ስርሆተ ገፅ

“ከአዘጋጆቼ ልምድ አግኝቻለሁ” ኤልሳቤት መላኩ የቴያትርና ፊልም ተዋናይት እና አዘጋጅ

ልጅነት

 አስታውሳለሁ ትንንሽ ልጆች ሆነን፤ አንድ የአክስቴ ባል ቤታችን እየመጣ እኔን፣ ወንድሜን እና እህቴን ትወና የሚመስል ነገር ያለማምደናል። ቤተሰቦቻችን ሲመጡ እነሱ ፊት ቀርበን እናሳያለን። ከዚህም ሌላ በቴሌቪዥን የሚተላለፉ ፊልሞችን የልጆች ፕሮግራሞችን እንከታተላለን። ትዝ ይለኛል በዓመቱ መጨረሻ ደብተሮቼ መጨረሻ ላይ የሚቀሩትን ወረቀቶችን በመሰብሰብ “የዓለሚቱ ታሪክ” በሚል ርዕስ የፃፍኳት ታሪክ ነበረችኝ። አሁን የት እንዳለች አላውቅም።

 በቴሌቪዥን ይቀርቡ የነበሩትን እንደ “Star Treck” የመሳሰሉ ፊልሞችን ከእህቴ ጋር እናይ ስለነበር ቀስ በቀስ ስሜቴ ወደዚያው መሳቡ አልቀረም። በዚያ ላይ ከ4ኛ ክፍል ጀምሮ ትምህርቴን የተከታተልኩት በካቶሊክ ትምህርት ቤት ነው። እና በገናና በሌሎችም በዓላት ጊዜ መንፈሳዊ ድራማዎች ይዘጋጃሉ። እኔም መተወን ጀመርኩ። ትንሽ፣ በጣም ቀይ፣ የዋህ ስለምመስል የቅድስት ማሪያምን ገፀ- ባህርይ ተላቭሼ ሰርቻለሁ።

 ከፍ እያልኩ ስመጣ እናቴ በኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ የውይይት ክበብ ሠራተኞች ከነቤተሰቦቻቸው ቴያትር የሚመለከቱበትን መንገድ ስለሚያመቻቹ ይዛን እየሄደች ቴያትሮችን እናይ ነበር። እናታችን ለአርት ልዩ ፍቅር ነበራት። ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤትና ሥነጥበብ ት/ ቤት የሚዘጋጁ ኮንሰርቶችንና ኤግዚቪሺኖችን፣ እንዲሁም የተለያዩ ፊልሞችን አይታ መጥታ በስሜት ስትናገር ስሰማ ሳላስበው ወደዚያ እየተሳብኩ መሄድ ጀመርኩ። አንድ ጊዜ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከገባሁ በኋላ ነው፣ ከጓደኞቼ ጋር በመንገድ ስንሄድ የቴአትር ማስታወቂያ ተለጥፎ ተመለከትን። እንድንገባ ጠየቅኋቸውና ገባን። ቴአትሩን ሳይ ይኼን ነገር ብሠራ እንደሚሳካልኝ ሆኖ ተሰማኝ። ወዲያው ቴያትር መማር አለብኝ ብዬ አሰብኩ።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

በእርግጥ ቴያትር አንደኛ ምርጫዬ አልነበረም። በአጋጣሚ ከጓደኞቼ መካከል ጀማነሽ ሰለሞን ቴያትር አንደኛ ምርጫዋ ሆኖ ሳለ በሌላ የትምህርት ዓይነት ተመድባ ነበር። ከዚያ ወደ ቴያትር የትምህርት ክፍል ሄዳ አመለከተች። ከዚያ በፊት ከአንዱ ዲፓርትመንት ወደሌላው ዝውውር አይቻልም ነበር። ጋሽ ደበበን ካነጋገረች በኋላ ዲፓርትመንቱ የሴት ተማሪዎች እጥረት ስለነበረበት የሚቻለውን እናደርጋለን የሚል ተስፋ ይዛ መጣች። ያንም ለእኔ ነገረችኝ። እኔም አመለከትኩ። ጌታቸው ታረቀኝም እንዲሁ አመልክቶ ነበር። በመጨረሻ ሶስታችንም ተሳካልንና ወደ ቴያትር ክፍሉ ተዛውረን ለመማር በቃን።

 ቴያትር መማር ስጀምር ፈተናዎች ነበሩብኝ። የመጀመሪያ ደረጃ ት/ ቤት ስንማር ክፍል ውስጥ ጫጫታ እንዳይኖር ተብሎ አቀማመጣችን ሁለት ሴቶች መሃል አንድ ወንድ፣ እና ሁለት ሴቶች መሃል አንድ ወንድ ነበር። ከወንዶች ጋር አናወራም። የ2ኛ ደረጃ ትምህርቴን ደግሞ የተከታተልኩት ቅድስት ማሪያም ነው። እዚያ ሴቶች ብቻ ነበርን። ይህ በቲያትር ሥራ ላይ ፈታኝ ሆኖብኝ ነበር። ከወንዶች ጋር ማውራትና መነካካት ስለነበር አፍራለሁ። ሆኖም መምህሮቼ የተለያዩ ጨዋታዎችን በማሳየት እንድለማመድ ረድተውኛል። ሌላው ችግሬ ጽሑፍ መሸምደድ አለመቻሌ ነበር። ይህንም እንዳሻሽል ጀማነሽና የሻሸወርቅ በየነ በጣም አግዘውኛል።

“ሆድ ይፍጀው” እና ሌሎች ቴያትሮች

ቴያትር ዲፓርትመንት ስንገባ ከ4ኛ ዓመት ተማሪዎች ውስጥ ሴቶች አልነበሩም። “ሆድ ይፍጀው” የተሰኘውን የፍስሃ በላይ ቴያትር ሊሠሩ ፈለጉና እኔና ጀማነሽ አብረናቸው እንድንሰራ ጠየቁን፤ ተስማማን።

ታሪኩ አንዲት ተገድዳ ባገባች የገጠር ልጅ፤ ባሏ በሆነው እና እሷ በምትወደው ሌላ ሰው ህይወት ዙሪያ የሚሽከረከር ነው። እኔ የልጅቷን ጓደኛ ጀማነሽ ደግሞ ልጅቷን ራሷን ወክለን ተጫወትን።

በእርግጥ አንዳንዶች አዲስ አበባ ተወልጄ እንደማደጌ የልጅቷ ገፀ-ባህርይ የሚከብደኝ መስሏቸው ነበር። በነገራችን ላይ እናቴ የመጣችው ከደሴ ነው። ቤት ውስጥ አክስቴ እና የአጎቴ ሚስት በዚያ አከባቢ ዘዬ ሲናገሩ እሰማቸው ነበር። በተጨማሪም ደራሲው ፍስሃ በላይ ይማም ወሎዬ ከመሆኑ በተጨማሪ የአንድ ሰፈር ሰዎችም ነበሩ። ቴአትሩ በብዙ ተመልካቾች ተወዷል። የመጀመሪያዬ እንደመሆኑ መጠን ብዙ ተምሬበታለሁ።

 ከዚያ በኋላ በተለያዩ የአፍሪካና አውሮፓ ሀገሮች የተተረጎሙ ቴያትሮችንም ሠርተናል። ለምሳሌ “ጥቁሩ መናኝ” የተሰኘውን ቴአትር ከ4ኛ ዓመት ተማሪዎች ጋር ተውነናል። “የኪዩፒድ ቀስት” የተሰኘውን ተውኔት ደግሞ ከ3ኛ ዓመት ተማሪዎች ጋር ሆነን ሰርተናል። ትዝ ይለኛል ቴአትሩ ረዥም ስለነበር ማንያዘዋል እንዳሻው፣ ከጀርመን ሀገር ትምህርቱን ጨርሶ ገና መመለሱ ነበር፣ እንዲያስተካክለው ተመረጠ። ኋላም “አማጭ” የተሰኘውን የመመረቂያ ቴያትራችንን አዘጋጅቶልናል።ከተመረቅን በኋላም አብረን እንድንሰራ ጠየቅን። የባህል ማዕከል አባልም አደረገን።

 በጀርመን የተማረውን በተለይ የ”ወለፈንድ” ተፅዕኖ የሚታይባቸውን ቴያትሮች አሠራን። ተመልካቹን ወደ አዲስ የቴያትር ዓይነት ለማምጣትና ለማለማመድ እንሠራ ነበር። በትርጉሙ በኩል ማንያዘዋል እንደሻው፣ አዳም ረታና ተፈሪ ዓለሙን አስታውሳለሁ።

በተለይ ማንያዘዋል ከተለመደው የቴአትር አሠራር ወጣ እንድንል አድርጎናል። “እንግዳ” የተሰኘ ቴያትር ጽፎ እሱ፣ እኔና ተፈሪ ዓለሙ ተውነንበት ለመድረክ አብቅተነዋል።

 “ያላቻ ጋብቻ”

 “ያላቻ ጋብቻ” ቴአትርን ለመሥራት የተነሳነው ለአብዬ መንግሥቱ ብለን ነው። በወቅቱ እሳቸው በጠና ታመው ሆስፒታል ነበሩ። ለማሳከሚያ ገንዘብ ለማሰባሰብና ለማስታወሻ እንዲሆን ከጻፏቸው ተውኔቶች ውስጥ ለምን አንዱን አንሰራም የሚል ሀሳብ ተነስቶ ነበር። አስተባባሪ የነበሩት ጓደኞቻችን ሔዱና አብዬ መንግስቱን ጠየቋቸው። አቶ አባተ መኩሪያ ጋ አንድ ሥራ እንዳላቸው ገለጹላቸው። ከዚያ ለጋሽ አባተ ነገርነው፤ በቴያትርና ባህል አዳራሽ ተዋንያን እንደሚሠራው አሳወቀን። የአብዬ መንግሥቱ ልጆች መሆናችንን ተናግረን ጋሽ አባተን ለመነው፣ ተስማማ። የተወሰነ ፈተና (ኦዲሽን) ከሰጠን በኋላ ሥራው ተጀመረ።

የአልጋነሽ ዱብ ዕዳ ገፀ-ባህርይ ተሰጠኝ። ወይዘሮ አልጋነሽ በዕድሜ የገፉ፣ ግዙፍ፣ በልጃቸው ማንኛውም ጉዳይ ላይ የሚወስኑ የፊውዳል ሴት፣ አምባገነን፣ የአካባቢውን ሰዎች የሚያሽቆጠቁጡ ናቸው። በዕድሜ እንራራቃለን። እንደ እሳቸው ዓይነት ሴት ደግሞ አይቼ አላውቅም። መረጃም አልነበረኝም። ጋሽ አባተ መኩሪያ እኔን ወደ ሴትየዋ ለማምጣት በጣም ደክሟል። ያኔ ገና ተመራቂ ነበርኩ። ለማመሳሰል አንድ ጣቃ ተሸንሽኖ እንደ ቀሚስ እለብሳለሁ። ትልልቅ ጡቶች በጨርቅ ተሰርተውልኛል። ሌሎች ነገሮችም ተጨምረው ገፀባህሪዋን ተጫወትኳቸው። በርካታ ሰዎች ወይዘሮ አልጋነሽን እንዳመጣኋት ነግረውኛል። እኔ ግን እስከመጨረሻው በስጋት ነበር የተጫወትኩት።

 ፊልሞች

 ዩኒቨርሲቲ እያለን የኢትዮጵያ ፊልም ማእከል ተቋቁሞ ነበር። አንድ ፊልም ለመሥራት ተዋናይ ፍለጋ ወደ እኛ መጡ። ፍላጎት ነበረኝ። “በህይወት ዙሪያ” የተሰኘው ፊልም (ድርሰቱ የከያኒ ተክሌ ደስታ ነው) ላይ ተወንኩ። ለተመልካች ደረሰ። ሁለተኛው “አስቴር” የተባለው ነበር። አቶ ሰለሞን በቀለ ወያ ነበር የመረጠን። ጥሩ እንደነበር

“በቅርቡ ከሰራኋቸው ቴያትሮች መካከል በጣም የወደድኩት “ከሠላምታ ጋር” የተሰኘውን ነው። አንዲት ሴት ለ30 ደቂቃዎች ያህል ብቻዋን ታወራለች። ለየት ያለችው ይህቺ ገፀ- ባህርይ ሶሥቴ አግብታ ትፈታለች”

 አስታውሳለሁ። ከዚህ በኋላ የቪድዮ ፊልሞች ተጀመሩ። መሥራት አልፈለግሁም። እናም በዘመነ ቪድዮ ሳልሰራ ቆይቼ ኋላ ላይ ልቤ ሲነሳሳ፤ የዲጂታል ጊዜ ሆነ።

አብርሃም ገዛኸኝ የተባለ ባለሙያ “ሎሚ ሽታ” የተሰኘ ፊልም ላይ እንድተውን ጠየቀኝ። ተስማማሁ። የፊልም ጽሑፉን ወደድኩት። ጥሩ ክፍያ ባይኖረውም ጥሩ ጊዜ አሳልፈናል። ተሸልሜበታለሁ። ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ በኋላ “አብስትራክት” በተሰኘ ፊልም ላይ ሰርቻለሁ። ያስቸግራል። ገፀ-ባህርይዋ ፊትዋ ላይ ጠበሳ አለባት፤ እሱን ለማምጣት በየቀኑ ፊቴ ሜክ አፕ እየተሰራ ሲላጥ ይከብድ ነበር። በዚያ ላይ ነገሩ ሲደጋገም በፊቴ ቆዳ ላይ ችግር ያስከትል ይሆን እያልኩ ስጨነቅ ቆይቻለሁ። ተቀርፆ ሲያልቅ ግን ጥሩ ሆነ።

 በተጨማሪም “የትኖራ” በተሰኘ ፊልም ላይም ሰርቻለሁ። አሁን ደግሞ “ትርታ” በተባለው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ እተውናለሁ። ቡድኑ ያስደስታል። ከእነሱ ጋር በመስራቴ እድለኛ ነኝ እላለሁ። ከተመልካቹም ጥሩ ጥሩ አስተያየቶች ይደርሱኛል።

የቴአትር ዝግጅት

ዝግጅት የጀመርኩት ትምህርት ላይ እያለሁ ነው። የዝግጅት ትምህርት ሲሰጠን ተመዳድበን እንሰራለን። ከተመረቅኩ በኋላም መንፈሳዊ ይዘት ያላቸውን ቴአትሮች በአብያተ ክርስቲያናት አዘጋጅቻለሁ። በእርግጥ እራሴ የፃፍኩትን ነበር የማዘጋጀው። የሚሠራው በምልክት ቋንቋ በመሆኑ ብዙ እንቅስቃሴ ያለበት ነበር።

በዝግጅት ወቅት ቴያትሩን መተንተን፣ በሚገባ መረዳት፣ ከተዋንያን ጋር መግባባት ያስፈልጋል። በተጨማሪም እንቅስቃሴን መተርጎም፣ አልባሳት፣ መብራት እና ሌሎችም የሚያርፉት አዘጋጁ ላይ ነው። ተዋናይት ሆኜ ከአዘጋጆቼ ልምድ አግኝቻለሁ። ማንያዘዋል እንደሻው፣ አቶ ተስፋዬ ገሠሠ፣ ተ/ፕሮፌሰር አቦነህ አሻግሬ፣ ሜሪ አዶሲደስ፣ ክሊፎርድ ኮከር እና ሌሎች አዘጋጆቼም ነበሩ።

 በቲያትር ቤት ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀሁት የመሠረት አታላይ ድርሰት የነበረውን “መንታ መርፌ”ን ነው። ጥሩ ነበር። ከስምንት ዓመታት በኋላ ደግሞ “የታፈነ ጩኸት” የተሰኘው የውድነህ ክፍሌ ድርሰት የተውኔት ግምገማውን አለፈ። በወቅቱ የቴያትር ቤቱ የተውኔት ገምጋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነበርኩ። ጥሩ ጽሑፍ መሆኑን ስላወቅን እንዲሠራ መረጥነው። አዘጋጅ ተመድቦለት እንዲሠራ ሲወሰንም በአጋጣሚ የቴያትር ቤቱ ማኔጅመንትም፣ የቴያትር ክፍልም፣ የተውኔት ገምጋሚ ኮሚቴም ሁሉም እኔን መረጡኝ። በጥሩ መንገድ ተጠናቀቀ። ተመልካቾችም ወደዱት። በዚያው ዓመት በተደረገ ውድድር በጽሑፍ፣ በዝግጅት እና በትወና አሸናፊ ለመሆንም ችሏል። ይሁን እንጂ እንደታሰበው ለረጅም ጊዜ በመድረክ አልቆየም።

 “ከሠላምታ ጋር” እና “ባዶ እግር”

 በቅርቡ ከሰራኋቸው ቴያትሮች መካከል በጣም የወደድኩት “ከሠላምታ ጋር” የተሰኘውን ነው። አንዲት ሴት ለ30 ደቂቃዎች ያህል ብቻዋን ታወራለች። ለየት ያለችው ይህቺ ገፀ-ባህርይ ሶሥቴ አግብታ ትፈታለች። የምታወራው ከባሎቿ ጋር ስላሳለፈቻቸው ጥሩና መጥፎ ጊዜያት ነበር። ደራሲና አዘጋጇ መዓዛ ወርቁ ናት። ግሩም ሥራ ነው። እንደማስታውሰው በሳምንት ሁለት ጊዜ በልዩ ልዩ መድረኮች (በዓለም ሲኒማ፣ በጣይቱና በግዮን ሆቴሎች) እንሠራው ነበር።

ከዚያ በኋላ በሶቅራጥስ ህይወትና ፍልስፍና ላይ በሚያጠነጥነው “ባዶ እግር” የተሰኘ ቴያትር ላይ (በብሔራዊ ቴያትር) ሰርቻለሁ። አዘጋጇ ራሔል ተሾመ ነች። በቴያትሩ የሶቅራጥስ ሚስት ሆና እሱን የምታበረታታውን ገፀ- ባህርይ ነው የተጫወትኩት። ለተወሰኑ ጊዜያት ሰርቼ በራሴ ምክንያት አቋርጫለሁ። ቴያትሩ አሁንም አለ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top