ከቀንዱም ከሸሆናውም

ሹማምንትና ቴያትር

“ፋቡላ /ተረት በተባለው ድርሰቴ ውስጥ የተመሰሉ አውሬዎች እርስ በርሳቸው ተነጋጋሪዎች አስመስዬ በፍጥረት አዘጋጅቼ በቲያትር ባሳይ የሚቀል ዘዴ መሆኑ ታወቀኝ። እንደዚሁ አደረግሁና ጥቂት መኳንንቶች በነበሩበት /በራስ ሆቴል/ አሳየሁ። የታተሙትም መጽሓፎቼ በገቢያ እንዲሸጡ አደረግሁ። በጣም ተፈላጊዎች ስለሆኑ ባንድ ቀን ውስጥ ብቻ 300 ያህል መጽሓፎች ተሸጡ። ወዲያው ወሬው ለንግስት ዘውዲቱ ደረሰላቸው። ወሬውን ያደረሱላቸው ሰዎች በመሆናቸው እሳቸውን የሚነካና የሚቃወም ሐሳብ ያለበት አስመስለው ድርሰቴን ተረጎሙላቸው። ንግስትም በየዋህነት እውነት መሰላቸውና በኔ ላይ ተቀየሙ። ወዲያው መቀየማቸውን ነግረው ለልኡል አልጋ ወራሽ የወቀሳ ስሞታ ተናገሩ። ልኡል አልጋ ወራሽም አስጠርተውኝ የንግስትን መቀየም ገለፁልኝ። መጽሓፎቼንም ሁሉንም ለልጅ መኮነን እንዳልካቸው እንዳስረክብ አዘዙኝ። የተሸጡትም መጽሓፎች እየተፈለጉ እንዲመጡ አዘዙ።

እኔም ከሦስት ሺህ መጽሓፎች 300 መቶ ብቻ ሲቀሩ ሁሉንም ለልጅ መኮነን እንዳልካቸው አቀረብኩ” ይላሉ።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ተውኔት የሆነውን የአውሬዎች ተረት /ፋቡላ/ መጽሐፍ የደረሱት ተ/ሃዋሪያት ተ/ ማሪያም ሲሆኑ በላፎንቴን ድርሰት ላይ የተመሠረተም ነው። ደራሲው በተረትና ምሳሌ አስመስለው በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ይታይ የነበረውን የስልጣን ብልግና ኋላ ቀርነትና ደካማ አስተዳደር ያመላከቱበት ነበር።

በመድረክ ቀርቦ ከታየ በኋላ ምንም እንኳን ታላቅ አድናቆት ያተረፈ ቢሆንም የሚነካካው የዚያን ጊዚያቱን ሹማምንትና ባላባቶች ስለነበረ እነዚሁ ሰዎች በትዕግስት አላለፉትም። ሁለተኛም እንዳይታይ ታገደ።

 አምሳሉ አክሊሉ “አጭር የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ ታሪክ”

የባንክ ብድር

የኢትዮጵያ ባንክ አዲስ አበባ 1900

የኢትዮጵያ ባንክ አዛዥ አዲስ አበባ እንደዚህ እንደውሉ የጠየቅሁዎትን መቶ ብር ያበድሩኝ። ይህንንም ገንዘብ ከነ ወለዱ በሐምሌ ወይም አስቀድሜ ባመት በመቶ ብር ወለዱ 15 ብር ጭምር ታስቦ እከፍልዎታለሁ። በተረፈ ዋሴ አቶ እገሌ ይህንን የተበደርኩትን ገንዘብ ከነወለዱ ይከፍልዎታል። በቀኑ ያልከፈልኩ እንደሆነ ግን ወለዱም ዋና ሆኖ መቶው ብር በወር በወሩ ብር ተሩብ ብር ተሩብ ይወልዳል። ይኸውም ወለድ ደግሞ በወሩ ዋና ይሆናል።

 እላይ እንደተባለው መቶ ብር ዋስ መሆኔ ተበድረው አቶ ተሰማ በማናቸውም ምክኒያት የተበደረውን ብር ከነወለዱ በሰጡት ቀን ያልከፈለ እንደሆነ እኔው እራሴ ዋናውን ከነወለዱ እከፍልዎታለሁ።

 የጥንት ማስታወሻ፣ በአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የተጻፈ

 የከተማ ወሬ 1

ኅዳር 29 ቀን 1918 ዓመተ-ምህረት የበዓለ ወልድ ዕለት በመድሃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የደጃዝማች ጌታቸው ልጅ ክርስትና ነበር። ስለዚህ ክርስትና ለማቋቋም የተሰበሰቡ ብዙ መኳንንት እጅግም የሴት ወይዘሮች ነበሩ።

ነገር ግን አቶ ተወልደ ብርሃን መድኅን በብርሃንና ሰላም እንዳስታወቁን በቀድሞ ልማድ ታስረናልና እንኳን እኔ ጌቶችም እንዳያይዋቸው ፊታቸውን ሸፍነው ነበር። ደግሞ ከልብሳቸው በላይ መልካሙ አቋቁማቸው እንዳይታይ በመጋረጃ ስለነበሩ እነ ወይዘሮ እገሊት ነበሩ ብዬ ለመጻፍ አልሆነልኝም። ስማቸውንም የጻፍኋቸውን አላየኋቸውም። ግን ጌቶች አሽከሮቻቸውን ባዩ ጊዜ እነሜቴ ይሆናሉ ብለው እጅ ሲነሱ እኔም አብሬ እጅ ነስቼ ነበርና በወሬ ነው እንጂ አይቻቸው አይደለም። ስለዚህ ስማቸውን በያንዳንዳቸው ለመፃፍ አልሆነልኝም እንጂ የሴት ወይዘሮችስ እጅግ ብዙ ነበሩ። ወይ ዓለም እጅግ ታስቸግራለች እስቲ የሮፓ ሴቶች ደረታቸውን መግለጥ የኛ ሴት ወይዘሮዎች ፊታቸውን መሸፈን የሚያስደንቅ ነገር ነው። ሽማግሌ ቢገኝ የኒህን የፊታቸውን መሸፈኛ ለኒያ ደረት መሸፈኛ መስጠት ነበር። ግን ምን ይሆናል ሰው ልማዱን ይወዳልና እንደ ፀሐይ የሚያበራ ፊታቸው እንዴት ነውር ያለበት ይመስል ይሸፈን። መሸፈንስ እንኳን ለነሱ ለሚከተሏቸው ገረዶችም አይገባ። ይህ ልማድ መቼም በወንዶች ቅናት የተነሳ በቱርክ አገር ነው የተጀመረው፤ ኋላ ወደ ግብፅ ኋላም ወደኛ ደረሰ። አሁን ግን ቱርክ ትቷል። ሴቶችም ፀሐይ ወጣልን እያሉ ደስ ብሏቸዋል ይባላል። የመሸፈን መምህሮች ሲተውት ተማሮቹ ለምን አንተወውም? …

ሐሙስ ታህሣሥ 8 ቀን 1918 ዓ.ም.

ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ

ኢዩኤል ዮሐንስ

የዜማ ፍቅር ወይም የቴያትር መመልከት ፍላጎት ያለው ሁሉ ኢዩኤል ዮሐንስን ያውቃል። ወጣቱ በድምፅም ሆነ በድርሰት ችሎታው የሀገር ፍቅር ማኅበር ምሰሶ ለመሆን ችሏል። ይህ በተፈጥሮው ደራሲ የሆነ ጉብል ሲተርክ፣

 “ከእለታት አንድ ቀን በአዲስ አበባ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ በዲያቆንነት ሙያ ላይ ሳለሁ ሟቹ ክቡር አቶ መኮነን ሃብተ ወልድ ድምጼን ሠምተው በማስጠራት በሀገር ፍቅር ማኅበር እንድሰራና በእርሳቸውም ቤት እንድኖር አደረጉኝ፤ ጊዜውም 1935 ዓ.ም. ሲሆን ዕድሜዬ ሃያ ዓመት ነበር። ወዲያውም ድምጼ በራዲዮ እንደተሠማ ወላጆቼ ሰምተው በመናደድ በፖሊስ አሳድደው ያዙኝና ለቅኔ ትምህርት ወደ ጎጃም ላኩኝ። ከዚያም ሁለት ዓመት እንደተማርኩኝ ክቡር አቶ መኮነን ደግሞ በፊናንስ መኮነን አሳድነው አስመጡኝና ስራየን እንድጀምር አስደረጉኝ። ወላጆቼም እንዳይቀየሙኝ አጥጋቢ ምክር ሰጥተው ስላስታረቁኝ ልቤ ረግቶ መጫወቴን ቀጠልኩ። የመጀመሪያዋ ዜማየ ነፃነት ገዳሜ የተባለችዋ ናት። ዜማዋን ተጫወትኋት እንጂ የደረሷት ሟቹ አቶ ዮፍታሔ ናቸው ይባላል። እስከዛሬ ከ300 በላይ የሆኑ ዜማዎች ሰላሣ አምስት ቲያትሮች ሃያ አምስት የሚሆኑ ኮሜዲዎች በመድረስ ለህዝብ እንዲቀርቡ አድርጌአለሁ። ከዜማዎቹም መካከል “ያገር ፍቅር ትዝታው” የተባለውን አብልጬ እወደዋለሁ።

” በ1957 ዓ.ም. ከታተመው “አስደሳቾቻችንን እንወቃቸው” የተሰኘ መጽሔት የተወሰደ የከተማ ወሬ

ሚያዚያ 29 ቀን ከማታው 12 ሰዓት በትልቁ በአውራጃው መንገድ ብዙ ሰራዊት በየክፍሉ ሁኖ ጠርብ ጠርቡን እየያዘ ሎጋው ሽቦ ብሎ እየጮኸ ሲያልፍ ዘበኞቹን አልታገድም ብሎ አቅቶዋቸው መንገደኛውን ሁሉ ሲያስቸግር አመሸ። ጩኸቱን ሰምተን ነገሩን ብንጠይቅ በአቶ ፋሲካ ቤት ግብር ተጠርቶ ሲበላና ሲጠጣ የዋለ ሰራዊት ነው አሉን። ቀርበን ነገሩን ብንመለከት ሁሉም ሰክሮ ነበር። አንዳንድ አእምሯቸውን ጨርሰው ያላጡ የተሸነፉ ባልንጀሮቻቸውን እየደገፉ ይዘው ይሄዱ ነበር። አያሌ ትልልቆች ሰዎች በበቅሎ ተቀምጠው ርካብ መርገጥ፣ ዛብ መጨበጥ አቅቶዋቸው፣ ንፋስ እንደሚያወዛውዘው መቃ ሁሉ ከኮረቻው ወደ ቀኝና ወደ ግራ እየተወዛወዙ፣ ለሚደግፏቸው ሰዎች ሲያስቸግሩ ላይታው ያስደንቃል። አንዳንድ ሰዎችም ጨርሶ እንደደረቀ ግንድ ሁነው ለሳንሳ እየተሸከሟቸው ይሄዱ ነበር። አንዱም ሰውዬ ከጉምሩክ በታች ባለው መንገድ በተነጠፈ ድንጋይ ላይ እንደሞተ ሆኖ ወድቆ ደርቆ የሚያነሳው ታጥቶ ወንድሙ የተባለ ዘበኛ ባጠገቡ ቁሞ ነበረ። የአቶ ፋሲካ የለጋስነታቸውና የሲሳዩ ብዛት እጅግ አድርጎ አስደነቀን፣ ግሩም ነው። ግን ሰውነታቸውን አጥተው እንደ ግንድ ደርቀው ለሳንሳ ሰው ተሸክሟቸው ይሄዱ የነበሩና የሚያነሳቸው አጥተው በየመንገዱ ወድቀው የቀሩ፣ አምባ ጓሮ አንስተውም የተፈነከቱትን በማየት በጣም አዘንን።

 ሰጭ በለጋስነቱ ብዙ መብልና መጠጥ ቢያቀርብ የተጠራ ሰው ልኩን አውቆ እስኪጠግብ ድረስ መብላት፣ እስኪረካ ድረስ መጠጣት ይገባዋል እንጂ ከልክ አልፎ በመብላትና በመጠጣት አእምሮውን አጥቶ ላይታው እስኪያስቀይም ድረስ መበላሸት አይገባውም።

 መብልና መጠጥ ጤናችንን እንድንጠብቅ በህይወት እንድንኖር ተሰጠን እንጂ ጤና አጥተን ህይወታችንን ልናበላሽበት እንዳልተሰጠን ማሰብ ይገባናል።

 ልኩን አለማወቅ ከእንስሳ መባስ እንደሆነ ማንም አያጣውም። ማር ይስሐቅም “ወእምከመ ረከብኮ ለመዓር ብላዕ እምኔሁ በዓቅም ሥሩዕ። ከመ ኢትቂዕ በጊዜ ጽጋብ።” (ማር ብታገኝ በመጠን ተመገብ። አብዝተህ ተመግበህ እንዳይወጣብህ) ብሏልና ከልክ አንለፍ።

 ሐሙስ ግንቦት 4 ቀን 1919 ዓም ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ

የእቴጌ ጣይቱ ጥሪ

እቴጌ ጣይቱ የዴር ሥልጣንን በር ከማስከፈታቸው ቀደም ብሎ በ1895 ዓ.ም. በኢየሩሳሌም ትልቅ ደብርና ምድር ቤት ያለው ቤተ-መንግሥት በሠላሳ ስምንት ሺህ ብር ገዝተው አሠርተዋል። በዛው ዘመን በኢየሩሳሌም በሚኖሩ የኢትዮጵያ መነኮሳት መካከል የተነሳውን ፀብ ለማብረድ ሲሉም እንዲህ ሲሉ ደብዳቤ ጽፈው ልከውላቸዋል።

 “የተላከ ከእቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዮጵያ፣ ይድረስ ከማኅበረ-ዴር ሡልጣን ወደብረ-ገነት ዘኢየሩሳሌም እንዴት ሰንብታችኋል እኔ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ። እናንተ ብትስማሙ እርስበርሳችሁ ብትፈቃቀሩ አንድነታችሁን ብታፀኑ ይሻላል እንጂ ትግሬ የብቻ ነው ሽዋ የብቻ ነው በጌምድር የብቻ ነው፣ ጎጃም የብቻ ነው እያላችሁ ጎሣ እየለያችሁ ብትጣሉ ምን ትረባላችሁ?….

አሁንም ስለ እግዚአብሔር ብላችሁ እናንተም እርስበርሳችሁ ተፋቀሩ ለእኛም ዳዊት ድገሙልን።”

ሰኔ 29 ቀን 1900 ዓም. አዲስ አበባ ተጻፈ

 “የነገሥታት ገድሎችና የፍቅር ታሪኮች መጽሐፍ ተቀንጭቦ የተወሰደ”

የሚአስደንቅ ትያትሮ

በኅዳር 23 ቀን እሑድ በዳግማዊ ምኒሊክ ተማሪቤት ከአቶ ዮፍታሔ የተጻፈ እጅግ የሚያስደንቅ ትያትሮ ነበረ። አሳቡም ቤተ- ሰዎች ሁሉ ደንቆሮዎች ሁነው ሳይስማሙ ሲጣሉ ሰምቶ አንድ ተማሪ ባለ መስማማት የሚገኘውን መከራ እንደሰበከና የቁምጥና ሕማም ያለባቸው ሰዎች ሁሉ ቦታ እንዲለይላቸው የሚያሳስብ ነበረ። የአዳራሹም ክፍል ሶስት ነበረ። በሶስተኛውም ክፍል እጅግ ብዙ ሕዝብ ነበረበት። በሁለተኛው ክፍል ጥቂት ሰዎች ነበሩበት። በመጀመሪያው ክፍል ግን ሶስት ወይም አራት ሰዎች ብቻ ነበሩ። ሕዝቡም በትያትሮው ማማር እጅግ ደስ ብሎት የመጀመሪያው ማዕርግ ተቀማጮች በማነሳቸው ቅር ብሎት ሔደ። ነገር ግን ከእንግዲህ ወዲህ ቦታቸው ባዶ እንዳይሆን ብርሃንና ሰላም ለባለቦታዎች ያሳስባል።

ሐሙስ ኅዳር 27 ቀን 1927 ዓ.ም. ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ

ከቀድሞ ማስታወቂያዎች

ማስታወቂያ

በርሻና በመስሪያ ሚኒስትር ውስጥ መንግስት ያወጣውን ደንብ እና ህግ ሳልተላለፍ፣ ደሀ ሳልበድል፣ የመንግስቱን ገንዘብ በጥንቃቄ ሠርቼ ቀድሞም ከሚሠራው ሠራተኛ ገቢ ገንዘብ አብልጬ አገባለሁ፣ የሚል ሰው እርሻና እመስሯ ምኒስቴር መጻፊያ ቤት ሁል ጊዜ ከጧቱ ከ3 ሰዓት እስከ 4 ሰዓት ድረስ፤ እየመጣ ቢነጋገር በደስታ እንቀበለዋለን። ደመወዙም እንደ ሥራው ገቢ እየታየ ይቆረጥለታል። ጥቅምት 11 ቀን 1918 ዓመተ ምሕረት። መኮንን ሀብተ ወልድ  ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ

በዘመን ቢራራቁም የመመሳሰላቸው ነገር

ቅዱስ ያሬድ

በተወለደ በሰባት ዓመቱ ለጌታ አደረ። የአጼ ገብረመስቀል ቢትወደድ ዥን አሰራሪ ዜና ገብርኤል ይሏል (ይባላል) ያደረለት ጌታ። “ጋሻ ቢያስይዙህ አትችል፣ ጦር ሾተል ቢያሸክሙህ አትችል ምን ትሆነን?” ብሎ መለሰው። ከዚያ ወዲያ እማራለሁ መጽሐፍ ብሎ እቤተ እግዚአብሔር ገባ። አመት ሙሉ መምህሩ ሳያውቀው ተቀመጠ። ከዚያ ወዲያ አወቁትና “ምንነው ምን ትሻለህ? ብለው ጠየቁት። እርሱም ሲል “እማራለሁ መጽሓፍ ብየ መጥቻለሁ፣ አቤቱ” ብሎ መለሰልዎ። “ንገሩት” አሉና አዘዙ። ሀ ሁ ሂ ማለት አውኮት አምስት ዓመት ተቀመጠ። “ፊደሉስ ታልገባኝ” ብሎ ሲሄድ እዛፍ ሥር አረፈ። እጥላ ተቀምጦ ሳለ ትል የዚያን ዛፍ ቅጸል እበላለሁ እያለ ሲወጣ ሲወርድ በሰባተኛው  ምን ትሻለህ? ብለው ጠየቁት። እርሱም ሲል “እማራለሁ መጽሓፍ ብየ መጥቻለሁ፣ አቤቱ” ብሎ መለሰልዎ። “ንገሩት” አሉና አዘዙ። ሀ ሁ ሂ ማለት አውኮት አምስት ዓመት ተቀመጠ። “ፊደሉስ ታልገባኝ” ብሎ ሲሄድ እዛፍ ሥር አረፈ። እጥላ ተቀምጦ ሳለ ትል የዚያን ዛፍ ቅጸል እበላለሁ እያለ ሲወጣ ሲወርድ በሰባተኛው ወጥቶ በላው። ያን አየና ተመልሶ ሰባት ዓመት ልምላ ብሎ እዚያው ገባ (ተመለሠ)።

 “የቅዱስ ያሬድ ታሪክና የግዕዝ ሥነ-ጽሑፍ” ከተሰኘው የፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ ጥናት የተቀነጨበ

ንጉስ ሮበርት ብሩስ

የስኮትላንዱ ንጉሥ ሮበርት ብሩስ (Robert Bruce) በጦርነት ተሸንፎ ራቅ ካለውና በጫካ ውስጥ ከሚገኘው ጎጆ ቤት ውስጥ ተቀምጧል። ሀገሩን ለመጠበቅ ባደረጋቸው ጦርነቶች ስድስት ጊዜ ተሸንፏል። ብዙ ወታደሮች ተገድለውበታል። ብዙዎቹ ቆስለውበታል። ብሩስ አዝኖና ተስፋ ቆርጦ ስለአደረጋቸው ጦርነቶች ያስታውሳል። ጠላቶቹ ከእሱ ወታደሮች እንደሚበልጡና ጠንካራም እንደነበሩ ተረድቷል። በጫካው ውስጥ ካለው ጎጆ ቤት ውስጥ እንዳለ ቀና ሲል በቋሚው እንጨት ላይ የምትሄድ ሸረሪት ይመለከታል። ሸረሪቷ ድር ለማድራት ትመላለሳለች። ቀጭኑን ክር ይዛ ከቋሚው እንጨት ጋር ለማያያዝ ትጥራለች። ይሁን እንጂ ሳይሳካላት ይቀራል። ስድስት ጊዜ ለመድረስ ሞክራ ይከሽፍባታል። ብሩስ በትዕግስቷ ይገረማል። ሰባተኛው ላይ ቀጭኑን ክር መሳይ ይዛ እንጨቱ ላይ ትደርስና ድሯን ታደራለች።

ብሩስ ከትንሿ ሸረሪት ትዕግስትን ስለተማረ ያመሰግናታል። እናም ለመጨረሻ ጊዜም ለመዋጋት ይዘጋጃል። ወታደሮቹን መርቶና ጦርነቱን አሸንፎም ስኮትላንድን ነፃ ያወጣታል።

 Pennel እና CUSACK ከፃፉት  የስኮትላንድ ታሪክ

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top