ፍልስፍና

ፍልስፍና ለምን ዳቦ አይጋግርም

ስለ ፍልስፍና ብዙ የተሳሳቱ አመለካከቶች አሉ። ከነዚህ ውስጥ አንዳንዶች “ፍልስፍና ዳቦ አይጋግርም፣ በድህነት እና በመልካም አስተዳደር እጦት ለሚሰቃይ ህዝብ ፍልስፍና ምኑም አይደለም። ፍልስፍና የቅንጦትና የሥራ ፈትነት ምርምር ነው።” የሚሉ አስተያየቶች ሲሰጡ ይሰማሉ። በሌላ በኩል ደግሞ “ፍልስፍና ከባህል፣ ከህግ፣ ከሃይማኖት፣ ከማኅበረሰብ አስተሳሰብ የሚነጥል፣ ሰዎችን የሚያሳብድ የቅዤት ትምህርት ነው። አንድ ሰው ፍልስፍና ከተማረ ከማንም ጋር መግባባት ይከብደዋል። ስለዚህ ፍልስፍና ሰዎችን ከማኅበረሰቡ የሚነጥል የርኩስ መንፈስ ጥንውት ነው።” የሚሉ በርካታ ናቸው። ሌሎች ወገኖችም አሉ። እነዚህ ደግሞ ፍልስፍናን አውቀው የሚፈሯት ወይም ችላ የሚሏት ናቸው። በመፈላሰፍ የአእምሮ ሥራ፣ ከፍተኛ የማሰላሰል ትዕግስት የሚጠይቀውን ቁርጠኝነት ድካም የሚፈሩት ናቸው። ወይም ከፈላስፎች የሚሰነዘርን ምክንያታዊ ትችት፣ የተሳሳተ አስተሳሰብን፣ ኢ-ምክንያታዊነትንና ግልፍተኝነትን፣ ግልብ ሐሳብን መንቀፍን የሚፈሩ የሃይማኖት፣ የሙያ፣ የፖለቲካ ጠበቃ ነን ባዮች ናቸው። አለማወቃቸው እንዲታወቅ የማይፈልጉቱ ናቸው እነዚህ።

የሃይማኖት መሪ፣ የፖለቲካ ባላደራ፣ የርዕዮተ ዓለም አራማጅ፣ የባህል ጠበቃ ነኝ ባይ ወይም በጥልቅ ማሰብንና መመራመርን የሚፈራ አለማወቁን ለመደበቅ የሚጥር፣ “አዋቂነቱን” ለማጉላት የሚፈልግ ሁሉም ከፍልስፍና ስትራቴጃዊ ማፈግፈግ ሲያደርጉ በአንድ ነገር ይስማማሉ። ፍልስፍና ዳቦ አይጋግርም፤ በችጋር ለሚሰቃይ ማኅበረሰብ ከፍልስፍና ይልቅ የልማት እንቅስቃሴዎች፣ መንገድና መብራት፣ ውሃና ትምህርት፣ መልካም አስተዳደርና ጤና፣ አምራች ኢንዱስትሪዎች ናቸው የሚያስፈልጉት በሚለው።

 በእውኑ ፍልስፍና ዳቦ አይጋግርምን? ለምንድነው የማይጋግረው? እንዴትስ ነው የማይጋግረው? እነዚህን የተለያዩ የሚመስሉ ግን በመሠረታዊ ይዘታቸው አንድ የሆኑ ጥያቄዎች ከመመለሳችን በፊት “ፍልስፍና ምንድን ነው?” የሚለውን በማብራራት እንጀምር። ፍልስፍና የቃሉ ትርጉም የጥበብ ፍቅር፣ እውነትን መሻት፣ ለዚያም መጓጋትና መጣር የሚል ነው። በጥልቅ ምርምርና ተመስጦ፣ በተች አቀራረብ፣ በተጠየቃዊ ትንታኔ፣ ሥርዓት ባለው የሥነ-አመክንዮ መንገድ ነገሮችን መመርመር፣ መፈተሽ ነው። ስለሐተታ ተፈጥሮ፣ ስለ ሕይወት ትርጉም፣ ስለ ማኅበራዊ ተቃርኖ፣ ስለ ነገረ ሕልውና (Existence)፣ አእምሮ (Knowledge)፣ ኅሊና (Mind)፣ ነፍስ/ያ (Soul)፣ ዲበ-አካል (Metaphysics)፣ ምንነት (Being)፣ ግብረገብ (Ethics)፣ ፋይዳ ወይም ዋጋ (Axiology)፣ ጥበብ፣ ፖለቲካ፣ ማኅበራዊ መስተጋብርና ሥነ አመክንዮ የሚያትት፣ የሚመረምር፣ የሚሞግት ወዘተ የትምህርት ዘርፍ ነው። ፍልስፍና ከፍተኛ የአእምሮ የመመራመር ውጤትና የሰው ልጆች በታሪክ ሂደት ውስጥ ያካበቱት የአስተሳሰብ መካዘን ነው። ከፍተኛ የህሊና ነጻነትንና ትእግስትን፣ ንጽሐ ልቡናንና ቀናነትን የሚጠይቅ የማሰብ ስራ ነው። ቀጥተኛና እርግጠኛ መልስ ከመስጠት ይልቅ ትክክለኛውን ጥያቄ ማቅረብን የሚመርጥ የመጠየቅ ሥራ ነው። በፍልስፍና ዘንድ የማይነካ የማይተች ዶግማና ቀኖና የለም። የሐሳብ መሻሻልና ያስተሳሰብ ብልጽግና የለውጥ ሂደት ነው ያለው። የፍልስፍና ዶግማዋ ጥያቄ ነው፣ ቀኖናዋም ሐተታና ሐሰሳ ናቸው። መፈላሰፍ ማለትም የሆነ ያልሆነውን የመዘባረቅ ወለፈንዲነት ወይም ቀውስነት ሳይሆን ሥርዓት ባለው መንገድ የነገሮችን መነሻና መድረሻ መመርመር፣ እውነትን መፈለግ፣ ነባራዊ ክዋኔዎችን መፈተሽና ማኅበራዊ ተቃርኖዎችን ማጋለጥ፣ የአስተሳሰብ ጽርየትንና ርቱዕነትን ማጎልበት ነው።

 አሪስጣጣሊስ (Aristotle) የተባለው የጥንት ዘመን ፈላስፋ “ፍልስፍና የትርፍ ሠዓት ሥራ ነው::” ሲል የሥራ ፈቶች ነገሮችን አንስቶ የመጣል ጫወታ ሳይሆን በተረጋጋ መንፈስ በኅሊና ርቀትና ልዕልና ወደ ሰማየ ሰማያት መመልከት፣ ወደ ጥልቁ መውረድ ነው። ከነገሮች ጀርባ ያለውን እውነትና ገፋኤ ኃይል ለማግኘት የመኳተን ሂደት ነው። ስለ ፍልስፍና በርካታ ፈላስፎች ብዙ ነገር ብለዋል። ሁሉንም የሚያስማማቸው ግን ፍልስፍና ከሚያዝ ከሚጨበጠው ነገር በስተጀርባ ያለውን መሠረታዊ እውነት ለመያዝ የሚደረግ የማያቋርጥ ጥረት ነው። የፍልስፍናም ፋይዳ ሁለንተናዊ ስለሆነ የማይዳስሰው የሕይወት ገጽታ የለም። ስለዚህ ፍልስፍና በንሥር ዓይን፣ ከፍ ካለ ሥፍራ ሆኖ (በሰቂለ ኅሊና) ዓለምን በወፍ በረር መቃኘት ጓዳ ጎድጓዳዋን መፈተሽ ነው።

 ፍልስፍና ማኅበራዊ ተቃርኖዎችን አስተሳሰባዊ ዝንፈቶችን ለማቅናት ዓይነተኛ መሣሪያ ነው። ወደ አስተሳሰባዊ ጽርየትና ባህርያዊ ቀናነት የሚወስድ መንገድ ነው። ወደ እርግጠኝነት የሚወስድ የመጠራጠሪያ መነጽር፣ ከድንቁርና ባርነትና ከጭንቀት፣ ከፍርሃት ቆፈን ነጻ የሚያወጣ ታዳጊ ኃይል ነው። በፍልስፍና የሚገኝ ጥቅምም ከወርቅና ከአልማዝ የከበረ ዋጋ ያለው ነውና ማንኛውም ሰው ሰራሽ ንዋይ ሊገዛው የማይችል ነው። አባ ሚካኤል የተባሉ የአንጋረ ፈላስፋ ደራሲ የተለያዩ ፈላስፎችን አባባሎች በሰበሰቡበትና በተነተኑበት መጽሐፍ “የፈላስፎች ፍልስፍናና የአዋቂዎች[ን] ዕውቀት” ሲገልጿት እንዲህ ይላሉ “ከብር፣ ከወርቅ፣ ከአልማዝ እርሷ ትበልጣለች ትመረጣለችም። እንዲሁም ልዩ ልዩ ጣዕምና መዓዛ ካላቸው ከአታክልት አበባዎች መዓዛ የርሷ መዓዛነት ይበልጣል። […] አንደበትህን በጥበብ፥ በዕውቀት፥ በቅንነት፥ በትዕግስት፥ በማስተዋል ጨው ታጣፍጠዋለች። ጠባይህን ያማረ የተወደደ፥ አነጋገርህን በሚሰሙት ሰዎች ዘንድ ተደማጭ ታደርገዋለች። ሥራህን ሁሉ ታከናውንልሃለች።” (ገጽ ፮)

 ወደ ተነሳንበት ጥያቄ እንመለስ። “ፍልስፍና ለምን ዳቦ አይጋግርም?” ጥያቄው ካንድ በላይ ትንታኔ አለው። አንደኛው ፍልስፍናን ለምን ዳቦ ለመጋገር ተግባራዊ ፋይዳ አናውለውም? የሚል የቁርጠኝነት ወኔ የተላበሰ ተነሳሽነት ነው። ሁለተኛ በውይይት ወይም ክርክር መሃል የፍልስፍና እውቀት ያለው ሰው ፍልስፍናማ ዳቦ ይጋግራል እንጅ! ለምን ዳቦ አይጋግር? የሚል መጠይቃዊ መልስ የያዘ ሊሆን ይችላል። ሦስተኛ በርግጥም ፍልስፍና ዳቦ አይጋግርም። ለምን ዳቦ አይጋግርም መሰለህ? ብሎ ወደቀጣይ ማብራሪያ የሚደረግ መንደርደሪያ ይመስላል። ጥያቄው በራሱ “ፍልስፍና ዳቦ አይጋግርምን?” ወደሚል ምቹና ክትነት (Precision) ቢለወጥ ለውይይታችን ይመቻል። መልሱም “አዎ” እና “አይ!” የሚል ይሆናል – አያዎ። አዎ ዳቦ አይጋግርም። የፍልስፍና ሚና ዳቦ ከመጋገርም በላይ ነውና። አይ ዳቦ ይጋግራል እንጂ! የዳቦ ጋጋሪውን ኅሊና በማረቅ፣ ስብዕና በማስተካከል ዳቦን እንዳያሳርረው፣ እንዳያሳንሰው የሚያግዝ መሣሪያ ነውና። የሚል መልስ ይይዛል። እናብራራው:-

 ዳቦ ምንድን ነው? በቁሙ ለራብ ማስታገሻ የሚጎረስ ቁራሽ ዳቦ ነው፣ ንጣይ እንጀራ። ወይም ፉት የሚባል ጠብታ ውሃ ነው የጥም ማስታገሻ – የነፍስ መቀጠያ። ያው ዳቦ ነው። ዳቦ ሰፋ ተደርጎ ሲተነተን ተምሳሌታዊ ውክልና ነው። ዳቦ መድኃኒት ነው የሕመም ስቃይን ማስታገሻ። ዳቦ ፍትህ ነው፣ ለተበደለ የኅሊና ካሳ፣ በዳይን መቅጫ። ዳቦ ፖሊስ ነው፣ ሰላም አስከባሪ። ዳቦ የእድገት ውጤት ነው በግልጽ የሚታይ ህንጻ፣ መንገድ፣ መብራት፣ ውሃ፣ ትምህርት ቤት ወይም መልካም አስተዳደር። 

“በዘመናዊ የሳይንስ እድገት ውስጥ የፍልስፍና የማይታይ እጅ እረጅም ነበር። በዘመናዊው ዓለም የፍልስፍና ሚና ጉልህ ነው። ዘመነ አብርሆ (Enligntenement)፣ ዘመነ ተሃድሶ (Renaissance) እና መሰል ሃይማኖታዊና አስተሳሰባዊ ለውጦች ፍልስፍናና ፈላስፎች የዘወሯቸው ማዕበሎች ናቸው ”

ዳቦ የማይታይ ረቂቅም ነው፣ አስተሳሰባዊ ልኅቀት፣ ስልጣኔ፣ ሰላም፣ እርጋታ፣ ነጻነት፣ ትፍስኅት ነው። ዳቦ ከታች ከእንስሳዊ ፍትወት እስከ ላይ ሰዋዊ ልዕልና የተዘረጋ የሕይወት ጣዕም ነው።

ፍልስፍና ዳቦ አይጋግርምን? ፈላስፋው እንደገበሬው በቆሎ አያመርትም፣ እንደ ሃኪሙ ሕሙማንን አይፈውስም፣ እንደ ኢንጅነሩ ሕንጻና መንገድ አይሰራም፣ እንደ ዳኛ አይፈርድም፣ አካውንታንት ወይም ማኔጀር ሆኖ አያገለግልም፣ ውሱን ርዕዮተ ዓለማዊ የፖለቲካ ዲስኩር አይዴሰኩርም፣ አይነግድም፣ ፖሊስ ሆኖ አይጠብቅም፣ በሕዝባዊ ትዕይንት ይህ ነው የሚባል የተለየ ሙያና ቀጥተኛ አገልግሎት አይሰጥም። በከፊል እውነት ነው። ፍልስፍና የነጻነት ኑባሬ ነው። የመንፈስን ልዕልና የጠባይን ቀናነት የሚያጎናጽፍ። ትምህርቱም ኅሊናን ያቀናል፣ የልቡናን ሠናይት ያጎለምሳል፣ ርቱዕነትንና ቀጥተኝነትን ያበለጽጋል ብለናል። በዚህም የዳቦ ጋጋሪውን መንፈስ ያድሳል፣ ጠባይ ያቀናል። ያላረረ፣ ያላነሰ፣ ያልተበላሸ፣ ያልኮመጠጠ ለሁሉም በእኩልነት የሚቆረስ መዓዛው የሚያውድ፣ ለስላሳና የሚያጠግብ ዳቦ ይጋግር ዘንድ ከዳቦ ጋጋሪው ጀርባ ፍልስፍና አለ። ይህ የፍልስፍና ዳቦ ጋጋሪነት በዓለም ታሪኮች ተስተውሏል።

 የጥንት ግሪኮች የፈላስፎችን ነገር ከቁብ አይቆጥሩትም ነበር። የማይጨበጥ ሐሳባዊ ዲስኩራችሁ ዳቦ አይጋግርልንም እያሉ ሰደቧቸው፣ ገደሏቸው (ሶቅራጠስ) አሳደዷቸው (አሪስጣጣሊስ)። ኋላ ላይ ከፍተኛ የፖለቲካ፣ የባህል፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ ቀውስና ድቀት ደረሰባቸው። ፈላስፎቹን ይታደጓቸው ዘንድ ፈለጓቸው። አላገኟቸውም። ፍልስፍናቸው እንደ ቺቸሮ (Cicero) ባሉ የሮማ ጸሐፍትና የፖለቲካ ሰዎች ወደ ላቲን ቋንቋ ተተርጉሞ በሮም ቤተ መንግሥትና የህዝብ አደባባዮች ዳቦ ይጋገርበት ነበር። ሮማውያን አቴናውያንን ሲወሯቸውም የፊተኞቹ ፍልስፍና ለኋለኞቹ የጋገረው ዳቦ የራሱ አስተዋጽኦ ነበረው።

 በስድስተኛው ክፍለ ዘመን የኖረ አንድ ቦያተስ (Boethius) የሚባል ፈላስፋ ነበረ። በሐሰት ተከሶ ወደ እስር ቤት የተወረወረና ኋላም በኢፍትሐዊነት በስቅላት የተቀጣ ሰው ነው። በእስር ቤት በነበረበት ጊዜ ፍልስፍናን በክብርት ሴት ወይዘሮ መስሎ ታጽናናው ዘንድ ይጠይቃት ነበር። The Consolation of Philosophy የተሰኘው መጽሐፉ የፍልስፍናን አጽናኝነት ያሳየበት ነው። ፍልስፍና በግል ሕይወትም በመከራ ጊዜ ዳቦ ትጋግራለች፣ የተጨነቀን በማጽናናት።

በመካከለኛው ክፍለ ዘመን የሃይማኖት ሰባኪዎች ዶግማና ቀኖናቸው እንዲሁም የሚገለጥ እውነት የሚሉት ዘይቤ ከፈላስፎቹ ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞን ገጠመው። ቄሶቹ ቸገራቸው። የፍልስፍናን ትችት መቋቋም የሚቻለው በራሷ በፍልስፍና እንደሆነ ሲገባቸው “ፍልስፍና ማለት እግዚአብሔር ወንጌሉን ለማያምኑ ሰዎች ቃሉን የሚያስተላልፍበት ሌላኛው መንገድ ነው።” ሲሉ ፍልስፍናን አጠመቋት፣ ክርስትናን በፍልስፍና ደጎሟት። ለዚህም ነው ቅዱሳን የተሰኙ ፈላስፎችን ወይም ፈላስፋ የተሰኙ ቅዱሳኖችን በብዛት የምናገኘው። የዓረቡ ዓለም ሙስሊም ፈላስፎች የነአሪስጣጣሊስን ፍልስፍናዎች ተርጉመው ባያስቀሩልን ኖሮ የአቴንስ ፈላስፎች ነገር ተረት ተረት ሆኖ

ይቀር ነበር። ፍልስፍና በቤተ መቅደስም በቤተ መስጊድም ዳቦ ትጋግር ነበር ማለት አይቻልም?

ከያንዳንዱ ሳይንቲስት ጀርባ ፈላስፋ የሚል ተቀጥላ ማግኘት ከባድ አይደለም። በዘመናዊ የሳይንስ እድገት ውስጥ የፍልስፍና የማይታይ እጅ እረጅም ነበር። በዘመናዊው ዓለም የፍልስፍና ሚና ጉልህ ነው። ዘመነ አብርሆ (Enligntenement)፣ ዘመነ ተሃድሶ (Renaissance) እና መሰል ሃይማኖታዊና አስተሳሰባዊ ለውጦች ፍልስፍናና ፈላስፎች የዘወሯቸው ማዕበሎች ናቸው። አሜሪካኖች የፈላስፎቹን ሐሳብ በሕገ መንግሥታቸው ላይ በደንብ ተጠቅመውበታል ይባላል። “ወንድማዊነት፣ እኩልነት፣ ነጻነት” የሚሉ መፈክሮችን አንግቦ የፈነዳውን የፈረንሳይ አብዮት ከቅርብ ርቀት የመራው የጀርመን ሐሳባዊ ፍልስፍና (German Idealism) ነው። Existentialism የተሰኘው የፍልስፍና ክንፍ የተፈጠረው በአንደኛውና ሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች አስከፊ ግፍ ይሰቃይ ለነበረውን የሰው ልጆች ሕይወት ብኩንነት መልስ ለመስጠት ነው። ያለ ፈቃድ ሞትን ለመመከት የተነሳ የነጻነት ጎህ። በ19ኛውና በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተነሱት እነ ማርክስና ከሱ በኋላ የመጡት Critical Social Theorists በካፒታሊዝም በዝባዥ የፖለቲካ ኢኮኖሚ የሚሰቃየውን ድሃውን፣ ጭቁን ሰራተኛውን ለመታደግና በአድሃሪ ምሁራኑ አድር ባይነትና ቸልታ በኢ-ምክንያታዊነት አስተሳሰብ የሚናውዘውን መንጋ ለማዳን ነው። የፍልስፍናን ሰይፍ፣ ጦርና ጋሻ በማንገብ ማኅበረ-ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተቃርኖውን ለመፍታት። በማኅበራዊ መስተጋብር ብልሹነት እያረረ ያለውን ዳቦ ለመታደግ፣ አዲስ ዳቦ ለመጋገር። የቅርብ ጊዜዎቹ የሴቶች መብት ተሟጋች፣ የአካባቢ ተቆርቋሪ እንቅስቃሴዎች ወዘተ፣ የዘመናችን አካባቢያዊና ዓለማቀፋዊ ተግዳሮቶች መፍትሄ ያገኙ ዘንድ የፍልስፍና የማይታይ እጅ (Invisible Hand) አሻራውን እየጣለባቸው ይገኛል። ሊጥልባቸውም ይገባል። ስለዚህ ፍልስፍና ከእስር ቤት እስከ ቤተ መንግሥት፣ እስከ ቤተ መስጊድና ቤተ መቅደስ ዳቦ ይጋግራል ብንል ከንቱ ድምዳሜ አይሆንም።

 ታዲያ ፍልስፍና ለምን ዳቦ አይጋግርም? እንዴትስ አይጋግርም? ፍልስፍና በእውነት የቅንጦት ነገር ነው ወይስ በጥብቅ የምንፈልገው ቁራሽ ዳቦ፣ የውሃ ጠብታ፣ የሞት ሽረት ጉዳይ? ለእንደኛ ዓይነቱ “ድሃ ማኅበረሰብ”ስ ፍልስፍና አያስፈልግምን? እናንተ በነዚህ ጥያቄዎች ላይ እየተወያያችሁ ከቆያችሁ፣ እኔስ ፍልስፍና በኢትዮጵያ  የነበረውንና የሚኖረውን ሚና ይዤ ለመመለስ አልፈቅድምን?  

1 Comment

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top