ጣዕሞት

አጭር ቆይታ ከሰአሊ በቀለ መኮንን (ተ/ፕሮፌሰር)ጋር

ምን ተሠርቷል?

 የሚሞክሩ ጋዜጠኞች አሉ። ትንሽ አቅም ያላቸው እና ፍላጎታቸው አስገድዷቸው የሚሠሩ፤ ከእዚያ ውጪ አቅም ስለሚጠይቅ የተዘጋጀ ተመልካች ባለ መኖሩ፣ አዘጋጅቶ ማቅረቡ የብዙ መገናኛ ብዙሀን ፍላጎት አይደለም። በእርግጥ ለዜና ሽፋን ያህል ወይም እንግዳ ሲኖር ይቀርባል። ይህንን ለማሻሻል መሠራት ይኖርበታል።

 አስተማሪነቱ የት ድረስ ነው?

  የስነ-ጥበብን አስፈላጊነት በሁለት መልኩ ልናየው እንችላለን። የመጀመሪያው አዝናኝነቱ ነው። ልክ እንደሌሎች ሜዳ ላይ የሚሆነውን አይተን መድረክ ላይ የሚዘጋጀውን ተመልክተን እንደምንዝናናው ሁሉ፤ ግድግዳ ላይ፣ ቤት፣ አዳራሽ፣ ሙዚየም ውስጥ ሰቅለን እየተመላለስን በማየት የምንደሰትበት ይሆናል።  ሁለተኛው እውቀት መሆኑን ነው። ልክ እንደሌሎቹ ማለትም እንደ ሒሳብ፣ እንደ ፊዚክስ፣ እንደ ጀኦግራፊ እና እንደ መሳሰሉት የምንማረው ዕውቀት ያለበት ዲስፒሊን (ትምህርት) ነው።

 በመዝናናት የምናገኘው የደስታ ትርፍ ትልቅ እና ተፈላጊ ቢሆንም ቀድመን ልኩንና መጠኑን የምናውቀው እዚያው ተጠቅመን ረስተንና ጥለን የምንሄደው ነው። ዕውቀት ወይም መዝናናት የተለበጠው ቁምነገር ወይም ይዘት ደግሞ እየተዝናናን በማወቅ እና በመረዳት ቀድመን ያልጠበቅነውን አዲስ ነገር የምናገኝበት አዲሱንም ነገር ለመጠየቅም ለመፈተን ለማሰብም የምንገደድበት ተጨማሪ ስሌት ያለው ክፍል ነው። ይሁን እንጂ ዜጎችን ሰዓሊ ወይም ቀራፂ ለማድረግ አይደለም። የሥነ-ጥበብ ትምህርት፤ ሌሎች እውቀቶችን በቀላሉ እና ውጤታማ በሆነ መልኩ በሰው ልጅ አእምሮ ማስረፅ ይቻላል።

  ሁለተኛው እራሱ እውቀት ሆኖ የሰውን ልጅ የቆየ አውሬነቱን፣ ፈርደ ገምድልነቱን፣ ፍትህ አልባነቱን፣ አለመግባባቱን፣ ተቻችሎ መኖር አለመቻሉን፣ ስሜታዊነቱንና የመሳሰሉትን፣ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ አብረውት እንዳያድጉ፣ አመዛዛኝ እንዲሆን፣ በተለይ ስሜት አስፈላጊ ቢሆንም መቼ እና የት መጠቀም እንዳለበት በመረዳት ከስሜታዊነት እንዲፀዳ ፍርድ አዋቂ አመዛዛኝ እንዲሆን ይረዳል። በዚህ መልኩ እንደ ስነ-ጥበብ ሊያስተምር የሚችል ዲሲፕሊን የለም። ይህንን እኔ አይደለሁም ያልኩት፤ አለም አቀፉ የሥነ-ጥበብ ምሁራን ማኅበር ባሳተማቸው መጽሐፎች ውስጥ በዝርዝር ተቀምጧል። ይህን ለመጠቀም እኛ ፈጥነን መሣፈር አለብን። ሰው ማፍራት ሐሳቡን ማሰራጨት ይኖርብናል።

 ዝግጅቱ ምን ይምሰል?

የሐሳብ ዓቅም፣ የገንዘብ እና የባለሙያ አቅም ያስፈልጋል። በተለይ የመንግሥት ሚድያ ላይ መሠራት አለበት። ይህ የሚሆነው ጋዜጠኞቹ በተጨማሪ ስለ ስነ-ጥበብ በቂ ትምህርት እና እውቀት እንዲኖራቸው ይገባል። ይህንን በተመለከተ የጎረቤት ሱዳንን ልምድ አስታውሳለሁ።

 ሀገር ማግኝት የሚገባትን፣ወገኖች መጠቀም ያለባቸውን ለምን ያጣሉ በሚል ተቆጭተው የተወሰኑ የጋዜጠኝነት ኮርሶችን በመውሰድ በሚድያ የሠሩ የሥነ-ጥበብ ባለሙያዎችን ተመልክቻለሁ። ይህ የቅርብ እሳት የማጥፋት ቴክኒክ ነው።

 በሀገራችን እንደሌሎቹ ትልልቅ ጉዳዮች መታየት ይኖርበታል። የሚጠላው ኃላፊ ሲኖር እንዳይቀር ወይም የሚወድደው ሲመጣ እንዳይሟሟቅ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። የመንግሥት ሚዲያ ከባለሙያዎች ጋር ገንዘብ በመመደብ የተወሰኑ ሰዎችን ቢያሰለጥኑ በርካታ ደጋፊዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ጥሩ ዝግጅት ካለ በርካታ ተመልካቾች ይኖራሉ። ዕውቀት ማትረፍ ሲጀምር ሰው እራሱ ጠያቂ ይሆናል።

 በአንድ የሥነ-ጥበብ ሥራ ውስጥ፤ ስንት ዓይነት ዕውቀት እንዳለ ይህ ዕውቀት ለሌሎች ዕውቀቶች ስለአለው አስተዋፅኦ በሚገባ መነጋገር፣ መከራከር፣ ማብራራት በተጨማሪም የስነ-ጥበብ ሰዎችን የህይወት ታሪክ ማቅረብ ይስፈልጋል። ጅማሬው አጠር ባለ መልኩ መሆን አለበት። ፍላጎት ሲጨምር ዝግጅቱ እየሰፋ መሄዱ አይቀርም። በእርግጥ አዲስ ዓይነት ባህል ለመፍጠር መሞከር ነው። ሰው ጥማቱ ምንድነው? ምን ይፈልጋል? ምን ዓይነት ዕውቀትስ እንዲጠማው ማድረግ ይቻላል? በሚማርክ ውብ እና ጠንካራ ዝግጅት ጥያቄዎቹን በመመለስ የተሻለ ፕሮግራም መሥራት ይቻላል። ተመልካቹ ከነባር አሰልቺ ዝግጅት አዲስ ነገር ለማየት ወደኋላ የሚል አይደለም።

በምን መልኩ ማየት ይቻላል?

 ሥነ-ጥበብን ዓለም ለሥልጣኔ የሚገላገለው እንዴት ነው? በሚገባ ሊታይ እና ሊወደድ በሚችል መልኩ ተፈታትቶ መታየት አለበት። ለምሳሌ ለምንድነው አረንጓዴ የተቀባ መደብ ላይ፤ በቀይ ቀለም የተቀባ ማስታወቂያ የማይነበበው? ለምንድነው ቀይ ቀለም አረንጓዴ መደብ ላይ የሚዘለው ዓይናችንን መረበሽ እስከሚችል ድረስ ማየት የማንችለው የትኞቹ ቀለማት ከየትኞቹ ቀለማት ጋር ነው በምጣኔ የሚቀመጡት? የቀለማት መቻቻል በህይወት ውስጥ ምሳሌነቱ ምንድነው? በተፈጥሮ ውስጥ ስምምነት እና ጥል ካለ፤ ስምምነት ምንድነው? ጥልስ ምንድነው? እንዴት ማስታረቅ ይቻላል?

  የፖለቲካ ሰዎች እና ተራ ዜጎች፤ ስለ አንድነት እና ልዩ ልዩነት፣ ስለ መመሳሰል እና መለያየት በማይጨበጥ ቲዮሪ ወይም በሰበካ ቋንቋ ብቻ ሲነታረኩ እና ላይተማመኑ ሲለያዩ እናያለን።  

ይህን ክርክር በቀላሉ እና በመተማመን ለመረዳት መሠረታዊ የሥነ-ጥበብ ትምህርት በመቅሰም ብቻ ሰርቶ፣ ሞክሮ በተግባር መነጋገር ይቻል ነበር።

  ልዩ ልዩነቶች በሥዕል ውስጥ፣ አንድ አካል ሆኖ እንዲቀመጥ የሚያስተሳስረው

“ልዩነት እና መመሳሰል ሁለቱም በየራሳቸው ለየብቻቸው ስዕል አይሆኑም። አንዱም ይሰለቻል። አንደኛውም ይበተናል። ስለዚህ ሁለቱም ተመጣጥነው ከልዩነትም ከመመሳሰልም ከተሳፈሩ በኋላ የማዋኃጃ እና ማስማሚያ የሃርመናይዜሽን ጥበብ ሥራ ላይ ማዋል ነው። ያኔ አንድ ሙሉ ራሱን የቻለ ሥዕል ይፈጠራል። ”

አንድ ነገር አለ። ልዩ ልዩ ነገሮች በምን ሃርመኒ ተስማምተው አንድ እንደሚሆኑ ተማሪው ሰርቶ ያምነዋል። የሚያያይዘው ነገር ከሌለ ሥዕልም ስለማይሆን ተቀድዶ ይጣላል። መምህሩም ውጤት አይሰጥም። ስለዚህ ልዩነት እና መመሳሰል ሁለቱም በየራሳቸው ለየብቻቸው ስዕል አይሆኑም። አንዱም ይሰለቻል። አንደኛውም ይበተናል። ስለዚህ ሁለቱም ተመጣጥነው ከልዩነትም ከመመሳሰልም ከተሳፈሩ በኋላ የማዋኃጃ እና ማስማሚያ የሃርመናይዜሽን ጥበብ ሥራ ላይ ማዋል ነው። ያኔ አንድ ሙሉ ራሱን የቻለ ሥዕል ይፈጠራል።

  አንድነት እና ልዩ ልዩነት በፖለቲካ ውስጥ ከመምጣቱ በፊት በሥነ-ጥበብ ውስጥ ተፈትኖ ተፈጥሮአዊ መልስ አግኝቷል። እናም ልኩን ሰው ነግሮን ሳይሆን የሰራነውን ቀዳደን ወይም አክብረነው ልናውቀው እንችላለን። ስለዚህ ሰዎች በእዚህ መስመር ሰዓሊ ለመሆን ሳይሆን ይህንን ፅንሰ ሃሳብ አመክንዮአዊ በሆነ መንገድ ለመማር እና ለማወቅ ይህን በሚገባ ተንትኖ ማስረዳት የእኛ ፈንታ ይሆናል።

የ”ጉማ” መስመር

ሚሸል ፓፓታኪስ ተወልደው ያደጉት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። በፊልም ሙያ ከታወቀው የሩሲያ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀዋል። ከ12 ዓመት በኋላ “ጉማ” የተሰኘውን ፊልም ለሀገራችን ተመልካች አቅርበዋል። በ1966 ዓ.ም. በታተመው “መነን” መፅሔት ላይ፣

 “ኢትዮጵያ ባህሏ፣ ታሪኳ የህብረተ-ሰብ አቋሟና የጅኦግራፊ አቀማመጧ ለፊልም ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ እምነት ስላደረብኝ ከአምስት መቶ ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ የፊልሙ ሥራ አልቋል” ይላሉ።

 ይህ ከሆነ ከአርባ ዓመት በኋላ ጉማ በመታሰቢያነት የሽልማት ስያሜ ሆኗል። የተሻለ ሥራ ለሠሩ በየዓመቱ ሽልማት ይሰጣል።

  የ”ጉማ” ፊልም ሽልማት መስራች እና ባለቤት ዮናስ ብርሃነ መዋ መጀመሪያ “የኢትዮጵያ ፊልም ውድድር ሽልማት የሚል ስያሜ እንደነበረው እና ጅማሬው የሚያበረታታ በመሆኑ “ጉማ ፊልም ሽልማት” በሚል መለወጡን ይናገራሉ።

 ከአርባ ዓመት በላይ በሙያው ለሠሩ እውቅና ይሰጣል። በየዓመቱ በትወና፣ በኤዲቲንግ፣ በዳይሬክቲንግ፣ በሲኒማቶግራፊና በሌሎችም ዘርፎች ሽልማት ይሰጣል። ለዚህም የተመረጡ ባለሙያዎች አሉ። ይመለከታሉ። ይመርጣሉ። አወዳድረው ይሸልማሉ።

  “የፊልም ኢንዱስትሪው ተዳክሟል የሚሉ አሉ። ይህ ትክክል አይደለም። ለፕሮዳክሽን የሚወጣው ገንዘብ ጨምሯል። ለሙያተኞች ክፍያው ከፍ ብሏል። ጠንካራ የፊልም ኢንዱስትሪ በመኖሩ፣ ኢንዱስትሪው ያፈራቸው የፕሮዳክሽን ካምፓኒዎች እና ባለቤቶች፣ ተዋንያን፣ አዘጋጆች እና ሌሎችም በቴሌቪዥን ጣቢያዎች ድራማዎች እናያለን። በእርግጥ የፊቸር ፊልሞች ተቀዛቅዘዋል። ያም ቢሆን በየዓመቱ የሚወጡት ፊልሞች እምብዛም አልቀነሡም” ይላሉ አቶ ዮናስ ብርሃነ መዋ።

 ከዚህ ይልቅ በፊት በጋዜጣ፣ በሬድዮና በቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች ላይ ፊልሞች እንደማይተዋወወቁ፤ እንዲሁም የፊልሞች ስርጭት ክልሎች ድረስ ከ109 እስከ 110 ከተሞች፣ ከመቶ እስከ ሁለት ሺህ ሰዎችን በሚይዙ አዳራሾች ይታዩ እንደነበረና ዛሬ ይህ አለመኖሩን ይናገራሉ።

 “ጉማ” ፊልም ሽልማት በየዓመቱ የሚታጩ ዘርፎችን ይጨምራል። ለፊልም ሥራው ትልቅ ድርሻ ያላቸውን በዕጩነት ያቀርባቸዋል።  

“የፊልም ሥራ በጋራ መሥራትን ይጠይቃል። ፕሮዲውሰሮች የለፉበትን ገንዘብ ነው ወደ ሲኒማው የሚያመጡት። አንድ ሰው ከሰባት መቶ እስከ አንድ ሚሊዮን ያወጣል። ለዚያውም ታሪካቸው በከተማችን 

“በእርግጥ የፊቸር ፊልሞች ተቀዛቅዘዋል። ያም ቢሆን በየዓመቱ የሚወጡት ፊልሞች እምብዛም አልቀነሡም” አቶ ዮናስ ብርሃነ መዋ”

ለሚያጠነጥኑ ፊልሞች፣ አምስት ስድስት ሰዎች ተባብረው አራት አምስት ሚሊዮን ብር ቢያወጡ፣ ድንቅ ፊልም ሊሠራ ይቻላል። በጋራ የመሥራትን ባህል ማዳበር ይገባናል” ይላሉ አቶ ዮናስ።  “ጉማ” የፊልም ሽልማት ዘንድሮም የተለያዩ ባለሙያዎችን የሸለመ ሲሆን ከተቋቋመ አምስት ዓመት ሞልቶታል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top