ግለ ታሪክ

በሩሲያ የተማሩ ቀደምት የኢትዮጵያ ዘመናዊ ምሁራን

ስለ ኢትዮጵያና ሩሲያ የባህል ወይም የትምህርት ግንኙነት በሚነሳበት ጊዜ ከአብርሃም ሃኒባል ታሪክ መጀመር የተለመደ ነው። አብርሃም ሃኒባል ወደ ሩሲያው ንጉሥ ቀዳማዊ ጴጥሮስ ቤተ-መንግስት የመጣው ከቱርክ ቢሆንም አሁን ኢትዮጵያዊነቱ በጥናት ተረጋግጧል። የሩሲያ ዘመናዊ ሥነ- ፅሁፍ መስራች እና የፍትህ ተሟጋች የነበረው የአሌክሳንደር ፑሽኪን ቅም አያትም ነው። አብርሃም ወደ ሩሲያ እንደደረሰ ንጉሠ ነገሥቱ ክርስትና ከአነሳው በኋላ በራሱ ቁጥጥር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን እንዲጨርስ አደረገ። ከዚያም ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ፈረንሳይ ላከው። አብርሃም በፈረንሳይ አገር የጦር ትምህርቱን በብቃት በመጨረስ የጦር በተለይ የምሽግ መሀንዲስ ሆኖ ከተመረቀ በኋላ ወደ አገሩ በመመለስ በተለያዩ ወታደራዊ መሰኮች አገልግሏል። ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ምሽጎችንና ሌሎች ወታደራዊ ተቋማትን ገንብቷል። በማዕረጉም እስከ ሌተናንት ጀኔራልነት ደርሷል። አንድ ከአገሩ ውጭ የሚገኝ አፍሪካዊ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ ብዙዎቹን አስገርሟል። ይህም ሰውየው ከፍተኛ ችሎታ ያለው መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው። ፑሽኪንም ስለዚህ ኢትዮጵያዊ ቅም አያቱ ከፍተኛ አድናቆትና ኩራት ይሰማው እንደነበር በተደጋጋሚ ገልጿል። ባለቅኔው የታላቁ ጴጥሮስ ጥቁር ባለሟል የሚለውን ልብ ወለድ የጻፈው በዚሁ በዝነኛው ቅም አያቱ የሕይወት ልምድ ላይ በመመርኮዝ ነው። ፑሽኪን ይህን ልብ ወለድ ጨርሶት ቢሆን ኖሮ ድንቅ መፅሐፍ ይወጣው ነበር። ይህ ከሆነ ወደ 150 ዓመት ገደማ ከአለፈ በኋላ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሩሲያ አንደገና ብቅ ማለት ይጀምራሉ። ከእነሱ መሀከልም አብዛኞቹ ትምህርት ለመቅሰም የሄዱ ነበሩ። አስተማማኝ መረጃዎች ስለሌሉን የመጀመሪያዎቹ የኢትዮጵያ ተማሪዎች መቼ ወደ ሩሲያ እንደሄዱ ለመናገር አይቻልም። ይሁን እንጂ ወደ አገሩ ከሚመለሰው አሺኖቭ ከተባለው መልክተኛ ጋር ሁለት የኢትዮጵያ ወጣቶች በ1888 እ.ኤ.አ. ወደ ሩሲያ እንደሄዱ ይነገራል። ዳሩ ግን እነኝህን ወጣቶች በሚመለከት ምንም መረጃ አልተገኘም።

 ከእነሱ በኋላ ኃይለማርያም ወንዴ የተባለ የሀረር ኗሪ ከማሽኮቭ የመልክተኛ ቡድን ጋር ለትምህርት ወደ ሩሲያ የሄደ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህም ሰው ለጥቂት ዓመታት በሩሲያ ትምህርቱን ሲከታተል ከቆየ በኋላ ወደ አገሩ ተመልሶ በሩሲያ ሌጋሲዮን ውስጥ አስተርጓሚ ሆኗል። በ1895 እ.ኤ.አ. ወደ ሩሲያ ከሄደው በፊታውራሪ ዳምጠው ከሚመራው የመልክተኛ ቡድን ጋርም ሁለት ወጣቶች ሄደዋል። በሻህ የተባለው እንደ ኃይለማርያም በሩሲያ ሌጋሲዮን ውስጥ ይሠራ እንደ ነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።

 እንደሚታወቀው የአድዋ ጦርነት ከተፈጸመ በኋላ የሩሲያ የቀይ መስቀል ማህበር ለቆሰሉት ወታደሮችና መኮንኖች እርዳታ የሚያደርግ አንድ የህክምና ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ይልካል። ይህ ቡድን በጦርነቱ ላይ ለተጎዱት ሰዎች እርዳታ ከማድረጉም በላይ የተወሰኑ ኢትዮጵያውያንን በተለያዩ የህክምና ሙያዎች አሰልጥኗል። ከዚህም ሌላ ቡድኑ ተልዕኮውን ጨርሶ ወደ አገሩ ሲመለስ በአፄ ምኒልክ ጥያቄ አምስት ወጣቶችን ትምህርት እንዲማሩ ወስዷቸዋል። እነሱም ጌኖ አራዳ፣ ዳኜ ቸርነት፣ ሰሙ ንጉሥ ወልደሚካኤል፣ ግዛው ወልደሚካኤል እና ክብረት ማሩ ናቸው። አፄ ምኒልክ ራሳቸው ወጣቶቹን ይከታተሏቸው ስለነበር፤ ከዚህ ሥራ እንዲማሩ የላኳቸውን አገልጋዮች ሁሉ በየሥፍራቸው አስገብተህ ትምህርት እንዲማሩ ስላደረክልኝ እግዚአብሔር ያመሰግንህ። እንደዚሁም ቶሎ ቶሎ ተግተው እንዲማሩ አድርግልኝ” በማለት ለዶክተር ሮድዜቪች የፃፉት ደብዳቤ ይመሰክራል።

 ወጣቶቹም የአውሮፓ ቋንቋ ስለማይችሉ ትምህርታቸውን ለመከታተል በመጀመሪያ ላይ የተቸገሩ ቢሆንም በአስተማሪዎቻቸው ድጋፍና ጥረት መሠረታዊ የመጀመሪያ ደረጃ ዕውቀት አግኝተው የተላኩበትን ዓላማ ለማሳካት ችለዋል። በዝንባሌያቸውና በችሎታቸው መሠረትም ግዛው ክብረትና ዳኜ ሕክምና፣ ጌኖና ስማ ንጉሥ ተግባረ ዕድ እንዲማሩ ተመደቡ። ከጌኖ በስተቀር ሁሉም ትምህርታቸውን ጨርሰው ተመልሰዋል። ይሁን እንጂ ከዚህም ሌላ የሙዚቃ ትምህርት እንዲማሩ አፄ ምኒልክ ሁለት ልጆችን በ1896 ወደ ሩሲያ ልከዋል። እነሱንም ይዘዋቸው የሄዱት ሥራቸውን ጨርሰው የሚመለሱ የሩሲያ ሙዚቀኞች ነበሩ። ከመረጃዎች እንደምንረዳው እነኝህ ሁለት ልጆች ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ አይመስልም።

 ሩሲያውያን ወደ አገራቸው ሲመለሱ በርካታ ልጆች ይዘው ይሄዱ እንደነበር መዛግብት ይጠቁማሉ። የአፄ ምኒልክ የቅርብ አማካሪ የነበረው ሊኦንትየቭ በየጊዜው ወደ አገሩ ወጣቶችን እየወሰደ ያስተምር እንደነበር የሩሲያ ጋዜጦች ጽፈዋል። ፊታውራሪ ተክለሐዋሪያትም ጥቂት ኢትዮጵያውያን በሩሲያ እንደነበሩና ሁለቱን ብርድ እንደገደላቸው በሕይወት ታሪካቸው ውስጥ ጠቅሰዋል።

“ንግሥት ዘውዲቱ ዙፋን ላይ ከወጡና ተፈሪ መኮንን እንደራሴ ከሆኑ ከኋላ ተክለሐዋርያት በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በኃላፊነት ሠርተዋል። እሱም በመጀመሪያ የጅጅጋ፤ ቆይቶም የጨርጨር አውራጃዎች ገዥ ነበሩ። በሥልጣን ላይ ሲቆዩ አውራጃዎችን በወረዳዎች በመሸንሽን የአስተዳደሩን መዋቀር ለማሻሻል እና የግብር አሰባሰቡን ስርዓት በአዲስ መልክ ለመዘርጋት ከተማዎችን በዘመናዊ መልክ ለመቀየስ ጥረዋል”

 ወደ ሩሲያ ሄደው ከተማሩት ኢትዮጵያውያን መካከል እንደ ተከለሐዋርያት ታሪኩ በደንብ የሚታወቅ የለም ብንል ማጋነን አይሆንም። ይህም የሆነው ሰውየው ትልቅ የሥልጣን ደረጃ በመድረሳቸው እና የሕይወት ታሪካቸውን ጽፈው ለትውልድ በማስተላለፋቸው ነው። ተክለሐዋርያት በዘመኑ እንደነበሩት የኢትዮጵያ ሰዎች ሁሉ የተወለዱበትን ዘመን በትክክል ባያውቁትም የትውልድ ዘመናቸው በ1876 ዓ.ም. አካባቢ ሳይሆን እንደማይቀር ይገመታል። በልጅነታቸው ያደጉት በራስ መኮንን ቤት ነው።

13 ዓመት ሲሆናቸው ራስ መኮንን አፄ ምኒልክን አስፈቅደው ለትምህርት ወደ ሩሲያ ላኳቸው። ይዟቸው የሄደው ሊኦንቲየቭ ነበር። ኦዴሳ እንደደረሱ ወደ ሩሲያ ንጉሥ ተልከው አብረዋቸው የሚጓዙትን አቶ ዮሴፍ ተክለሐዋርያትን ከኮሎኔል ማልቻኖቭ ጋር አስተዋወቁት። ኮሎኔሉም ወደ ቤቱ ወስዶ እንደ ልጁ አሳደገው።

 ተክለሐዋርያት ለሦስት ዓመታት በቤት ውስጥ ሲማሩ ከቆዩ በኋላ በፒተርቡርግ በሚገኝ የካዴት ትምህርት ቤት ገቡ። የሚሰጠውን ትምህርት አጠናቅቀው ከጨረሱ በኋላ በሚሀኤል የመድፈኛ ጦር

ትምህርት ቤት ገብተው ትምህርታቸውን ቀጠሉና መኮንን ሆነው ተመረቁ። ይሁን እንጂ ተክለሐዋርያት ትምህርታቸውን ጦር አካዳሚ ገብተው ለመቀጠል ስለፈለጉ ለሦስት ዓመት ዜግነታቸውን ለመለወጥ እንዲፈቀድላቸው ለአፄ ምኒልክ በሩሲያ ሌጋሲየን በኩል ቢያመለክቱም መልስ ስለአላገኙ ወደ አገራቸው ለመመለስ ተገደዱ።

ተክለሐዋርያት በሩሲያ ከ11 ዓመት በላይ የቆዩ ሲሆን አገሪቷንና ሕዝቦቿን ከልብ ያደንቁ እና ያፈቅሩ እንደነበር ከታሪካቸው እንረዳለን። “የመስኮቦች ባሕሪ ግልፅ ነው። መውደዳቸውን ወይም መጥላታቸውን አይሸሽጉም። እብሪት ሰው መጠየፍ የለባቸውም” ብለዋል። በመጽሐፉ ወሰን አንዱ ምዕራፍ “በሩሲያ አባትና እናት አገኘሁ፤ የትምህርት ጎዳናም ተከፈተለኝ” የሚል ርዕስ ሰጥተውታል። ይህም የሰውየውን ውለታ አክባሪነትና ጨዋነት ያሳያል።

ወደ አገራቸው እንደተመለሱ ከአፄ ምኒልክ ፊት ቀርበው ምን እንደተማሩ አስረዱ። ንጉሡም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ለተክለሐዋርያት የቀኝ አዝማችነትን ማዕረግ ሰጥተው በፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ሥር የመድፈኞች አለቃ አድርገው ሸሟቸው።

ተክለሐዋርያት ሹመቱን ሳይቀበሉ ከንጉሡ ፊት ቀርበው ወደ አውሮፓ ሄደው ትምህርታቸውን መቀጠል እንደሚፈልጉ ገለጹላቸው። ንጉሡም ለስንቅ 3000 ብር በወርቅ እንዲሰጣቸው አዝዘው ወደ አውሮፓ ሄደው እንዲማሩ ፈቀዱላቸው። ለሦስት ዓመታት በአውሮፓ ፈረንሳይኛ፣ እንግሊዝኛና የእርሻ ትምህርት ተምረው ከጨርሱ በኋላ በ1912 እ.ኤ.አ. ወደ አገራቸው ተመለሱ።

 ብዙ ነገሮች ተለዋውጠው ጠበቋቸው። አፄ ምኒልክ ሞተዋል ወይም አንደበታቸው ተይዞ መናገር አቅቷቸዋል፤ እንደራሴው ራስ ተሰማ ስለሞቱ ወጣቱ ኢያሱ እንዳልተገራ በቅሎ ይቧርቃል። በዚህ ጊዜ ተክለሐዋሪያት ሳያስቡትና ሳይወዱ በፓለቲካ ሽኩቻ ውስጥ ይገባሉ። እሳቸው ከጻፉት የህይወት ታሪካቸው እንደምንረዳው ተክለሐዋርያት በመጀመሪያ ሐሳባቸው ልጅ ኢያሱን ለማረም ነበር። “ፋቡላ” የሚባለውን መጽሐፍ የጻፉት ለዚሁ ጉዳይ እንደነበር በመቅድማቸው ላይ ይገልጹልናል። ይሁን እንጂ ኢያሱ የሚታረም ስላልሆነ ተክለሐዋርያት የተቃዋሚውን ጎራ ተቀላቅለው ኢያሱን    

“ወደ አገራቸው እንደተመለሱ ከአፄ ምኒልክ ፊት ቀርበው ምን እንደተማሩ አስረዱ። ንጉሡም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ለተክለሐዋርያት የቀኝ አዝማችነትን ማዕረግ ሰጥተው በፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ሥር የመድፈኞች አለቃ አድርገው ሸሟቸው”

ለመጣል በተደረገው ትግል የማይናቅ ሚና ተጫውተዋል። ንግሥት ዘውዲቱ ዙፋን ላይ ከወጡና ተፈሪ መኮንን እንደራሴ ከሆኑ ከኋላ ተክለሐዋርያት በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በኃላፊነት ሠርተዋል። እሱም በመጀመሪያ የጅጅጋ፤ ቆይቶም የጨርጨር አውራጃዎች ገዥ ነበሩ። በሥልጣን ላይ ሲቆዩ አውራጃዎችን በወረዳዎች በመሸንሽን የአስተዳደሩን መዋቀር ለማሻሻል እና የግብር አሰባሰቡን ስርዓት በአዲስ መልክ ለመዘርጋት ከተማዎችን በዘመናዊ መልክ ለመቀየስ ጥረዋል። እነኚህ ለውጦች የባለ መሬቶችንና የሌሎች ባለሀብቶችን ጥቅም በተወሰነ ደረጃ በመንካታቸው ባላንጣዎቻቸው በሸረቡባቸው ሴራ ከቦታቸው ተነስተው ታስረዋል።

 አፄ ኃይለሥላሤ ዘውድ ከጫኑ በኋላ ተክለሐዋርያት የገንዘብ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። ሥልጣን ላይ እያሉ አንዳንድ አዳዲስ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ በማድረጋቸው ከአንዳንድ ባለሥልጣናት በመጋጨታቸው ብዙም ሳይቆዩ ከቦታቸው ተነስተዋል። ከዚህ በኋላ መቀመጫቸው በፓሪስ ሆኖ የፈረንሳይ፣ የእንግሊዝና በጄኔቭ የሚገኘው የመንግሥታቱ ማህበር አምባሳደር ሆነው ወደ ውጭ ተላኩ። በመንግሥታቱ ማህበር ውስጥም ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ የምትፈጽመውን አሻጥር ለማጋለጥ በንቃት ሠርተዋል።

እንዳየነው ተክለሐዋርያት በሃያኛው ምዕተ ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ላይ በኢትዮጵያ ማህበረ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ከሥራቸው ሁሉ ጉልህ ቦታ ያለው እና ስማቸውን ህያው ያደረገው ሕገ መንግሥት ለማርቀቅና ተቀባይነት እንዲያገኝ የፈጸሙት ተግባር ነው። ሕገ መንግሥቱን በ1931 እ.ኤ.አ. ያረቀቁት ተክለሐዋርያት ሲሆኑ ረቂቁንም ንጉሠ ነገሥቱና መኳንንቱ አይተው አንዳንድ እርማት ካደረጉበት በኋላ ጸድቋል። ይህ ህገ መንግሥት የንጉሠ ነገሥቱን ሥልጣን በመገደብ በኩል ያመጣው ለውጥ ባይኖርም ብዙ ተራማጅና ለኢትዮጵያ አዲስ የሆኑ ሐሳቦችን ይዟል ብንል አንሳሳትም። ለምሣሌ የምክር ቤቶች እንዲቋቋሙ ሰዎች ያለፍርድ ቤት ውሳኔ እንዳይያዙና ንብረታቸው እንዳይወረስ ሰዎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ በነፃነት እንዲዘዋወሩና ሌሎች ተመሳሳይ መብቶች በሕግ ተደንግገዋል። ሕገ መንግሥቱ በዘውዳዊ አገዛዝ ማዕቀፍ ውስጥ ቢሆንም ለዘመኑ ተራማጅ የሕግ ሰነድ እንደነበር አያጠራጥርም።

 ተክለሐዋርያት “ፋቡላ” እና “ትንሽ መፈተሻ ስለ እርሻ ትምህርት” የተባሉ ሁለት መጻሕፍትን ለንባብ ያበቁ ሲሆን በተለይ የመጀመሪያው ለአገራችን የተውኔት ዕድገት እንደፈር ቀዳጅ ይቆጠራል። ኦቶባዮግራፊ በሚል መጠሪያ የጻፉት የሕይወት ታሪካቸውም ከሞቱ በኋላ ታትሞ ለአንባቢያን ቀርቧል።

እሱም በሃያኛው ዘመን መጀመሪያው ሩብ ላይ ስለነበረችው ኢትዮጵያና ስለ ደራሲው ሕይወት የሚገልጽ ዝርዝር መረጃዎችን የያዘ ጠቃሚ መጽሐፍ ነው። በአጠቃላይ ተክለሐዋርያት በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ጉልህ አሻራቸውን አሳርፈው ያለፉ ምሁር ናቸው።

 በአጠቃላይ በ19ኛው ምዕተ ዓመት መጨረሻና በ20ኛው መጀመሪያ ላይ ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውያን በሩሲያ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን ከእነሱ ውስጥ አንዱ ተክለሐዋርያት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ሌሎችስ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። በዚህ ዘርፍ የተደረጉ ጥናቶች በሌሎች አገሮች የተማሩትንም ምሁራን ያጠቃልላል። ስራዎቹ ቀደምት ምሁራን ላይ ያተኮሩ በመሆናቸው በአሁኑ ጊዜ መልስ ለመስጠት አሰቸጋሪ ይሆናል። ጠለቅ ያለ መረጃ የማሰባሰብና የማጥናት ሥራም መካሄድ አለበት።

ይህችም አነስተኛ ጽሑፍ በዚህ ዘርፍ ያለውን ክፍተት ለመሙላት እንደተደረገ ሙከራ ልትቆጠር ትችላለች

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top