ቀዳሚ ቃል

ኪነ-ጥበብ እና መንግሥት

ኪነ-ጥበብ ከጅምሩም ቢሆን ተንጋድዶ እንዳያድግ የጣሩ፤ ያለ ቦታው ተገኝቶ፣ ያለ ስሙ ተጠርቶ እንዳይቀር የደከሙ፤ ከሰዎች ጋር የመወዳጀት፣ ሰዎችን የመቅረፅ ብርታቱን ያጤኑ፣ ለሀገር ዕድገት፣ ለሀገር ለውጥ ያለውን ጠቀሜታ የጠቆሙ፣ እንደዋዛ እየፈዘዘ፣ እንደነገሩ እየደበዘዘ መሄዱን ታዝበው ድምፃቸውን ያሰሙ፣ የድክመቱን ቦታ ያሳዩ ባለሙያዎች ቢኖሩም፣ እንደታሰበው የሀገራችን የኪነ-ጥበብ ዕድገት ከፍ ከማለቱ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

ባለሙያዎቹ ማህበር አቋቁመው ስለ ስራቸው ተወያይተው እንደ አቅማቸው እንደ ተሰጥ ኦዋቸው ዘርፉን ለማሳደግ ጥረዋል፡፡

መንግሥት የፈጠራ ሥራዎች የሀገርን ባህላዊ ፣ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ፣ ሳይነሳዊ እና ቴክኖሎጂያዊ ልማትን ለማሳደግ ድርሻቸው ከፍ ያለ ነው ብሎ፤ ኪነ-ጥበብ እና ተመሳሳይ የፈጠራ ሥራዎች ውጤታማ የሚሆኑት ዕውቅና ሲሰጣቸው፣ ጥበቃ ሲቆምላቸው እንደሆነ ጠቅሶ አዋጅ አውጥቷል፡፡ በተለያዩ ጊዜያትም ከተወሰኑት የማህበሩ አባሎች ጋር ተወያይቷል፡፡

ይሁን እንጂ፤ ከያኒያኑ የጠየቋቸው ሳይመለሱ፣ የጠበቋቸው ሳይፈፀሙ ቆይተዋል፡፡ መገልገያ መሳሪያዎችን ከውጭ ሀገር ለማስመጣት የሚጠየቁት ታክስ ያልጠበቁት በመሆኑ የራቁ፣ ደክመው የፈጠሯቸው ሥራዎቻቸውን በህገ-ወጥ መንገድ የሚነጠቁ፣ ችግሮቻቸውን የሚፈቱበትን ማህበር ለማቋቋም በህጋዊ መንገድ ሲጥሩ የተከለከሉ፣ የተፃፉትን ህጎች በአግባቡ የሚፈፅሙ፣ የተበዳዮችን ድምፅ የሚሰሙ ኃላፊዎች አንሰው በማየታቸው ተስፋ እንደቆረጡ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

በተደጋጋሚ እንደሚታየው መንግሥት በተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች ላይ ለሚገኙ ባለሙያዎች ጥሪ የሚያቀርበው፣ ሰብስቦ የሚያነጋግራቸው፣ “የሀገር ጉዳይ ብሎ” ትዕዛዝ የሚያስተላልፈው ድንበር መደፈሩን፣ ለአባይ “አለመዘመሩን” ሊያስታውሳቸው ሲፈልግ ይመስላል፡፡

መወያየቱ፣ ችግሮቹን ለመቅረፍ መነጋገሩ፣ ሌሎች የሙያ ዘርፎችን ለማጠናከር እንደሚታሰበው ሁሉ ለኪነ-ጥበቡም ትኩረት የመስጠቱ አስፈላጊነት አጠያያቂ አይሆንም፡፡

መንግሥት በለውጥ ሂደት ላይ መሆኑን በሚናገርበት ዛሬም፣ ስለ ኪነጥበብ በማሰብ ዘርፉን ለመጠበቅ የወጣው አዋጅ እንዲፈፀም፣ የሙያው ባለቤቶች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች በአግባቡ እንዲመለሱ በመነጋገር አዲስ መንገድ ያሳያል የሚል ተስፋ አለን፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top