መጽሐፍ ዳሰሳ

“የበቀል ጥላ” የመጽሐፍ አስተያየት

ደራሲ፡- ገስጥ ተጫኔ

የልቦለዱ ርእስ፡- የበቀል ጥላ

የኅትመት ዘመን፡ 2010

የታተመበት ቦታ፡- አዲስ አበባ

የመሸጫ ዋጋ፡- ብር 70

አስተያየት አቅራቢ፡- ደረጀ ገብሬ (ረ/ፕሮፌሰር፣ አ.አ.ዩ.)

መግቢያ

ይህ ‹‹የበቀል ጥላ›› የተሰኘ ልቦለድ የደራሲው 10ኛው የታተመ መጽሐፍ ነው። ደራሲውንና ባለአስተያየቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀቻቸው መጽሐፍ ‹‹የናቅፋው ደብዳቤ›› የተሰኘች አነስተኛ መጽሐፍ ነች። ዘመኑም ምናልባት 1973 ሳይሆን አይቀርም። ከዚያ በኋላ ‹‹እናት አገር››፣ ‹‹የፍቅር ቃንዛ››፣ ‹‹ነበር›› ክፍል አንድና ሁለት፣ ‹‹የማክዳ ንውዘት››፣ ‹‹የረገፉ ቅጠሎች›› ‹‹የእማዋዬ እንባ›› እና ‹‹የቀድሞ ጦር›› የተሰኙት ዘጠኝ መጻሕፍት የደራሲው ሥራዎች ናቸው።

 የዚህ አስተያየት ዋነኛ ትኩረት ስለሆነው ስለ ‹‹የበቀል ጥላ›› ቅርጽና ይዘት አስተያየት ከማቅረብ በፊት ስለመጽሐፍ አስተያየት ምንነትና ጠቀሜታ ባጭሩ መግለጽ ያስፈልጋል።

 በመሠረቱ አንድ የታተመ መጽሐፍ ወደገበያ ወይም ወደ አደባባይ ከወጣ በኋላ ሀብትነቱ የአንባቢዎቹ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። አንባቢዎች በገባቸው፣ ኅሊናቸው  በፈረደላቸው፣ ገጠመኛቸው በሠፈረላቸው ቁና መሠረት ያሻቸውን ሊሉ ሙሉ መብትም ፈቃድም አላቸው። ይህም አስተያየት የሚቀርበው ያንባቢነትና የባለመብትነት ድርሻን ከግምት በማስገባት ነው፤ ደራሲው ወይም አሰናጂው የሚኖረው ቋሚ ባለቤትነት ስሙ ከመጽሐፉ ጋር ተዋህዶ መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ የሚሰነዘረውን አስተያየት ለማንሳትም ሆነ ለመጣል የግል ውሳኔው ነው፤ እነዚህ ነጥቦች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ደራሲው ከተመለከተበት አቅጣጫ ውጪ አንባቢስ ስለጉዳዩ የሚያስበው፣ የሚያውቀው ወይም የተለየ ሀሳብ ካለ ያንን ለመጠቆምና ለማጋራት ስለሚረዳም ጭምር ነው።

ሁለተኛው ነጥብ በመጽሐፍ ላይ አስተያየት ማቅረብና በልዩ ልዩ አግባቦች ማሰራጨት የተለመደና ረጅም ዘመን ያለው ልምድ ነው። ይህ ልምድ ትምህርታዊና መረጃ አቀባይ ነው ተብሎም ይወሰዳል። አንድ መጽሐፍ ላይ የሚቀርብ አስተያየት ለተለያዩ ወገኖች የተለያዩ ጥቅሞች እንደሚያበረክት ይታወቃል። እነዚህም ወገኖች፡-

ሀ. መጽሐፉን ያላነበቡና ለማንበብ ፈልገው ጊዜና ገንዘብ ለመመደብ የሚችሉ መረጃ ፈላጊዎች፣

ለ. አንብበው የተረዱትን ሀሳብ ሌሎች እንዴት ያዩት ይሆን የሚል ጠያቂ አእምሮ ያላቸው ወገኖች፣ ሐ. መጽሐፉን በልዩ ልዩ ምክንያት ማንበብ ያልቻሉና ጥቅል መረጃ የሚፈልጉ ጉጉዎች፣

 መ. የመጽሐፉን አስተያየት እንደመረጃ ምንጭ ተጠቅመው መዝናናት የሚፈልጉ፣ የሰዎችን ያስተያየት ፈለግ መመርመር የሚሹ እና ሌላም ምክንያት ያላቸው የመጽሐፍ ወዳጆች ናቸው።

ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ መጽሐፉ በገሀድ በአደባባይ ሕዝብ እንዲያውቀው መድረክ ሲመቻች አንዳንድ ዋና ዋና ነጥቦቹን በመጠቃቀስ ያላነበቡ ሰዎች ቢያነቡት የሚያገኟቸውን ፍሬ ነገሮች አስቀድሞ በመጠቆም መቀስቀሻ ሀሳብ ማቅረብ ነው። በአጭሩ ማስተዋወቅ እንዲሉ! የዚህ አስተያየት መነሻም ማስተዋወቅ በሚለው ነጥብ ላይ ባመዛኙ ያተኩራል።

 የበቀል ጥላ ጥቅል ጉዳይ

 የዚህ መጽሐፍ መቼት በለሚ አካባቢና ከ1966 ዓ.ም. በፊት ባሉት ጊዜዎች ላይ የተመሠረተ ነው። በአንድ አካባቢ ባሉ የተለያዩ ቤተሰቦች የእለት ውሎና አዳር ላይ ተመስርቶ በመኩሪያ በኩል ፈለቀ ማመጫን፣ በይመኙሻል በኩል ጓንጉልን፣ በዘገየ በኩል ገላግሌን፣ ትምህርቷን ባቋረጠችው በብርጓል በኩል ወስላታ መምህራንን፣ በጌታቸው በኩል የወንጀል ክትትልን፣ በአምሳ አለቃ ክፈተው በኩል በሕግ ስም ተሞዳሟጅ ባለሥልጣኖችን፣ በወሰኔና በፈጠነ አማካይነት በቀልን አስተሳስሮ ያቀረበልንና ከስድሳ ዓመታት በፊት የነበረውን የአንድ አካባቢ ማህበረ ፖለቲካ ገጽታ እንካችሁ የሚል ልቦለድ ነው። በየበቀል ጥላ ውስጥ የሚነሱት የግብርና ከእጅ ወደአፍ ሕይወት፣ ከችጋር ጋር ግብግብ (ገጽ 11- 18)፣ የዘመናዊ ትምህርት አያያዝና ውጤት፣ የአካባቢ አካላዊ ገጽታ፣ የኅብረተሰብ ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ትስስር፣ ሸረኝነትና የዋኅነት፣ ሀቀኝነትና አስመሳይነት፣ በቀልና ሽንፈት፣ ሴሰኝነትና ባካኝነት … እነዚህና ሌሎችም አንባቢዎች ገጽ በገለበጡ ቁጥር ፈልፍለው የሚያወጧቸው እውነቶች ተዋድደውና ተጋምደው ቀርበውበታል።

 ዋና ዋና ጉዳዮች፡- ትውውቅ

 ወጣት ገጸባህርያቱን ከጳጉሜ የመጨረሻ ቀን ጋር አስማምቶ ያቀርባቸዋል- እንዲህ ሲል!

በዚህ መካከል የደብተራ እንዳይላሉ ላም ላይ ጥቃት ደረሰ፤ ጥቃቱ አቶ ፈለቀንና መኩሪያን የመጀመሪያ ተጠርጣሪ ቢያደርግም፣ ጌታቸው ፖሊሱ በአካባቢው በተገኘው መረጃ መሠረት አቶ ፈለቀን ጠርቶ ቢጠይቅም፣ ስውር ደባ እንዳለው ይሸተው ጀምሯል። ወንጀል የተሠራባቸው ዱላና ቢላ እዚያ መገኘታቸው ያለ እቅድ የተፈጸሙ መዝረክረኮች ሆነው አልታይህ ይሉት ጀምሯቸዋል” 

 “… የድንክዬዋ ወር የመጨረሻ ቀን … እንቁጣጣሽን ሊቀበሉ አበባ የሚቀጥፉ፣ እንግጫ የሚነቅሉ፣ ሳዱሎችና እነሱን ያጀቡ ጋሜዎች ከአረዳው ግርጌ በተሰተረው መስክ ላይ ተሠራጭተዋል። መኩሪያ አደይ አበቦችን እያቆላለፈና እየጎነጎነ የሠራውን የአበባ አክሊል ለእህቱ ጓደኛ ለይመኙሻል ሰጣት። እርሷም አናቷ ላይ አስቀመጠችው።” (ገጽ 1)

ይህ የጉንጉን ስጦታ የመኩሪያን እህት ለጥያቄ፣ በአካባቢው ያሉትን ዘገየንና ዘነበችን ለቅናት ያነሳሳል። ይህች በድንክዬ ወር መጨረሻ የተፈጸመች ድርጊቲት ገጽ በገለበጥን ቁጥር እነዚህን ወጣቶች ወደልዩ ልዩ መሳሳቦች ስትመራቸው እናገኛታለን።

 ድንቅ የግጭት መነሻ ሆና መኩሪያና ዘገዬ በይመኙሻል ላይ የፍቅር ዓይናቸውን ይጥላሉ። ወጣትነት ባንቀለቀለው እሳት በውስጣዊ ፍቅርና ቅናት ሲብሰለሰሉ እናገኛቸዋለን። መኩሪያ ይመኙሻልን የግሉ ለማድረግ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ለመፈጸም ሲተጋ፣ ዘገየ ለመኩሪያ ባላንጣ በመሆን ቢችል ለግሉ ለማድረግ፣ ካልቻለም የመኩሪያን ምኞት ለማጨናገፍ ሲጣጣር እናየዋለን። አልፎ ተርፎ የሁለቱን ግንኙነት ለማበላሸት እስከመማል ይደርሳል።

 ዘገየ ምንም እንኳ በአካልና በእድሜ ከመኩሪያ ጋር ተመጣጣኝ ቢሆንም በሥነምግባር ከእኩዮቹ የሚያንስ ነው። ሴሰኝነት አብዝቶ ይታይበታል፣ የብርጓልን ይመኛል። አካላዊ  ትስስርም ይመሠርታል። ዘነበችን እያሽኮረመመ ወደ አልተፈለገ ድርጊት ይገፋፋል። የአባቱን ጎተራ እየዘነጠለ በሚያቀርብላት ስጦታ ከማዘንጊያሽ ጋር ሸማ ይጋፈፋል። በዚህም በጌታቸው ፖሊሱ የፉክክር ዓይን ውስጥ ይገባል።

አይገቡ ፉክክር እየገባ በየአጋጣሚው ድብደባ ይደርስበታል። በየብርጓል ወዳጅ በሲሳይ ተፈንክቶ ለሳምንታት እቤት ዋለ፤ እርሻ ቦታ አበያ በሬ ጠምዶ ሲያርስ በሬው እርሻ መሀል ተኝቶ አልነሳ በማለቱ በደረሰበት የመንፈስ ውርደት የተነሳ ከመኩሪያ ተጋጭቶ በጅራፍ ተገሸለጠ፤ እጥምቀት ክብረበዓል ላይ ክትክት (ምክቶሽ) ገብቶ መኩሪያ ፈልጦ ጣለው። የአቅሙ ጉዳይ አላዋጣ ሲለው ደግሞ ወሬ ማናፈስና ማዋሸክ ዋነኛ ሥራው ሆነ።

ፈጠነ ጥጋቡ በግብርና ሥራ ባለሙያነት ወደ ለሚ ቢመጣም ሥውር ተልእኮ ለማሳካት አቅዶ የተነሳ መሠሪ ሰው ነው። የመንደር ወሬ እያነፈነፈ፣ አንዱን ካንዱ እያጣረሰ ወደግቡ የሚንደረደር ሸውከኛ ነው። በዚህም የተነሳ ደብተራ እንዳይላሉ በክፉ እንደሚያዩዋቸው ላቶ ፈለቀ ያሳብቃል፤ ለደብተራ እንዳይላሉ ተጠንቀቅ እያለ ያሳስባል። ለመኩሪያ ዘገየ ጠላቱ እንደሆነ ይነግራል፤ ሩቅ አሳቢ አድቢ ሆኖ ተስሏል። የአቶ ፈለቀ ማመጫ ቤት ቃጠሎ በፖሊሳዊ ክትትል ሳይሆን በአፈርሳታ እንዲዳፈን ፖሊሶችን ይገፋፋል። ይህም አድራጎቱ የጌታቸው ፖሊሱን የጥርጣሬ ቀስት እንዲደገን ያደርጋል።

 ጌታቸው ፎሊሱ ዘወትር በሚያጨሰው ሲጋራ ሰበብ ተለይቶ የሚታወቅ የወንጀል መርማሪ ነው፤ የትም የትም ብሎ ማዘንጊያሽ ማረፊያው ነች። ማዘንጊያሽ የቀን ሠራተኛው የፈይሳ፣ የዘገየ፣ የጌታቸው፣ የሌላም አልፎ ሂያጅ ሁሉ መተንፈሻ ብትሆንም፣ ለጌታቸው የዕለት ስሜታዊ ግለቱ ማብረጃ ሆና ከማገልገሏ ውጪ ብዙም ግድ የሚሰጣት ሆኖ አይታይም። ከመደበኛ ሥራውና እለት እለት ከሚያጋጥሙት ወንጀሎች በተጨማሪ አንዳንድ ያልታሰቡና እንግዳ የወንጀል ክስተቶች እየተጋረጡበት ይጨነቃል።

 ለምሳሌም፡- የወፈፌዋ ወሰኔ የልጅ ገዳይ ጉዳይ፣ የደብተራ እንዳይላሉ ላም ምላስ መቆረጥና የአቶ ፈለቀ ማመጫ ቤትና ንብረት መቃጠል እጅግ አሳሳቢ ሆነውበት ሲብከነከን ይውላል፤ ያድራል፤ አለቃው ከአካባቢው ሰዎች ጋር በሚያደርገው ያልተገባ ግንኙነት በሥራው ላይ እንቅፋት ይሆንበታል። አልፎ ተርፎ ተጠርጣሪ ሊያስመልጥ ሲሞክር ያገኘዋል። ይባስ ብሎም በተጠርጣሪ ላይ የይያዝ ማዘዣ እንዳያወጣ ሲያስፈራራው ይታያል። ጌታቸው ግን በ‹‹ልዝብ ሰይጣንነት›› ማስፈራሪያውን ባለመቀበል ሥራውን አጥብቆ ይከታተላል።

 የዚህ ልቦለድ ዋና ትኩረት በወንጀል ነክ ጉዳዮች ላይ የሚደረግ ክትትል ቢመስልም አቢዩ ጉዳይ የኅብረተሰቡን መሠረታዊ ግንኙነት የተፈታተነው በተራ በቀል ይፈጸማል

ተብሎ የማይታመን የደብተራ እንዳይላሉ ላም ምላስ መቆረጥና የመኩሪያ ዱላና ያባቱ ቢላዋ ደብተራ እንዳይላሉ በረት አካባቢ መገኘት አንዱ የጌታቸው ተግዳሮት ሆነ፤ እሱን ያዝኩ ጨበጥኩ እያለ ወሰኔ ስለልጇ ጉዳይ የሰጠችው መረጃ እጅጉን ወጥሮ ያዘው፤ እነዚህን ሁለቱን ሳይፈታ የአቶ ፈለቀ ማመጫ ቤት ንብረት በእሳት ወደመ።

ወፈፌዋ ወሰኔ ወፈፌነቷ ታምኖላት እንደልቧ እየተናገረች ስለልጇ ገዳይ አለኝ የምትለውን መረጃዋን ለጌታቸው በምስጢር ታቀብላለች። ‹‹ከአለቃህ ጋር አረቄ እየጠጣ›› እያለች በነገር ትሸነቁጠዋለች። ሄድ መጣ እያለች የልጇን ገዳይ መውጫ መግቢያ አጥንታ ጉዳትም ታደርሳለች። ላደረሰችው ጉዳት ወፈፌነቷ ሽፋን ሲሆንላት እናያለን። ወፈፌነቷን የጠረጠረ ፖሊሱ ጌታቸው ብቻ ሳይሆን አይቀርም። በኋላም እውነት ሆኖ ያገኘዋል።

 የነጠላ ሁነቶች ጥምረት

 ከዚህ በላይ የቀረቡት የልቦለዱ ተሳታፊዎች መገለጫዎች ናቸው እንዲህ ንባባችንን በየገጹ እየመሩ ወደፊት እያባበሉ የሚወስዱን። በነዚህ ሰብእናዎችና ማኅበራዊ ግንኙነቶች ውስጥ አስፈላጊ በሆነ ቦታ ሁሉ ብቅ የሚሉ ሰው ሰው የሚሸቱ ድርጊቶች እናነባለን። አንዳንዶቻችን፣ በተለይ የገጠራማ አካባቢ እድገት ያለን ሰዎች የተሳተፍንባቸውን የልጅነትና የጉርምስና ወዞች ፍንትው አድርገው ዛሬ እንደሆነ ሁሉ ያሳዩናል። አንዱ የሆነውን የህዳር ጎጆ ጉዳይ ለአብነት ልጥቀስ፤

 በዚህ በከተማችን የመንደር ቆሻሻ ሁሉ  ተሰብስቦ ከሚቃጠልባቸው እለታት ዋና ሕዳር 12 ቀን ነው። የከተማው ቆሻሻ ማቃጠልና የገጠሩ ህዳርን ማጠን ይለያያሉ ይመስለኛል። በገጠሩ በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት መሠረት የሚደረግ ‹‹… በምድር ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ጸሎተ እጣን ተደረገ›› በሚል መነሻ ሕጻናት ተሰብስበው የሚያከብሩት የሕዳር ሚካኤል በአል አለ (ዛሬ ይኑር አይኑር አላውቅም)።

በዚህ እለት እረኞች ከየቤታቸው የሚሰጣውን የበአል መታሰቢያ ዳቦና ጠላ ይዘው እንደ ቅርርባቸው ጎጆ በጋራ ሰርተው ተሲያት ላይ ይመገባሉ። ይህ ልማድ በየበቀል ጥላ ውስት ፍንትው ተደርጎ ቀርቧል።

ሕዳር አሥራ ሁለት ቀን የእረኞች በአል ነው። እረኞች በዚህ ቀን ወላጆቻቸው ጣልቃ ሳይገቡባቸው በራሳቸው ጎጆ ራሳቸውን የሚያስተናግዱበት፣ የራሳቸውን ዓለምና የራሳቸውን ደስታ የሚፈጥሩበት ቀን ነው። ለልጆች የሚጥም ጥሩ ድግስ አለው። ሙልሙል ዳቦ፣ የኑግ ልጥልጥ፣ የሰሊጥ ፍትፍት፣ እርጎ፣ አይብ፣ ለበአሉ ይሰናዳል።

 ለተፈራ ተብላ በመኩሪያ መሀንዲስነት የተሰራችው ጎጆ ከላይ የተጠቀሱትን ዝግጅቶች ሁሉ አሟልታለች፤ በተጨማሪም ‹‹በክብር እንግድነት›› ለሚገኙ ታዳሚዎች ጥሩ ጠላ እንዲኖራት ተደርጓል።…. (ገጽ 38)

በዚህ የልጆች በአል ሰበብ በርካታ ጉዳዮች ከትዝታ ማህደር አፈትልከው ይወጣሉ። የጉብሎችና ሳዱሎች ፍቅር ጮራውን ሲዘረጋ፣ የእኩያ ጨዋታውና ድሪያው ሲፈካ፣ ደስታና ፈንጠዝያ እንደፍም ሲንተረከክ፣ እንደፀሐይ ብርሃን ሲደምቅ ወለል ብሎ እንዲታይ ሆኖ ተስሏል። እረኞች ‹‹ሕዳር ሕዳር ወተትሽ እማር›› ጎጇቸውን እየዞሩ ሲጨፍሩ፣ ሲዘፍኑ፣ አመሻሽ ላይም የተመገቡባቸውን ቁሳቁሶች በመሰብሰብ ‹‹ሕዳር ኮበለለች፣ እንቅቧን አዘለች፣ ልጇን አስከተለች›› በማለት ጎጇቸውን በቃላዊ ግጥም ተሰናብተው ሲለያዩ ያስታውሳል። ይህን ደስታና የፍሰሐ ጸዳል የሚያረክስ አንዳንድ ሸርና ተንኮልም ብቅ ይላል። በነመኩሪያ አካባቢም የሆነው ይኸው ነው። በዘገየ ጣልቃ ገብነት (ገጽ 42) የነምንይሹ ፈንጠዝያ ይገደባል።

 የአቶ ፈለቀ ክምር ውቂያ፣ የአቶ ጓንጉል እርሻ ሰበብ ሆኖ የተሰበሰቡ የአካባቢው ነዋሪዎች የሚያሳዩዋቸው የሥራና የማኅበራዊ ግንኙነት መገለጫዎች በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሱ የአብሮ መኖር አብነቶች ናቸው።

በነዚህ ውስጥ ነው ከአለፍ አገደም ግላዊ ትካሮች ብቅ ጥልቅ፣ ብርት ጭልም እያሉ አንባቢን ወደፊት የሚስቡት። የመኩሪያ ዋሽንት፣ የይመኙሻል መዋለል፣ የብርጓል መሰደድ፣ የፈጠነ ነገር ማወሳሰብ፣ አቶ ፈለቀ ልጅህን ለልጄ ብለው አቶ ጓንጉል ዘንድ ሽማግሌ መላክ፣ የዘገየ አባት አያ ገልግሌም ወደ አቶ ጓንጉል ለተመሳሳይ ጉዳይ ሽማግሌ መላክ የሚጠቀሱ ሰዋዊ ጉዳዮች ናቸው። በነዚህ መላላኮች ውስጥ ልጅ ተጠያቂው የሰጡት መልስ ሁሉ የበቀል ጥላ ፍንጥቅጣቂ ሁነቶች ናቸው።

አዋቂዎቹ በሀገር ባህል ደንብ መሠረት የሚፈቅዱትንም፣ የሚነሱትንም እየተነጋገሩ ተስማምተው በሚኖሩበት ሕይወት ውስጥ ያልበሰሉ ጎረምሶች ደግሞ ጠብ ጠብ እየሸተታቸው፣ በልባቸው የተጫረውን ፍቅርና ቅናት በየፊናቸው እዳር ለማድረስ ሲታትሩ አጥፊና ተከላካይ ሆነው ማየታችን የልቦለዱ ንዑሳን የታሪክ ማራመጃዎች ናቸው።

ትረካው እየናረ ሲሄድ በተላኩ ሽማግሌዎች ሰበብና በወላጆች ስምምነት ምክንያት ይመኙሻል ለመኩሪያ፣ ዘነበች ለዘገየ ተሰጡ። ዘገየ ባይረካም፣ ቀደም ሲል በፈጠረው የሴሰኝነቱ ተጽእኖ ዘነበችን በማስረገዙ የተነሳ፣ በአባቱም ቁጣና ተግሳጽ ሊያገባት ግድ ይሆንበታል።

በዚህ መካከል የደብተራ እንዳይላሉ ላም ላይ ጥቃት ደረሰ፤ ጥቃቱ አቶ ፈለቀንና መኩሪያን የመጀመሪያ ተጠርጣሪ ቢያደርግም፣ ጌታቸው ፖሊሱ በአካባቢው በተገኘው መረጃ መሠረት አቶ ፈለቀን ጠርቶ ቢጠይቅም፣ ስውር ደባ እንዳለው ይሸተው ጀምሯል። ወንጀል የተሠራባቸው ዱላና ቢላ እዚያ መገኘታቸው ያለ እቅድ የተፈጸሙ መዝረክረኮች ሆነው አልታይህ ይሉት ጀምሯቸዋል። ይህን እያሰላሰለ ባለበት ሁኔታ መኩሪያ ድንገተኛ አደጋ አድርሶ መሰወሩ ተጨማሪ ራስ ምታት ሆኖበታል።

 ወዲህ ደግሞ ፈጠነ ጉዳዩን የመርማሪ ያህል እየተከታተለ መረጃ ያቀብለዋል። ይህም አንድ አሳሳቢ ነጥብ ሆኖ ‹‹ለምን? ምን ይፈይድለታል? ከመደበኛ ሥራው ውጪ እንዲህ ያሉ የሰዎች አስጊ ተግባራት ለምን ጉዳዩ ሆኑ?›› እያለ እንዲያብሰለስል ይገፋፉታል።

 በዚሁ ዓይነት አንባቢም ጉጉት ያድርበታል፤ የፈጠነ ነገር! ከዚህ በላይ በቀረቡት ላይ አተኩሮ የሚንቀሳቀሰውን ጌታቸው ፖሊሱን ከእነዚህ የወንጀል ድርጊቶች በስተጀርባ አድብቶ የሚላወስ ሰው አለ የሚለው  ጥርጣሬ ሥራውን አወሳስቦበት ቁጭ አለ።

በመሆኑም በአንዲት ትንሽ የወረዳ ከተማና አካባቢ ባሉ መኖሪያ መንደሮች ውስጥ አራት አስጨናቂ የምርመራ ርእሰ ጉዳዮች ይገጥሙታል- ጌታቸው ፖሊሱን። በግልጽ የወጡ ተጠርጣሪዎችን በሕግ መሠረት በአግባቡ በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ አስቀድሞ ይከነክነው የነበረውን የወፈፌዋ ወሰኔን ጉዳይ የመከታተል ቅድሚያ ይሰጣል። በእሸቱ አንካሴ መወጋት እርቅ መውረዱ ለጊዜው ፋታ ቢሰጠውም የላሟ ምላስ መቆረጥና ሞት፣ የአቶ ፈለቀ ማመጫ ቤት መቃጠል እንዲህ በቀላሉ እንደማይወጣው ክፉኛ ገምቷል።

የሆኖ ሆኖ ወፈፌዋ ወሰኔ ስለልጇ ገዳይ የሰጠችውን ማስረጃ በተጨባጭ ካረጋገጠ በኋላ ለአለቃው አምሳ አለቃ ክፈተው ሲነግረው ትብብር ባለማሳየቱ ክፉኛ ይበሳጫል። የመጣው ይምጣ የሚል ቁርጠኛ  ውሳኔ በማሳደሩ፣ አምሳ አለቃው ምስጢር አውጥቶ ምርመራውን ሊያደናቅፍ መቻሉን በመጠርጠሩ የእውነተኛ መርማሪ ፖሊስ ተግባሩን በመወጣት የወሰኔን ልጅ በቅናት ተነሳስቶ በጩቤ ወግቶ የገደላትን፣ መምህር ኤፍሬምን በቁጥጥር ስር ለማዋልና ወንጀሉን በተጨባጭ ለማረጋገጥ ችሏል።

 የቀረው የላሟና የቤት ቃጠሎው ጉዳይ ነው። ይህንንም አጋጣሚ በፈጠረለት እድል ተጠቅሞ ጭራውን ይይዛል። የያዘውን ጭራ ሊያስለቅቀው አሁንም የስውር ወንጀለኛው ያረቄና የመሸታ ቤት ተርቲመኛ የሆነው አምሳ አለቃ ይወለግድበታል። አምሳ አለቃው በወሲብ ግንኙነትና በመተያያ አቀባባይነት ከሚጠቅሙት ወይዘሮ አሰለፈች የሚደርስበትን ወቀሳ በመፍራትና ኃላፊነቱን በማግሸሽ ተጠርጣሪው እንዳይያዝ ሲጣጣር ይታያል፣ ጌታቸው ፖሊሱም ወግድ በማለትና ቀድሞ የሚያውቀውን ድክመትም ለመጠቀም በመቁረጡ ምክንያት ተጠርጣሪው ተይዞ ቤቱ እንዲበረበር ይገደዳል።

 ተጠርጣሪውም በማን አለብኝነትና የአምሳ አለቃውን ወዳጅነት በመተማመን ትከሻ ቢያሳይም ‹‹እውነትና ንጋት እያደር ይወጣል›› እንደሚባለው ስውር ወንጀለኛነቱን የሚያረጋግጥ ማስረጃ በጓዳው ተደብቆ ይገኝበታል። በፈጠነ ጓዳ የመኩሪያ ሸራ ጫማ፣ ከሞተ ውሻ አፍ በተገኘ ብጣሽ ጨርቅና የፈጠነ ጃኬት መግጠም የስውሩን ወንጀለኛ ገሀድ ያወጡታል።

 በልጅነት በጆሮ የምትንቆረቆር የበቀል  ጠብታ አድጋና ተንሰራፍታ ጅረት ትሆናለች። በጅረትነቷም አልፎ ሂያጁን ሁሉ፤ ቀድሞ ይሁነኝ ብሎ ያላስተዋላትን ሁሉ እየደፈቀች አፈር ታስግጣለች። አቶ ፈለቀ ማመጫም የመንግሥት ግዳጅ ለመወጣት ሲሉ በሠሩት ነፍስ የማጥፋት ተግባር የሟች ጥጋቡ ጭንቅል ልጅ አድጎና ተመንድጎ ከነዘርማንዘራቸው ሊያጠፋቸው ሲጣጣር ሳያስተውሉት፣ ሳይጠረጥሩት፣ በመክረማቸውና በቤታቸው ወጪ ገቢ እንዲሆን በመፍቀዳቸው ምሰሶው ሲቀር ቤታቸው ዶጋ አመድ ሆነ። የምሰሶው አለመቃጠል ምንም እንኳ የዋናው ጉዳይ ተዋናይ ሕይወት ቅጥብ አለመድረሷን ጠቋሚ ቢሆንም ፍዳው ግን ሊለቃቸው እንዳልቻለ በሚያስገነዝብ አኳኋን ፈጠነ ‹‹አዎ የዛሬው ቀን መሽቷል። የበቀል ቀን ግን ጨርሶ አይመሽም›› አላቸው (ገጽ 313)፤ እሳቸውም ‹‹አይ እኛ፣ እስተመቼ ይሆን እንዲህ ሆነን የምንዘልቀው?›› ሲሉ ያጉተመትማሉ።

 የበቀል ጥላም ተገልጣ፣ ገሀድ ወጥታ

 “በዚህ የበቀል ጥላ ውስጥ የተነሱት ዋና ዋና ጉዳዮች የማኅበራዊ ኑሮ ትስስር፣ የሰው ለሰው ግንኙነት፣ ፍቅር፣ ጥላቻ፣ ቂም በቀልና አልሸነፍም ባይነት መነሻቸውና መቼታቸው ከስድሳ ዓመት በፊት የተደረገ ሁነትን የሚንተራስ ቢሆንም ዛሬም ቢሆን በገጠሪቱ የአገራችን ” 

መኩሪያንና ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ነጻ አውጥታ፣ ሁነኛ ተጠርጣሪዎችን አጋልጣ፣ እነመኩሪያንና ዘገየን ወደትዳር አሻግራ መምህር ኤፍሬምን ፍቼ ወህኒ፣ ፈጠነን ከለሚ ወህኒ ቤት አመልጣለሁ ብሎ በመሮጡ ወደአፈር መልሳ፣ ጌታቸው ፖሊሱን በአስር አለቅነት ማእረግ አንበሽብሻ፣ ከሲጋራው አፋትታ፣ ከወሰኔ አጋብታ ትደመደማለች።

 የማጠቃለያ ነጥቦች

በዚህ የበቀል ጥላ ውስጥ የተነሱት ዋና ዋና ጉዳዮች የማኅበራዊ ኑሮ ትስስር፣ የሰው ለሰው ግንኙነት፣ ፍቅር፣ ጥላቻ፣ ቂም በቀልና አልሸነፍም ባይነት መነሻቸውና መቼታቸው ከስድሳ ዓመት በፊት የተደረገ ሁነትን የሚንተራስ ቢሆንም ዛሬም ቢሆን በገጠሪቱ የአገራችን ክፍሎች ተወግደዋል ማለት አይቻልም። በቀድሞ ዘመን መስተዋትነት ዛሬን እንድናይና እንደገና እንድናሰላስል የሚያስገድድ ትረካ ያለበት ልቦለድ ነው ብየ አምናለሁ- የበቀል ጥላ።

 መጽሐፉ የተሳለበትን አካባቢና ሁነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ፣ የቋንቋው ለዛ የሚጥም፣ እጅግም ያልተንዛዙ ሁነቶችና ድርጊቶች ተጣጥመው የቀረቡበት በሳል ሥራ ነው ማለት ይቻላል። ባነሳው የበቀል ጉዳይም ቀደም ሲል በደራሲ አንዳርጌ መስፍን ድርሰቶች ውስጥ በ‹‹ጥቁር ደም›› እና በ‹‹ደም በደም›› የተተኮረበትን በዳኛቸው ወርቁ ‹‹አደፍርስ›› ውስጥ የቀረበ ‹‹ወንድሙን ሲገድሉት ወንድሙን ካልከፋው አቅርቡለት ልብሱን፣ የወንድሙን ሱሪ፣ ደሙ እንዲከረፋው።›› (ዳኛቸው 258)

 የበቀል ጥምን የመወጣት ባህል በተለየ ጊዜና ቦታ እንደገና እንዲነሳና እንዲታሰብበት፣ ዛሬንም እንደገና እንድንመለከትበት የቀረበልን አጉሊ መነጥር ነው ማለት ይቻላል።

 ደራሲው ይህን ሁሉ የተወሳሰበ ትረካ ለመፍጠር የተጋውን ያህል፣ በዘዬም ሆነ አካባቢ ገለጻ የተሳካለትን ያህል፣ ባህላዊነትና ዘመናዊነት ያላቸውን ግጭት ለመጠቆም ያደረገውን ጥረት ያህል በአርትኦት ሥራ ላይ በቂ ጥረት አድርጓል ለማለት አይቻልም።

 በቃላት ግድፈት፣ በፊደላት አለመሟላት፣ በሥርዓተ ነጥብ ሥርዓት አለመጠበቅ ላይ ጥቂት ጉድለቶች ታይተዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ጉድለቶች መጽሐፉን ለማንበብ የሚያስቸግሩ ጉልህ እንከኖች አይደሉም።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top