አድባራተ ጥበብ

የአኙዋክ የ“ክዎር” የእርቀ-ሰላም ሕጎችና መንገዶች

ኢትዮጵያ የኅብረባህል ሀገረሙዚየም ነች። ባህሎች የግልና የወል መገለጫ ባህርያት አላቸው። በእነዚህ የልዩነትና የተመሳሳይነት ባሕርያት ምክንያት በኅብረ-ባህልነት ይገለፃሉ። ዛሬ በዚህ አጭር ጽሑፍ ለአንባብያን ለማቅረብ ትኩረት ያደረኩት በኢትዮጵያ የናይሎ ሠሐራ ህብረተሰቦችና ማህበረሰቦች አንዱ በሆነው፣ በጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ በሚገኘው፣ አኙዋ (“አኙዋክ”) ተብሎ በሚጠራው ህብረተሰብ ትውፊታዊ የ“ክዎር” (የእርቀ-ሰላም) ሕጎች፣ ደንቦችና ዘዴዎች ላይ ነው።

 በቀጥታ ወደ ርዕሰ-ጉዳዩ ከማምራቴ በፊት ግን አኙዋ በሚለውና በትእምርተ-ጥቅስ “አኙዋክ” በሚል የተጠቀሱትን የህብረተሰቡ የወል ስያሜ ተደርገው በሚያገለግሉበት የአጠቃቀም መካከል የይዘት ልዩነት መኖሩን ለአንባብያን ማስታዎስ ጠቃሚ ይመስለኛል። ይኸውም “አኙዋ” ስንል ዛሬ ወይም አሁን በሕይወት ያለውን ትውልድ ማለታችን ነው። “አኝዋክ” ስንል ግን ዛሬ በሕይወት የሌሉትን፣ ያለፉትን ትውልዶች ሁሉ የሚጠቅስ ትርጉም ያለው ነው። ከዚህ አኳያ በስያሜዎቹ አጠቃቀም ወይም ትርጉም ላይ ሰፊ ልዩነት መኖሩን ባለማወቅ የዛሬውን፣ በሕይወት ያለውን፣ ትውልድ “አኝዋክ” እያልን መጥራት ስህተት ብቻ ሳይሆን ኅልውን ኅልውነት እንዳልሆነ አድርጎ ማየት መሆኑን ጨምሮ መረዳት ተገቢ ይሆናል ማለት ነው። ይህን በማስታወስ ወደ ርዕሰ-ጉዳዩ እናምራ።

ክዎር በዋነኛነት በህብረተሰቡ አባላት መካከል የሚከሰቱ ቅራኔዎችንና ከባድ ወንጀሎችን በመቆጣጠርና መፍትሔ በመስጠት ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ለመመለስ የተቋቋመ ሕግ ነው። በህብረተሰቡና በባህላዊ አስተዳዳሪዎች መካከል ለሚፈጠሩ ግጭቶች መፍቻ ተደርጎ የሚያገለግለው ሕግ ደግሞ “አጌም” ይባላል። “አጌም” ማለት በጥሬ ትርጉሙ ጥፋት የተገኜበትን ንጉሥ (ኜያ) ወይንም ኳሮ (ቆሮ) በህዝብ ዐመፅ ከስልጣን የማስወገጃ ሕግና መንገድ እንደማለት ነው። በህብረተሰቡ ፍልስፍና መሠረት “ክዎር”ም ሆነ “አጌም” እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ዐሠርቱ ትዕዛዛት መለኮታዊ፣ ሚቶሎጂያዊ፣ የአመጣጥ ታሪክ አላቸው። ከሰማያዊ ኃይል (ከፈጣሪ) የተሰጠ ቅዱስ (sacred) ታሪክ አላቸው። እነዚህም ከኦቹዶ (‹ኦኪሮ›ም ይባላል) ሕግና ሥርዓት ባልነበረበት በዘመነ-ጭካኔ ለጥንታውያን አኙዋኮች የተሰጠ የሰላምና የደህንነት ማስጠበቂያ ሕግና መንገድ ተደርገው ይተረካሉ፤ ይተረጎማሉ፤ ከዚያን ጊዜ አንስቶ

“በክወር ሕግ መሠረት በገንዘብ መልክ የሚከፈል የጥቁር ደም ካሣ አርኪነትና ተቀባይነት የለውም። የጥቁር ደም እርቀ-ሰላም እውነተኛ ትርጉም ጥብቅ ዝምድናን የሚፈጥርና የሚያጠናክር ብይን መሆን አለበት። በመሆኑም በአኙዋዎች ዘንድ ልጃገረድ የጥቁር ደም ካሣ ተደርጋ ለሟች ቤተ-ሰብ ትሰጣለች ”

በታሪክ ሂደት ከትውልድ ወደ ትውልድ በቀልም በድርጊትም እየተላለፉ የመጡ ትውፊታዊ እሴቶች ናቸው። ይሁንና የዛሬው ትኩረታችን በክዎር ደንቦች ላይ ይሆናል።

የክዎር መገለጫ ድርጊቶችና ደንቦች፡-

 ክዎር በዋነኛነት በህብረተሰቡ አባላት መካከል የሚከሰቱ የተለያዩ ግጭቶችንና ከባድ ወንጀሎችን በመቆጣጠርና መፍትሔ በመስጠት ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ለመመለስ በባህል የተቋቋመና የሚያገለግል ሕግ ነው ብለናል። እነዚህን ከመሳሰሉ ግጭቶችና ከባድ ወንጀሎች መካከል የነፍስ ግድያን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በክዎር ሕግ መሠረት አንድ በእጁ ነፍስ የጠፋበት አኙዋ ሁኔታ እንደተፈፀመ ወደ ቤተ-ሰቡ ወይም ወደ ሌላ ቦታ ሳይሆን በተቻለው መጠን ጊዜ ሳያጠፋ – በፍጥነት – መሄድ ያለበት ወደ ንጉሡ ወይንም ወደ ኳሮው ሠፈር (ቡራ) ነው። በዚህ ሁኔታ ፈጥኖ በመድረስ እያለበት በመንገድ ላይ በመዘግየት ወይም ወደ ሌላ ቦታ በመሄድ በሚወስደው ጊዜ ውስጥ የሟች ወገን አግኝቶ የደም መመለሻ ቢያደርገው ሰውየው ደመ-ከልብ ሆኖ ይቀራል። ነገር ግን በባህሉ መሠረት በፍጥነት ወደ ንጉሡ ወይንም ወደ ኳሮው ሠፈር (ቡራ) ከደረሰ ስለተፈፀመው ችግር ምንም ነገር ሳይጨምር ሳይቀንስ የድርጊቱን ታሪክ አንድ በአንድ ዘርዝሮ ለንጉሡ ወይንም ለኳሮው አስረድቶ፣ መሣሪያውን አስረክቦ፣ “ጥግ ይሰጠኝ” ብሎ ይጠይቃል። ሕጉ ንጉሡን ወይንም ኳሮውን እንዲህ ያለ አጋጣሚ የደረሰበትን ሰው በቡራው (በቤተ-መንግሥቱ) ግቢ ውስጥ ለማቆየትና ለመጠበቅ ያስገድደዋል። ስለዚህ ሰውየው ምግብና መጠጥ እየተሰጠው በግቢው ውስጥ ደህንነቱ ተጠብቆ እንዲቆይ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ጉዳዩ እንዳወቀ ጊዜ ሳያጠፋ ወዲያው ለገዳይና ለሟች ቤተሰቦች መላክተኛ በመላክ ወደ ቡራው እንዲመጡ ማድረግ አለበት። ይህን ሳያደርግ ቀርቶ ወይም መልእክተኞቹ ዘግይተው የሟች ቤተሰቦች በገዳይ ቤተሰቦች ላይ የበቀል አፀፋ ቢወስዱ ተጠያቂው እሱ ይሆናል። ይህ መዘዙ ብዙ ነው። ‹አጌም› አስነስቶ ሊገረፍ ወይም ከዙፋኑ ሊወርድ ይችላል። በመሆኑም ንጉሡ ወይንም ኳሮው የላካቸው መልእክተኞች የሟችንና የገዳይን

የቅርብ ዘመዶች ስለተፈጠረው ችግር ነግረው ጊዜ ሳይፈጁ ወደ ቡራው ይዘዋቸው መምጣት አለባቸው። ለግራ ቀኙ ቤተሰቦች መላክተኞች ሲላኩ ንጉሡ ወይንም ኳሮው በተጓዳኝ የሚያደርጓቸው ጉዳዮች አሉ። እነዚህም የሀገር ሽማግሎች በያሉበት ተጠርተው እንዲመጡና የአካባቢው ነዋሪዎች ለሟች ቤተሰብ በ“ኦቶችንግ” መልክ በገንዘብም ይሁን በጥሬ ዕቃ የሚከፈል ስጦታ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ መጠየቅ ናቸው።

 ከዚህ ላይ “ኦቶችንግ” ተብሎ የተጠቀሰው በአፋዊ ትርጉሙ “የእጅ ማሠሪያ፣ በቀል ላለመውሰድ ቃል ኪዳን መግቢያ” እንደማለት ነው። በደንቡ መሠረት ለሟች ቤተሰብ “ኦቶችንግ” የሚከፍለው ንጉሡ ወይንም ኳሮው ነው። በእጅ ማሠሪያነት የሚከፈሉት ባህላዊ ዕቃዎች ወይም ገንዘቦች “ዲሙኝ” ወይም “የኦቴኖ ጦር” ናቸው። “ዲሙኝ” ልዩና ውድ የሆነ ጨሌ ነው። ጦሩ ኦቴኖ የተባለ የአኙዋ ጥበበኛ ለመጀመሪያ የሠረው ጥንታዊ ጦር ነው። በአሁኑ ጊዜ ወደ ብር እየተለወጠ መጥቶ ሊሆን ይችላል። ንጉሡ ወይንም ኳሮው “የእጅ ማሠሪያ” (“ኦቶችንግ”) ከአካባቢው ነዋሪዎች አስተዋፅኦ ለመጠየቅ የሚገደደው ራሱ ለመክፈል የማይችል ወይም ለጊዜው የሌለው ከሆነ ብቻ ነው።

 ከላይ እንደተጠቀሰው የተጠሩት የሀገር ሽማግሎችና የገዳይና የሟች ቤተሰቦች እንደመጡ የ”ኦቶችንግ” ሥነ-ሥርዓቱ በንጉሡ (ኜያው) ወይንም በኳሮው መሪነት ተከናውኖ ለሟች ቤተሰቦች በሽማግሎች ነባሪነት ይከፈላል ወይም በቀል እንዳይወስዱ እጃቸው ይታሠራል። ይህ ሥነ-ሥርዓት ከተከናወነ በኋላ የነበሩት ሽማግሎች ሌሎች ሽማግሎችን ጨምረው የእርቀ-ሰላሙ ሂደት እንዲጀመርና እንዲከናወን ከዚያው ላይ ኃላፊነት ይሰጣቸዋል።

 ከዚህ በመቀጠልም ከአምስት ስድስት ቀናት በኋላ ነፍስ በእጁ አጥፍቶ ከንጉሡ ቡራ ወይንም ከኳሮው ግቢ ውስጥ ጥግ ተሰጥቶት የቆየው ሰው ያለ ስጋት ወደ ቤቱ ሄዶ እንደ ወትሮው በሰላም መኖሩን ይቀጥላል። “ኦቶችንግ” ከተከፈለ በኋላ የሟች ቤተሰብ በእርሱ ላይ የሚያደርሰው ጉዳትም ሆነ በቀል አይኖርም። ምክንያቱም የ“ኦቶችንግ” ሥርዓተደንብ ከተከናወነ በኋላ በቀል መውሰድ በህብረተሰቡ ዘንድ ለልጅ ልጅ የሚተርፍ “አሼኒ” (ክፉ እርግማን) ይደርሳል ተብሎ  ስለሚታመንበት ነው።

ይህ የክዎር አንዱ መሠረታዊ ገፅታ ቢሆንም ጉዳዩ ግን በዚሁ የሚቋጭ አይሆንም። የሀገር ሽማግሎች ነፍስ የጠፋበትን ችግር መንስዔነገር አጥንተው፣ ጥፋተኛውን ለይተው፣ ብይን በመስጠት ካሣ መወሰንና ማስከፈል፣ የደረሱበትን ደረጃም በየጊዜው ለንጉሡ ወይንም ለኳሮው መግለፅ አለባቸው። ይህ ሳይሆን ችግሩ መፍትሔ አገኜ ማለት አይቻልም። ስለዚህ የሀገር ሽማግሎች የግራ ቀኙን አቋም

“ከዚህ በመቀጠልም ከአምስት ስድስት ቀናት በኋላ ነፍስ በእጁ አጥፍቶ ከንጉሡ ቡራ ወይንም ከኳሮው ግቢ ውስጥ ጥግ ተሰጥቶት የቆየው ሰው ያለ ስጋት ወደ ቤቱ ሄዶ እንደ ወትሮው በሰላም መኖሩን ይቀጥላል። “ኦቶችንግ” ከተከፈለ በኋላ የሟች ቤተሰብ በእርሱ ላይ የሚያደርሰው ጉዳትም ሆነ በቀል አይኖርም ”

መርምረው፣ የምሥክሮችን ቃል ተቀብለው፣ የችግሩን ባሕርይ ተረድተውና አመዛዝነው ፍርድ ይሰጣሉ። ፍርዱ ተቀባይነት ያለው፣ ተመልሶ የማያገረሽ፣ ቂም የሚሽር፣ ደም የሚያደርቅ እርቀ-ሰላም የሚያስገኝ መሆን አለበት። በክወር ሕግ መሠረት በገንዘብ መልክ የሚከፈል የጥቁር ደም ካሣ አርኪነትና ተቀባይነት የለውም። የጥቁር ደም እርቀሰላም እውነተኛ ትርጉም ጥብቅ ዝምድናን የሚፈጥርና የሚያጠናክር ብይን መሆን አለበት።

 በመሆኑም በአኙዋዎች ዘንድ ልጃገረድ የጥቁር ደም ካሣ ተደርጋ ለሟች ቤተ-ሰብ ትሰጣለች። ስትሰጥም የሀገር ሽማግሌ፣ ዘመድ አዝማድ ተሰብሰቦ፣ ከብት ታርዶ፣ ሥጋው ከሁለት ተከፍሎ ለግራ ቀኙ ወገኖች ተሰጥቶ፣ “በመካከላችን ክፉ ነገር ደግሞ አይድረስብን” ተብሎ የአጥንት ሠበራ ሥርዓተ-ደንብ ተፈፅሞ ነው እንጂ እንዲሁ በግብር ይውጣ አይደለም። ልጅቱም የገዳዩ ልጅ መሆኗ ይመረጣል።

ሆኖም ገዳዩ ሴት ልጅ ላይኖረው ይችላል። ይህ ከሆነ ችግሩ የቤተሰብ ችግር በመሆኑ የገዳዩ የእህት፣ የወንድም፣ ካልቻለ ደግሞ የአክስት ወይም የአጎት ልጅ የምትሆንበት አጋጣሚ ይኖራል። ለዐቅመ-ሄዋን የደረሰችም ትሁን አትሁን ልጅቷ ለሟች ቤተሰብ በካሣ መልክ ትተላለፋለች። ለዐቅመ-ሄዋን የደረሰች ከሆነች የሟች ወንድም ካልሆነም የሟች ቅርብ ዘመድ ያገባታል። ገና ያልደረሰች ትንሽ ልጅ ከሆነች ደግሞ በሟች ቤተሰብ እንደ ልጅ አድጋ ለዐቅመ-ሄዋን በደረሰች ጊዜ ከዚያው ቤተሰብ አንዱን ታገባለች። በዚህ መልክ ልጆች በመውለድ ደም በተቃቡት ቤተሰቦች መካከል ጥብቅ ዝምድና በመፍጠር ፍቅርንና ሰላምን በዘላቂነት ታወርዳለች ማለት ነው።

በአጠቃላይ ከባህሉ ውጭ የሆንን አንባቢዎች የተለያየ ግምት ሊኖረን መቻሉ ግድ ነው። ትምህርት-ቀመስ ፊደላውያንም እንደዚሁ የተለየ አስተያየት ሊኖራቸው ይችላል። በፀሐፊው ዓይን ግን እንዲህ ያሉ ባህሎችን መሠረት አድርጎ በዘመኑ ጤነኛ አስተሳሰብ ማዘመን ለመልካም አስተዳደር፣ ለዲሞክራሲና ለአእምሮ/ለእውቀት ዕድገት ጠቃሚነት አለው ብየ አምናለሁ። ለምሳሌ ወንጀል ፈፅሞ ለአስተዳደራዊ ተቋማት በአእምሮው ትዕዛዝ እጅ መስጠትና ስለአጋጣሚው እውነቱን መናገር መፋፋት ያለበት ድንቅ እሴት ነው። ንጉሡም (ኜያውም) ሆነ ኳሮው ነብስ አጥፍቶ ወንጀል ፈፀምኩ ብሎ እጅ የሰጠን ሰው “ወንጀለኛነትክን ያመንክ ነህ” ብሎ እንደ እባብ ከመቀጥቀጥ ተቆጥቦ፣ ጥግ ሰጥቶ፣ ቤተሰቦችም ከመዳማት በኦቶችንግ ሥርዓተ ደንብ እንዲርቁ የማድረግ ኃላፊነት ያላቸው መሆኑን አውቀው በገቢር ማዋላቸው ሊለማ የሚገባው ድንቅ እሴት ነው። በቆየው ባህላዊና ማህበራዊ አውድ የእርቀ-ሰላም ምልክት ተደርጋ በካሣ ትሰጥ የነበረችውን ልጃገረድ አሁን ከተደረሰበት የዕድገት ደረጃ አንፃር ከህብረተሰቡ ጋር በመማማር ወይም በትምህርት ሥርፀት ለመቀየር ችሎታንና አቅምን መገንባት እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top