የታዛ ድምፆች

የልማታዊ ጋዜጠኝነት ምንነትና የትግበራ ተቃርኖ

በዓለማችን ሚዲያ በማህበረሰቡ ህይወት ውስጥ የተጎናጸፈው ስፍራ በጣም ከፍተኛ መሆኑ ለብዙዎቻችን ግልጽና የማያሻማ ነው። በ16ኛው እና በ17ኛው ምዕተ ዓመታት በአሜሪካ እና በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት አሃዱ ተብሎ የተጀመረው የጋዜጠኝነት ሙያ ዛሬ መጠኑም ሆነ ውስብስብነቱ ገዝፎ በእያንዳንዱ የዓለማችን ማህበረሰብ ህይወት ውስጥ የራሱ የሆነ ተጽእኖ በማሳደር ላይ ይገኛል። የጋዜጠኝነት ሙያ ከምዕራባውያን ለዓለም የተሰጠ በረከት ስለመሆኑ ማንም ሊክደው የማይችለው ሀቅ ነው። በእንደኛ ያሉ ሀገራት ሙያው የተዋወቀው በቅርቡ መሆኑ ይህን ሀሳብ ይደግፈዋል። ልማታዊ ጋዜጠኝነት ከመነሻው የአዳጊ ሀገራት ምሁራን በምዕራባውያን ሚዲያ አዘጋገብ ላይ ባላቸው ቅሬታ ምክንያት እንደ ተለዋጭ መፍትሄ የመጣ ነው። ከጀማሪዎቹ አንዱ እንግሊዛዊው አለን ቻክሊ መሆኑን ስንመለከት ደግሞ ይህም የጋዜጠኝነት አይነት ራሱ የምዕራባውያን በረከትነቱን በማያሻማ መልኩ ያሳየናል። ውሎ አድሮ ግን የአዳጊ ሀገራት መንግስታት በፈጠሩት ለራስ የማመቻቸት ሂደት ሰበብ የሚገባውን ክብር እያጣ ሊመጣ ችሏል። አበርካቾቹ ምዕራባውያን ወገኖችም ለዚህ የጋዜጠኝነት ዘውግ ጥይት የማይበሳው ጀርባቸውን ከሰጡት ቆይተዋል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው በዚህ ዘርፍ የተጻፈ አንድም ራሱን ችሎ የቀረበ መጽሐፍ አለመኖሩ ነው። በምርምር ዘርፍም ቢሆን ባለፉት 30 እና 40 ዓመታት በዚህ መስክ የተደረጉ ጥናቶች እዚህ ግቡ የማይባሉ ናቸው።

 መርሆውን ተከትሎ በአግባቡ ቢሰራ ልማታዊ ጋዜጠኝነት ለእንደኛ ያሉ ሀገራት ጠቃሚነቱ ወደር የለሽ ነው። ልማታዊ ጋዜጠኝነት ሁሌ ሲደረግ እንደምናየው መንግስት የሚለውን ብቻ ወደ ህዝብ የሚያወርድ የገደል ማሚቶ አይደለም። ይህ የጋዜጠኝነት ዘርፍ ብዙ የመረዳት ችግር ያለባቸው ሰዎች በሚሰጡት የተሳሳተ ትርጓሜ ምክንያት ጉዳት እየደረሰበት መሆኑም ግልፅ ነው።

ይህን የጋዜጠኝነት ዘውግ እንደ አመለሸጋ የማደጎ ልጅ የተመለከቱ የ3ኛው ዓለም ሀገራት መንግስታት በሚመቻቸው መልኩ እየኮረኮሙና እያበጃጁ ስለተጠቀሙበት በብዙሃን ዘንድ ያለውን ምልከታ አበላሽተዋል። እነዚህ መንግስታት በተመለከቱበት መነጽር የሚያየው ሰው መብዛቱ ተስፋ አስቆራጭ የሚሆነው ስለ ዘውጉ እውቀት በሌላቸው ዘንድ ብቻ አይደለም። በጠቃሚነቱ ላይ መጠነ ሰፊ ዕምነት ባሳደሩ ወገኖችም ጭምር እንጂ። በአንዳንድ ሀገሮች፣ በተለይም ልማታዊ ጋዜጠኝነትን ፈጠን ብለው በተቀበሉት የደቡብ ምስራቅ ኤሽያ ሀገራት፣ የቀዝቃዛውን ጦርነት ማብቃት ተከትሎ የሃይልና የፖለቲካ ሚዛኑ በምዕራባውያን እጅ መውደቁን በማየት ወደ መደበኛው የምዕራባውያን የጋዜጠኝነት አሰራር ተመልሰዋል። ይህም ጋዜጠኝነቱን ገና እየጀመሩ የነበሩ ብዙ የአፍሪካና ሌሎች አዳጊ ሀገሮችን ግራ ያጋባ ክስተት ቢሆንም የመንግስት አጋርነት ጸባዩን የወደዱለት አንዳንድ መሪዎች ወዳጅነታቸውን የሚያቋርጡበት ሌላ አማራጭ በማጣታቸው ይመስላል ከዚህ የልማታዊ ጋዜጠኝነት ዘውግ ላይ እንደተጣበቁ መቅረታቸውን እናያለን። ይልቁንም የዘውጉን መርሆዎች በመጠምዘዝ ወደ ተራ የህዝብ ግንኙነት ስራነት በማውረድ ትክክለኛ መስመሩን ስቶ የጋዜጠኝነት የእንግዴ ልጅ እንዲሆን አድርገውታል።

 ከመጀመሪያው ብንነሳ የልማታዊ ጋዜጠኝነት አስፈላጊነት በሶስት አበይት እውነታዎች ላይ ይመሰረታል። የመጀመሪያው ፈጣን የሆነ ልማት ለእንደኛ አይነት ታአዳጊ ሀገራት አሰፈላጊ ነው የሚለው ነው። ምንም በማያከራክር ሁኔታ ልማት ያስፈልገናል። በተለይም አፍሪካን በመሳሰሉ ብዙ አህጉራት የሚገኙ ሕዝቦች አሁን ካሉበት ድህነት በፍጥነት መውጣት ይጠበቅባቸዋል። ይህ መሆን ካልቻለ ህልውናቸው አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይደርሳልና። ሁለተኛው ምክንያት ሆኖ የቀረበው ሚዲያ ወይንም ጋዜጠኝነት ልማትን የማገዝ አቅማቸው በጣም ከፍተኛ መሆኑ ነው። ይህም በምርምር የተደገፈ እውነታ ነው። ሚዲያ ባለው ተደራሽነት ምክንያት ልማትን በማፋጠን ተግባር ላይ ሊውል ይችላል። ሶስተኛው ሚዲያ ያን ያህል ለልማት ጠቃሚ ከሆነ ልማታዊ ጋዜጠኝነት እንደ አንድ የሚዲያ ዘውግ አዳጊ አገራት ለሚያደርጉት የእድገት መፍጨርጨር ከባድ እገዛ ሊያደርግ ይችላል ተብሎ መታመኑ ነው። በልማት ላይ ያተኮረ ጋዜጠኝነት ከሌሎች ትርፍ ተኮር ጋዜጠኝነት ትግበራዎች በተሻለ ሁኔታ ልማትን ማገዝ ይችላል ቢባል ስህተት አይሆንም። ስለዚህ የልማታዊ ጋዜጠኝነት አስፈላጊነት ከነዚህ ምክንያታዊነትን ከተላበሱ እምነቶች የመነጨ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ጋዜጠኝነት ለልማት ቢውል ያለው ፈይዳ ሰፋ ያለ ነው። ይህን ፋይዳ ለመገንዘብ በጥሞና ስለአዳጊ ሀገራት ነባራዊ ሁኔታ ለመረዳት መሞከርን ይጠይቃል። ይህን ማድረግ የሚያስከፍለው ዋጋ የለውም።

ግልፅ መሆን የሚገባው ነገር ከመሰረቱ ልማታዊ ጋዜጠኝነት ማእከሉ ያደረገው በእውቀቱ ተኮፍሶ በማህበረሰቡ ታዛ ላይ ተመቻችቶ እየተንፈላሰሰ የሚኖረውን ጥቂት ምሁር ነኝ ባይ ወገን አይደለም። የዚህ ጋዜጠኝነት ትኩረት በተለያዩ ምክንያቶች በተለይም በዕውቀት ማጣት ህይወታቸውን በጨለማ የሚመሩ ብዙሃንና የጊዜውን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለመረዳት መሰረታዊ እውቀት አጥተው ግራ የተጋቡት የህብረተሰብ ክፍሎችን ለይቶ በዓለም ላይ እየተከሰተ ያለውን ሂደት በሚገባቸው ቋንቋ እያዋዛ ለማስተማርና ለማሳወቅ ያለመ ጋዜጠኝነት ነው። የልማታዊ ጋዜጠኝነት ጠንሳሾች እነ አለን ቻክሊ ይህን ሀሳብ ሲጀምሩት የታያቸው ነገር ቢኖር መደበኛው (mainstream) ሚዲያ አብዛኛውን ማህበረሰብ ችላ ማለቱ እና ገንዘብና ትርፍ በማሳደድ ላይ መጠመዱ ነበር። በተጨማሪም ገበያ ተኮር (market driven) ሚዲያ አደብ ያለው ጋዜጠኝነት የሚጠበቅበትን የማህበረሰብ ሃላፊነትና ተጠያቂነት ለመወጣት ያለው ተነሳሽነት በጣም የወረደ ነው ብለው ስላሰቡ ነው።

 ይህ ጋዜጠኝነት የቀረበውም የነበረውን የጋዜጠኝነት አትኩሮት ወደ ልማት በማዞር የህዝብን የልማት ተሳታፊነት ለማሳደግ ታልሞ ነው። እንግሊዛዊው አለን ቻክሊ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን ስለ ታዳጊ ሀገራት የሚዘግቡበት መጠን፣ አቅጣጫና ሁኔታ የተሳሳተ መሆኑን ይተች ነበር። ምዕራባውያን ስለ አዳጊ ሀገራት በተለይም ስለ አፍሪካ ሲዘግቡ ዜናቸው ስለ ረሀብ፣ ጦርነት፣ ቸነፈርና የመንግስት ግልበጣ ካልሆነ ዜና እንደማይመስላቸው ቻክሊ ትዝብቱን አስቀምጧል። ምንም አይነት መልካም ነገር በነዚህ አዳጊ ሀገራት ውስጥ ይኖራል ብለው ለማሰብ የተሳናቸው እንደሆኑ ዜናዎቻቸውን ያጠኑ ምሁራን ያብራራሉ። ለዚህ ነው ለአዳጊ ሀገራት የራሳቸው የሆነ፣ ክፉና ደጋቸውን ለይቶ፣ በአግባቡ የሚዘግብላቸው ሚዲያ አስፈላጊ ነው የሚለው ሀሳብ የመነጨው። ልማታዊ ጋዜጠኝነት ከመደበኛው የጋዜጠኝነት አሰራር የሚለይበት ዋነኛው መንገድ ክፉ ክፉን እየመረጠ በመዘገብ ህዝብን ተስፋ የሚያስቆርጥ ሳይሆን፣ ክፉና ደጉን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ የሚያቀርብና መጠነኛም ብትሆን ለህዝቦች ተስፋን የምትጭር ጭላንጭል እድገት ወይም ለውጥ ካለች ያቺን ማሳየት የሚፈልግ ነው። በዚህም ላይ ተመርኩዞ ህዝቡ ለበለጠ ስራ እንዲነሳሳ ይቀሰቅሳል።

 እውነተኛው ልማታዊ ጋዜጠኝነት ከመዝናኛ ይልቅ ትምህርታዊ የሆኑና የህዝቡን ህይወት የሚለውጡ መረጃዎችን በማቀበል ላይ ያተኩራል። መንግስትንም ፈታኝ በሆኑ የህዝብ ችግሮች ላይ እንዲያተኩር አቅጣጫ ያሳያል፣ ያስተምራል፣ ይገስፃል። በየአካባቢው ያሉ፣ ለህዝብ ጥቅም የተጀመሩ የመንግስት ፕሮጀክቶች ትኩረት እንዲያገኙ ይከታተላል፣ ሂደቱን ይገመግማል፣ ግልጸኝነት እንዲሰፍን በመስራትም ሙስናን በብርቱ ይታገላል። የልማታዊ ጋዜጠኝነትን ዓላማና ግዳጅ ይዞ ይንቀሳቀሳል። ለልማት ከፍተኛ ሚና ያላቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ መርጦ ያተኩራል። መብቱን ማስጠበቅ ላቃተው እና ፍትህ ለጠማው ብዙሃን ድሀ ጆሮ ሰጥቶ በማድመጥ ድምፁ በመሆን ያገለግላል። የሚያስፈልጋቸውን መረጃ ቀለል ባለ መንገድ በሚገባቸው መልኩ ያዘጋጃል። ብዙ ጊዜ እንደምናየው በፕሮጀክቶች ማለቂያ ላይ ባሉ በዓላት ላይ ተገኝቶ የሪባን ቆረጣን ማድመቅ ሳይሆን ለፕሮጀክቶች ትግበራ ሂደት ሰፊ ትኩረት ይሰጣል። ይህ የጋዜጠኝነት አይነት አሳታፊ ነው። ደጋፊም ይሁን ተቃዋሚ ለሁሉም እኩል ድምጽ ይሰጣል። አግራዋል እና ሾው እንደሚሉት ከሆነ ልማታዊ ዜና የልማት እቅዶችን፣ ሂደቶችን፣ ፖሊሲዎችንና ችግሮችን በጥልቀት ይገመግማል፣ ይለካል፣ ይተነትናል። በእቅድ እና በትግበራ መሀከል ያለውን ልዩነት ይገመግማል፣ ለምን? ሲልም ይጠይቃል። ለልማት ፕሮጀክቱ አስፈላጊነት መንደርደሪያ መረጃዎችን ይሰጣል። ልማቱ በትክክል ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን ፋይዳ ያስረዳል።

 በብዙ ሀገራት ሥራ ላይ እንደመዋሉ የዚህ ጋዜጠኝነት አተገባበር በየሀገሩ ለምን ተለያየ? የሚለው ጥያቄ በጣም አስፈላጊ ይመስላል። ኩነዚክ እንደሚለው እ.ኤ.አ. በ1970ዎቹ መጨረሻ በተለያዩ የልማታዊ ጋዜጠኝነት አፈፃፀም ልዩነቶች ምክንያት መከፋፈል ጀመረ። እናም በ1970ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ዘውጉ በሁለት ተከፈለ። እነዚህም የምርመራ ዘጋቢ ዐይነት (Investigative Type) እና ‘የአምባገነንነት ወዳጅ’ (authoritarian benevolent) የሚባሉት ሆነው እናገኛቸዋለን። የመጀመሪያው ዐይነት ከምዕራባውያን የምርመራ ዘጋቢ ጋዜጠኝነት ጋር የሚመሳሰል ሆኖ የልማት ፕሮጀክቶችን ከእቅዳቸው ጀምሮ እስከ ማጠናቀቂያቸው ድረስ በጥልቀት መገምገም ያስፈልጋል የሚል አቋም የያዘና ጋዜጠኞች ነፃነታቸው ተጠብቆ በገለልተኝነት መስራት አለባቸው የሚል እምነት የሚያራምድ ነው። ሁለተኛው አይነት ግን ለልማት ሲባል ጋዜጠኛው የመንግስት ደጋፊነት ሚና መጫወት አለበት የሚል አቋም የያዘ ሲሆን የብዙ አዳጊ ሀገራት መንግስታትን ቀልብ በይበልጥ የሳበው ይህ አይነቱ ጋዜጠኝነት ነው። ይህ የልማታዊ ጋዜጠኝነት አይነት የሚከተሉትን ባህሪያት ያሳያል። ዲሞክራሲን እንደ ቅንጦት ያያል፣ ፈጣን እድገት ለማምጣት ከተፈለገ የሰዎች መብትና ነፃነት ለጥቂት ጊዜ በመስዋዕትነት ሊታለፍ ይገባል ይላል። ልማትን ለማምጣት ሁሉም ከመንግስት ጋር መቆም ያሻዋል ባይም ነው። በተጨማሪም ችግሮች እንዳይከሰቱ በሚል ሰበብ መረጃን መምረጥና በጥንቃቄ መያዝ ያስፈልጋል ብሎ ያምናል። ለእድገትና ለህዝብ ጥቅም ሲባል ሳንሱር መኖሩ አስፈላጊ ነው እስከማለትም ይደርሳል።

 ይባስ ብሎ ከ1980 በኋላ ባሉት ጊዜያት የልማታዊ ጋዜጠኝነት አተገባበር በየሀገሩ እየተለያዬ መጥቶ ሮማኖ እንዳለው ከሁለት ወደ 5 አይነትነት አድጎ እናገኘዋለን። እነዚህ የዘውጉ አይነቶችም አንደኛው ጋዜጠኞች እንደ ሀገር ገንቢዎች (Journalists as Nation Builders)፣ ሁለተኛው ጋዜጠኞች እንደ መንግስት አጋሮች (Journalists as Government Partners)፣ ሶስተኛው ጋዜጠኞች እንደ የለውጥ አራማጆች (Journalists as Agents of Empowerment)፣ አራተኛው ጋዜጠኞች እንደ የሕዝብ መብት ጠባቂዎች (Journalists as Watchdogs)፣ እና የመጨረሻው ጋዜጠኞች እንደ የግልፀኝነት ጠባቂዎች (Guardians of Transparency) የሚሉ ናቸው። በአፍሪካና በሌሎች መንግስታት ዘንድ ተመራጭ ሆኖ የቀረበው ጋዜጠኞች እንደ መንግስት ወዳጅ/ አጋር የሚለው መሆኑ ግልፅ ይመስላል።

ለልማታዊ ጋዜጠኝነት ዋነኛ ፈተና ሆነው የዘለቁ ነገሮችን ስንመለከት መጠነ ሰፊ ሆነው እናገኛቸዋለን። አብዛኞቹ በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎችም ሆኑ የዚህ ዘርፍ ምሁራን ጋዜጠኝነትን የተማሩት በምዕራባዊ የጋዜጠኝነት መርሆዎች፣ በምዕራባውያን መምህራን እና በነዚሁ ሰዎች በተጻፉ መጻሕፍት ስለነበረ ለምዕራባዊው ጋዜጠኝነት ከፍተኛ ቦታ ይሰጣሉ እንደ ሂንዚች አገላለጽ። ለአዳጊ ሀገራት የተለየ የጋዜጠኝነት አማራጭ ማስፈለጉን አያምኑበትም። በዚህ የተቀኙ ሰዎች ልማታዊ ጋዜጠኝነትን መንግስት እንደሚመቸው የሚያበጀው አድርገው ይወስዳሉ። ሥጋታቸው በመጠኑም ቢሆን ተቀባይነት እንዳለው ግልፅ ነው። ፍራቻቸው ጋዜጠኞች ከመንግስትና ከፖለቲከኞች ጋር ማበር ከጀመሩ ራሳቸውን ችለው መቆም ይሳናቸዋል፣ በመንግስት ተጽእኖ ስርም ይወድቃሉ የሚለው ነው። መንግስትን ላለማስከፋት ራስን በማረም (self-censorship) ተግባር ውስጥ ይዘፈቃሉ:: ይህም ለጋዜጠኝነት በጣም አስፈላጊ የሆነውን ተአማኒነት ያሳጣቸዋል። ጋዜጠኝነት ያለተአማኒነት አንድ እርምጃ መጓዝ አይችልምና።

 ልማታዊ ጋዜጠኝነት ውጤታማ እንዲሆንና የታሰበለትን ግብ እንዲመታ በጣም ከሚያስፈልጉት ነገሮች ውስጥ ዋነኞቹ የሚከተሉት ሊሆኑ ይችላሉ። አንደኛ ግልፀኝነትንና ተጠያቂነትን ያሰፈነ ወይም ለማስፈን ከልቡ ጥረት የሚያደርግና ሚዲያን በዚህ ጉዳይ እንደ ጠቃሚ የማህበረሰብ ተቋም የሚያይ መንግስት፤ ሁለተኛ ትክክለኛ፣ የተሟላ፣ ወቅታዊና ተአማኒነት ያለው መረጃ ለማህበረሰቡ በነጻነት የሚያደርስ ጋዜጠኛ፤ ሶስተኛ ከትርፍ በፊት የህብረተሰቡን ጥቅም የሚያስቀድም የሚዲያ ተቋም፤ እና የመጨረሻው መብቱን የተረዳና ለሁለንተናዊ እድገቱ በቁርጠኝነት የተነሳ ህዝብ መኖር ናቸው። እርግጥ ነው እነዚህን የተቀደሱ መስፈርቶች ለሟሟላት ሊከብድ ይችላል። ቢሆንም ግን ወደዚህ የሚያስጠጋ ስራ ካልተሰራ የሚናፈቀውን ትክክለኛ ጋዜጠኝነት እውን ማድረግ ያዳግታል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top