ፍራንክ ስጠን!” እያሉ ያዋክቡት ጀመር። ያኔ ዱሮ ድሀ በነበረበት ጊዜ ለማኞች ዞር ብለውም አያዩትም። አሁን በመንገድ አላሳልፍ ብለዋል።

 ቤት ሲደርስ አዲሷ ሚስቱ ቀይ ቀሚስ ለበሳ አረንጓዴ ሹራብ ደርባ አገኛት። ትኩረቴ አልተለየሽም በሚል ቂጧ ላይ በእጁ ቸብ አደረጋት።

ትክ ብላ አየችውና “የማትረባ! ደንቆሮ! ከተከበረች ሴት ወይዘሮ ጋር ስትሆን ምን ማድረግ እንዳለብህ አታውቅም ማለት ነው? የምታፈቅረኝ ከሆነ እጄን መሳም ነው ያለብህ እንጂ እንደ ወሮበላ ቂጤን እንድትመታኝ አልፈቅድልህም” አለችው በቁጣ።

 “ምን አይነት ኑሮ ነው ሰዎች የሚኖሩት!” ብሎ አሰበ ፍዮዶር። “መዝፈን የለብህም፣ ሙዚቃ መጫወት የለብህም፣ ከሴት ጋር መቃለድ የለብህም … ይገርማል!”

ገና ቁጭ ብሎ ከሚስቱ ጋር ሻይ እንኳ ሳይጠጣ ሰማያዊ መነፅር ያደረገው ሰይጣን መጣና “ፍዮዶር በእኔ በኩል የሚጠበቅብኝን ግዴታ ተወጥቻለሁ። አንተነህ ግዴታህን ያልተወጣህ። ስለዚህ ና ፈጠን በልና መስማማትህን ፈርመህ ተከተለኝ” አለው። ከዚያ በቀጥታ እየመራ ወደ ሲኦል ይዞት ሂደ። ሰይጣኖች ከየአቅጣጫው ተሰበሰቡና “ጅል! ድንጋይ ራስ! የማትረባ! አህያ!” እያሉ በመጮህ ያዋክቡት ጀመር!

 ሲኦል ውስጥ አስቀያሚ የሆነ የጋዝ ሽታ ነበር። በድንገት ሽታው ጠፋ። ፍዮዶርም ዐይኖቹ ተገለጡና ጠረጴዛውን፣ ጫማውንና ትንሽዋን ፋኖስ አየ። የፋኖሱ ጠርሙስ ጠቁሯል። ከውስጡ የሚወጣው የሚገማ ጭስ ከማብሰያ ክፍል የሚወጣ ጭስ ይመስላል። ጠረጴዛው አጠገብ ሰማያዊ መነፅር ያደረገው ደንበኛው ቁሞ በቁጣ “አንተ ጅል! ድንጋይ ራስ! አህያ! ቆይ አሳይሃለሁ! ወሮበላ!

እንድትሰራ የተነገረህ ከአስራ አምስት ቀን በፊት ነበር። ግን እስከአሁን ድረስ ሠርተህ ማስረከብ አልቻልክም። ይህን ያህል ጊዜ አንተ ዘንድ መመላለስ አለብኝ? አንተ እርጉም! አንተ አውሬ!” እያለ ሰደበው። ፍዮዶር ራሱን እየነቀነቀ ጫማውን መሥራት ቀጠለ። ደንበኛው ግን ለረጅም ጊዜ ሲያስፈራራው ቆየ።

 “ጌታዬ ለመሆኑ የአንተ ሥራ ምንድነው?” በማለት ፍዮዶር ጠየቀ።

 “እኔማ የቤንጋል መብራትና የርችት ሠራተኛ ነኝ::”

 የቅዳሴ ሰአት መድረሱን ለማብሰር መደወል ጀመሩ። ፍዮዶር ጫማውን ጨርሶ ለደንበኛው አስረከበ። ከዚያ የሠራበትን ገንዘብ ተቀብሎ ወደ ቤተክርስቲያን ሄደ።

ሠረገላዎችና በበረዶ ላይ የሚንሸራተቱ ጋሪዎች ወዲያና ወዲህ ይዘዋወራሉ። ነጋዴዎች፣ ሴቶች፣ ወታደሮች ከተራው ህዝብ ጋር ይተራመሳሉ። ፍዮዶር አሁን በሌሎች አልቀናም፣ እድሉንም አልረገመም። አሁን ሀብታምና ድሀ እኩል አፈር እንደሚበላቸውና በምድር ላይ ለሰይጣን የነፍስን ቅንጣት እንኳ ፈርሞ የሚያሰጥ ምንም አይነት ምክንያት እንደሌለ ለማወቅ ችሏል።   

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top