ማዕደ ስንኝ

የኘሮፌሰር እሸቱ ጮሌ ግጥሞች

ኘ/ር እሸቱ ጮሌ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው እውቅ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች አንዱ ነበር። ኘ/ር እሸቱ ከኢኮኖሚክስ ምሁርነቱ ባላነሰ ደረጃ በ1960ዎቹ በነበረው ንቁ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ተሳታፊነቱም (አንዳንዴ መሪነቱም) ይታወቃል። ለስነጥበብ እንግዳ ባይሆንም በገጣሚነት ግን እምብዛም አይታወቅም።

 ኘ/ር እሸቱ የተወለደው በ1937 ዓ.ም በነጌሌ ቦረና ነበር። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን እዚያው ነጌሌ ካጠናቀቀ በኋላ የሁለተኛና የኮሌጅ ትምህርቱን በጄኔራል ዊንጌትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ (ኋላ የቀዳማዊ ሃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ) ተከታትሏል። በ1958 ዓ.ም ከኮሌጁ ሲመረቅ ባስመዘገበው ከፍተኛ ውጤት የሜዳሊያ ተሸላሚ ነበር። ከምረቃ በኋላ በዩኒቨርሲቲው በረዳት መምህርነት ተቀጥሮ ጥቂት አገልግሎ የድህረ ምረቃ ትምህርቱን በአሜሪካን ሀገር በኢሊኖይስና ሲራኪዩስ ዩኒቨርሲቲዎች ተከታትሎ በ1965 ዓ.ም በዶክተርነት ማዕረግ ተመርቋል። በስራው ዓለም በዩኒቨርሲቲ መምህርነት፣ በዲንነት፣ በምርምር ተቋም ዳይሬክተርነት አገልገሏል። በ1990 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ከመለየቱ በፊት በተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ቢሮ የኢኮኖሚ አማካሪ ሆኖ ሰርቷል።

 ኘ/ር እሸቱ ግጥም መጻፍ የጀመረው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ ነበር። ብዙዎቹን ግጥሞቹን የጻፈው በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሲሆን በአማርኛ አንድ፣ በፈረንሳይኛ አንድ ግጥም ጽፏል። የአማርኛ ግጥሙ ‹‹ምቀኝነት››፤ የፈረንሳይኛ ግጥሙ ደግሞ ‹‹የመሃይም አስተያየት›› (Une remarque ignoante) የሚል ርዕስ ነበረው። ሁለቱም ግጥሞቹ በሰኔ 1951 ዓ.ም በጄኔራል ዊንጌት ተማሪዎች መጽሄት ላይ ታትመው ወጥተዋል። ይህ ሲሆን ኘ/ር እሸቱ የ10ኛ ቢ ተማሪ ነበር። አስራ ሁለት የሚሆኑት የእንግሊዝኛ ግጥሞቹ ከ1954 እስከ 1959 ዓ.ም ድረስ በነበሩት አምስት ዓመታት ውስጥ ‹‹አንዳንድ ነገሮች›› ተብሎ በሚታወቀው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የስነጽሁፍ መጽሄት ላይ ታትመዋል።

ከፍ ሲል የሰፈሩትን የመግቢያ ሃሳቦች ያገኘሁት ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ ‹‹የዶ/ር እሸቱ ጮሌ ግጥሞች›› በሚል ርዕስ በኢንተርኔት https:// www.scribd.com/document/182178383/Eshetu-Chole-Poemspdf ላይ ባሰፈረውና ለግጥሞቹ መንደርደሪያ ከተጠቀመባቸው ጥቂት አንቀጾች ነው። ዶ/ር ፈቃደ የኘ/ር እሸቱን ግጥሞች ያሰባሰበው የኢትዮጵያን የፈጠራ ስነጽሁፍና ሂስ በተመለከተ እንደ እ.ኤ.አ በ1981 እና 1982 በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያካሂደው ለነበረው የጥናትና ምርምር ስራ ነበር። ለዚህ ጥናት ያሰባሰባቸው 13 የእንግሊዝኛ ግጥሞች ነበሩ።

 ምናልባት ብዙ ሰው እንደሚስማማው የኘ/ር እሸቱ የስነግጥም አድናቂነት ድንገት ፍንትው ብሎ የወጣው በ1985 ዓ.ም ዶ/ር ፈቃደ ‹‹ጩኸት›› በሚል ርዕስ ላሳተመው የግጥም መጽሐፍ በጻፈው አስደማሚ መግቢያ ነበር። መግቢያው ለግጥሞቹ አውድ አበጅቶላቸዋል፤ ትርጉም ሰጥቷቸዋል። መግቢያውን ደጋግሜ አንብቤዋለሁ፤ አነበዋለሁም፣ ነገር ግን ለእኔ ዘወትር አዲስ ነው ሰርክ እሸት እሸት የሚል!

 ዶ/ር ፈቃደ በግጥሞቹ ግርጌ ያስቀመጣቸው የአውሮጳውያን አቆጣጠር ዓመተ ምህረቶች ግጥሞቹ የተጻፉበትን ዘመን የሚያመለክቱ ከሆነ፣ ኘ/ር እሸቱ ብዙዎቹን ግጥሞቹን የጻፈው በ1959 ዓ.ም ነው። ሰባቱ ግጥሞች የተጻፉት በዚያን ዓመት ነበር። ያ ዓመት ኘ/ር እሸቱ የኮሌጅ ትምህርቱን አጠናቅቆ የመምህርነት ስራውን የጀመረበት ዓመት ነበር። የተቀሩት ግጥሞች በ1951 እና በ1956 ዓ.ም መካከል በነበሩት ዓመታት የተጻፉ ናቸው።

 የኘ/ር እሸቱ ግጥሞች ከወጣት አዕምሮ የፈለቁ፣ ጉልበትና ውበት ያላቸው ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። ጭብጣቸው ነፃነት፣ ብቸኝነት፣ ትዝታ፣ ዝምታ፣ ኑሮና የኑሮ ፈተና፣ ወዘተ ነው። ጥመውኝ አንብቤአቸው፤ ደስ ብሎኝ እንዳቅሜ ተረጐምኳቸው። ልክ ለዶ/ር ፈቃደ “ጩኸት” እንደተጻፈው መግቢያ እሸት እሸት የሚሉ ናቸው።

ነፃነት

ሰላም ነው፣ ሃብት ነው፣ ብርሃን ነው ነፃነት፤

ነፃነት ምቾች ነው ባለ ዝና ህይወት፤

ለተድላ ደስታ መነሻ መሰረት።

ደም መፋሰስ የለ፣ ወይ ውጊያ ጦርነት፣

ለመጨፋጨፊያ የሆነ አንዳች ምክንያት።

ነፃነት ያለው ህዝብ እጅግ ደስተኛ ነው፣

ከዚህ የበለጠስ ከቶ ምን ሊሻ ነው?

የማይገሰስ መብት፣ የማያዳላ ፍርድ፣ ሚዛናዊ ህጐች፣

እኒህ አይደሉም ወይ የሰላም ጠበቆች።

የነፃነት ብርሃን የአርነት ጮራ

ናቸው የሚመሩት፣

የሰው ልጅን ዕድገት፣ ብልጽግና ልማት፣

እንዲህ ከሆነማ ይሁና ግባችን ዘወትር ነፃነት፣

የክብር የዝና ገናና ማማ ላይ፣

እመር ብለን ወጥተን ጉብ እምንልበት።

………………

1951

መንገደኛው

ቀዝቀዝ ባለው ምሽት፣

ክዋክብት በበዙበት፣

እንዲያው እንደዘበት፣ ተንጋልዬ አረፍ እንዳልኩ፡

የሆነ ሃሳብ ውልብ አለ በአዕምሮዬ፣ ዓይኖቼን ሰማዩ ላይ

እንደተከልኩ።

ድንገት ግራ ገባኝ እንደ መንገደኛ፣

ባዕድ ሃገር ያለ ባይተዋር ብቸኛ።

ልቤን ገባው ፍርሃት፣

ላለፈው ትዝታ፣ ለሚመጣው ናፍቆት፣

ሽምቅቅ ኩምትር አለ የራደው ጉልበቴ፣

ደነዘ አከላቴ።

ዓለም እንደሆነ ባለቤት የላትም፣

አይደለች የማንም፣

ሁሌ አዲስ እንግዳ፣

ድንገት ማሰብ ጀመርኩ፣

የሄድኩትን መንገድ ያጋመስኩትን፣

የቀረኝን ደግሞ የምሄደውን፣

መንገድ እንደመታው፣ ድካም እንደያዘው፣ ምስኪን መንገደኛ፣

እፎይ አልኩ፣ ተነፈስኩ፣

ወጡ ቃላቶቹ ከአፌ ፈትለክ ብለው፣

እንዲህ አልኩ፦

“መንደገኛ ነኝ በባዕድ ሃገር”፣

ምንም መሪ የሌለኝ፣ መንገድ በሌለው ምድር።

እንዲህ ነው ኑሯችን

ህይወት የምንለው፣

ዘወትር ግብግብ ማቆሚያ የሌለው።

የጥሩ የመጥፎ፣

የመውደድ የመጥላት፣

የሞትና ህይወት።

መባተል ነው መድከም፣

ምንም ዕረፍት የለም።

እስክንሞት ድረስ በደረሰ ለቱ፣

ምንም ዓይነት ስራ የማንሰራበቱ።

መሳቅ ነው፣ ማልቀስ ነው፣

ዕጣችን ይኸው ነው።

በራስ ላይ መቀለድ፣ ነፍስን ማባበል፣

ወይ እስኪሸነፉ፣ ወይ እስኪያሸንፉ፣ ማቆም የለም ትግል።

ብድግ ብሎ ጉዞ፣ ደግሞ ማፈግፈግ

ደፋር መስለን ዳንዴ፣ ፍርሃትን አቅፈን፣

ተስፋን ስንቅ አድርገን፣ ደግሞ ተስፋ ቆርጠን።

ደስታ በሃዘን፣ ድልም በሽንፈት፣

ባለ ተስፋ መሆን፣ በተስፋ ማጣት፣

ብርሃን በጨለማ፣ ሞትም በህይወት፣

አንዱ አንዱን ሲከተል፣

ሰው ሰውን ሲከተል፣ ልክ እንደ ቅፍለት።

እንዲህ ነው ኑሯችን!

ህይወት የምንለው፣

ዘወትር ግብግብ ማቆሚያ የሌለው።

የጥሩ የመጥፎ፣

የመውደድ የመጥላት፣

የሞትና ህይወት።

መባተል ነው መድከም፣

ምንም ዕረፍት የለም።

እስክንሞት ድረስ በደረሰ ለቱ፣

ምንም ዓይነት ስራ የማንሰራበቱ።

መሳቅ ነው፣ ማልቀስ ነው፣

ዕጣችን ይኸው ነው።

በራስ ላይ መቀለድ፣ ነፍስን ማባበል፣

ወይ እስኪሸነፉ፣ ወይ እስኪያሸንፉ፣ ማቆም የለም ትግል።

ብድግ ብሎ ጉዞ፣ ደግሞ ማፈግፈግ

ደፋር መስለን ዳንዴ፣ ፍርሃትን አቅፈን፣

ተስፋን ስንቅ አድርገን፣ ደግሞ ተስፋ ቆርጠን።

ደስታ በሃዘን፣ ድልም በሽንፈት፣

ባለ ተስፋ መሆን፣ በተስፋ ማጣት፣

ብርሃን በጨለማ፣ ሞትም በህይወት፣

አንዱ አንዱን ሲከተል፣

ሰው ሰውን ሲከተል፣ ልክ እንደ ቅፍለት።

እንዲህ ነው ኑሯችን!

………………………

1954

ዘወር ብለው ሲያዩት

ረዥም ነው ጊዜው ካለፈ ቆይቷል፣

ግን ትዝታው ባይኔ እስካሁን ያበራል።

አልፈዋል ጊዜያቱ የዚያ የልጅነት፣

የሳቅ የጨዋታው፣

ሟሸዋል ዓይኖቹ ቦግ ጐላ ያሉት፣

ተንቀልቃይ እሳትን ከሩቅ የሚተፉት።

ጥቁር የነበረውን ፀጉር፣ ጊዜ አገርጥቶታል፣

ለስላሶቹን ጉንጮች መስመር ወሯቸዋል።

አልፈዋል ጊዜያቱ፣

የየዋህነቱ፣

የህይወት ብርታቱ።

በፍቅር የሞቀው ልብ፣ ቀዝቀዝ ማለቱ፣

ፈልቶ የነበረው፣ ደም በረድ ማለቱ።

ብስራቱ የቅዝቃዜው፣

የመጨረሻው መቅረቡን ነው።

………………….

1959

ጨለማ

ጨለማ ያስፈራል፣

እርኩስ ሃሳብ ያሳስባል፣

መጥፎ ትዝታን ያስታውሳል።

ቁጭ ብዬ በጨለማ፣

የሌለ ነገር ስመለከት፣ የማይሰማ ድምፅ ስሰማ።

ቁጭ ብዬ በፀጥታ፣

ጠበቅሁ ተስፋ አድርጌ በእርጋታ።

ብርሃን ጨለማን ገስሶ፣

እፎይ እንድል ገላግሎኝ፣

ከባዶ ዋይታ ለቅሶ።

………………….

1955

ፈተና

ጨዋ የሚባል ሰው፣

ፈተናን በትዕግስት ያለፈ ነው፣

ይባላል፣

ግና! በይህ በእኛ ዘመን፣

ሰው በወንድሙ ላይ፣ ጭካኔን አብዝቷል፣

ፍፁም ትዕግስት አጥቷል።

ሽንፈት በዝቷል፣ ተስፋ መቁረጥም፣

በየሰው ትከሻ ላይ፣ ተከምሯል እንደ ሸክም።

ማነው ታዲያ፣ ይህን መርግ የሚያወርድ?

ለሰው ከሰው በላይ፣ ማን ሊሆነው ዘመድ?

…………………

1955

እንቅልፍ

ቀንም፣ ሌትም፣

ጧትም ማታም፣

አረፍ ማለት አይቀርም፣

ሸለብ ማለት አይቀርም፣

በእንቅልፍ፣

በሞት ታናሽ ወንድም።

ምነዋ?!

ያቺ የመጨረሻ ዕለት፣

እብስ የሚሉባት፣

ምናለ?!

ሞትን አቀማጥለው፣

አባብለው፣ አድሰው፣

እንደ እንቅልፍ አድርገው፣

ልክ እንደ ሰመመን፣

ብትሆን?!

ጋደም ያልን እንደሆን፣ ጭንቅ ወዲያ ብለን ነው፣

ተኛን ያልን እንደሆን፣ ሞተን ነው ለጊዜው።

ከዘላለም እንቅልፍ፣ ከሞት ሃያል ጭብጥ፣

ነፍሳችንን ይዘን አንችልም ለማምለጥ።

አሊያ፣ ይሆን እንዴ?

ሞት ረዥም እንቅልፍ፣ እንደሚነገረን፣

ቀና የምንልበት፣ ነቃ የምንልበት እንቅልፉ ሲያልፍልን?

ጊዜ

ጊዜ የተወለደው፣

በባዶነት ውስጥ ነው።

እናም!

በባዶነት ውስጥ፣ ጊዜ መልሶ ቢያልፍም፣

በጭራሽ ሞቶ አይሞትም።

ባዶነት አልቦን ይወልዳል፣ ትርጉሙም ይገኛል ከዚያ፣

ከድቅድቁ ጨለማ ውስጥ፣ በተጀቦነው በእርሱ ዙሪያ።

ከመኖር፣

ወዳለመኖር።

እርጅና አይሉት፣

ወጣትነት፣

የሁሉ ወዳጅ፣ የማንም ጠላት።

እልፍ ሚሊዮኖች፣ ሰርክ ቢታትሩ ባዶውን ለመሙላት፣

ጊዜ እንደሁ ይጓዛል፣ በጀመረው መንገድ፣ አይቆምም ለዘበት፣

እርሱ እንደሁ አይሞታት!

……………….

1956

እንቅልፍ አልባ ሌሊት

ሌሊቱ ረዥም ነው፣

ድቅድቅ ነው ጨለማው፣

ከለ ለት ሩጫ፣

አረፍ የሚሉበት፣

ፀጥ የተባለበት፣

ዝም የነገሰበት።

ይመስለኛል ለእኔ… ዋ እኔን!

ይብላኝ!

ለዚያች ብኩን ነፍስ፣ ዕረፍትን ከቶ ለማታውቅ፣

ይብላኝ!

ለተሰቃየችው ልብ፣ በድቅድቅ ጨለማም ቢሆን፣ ክፉኛ

ለምትደልቅ።

ይብላኝ!

ለዚያ ዕረፍት ላጣ አዕምሮ፣

እርጭ ባለ ሌሊት፣ ጣልቃ ሚገባ አሳብሮ።

የጨለማን ግርማ ሞገስ፣

ያለፍርሃት ለሚገስ፣

ሃሳብን በሃሳብ ለሚቀሰቅስ፣

ስቃይን በስቃይ ለሚያስዳስስ።

ይመስለኛል ለእኔ… ዋ እኔን!

ሰላማዊው ሌሊት እንዲህ የሚያልፍ፣ የአዲስ ቀን ህይወትን

ጀባ ብሎ፣

ከእንቅልፍ አልባ ሌሊት ጋር አዳብሎ።

……………….

1959

ግጥም

ጭፍግግ ብዬ፣

እንደ ሐምሌ ዳመና ክረምት

ስቅይት እያልኩ፣

ብቻዬን በብቸኝነት

ስረግም

የህይወትን ባዕድነት

እኔ!

…………..

1959

መንታ ሃሳብ (“ወስዋስ”)

ከነፍን በጨለማው ውስጥ፣ የዋህ ውበትን ትተን፣

ጥሬውን አገር ቤት፣ እርጥቡን ባላገር እንደዘበት አልፈን።

ነዳን በጨለማው ውስጥ፣

ስልጣኔና ከተማው፣ ያለው ከኋላችን ነው፣

ከሃሜት ከነድብርቱ፣ ከነግሳንግስ ኳኳታው።

ግና!

የተጨነቀች ነፍስ፣ መውጫዋን ሁሌ ትሻለች፣

ቀለም፣ ጣዕም ከሌለው ባዶ የከተማ ህይወት፣

አምላኬ ሆይ አውጣኝ እያለች።

ሆኖም!

ሰላም ከቶ የት አለ፣ ከህይወት ማምለጥ አይቻል፣

አንዴ ዘው ብለው ከገቡ፣ ከድቅድቁ ደይን መሃል።

ከዚያማ!

ማመንታት የሚባል የለም፣ ወደ ላይ ወደታች ሌላ፣

ወደፊት ብርሃን የለ፣ ተስፋም ከወደኋላ።

…………

1959

ትዝታ

ያ ትናንት፣

ባለፈ ትውስታ የተጨናነቀው፣

በአዕምሮአችን ጓዳ ይዘን ያስቀረነው፣

ያላሽቀነጠርነው፣

ከቶ ምንም የለው፣

ከትዝታ በቀር፣

ናፍቆትም ጥላቻም፣ ዝምታን ለመስበር።

ራስ ወዳዶቹ ጠርጣሪ ዓይኖችሽ፣

ሰው እንደተራቡ አፍጥጠው ያዩኛል፣

ዘወትር በህልሜ እንቅልፍ ይነሱኛል።

…………

1959

ዝምታ

ዝምታ ጥልቅ ነው፣

መስፈሪያ የሌለው አይለኬ ነገር፣

ዝምታ ሃያል ነው ባለ ግርማ ሞገስ፣

በእንቶ ፈንቶ ወሬ፣ በሃሜት በጉራ

ከቶ ‘ማይገሰስ።

ዝምታ ውበት ነው፣

እውነት ናት ዝምታ፣

ለምን? የተባለ እንደሁ፣

እውነት ውበት ናታ።

ዝምታ ሰላም ነው፣

ሰላም፣ ፍፁም ሰላም፣

ደስታ ነው ፍስሃ፣

በእኛ ርካሽ ህይወት፣ ከቶ ያልተበረዘ፣

እንባ ዝምታ ነው፣

ፈገግታም እንዲሁ፣

ፍቅርም ዝምታ ነው፣

ሞትም እንደዚሁ።

ዋአአአአአአአ…….!

ምነዋ ህይወትም፣ ብትሆን ላንድ አፍታ፣

ንጽህት እንደ ዝምታ።

……………….

1959

ዘላለማዊው

ካሣ አባ ታጠቅ

ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው

የቋጥኙ ላይ ሬሳ

የዚያ አንበሳ

የካሳ

በመቶ ዓመቱ ቢያገሳ

ስንቱን ስንቱን ቀሰቀሰውሳ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top