ጥበብ በታሪክ ገፅ

የተሰራው መንገድ ለስትራተጂ ውጊያእንጂ፤ ሀገሪቷን ለመርዳት የታሰበ አይደለም

ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ

አቤቱ እያሱ 5ቱን ደምቦች ባሻሻሉበት ዓመት አክሊሉ ሀብተወልድ ቢሸፍቱ ወረዳ “ደምቢ” ከተባለች ቀበሌ ተወለዱ። አካባቢውን ለማየት ወደዚያ ተጉዠ ነበር። አክሊሉ እስከ ሰባት ዓመታቸው ድረስ ያደጉበት የደምቢ ሜዳ ዛሬም ህፃናት ይቦርቁበታል።

 አክሊሉ ስድስት ዓመት ሲሆናቸው አባታቸው አለቃ ሀብተወልድ በሞት ስለተለዩዋቸው ስለእሳቸውና ስለ ወንድሞቻቸው የወደፊት ህይወት የተጨነቁት ታላቅ ወንድማቸው መኮነን ሀብተወልድ ሀላፊነት ወሰዱ። መኮነን ያንጊዜ ዕድሚያቸው ሃያ አምስት ሲሆን በጉምሩክ ዋና መሥራቤት የሒሳብ ሹም ሆነው ተሸመዋል። እነ አክሊሉን አዲስ አበባ አምጥተው ለማስተማር ያስባሉ። ይሁን እንጂ ትንንሾቹን ልጆች ለመውሰድ ቀላል አልሆነላቸውም። ኋይለኛ እንደሆኑ የሚታወቁት እናታቸው እመት ያደግ ደጉ ፍልፍሉ ልጆቻቸው በድቁና እንዲያገለግሉ ፈልገው ነበር።

 መኮነን አዲስ አበባ ደርሰው አዲሱን ስራቸውን ተረክበው ሁለት ወር ቆይተው ከእናታቸው ጋር የገናን በዓል ለማክበር ይመለሳሉ። ታኅሳስ 28፣ 1911 ዓም ላይ ነበር ቤት ሲደርሱ ትንንሾቹን ወንድሞቻቸውን አላገኙዋቸውም፤ የት እንደሄዱ ይጠይቃሉ። መክብብ አካለወርቅ እና አክሊሉ ሀብተወልድ እንጠጦ ራጉኤል ትምህርት ላይ እንደሆኑ ይነገራቸዋል። ይደነግጣሉ። እሳቸው ወንድሞቻቸው አዲስ አበባ ሄደው ዘመናዊ ትምህር እንዲማሩ ይመኙ ነበር። እናታቸው ሀሳቡን አልተቀበሉም። ልጆቹ የቤተ-ክርስቲያን አገልጋይ መሆን እንዳለባቸው አምነዋል። መኮነን ዘዴ ፈለጉ። የእናታቸው የንስሃ አባት መምሬ ገብረዮውሃንስ ወደ አሉበት ሄደው አማላጅ እንዲሆኗቸው ጠየቁ። እመት ያደግደጉ በቀላሉ ባይስማሙም ቆይተው ትንሹ አክሊሉ እንዲሄድ ፈቀዱ።

 ህልም፣ ጉዞ እና ትምህርት

መኮነን ሀብተወልድ ሌላ ችግር ገጠማቸው። አክሊሉ ከወንድሞቻቸው ተለይተው እንደማይሄዱ ተናገሩ።የወንድሞቻቸውም ሃሳብ ተመሳሳይ ሆነ። ሌሎችም ከሁለት ወር በኋላ እንደሚወስዷቸው ሊያሳምነዋቸው ቢሞክሩም ወንድማማቾቹ ፍቃደኞች አልነበሩም።ሦስቱንም ትተው ወደ አዲስ አበባ ይመለሳሉ። የዛን ሰሞን እናታቸው እመት ያደግድጉ ህልም ያልማሉ። መኮነን ሀብተወልድ በክብር ልብስ አሸብርቀው ወርቀ ዘቦ የተለጠፈበት ካባ ደርበዋል። ባርኔጣ አድርገዋል። ሦስቱን ወንድሞቻቸውን አስከትለው ታላቁን ቤተ-መንግሥት እየዞሩ መሬት ያስለካሉ እያስለኩ ይሰጣሉ። ከህልማቸው ሲነቁ ለህልማቸው ፍቺ ፍለጋ አልሔዱም። የልጆቹ ዕድል በታላቅ ወንድማቸው እጅ መሆኑን ፈጣሪ እንደነገራቸው አወቁ።

 መኮነን ሀብተወልድ መልዕክቱ ደረሳቸው። ተደሰቱ። መክቢብ አካለወርቅ እና አክሊሉ ቅዳሜ ጥር 14፣ 1911 ዓም ከእንጠጦ ራጉኤል ተነስተው በበቅሎ አዲስ አበባ ደረሱ። ከሁለት ቀን በኋላ ሦስቱም ዳግማዊ ምኒሊክ ትምህር ቤት ገቡ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ፈጽመው ለከፍተኛ ትምህር ወደ ፈረንሳይ ሀገር እስከተላኩበት ድረስ ወንድማቸው ቤት ለ8 ዓመታት ሲኖሩ “ ምክር መስጫ ” የተባለ ፕሮግራም ይዘጋጅላቸዋል። ፕሮግራሙ አቶ መኮነን በእነ አክሊሉ አእምሮ ውስጥ የሀገር መውደድ ስሜት እንዲጎላ እና ሀገርን ወደ ሥልጣኔ የማራመድ ፅኑ አቋም እንዲኖራቸው ለማድረግ የታሰበ ነበር።

 አክሊሉ በግብፅ ሀገር ካለው የፈረንሳይ ሊሴ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተምረው በፓሪስ እውቁ የሰርቦን ዩኒቨርሲቲ በሕግ ኤል ኤል ቢ ተመርቀዋል። ትምህር ላይ እንዳሉ ሀገራቸው ጥንታዊ እና ነፃነቷን ጠብቃ የቆየች መሆኗን ለአገኙት ሁሉ ተናግረዋል። ጥረታቸውን የተረዱት ጃንሆይ ኋላ ላይ በጄኔቭ የኢትዮጵያ ዴሊጌሽን ዋና ጸሐፊ እንዲሆኑ መርጠዋቸዋል። ከእነዚህ በኋላም አክሊሉ ሀብተወልድ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ በፕሬስ አታሼነት ሠርተዋል።

ወደ ሀገር ቤት መመለስ እና ኃላፊነት

አቶ አክሊሉ ሀብተወልድ ከፈረንሣይ ወደ ሀገር ቤት ለመግባት ሲሉ ችግር ያጋጥማቸዋል። ፓስፖርታቸውን ይነጠቃሉ። የፈረንሳይ መሪ የነበሩት ላቫል ለጀርመኑ መሪሂትለር በመወገን ይክዷቸዋል።

አቶ አክሊሉ ሌላ ፓስፖርት ለማውጣት ይገደዳሉ። “ቶማስ ወልድ” የሚል ስም ተጠቅመው ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳሉ። ለንጉሱ የደረሰባቸውን ሁሉ ያስረዷቸዋል። ጃንሆይ ለአክሊሉ በጽሕፈት ሚኒስቴር ውስጥ አንድ ቢሮ ይሰጧቸዋል። ገና በ32 ዓመታቸው ንጉሡን በህግ ጉዳዮች ላይ ማማከር ይጀምራሉ። ለመሪዎች የሚለውን ዲስኩር እና መልዕክት የማሰናዳ ኃላፊነት ይሰጣቸዋል። ከእዚህ በኋላ የጽሕፈት ሚኒስቴር ምክትል ሆነዋል።

 ከ1933 ዓም. በኋላ ባንክ በሀገራችን በዘመናዊ መልክ ሲመሰረት የእንገሊዝ ሰዎች ተሳትፈው ነበር። ብሔራዊ ባንክ ሲቋቋም በእነሱ ቁጥጥር ሥር ለማድረግ አስበው ዋና ጽሕፈት ቤቱን እንግሊዝ የቦርድ ኃላፊዋን ደግሞ ንግስታቸውን ለመሾም ፈልገው ነበር። አቶ አክሊሉ ሀብተወልድ ሐሳቡን በመቃወም የባንኩ ዋና ጽሕፈት ቤት በሀገራችን እንዲሆን እንዲሁም የባንኩ የቦርድ አባላት የእኛው ሰዎች ሆነው እንዲያገለግሉ አስወስነዋል። (ይህን በግል ማስታወሻቸውም ላይ ጽፈውታል)

 ሀሳብ እና ስኬት

 የተ.መ.ድ ቻርተር ከመፈረሙ በፊት በህጎች ላይ የማሻሻያ ውይይት ለማድረግ ይቀርባል። ያኔ አቶ አክሊሉ ሀብተወልድ ከሥራ ባደርቦቻቸው ጋር ወደ ሳንፍራንሲኮ ይሔዳሉ። ጉባኤው ሲጀመር ሀገር ጥቃት ሊደርስብኝ ይችላል ካለች የሴኩሪቲ ካውንሲሉ መሰብሰብ እንደሚኖርበት ሀሳብ ያቀርባሉ። አሜሪካኖች በምን ማስረጃ ተደግፈን ነው ሀገር ችግር ውስጥ መውደቋን የምናውቀው በሚል ለመከራከር ይሞክራሉ። አቶ አክሊሉ ታሪክ ጠቅሰው በ1929 ጣሊያን የፈፀመቸውን ግፍ በተመለከተና ሀገራቸው ለሊግ ኦፍ ኔሽን አቤቱታ ብታቀርብም ሰሚ ማጣቷን ያስታውሳሉ። ሀሳባቸው ተቀባይነት ያገኛል። ሰኩሪቲ ካውንስሉ ከእዚህ በኋላ መሰብሰብ መጀመሩ ይነገራል። ከስብሰባው በኋላ አቶ አክሊሉ ፈጥነው ወደ ሀገር ቤት አልተመለሱም። ሀገራቸው አየር መንገድ እንዲኖራት በመፈለግ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ስምምነት ፈጥረዋል። ጥረታቸውም ተሳክቶ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተመስርቷል።

 ክርክር እና ካሳ

በ1938 ዓም. አቶ አክሊሉ የፓሪሱ የሰላም ኮንፈረንስ ላይ ይገኛሉ። በወቅቱ የኢትዮጵያ የቅርብ ወዳጅ የተባሉት አሜሪካ፣ መስኮቭ፣ እንግሊዝና ፈረንሳይ ባሉበት ጣሊያን በሀገራቸው ላይ ላደረሰችው ጉዳት የጦር ካሳ ለማስከፈል ትሟገታለች። ተወካዮቻቸው፣ ቤት መብራት፣ መንገድ መስራታቸውን በስዕላዊ መግለጫዎች አስደግፈው ተከራከሩ።

አቶ አክሊሉ የተሰራው መንገድ ለስትራቴጂ ውጊያ ተብሎ እንጂ ሀገሪቱን ለመርዳት የታሰበ አይደለም በማለት አስረዱ። አብዛኞቹ ተሳታፊዎች የአቶ አክሊሉ ሀብተወልድ ክርክርን አደነቁ። ከጉባኤው በኋላ ጣሊያን 25 ሚሊዮን የጦር ካሳ እንድትከፍል ተወሰነ።

የጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ መጨረሻ

 (የሕግ ምሁሩ አቶ ተሸመ እንዳጫወቱኝ) አቶ ተሸመ በንጉሡ ዘመን ሚኒስቴር ዴኤታ ነበሩ። በ1966 ዓም. ከየካቲት ወር ጀምሮ የመሳፍንቱ እና የመኳንንት ወገኖች ስልጣን ለመያዝ ግብግብ ገጠሙ። በሌላ በኩል የወታደሩ የተማሪውና የሌሎችም አመፆች የጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉን ካቢኔ አስጨነቀ። ያኔ ከእሳቸው የተሻለ የሚታመን ሰው ንጉሡ እንዲያስቀምጡ በመናገር ሥልጣናቸውን በገዛ ፍቃዳቸው ይለቃሉ።

ማስታወሻ

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌደሬሽን እንድትቀላቀል ለ7 ዓመታት ደክመዋል። ልፋታቸው ውጤት አምጥቷል።

• ትምህርታቸው ጥልቅ አስተሳሰብ እንዲይዙ፣ የዲፕሎማሲ እይታ እንዲኖራቸው፣ ቢያግዛቸውም በንባብ ያገኙት ዕውቀት ከፍ ያለ ነበር። ሁለት ሺህ የሚጠጉ መጽሐፎች ነበራቸው። በወታደራዊ መንግሥት ትዕዛዝ ተቃጥለዋል። (የወንድማቸው ልጅ አቶ አምዴ እንዳጫወቱኝ)

 • ሚያዚያ 4፣ 1918 ዓም ለፓርላማ የሚኒስትሮቻቸውን ሹመት ሲያቀርቡ ሃያ ሦስት ደቂቃ የሚፈጅ ንግግር አሰምተዋል። አንድ ሚኒስቴር የተሰጠውን ኃላፊነት ካልተወጣ በሌላ ሚኒስቴር እንደሚተካ ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንዲሁ የተቀበለውን አደራ በትክክል ካልተወጣ ቦታውን መልቀቅ እንዳለበት ተናግረዋል።

 • ምግብ እየበሉ ለስላሳ ሙዚቃ መስማት ያስደስታቸዋል።

 • ከፈረንሳዊቷ ባለቤታቸው ማዳም ኮሌት ጋር ሲደንሱ ፎቶግራፍ ተነስተዋል። (የታንጎ እና የቫልስ ዳንስ እንደሚወዱ ተነግሮኛል።)

• ከቤት እንስሳት ለውሻ የተለየ ፍቅር ነበራቸው።

 • ለመዝናናት ወደ ቢሸፍቱ ሆራ መሔድን ይመርጣሉ።

• የቅርብ ወዳጆቻቸው በአይቬሪኮስት የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አቶ መሸሻ ኃይሌ፣ ጀነራል እያሱ እና አቶ ጋሻው ዘለቀ ነበሩ።

 የጽሑፉ አቅራቢ እዝራ እጅጉ ሙላት ለ18 ዓመት በጋዜጠኝነት ያገለገለ ሲሆን የ8 ሰዎችን ግለ ታሪክ በዲቪዲ እና በኦዲዮ ሲቲ አሳትሟል። ተወዳጅ ሚድያ ; የተሰኘ የራሱን ድርጅት መሥርቷል።በጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ የህይወት ታሪክና ሥራዎቻቸው ላይ ለ2 ዓመታት የምርምር ጽሑፎችን አቅርቧል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top