ጥበብ በታሪክ ገፅ

የአኙዋዎች አጌም- ዐመፅ ለሰላም

አኙዋዎች በባህልና በማህበረሰብ የተፈጠሩ፣ በታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፉ የመጡ፣ ከጥንታዊ አባቶቻቸው የተረከቧቸው ድንቅ የሆኑ ሁለት የሰላም መንገድ እሴቶች አሏቸው። አንደኛው ባለፈው እትም የአኙዋ ህብረተሰብ የ“ክወር” (የእርቀ-ሰላም) ባህል በሚል ርዕስ በጥቂቱ ለአንባብያን ያቀረብኩት ነው። ለማስታወስ ያህልም የ“ክወር” ባህል በህብረተሰቡ አባላት መካከል በተለያዩ ምክንያቶች የሚነሱ የነብስ ግድያን ጨምሮ የተለያዩ ባሕርያትና ደረጃዎች ያሏቸውን የግጭት ዓይነቶች ለመፍታት የሚያገለግል ትውፊታዊ የሰላም ጥበቃ መንገድ ወይም ዘዴ ነው። ሁለተኛው “አጌም” ተብሎ የሚጠቀሰው የአኙዋ የሰላም መንገድ ነው። በመሆኑም በዚህ እትም የቀረበውን የ”ክወር” የእርቀ-ሰላም ባህል እንደመነሻ በማድረግ የብሔረሰቡን የ“አጌም” ባህል እንደሚከተለው በአጭሩ አቅርቤዋለሁ።

ሁለቱም የሰላም መንገዶች ከእም ሀበ አልቦ ነገር በብሔረሰቡ ታሪክ ውስጥ ሥርፀት አግኝተው በአገልግሎት ላይ የዋሉ ሥራተ- ሕጎች አይደሉም – የአፈጣጣር ምክንያቶችን ወይም የጥንተ-ነገር አመጣጥ አመክንዮቶችን የሚገልፅ መለኮታዊ የሥነ-ኅላዌ ታሪክ (ሚቶሎጂ) አላቸውና! ሙሉ ታሪኩ ረጅም ከመሆኑ የተነሳ በዚህ አጭር ጽሑፍ ለማስፈር አስፈላጊ አይሆንም። ሆኖም ለአንባብያን ግንዛቤ ይረዳ ዘንድ የታሪኩን አሕፅሮተ – ቢጋር እንደሚከተለው ለማስፈር ተሞክሯል፡ እነሆ! በጥንት ዘመን ሕግ አልነበረም። ፍትኅ አልነበረም። ሥርዓት አልነበረም። በዚያን ዘመን ሕግ ጉልበት፣ ኃይል ነበረች። … ታዲያ በዚያን ዘመን አንድ ጨካኝ፣ ርኅራኄ የሌለው አረመኔ ገዥ ነበረ። ሀብት ይዘርፋል። ህፃናትን፣ ልጃገረዶችንና ሴቶችን ዘርፎ፣ ደፍሮ፣ ሲያሰኜው ይገድላል። ለአውሬ ይሰጣል። ሰው ሲደሰት ከሚያይ ይልቅ፣ አውሬ የሰው ሥጋ በልቶ ሲደሰት የበለጠ ደስታ ይሰማው ነበር ይባላል። … ያ ክፉ ገዥ ሰው ሁሉ “ቶር” (ጨዋታ፣ ጭፈራ፣ …) እንዳያደርግ ከለከለ። ሰው ሁሉ በሰላም ውሎ ማደር፣ በሰላም አድሮ መዋል፣ አልችል በማለቱ ያዝን፣ ያለቅስ፣ ነበር። …

ህዝቡ በዚህ ሁኔታ በፍርሀትና በሀዘን ተውጦ ሳለ አንድ ቀን የወንዝ ንጉሥ ከባህር ወጥቶ መጣ። … ስሙም “አቹዶ” ይባላል። “ኡኪሮ”ም ይባላል። ከመጣ በኋላ … ወደ ነዋሪው መንደር ሄዶ ተቀመጠ። እህል አይበላም፤ ውሀ አይጠጣም። … በዚህ ሁኔታ አቹዶ ከእህል ከውሀ ታቅቦ ከነዋሪው ጋር ተቀምጦ ስለ ሕግ፣ ስለ አስተዳደር፣ ስለ ፍትኅ ማስተማር ጀመረ። ከዚያ ያ ጨካኝ ገዥ ስለ አቹዶ ከወንዝ ባህር ወጥቶ በመምጣት ሰውን ሁሉ ስለ ሕግ፣ ስለ አስተዳደር፣ ስለ ፍትኅ ማስተማር መጀመሩን ሰማና ታዛዦቹን ሂዱና ግደሉት አላቸው። ሄዱ። ሄደው ሊያሰቃዩትና ሊገድሉት ሲሰናዱ ግን “አቹዶ” በመጀመሪያ ወደ ነብርነት ተቀየረ። ወዲያው ወደ አንበሳነት ተቀየረ። ከዚያ ዝሆን ወደሚውጥ ግዙፍ ወደሆነ ዘንዶነት ተቀየረ። … በመጨረሻ ወደ ሰውነት ቅርፁ ተቀየረባቸው። በዚህ ጊዜ ሊገድሉት የመጡት አሽከሮች በፍርሀት ተውጠው ተመልሰው ሄደው ያዩትን ተአምር ለዚያ ጨካኝ ገዥ ነገሩት። …. እሱም እንደነገሩት በቁጣ ተነስቶ አቹዶ ወደሚገኝበት መንደር ታዛዦቹን አስከትሎ መጣ። እንደመጣም አቹዶ በመጀመሪያ እንዳደረገው ቅርፁን በቅፅበት በመለዋወጥ አሳየውና እንደገና ወደ ሰውነት ቅርፁ ተቀይሮ ተመለከተው። ያን ተአምር እንደተመለከተም ያ ጉልበተኛና ጨካኝ ሰው ከአቹዶ ፊት እንደቆመ ጉልበቱ እንደቄጠማ ተብረከረከ። አንደበቱንም ተሳነው። መናገር አልቻለም። … ከዚያ መቆም አቅቶት ወደቀና ከመሬት ላይ ወገቡን እንደተመታ እባብ መላወስ ጀመረ። መቀመጥ አልቻለም። መቆም አቃተው። …

 በመጨረሻም አቹዶን ሰማያዊ መለኮትና ኃይል ያለው ነው ብሎ አመነ። … ከዚህ በኋላ አቹዶ በእጁ ነካውና “ተነስ” አለው። ይህን እንዳለው ከወደቀበት ተነሳ፤ አንደበቱም ተፈታ። … አቹዶንም ወደ ቤቱ ወሰደውና ለብቻው የሚኖርበት ቤት ሰጠው። እህል እንዲበላና ውሀ እንዲጠጣም ለመነው። አሪየት የምትባል ልጁንም ከቤቱ እሳት እንድታነድለት፣ ምግብና ውሀ እንድታቀርብለት አደረገ። … አቹዶ ግን ምግብም አልበላም፤ ውሀም አልቀምስም እንዳለ ማስተማሩን ቀጠለ። … ያ ጨካኝ የነበረ ገዥም ትምህርት ተቀብሎ አደነቀ። ከዚያም ኦቹዶ ለፈፀምከው ግፍ ህዝቡን ይቅርታ ጠይቅ አለው። እርሱም ህዝቡን ሰብስቦ ይቅርታ ጠየቀ። ህዝቡም “እሽ” ብሎ ይቅር አለው። …

 ከዚያም አቹዶን “አንተ ንጉሣችን ሁንልን!” ብሎ ለመነው። … አቹዶም “እኔ የውሀ ንጉሥ ነኝ። … ሌላ ምረጡ” ብሎ እንቢ አለ። ሆኖም ህዝቡ ሀሳቡን እሽ ብሎ ሊቀበለው ባለመቻሉ የመጀመሪያው “ኜያ”፣ (የመጀመሪያው የሀገሩ ንጉሥ) አድርጎ መረጠው። እሱም የህዝቡን ፍላጎት ተቀብሎ ንጉሣቸው ሆኖ የሮኒን፣ አጌምንና የክወርን ሕጎችና ሥራተ-ደንቦች አስተማረ። … ከአሪየትም አንድ ልጅ አስረገዘ። … ሀገሩም ሰላም ሆነ። …

በመጨረሻ ግን ከሰዎች ፊት እንደተቀመጠ “እኔ አገሬ ውሀ ነው። ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ውሀ ግዛቴ መመለስ አለብኝ። የት ሄደ ብላችሁ

“የአጌም መነሻ ምክንያትና የአፈጣጠር ታሪክ በአጭሩ ይህን ይመስላል። አጌም በግብታዊነት አይከናወንም። አጌም የአፈፃፀም ደረጃዎችና ደረጃዎቹ የሚከተሏቸው ደንቦች አሉት። ወደ እነዚህ ከማምራታችን በፊት ግን “አጌም” የሚለው ቃል ወይም ፅንሰ-ሀሳብ የሚሰጠው ፍች ምን እንደሆነ በስፋትና በጥልቀትም ባይሆን ለግንዛቤ እንዲረዳ በአጭሩ መግለፅ አስፈላጊ ይሆናል”

እንዳትጨነቁ። … ከዚያ ህዝቡ ይጠብቀኛል …” ብሎ ተናገረ። ይህን እንደተናገረ ወደ የት እንደሄደ ሳይታወቅ ከዓይን ተሰወረና ወደ ውሀ ተመለሰ። እርሱ ከተሰወረ በኋላ በምትኩ አሪየት አገሩን ማስተዳደር ጀመረች። ቆይታም ወንድ ልጅ ወለደች። ስሙም ጊሎ ይባላል። … ጊሎ በእናቱ ሞግዚትነት አድጎ የአባቱን ዙፋንና የአስተዳደር ሕጎች ወርሶ ሁለተኛው የአኙዋ ታላቅ ኜያ (ንጉሥ) ሆነ። …. የአጌምን፣ የክወርን ሕጎችና የሮኒን (የመሪ ምርጫ) ሥራተ-ደንቦችንም አጠንክሮ ህዝቡን አስተማረ። … ጊሎ የአኙዋ መሥራች አባትነው። ወደር የሌለው ኜያ (ንጉሥ) ነበረ። …

 የአጌም መነሻ ምክንያትና የአፈጣጠር ታሪክ በአጭሩ ይህን ይመስላል። አጌም በግብታዊነት አይከናወንም። አጌም የአፈፃፀም ደረጃዎችና ደረጃዎቹ የሚከተሏቸው ደንቦች አሉት። ወደ እነዚህ ከማምራታችን በፊት ግን “አጌም” የሚለው ቃል ወይም ፅንሰ-ሀሳብ የሚሰጠው ፍች ምን እንደሆነ በስፋትና በጥልቀትም ባይሆን ለግንዛቤ እንዲረዳ በአጭሩ መግለፅ አስፈላጊ ይሆናል። ከባህላዊ ፍችው አንፃር ሲታይ “አጌም” ማለት በታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ ተላልፈው የመጡና በህብረተሰቡ ዘንድ እንደ ትልቅ እሴት ተቆጥረውና ተከብረው የኖሩ ጥንታዊ አባቶች የመሠረቷቸው ሕጎች በባህላዊ የአስተዳደር ተቋማት መሪዎች መጣሳቸው ሲታወቅ ሰላምን ለመመለስ የሚከናወን “ህዝባዊ ዐመፅ” እንደማለት ነው።

 ከዚህ ውጭ “አጌም” ብዙዎቹ ተመራማሪዎች እንዳሰፈሩት መነሻም፣ መድረሻም የሌለው “ግርግር” (“riot”) ወይም ደግሞ “ህዝባዊ አብዮት” ማለት አይደለም። ጃፓናዊው አንትሮፖሎጂስት ፕሮፌሰር ኩሪሞቶ ኢዜይ እንደገለፁት መንስዔም፣ ዓላማም፣ የሌለው ድንገታዊ ወይም ግብታዊ የሆነ “ግርግር”፣ “ረብሻ” ወይም “ፍርሻ” አይደለም። በአንፃሩ ደግሞ አጌም ሥር-ነቀል ለውጥ ለማድረግ የሚከናወን ተቃውሞ ስላልሆነ በአንትሮፖሎጂስቶች ዘንድ ዘወትር የሚጠቀሱት ዕውቁ እንግሊዛዊ ሰር ኢቫንስ ፕሪቻርድ አንድ ጊዜ “ህዝባዊ አብዮት” በሌላ ጊዜ “ግርግር” (“riot”) እንደሚሉትም አይደለም።

ከዚህ በተጨማሪ ክወርንና አጌምን የሚያመሳስላቸው የሰላም ማስጠበቂያ መንገዶች በመሆናቸው እንጂ በመካከላቸው ሰፊ ልዩነት አላቸው። ከላይ እንደተጠቀሰው ክወር የሚያገለግለው በህብረተሰቡ አባላት፣ በግለሰቦች፣ በቡድኖች፣ በቤተሰቦች፣ በማህበረሰቦች፣ ወዘተ. መካከል የተፈጠረን ጥል ወይም ከባድና ቀላል ግጭት ለመፍታት ነው። በአንፃሩ አጌም የሚካሄደው በህዝቡና የአባቶችን ሕግጋት በመጣስ ጥፋት በተገኜባቸው የባህላዊ አስተዳደር ተቋማት መሪዎች መካከል ነው።

 “ሮኒ” የሚለው ቃል ደግሞ ህዝብ የሚሳተፍበት የንጉሥ ወይም የኳሮ ምርጫ ሂደት፣ የምርጫ ምክክር ጉባኤ፣ እንደማለት ነው። በቆየው ልማዳዊ አሠራርና ደንብ መሠረት ከፍተኛውን በትረ-ሥልጣን የሚይዘው “ኜያው” (ንጉሡ) ነው። በኜያው ሥር በተዋረድ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ “ኳሮዎች” ያስተዳድራሉ። በባህሉ መሠረት

“መናፍስቱ ቅሬታ ያድርባቸውና ይከፋሉ፤ ይበሳጫሉ፤ በቁጣ ብዛትም የ“አሼኒ” መዓት በሕይወት በሚገኘው ደካማ ትውልድ ላይ ቅጣት ለማውረድ ይገደዳሉ። ይህ ከሆነ ደግሞ ድፍን ወይም ከፊል አኙዋ በቋያ እሳት ሊወድም፣ በውሀ ሊጥለቀለቅ፣ በወራሪ ሊዘረፍ፣ በወረርሽኝና በረሀብ ሊያልቅ፣ ወዘተ. ይችላል። ይህን ከመሰለው የ”አሼኒ” ቅጣት ለመራቅ ጥንቃቄ ማድረግ የኅላዌ ዋስትና ይሆናል ማለት ነው”

ኜያውም ሆነ ኳሮዎች የሚመረጡት በህዝብ ምክክር፣ ውይይት፣ ስምምነትና ይሁንታ ብቻ ነው። ስለዚህ በአኙዋዎች ዘንድ ይህ በህዝብ ተሳትፎ የሚከናወን የንግሥና እና የሹመት አሰጣጥ ባህላዊ አሠራር የሚኖረው ሂደትና የሚከተለው ደንብና “የስምምነት ማረጋገጫ” ሥርዓተ-ክንዋኔ (ritual) “ሮኒ” ተብሎ ይታወቃል። ሮኒ በተከታታይ ሊካሄድና ረዘም ያለ ጊዜ ሊጠይቅ ይችላል። የምርጫ ሥርዓተ- ክንዋኔውም የተወሰኑ መሥፈርቶችን የተከተለ ነው። ለምሳሌ ለንግሥና ወይም ለሹመት የታጨው ሰው ሰብዕና አንዱና ዋናው አጀንዳ ነው። ከሰብዕና መመዘኛ መሥፈርት መካከልም ግለሰቡ በመራጮች ዘንድ በሕይወት ዘመኑ አጋጣሚዎች ያሳየው ትዕግሥት፣ ትኅትና፣ አክብሮት፣ ርኅራኄ፣ ለጋሥነት፣ ሚዛናዊነት፣ የንግግር ችሎታ፣ ወዘተ. የመወያያ ነጥቦች ይሆናሉ። ህዝቡ በእነዚህና እነዚህን በመሳሰሉ ሥነ-ምግባራዊ ጠባዮች ላይ ይከራከራል፤ በተቃውሞ ወይም በድጋፍ አስተያየት ይሰጣል። እነዚህንም ያመሳክራል።

 ከባህሉ አንፃር ሲታይ የሮኒ ሥርዓተ-ክዋኔ የሚካሄደው በግለሰቡ ሰብዕና ላይ በህዝቡ ዘንድ አመኔታ ሳይፈጠር ለሥልጣን የበቃ እንደሆነ ቀደምት አባቶች ደንብተውና ይበጃል ብለው ለትውልድ ያስተላለፏቸውን፣ ህብረተሰቡም ከምንም በላይ የኅላዌ መሠረት አድርጎ የሚያያቸውንና የሚያከብራቸውን እሴቶች፣ ሕጎች፣ ሲጥስ ዞሮ ዞሮ የህዝብ የቁጣ ማዕበል ወይም አጌም ያስነሳል፤ ከዚህም በላይ ህዝቡ ሊያደርገው የሚገባው የጥንቃቄ ጉድለት “አሼኒ” ያስከትላል ከሚል ብርቱ ሥጋት የመነጨ ነው ማለት ይቻላል።

 “አሼኒ” ማለት “የሙታን አባቶች መናፍስት እርግማን” ማለት ነው። ይህም ከእምነት፣ ከአምልኮ፣ ከመንፈሳዊ ሕይወት ብሎም ከኅልውና ጋር ጥብቅ ትስስር አለው። በቆየው ትውፊታዊ (ፎክ) እምነት መሠረት በሕይወት ያለውን ትውልድ ከክፉ አደጋ የሚጠብቁት የሙታን አባቶች መናፍስት ናቸው። ይህን የሚያደርጉት ግን ትውልዶች ቀደምት አባቶች በሕይወት እያሉ ያወረሷቸውን ሕጎች፣ ትእዛዛት፣ ፈቃድና ፍላጎት በመጠበቅና በማሟላትና ደስ በማሰኜት ማረጋገጥ እስከቻሉ ድረስ ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ መናፍስቱ ቅሬታ ያድርባቸውና ይከፋሉ፤ ይበሳጫሉ፤ በቁጣ ብዛትም የ“አሼኒ” መዓት በሕይወት በሚገኘው ደካማ ትውልድ ላይ ቅጣት ለማውረድ ይገደዳሉ። ይህ ከሆነ ደግሞ ድፍን ወይም ከፊል አኙዋ በቋያ እሳት ሊወድም፣ በውሀ ሊጥለቀለቅ፣ በወራሪ ሊዘረፍ፣ በወረርሽኝና በረሀብ ሊያልቅ፣ ወዘተ. ይችላል። ይህን ከመሰለው የ”አሼኒ” ቅጣት ለመራቅ ጥንቃቄ ማድረግ የኅላዌ ዋስትና ይሆናል ማለት ነው።

 በእምነቱ መሠረት የ“አሼኒ” ቅጣት የሚደርሰው ኜያው እንዲሁም ኳሮው በሥልጣን ላይ ሆኖ በሚያሳየው የደንብ ጥሰት ብቻ ሳይወሰን በሮኒው (በምርጫው) ሂደት ባደረገው የጥንቃቄ ጉድለት ህዝቡም የቁጣው ሰለባ እንደሚሆን ራሱ ባህሉ ይነግረዋል፤ ይመራዋል፤ ያስጠነቅቀዋል። ስለዚህ ከዚህ አንፃር ሲታይ ህዝቡ ለሚከሰተው ችግር ሁሉ ራሱንም ተጠያቂ አድርጎ ይመለከታል ማለት ነው። በአጠቃላይ በእነዚህና በመሳሰሉት በባህሉ የተፈጠሩ፣ ያደጉና የተዋቀሩ እዞች በመመራት ህዝቡ ከ“አሼኒ” ቅጣት ለመዳንና ከሙታን አባቶች መናፍስት ጋር ለመታረቅ ባህሉ በሚፈቅድለት በ”አጌም” (በህዝባዊ ዐመፅ) አማካይነት ጥፋት የተገኘበትን ኜያ ወይም ኳሮ አስወግዶ በሌላ መተካትን እንደ ግዴታ፣ እንደኃላፊነት ወስዶ እንዲያከናውን አስችሎታል።

 ለዛሬው ይህን ከተመለከትን ዋናው ጉዳይ “አጌም” ምን ደረጃዎችንና ደንቦችን ይከተላል? በየደረጃዎቹስ በማን፣ እንዴት፣ መቼ፣ የት ይከናወናል? ምን ታሳቢ አማራጮችና አቅጣጫዎች ይኖሩታል? በምን ምክንያት? የአጌም ውጤቶች ምን ይመስላሉ? ጥያቄዎች ናቸው። በመሆኑም የእነዚህን ጥያቄዎች ምላሽ በሚቀጥለው እትም ይጠብቁ። 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top