ስርሆተ ገፅ

“ከሌሉን ነገሮች ይልቅ ያሉን ነገሮች ይበልጣሉ” ሲኒማቶግራፈር ሰው መሆን ይስማው

በርካታ ፊልሞች እና የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች ላይ ከካሜራ ጋ የተገናኘ ሥራ ሠርቷል፡፡ የፊልም ጽሑፍ ጸሐፊ እና አዘጋጅ ነው፡፡

ስለ ሲኒማቶግራፊ ልትነግረንኝ ትችላለህ?

ሰው መሆን፡- ሲንማቶግራፊ ስሜት ነው። ልክ እንደትወና፣ እንደ ዝግጅት እና እንደሌሎችም የኪነ-ጥበብ ቅርፆች ሁሉ፣ በካሜራ፣ በብርሃንና በሌሎች ነገሮች ስሜትህን ለሌሎች የምታጋባበት፣ ለሌሎች ሃሳብህን የምትገልጽበት መንገድ ነው።

 ሲኒማቶግራፊ ውስጥ በርካታ ጉዳዮች አሉ። አንድ ስዕል ውስጥ መብራት አለ- ብርሃኑ፣ ቅንብር [composition]፣ ምስሉ የሚዋቀርበት፣ ገፀ- ባህርያቱ የሚቆሙበት መንገድ፣ ሌሎችም በርካታ ጉዳዮች አሉ። እናም ሲኒማቶግራፊ ስሜትንና ሃሳብን ለሌሎች የማጋባት ትልቁ የፊልም መሳሪያ ነው።

 በሃገራችን እየሰራንበት አይደለም። በእርግጥ አሁን ቴክኖሎጂው እያደገ ሲመጣ የካሜራው ሁኔታ ከፍ እያለ ሲታይ በትንሽ ብርሃን የተለየ ዓይነት ድባብ ለመፍጠር የሚዳረጉ ጥረቶች አሉ። ሲኒማቶግራፊ የሃሳብ ጉዳይ ነው። ቆንጆ ምስል ስለተቀረፀ ብቻ ታዋቂ ሲኒማቶግራፈር መሆን አይቻልም።

በሀገራችን ለስኒማቶግራፊ አስቸጋሪ እና ምቹ የምትላቸው የትኞቹ ናቸው?

 ሰውመሆን፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያስገርሙ ምስሎችን ማግኝት ይቻላል። ለምሳሌ ቁልቢ ላይ ካሜራችንን ማክሰኞ ገበያ ላይ ብናጠምድ አረንጓዴ፣ ሰማያዊ እና የተለያዩ ቀለማትን የለበሱ ገበያተኞችን ምስል በቀላሉ እናገኛለን። በምስል ደረጃ በሃገራችን ማራኪ የሆኑ በርካታ ነገሮች አሉን።

በሌላ በኩል ፈተናዎች አይጠፉም። አንዱ የእውቀት ማነስ ይመስለኛል። ባለሙያው ራሱን ከማስተማር ውጪ አማራጭ የለውም። ከኢንተርኔት ነው ብዙ ነገሮችን የምንማረው ያ ደግሞ ከወጪ አንፃር ውድ ነው። ሌላው ጥልቅ ምስል መውሰድ የምንችልበት ካሜራ የለንም። ትላልቅ የመብራት መጠቀሚያዎች አናገኝም።

 “በኬኒያ ባለሙያዎች መገልገያ መሣሪያዎቹን እንደተራ ዕቃዎች በእጃቸው፣ በሻንጣዎቻቸው አንጠልጥለው ይዘዋቸው ይገባሉ። በሃገራችን ለካሜራ ሁለት ሚሊዮን ብር ቀረጥ ሊከፈልበት ይችላል ”

በኬኒያ ባለሙያዎች መገልገያ መሣሪያዎቹን እንደተራ ዕቃዎች በእጃቸው፣ በሻንጣዎቻቸው አንጠልጥለው ይዘዋቸው ይገባሉ። በሃገራችን ለካሜራ ሁለት ሚሊዮን ብር ቀረጥ ሊከፈልበት ይችላል። የሃገራችንን ውበት እንድናሳይ የሚፈለግ አይመስለኝም። ያም ቢሆን ከሌሎች ነገሮች ይልቅ ያሉን ነገሮች ይበልጣሉ።

ያሉንን መልካም ነገሮች ወደ ቋንቋ ቀይሮ ማቅረብ ላይ ደካሞች ነን። አዳዲስ ነገሮችን የመሞኮር እና ራስን ማስተማር ላይ ክፍተት እንዳለ ይሰማኛል።

 ስለ ዕይታ እና ሲኒማቶግራፊ ቅርበት የምትለኝ ካለ?

ሰውመሆን፡- ሲኒማቶግራፈር ስትሆን ብዙ ነገሮች በስርዓት የተቀመጡ ቅንብሮች እንዲሆኑ ትፈልጋለህ። ዓይኖችህን የሚይዙ ነገሮችም እንዲሁ ናቸው። ለምሳሌ የተንጣለለ ትልቅ ቪላ ቤት ጎን፣ የፈራረሰች ትንሽ ጎጆ፣ ብትመለከት ይህን ልዩነትዝምብለህ ማለፍ አትችልም። መጀመሪያ ያየኸውን በካሜራ ትቀርፀዋለህ። ወይም እቀርፀዋለሁ ብለህ በዕዝነ ልቦናህ ታስቀምጠዋለህ።

 ከሰራኸው የተሻሉ ናቸው የምትላቸው የትኞቹ ናቸው?

 ሰውመሆን፡- በጣም የምወደው አንዴ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ሲጠየቅ የመለሰውን ነው። “የትኛውን ስራህን ትወዳለህ? ሲባል “የሚቀጥለውን ሥራዬን” ነበር ያለው። የሚቀጥለው ሥራህ እያደገ እየተሻለ እንዲሔድ ትመኛለህ። እኔ የተሻለ ነገር ለመሥራት የጣርኩት የሰለሞን ቦጋለ ፊልም ላይ ነው። ገና አልወጣም። ከእዚህ ሌላ “ባላገሩን”፣ “ቀሚስ የለበስኩ ለታ”፣ “አዲናስ”፣ “ዓለሜ” የምወዳቸው ናቸው።

ስለ ፊልም ትምህርት ቤት ምን ሀሳብአለህ?

ሰው መሆን፡- የፊልም ትምህርት ቤቶች ያስፈልጉናል። ይህን ሳስብ ከሀገር ወጥቼ መማርን እመኛለሁ። በእርግጥ አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች እየጀመሩ ናቸው። ከውጭ ሀገር ሲኒማቶግራፈሮችን፣ አዘጋጆችን እያስመጡ ስልጠና ቢሰጥ ጥሩ ይመስለኛል። [mandela’s gun] የሚል ፊልም ላይ ተሳትፌአለሁ። የአዘጋጁ አስተርጓሚ ነበርኩ። ከእነሱ ብዙ ተምሬአለሁ።

ለጀማሪዎች ምን መልዕክት አለህ?

 ሰው መሆን፡- ሲኒማቶግራፊ ላይ የተፃፉ በርካታ መፅሓፎች አሉ። እነሱን ቢያነቡ መልካም ነው። ፊልም ማየት እና መስራት አንዱ የመማሪያ መንገድ ይመስለኛል። በቀላሉ ካሜራ ተከራይተው ከተማ ውስጥ እየተዟዟሩ በመቅረፅ ኤዲት ቢያደርጉ ብዙ ነገሮች መማር ይችላሉ። በተንቀሳቃሽ ስልክም ቢሆን መሞከር፤ በተጨማሪም ፎቶግራፍ ማንሳት፣ በሲኒማቶግራፊ ማራኪ ስለተባሉ ትዕይንቶች ከሰዎች ጋር ማውራት፣ አሰራራቸውን መፈተሽ በሲኒማቶግራፊ የታጩ ፊልሞችን ማየት ከካሜራ ጀርባ ያሉ ቪዲዮዎችን፣ የሥዕል ኤግዚቪሽኖችን መመልከት ልምድን ያጠናክራል።  የተለያዩ ቪዲዮዎችን ከተመለከቱ በኋላ ሳቢ የሆኑ ምስሎችን በመምረጥ እኛ ብንሆን እንዴት እንሰራቸዋለን ወይም ዕድሉን ብናገኝ እንሞክራቸዋለን ብለው ማሰብ አለባቸው። በእዚህ መንገድ አቅማቸውን ሊያሳድጉ ይችላሉ ብየ አስባለሁ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top