ዘባሪቆም

የፌስቡክ ‘ኮመንቶች

የመግቢያ እንጉርጉሮ ….

White thumb up next to the like from social networks on blue background

“ታምር በበዛበት በኢንተርኔት ዓለም፣ ፌስቡክ ላይ አይታይ፣ አይነበብ የለም”

ባንድ ወቅት ‘ትንሹ ቴዲ አፍሮ’ በሚል ስም የተለቀቀ አንድ የአማርኛ ዘፈን ፌስ ቡክ ላይ ተለጥፎ አየሁ። በበኩሌ “ትንሹ ‘ቴዲ አፍሮ’ የሚለው ‘ትልቁ ‘ተዳፍሮ’ በሚል ይስተካከል” ለማለት እየዳዳኝ ትኩረቴን ወደ ሌሎቹ ኮመንቶች (አስተያየቶች) መለስኩ። ከስሩ ከተደረደሩት አስተያየቶች መካከል:- “ትንሹ ቴዲ አፍሮ የቴዲ አፍሮ ልጅ ብቻ ነው” “ቴዲ አፍሮ ትንሽ ትልቅ የለውም”… ወዘተ የመሳሰሉ ቅሬታ አዘል አስተያየቶችን እየቃኘሁ ወረድ ስል፡-

“… የኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር 8ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ‘በህዝብ ተሳትፎ ህዳሴዋን በማረጋገጥ ሰንደቅ ዓላማዋን ከፍ ከፍ ለማድረግ እየተጋች ያለች ሀገር ኢትዮጵያ’ በሚል መሪ ቃል ነገ ይከበራል!” የሚል ሰርጎ ገብ ማስታወቂያ በማየቴ ከተዳፍሮ ንዴቴ ተዳፍኖ ወደኖረ ብሔራዊ ስሜቴ ተሸጋገርኩ።

በፌስቡክ ኮመንቶች ዙሪያ ወደፊት የምለው አላጣም። ለዛሬ ጥቂት ትዝብቶችን ልዘክር። አንድ ማለዳ ፌስቡኬን ስከፍት:- “ለተቸገረ ሰው ይመጠጣል ከንፈር፣ ስንት ሰው አለቀ ዘንድሮ እኛ ሰፈር” የሚል ግጥም አየሁ።

 ግጥሙ እኔ ዘንድ ሲደርስ አንድ ፍሬ ላይክ (የመወደድ ምልክት) ነበረው። ከዚሁ ነጠላ ላይክ ስር ደግሞ “Thanks everyone!” (ሁላችሁንም አመሰግናለሁ) የሚል የገጣሚው ምስጋና ሰፍሯል። ፀሃፊው ይህንን ብቸኛ አድናቂ “Everyone” ለማለት የተነሳሳው በሰው ብቻ ሳይሆን በስዋሰው እጥረት ጭምር መሆኑን ስረዳ ያላንዳች ስስት ሙሉ ላይክ ቸርኩት። ካፍታ ቆይታ በኋላ ወደ ግጥሙ ስመለስ ግን “Thank you every two!!” የሚል ኮመንት አክሎ ውለታዬን ዓመድ አ’ርጎት አየሁ።

 የፌስ ቡክ እንግሊዝኛን በተመለከተ ሙያተኞችን ለምርምር እየጋበዝኩ ባየሁት ቁጥር የሚያሳቅቀኝን አንድ ምሳሌ ብቻ ላንሳ! ባለፈው ወደ አሜሪካ የመጣች የልጅነት ጎረቤቴ ከፊል ጡቷን፣ ሙሉ እምብርቷንና ያገር ናፍቆቷን የሚያንፀባርቅ ፎቶ ለጠፈች። ነገሩ ውስጤን ቢበላኝም የሰፈር ልጅ አለኝታና አጋርነቴን ለመግለፅ ፎቶውን ላይክ በማድረግ ተባበርኩ።

 ጎረቤቴ በፎቶው ዙሪያ የሚጎርፍላትን እልፍ ሙገሳና ጥቂት ወቀሳ ስታስተናግድ ውላ የላይክና ኮመንቱ ጋጋታ ጋብ ሲል “Thank you gays” በሚል ግልብ እንግሊዝኛ ምስጋናና ስድብ አሸክማን ወጣች። በሌላ ቀን ከቆንጆ የፕሮፋይል ፎቶዎች መካከል አዲስ አበባ ካለች ወጣት ጋር በውስጥ መስመር ቻት ማድረግ (ማውጋት) ጀመርን። ጓደኛዬ ዲቦ እንደሚለው አዲሳ’ባ ቻት ከማድረግ እዚሁ አሜሪካ ውስጥ ችት ማድረግ 

“ጎረቤቴ በፎቶው ዙሪያ የሚጎርፍላትን እልፍ ሙገሳና ጥቂት ወቀሳ ስታስተናግድ ውላ የላይክና ኮመንቱ ጋጋታ ጋብ ሲል “Thank you gays” በሚል ግልብ እንግሊዝኛ ምስጋናና ስድብ አሸክማን ወጣች። ”

(መባለግ) በእጥፍ ያተርፋል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ኔትዎርክ የሚለው ቃል የገባው ‘ኖት ወርክ’ (አይሠራም) የሚለውን ድግግሞሽ ለማቅለል ብቻ ነው። ያም ሆኖ እነሱ ከዋይፋይ እኛ ደግሞ ከዋይፍ ችግር እስክንላቀቅ ከመቻቻል ያለፈ አማራጭ አይታለምም።

እናም ይህችን ቆንጆ “እንዴት ነሽ?” አልኳት

 “አለሁ፣ እግዚአብሔር…” እንዳለችኝ ድምጿ ሲጠፋ ዲያቢሎስ እጇን ይዞ ያስቆማት እንጂ ኔትዎርክ ተቋርጦ የወጣች አልመስል አለኝ። በዚህ ሁኔታ ከመግባባት አልፎ ለመጋባት የበቃ ሰው ካለ የ’ድሜውን እኩሌታ ለኢንተርኔት የገበረ መሆን አለበት ስል አሰብኩ ።

 በመጨረሻ ፊቴን ወደ ገዛ ፌስቡክ ገፄ ሳዞር ከወራት በፊት የለጠፍኩት ሽንጣም አብዮታዊ ግጥሜ ውሃ እንዳጣ ችግኝ በላይክና ኮመንት እጥረት ጠውልጎ በማየቴ አምርሬ አዘንኩ። በዚህ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ እያለሁ ግን ሌላ የግጥም ሃሳብ በውስጤ ሲመላለስ ተሰማኝና የመጨረሻ ዕድሌን ለመሞከር “ለፌስ ቡክ ጓደኞቼ” በሚል ደማቅ ርዕስ ተከታዩን የመዝጊያ እንጉርጉሮ ለጥፌ ወጣሁ:-

ግጥሜን አንብባችሁ፣

ዝም አላችሁ ምነው፣

 በዚህ ዘመን እኮ፣

ሰው የሚመዘነው፣

ባለው ልክ ሳይሆን፣

ባለው ‘ላይክ’ ጭምር ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top