ማዕደ ስንኝ

የረድኤት ተረፈ ግጥሞች

1. የሞት መንገድ

እኔ ኩሬዪቱ ከራሴ መንጭቼ ራሴን ምሞላ

እያግበሰበሰ ቍልቍለት የሚተም

እርሱ ወራጅ ውሃ።

ኩሬ መኾን መልካም

ቢመጡበት እንጂ ዐልፎ ኽያጅ አይነካም።

ክፉ መኾን ወራጅ፡ ክፉ የኾነ እርሱ፡

በየደረሰበት ያገኛትን ኹሉ ፈስሶ ማረስረሱ።

ሴት መኾን መታፈር

ፈልቆ ቢመነጭም በጒድጓድ መታቈር።

ወንድነት ቍልቍለት እንደ ወራጅ

ውሃ

ሽቅብ መኼድ ማያውቅ፡ ኹሉንም ሚያገባ።

እኔ ኩሬዪቱ

የዛሬ ስንት ዓመት ከነበርኩበቱ

አንተን ጠብቃለኹ።

ስትኼድ አገኘኸኝ፡

ስትኼድ አገኘኻት፡

ያቺንም ይቺንም ይኸንን አውቃለኹ።

ኩሬ መኾን መልካም፡

አሁን ደፈራርሶ መልሶ ይጠራል።

ደሞ መጪውንም አምሮ ይጠብቃል።

ስትኼድ ያገኘኸኝ፡

ያደፈራረስኸኝ፡

ስትመለስ ያለኹ፡

ዛሬም ኵልል እንዳልኹ እጠብቅሃለኹ።

ዳሩ አትመለስም።

2. የማይወዳደር …

የማይወዳደር እኩያ የሚያጣ

ከልቤ ግርጌ ሥር ጣፋጭ ስሜት ወጣ።

ተሰማኝ፡ ወደድኩሽ። ያንቺን ጣም ለየኹኝ፤

ቈዳዬ ቀመሰሽ፡ ምላሴን ከዳኹኝ።

ኬትኛው አካሌ ፍቅርሽ የወደቀው፡

የሚያርበተብተኝ ጥፍሬን የሚነዝረው?

አካልስ አለው ወይ የሚታይ፡

ሚቀመስ፡

ወንድነት ገላዬን ነክቶ ሚያጐለምስ?

ትንፋሼን ቋጠርኩት ፍቅርሽን ላደምጠው።

የትኛው አካሌን ልሶ እንዳላመጠው

ንገሪኝ አንቺዬ …

‹‹ከደጅ እንዳያድር ዳስም ልጣልለት፤

እንዲህ ያለ ፍቅር አያድርም ከኔ ቤት።

በአዳፋዬ ባያድፍ ንጹሕ፡ ጥሩ ፍቅርሽ፡

ከቆሸሸ ገላ፡ ከዚህ በድን ይሽሽ …››

እንዲ ያል ልመና ሚዛን አያነሣም፤

የፍቅር ባሕርይ ዙፋንን አይሻም!

የት ጋ ነው ሚሰማኝ?

ምኔን ነው የያዝሺው?

የት ጋ ነው ያጣኹሽ?

ምኔን አገኘሺው?

ብቻ፡ ከልቤ ሥር ስሜቴ ይፈልቃል።

የደረስሽበትን

ያልደረስሽበትን

ረቂቁ ፍቅርሽ፡ እርሱ ብቻ ያውቃል።

3. አፋልጉኝ ‘ጠቃሚ’!

እንደው ታውቁ እንደኾን

ገላው ለሟሸሸ፡ ቈዳው

ለሰፋበት፡

እሳት እንደበላው የለበሰው ሥጋ

ለኰሰመነበት…

እንደው ታውቁ እንደኾን

በኅሊናው ዕዳ ዘወትር ለሚቀጣ፡

ኀጢአት ለተመቸው ነፍሱን

ለሚያስቆጣ…

እንደው ታውቁ እንደኾን

ነውሩን በጕያው እንደእሳት ታቅ

ጻድቅ የሚመስል በለበሰው ቀፎ…

እንደው ታውቁ እንደኾን

ጥርሱን ለሚያፈካ ከድቅድቁ ታግሎ፡

ልቡን ለሚያጠለሽ በጉባኤ ገኖ…

እንደው ታውቁ እንደኾን

በጨለማ ካባ ራሱን ደብቆ

በብርሃን ገመድ ለሚሞተው ታንቆ…

እንደው ታውቁ እንደኾን

በኵነኔ ኹሉ ሰቀቀን በጣጥቆት

ቍርበቱ ለሰፋው፡

በቀን ለሚጸጸት፡ ሲመሽ ለሚያጠፋው፣

ቈዳ የሚጠቅም ታገኙ እንደኾን፡

ገላ የሚጠግን ታገኙ እንደኾን፡

መዋያውን ልወቅ፡ ባመሸበት ልደር፤

በሚደቈስ ገላ ጽድቄን ለመጋገር።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top