ጥበብ እና ባህል

የአማርኛ ፊልሞቻችን የባህል መስታዎት ወይስ መጋረጃ

መግቢያ

በሀገራችን ፊልም (ተንቀሳቃሽ ምስል) መታየት የጀመረው በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ስለመሆኑ ጳውሎስ ኞኞ “አጼ ምኒልክ” በተሰኘው መጽሐፉ ላይ ጠቅሶታል። አዲሱ የጥበብ ዘርፍ ኢትዮጵያ የደረሰው ፈረንሳያውያን የሉሜየር ወንድማማቾች ከአስተዋወቁት ከጥቂት ዓመታት በኋላ ነበር። በቀዳሚነት ወደ ሀገራችን የመጣው ፊልም መንፈሳዊ ይዘት የተላበሰ ሆኖ ንጉሱና መኳንንቱ ተመልክተውታል።

ያ ዘመን በርካታ አዳዲስ ነገሮች የተዋወቁበት እንደመሆኑ በብዙኃኑ ዘንድ ከመቀበል ይልቅ ነቀፋው የበረታ ነበር። ፊልሙን የተመለከቱት የልዑላውያን ቤተሰቦች እንደ ሰይጣን ስራ ቆጥረው ከመተቸት ወደ ኋላ አላሉም። ነገር ግን ንጉሱና አማካሪያቸው የመረጡት ከሃይማኖት ጋር የተገናኘ ፊልም በመሆኑና ተደራስያኑ ላይ ሥነልቦናዊ ተጽዕኖ በማሳደሩ አጸፋው የከፋ እንዳይሆን ታድጎታል ተብሎ ይገመታል። በዚህ መልክ መታየት የተጀመረው ፊልም በጣሊያን ወረራ ወቅት በአዲስ አበባና በክፍለ ሃገር ከተሞች የሲኒማ አዳራሾች ተሰርተውለት እየተለመደ መጣ።

ይሁን እንጂ “ሂሩት አባቷ ማን ነው” እና “ጉማ” በአማርኛ ተሰርተው እስኪቀርቡ ድረስ የሚታዩት ሁሉ የውጭ ምርቶች ነበሩ። በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን ሁለቱ ልቦለዳዊ ፊልሞች ተጠቃሾች ሲሆኑ በደርግ ጊዜ በአንጻራዊነት ዘጋቢ ፊልሞች ላይ የማተኮር አዝማሚያ ታይቷል።

ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ ደግሞ ሁለቱም (ልቦለዳዊ በሲኒማዎች እና ዘጋቢ በመገናኛ ብዙሃን) በተጓዳኝ እየተጓዙ መጥተዋል። እንደ ታሪክ መንደርደሪያ የተነሱት ሥራዎች ከባህል አንጸባራቂነት አኳያ ሲፈተሹ “ጉማ” ከርእሱ አንስቶ ኢትዮጵያዊነትን በደንብ ይገልጻል። እርግጥ ባህል በተለያዩ ደረጃዎች ይተረጎማል። የሚገለጽባቸው መንገዶች ደግሞ የተወሰነ ቅርጽ ያስይዙታል። አለባበስ፣ አመጋገብ፣ ማህበራዊ መስተጋብር፣ ጭፈራ፣ ለቅሶ፣ ልማድ፣ እምነት፣ ዕደጥበባት እና ሌሎችም የባህል መከሰቻዎች ናቸው።

ለመሆኑ የአማርኛ ፊልሞች ባህልን ከማንጸባረቅ አንጻር ምን ይመስላሉ? የተወሰኑትን በመምረጥ በጥልቀት ሳይሆን ጎልተው በሚታዩ የባህል መገለጫዎች ላይ አጽንኦት ለመስጠት ተሞክሯል።

ለብዙ የሥነሰብዕ ምሁራን የብያኔ ፈተና ከሆኑ ቃላት መካከል “ባህል” አንዱ ነው። አሜሪካውያኑ የአንትሮፖሎጅ ተመራማሪዎች ክሮይቤር እና ክሉክሆን እ.ኤ.አ. በ1951 የባህልን ፍችና ገለጻ በጥንቃቄ ፈትሸው 164 የተለያዩ ብያኔዎችን አሰባስበዋል።

የዘርፉ ባለሙያዎች የጋራ የሆነ ትርጓሜ ለመስጠት ለረጅም ጊዜ ጥረዋል። ደክመዋል። ይሁን እንጂ ከ1990ዎቹ ወዲህ ችግር እየፈጠረ የመጣው የተፈጥሮው ጉዳይ ተደርጎ መወሰዱ ነው ይላል።

ሌላው አቭሩች የተባለ አጥኝ ባህልን ለመግለጽና ለማብራራት የታዩ ሙከራዎችን በሶስት ምሁራን የሃሳብ አለመግባባት አስረጅነት ታግዞ ያቀርባል። ይኸውም ማቲው አርኖልድ ከማህበራዊ ሳይንስ ይልቅ ለሥነ ውበት ያደላ “ልዕለ ባህል” አለ ሲል ኤድዋርድ ታይለር በበኩሉ የአንድ ማህበረሰብ አካል የሆነ ግለሰብ የሚታደለው እውቀት፣ እምነት፣ ኪነጥበብ፣ ስነ ምግባር፣ ወግ፣ ህግ፣ እንዲሁም ፍላጎትና ችሎታ ተጨምቀው አንድ ላይ “ባህል” ናቸው በማለቱ የተሻለ ተቀባይነት አግኝቶ ቆይቷል።

ከአርኖልድና ታይለር በተቃራኒ የተነሳው ቦኦስ የባህልን ታላቅና ታናሽ መለየት እንደማይቻልና ኋላቀርን ከዘመናዊ ነጥሎ ማስቀመጥ እንደማይታሰብ ያስረዳል።

የባህል ፍች ላይ የሚስተዋሉት አለመግባባቶችና ክርክሮች የማይጠሩ መሆናቸውን ከገለጻዎቹ ብዛቶችና ልዩነቶች ስፋት ተነስቶ መረዳት ቀላል ይሆናል። ይሁን እንጅ ለዚህ ጽሑፍ ያመች ዘንድ ከሃተታ ትርጉም የታይለርን ግምት ውስጥ በማስገባት ሌሎች መገለጫ ባህርያት መጨመሩ አስፈላጊ ሆኗል።

 የመጀመሪያው ባህል በተለያየ የጥልቀት ደረጃ ይንጸባረቃል የሚለው ነው። እንደ ስሸይን ገለፃ የአንድን ቡድን ወይም ድርጅት ባህል በመተንተን ሂደት ውስጥ ባህል ራሱን የሚያራግብባቸውን ሶስት ዋና ዋና ደረጃዎች መለየት ያስፈልጋል። እነኝሕም፡- የሚታዩ ጥበባዊ ሃቆች፣ እሴቶች እና መሰረታዊ አስተሳሰቦች ናቸው።

ባህል በባህሪይና በባህሪይ አተረጓጎም ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ ነው። ሆፍስቴዴ (1991፡ 8) እንደሚለው አብዛኞቹ ባህሎች አካላዊ ግዝፈትና የሚታይ ትርጉም ቢኖራቸውም “ባህላዊ ፍቻቸው” በግልጽ የሚገባቸው ለአድራጊዎቹና ለባለቤቶቹ ይሆናል።

 ሦስተኛው ባህል ከዓለማቀፋዊ የሰው ልጅ ተፈጥሮም ሆነ ግለሰባዊ ሰብዕና መለየቱ ነው። ባህል የምንማረውና የምንለምደው እንጅ የምንወርሰው ባለመሆኑ ከግለሰብ ዘር ሳይሆን ከማህበራዊ ሥነምህዳር ይመዘዛል።

 አራተኛው ባህል በሥነ ውበታዊ ዑደት ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ሙሉ በሙሉ ሥነ ህይወታዊ የሆኑት ምላሾቻችን ማለትም ማስነጠስ፣ ማዛጋት፣ ማሳል፣ መብላት እና የመሳሰሉት በባህል ጫና ሥር ይወድቃሉ። ለምሳሌ ሁሉም ሰው ለመኖር መብላት አለበት። ነገር ግን ከማን ጋር እንደምንበላ፣ ምን እንደምንበላ፣ ስንቴ እንደምንበላ፣ ምን ያክል እንደምንበላ የሚዳኙት በለመድነው (በተማርነው) ባህል መሰረት ይሆናል።

ፊልምና ባህል

በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የባህል ዘርፍ ተሰጧቸው በደንብና መመሪያ ከሚንቀሳቀሱት ውስጥ አንዱ ፊልም ነው። ሃገራትም የየራሳቸውን የአሰራርና ድጋፍ ሥልት ቀይሰው መስኩን የባህላቸው ማንጸባረቂያ መሳሪያ አድርገውታል።

ለምሳሌ ህንዶች ባህላቸውን ለማካተት ሲሉ በፊልሞቻቸው ታሪክ ውስጥ ሰርግ፣ ልደትና ድግስ ብዙዎቹ ላይ አይቀሩም። ምክንያቱም በዚህ ውስጥ አጨፋፈር፣ አዘፋፈንና አለባበስ ስለሚገለጹ። አሜሪካ በሆሊውድ ብዙ ነገሯን ሽጣለች። ኢትዮጵያ ከዚህ እሳቤ አኳያ ስትታይ በልጆቿ ከሚሰሩ ፊልሞች ግብር ትሰበስባለች እንጂ ባህሏን በማስተዋወቅ በኩል ተጠቃሚ ነች ለማለት አያስደፍርም።

ምክንያቱም እስካሁን ድረስ የአሰራር ሥርዓት ያልተዘረጋለት በዘፈቀደና በግለሰቦች ጥረት የሚመራ ስለሆነ። እርግጥ የፊልም ፖሊሲው ስለጸደቀ፣ ፈጥኖ ወደተግባር ከተገባ መልካም ነገር መጠበቅ ይቻላል። በፊልም ታሪክ ባህል በአለባበስ፣ አመጋገብ፣ ማህበራዊ መስተጋብር፣ የሙዚቃ ትውፊትና ሌሎችም መንገዶች ይንጸባረቃል።

 አልባሳት ዘመን ተናጋሪ፣ ቦታ ጠቋሚ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደረጃዎችን የሚያመላክቱ ናቸው። በፊልም ስራ ውስጥ አልባሳትን ዲዛይን የሚያደርግ ራሱን የቻለ ባለሙያ አለ። ይህ ጽሑፍ በዳሰሳቸው ፊልሞች ግን 98 በመቶ የተሳተፉት ዲዛይነሮች ሳይሆኑ አልባሳት መራጮችና አልባሾች ናቸው። ያም ሆኖ የገጸባህያርቱን የኑሮ ሁኔታ፣ ሥነ ልቦና፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ ህይወት እና መቼቱን በመግለጽ ረገድ ብቁ ሆነው ተገኝተዋል።

አመጋገብ

 የማንኛውም ፊልም ታሪክ አራማጆች እንደሰው ልጅ የሚራቡና የሚጠሙ ገጸ ባህርያት ናቸው። በተሰጣቸው ዓለም ሲኖሩ ሁሉም ሰብዓዊ ፍጡር የሚበላውና የሚጠጣው ምግብና መጠጥ ያስፈልጋቸዋል።

 ሃገራችን የራሷ ብቻ የሆኑ እንጀራ፣ ጠላና ጠጅ አሏት። ምግብ ፖለቲካ በሆነበት በዚህ ጊዜ የኛ የምንላቸውን ምን ያክል በታሪኮቻችን ተጠቅመናል ካልን በተመረጡ ሃያ ፊልሞች 145 ጊዜ ምግብ የተበላ ሲሆን 178 ጊዜ መጠጥ ቀርቧል።

ከምግብ ፒዛና በርገር፣ ከመጠጥ ድራፍት በገጸባህርያት ዘንድ እንደሚዘወተሩ ይታያል። በተለይ አስቂኝ የፍቅር ፊልሞች ላይ የሚሳሉ ገጸባህርያት የሚመገቡት ፒዛ፣ በርገርና ፓስታ ሲሆን ጭማቂም ይጠቀማሉ። ሲጣሉ ወይም ሲለያዩ አልኮል ጠጪዎች ይሆናሉ። ጉልበት ሰራተኞችና የኔ ቢጤዎች ደግሞ ፓስታ በእንጀራ በተዝረከረከ አቀራረብና በመሻማት ይበላሉ።

ማህበራዊ መስተጋብር

 በማህበራዊ መስተጋብር ውስጥ የእርስ በእርስ ተግባቦት (ቋንቋ አጠቃቀም፣ የአነጋገር ዘዬዎች፣ ሥነ ቃል፣ ተረትና ምሳሌዎች፣ ሰላምታ አሰጣጥ)፣ መረዳጃ ስልቶች (ዕድር፣ ዕቁብና ደቦ) እንዲሁም ሃገራዊ ዳኝነቶች (አፈርሳታና በልሃ ልበልሃ) ተጠቃሾች ናቸው።

 በዚህ ረገድ የቋንቋ አጠቃቀማችን ከርዕስ አሰጣጣችን ይጀምራል። ለአብነት ያክል ከሃያዎቹ ፊልሞች አራቱ እንግሊዝኛ (ላውንደሪ ቦይ፣ ኤፍ ቢ አይ፣ ፔንዱለም፣ ሜድ ኢን ቻይና)፣ አንደኛው ሂብሩ (ረቡኒ)፣ ሌላኛው ውጭ የሚገኝ የቦታ ስም (ሂሮሽማ)፣ አንደኛው ደግሞ አማርዝኛ (ባለ ታክሲው)፣ ሁለቱ በአሃዝና ፊደል (400 ፍቅር እና ሰኔ 30) ሲሆኑ ቀሪዎቹ አስራ አንዱ የአማርኛ ስያሜዎች ናቸው። ንግግሮች የእንግሊዝኛ ተጽእኖ ያረፈባቸው ሲሆኑ አንዳንዶቹ ሆን ተብሎ ቋንቋውን በሚሳሳቱ ጊዜ የሚፈጠርን የሳቅ ምንጭ ታሳቢ በማድረግ ቀርበዋል።

 ዘዬዎች፣ ተረትና ምሳሌዎች፣ ሥነቃሎች ከተማ ላይ ባለ መቸት ግልጋሎት ሲሰጡ አልታየም። ወደ ገጠር ወጣ ባሉ ትዕይንቶች ላይ ብቻ እናገኛቸዋለን።

 “አንችም ጨካኝ ነበርሽ ጨካኝ አዘዘብሽ

 እንደ ገና ዳቦ እሳት ነደደብሽ።” (አሜን ፊልም)

“ምክርና ቡጢ ለሰጭው ቀላል ነው” (የአርበኛው ልጅ)

ስሄድ አገኘኋት ስመለስ አጠኋት – እንቆቅልሽ (ረቡኒ)

 “ላታመልጭኝ አታሯሩጭኝ” (አፋጀሽኝ) የሚሉትን መጥቀስ ይቻላል።

 ሌላው ፊልሞቻችን እየረሷቸው ካመጧቸው ጉዳዮች ሰላምታ አሰጣጣችን፣ ዕድር፣ ዕቁብና ደቦ ናቸው። “ደህና ዋላችሁ፣ ደህና አደራችሁ፣ እግዚአብሔር/አላህ ይመስገን” መባባል ቀርቶ “ሃይ…ሃይ” ወይም በዝምታ መተላለፍ ይበዛል። መረዳጃ ማህበራቱም ወደ ጎን ተትተዋል። እርግጥ አልፎ አልፎ ሰላምታ አሰጣጡንም ሆነ መረዳዳቱን (በተለይ ትልልቅ ሰዎችና የገጠር ቀረጻ ባለባቸው ፊልሞች) እናያቸዋለን።

 ልማዳዊ ዳኝነት ከተነሳባቸው ፊልሞች አንዱ “አሜን” ነው። ግጭትን በሽምግልና የመፍታት ብልሃት ፍቅርና መተሳሰብን ይጨምራል፤ ቂምና በቀልን ያስቀራል። በተለይ በአሁኑ ሰዓት ሰው ሰውን እየገፋ በመጣበት ጊዜ መሰል ባህላዊ እሴቶች ቢጠናከሩ ትሩፋቱ ከፍ ያለ ይሆናል።

የሙዚቃ ትውፊት

 በደስታና ሃዘን የሚዜሙ ዜማዎችና አካላዊ እንቅስቃሴዎች (ጭፈራዎችና ውዝዋዜዎች) እንዲሁም የሚያዙና የምንጠቀማቸው የሙዚቃ መሳሪያዎች ከታሪኮቹ ጋር ተስማምተው ቢካተቱ ተደራስያንን የመያዝ ጉልበት ይኖራቸዋል።

 ኢትዮጵያዊ የሆኑ የሙዚቃ መሳሪያዎችን መሰንቆ፣ ክራርና በገናን በአሜን፣ ረቡኒ፣ አፋጀሽኝ፣ ፔንዱለም፣ የወንዶች ጉዳይና የአርበኛው ልጅ ላይ እንሰማቸዋለን። በተለይ ደግሞ በረቡኒ ታሪክ ውስጥ ሙዚቃ የምዕራባውያንና የሃገራችን ትውፊት ማነጻጸሪያ ሆኖ ቀርቧል። በገና ለአሳዛኝ ስሜቶች፣ መሰንቆና ክራር ቀለል ላሉ ስሜቶች ማጀቢያ እየሆኑ አገልግለዋል። “አሜን” ፊልም ላይ ሙዚቃን የህክምና መሳሪያ በማድረግ ተጠቅመውበታል።

በአጠቃላይ ከከተማ እልፍኝ ወጥተው የገጠሩን መንደር የነኩት ፊልሞች በተሻለ መልኩ ባህላዊ እሴቶችን ይዘው ተገኝተዋል። በአንጻሩ ደግሞ ሙሉ ታሪካቸው አዲስ አበባ ውስጥ ተጀምሮ ያለቀ “ዘመናዊነት” በሚል ሰበብ ሃገራዊ ለዛቸው ተሸርሽሯል። ያደገበትና የኖረበት ማንነት በገጠሩ የተቃኘ ከውጭ በተሰማና በታየ ማህበራዊ እውነታ መድረኩ ተይዞ የብዙሃኑ ባህል እንዳይከለል ሊታሰብበት ይገባል።

 ለዚህ ደግሞ የፊልም ሙያተኞች የሃገራቸውን ባህልና ታሪክ ማወቅ፣

 “ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ” ነውና በሙያው ውስጥ ያሉ ፊልም ሰሪዎች፣ ተዋንያን፣ ፕሮዲውሰሮችና በጥቅሉ በዘርፉ የተሰማሩት ሁሉ ለሙያው ክብር መስራት ፣

 የባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤቶች ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ እሴቶችን ለትውልድ ማሳወቅና ድጋፍ መስጠት፣

 ዘርፉ በፖሊሲው እንዲመራ ማድረግ እንዲሁም፤ የትምህርት ተቋማት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚገባቸው በመፍትሔነት መጠቆም ያስፈልጋል።

 ማስታወሻ፡- ይህ ጽሑፍ በተመረጡ ሃያ የአማርኛ ፊልሞች ላይ ቅኝታዊ ጥናት በማድረግ ለመድረክ የቀረበ ነው፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top