ቀዳሚ ቃል

የሀገር ባለውለታ ያልናቸውን ረስተናቸው ይሆን?

የሀገር ባለውለታ ያልናቸውን፣ እንደዘመናቸው፣ እንደችሎታቸው፣ ሠርተው ያለፉትን፣ ያላቸውን ያካፈሉንን በምርምራቸው ውጤት ከያኒውን ያነቃቁ፣ በጽሑፎቻቸው በተደራሲያን የተከበሩ፣ ላበረከቱት ምልክት ተዘንግቶ፣ ለሚታወሱበት የ”አስታዋሾች” ማኅበር ጠፍቶ፣ ለማውራት ያህል “ነበሩ” በሚል መታለፋቸው ተለምዷል።

  ሙግስናቸውን ፍለጋ ቀርበናቸው፣ ስህተታችንን ሲጠቀሙን ለጊዜው የሸሸናቸው፣ በእነሱ ስራዎች ውስጥ የራሳችንን ሙከራ ያቀረብን፣ በእነሱ ታዋቂነት ውስጥ ስማችንን ለማስተዋወቅ የደከምን፣ ለሠሩት፣ ያለስስት ያላቸውን ዕውቀት ለሠጡት ደጋግመን ስማቸውን አነሳን፤

  ከፃፉት አስፈቅደን እየወሰድን፣ ከተናገሩት እየጠቀስን ተጠቅመን፤ ካዩት ቀዳዳ ለማየት ሞክረን ያደነቅናቸው፣ ያከበርናቸው፣ በሞት ሲለዩን በጊዜ ከተገደበው ሃዘናችን፣ ለማፅናኛ ከሚሆነው ንግግራችን ውጪ መች ያልነውን ሰርተን እናውቃለን?  

ሕይወታቸው ማለፉን የሰማን ሰሞን፣ ከሥራዎቻቸው ጥቂቱን ዘግበን፣ ብዙዎቹን ትተን ግፋ ቢል ዓመታቸውን ዘክረን፣ ከጠነከርን ጨምረን ስለሰሩት ለመመስከር ተሰባስበን ስለራሳችን እያሰብን ረስተናቸዋል። በስማቸው ማኅበር ቢጤ መሥርተን ሳይቆይ አፍርሰነዋል።

  ለጥቂቱ እንደሆነው ሐውልት ከማቆም፣ መንገድ ከመሰየም፣ ስማቸው የምርምር ተቋማት መጠሪያ ከመሆኑም በላይ ያደነቅናቸው ሥራዎቻቸውን እያቀረብን፣ የተማረክንባቸውን ስልታቸውን እየፈተሸን፣ ባላየናቸው፣ ባልደረስንባቸው ላይ መች በቅጡ ተወያይተናል?

 ማኅበር ብጤ መሥርተን፣ ሩቅ ሀገር ባንሔድም በውጭ ሀገሮች እንደሚሆነው በሀገራችንም ተጀምሮ እንደነበረው፣ (የደራሲው የትውልድ ቦታ በፈጠራ ሥራዎቻቸው ውስጥ ስለአሉት ሥፍራዎች፣ የባለታሪኮቹ መዋያዎች …) ድረስ ባንዞርም ከያለንበት ተጠራርተን ባለን ጊዜ ተነጋግረን፣ እነዚህ የሀገር ባለውለታ የምንላቸውን ሌሎች ሲጠይቁን ችላ ያልናቸውን ልናስታውሳቸው፤

 ባለን ስፍራ ተገናኝተን፣ ሳናቋርጥ ስለእነሱ አውርተን፣ ስለሠሩት አንስተን፣ ያበረከቱትን ማስተዋወቅ ይኖርብናል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top