ሥነ-ጽሑፍ

የዕዝራ – አብደላ ሂሶች መለያ ጠባያት

አብደላ ዕዝራ ከ1980ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ በተለያዩ የስነጽሑፍ መድረኮች (በአብዛኛው መጽሔቶች እና ጋዜጦች) ላይ በሚያቀርባቸው ሂሳዊ ንባቦቹ የምናውቀው እና ሃያሲ የሚለውን “ማዕረግ” ባልተጻፈ ስምምነት ከሰጠናቸው አንድ ሁለት ሰዎች መሐል የምናገኘው ሃያሲ ነበር። በሥራው ምክንያት በአባቱ አገር የመን እየኖረ ከስነጽሑፋችን ላለመራቅ ለእረፍት በመጣ ቁጥር ስለመጻሕፍት ይጽፍ እና ይናገር የነበረ ቢሆንም፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ከሥራው ራሱን በጡረታ አሳርፎ፣ ስነጽሑፋዊ ሂስን ሥራዬ ብሎ ሂሶቹን፣ ዳሰሳዎቹን፣ ማፍታቻዎቹን በአዲስ አድማስ ጋዜጣ እና በተለያዩ መድረኮች ላይ በተከታታይ ማካፈል ጀምሮ ነበር። የስነጽሑፍ መጽሔት የማቋቋም፣ ለኪነት ሰዎች መሰባሰቢያ እና የፈጠራ ሥራቸውን ማከናወኛ (ሬዚደንስ) ተቋም የመመሥረት ብሎም ሂሳዊ ሥራዎቹን የማሳተም ዕቅዶች እንደነበሩት ከራሱም፣ ከቅርብ ወዳጆቹም ሰምተናል። ሆኖም ሙሉ ትኩረቱን ስነጽሑፍ ላይ ማድረግ እንደጀመረ የዛሬ ሁለት ዓመት በሞት ተለይቶናል።

 ይህ ጽሑፍ ሀያሲ አብደላ ዕዝራ በተለያዩ ጊዜያት ለመድረክም ይሁን ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጽፏቸው ከነበሩ ሂሳዊ ንባቦቹ፣ በተለይ ከራሱ ከዕዝራ ባገኘኋቸው 24 ሂሳዊ ንባቦቹ ጠባያት ላይ ያተኮረ ነው። ዓላማውም የአብደላ ዕዝራን የሂስ መርሆ ከጽሑፎቹ ላይ በስሱ ዳስሶ ለማሳየት በመሞከር፣ ሰውየውም ሆነ አበርክቶዎቹ እንደዋዛ ተረስተው እንዳይቀሩ የበኩልን ማዋጣት ነው። (በነገራችን ላይ አብደላ – ዕዝራ በሕይወት ሳለ እናቱ ያወጡለትንም አባቱ የሰየሙለትንም ስሞች እንዳስፈላጊነቱ ለመጠሪያው ይጠቀምባቸው ስለነበረ ነው፣ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ አንዱን ሰው ዕዝራም አብደላም እያልኩ ስጠራው የምታገኙኝ።)

ባለቅኔ እና ሀያሲው ዮሐንስ አድማሱ ከ1933 -1960 በተጻፉ የአማርኛ የፈጠራ መጻሕፍት ላይ በብስጭት በጻፈው ትችት መግቢያ ላይ፣ “ኂስ ለሥነ ጽሑፍ ሕይወት መጠበቂያ ዓይነተኛውና ፍቱን መድኃኒቱ ነው፣” ይላል። ዕዝራ ይህንን ስነጽሑፍን በሕይወት የማቆየት ሚና በገዛ ፈቃዱ መውሰዱን ከሂሳዊ ንባቦቹም ሆነ ከመጻሕፍት ዳሰሳዎቹ እንገነዘባለን። ዕዝራ በርቅቀታቸው፣ በቋንቋ ውበታቸው፣ በምሰላቸው አንብቦ ያደነቃቸው ድርሰቶች ለምን ሂሳዊ ንባብ ተነፈጉ የሚለው ቁጭት ከስነጽሑፍ ፍቅሩ ጋር ተደምሮ በየሳምንቱ በቸርነት ሂሳዊ ንባቦችን ለመጻፍ ያተጋው ይመስለኛል። ይህንኑ ቁጭቱን በተለያዩ ንባቦቹ ላይ ገልጾትም እናገኛለን። ለምሳሌ “አስራ አራት ጊዜ ምናብና ተመስጦ የደቀንለት መጽሐፍ” በሚል ርእስ “ኩርቢት” በተባለው የአለማየሁ ገላጋይ የአጫጭር ልቦለዶች መጽሐፍ ላይ ባደረገው ሂሳዊ ንባብ መንደርደሪያ ላይ የአለማየሁ “ድንቅና ኮስታራ ልቦለዶች” ሂስ መነፈጋቸውን በቁጭት አንስቶ እንዲህ ይጠይቃል፡ – “ኧረ ለመሆኑ ከዘመነኛ – – ልቦለድ ደራሲያን፣ የማን የፈጠራ ውጤት ነው ለአጥጋቢ ባይሆንም፣ ለበቂ ሂሳዊ ንባብ የተጋለጠው?”

ስንዴውን ማባዛት መምረጡ

 በእዝራ የሂስ መርህ አንድን ስነጽሑፍ በሕይወት የሚያቆየውም ይሁን ከተሳካለትም የሚያሳድገው፣ ደራሲው አብዝቶ ስላፈራው አረም ሲሸማቀቅ እና ሲፀፀት እንዲኖር መውቀስ ሳይሆን፣ በኩንታል አረም መሐል ያፈራትን ስንዴ ለከርሞ እንዲያበዛት ማበረታታት ይመስላል። ምንም እንኳን “ኂስ ጉድለትንም ጥራትንም መግለጫ ጥበብ” ቢሆንም ዕዝራ ግን በምርጫው የድርሰቶቻችንን ድክመት እያደበዘዘ፣ በቀጣይ ሥራዎቻችን ልናጎለብታቸው የሚገቡትን ጥቂት ብቃቶቻችንን አድምቆ ማሳየትን ሥራዬ ብሏል።

 ለዚህ ማሳያ እንዲሆነኝ፣ ዕዝራ አንድ ስሙን ስለማልጠቅሰው የግጥም መድበል፣ በጻፈው የማስተዋወቂያ ጽሑፉ ላይ ካነበባቸው ግጥሞች አብዛኞቹ ስላላስደሰቱት፣ እንደ ብዙዎቻችን ይሄ መጽሐፍ ባይታተም ይሻል ነበር ብሎ በመፍረድ ፋንታ ገጣሚውን ስለቀጣይ ሥራው ሲያበረታታው እናገኛለን። በጽሑፉ መደምደሚያ፣ “ገጣሚው … በለጣቂ ሥራው፣ የላቀ ጥበባዊ ሁከት፣ የተላመድነውን ሁነት እየላጠ ተናዳፊ ግጥሞች እንደሚለቅብን መጽሐፉ ያበስራል።” ይላል። ሌላ ጊዜ/ቦታ ደግሞ ከአንድ ዕውቅ ገጣሚ የአጫጭር ልቦለድ ሥራዎች ያልወደደውን ሥራ መጥቀሱ የወደዳቸውን እንዳይሸፍንበት የሰጋ፣ ወይም ደግሞ ለደካማው ሥራ ይቅርታን የሚለምንለት ይመስል፣ ከሚላን ኩንዴራ “The Art of the Novel” ጠቅሶ አንባቢውን/ ደራሲውንም ጭምር ያባብላል (ይሄ)፡ – ‘All great works (precisely because they are great) contain something unachieved.` (በዕዝራ

ትርጓሜ፡- “የልሂቃን ትልቅ የጥበብ ውጤት የሚመስጠን፣ የሚያነቃቃን በሰመረላቸው ፈጠራ ብቻ ሳይሆን፣ ሞክረውት አልሰበሰብ ባለ ምናባቸው ጭምር እንጂ።”)

ዕዝራ የድርሰቶቻችን ብርታቶች ላይ ማተኮሩ በህትመት ያገኘናቸው የፈጠራ ድርሰቶች በቁጥር እንጂ በኪነታዊ ብቃታቸው የሚደነቁ አለመሆናቸውን አጥቶት አይደለም። እንዲያውም የነቢይ መኮንንን ግጥሞች በሚተነትንበት “እማይነትበው ስውር-ስፌት” የሚል ጽሑፉ ላይ ይህንን ሁኔታ በተለይ ከአማርኛ ግጥሞች አንጻር ሲገልፀው እንዲህ ይላል፡-

 የአማርኛ ግጥም ህትመት ቢበራከትም፣ ዘመን ተሻግሮ የሚፈካው በቁጥር ነው። እየዘገበ ቤት የሚመታ፣ ቋንቋው የማይናደፍ፣ እሳቦቱ ወዲያውኑ የሚነጥፍ ግጥም አቅም ያንሰዋል። አሰልቺና ደነዝ በመሆኑም የጥሞናን ጊዜ ሲያመክን ለገጣሚው አይሰቅቀውም። በአንፃሩ ጥቂቶች የሚመስጥ፣ የሚያባንን፣ እያደረ ከአእምሯችን የሚንቀለቀል ግጥም ለኩሰዋል።

 ያም ሆኖ ዘጋቢዎቹ፣ የማይናደፉቱ (በፍዝ ቋንቋ የተጻፉቱ)፣ ወይም እሳቦቶቻቸው እንደ ተን ፈጥነው የሚጠፉብን ግጥሞች ላይ ጊዜውን፣ ስሜቱን ምናቡንም ሲያባክን አናገኘውም። ለዚህም ይመስላል፣ የሂስ ጠንካራ እና ደካማ ጎን መዛኝነት ላይ አምፆ ትኩረቱን ሙሉ በሙሉ “ተናዳፊ” የሚላቸው ግጥሞች ላይ በማድረግ፣ ለተከታታይ ሳምንታት “ተናዳፊ ግጥሞች” በሚል ዐቢይ ርዕስ ሥር  ግጥሞችን ማመስጠርን የመረጠው።

በአንድ ወገን የዕዝራ በልማዳዊው የሂስ ደንብ ላይ ማመጽ በአብዛኛው ለሂስ ከሚመሰጥበት፣ በምናብ ከሚዛመድበት ዘውግ፣ ከግጥም አመጸኝነት የመነጨ ሊሆን ይችላል። ቴዎድሮስ ገብሬ “የአማርኛ ስነግጥም” ለተባለው የብርሃኑ ገበየሁ መጽሐፍ፣ (ይህንን የግጥም ማስተማሪያ መጽሐፍ ዕዝራ በተደጋጋሚ ይጠቅሰዋል) በጻፈው የጀርባ ገፅ አስተያየት፣ “ሥነግጥም ታስቦበት በስርዓትና በጥበብ የሚከናወን አመጽ ነው፣” ይላል። ምናልባትም የዕዝራን የሂስ ቋንቋ ውበት እና ምናባዊ ምስል ፈጠራውን ስናየው ሰውየው ከገለልተኛ ሀያሲነት ይልቅ እንደዘመነኞቹ ሀያሲያን በዳግም ድረሳ (re-creative process) ከገጣሚያኑ ጋር የፈጠራ ሂደቱን እንደሚጋራ እንገነዘባለንና፤ በነባሩ “ኂስ ጉድለትንም ጥራትንም መግለጫ ጥበብ ነው” የሚል መርሆ ላይ አማፂ ሆኖ የምናገኘው እንደ ዳግም ድረሳው ሁሉ፣ አመፁንም ከግጥሞቹ ተምሮ ነው ብዬ እገምታለሁ።

 ዕዝራ የስነጽሑፍ ሥራዎችን ከመመዘን ይልቅ ማመስጠር፣ መፈከርን በመምረጡ አመጸ እንበል እንጂ ለግጥምም ሆነ ለዝርው ድርሰቶች የሚቀበላቸውን የስነጽሑፍ ደንቦች  ሲያፀናም እናገኘዋለን። ያም ሆኖ ግን ከጥራዝ ነጠቅ ንባብ ተነስተን ግጥም እንዲህ መሆን አለበት፣ ልቦለድ እንዲያ መሆን የለበትም እንደምንለው እንዳብዛኞቻችን ድምዳሜ አይሰጥም፤ የሚጽፈው ደንቦቹ በየጊዜው፣ በየአውዱ ስለሚቀያየሩለት/በት የፈጠራ ሥራ እንደሆነ አይዘነጋም፤ ይልቅ በተዘዋዋሪ እንዲህ ቢሆን ይሻላል በሚል ትህትና እና በድግግሞሹ ሥር በሥር ደንብ ሲያስተዋውቅ እና ሲያስለምድ ቆይቷል። ለምሳሌ፣ የግጥምን የትርጉም አሻሚነት (ambiguity) ከአንዱ ገጣሚ ጋር በማድነቂያነት፣ ከሌላው ጋር በጉድለት መጠቆሚያነት በተደጋጋሚ ከማንሳቱ እና ከማስረዳቱ የተነሳ አሻሚነትን ገጣሚያን ሊያስቡበት የሚገባ የግጥም አላባ መሆን አለበት የሚል ደንብ ማበጀቱን እናያለን፤ እንዲያውም የግጥም የትርጉም አሻሚነት ግጥሙን አንባቢው ልብ ውስጥ ያከርመዋል የሚል አቋሙን ጽሑፎቹ ውስጥ ደጋግመን እናነባለን።

 ወደኋላ ላይ በተከታታይ ይጽፈው እንደነበረው

“በርግጥ አንዳንድ ጊዜ በማናበብ ስም ታላላቅ ደራሲያንን ስንጠራ፣ አንባቢው ለትንታኔ ያቀረብነውን ድርሰት ከእነሱ ጋር እንዲያነጻጽር ፈልገንም ይሁን ሳንፈልግ እንገፋፋዋለን። በዕዝራ ሂሳዊ ንባቦች ላይ አልፎ አልፎ አንዱን ግጥም ከሌሎች የተሻሉ ግጥሞች ጋር በማናበብ ያንን ግጥም በተሻሉት ግጥሞች ትከሻ ላይ አቁሞ ለማሳየት የመሞከር አዝማሚያም አይቻለ ”   

ደግሞ “ተናዳፊነት” ለጥሩ ግጥም አይረሴነትን የሚያጎናጽፍ ባህርይ ነው ይል ነበር። ግጥሞች ፍዝ ስሜትን ሊያውኩ ይገባል ይላል። “ርቀትና ቅርበት ሊላተሙ ነበር” በተባለው እና የበዕውቀቱ ስዩምን ግጥሞች ባነበበበት ፍካሬው በዕውቀቱ ስዩምን በ“ተናዳፊ” ግጥሞቹ ምክንያት “ብርቅ” ገጣሚ ብሎ ይሾመዋል፡- “የአማርኛን ግጥም አንዳንድ ወጣት ብዕሮች አስቀይመውታል። ቤት ለመታ፣ ከጫፉ ዜማ ላንጠባጠበ ስንኝ – ሳይመሰጡ – ወረቀታቸውን ይደቅናሉ። ፍም(ን) እኮ ጤዛ ያሰጋዋል፤ ብዙዎቹ ፍምና ጤዛ ቀርቶ፣ ስጋት ሳይሆን ፍዝነትና የፈሰሰን ውሃ መርጠዋል። ይነበባል፤ ይረሳል። ጥቂት ወጣቶች ግን ብርቅ ናቸው። አንዱ በዕውቀቱ ስዩም ነው። ግጥሞቹ ገለልተኛ አይደሉም፣ ይናደፋሉ።”

በይነ-ቴክስታዊ አዝማሚያው

 የእዝራ የሂስ ስልት የደራሲውን ተቋማዊ ህልውና ክዶ፣ የግጥሙንም ይሁን የልቦለዱን ትርጉም ከድርሰቱ ላይ ብቻ መፈለግ ላይ ያተኮረ ነው። ደራሲው ምን ለማለት ፈልጎ ነው ብሎ የድርሰቱን አቅም ከመገደብ ይልቅ ድርሰቱ ምን ይነግረኛል ብሎ ሥራውን የመመርመሩን አካሔድ እንደሚከተል ለመረዳት በተለይ ጥልቅ ሂሳዊ ንባቦቹን ማንበብ ብቻ በቂ ነው። ከዚህም ባሻገር በዚህ የቴክስቹዋል አናሊስስ ድርሰትን የማንበቢያ መንገድ ቀማሪነቱ የሚታወቀውን የሮላንድ ባርትን “The author is dead” የሚል ጽሑፍ ጠቅሶ የራሱን የትንታኔ አዝማሚያ የጠቆመበትም ጽሑፍ ይህንኑ የሚያረጋግጥልን ነው።

 ይሄ የነባርት ሂሳዊ አካሔድ የትኛውም ድርሰት ብቻውን አይቆምም፤ ድርሰቱ ምሉዕ የሚሆነው ከሌሎች ጽሑፋዊም ሆኑ በሌላ መልክ የቀረቡ ቴክስቶች ጋር ሲናበብ ነው የሚል አቋምም አለው። ዕዝራ በዚህ የፍሬንች ስኩል ሂሳዊ አተናተን እንደተመሰጠ ከሚያሳዩን የሂሱ ጠባያት አንዱ አንድን ድርሰት ብቻውን ሲፈክረው አለማግኘታችን ነው። ብዙ ጊዜ የሚያተኩረው ግጥሞች ላይ እንደመሆኑ፣ አንድን ግጥም ሲተነትን ግጥሙን መድበሉ

ውስጥ ካሉ ግጥሞች ጋር ያናብባል (ይህንን ኢንትራ-ቴክስቹዋሊቲ ይሉታል)፤ ግጥሙን በዚያ መድበል ውስጥ ካልተካተቱ የገጣሚው ሌሎች ግጥሞች ወይም ዝርው ድርሰቶች ጋር እና ከሌሎች ድርሰቶች ጋር ያናብባል (ኢንተር ቴክስቹዋሊቲ ይባላል)። የዕዝራ ሀያሲነት ከጥልቅ ንባብ የተገኘ መሆኑን ከምናይባቸው የሂሱ ጠባያት አንዱ ይሄ አናባቢነቱ ነው። ለዚህ ጉልህ ምሳሌ የሚሆነን ኤፍሬም ስዩም የተረጎመው አንድ ባለሁለት መስመር የግዕዝ ቅኔ በአጭሩ ሲተነትን፣ ከስምንት መጻሕፍት ላይ የቅኔ መረዳቱን ሙሉ የሚያደርጉለትን ግጥሞች፣ ሐሳቦች፣ አጭር ልቦለዶች፣ ረዥም ልቦለድ ጠርቶ በማናበቢያነት ሲያውላቸው ታገኙታላችሁ። እዚህ ላይ ቁምነገሩ ብዙ መጻሕፍትን የመጥራት ጉዳይ ሳይሆን፣ ሰውየው በምሥክርነት የጠራቸውን ሰዎች በተገቢው ሥፍራ ማስገባቱ ነው።

 በርግጥ አንዳንድ ጊዜ በማናበብ ስም ታላላቅ ደራሲያንን ስንጠራ፣ አንባቢው ለትንታኔ ያቀረብነውን ድርሰት ከእነሱ ጋር እንዲያነጻጽር ፈልገንም ይሁን ሳንፈልግ እንገፋፋዋለ በዕዝራ ሂሳዊ ንባቦች ላይ አልፎ አልፎ አንዱን  ግጥም ከሌሎች የተሻሉ ግጥሞች ጋር በማናበብ ያንን ግጥም በተሻሉት ግጥሞች ትከሻ ላይ አቁሞ ለማሳየት የመሞከር አዝማሚያም አይቻለሁ። ይህንን ማድረግ ደከም ያለውን ገጣሚ የተሻለ ነገር ይዞ እንዲቀርብ ያበረታታው ይሆናል፤ የዕዝራም ምክንያት ይሄ ይመስለኛል፤ ነገር ግን በተቃራኒው እንዲህ ያለው ሂስ ደካማው ደራሲ ደረጃውን አውቆ፣ ድክመቶቹን ለይቶ ለመሻሻል እንዲሞክር ከመገፋፋት ይልቅ ልቡን አሳብጦ እዚያው ድክመቱ ላይ እንዲከርም ሊያደርገውም ይችላል።

 ከነዚሁ ከሚጠራቸው የፈረንሳይ የስነጽሑፍ ፅንሰ ሀሳብ ቀማሪዎች ጋር የሚያመሳስለው ሌላው ነጥብ፣ ሂስ ከስነጽሑፍ ሥራው ተነጥሎ እንዳይታይ ለሂሳዊ ድርሰቶቹ ውበት መጠንቀቁ ነው። አንዳንድ ጊዜ የእሱ ሂሳዊ ንባቦች ከሚተነትናቸው ድርሰቶች በላይ በዘይቤ በታሸ፣ ከሰርክ መግባቢያ ከፍ ባለ ቋንቋ እና በአመስጣሪው የላቀ ምናባዊነት ተጽፈው ይገኙና ከሂስነት ይልቅ ወደ ፈጠራ ድርሰትነት ያዘነብላሉ። ለወትሮው ሀያሲን ፈራጅ፣ ደራሲን ተከሳሽ አስመስሎ የሚያሳየውን አካሄድ ትቶ፣ ራሱን የፈጠራ ሂደቱ አካል ማድረጉን ከጽሑፎቹ እንረዳለን።

 በርግጥ ይሄ በፈጠራ ሂደቱ የመሳተፍ ነገር መልካም ቢሆንም ሀያሲው ሚዛኑን ካልጠበቀ የሚያሔሳቸውን ሥራዎች ውበት ከማሳየት ይልቅ በራሱ ምናብ የመመሰጥ፣ ወይም ድርሰቶቹን አላቅማቸው የማንጠራራት አደጋ ሊኖረው ይችላል። ሁለቱንም ዓይነት ችግሮች አልፎ አልፎ በዕዝራ ሂሶች ውስጥ አይቻለሁ። (በአንባቢ ልቤ “ይሄ ዕዝራ አሁንስ አበዛው!” ብዬ የተበሳጨሁባቸው ሂሶች አሉ።) ለምሳሌ፣ ለሂሳዊ ንባብ ከመረጣቸው የዕውቅ ከያኒያን ሥራዎች ይልቅ በማናበቢያነት (አንዳንዴም በጽሑፍ ማስዋቢያነት) በሚጠቅሳቸው ሥራዎች እንደተመሰጠ በግልፅ ያስታውቅበታል።

በአጠቃላይ፣

 ዕዝራ ሂስ ጎድሎብን ሳለ፣ ከጉድለታችንም ተከታታይ የግጥም ሂስ ደግሞ ጠፍቶብን ሳለ ግጥምን ያክል አመጸኛ የድርሰት ዘውግ ለማጥናት እና ለመተንተን መነሳቱን አይተን፣ ለስነጽሑፍ ፍቅሩ ሲል ቴዎድሮስ ገብሬ እንደሚለው፣ “አዲስ ስርዓት” የመትከልን፣ ግጥምን መልሶ የመፍጠርን ያህል ፈታኝ” ኃላፊነትን እንደወሰደልን ልንረዳ ይገባል። እዝራ ይህን የባህል እና ስነጽሑፍ ተቋማት የሸሹትን ኃላፊነት በግሉ ወስዶ፣ ከማንም ሽልማትም ይሁን ክፍያ ሳይጠብቅ፣ በብቃትም በትጋትም ይወጣልን ጀምሮ ነበር።

ዕዝራን ማጣት ወግ ያለው እና ፍቅርን መነሻውም መድረሻውም ያደረገ ደግ፣ ትጉህ የግጥም ሀያሲ ማጣት ነው። የደራሲያኑን ምርኩዝ ማጣት ነው። ዘመኑ የሂስ ባህል ያልዳበረበት እንደመሆኑ፣ እንዲህ እንደ ዕዝራ ያሉ ብርቅ ሀያሲያን ሲገኙ፣ ሥራዎቻቸው የሂስ እና የምርምር ዕድል ሊነፈጉ ስለማይገባ፤ የስነጽሑፍ ተማሪዎች እና ተመራማሪዎች ሂሱን ለመተንተንም ይሁን ለመሔስ (በሂስም ላይ ሂስ አለበትና) ሥራዎቹን አጥንተው የዕዝራን አስተዋፅዖዎች በጥልቀት ቢያሳዩን ደግ ነው ብዬ አምናለሁ።

ማስታወሻ፣ ይህ መጣጥፍ ከዚህ በፊት በተለያዩ አጋጣሚዎች ስለዕዝራ ለአንባቢዎች እና ለአድማጮች ያቀረብኳቸው ጽሑፎች የመጨረሻው ሞክሼ እንጂ፣ አዲስ ጽሑፍ አይደለም።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top