አድባራተ ጥበብ

“የቅጂ መብት ጉዳይ በመደበኛ ፍርድ ቤት ሳይሆን በህግና በኪነጥበብ ባለሙያዎች ሸንጎ ቢታይ ወጪንና ጊዜን ይቆጥባል”

አቶ መኮንን ሰሙ፣ የህግ ባለሙያ

መነሻ ሐሳብ

አርሲ ቀርሳ ከተባለው መንደር ውስጥ የአስራ አራት ዓመቷ ልጅ ተጠልፋ ትደፈራለች። ደፋሪዋ ከቤት እንዳትወጣ ይቆልፍባታል። የምትጠብቃት ሴት ከውጭ እንድትቆም ያዝዛል።

አንድ ቀን ጠባቂዋ በር ከፍታ ታዳጊዋ ወደ አለችበት ክፍል ስትገባ፤ ልጅቷ አጋጣሚውን ተጠቅማ ለማምለጥ ትሞክራለች። የሰውየውን ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ይዛ ትወጣለች። መንደሩን እያቆራረጠች ትሮጣለች። የማምለጫዋ ወሬ ይደርስ እና ደፋሪዋ ሰምቶ በሔደችበት አቅጣጫ ይፈልጋታል። አይቷት እየቀረበ ሲመጣ ዞራ ለማስፈራራት ሁለቴ ወደ ላይ ትተኩሳለች። ሳይቆም ይጠጋታል። ተኩሳ ትገለዋለች በፖሊስ ተይዛ ክስ ይመሰረትባታል። ዜናውን በሬድዮ የሰሙት የኢትዮጵያ ሴት የህግ ባለሙያዎች ማህበር መሥራች እና በወቅቱ የሥራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ስለጉዳዩ ከማህበሩ አባላት ጋር ይወያያሉ። ለታዳጊዋ ጠበቃ እንዲመደብላት ይስማማሉ። ወ/ሮ እታገኘሁ ለሜሳ ይመረጣሉ። ዝግጅቱ ይጀምራል። ጠበቃዋ ተከሳሿን ወክለው ይከራከራሉ። ከአድካሚ ክርክሮች በኋላ ታዳጊዋ ከተከሰሰችበት ድርጊት ነፃ ተብላ ትለቀቃለች። ይህ የሆነው ከዛሬ 22 ዓመት በፊት ነበር።

ይህንን የሰማው ዘረሰናይ ብርሃነ መሐሪ በድርጊቱ ላይ ተመስርቶ የፊልም ጽሑፍ ለመፃፍ ያስባል። በቅድሚያ አካባቢውን ማየት ይፈልግና ወደዚያው ይጓዛል። ሲደርስ ወደ ፖሊስ ጣቢያ፣ ወደ ፍርድ ቤት ይሔዳል። መዝገቦችን ያገላብጣል። ወደ ኢትዮጵያ ሴት የህግ ባለሙያዎች ማህበር ያመራል። ወ/ሮ መአዛ አሸናፊን ያገኛል። መረጃዎች ይሰበስባል። ታዳጊዋን አፈላልጎ ያጣታል። ልጅቷ ሀገር ውስጥ አለመኖሯን ሲሰማ፤ ቤተሰቦቿን ያነጋግራል። ጥያቄዎች አቅርቦ የተመለሱትን፣ መዛግብት ፈትሾ ያገኛቸውን ጽሑፎች በተለያዩ መልኮች ያረጋግጣል። በመጨረሻም ጥናቱን ጨርሶ ለመፃፍ ይዘጋጃል።

የፊልም ጽሑፍ እና ድጋፍ

 ለመፃፍ ምን ያህል ጊዜ ወሰደብህ?

 ዘረሰናይ፡- አምስት ዓመት ፈጅቶብኛል። ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የፊልም ጽሑፍ መፃፍ እንዳለበት አምኛለሁ። ይህን ዕድል መጠቀም ነበረብኝ። አንዳንዶች በቀላሉ ተጽፎ እንደሚሰራ ጠቆሙኝ። አልተስማማሁም። ረጅም ጊዜ ቢወስድብኝም “ድፍረት”ን ፅፌ ላጠናቅቅ ችያለሁ። ከቀረፃው በፊት ገንዘቡን እንዴት አገኘህ? ዘረሰናይ፡- ምህረት አያሌው ማንደፍሮን በአጋጣሚ ኒውዮርክ አገኘኋት። ከአይዳ አሸናፊ ጋር “ጉዞ” የተሰኘውን ዶክሜንተሪ ፊልም ስንሰራ ነበር የተዋወቅነው። ምን እየሰራሁ እንደሆነ ስትጠይቀኝ ለፊልም ፅሑፍ አዘጋጆቼ ገንዘብ እንደምፈልግ ነገርኳት። ጽሑፉን እንዳሳያት ነገረችኝ። ኢትዮአሜሪካዊ አርቲስት ነች። ጽሑፉን አንብባ ወደደችው። እናም 325,000 ዶላር ሰጠችኝ።

 የተዋንያን መረጣ እና ቀረፃ

 የተዋንያን መረጣ ምን መልክ ነበረው?

ዘረሰናይ፡- ታዳጊዋን ሆና የምትሰራውን ልጅ ለማግኝት ወደ 3 ሺህ የሚጠጉ ልጆችን አይተናል። ወላጆቻቸውን እያስፈቀድን፣ ከትምህርት ቤት የሚመጡትን መኪና እያዘጋጀን፣ ቅዳሜ እና እሁድ ስቱዲዮ ወስደን፣ እየቀረፅን ለመለየት ሞክረናል። ስምንት ወርም ፈጅቶብናል።

ሌሎቹን አብዛኛዎቹን ድርጊቱ የተፈፀመበት ቦታ ነዋሪ የሆኑትን መርጠናል። ከዚህ በፊት ፊልም ላይ ተውነው ባያውቁም ቀረፃውን በጥንቃቄ አካሂደናል። ደጋግመን በተለያዩ አቅጣጫዎች ስለሰራን ተሳክቶልን ነበር።

ድጋፍ እና ሽልማቱ በአጭሩ ምን ይመስል ነበር?

 ዘረሰናይ፡- ጆሊ ምህረቱ ፊልሙን ስታይ በጣም አዝና ነበር። አንድ ታዋቂ ተዋናይ ማየት እንዳለበት በመፈለጓ አንድ ሰው ጠቆመችኝ። ሰውየው የእሷን ስዕሎች ሐሳብ የሚፈጥር እና የታዋቂዋ ተዋናይት አንጆሊና ጆሊ ተወካይ ነው። ደውላለት ፊልሙን አንጆሊና ጆሊ እንድታየው ነገረችው። አውስትራሊያ ፊልም ቀረፃ ላይ ነበረች። በዲቪዲ ተላከላት። አይታው ደወለችልኝ። አለም አቀፍ ትልልቅ ውድድሮች ውስጥ እንዲገባ ድጋፏን ጠየቅናት። #ፊልሙን እየረዳሁት ነው እና እባካችሁን ደግፉት; ብላ ለትልልቆቹ የፊልም ፌስቲቫሎች ማለትም ለሳንዳንስ እና ለበርሊን ፃፈችልን። ሁለቱም ጋ ገባን። እናሸንፋለን ብለን አላሰብንም። ዋናው ነገር ኢትዮጵያዊ ፊልም ውድድር ውስጥ መግባቱን በራሱ እንደ ትልቅ ሽልማት ቆጥረነዋል። በሁለቱም ፌስቲቫሎች እና በሌሎችም የተለያዩ ዘርፎች ልናሸንፍ ችለናል።

እገዳ፣ ክርክር እና ውጤቱ ፊልሙ እንዴት ታገደ?

 ዘረሰናይ፡- በመጀመሪያ ፊልሙን ያሳገደችው እውነተኛ ባለታሪኳ ነበረች። ከእሷ ጋር ከተስማማን በኋላ በቴአትር እና በሲኒማ ቤቶች በርካታ ተመልካቾች ተመልክተውታል። ከአንድ ወር በኋላ እንደገና መታገዱ ተነገረን። ያሳገዱት የታዳጊዋ ጠበቃ የነበሩት ልጆች ናቸው። ወይዘሮዋ ህይወታቸው ካለፈ 15 ዓመት አልፏቸዋል። ምክንያቱን ስናጣራ “የእናታችንን ንግግር ሳያስፈቅዱን ተጠቅመዋል።” የሚል ነበር። ከሳሾቹ 1 ሚሊዮን ብር ለኢኮኖሚ ጉዳት ካሳ እና 100 ሺህ ብር ለሞራል ጉዳት ካሳ መጠየቃቸውን ሰማን።

አቶ መኮንን ሰሙ፡- ከሳሾቹ “የእኛ እናት የፊልሙ ስራ አመንጪ ናት። ስለዚህ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ሞራላዊ መብት አለን።” የሚል ክስ መሰረቱ።

ክርክሩ እንዴት ነበር?

አቶ መኮንን፡- የነሱ ክርክር የሚመስለው “የእኛ እናት በዋናው ጉዳይዋ ላይ በጥብቅና ሙያዋ አገልግሎት ሰጥታለች። በጥብቅና ሙያዋ አገልግሎት ስትሰጥ በፍርድቤት ላይ በጥብቅና ያደረገችው ንግግር የህግ ጥበቃ አለው። ስለዚህ ይሄ መብታችን ተጥሷል።” የኛ ክርክር ደግሞ እርግጥ ነው፤ ንግግር በህግ ጥበቃ ይደረግለታል። ነገር ግን አንድ በህግ በዚህ በቅጂ እና ተዛማች መብቶች ጥበቃዎች በምንለው አዋጅ ቁጥር 410/96 አንድ የስራ አመንጪ ሊባል የሚችለው የአእምሮ ስራ ውጤት የሰራ ሲሆን ነው። ከሳሾች በዚህ ረገድ ያመነጩት የስራ ውጤት የለም። በፊልሙ ስራ ውስጥ ምንም ዓይነት የስራ ተሳትፎ የላቸውም። እነሱም ተሳትፎ አለን አላሉም። ለመሆኑ አንድ ሰው የስራ አመንጪ ለመባል በቅጂ እና ተዛማጅ መብቶች በህግ ጥበቃ የሚደረግለት የአእምሮኣዊ ስራ መስራት አለበት። በአዋጁ አንቀፅ 2 ንኡስ አንቀፅ 30 አንድ በቅጂ መብት የሚጠበቅ የፈጠራ ስራ በስነ-ፅሑፍ፣ በኪነ-ጥበብ እና በሳይንሳዊ መስኮች የተከናወነ የፈጠራ ስራ መሆኑን እና በምሳሌነት የተወሰኑ ስራዎችን ይዘረዝራል። ከእነኚህ ዝርዝሮች ውስጥ ጠበቃው በችሎት ላይ የሚያደርገው ንግግር ሊካተት ይችላል። ነገር ግን ሲካተት እንዴት ነው የሚካተተው? የሚለውን ነው ማየት ያለብን። ከሳሾች እናታቸው የሰሩትና የስራ አመንጪ ወይም የጋራ የስራ አመንጪ የሚያደርጋቸው የአእምሮ ፈጠራ ስራ ምን እንደሆነ አላስረዱም። ነገር ግን በክርክር ወቅት በፍርድ ቤት ያቀረቡት ክርክር፤ ክርክር እና ንግግር የህግ ጥበቃ ያለው እና የጠበቃው መብት ነው ለማለት ነው የፈለጉት። በቅጂ እና ተዛማጅ መብቶች አዋጅ አንቀፅ ሁለት ንኡስ አንቀፅ ሰላሳ ከተዘረዘሩት ስራዎች ውስጥ ንግግር ይገኝበታል። ይሁን እንጂ ይሄው ስራ ጥበቃ ሊያገኝ የሚችለው በህጉ የተዘረዘሩት መስፈርቶች ወጥነትና ግዙፍነት ሲያሟላ እና እንዲሁም ህጉ ጥበቃ አይደረግላቸውም ብሎ ከዘረዘራቸው ስራዎች ውጪ ሆኖ ሲገኝ ነው። አንደኛው ወጥነትና ግዙፍነት ያለው መሆን አለበት። ሁለተኛው ደግሞ ህጉ ራሱ እነኚህ ስራዎች ጥበቃ አይደረግላቸውም፤ ግዙፍ እና ወጥነት ያላቸው ቢሆኑም ለማለት ነው። ጥበቃ አይደረግላቸውም ያላቸው ደግሞ ያወጣቸው አሉ።

 አሁን ወጥነት እና ግዙፍነት ምን ማለት ነው? የሚለው ነው የኛ ክርክር እንግዲህ። ፍርድ ቤቱም በመጨረሻ የያዘው ጭብጥ ከዚህ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ነው። በርካታ ክርክሮች ቀርበዋል። ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ትኩረት አድርጎ ጭብጥ በያዘበት እና ለውሳኔው መሰረት ወደ አደረገው አንዱ ክርክራችን ብንሔድ ወጥነት እና ግዙፍነት ያለው ስራ የላቸውም፤ የሚለው ክርክራችን ነው። ወጥነቱ ወይም ኦሪጅናል ማለት ከሌላ ሰው ያልተቀዳ ማለት ነው። የከሳሾች እናት ያደረጉት ንግግር ከሌሎች ኦሪጂናል የሚያሰኝ ወይም ወጥነት ያለው የሚያሰኝ ነገር የለም ነው። ግዙፍነቱን በሚመለከት በአዋጁ አንቀፅ 2 ንኡስ አንቀፅ 11 ላይ እንደተገለፀው፤ የአንደኛው አምሳያ ግዙፍነት ምንድነው? አንድ ስራ ምስል ወይም ድምፅ ነው ግዙፍነት ማለት። ወደ ድምፅ ወደ ምስል የተቀየረ ወይም የአንደኛው አምሳያ ምትክ ለዚህ ተብሎ በተዘጋጀ መሳሪያ እንዲባዛ ወይም እንዲሰራጭ ማድረግ ማለት ነው። መሰራጨት አለበት። ለህዝብ ሊታይ ሊደመጥ በሚችል መልክ የተባዛ እና የተሰራጨ በሽያጭ ይሁን በስጦታ ይሁን በውሰት ይሁን በእነኚህ በአንድ መልክ ለህዝብ የተባዛ እና የተሰራጨ መሆን አለበት። በዚህ መልክ አሁን ግዙፍነት እንዲያገኝ ለዚህ አላማ ተብሎ በተዘጋጀ መሳሪያ ተባዝቶ እንዲሰራጭ የተደረገ ሳይሆን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ወይም የችሎት ውሎ እንደ ማንኛውም ጉዳይ የተመዘገበ እንጂ በዚህ መልክ እንዲሰራጭ ተብሎ ግዙፍነትን ያገኘ ንግግር የላቸውም። በአዋጁ ንኡስ አንቀፅ አንድ

መሰረትም የፍርድ ሒደት የተደረገው ንግግር በበቂ መጠን የታተመ እና የተሰራጨ መሆን ይጠበቅበታል ግዙፍነት ያገኛል እንዲባል። ጥበቃ እንዲያገኝ ሥራው መታተም አለበት። የታተመ ስራ ማለት ደግሞ አንድን ሥራ ወይም የድምፅ ሪከርዲንግ ተጨባጭነት ያላቸው ቅጂዎች በሽያጭ፣ በኪራይ፣ በውሰት እንዲሁም የቅጂዎችን ባለቤትነት ወይም ይዞታ ለማስተላለፍ እንደሁኔታው በስራው አመንጪ ወይም በቅጅው ባለመብት ወይም በድምፅ ሪከርዲንግ በፕሮዲውሰሩ ፈቃድ በበቂ መጠን ለህዝብ የቀረበ ሥራ መሆን አለበት። በዚህ መልክ የቀረበ ሥራ የለም። በዚህ መልክ የቀረበ ሥራ ኖሯቸው በህጉ መሠረት የፈጠራ ሥራ ሊባል የሚችል ስራ ኖሯቸው ያ መብት አልተደፈረም። ስለዚህ በፍርድ ቤት ላይ ያደረጉት ንግግር አንደኛ ቀጥታም አልተቀዳም። እሳቸው ያደረጉት ንግግር ሌሎቹ ከተፈቀደው በላይ አንዳንድ ጊዜ አሁን ጥበቃ የተደረገለት እንኳን መብት ቢሆን በህግ ከተፈቀደው በላይ ሲሆን ካልተኬደ ድረስ፤ ቃል በቃል እስካልተቀዳ ድረስ ንግግር አድርጓል፣ ከሱም ንግግር ኮት ተደርጓል (ተጠቅሷል) ተብሎ እንኳን ክስ ሊቀርብ ወይም ክርክር ሊቀርብ አይቻልም።

ምን ቢሆን ይሻላል?

አቶ መኮንን፡- የቅጂ መብት /copy right/ ለሥነ-ፅሑፍ እና ለአርት ሥራዎች ጥበቃ የሚያደርግ በተለይም የማባዛት እና የማሰራጨት መብቶችን የሚሰጥ ነው። በሌላም በኩል በህገ-ወጥ መንገድ የሚፈፀሙ የማባዛት እና የስርጭትን ተግባራት የሚከላከል እና የአእምሯዊ ንብረቶች አንዱ ዘርፍ በሆነው የቅጂ እና ተዛማጅ መብቶች ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ህጉም ጥበቃ የሚያደርገው ለሃሳቡ ሳይሆን ሃሳቡ ለተገለፀበት (expression of ideas) የጥበብ መንገድ ይሆናል።

 ህጉ ወጥነት እና ግዙፍነት ለአላቸው ሥራዎች ጥበቃ ያደርጋል። የሥነ-ጽሑፍ እና የአርት ፈጠራዎችን ያበረታታል። ይሁን እንጂ ከህጉ ድንጋጌዎች ጋር አግባብነት የሌላቸው ክሶች እየቀረቡ፤ ፊልሞች በሚመረቁበት ቀን ጭምር የእግድ ትዕዛዝ እየተሰጠባቸው፤ በዚህ ምክንያት ለዓመታት ሳይታዩ ጊዚያቸው ያልፋል። በጊዜ ብዛትም ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ዕውቀት እና ጊዜ ፈሶባቸው የተሰሩት የኪነጥበብ ሥራ ውጤቶች ለስርቆት ይጋለጣሉ። በህገ-ወጥ መንገድ እየተባዙ ይሰራጫሉ። ባለሙያዎች ሊካስ እና ሊመለስ ለማይችል ከፍተኛ የኢኮኖሚ እና የሞራል ጉዳት ስለሚደርስባቸው ተስፋ ይቆርጣሉ።

በመሆኑም በእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች የሚሰጡ የእግድ ትዕዛዞች የሚያስከትሉት ውጤት ክርክር ገና ባልተሰማው ዋናው ጉዳይ 

“ከሳሾቻችን ቀደም ብሎ የሚያስይዙት ነገር መኖር ነበረበት። ካሸነፍን ልንጠይቃቸው ይገባል። ይሁን እንጂ ሀብት እና ንብረት የለንም ብለው አላስመዘገቡም። ፍርድ ቤቱም ተቀብሏቸዋል። አንድ ሰው ከስሶ ቢረታ (ቢሸነፍ) ለተጎጂው ማድረግ ያለበት ምንድነው? ይሄ መታሰብ አለበት።”

   አስቀድሞ ፍርድ ከመስጠት የማይተናነሱ ስለሆኑ ከፍ ያለ ጥንቃቄ ሊደረግባቸው ይገባል። በተቻለ መጠን በቀረበው ክስ ላይ ከሳሹ ተጣሰብኝ የሚለው መብት በእርግጥም በህግ ጥበቃ የተሰጠው መብቱ ያለፈቃዱ በሥራ ላይ የዋለ መሆኑን፤ የእግድ ትዕዛዝ በመስጠት ጉዳቱን መከላከል፣ ወደፊት የፍርድ ባለመብት ቢሆን በመብቱ መጣስ ምክንያት የደረሰበትን ጉዳት በማናቸውም መንገድ ለመካስ የማይቻል መሆኑ ካልተረጋገጠ በቀር የእግድ ትዕዛዝ እንደሌሎች መደበኛ ጉዳዮች እንደቀረበ ባይሰጥ መልካም ነው።

ከዚህም በተጨማሪ እንደ ናይጄሪያ በመሳሰሉ ሀገሮች እንዳለው የቅጂ መብት ጉዳይ በመደበኛ ፍርድ ቤት ሳይሆን በህግ ባለሙያዎች እና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በሚዋቀር ትሪቡዩናል ቢታይ ወጪ እና ጊዜ ይቆጥባል። በተጨማሪም የባለሙያዎች ተገቢ እገዛ ስለሚያገኝ የበለጠ ውጤታማ ይሆናል።

ይህም እስኪደራጅ በፍርድ ቤቶች አሰራር ለአንዳንድ ጉዳዮች የተለዩ ችሎቶችን በማቋቋም ጉዳዮችን ለማቀላጠፍ እንደሚደረገው ጥረት ሁሉ፤ ለቅጂ መብቶችም ልዩ ችሎት በማቋቋም ጉዳዮቹ በተፋጠነ ሁኔታ መፍትሔ (ውሳኔ) እንዲያገኙ በፍርድ ቤቶች ቢታሰብባቸው መልካም ነው እላለሁ።

ከውሳኔው በኋላ

ዘረሰናይ፡- ፍትህን በማግኘታችን በጣም ደስተኞች ነን። ክሱ ውድቅ መሆኑ አበረታች ነው። ለሌሎች አስተማሪ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ደርሶብኛል። ፊልሙ እየታየ ክርክሩ ይቀጥል ብለን ነበር፤ አልተፈቀደልንም።

 ከሳሾቻችን ቀደም ብሎ የሚያስይዙት ነገር መኖር ነበረበት። ካሸነፍን ልንጠይቃቸው ይገባል። ይሁን እንጂ ሀብት እና ንብረት የለንም ብለው አላስመዘገቡም። ፍርድ ቤቱም ተቀብሏቸዋል። አንድ ሰው ከስሶ ቢረታ (ቢሸነፍ) ለተጎጂው ማድረግ ያለበት ምንድነው? ይሄ መታሰብ አለበት።

አቶ መኮንን፡- የቀረበው ክስ ሊነሳ ይገባል የሚለው ክርክራችን የበለጠ ተቀባይነት አግኝቶ አሁን በገለፅኩት ዓይነት ፍርድ ቤቱም ጭብጡን ይዞ በዚህ ዓይነት ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊም ሆነ ሞራላዊ መብት የላቸውም በሚል የፍርድ ባለ መብቶች ሆነናል። ይሄ ክርክር እንግዲህ የተጀመረው ጥቅምት ወር 2007 ዓ.ም. ነው። ውጤት ያገኘው በመጋቢት ወር መጨረሻ 2010 አካባቢ በዚህ ዓመት ነው። እንግዲህ ሶስት ዓመት ከስድስት ወር ያህል ፈጅቷል። ፊልሙ ከታገደ በኋላ በርካታ ፌስቲቫሎች እጩ ቢያደርጉትም መወዳደር አልቻለም። ሊያገኝ የሚገባውን ተገቢውን ጥቅም፣ የፊልሙ ለሙያዎች እና የፊልሙ አዘጋጆች ሊያገኙት የሚችሉትን ሞራላዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በእጅጉ ጎድቶታል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top