ከቀንዱም ከሸሆናውም

የሐውልት ሥራ

በጥንታዊቷ ከተማ በአክሱም እንደ ቀድሞዎቹ ነገሥታት ቤተክርስቲያን ለማሠራትና የሠላም መታሰቢያ ለማኖር የጃንሆይ ምኞት ስለሆነ የሥራ ሚኒስትሩ ፊተውራሪ ታፈሰ ሀብተሚካኤል የቦታውን ፕላን አስጠንተውና አዘጋጅተው እንዲያቀርቡ ታዘው ሚያዚያ 8 ቀን ከመሃንዲሶች ጋር በባቡር ተሳፍረው በጅቡቲ በኩል ወደ ምጽዋ ተጓዙ። ከዚያም በአሥመራ ላይ አልፈው አክሱም ገብተው የቦታውን ፕላን ሲያስጠኑ ሰነበቱ። ወጣቱ

“የሐወልቱንም ስዕል ተመልክተው በዚያው አምሳል አንድ ሐወልት አዲስ አበባ አራት ኪሎ በሚባለው ስፍራ ላይ እንዲሠራ ለሥራ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ ሰጡ”

ልጅ ተድላ ኃይሉም ሪፖርት ለማድረግ አብሮ ሔዶ ነበር።

ፊተውራሪ ታደሰ በአክሱም የቦታውን ፕላን አስጠንተውና የሀውልቶችን ስዕል በፎቶግራፍ አስነስተው ካበቁ በኋላ በሄዱበት መንገድ ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ። ግርማዊ ንጉሠነገሥቱም ፕላኑን ተመልክተው ሥለ አሠራሩ ያስቡበት ጀመር።

የሐወልቱንም ስዕል ተመልክተው በዚያው አምሳል አንድ ሐወልት አዲስ አበባ አራት ኪሎ በሚባለው ስፍራ ላይ እንዲሠራ ለሥራ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ ሰጡ። ፊተውራሪ ታፈሰም ሥራውን በተሎ አስጀምረው በለጣቂው ዓመት አስፈፅመውታል።

 ይህ ሐወልት ኢጣሊያኖች በወራሪነት አዲስ አበባ በገቡበት ዘመን በ1928 ዓ.ም. ከወደ ሥሩ በሞደሻ ሰባብረውና አፍርሰው በትሬንታ ኳትሮ ካሚዮን አስጎትተው የጣሉት ነው።

ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ (1922-1927) ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ

የባቡር ታሪክ ባዲሳባ

የ ሰርኪስ ባቡር በ1898 ዓም. አዲስ አበባ ከተማ ደርሶ ስለታየ የዘመኑ ድንቅ ሆኖ ከረመ። ይህ ባቡር (በተለምዶ አነጋገር ባቡር የሚባለው ሞተር ያለው ሁሉ ነው። ዛሬም ቢሆን አንዳንድ በእድሜ የገፉ ሰዎች መኪናና ወፍጮን ባቡር ይላሉ።) በእሳት ኃይልና በውሃ እንፋሎት እየተነዳ የሚሔድ ነው። ሙሴ ሰርኪስ ባቡሩን እስከ ጅቡቲ ድረስ በመርከብ አስመጣና ከዚያ በኋላ በምድር ባቡር አስጭኖ የምድር ባቡር ሃዲድ እስከደረሰበት እስከ ኢሳ ወረዳ አደረሰው። ከዚያም ባቡሩን አገጣጥሞ በበረሃው የነጋዴ መንገድ፤ በሐረርጌ ግዛት በታዘዘለት ህዝብ እያስገፋ ተጉዞ በአዋሽ ወንዝ አደረሰው። ከዚያም የምንጃር ባላገር ታዞለት መንገዱን በመደልደልና ባቡሩን በመግፋት እየረዳው በሸንኮራ ላይ ተጉዞ አዲስ አበባ አደረሰው። ህዝቡም የባቡሩን ስም በአስመጪው ነጋዴ በሙሴ ሰርኪስ ስም ሰይሞ “የሰርኪስ ባቡር” እያለ ይጠራው ጀመር።

ባቡሩ ወደ አዲስ አበባ በተቃረበ ጊዜ ዳግማዊ ምኒልክ ከከተማቸው ውጪ በመንገድ ላይ ሆነው ተቀበሉት። አዲስ አበባ ከደረሰ በኋላም አንድ ቀን የባቡሩን ትርእይት ለሠራዊት ለማሳየት በአቡን ሰፈር አጠገብ በመንገድ ዳር ትልቅ ድንኳን ተተክሎ በዓል ተደረገ። ዳግማዊ ምኒልክ ከመኳንንታቸው ጋር መጥተው በድንኳን ውስጥ ከፍ ካለ ሥፍራ ላይ በወምበር ተቀመጡና ሙሴ ሰርኪስ ባቡሩን ወደፊትም ወደኋላም እያስነዳ የፉጨት ድምፁን እያሰማ ሁኔታውን አሳየ። ዳግማዊ ምኒልክም በባቡሩ ጋሪ ላይ ተቀምጠው ጥቂት ተጓዙበት። ከዚህ ጊዜ በኋላ ባቡሩ ተሰናክሎ ቆሞ ነበር። የቆመበት ቦታም “ሰባራ ባቡር” ተብሎ እስከአሁን ድረስ በዚህ ስም ይታወቃል። የዘመኑ አዝማሪም፡-

 “ብነግርሽ ብነግርሽ አታጠናቅሪ

 እንደ ሰርኪስ ባቡር ተገትረሽ ቅሪ” ብሎ ገጥሟል።

 ከ “የኃያኛው ክፍለ-ዘመን መባቻ” መጽሐፍ የተወሰደ

የጥንቱ ቅጣት

በ ጥንቱ ጊዜ በተደጋጋሚ ሌባ ወይም ጥፋተኛ ላይ የሚፈረደው ከፍተኛው የግርፋት ቅጣት አርባ ጅራፍ ነበር። ይሁን እንጂ ሰላሳ ዘጠኝ እንደተገረፈ የአቆጣጠር ስህተት እንዳለ በማለት ግርፋቱ ይቆማል። የመገረፊያውም ጅራፍ እንዲለዝብ በየጊዜው ሞራ እየተቀባ በታላቁ ቤተ-መንግሥት “አላማጣ” ተብሎ በህዝብ በሚጠራው ስፍራ ይቀመጥ ነበር።

 በሞት እንዲቀጣ በዙፋን ችሎት ፍርዱ የፀናበት ሰው ቅጣቱ ይፈፀምበት የነበረው፤ በመጀመሪያ ጊዜ አሁን የቂርቆስ ቤተ-ክርስቲያን ከሚገኝበት አካባቢ ሲሆን፤ በኋላም የጥይት ማነጣጠሪያ ቀዳዳ ባለው አሁን የጥይት ፋብሪካ በሚገኝበት አካባቢ በተሠራ አንድ የግንብ ቤት ውስጥ ነበር።

የተፈረደበት ሰው ፍርዱ ሲነገረው ኮሶ የመጠጫ ጊዜ እንዲሰጠው ይጠይቅና ለኮሶ የሦስት ቀን ጊዜ ይሰጠዋል። በዚሁም ጊዜ ውስጥ የተፈረደበት ሰው ኑዛዜ ያደርጋል። ከዚያ በኋላ በጥይት የሚደበደብ ሲሆን ከከሳሹ ቤተ-ዘመዶች በአንደኛው ተፋላሚነት ይደበደባል። ስቅላት ሲሆን ግን በወኽኒ ቤቱ ወገኛ (ለእዚሁ የተመደበው ሰው) አማካይነት ቅጣቱ ይፈፀምበታል። ስቅላቱ ይፈፀም የነበረው አሁን የዳግማዊ ምኒልክ ሐወልት ከቆመበት ስፍራ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያን አቅራቢያ በቅሎ በነበረ አንድ ትልቅ ሾላ ላይ እንደነበረ ይነገራል። ተከሳሹ ሲሰቀል የመስቀያው ገመድ ቢበጠስ ለሁለተኛ አይሰቀልም። በነፃ ይለቀቅ ነበር።

በዚሁም አንፃር ተፈርዶበት በጥይት ሲደበደብ ሳይሞት ቆስሎ አምልጦ የነበረ አንድ ሰው፤ ከጊዜ በኋላ በከተማ ሲዘዋወር ተገኝቶ እንደገና ሊደበደብ ይገባል። የሚል ክርክር በ1942 ዓም. ሲቀርብ አስቸጋሪ ጉዳይ ሆኖ በመገኘቱ የውጭ አገር ተወላጆች የሆኑ ዳኞችና ኢትዮጵያውያን ዳኞች በሚገኙበት እንዲታይ ተደርጎ በጥንቱ ልማድ ሲሰቀል ገመዱ የተበጠሰ ሰው እንደገና እንደማይሰቀለው ሁሉ በጥይትም ሲደበደብ ሳይሞት የቀረ ሰው እንደገና መደብደብ አይገባውም የሚል አሳብ በመሰንዘሩ ሁለቱም ሃሳብ ለንጉሠነገሥቱ ቀርቦ በኢትዮጵያውያኑ አሳብ እና በጥንቱ ልማድ መሠረት የተባለው ሠው በድጋሚ ከመደብደብ እንዲድን ተወስኗል።

ከ”ኢትዮጵያ ሕግና የፍትህ አፈፃፀም ታሪክ

አሰፋ አባተ

የ አሰፋ አባተን ችሎታ በስሚ ሰሚ ያረጋገጡ ሁሉ ያፈላልጉት እና ጎጆዋቸው ብቅ እንዲልም ጥሪ ያቀርቡለት ጀመር። ደስ ብሎት ፍቃዳቸውን ይፈፅማል። አንድ አባተ ኃይሉ የተባለ የየጁ አውራጃ ነጭ ለባሽ ጦር አዛዥ የግል አዝማሪ እንዲሆን አሰፋን አባብሎ ይወስደዋል። በርስተ-ጉልቱም እንዲያስገብር ሹመት ይሰጠዋል። በጊዜው አንዳንድ ባላባቶች አዝማሪዎቻቸውን በሚገዙት ሀገር ውስጥ ያስገብሩላቸው ዘንድ ይሾሟቸዋል። ይህም ህዝቡም የአዝማሪውን መሾም ሲሰማ በመኸር ጊዜ በደምብ እንዲገብር የሚገፋፋ ስለሆነ ነው። በነገራችን ላይ አንድ አዝማሪ እንዲያስገብር በተሾመበት ሀገር ሌላ አዝማሪ እንዲዘፍን አይፈቅድለትም። አይቻልም። መዝፈን ቢፈልግ እንኳን በስፍራው የተሾመውን አዝማሪ ፍቃድ መጠየቅ አለበት።

አሰፋ አባተ ባለሟል አዝማሪ ሆኖ ከተወሰደ በኋላ ከበርካታ ዘማሪያን ረድፍ በመሰለፍ አልጋ ወራሹ ዘንድ ቀርቦ በዘፈነበት ጊዜ በድምፁ እጅግ ከመደነቃቸው የተነሳ ሽጉጥ እና ጠመንጃ ሸልመውት ነበር። የቤተመንግሥቱን ሥርዓትና እና ህግ እየለመደ እንዲያድግ ተደረገ።

ውሎ ሲያድር ግን የቤተ-መንግሥቱን ግቢ ጠላው። ለአልጋ ወራሹም የፍቃድ ጥያቄ ካቀረበላቸው በኋላ ያሰበው ተፈፀመለት። ደሴን ለቅቆ ወደ መቀሌ አመራ። መኮብለሉን ስለአወቁበት ተይዞ ደሴ አልጋ ወራሹ ዘንድ መጣ። አሠፋ በአልጋ ወራሹ ግቢ ጥቂት ቆይታ ከአደረገ በኋላ በድጋሜ ጠፍቶ በመውጣት በየአውራጃው እየተዘዋወረ መዝፈን ይጀምራል።

 እንደገናም ታስሶ ከተያዘ በኋላ ወደ ቤተመንግሥቱ ተመለሠ። የኋላ ኋላ ጠፍቶ ማስቸገሩ ሲደጋገም የፈለገበት እንዲሄድ ፍቃድ ተሠጠው።

 ቤተ-መንግሥቱን የጠላበት ምክኒያት ምን እንደሆነ ግን ግልፅ አልነበረም።

 ከ”ብርቆቻችን” መጽሔት

እመ ሕዝብ

በ ኢትዮጵያ ሰላማዊ ሰልፍ ህጋዊ የብሶት መገለጫ ሆኖ በስራ ላይ የዋለው ንጉሠ-ነገሥት ዳዊት ከ1365 እስከ 1395 ዓ.ም. ለሰላሳ ዓመታት በመራበት ጊዜ ነበረ። ንጉሥ ዳዊት ከጥንቶቹ ነገሥታት ለየት ባለ መንገድ የሰላማዊ ሰልፍ ሕግ አውጥቷል። የሰልፉን ሁኔታ የሚከታተለው እመ ሕዝብ የተባለው የሠለሞን ዘበኛ ሲሆን፤ እመ ሕዝብ ማለት የሕዝብ እናት ማለት ነው። ሕዝቡ ሰላማዊ ሰልፍ ሊያቀርብ የሚችለው ለአስተዳዳሪነት የተሾሙት ገዥዎች በደል ሲፈፅሙበት ይሆናል። ይሁን እንጂ ገዥው አደረሰብን የሚሉትን በደል በቅድሚያ ለእመ ሕዝብ የሰላም ዘበኛ አዛዥ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። ዘበኛውም በቅድሚያ የቀረበለትን አቤቱታ ይመረምራል። ሁኔታው

ሶስተኛ የሰልፍ መሪው ከሚይዛት የተላጠች እንጨት ላይ የሀገሪቷን ሰንደቅ ዓላማ በአመድ ላይ ጣሏት፤ በእዚህም ምክኒያት ሀገሪቷን አመድ ወረሳት”

ገበሬውን የጎዳ ሆኖ ካገኘው ገበሬው ከቦታው ሳይነቃነቅ ለንጉሠ-ነገሥቱ በማስረዳት በዳይ የተባለው ገዥ ባስቸኳይ ከስልጣን እንዲወርድ ይደረጋል። ሕዝብ ላይ በደል በማድረስ ተከስሶ የተነሳ ባለስልጣን ከተከሰሰበት ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ተዘዋውሮ እንዲሰራ አይደረግም።

 በእዚያ ዘመን የሚደረገው ሰላማዊ ሰልፍ በግድ የለሽነት እና በችኮላ ሳይሆን እውነት፣ ተጨባጭና ወደ ዳኝነት ቀርቦ የሚያስወቅስ በደል መሆኑን በተገቢው ደረጃ ያጣራል። ከዚያም ሰልፈኞቹ፣

አንደኛ የእርሻ መገልገያ የሆኑትን ወገል፣ መዋጆ፣ መደላድል (የበሬ ጫንቃ) ቀንበርና ሞፈር፣ ድግርና ወገል፣ ጅራፍ፣ ምራን እና የመሳሰሉትን በነፍስ ወከፍ በመሸከም፤

 ሁለተኛ የተላጠ እንጨትና ባዶ ጎተራ አመድ ቆንጥሮ በትንሽ ጨርቅ ከቀኝ ክንዱ ላይ በማሰር፤

 ሶስተኛ የሰልፍ መሪው ከሚይዛት የተላጠች እንጨት ላይ የሀገሪቷን ሰንደቅ ዓላማ በአመድ ላይ ጣሏት፤ በእዚህም ምክኒያት ሀገሪቷን አመድ ወረሳት። አስተዳዳሪው እንደ በረሃ ዝንጀሮ የሰው ንብረት የሆነውን የእህል ክምር ገልብጦ ይበላል። እንዲሁም የግብርና መሣሪያዎቹ እና የጎተራው ትርጉም፤

 “ከእንግዲህ ወዲህ አርሰን ምርት አናመርትም፤ የአጤ ቆሎም አንከፍልም። የበሬ ዕቃዎቻችንን ንጉሠ ነገሥቱ ተረክቦ ከሚያውልበት ያውል ጎተራው ባዶ ነው” በማለት ይፈታል።   

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top